በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በተስፋችሁ ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ

በተስፋችሁ ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ

“እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው።”—ዕብ. 11:1

መዝሙሮች፦ 81, 134

1, 2. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ያላቸው ግሩም ተስፋ የሰይጣን ዓለም ክፍል የሆኑ ሰዎች ተስፋ ከሚያደርጓቸው ነገሮች የሚለየው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን አስፈላጊ ጥያቄዎች እንመረምራለን?

እውነተኛ ክርስቲያኖች የተዘረጋላቸው ተስፋ ምንኛ ግሩም ነው! ቅቡዓንም ሆንን “ሌሎች በጎች” ሁላችንም የአምላክ ዓላማ ሲፈጸምና የይሖዋ ስም ሲቀደስ ለማየት እንጓጓለን። (ዮሐ. 10:16፤ ማቴ. 6:9, 10) ይህ፣ ማንኛውም ሰው ሊኖረው ከሚችለው ሁሉ የላቀ ተስፋ ነው። በተጨማሪም አምላክ ቃል የገባው “አዲስ ሰማያት” ወይም “አዲስ ምድር” ክፍል ሆነን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እንጠባበቃለን። (2 ጴጥ. 3:13) እስከዚያው ድረስ ደግሞ የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ይበልጥ እየበለጸጉ ሲሄዱ ለማየት እንናፍቃለን።

2 የሰይጣን ዓለም ክፍል የሆኑ ሰዎችም ተስፋ የሚያደርጓቸው ነገሮች አሉ፤ ሆኖም ተስፋቸው መፈጸም መቻሉን ይጠራጠሩ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቁማርተኞች ሎተሪ እንደሚያሸንፉ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ይሁንና ማሸነፋቸውን እርግጠኞች መሆን አይችሉም። በሌላ በኩል ግን እውነተኛ እምነት ሲባል ለክርስቲያኖች የተሰጠውን ተስፋ “በእርግጠኝነት መጠበቅ” ማለት ነው። (ዕብ. 11:1) ይሁንና በተስፋህ ላይ ያለህን እምነት ይበልጥ ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው? ደግሞስ ተስፋ በምታደርጋቸው ነገሮች ላይ ጠንካራ እምነት ማዳበርህ ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

3. የክርስቲያኖች እምነት በምን ላይ የተመሠረተ ነው?

3 እምነት፣ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ሲወለዱ ጀምሮ የሚኖራቸው ባሕርይ አይደለም፤ በራሱ ሊዳብርም አይችልም። እምነት ማዳበር ከፈለግን የአምላክ መንፈስ ልባችንን እንዲመራው መፍቀድ አለብን። (ገላ. 5:22) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ እምነት እንዳለውም ሆነ እንደሚያስፈልገው አይናገርም። ይሖዋ ሁሉን ቻይና ፍጹም ጥበብ ያለው በመሆኑ ዓላማውን ዳር እንዳያደርስ የሚያግደው ምንም ነገር የለም። በሰማይ ያለው አባታችን፣ ቃል የገባቸውን በረከቶች እንደሚያመጣ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ስለሆነ እነዚህን ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ አድርጎ ይቆጥራቸዋል። በመሆኑም “እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል!” በማለት ተናግሯል። (ራእይ 21:3-6ን አንብብ።) የክርስቲያኖች እምነት፣ ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን የሚጠብቅ “ታማኝ አምላክ” እንደሆነ ባላቸው እውቀት ላይ የተመሠረተ ነው።—ዘዳ. 7:9

ከጥንት የእምነት ምሳሌዎች ትምህርት መውሰድ

4. በቅድመ ክርስትና ዘመን የኖሩ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ምን ተስፋ ነበራቸው?

4 በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ 16 ወንዶችና ሴቶች ስም ተጠቅሷል። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ዘገባ ስለ እነዚህና “በእምነታቸው ምክንያት በመልካም [ስለተመሠከረላቸው]” ሌሎች በርካታ ሰዎች ይናገራል። (ዕብ. 11:39) ሁሉም ቢሆኑ አምላክ፣ ተስፋ የተሰጠበትን “ዘር” እንደሚያስነሳ እንዲሁም ይህ ዘር ሰይጣንንና ተባባሪዎቹን በሙሉ በማጥፋት የይሖዋን ዓላማ እንደሚፈጽም ‘በእርግጠኝነት ይጠብቁ’ ነበር። (ዘፍ. 3:15) እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በሞት ያንቀላፉት፣ ተስፋ የተሰጠበት “ዘር” ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ሕይወት ለማግኘት የሚያስችል መንገድ ከመክፈቱ በፊት ነው። (ገላ. 3:16) ያም ቢሆን ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽም አምላክ በመሆኑ ከሞት ተነስተው ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ፤ በዚያም ፍጹም ሕይወት ያገኛሉ።—መዝ. 37:11፤ ኢሳ. 26:19፤ ሆሴዕ 13:14

5, 6. አብርሃምና ቤተሰቡ ለተስፋቸው መሠረት የሆናቸው ነገር ምንድን ነው? እምነታቸው ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ያደረጉትስ እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

5 ዕብራውያን 11:13 በቅድመ ክርስትና ዘመን ስለኖሩ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እነዚህ ሁሉ የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ባያዩም እምነታቸውን እንደጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከሩቅ አይተው በደስታ ተቀበሉት።” ከእነዚህ መካከል አንዱ አብርሃም ነው። ይሁንና አብርሃም፣ ተስፋ የተሰጠበት “ዘር” በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው አስደሳች ሕይወት በአእምሮው ቁልጭ ብሎ ይታየው ነበር? ኢየሱስ ለተቃዋሚዎቹ የተናገረው ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ ግልጽ መልስ ይሰጠናል፤ “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን እንደሚያይ ተስፋ በማድረግ እጅግ ተደሰተ፤ አይቶትም ደስ ተሰኘ” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 8:56) ሣራ፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ሌሎች በርካታ የአምላክ አገልጋዮችም “አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን” ከተማ ይኸውም ወደፊት የሚቋቋመውን የአምላክ መንግሥት በጉጉት ይጠባበቁ ነበር።—ዕብ. 11:8-11

6 አብርሃም እና ቤተሰቡ እምነታቸው ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ያደረጉት እንዴት ነው? ስለ አምላክ የተማሩት፣ ታማኝ የሆኑ አረጋውያን የሚናገሩትን በመስማትና አምላክ ከገለጠላቸው ነገር አሊያም እምነት የሚጣልባቸው ጥንታዊ መዛግብትን በማንበብ ሊሆን ይችላል። ይበልጥ የጠቀማቸው ግን የተማሩትን ነገር አለመርሳታቸው እንዲያውም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች እንዲሁም የእሱን ትእዛዛት ከፍ አድርገው መመልከታቸውና በእነዚህ ላይ ማሰላሰላቸው ነበር። እነዚህ ወንዶችና ሴቶች ተስፋቸው እውን እንደሚሆን እርግጠኞች ስለነበሩ ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ሲሉ ማንኛውንም መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች ሆነዋል።

7. ይሖዋ እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን እኛን ለመርዳት ምን ዝግጅቶች አድርጎልናል? ከእኛስ ምን ይጠበቃል?

7 ይሖዋ፣ እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን እኛን ለመርዳት ሲል ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በደግነት ሰጥቶናል። “ደስተኛ” እና ‘ስኬታማ’ ለመሆን ከፈለግን የአምላክን ቃል አዘውትረን ከተቻለም በየዕለቱ ማንበብ አለብን። (መዝ. 1:1-3፤ የሐዋርያት ሥራ 17:11ን አንብብ።) በተጨማሪም በቅድመ ክርስትና ዘመን እንደኖሩት የይሖዋ አገልጋዮች፣ አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰል እንዲሁም የእሱን ትእዛዛት መጠበቅ አለብን። ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይሰጠናል። (ማቴ. 24:45) ይሖዋ ከሚያቀርብልን መንፈሳዊ ማዕድ የምንመገብ ከሆነ የመንግሥቱን ተስፋ ‘በእርግጠኝነት እንደጠበቁት’ በጥንት ዘመን የኖሩ የእምነት ምሳሌዎች እንሆናለን።

8. ጸሎት እምነታችንን ለማጠናከር የሚረዳን እንዴት ነው?

8 በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ የአምላክ ምሥክሮች እምነታቸው ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን የረዳቸው ሌላው ነገር ደግሞ ጸሎት ነው። አምላክ ለጸሎታቸው የሚሰጠውን መልስ መመልከታቸው እምነታቸውን አጠናክሮታል። (ነህ. 1:4, 11፤ መዝ. 34:4, 15, 17፤ ዳን. 9:19-21) እኛም ይሖዋ እንደሚሰማንና በደስታ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጠን ስለምናውቅ የሚያስጨንቀንን ነገር ሁሉ አውጥተን ለእሱ መናገር እንችላለን። አምላክ ለጸሎታችን መልስ ሲሰጠን ደግሞ እምነታችን እየጠነከረ ይሄዳል። (1 ዮሐንስ 5:14, 15ን አንብብ።) እምነት ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ኢየሱስ እንደመከረን ‘ደጋግመን መለመን’ ይኖርብናል።—ሉቃስ 11:9, 13

9. ስለ ራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለ እነማንም መጸለይ ይኖርብናል?

9 ይሁን እንጂ የምንጸልየው አምላክ እንዲረዳን ለመጠየቅ ብቻ መሆን የለበትም። ይሖዋን በየዕለቱ እንድናመሰግነውና እንድናወድሰው የሚያነሳሱንን ‘ድንቅ ሥራዎቹን ዘርዝረን መጨረስ አንችልም!’ (መዝ. 40:5) በተጨማሪም ጸሎታችን፣ ‘በእስር ላይ ያሉትን ከእነሱ ጋር ታስረን እንዳለን አድርገን በማሰብ ሁልጊዜ እንደምናስታውሳቸው’ የሚያሳይ መሆን አለበት። ከዚህም ሌላ ለመላው የወንድማማች ማኅበር በተለይም ‘በመካከላችን ሆነው አመራር ለሚሰጡት’ ልንጸልይ ይገባል። ይሖዋ፣ ሁላችንም ለምናቀርበው ጸሎት መልስ እንደሚሰጥ ስንመለከት ልባችን በደስታ ይሞላል!—ዕብ. 13:3, 7

አቋማቸውን አላላሉም

10. ንጹሕ አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኛ ያልሆኑ የአምላክ አገልጋዮችን ምሳሌ ጥቀስ። እንዲህ ለማድረግ ኃይል ያገኙት እንዴት ነው?

10 በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በስም ያልተጠቀሱ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች በጽናት የተወጧቸውን መከራዎች ዘርዝሯል። ለአብነት ያህል፣ ሐዋርያው ልጆቻቸውን በሞት ስላጡና በኋላም በትንሣኤ ስለተቀበሉ የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ ሴቶች ጠቅሷል። በተጨማሪም “ቤዛ ተከፍሎላቸው ነፃ መሆን ስላልፈለጉ” ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ገልጿል፤ እነዚህ ሰዎች “ይህን ያደረጉት የተሻለ ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ ነው።” (ዕብ. 11:35) ጳውሎስ ይህን የተናገረው እነማንን በአእምሮው ይዞ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ባንችልም አምላክን በመታዘዛቸውና የእሱን ፈቃድ በመፈጸማቸው በድንጋይ ተወግረው ስለሞቱት ስለ ናቡቴ እና ስለ ዘካርያስ መናገሩ ሊሆን ይችላል። (1 ነገ. 21:3, 15፤ 2 ዜና 24:20, 21) ዳንኤልና ጓደኞቹም ንጹሕ አቋማቸውን ቢያላሉ “ነፃ መሆን” የሚችሉበት አጋጣሚ ነበራቸው። እነዚህ ወጣቶች በአምላክ ኃይል ላይ እምነት ስለነበራቸው “የአንበሶችን አፍ ዘግተዋል” እንዲሁም “የእሳትን ኃይል አጥፍተዋል” ሊባልላቸው ችሏል።—ዕብ. 11:33, 34፤ ዳን. 3:16-18, 20, 28፤ 6:13, 16, 21-23

11. አንዳንድ ነቢያት እምነት ስለነበራቸው የትኞቹን ፈተናዎች በጽናት ተቋቁመዋል?

11 እንደ ሚካያህ እና ኤርምያስ ያሉት ነቢያት ‘መዘባበቻ በመሆንና ወህኒ ቤት በመጣል ፈተና ቢደርስባቸውም’ እምነት ስለነበራቸው ተቋቁመውታል። እንደ ኤልያስ ያሉ ሌሎች ደግሞ “በየበረሃው፣ በየተራራው፣ በየዋሻውና በምድር ውስጥ ባሉ ጉድጓዶች ተቅበዝብዘዋል።” ሁሉም መጽናት የቻሉት “ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት [ይጠብቁ]” ስለነበር ነው።—ዕብ. 11:1, 36-38፤ 1 ነገ. 18:13፤ 22:24-27፤ ኤር. 20:1, 2፤ 28:10, 11፤ 32:2

12. ፈተናዎችን በጽናት በመወጣት ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የተወው ማን ነው? ለመጽናት የረዳውስ ምንድን ነው?

12 ጳውሎስ የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ የተለያዩ ወንዶችንና ሴቶችን ከዘረዘረ በኋላ ከሁሉ የላቀ አርዓያ ስለሆነው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። ዕብራውያን 12:2 “ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል፣ የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል፤ እንዲሁም በአምላክ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል” ይላል። በእርግጥም፣ ኢየሱስ በጣም ከባድ ፈተናዎችን በመቋቋም የተወውን የእምነት ምሳሌ ‘በጥሞና ማሰብ’ ይኖርብናል። (ዕብራውያን 12:3ን አንብብ።) እንደ አንቲጳስ ያሉ በጥንት ዘመን የነበሩና ሰማዕት የሆኑ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በንጹሕ አቋማቸው ጸንተዋል። (ራእይ 2:13) በመሆኑም እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች የላቀ ትንሣኤ ያገኛሉ፤ ይኸውም ከሞት ተነስተው በሰማይ ይኖራሉ፤ ይህ ደግሞ የጥንቶቹ የእምነት ሰዎች ተስፋ ያደርጉት ከነበረው “የተሻለ ትንሣኤ” እንኳ የበለጠ ነው። (ዕብ. 11:35) በሞት አንቀላፍተው የነበሩት ታማኝ ቅቡዓን በሙሉ፣ የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተወለደ ብዙም ሳይቆይ ከሞት ተነስተው መንፈሳዊ ሕይወት ተቀብለዋል፤ እነዚህ ቅቡዓን ከኢየሱስ ጋር ሆነው በሰው ልጆች ላይ ይገዛሉ።—ራእይ 20:4

ዘመናዊ የእምነት ምሳሌዎች

13, 14. ወንድም ሩዶልፍ ግራይሸን ምን ፈተናዎች አጋጥመውታል? ለመጽናት የረዳውስ ምንድን ነው?

13 በዘመናችን ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአምላክ አገልጋዮች ተስፋቸው ብሩህ ሆኖ እንዲታያቸው በማድረግ እንዲሁም የተለያዩ ፈተናዎች እምነታቸውን እንዲያዳክሙባቸው ባለመፍቀድ የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለዋል። በ1925 በጀርመን የተወለደውን ሩዶልፍ ግራይሸንን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ወንድም ሩዶልፍ፣ ቤቱ ግድግዳ ላይ ተሰቅለው የነበሩትን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክቶች የሚያንጸባርቁ ሥዕሎች ያስታውሳል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከሥዕሎቹ መካከል አንዱ ተኩላና የበግ ጠቦት፣ ነብርና የፍየል ጠቦት እንዲሁም አንበሳና ፍሪዳ በሰላም አንድ ላይ ሆነው አንድ ትንሽ ልጅ ሲመራቸው የሚያሳይ ነበር። . . . እንዲህ ዓይነቶቹ ሥዕሎች በውስጤ አንድ የማይፋቅ አሻራ ቀርጸዋል።” (ኢሳ. 11:6-9) ወንድም ሩዶልፍ፣ በመጀመሪያ የናዚ ጌስታፖ በኋላም የምሥራቅ ጀርመኑ ሽታዚ ከባድ ስደት ቢያደርሱበትም ምድር ገነት እንደምትሆን ያለው ጠንካራ እምነት አልተዳከመም።

14 ወንድም ሩዶልፍ ሌሎች መከራዎችም ደርሰውበታል፤ የሚወዳት እናቱ በራቨንስብሩክ ወደሚገኘው የሴቶች ማጎሪያ ካምፕ ከተላከች በኋላ በተስቦ ሞተች፤ እንዲሁም አባቱ እምነቱ በመዳከሙ የተነሳ የይሖዋ ምሥክር መሆኑን እንደካደ በሚገልጽ ሰነድ ላይ ፈረመ። ወንድም ሩዶልፍ ከእስር ከተፈታ በኋላ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት የማገልገል መብት ያገኘ ሲሆን ከጊዜ በኋላም ወደ ጊልያድ ትምህርት ቤት ተጠራ። ከዚያም ሚስዮናዊ ሆኖ ወደ ቺሊ ተላከ፤ በዚያም በድጋሚ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት አገልግሏል። የሚያሳዝነው ግን የወንድም ሩዶልፍ መከራ ገና አላበቃም ነበር። ፓትሲ ከምትባል ሚስዮናዊት ጋር ትዳር በመሠረተ በዓመቱ ሴት ልጃቸውን በሞት አጡ። ውሎ አድሮ ደግሞ ውድ ባለቤቱ ገና በ43 ዓመቷ ሞተችበት። ወንድም ሩዶልፍ እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች በጽናት ተቋቁሟል፤ የሕይወት ታሪኩ በነሐሴ 1, 1997 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 20-25 ላይ በወጣበት ወቅት፣ በዕድሜ ከመግፋቱም ሌላ የጤና እክል ቢኖርበትም የዘወትር አቅኚና የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነበር። [1]

15. ስደትን ተቋቁመው በደስታ የጸኑ ዘመናዊ የይሖዋ ምሥክሮችን ምሳሌ ጥቀስ።

15 የይሖዋ ምሥክሮች ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም ምንጊዜም በተስፋቸው ይደሰታሉ። ለምሳሌ በሲንጋፖርበኤርትራ እና በደቡብ ኮሪያ በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ታስረዋል፤ አብዛኞቹ የታሰሩት ኢየሱስ ሰይፍ እንዳንመዝ የሰጠውን ትእዝዝ በማክበራቸው ነው። (ማቴ. 26:52) በመቶዎች ከሚቆጠሩት ከእነዚህ እስረኞች መካከል በኤርትራ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ከ20 ዓመት በላይ ያሳለፉት ነገደ፣ ይስሃቅ እና ጳውሎስ ይገኙበታል። እነዚህ ወንድሞች በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን የመጦርም ሆነ ትዳር የመመሥረት ነፃነታቸውን የተነፈጉ እንዲሁም ከባድ ግፍ የተፈጸመባቸው ቢሆንም በታማኝነት ጸንተዋል። jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ በሚገኘው ፎቶግራፋቸው ላይ እንደሚታየው አዎንታዊ አመለካከት አላቸው፤ ይህም እምነታቸው ጠንካራ እንደሆነ ያሳያል። በእስር ቤቱ ጠባቂዎች ዘንድም እንኳ አክብሮት ማትረፍ ችለዋል።

በጉባኤያችሁ ከሚገኙ ዘመናዊ የእምነት ምሳሌዎች ተሞክሮ ትምህርት እያገኛችሁ ነው? (አንቀጽ 15, 16ን ተመልከት)

16. ጠንካራ እምነት ምን ለማድረግ ይረዳሃል?

16 በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች ከባድ ስደት አላጋጠማቸውም። እነሱ የደረሰባቸው የእምነት ፈተና ሌላ ነው። ድህነትን ተቋቁመው የሚኖሩ አሊያም በጦርነት ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት መከራ የደረሰባቸው በርካታ ወንድሞች አሉ። ሌሎች ደግሞ እንደ ሙሴና የጥንት የእምነት አባቶች፣ በዚህ ዓለም ላይ የተደላደለ ሕይወት ወይም ዝና የማግኘት አጋጣሚያቸውን መሥዋዕት አድርገዋል። ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድና የራሳቸውን ፍላጎት በማሟላት ላይ ያተኮረ ሕይወት እንዲመሩ በሚቀርብላቸው ፈተና ላለመሸነፍ ከፍተኛ ትግል ያደርጋሉ። እነዚህ ወንድሞች እንዲጸኑ የረዳቸው ምንድን ነው? ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንዲሁም ይሖዋ ማንኛውንም የፍትሕ መጓደል እንደሚያስተካክልና ታማኝ አገልጋዮቹን ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት በመስጠት እንደሚባርካቸው ያላቸው ጠንካራ እምነት ነው።—መዝሙር 37:5, 7, 9, 29ን አንብብ።

17. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው? በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ምን ይብራራል?

17 አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ማሰላሰል እንዲሁም አዘውትሮ መጸለይ እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን እንዴት እንደሚረዳን በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ተመልክተናል። ጠንካራ እምነት ማዳበራችን ደግሞ ለክርስቲያኖች የተሰጠውን ተስፋ ‘በእርግጠኝነት በመጠበቅ’ የእምነት ፈተናዎችን ለመቋቋም ይረዳናል። ሆኖም የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ እንደሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት የሚሰጠው ፍቺ ሌላም የሚጨምረው ነገር አለ።

^ [1] (አንቀጽ 14) “ፈተናዎች ቢፈራረቁብኝም ተስፋዬ አልደበዘዘም” በሚል ርዕስ በግንቦት 2002 ንቁ! ላይ የወጣውን በስሎቫኪያ የሚኖረውን የወንድም አንድሬ ሃናክን የሕይወት ታሪክም ተመልከት።