እውቅና ማግኘት የምትፈልጉት በማን ዘንድ ነው?
“አምላክ . . . ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።”—ዕብ. 6:10
1. ሁላችንም ምን ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለን? ይህስ ምንን ይጨምራል?
አንድ የምታውቁትና የምታከብሩት ሰው ስማችሁን ቢረሳው፣ ይባስ ብሎ ደግሞ ማን እንደሆናችሁ እንኳ ቢዘነጋ ምን ይሰማችኋል? እንዲህ ያለው ሁኔታ በጣም ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ሁላችንም በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለን። ሰዎች እንዲሁ በስም እንዲያውቁን ብቻ ሳይሆን ለማንነታችንና ላከናወንናቸው ነገሮች እውቅና እንዲሰጡን ጭምር እንፈልጋለን።—ዘኁ. 11:16፤ ኢዮብ 31:6
2, 3. በሌሎች ዘንድ ለመታወቅ ያለን ፍላጎት ሊዛባ የሚችለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
2 እንደ ሌሎች ተፈጥሯዊ ፍላጎቶቻችን ሁሉ በሌሎች ዘንድ ለመታወቅ ያለን ፍላጎትም በአለፍጽምናችን ምክንያት ሊዛባና ሚዛኑን ሊስት ይችላል። በመሆኑም ሰዎች ተገቢ ያልሆነ እውቅና እንዲሰጡን መፈለግ ልንጀምር እንችላለን። የሰይጣን ዓለም ዝነኛ የመሆንና በሌሎች ዘንድ እውቅና የማግኘት ፍላጎት በውስጣችን እንዲቀጣጠል ያደርጋል፤ ይህም በእርግጥ እውቅና ሊሰጠውና ሊመለክ ለሚገባው አካል ማለትም በሰማይ ላለው አባታችን ለይሖዋ አምላክ ትኩረት እንዳንሰጥ እንቅፋት ይሆንብናል።—ራእይ 4:11
3 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ዘመን አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች እውቅና ማግኘትን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት ነበራቸው። ኢየሱስ ሉቃስ 20:46, 47) በተቃራኒው ኢየሱስ፣ አነስተኛ መዋጮ ያደረገችን አንዲት መበለት አድንቋል፤ ምናልባትም ይህች ሴት ያደረገችው መዋጮ በሌሎች ዘንድ ምንም ትኩረት አልተሰጠው ይሆናል። (ሉቃስ 21:1-4) ኢየሱስ ይህችን መበለት አድንቆ መናገሩ እውቅና ማግኘትን በተመለከተ ከሌሎች የተለየ አመለካከት እንዳለው ያሳያል። ይህ ርዕስ እንዲህ ያለውን በይሖዋ አምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል።
ተከታዮቹን እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸዋል፦ “ዘርፋፋ ልብስ ለብሰው መዞር ከሚወዱ፣ በገበያ ቦታ ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ከሚሹ እንዲሁም በምኩራብ ከፊት መቀመጥ [“በምኩራብ የተሻለውን መቀመጫ” ግርጌ]፣ በራት ግብዣ ላይም የክብር ቦታ መያዝ ከሚፈልጉ ከጸሐፍት ተጠንቀቁ።” አክሎም “እነዚህ የከፋ ፍርድ ይጠብቃቸዋል” በማለት ተናግሯል። (ከሁሉ የላቀው እውቅና
4. ከሁሉ የላቀው እውቅና የትኛው ነው? ለምንስ?
4 ታዲያ ልንጣጣርለት የሚገባው ከሁሉ የላቀ እውቅና የትኛው ነው? ይህ እውቅና ሰዎች በትምህርት፣ በንግድ ወይም በመዝናኛው መስክ ለማግኘት የሚጣጣሩት ዓይነት እውቅና አይደለም። ጳውሎስ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት ከሁሉ የላቀው እውቅና የትኛው እንደሆነ ያሳያሉ፦ “አሁን . . . አምላክን አውቃችኋል፤ እንዲያውም አምላክ እናንተን አውቋችኋል፤ ታዲያ ደካማና ከንቱ ወደሆኑ ተራ ነገሮች መመለስና እንደገና ለእነዚህ ነገሮች ባሪያ መሆን ትፈልጋላችሁ?” (ገላ. 4:9) የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ በሆነው አምላክ መታወቅ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! አምላክ ከእኛ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ፈቃደኛ ነው። አንድ ምሁር እንደገለጹት “እሱ በሞገስ ዓይኑ የሚመለከተን ሰዎች እንሆናለን” ማለት ነው። ይሖዋ እኛን እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ሲቆጥረን በሕይወት የምንኖርበትን ዓላማ እናሳካለን።—መክ. 12:13, 14
5. በይሖዋ ለመታወቅ ከእኛ ምን ይጠበቃል?
5 ሙሴ እንዲህ ያለውን በረከት አግኝቶ ነበር። የይሖዋን መንገዶች ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ለማወቅ በለመነበት ጊዜ ይሖዋ “በፊቴ ሞገስ ስላገኘህና በስም ስላወቅኩህ የጠየቅከውን ይህን ነገር እፈጽማለሁ” በማለት ምላሽ ሰጥቶታል። (ዘፀ. 33:12-17) ይሖዋ እኛንም በግለሰብ ደረጃ ሊያውቀን የሚችል ሲሆን ይህ ደግሞ ብዙ በረከቶች ያስገኝልናል። ሆኖም በይሖዋ ዘንድ እውቅና ለማግኘት ከእኛ ምን ይጠበቃል? እሱን መውደድና ሕይወታችንን ለእሱ መወሰን ይኖርብናል።—1 ቆሮንቶስ 8:3ን አንብብ።
6, 7. ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ወደማጣት የሚመራን ምን ሊሆን ይችላል?
6 ይሁንና በሰማይ ካለው አባታችን ጋር የመሠረትነውን ውድ ዝምድና ጠብቀን መኖር ያስፈልገናል። ጳውሎስ እንደጻፈላቸው የገላትያ ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ዓለም ለሚያቀርባቸው “ደካማና ከንቱ [የሆኑ] ተራ ነገሮች” ባሪያ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል፤ ይህም በዓለም ዘንድ አድናቆት ለማትረፍ ከመጣጣር መቆጠብን ይጨምራል። (ገላ. 4:9) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የገላትያ ክርስቲያኖች በአምላክ ለመታወቅ በቅተው ነበር። ሆኖም ጳውሎስ እንደተናገረው እነዚሁ ወንድሞች ከንቱ ወደሆኑ ነገሮች “መመለስ” ጀምረው ነበር። በሌላ አነጋገር ጳውሎስ “እድገት አድርጋችሁ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሳችሁ በኋላ፣ ትታችኋቸው ወደመጣችኋቸው ዋጋ የሌላቸውና የማይረቡ ነገሮች እንዴት ትመለሳላችሁ?” እያላቸው ነበር።
7 እኛስ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል? አዎ። ለመጀመሪያ ጊዜ ይሖዋን ስናውቅ እኛም ልክ እንደ ጳውሎስ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች መሥዋዕት አድርገን ሊሆን ይችላል። (ፊልጵስዩስ 3:7, 8ን አንብብ።) ምናልባትም ከፍተኛ ትምህርት መከታተል፣ በሥራችን እድገት ማግኘት ወይም በንግዱ ዓለም ተጨማሪ ገንዘብ ማካበት የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች ትተን ይሆናል። አሊያም ደግሞ የሙዚቃ ተሰጥኦዋችን ወይም የስፖርት ችሎታችን ዝነኛና ሀብታም ሊያደርገን ይችል የነበረ ቢሆንም እኛ ግን እነዚህን ሁሉ ነገሮች ወደ ጎን ገሸሽ አድርገን ሊሆን ይችላል። (ዕብ. 11:24-27) ታዲያ በዚህ ረገድ ያደረግናቸውን ጥሩ ውሳኔዎች ‘በሞኝነት እንዳመለጡን አጋጣሚዎች’ አድርገን በመቁጠር መቆጨት ብንጀምር ይህ ምንኛ ጥበብ የጎደለው ነገር ይሆናል! እንዲህ ያለው አስተሳሰብ “ደካማና ከንቱ” ናቸው ብለን የተውናቸውን ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች መልሰን ወደመፈለግ ሊመራን ይችላል። *
ቁርጥ ውሳኔያችሁን አጠናክሩ
8. በይሖዋ ዘንድ እውቅና ለማግኘት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር ምን ሊረዳን ይችላል?
8 በዓለም ሳይሆን በይሖዋ ዘንድ እውቅና ለማግኘት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? ሁለት አስፈላጊ እውነታዎችን ማስታወስ ይኖርብናል። አንደኛ፣ ይሖዋ በታማኝነት ለሚያገለግሉት ምንጊዜም እውቅና ይሰጣል። (ዕብራውያን 6:10ን አንብብ፤ ዕብ. 11:6) አገልጋዮቹን በግለሰብ ደረጃ የሚያደንቃቸው ከመሆኑም ሌላ ታማኞቹን ችላ ማለት ለእሱ ‘ፍትሕ እንደማዛባት’ ነው። ይሖዋ ምንጊዜም “የእሱ የሆኑትን ያውቃል።” (2 ጢሞ. 2:19) በተጨማሪም ‘የጻድቃንን መንገድም’ ሆነ እነሱን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን ያውቃል።—መዝ. 1:6፤ 2 ጴጥ. 2:9
9. ይሖዋ ሕዝቡ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ ለማሳየት ሲል ያከናወናቸውን አስደናቂ ነገሮች ጥቀስ።
9 ይሖዋ ሕዝቡ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ ለማሳየት አስደናቂ ነገሮችን ያደረገባቸው ጊዜያት አሉ። (2 ዜና 20:20, 29) ኃያል የሆነው የፈርዖን ሠራዊት እያሳደደው የነበረውን ሕዝቡን ቀይ ባሕር ላይ ያዳነበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (ዘፀ. 14:21-30፤ መዝ. 106:9-11) ይህ ክንውን በጣም አስገራሚ ከመሆኑ የተነሳ በዚያ አካባቢ የነበሩ ሰዎች ከ40 ዓመታት በኋላም እንኳ ስለዚህ ጉዳይ ያወሩ ነበር። (ኢያሱ 2:9-11) እኛም ከረጅም ጊዜ በፊት የተነገረውን የማጎጉን ጎግ ጥቃት በምንጋፈጥበት ወቅት ይሖዋ ፍቅሩንና ኃይሉን ያሳየባቸውን እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ማስታወሳችን ምንኛ ያበረታታናል! (ሕዝ. 38:8-12) በዓለም ሳይሆን በአምላክ ዘንድ እውቅና ለማግኘት መጣጣራችን በተለይም በዚያን ጊዜ በጣም እንደሚያስደተን የታወቀ ነው።
10. ይሖዋ ለሰዎች እውቅና የሚሰጥበትን መንገድ በተመለከተ ምን ነገር ልናስታውስ ይገባል?
10 ልናስታውስ የሚገባን ሁለተኛው እውነታ ደግሞ የሚከተለው ነው፦ ይሖዋ ፈጽሞ ባልጠበቅነው መንገድ እውቅና ሊሰጠን ይችላል። በሌሎች ለመታየት ሲሉ ብቻ መልካም ነገሮችን የሚያደርጉ ሰዎች ከይሖዋ ምንም ብድራት እንደማያገኙ ተነግሯቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ከሰዎች ውዳሴ ባገኙ ጊዜ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። (ማቴዎስ 6:1-5ን አንብብ።) በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ ሌሎችን የሚጠቅም ተግባር ቢያከናውኑም ለዚህ ተገቢውን እውቅና ያላገኙ ሰዎችን አባቱ ‘በስውር እንደሚያያቸው’ ተናግሯል። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ተግባሮችን ትኩረት ሰጥቶ የሚያይ ሲሆን ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው ወሮታ ይከፍለዋል። ሆኖም ይሖዋ ፈጽሞ ባልጠበቅነው መንገድ ብድራታችንን የሚከፍልበት ጊዜ አለ። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
አንዲት ትሑት ወጣት ያልጠበቀችውን እውቅና አገኘች
11. ይሖዋ ወጣት ለነበረችው ለማርያም እውቅና የሰጣት እንዴት ነው?
11 የአምላክ ልጅ ሰው ሆኖ የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ ይሖዋ ማርያም የተባለችን አንዲት ትሑት ድንግል የዚህ ልዩ ልጅ እናት እንድትሆን መረጣት። ማርያም የምትኖረው ከኢየሩሳሌምና ዕፁብ ድንቅ ከሆነው ቤተ መቅደሷ ርቃ በምትገኘውና እምብዛም በማትታወቀው የናዝሬት ከተማ ውስጥ ነበር። (ሉቃስ 1:26-33ን አንብብ።) ማርያም ለዚህ ልዩ መብት የተመረጠችው ለምንድን ነው? መልአኩ ገብርኤል “በአምላክ ፊት ሞገስ [እንዳገኘች]” ነግሯታል። ከጊዜ በኋላ ከዘመዷ ከኤልሳቤጥ ጋር ያደረገችው ውይይት እንደሚያሳየው ማርያም ጥልቅ መንፈሳዊነት ያላት ሰው ነበረች። (ሉቃስ 1:46-55) አዎ፣ ይሖዋ ማርያምን ትኩረት ሰጥቶ ይመለከታት የነበረ ሲሆን ላሳየችው ታማኝነት ይህን ያልተጠበቀ መብት ሰጥቷታል።
12, 13. ኢየሱስ በተወለደበትም ሆነ ከ40 ቀናት በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ በተወሰደበት ጊዜ ይሖዋ ልጁ እውቅና እንዲያገኝ ያደረገው እንዴት ነው?
12 ከጊዜ በኋላ ማርያም ኢየሱስን ስትወልድ ይሖዋ በኢየሩሳሌምና በቤተልሔም የነበሩት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ባለሥልጣናት ወይም ገዢዎች ስለዚህ ጉዳይ እንዲያውቁ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ከቤተልሔም ውጭ ሜዳ ላይ በጎቻቸውን ሲጠብቁ ለነበሩ እዚህ ግቡ የማይባሉ እረኞች መላእክት ተገለጡላቸው። (ሉቃስ 2:8-14) ከዚያም እነዚህ እረኞች ሄደው አዲስ የተወለደውን ሕፃን አዩት። (ሉቃስ 2:15-17) ማርያምና ዮሴፍ፣ ኢየሱስ ክብር የተሰጠው እንዲህ ባለ መንገድ እንደሆነ ሲያዩ ምንኛ ተደንቀው ይሆን! ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድና ሰይጣን ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ ምን ያህል ልዩነት እንዳለው ለማስተዋል ሞክር። ሰይጣን ኢየሱስንና ወላጆቹን እንዲጎበኙ ኮከብ ቆጣሪዎችን በላከ ጊዜ መላው የኢየሩሳሌም ሕዝብ የኢየሱስን መወለድ በመስማቱ ተሸብሮ ነበር። (ማቴ. 2:3) የኢየሱስ መወለድ በዚህ መልኩ ለሕዝብ ይፋ መደረጉ በርካታ ንጹሐን ሕፃናት እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል።—ማቴ. 2:16
13 ኢየሱስ ከተወለደ ከ40 ቀናት በኋላ ማርያም ከቤተልሔም ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኘው በኢየሩሳሌም ባለው ቤተ መቅደስ ለይሖዋ መሥዋዕት ማቅረብ ይጠበቅባት ነበር። (ሉቃስ 2:22-24) ከዮሴፍና ከኢየሱስ ጋር ስትጓዝ፣ በቤተ መቅደሱ የሚያገለግለው ካህን ኢየሱስ ወደፊት ለሚጫወተው ሚና በሆነ መንገድ ለየት ያለ እውቅና እንደሚሰጥ አስባ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ እውቅና አግኝቷል፤ ሆኖም ማርያም በጠበቀችው መንገድ ላይሆን ይችላል። ይሖዋ፣ ስምዖን የተባለ “ጻድቅና ለአምላክ ያደረ” ሰው እንዲሁም የ84 ዓመት መበለት የሆነች ሐና የተባለች ነቢዪት ይህ ልጅ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ወይም ክርስቶስ በመሆን ለሚጫወተው ሚና እውቅና እንዲሰጡ አድርጓል።—ሉቃስ 2:25-38
14. ይሖዋ ማርያምን የባረካት እንዴት ነው?
14 ማርያምን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ ቀደም ሲል እውቅና እንደሰጣት ሁሉ ልጁን በመንከባከብና በማሳደግ ላሳየችው ታማኝነትስ ተገቢውን እውቅና ይሰጣት ይሆን? እንዴታ። አምላክ፣ ማርያም ያከናወነችው ተግባርና የተናገረቻቸው ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገቡ አድርጓል። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ማርያም አብራው ልትጓዝ አልቻለችም። ምናልባትም መበለት ስለሆነች ከናዝሬት መውጣት አልቻለች ይሆናል። በዚህ ምክንያት ብዙ አጋጣሚዎች ያመለጧት ቢሆንም ኢየሱስ በሞተበት ጊዜ ግን ከጎኑ ነበረች። (ዮሐ. 19:26) በኋላም ከጴንጤቆስጤ ዕለት በፊት በነበሩት ቀናት በኢየሩሳሌም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ነበረች። (ሥራ 1:13, 14) በመሆኑም በጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ በወረደ ጊዜ እሷም በመንፈስ ተቀብታ እንደሚሆን መጠበቅ እንችላለን። ይህ ማለት ደግሞ ከኢየሱስ ጋር ለዘላለም በሰማይ አብራ የመሆን አጋጣሚ አግኝታለች ማለት ነው። በእርግጥም ማርያም በታማኝነት ላከናወነችው አገልግሎት አስገራሚ በሆነ መንገድ ወሮታ አግኝታለች!
ይሖዋ ለልጁ የሰጠው እውቅና
15. ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ እውቅና የሰጠው እንዴት ነው?
15 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በወቅቱ በነበሩት የሃይማኖት ወይም የፖለቲካ መሪዎች ዘንድ አክብሮት የማትረፍ ፍላጎት አልነበረውም። ዋናው ፍላጎቱ በይሖዋ ዘንድ ሞገስ ማግኘት ነበር። በመሆኑም ይሖዋ በሦስት የተለያዩ ወቅቶች በቀጥታ ከሰማይ በመናገር እውቅና ሲሰጠው ምንኛ ተበረታቶ ይሆን! ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ተጠምቆ እንደወጣ ይሖዋ “በጣም የምደሰትበት የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 3:17) ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ከኢየሱስ ሌላ ይህን የሰማው መጥምቁ ዮሐንስ ብቻ ነው። ከዚያም ኢየሱስ ከመሞቱ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ይሖዋ ኢየሱስን አስመልክቶ “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” በማለት የተናገረ ሲሆን ይህንንም ሦስት ሐዋርያቱ ሰምተዋል። (ማቴ. 17:5) በመጨረሻም ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ይሖዋ በድጋሚ ልጁን ከሰማይ አነጋግሮታል።—ዮሐ. 12:28
16, 17. ይሖዋ ኢየሱስን ባልተጠበቀ መንገድ ያከበረው እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ አምላክን ሰድቧል በሚል የሐሰት ክስ ተወንጅሎ የውርደት ሞት እንደሚሞት ቢያውቅም የእሱ ሳይሆን የይሖዋ ፈቃድ እንዲፈጸም ጸልዮአል። (ማቴ. 26:39, 42) እውቅና ማግኘት የሚፈልገው ከዓለም ሳይሆን ከአባቱ ብቻ ስለነበር “የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል።” (ዕብ. 12:2) ታዲያ ይሖዋ እውቅና የሰጠው እንዴት ነው?
17 ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ፣ ቀደም ሲል በአባቱ ዘንድ የነበረውን ክብር መልሶ የማግኘት ፍላጎት እንዳለው ገልጾ ነበር። (ዮሐ. 17:5) ኢየሱስ ከዚህ ያለፈ ነገር የማግኘት ፍላጎት እንደነበረው የሚጠቁም ምንም ነገር የለም። በሰማይ ባለው ቦታ ረገድ አንድ ዓይነት “እድገት” አገኛለሁ ብሎ አልጠበቀም። ሆኖም ይሖዋ ምን አደረገ? ኢየሱስን ፈጽሞ ባልተጠበቀ መንገድ አክብሮታል፤ ከሞት ካስነሳው በኋላ “የላቀ ቦታ [የሰጠው]” ከመሆኑም ሌላ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ለማንም ተሰጥቶ የማያውቅ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት እንዲያገኝ አድርጓል! * (ፊልጵ. 2:9፤ 1 ጢሞ. 6:16) በእርግጥም ኢየሱስ ለተከተለው የታማኝነት ጎዳና አስደናቂ በሆነ መንገድ እውቅና አግኝቷል!
18. በዚህ ዓለም ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት እንዳንጣጣር ምን ሊረዳን ይችላል?
18 በዚህ ዓለም ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት እንዳንጣጣር ምን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋ ምንጊዜም ለታማኝ አገልጋዮቹ እውቅና እንደሚሰጥና አብዛኛውን ጊዜም እንዲህ የሚያደርገው ባልተጠበቀ መንገድ እንደሆነ እናስታውስ። ወደፊትስ ቢሆን ይሖዋ ያልጠበቅናቸውን በረከቶች አዘጋጅቶልን እንደሆነ ማን ያውቃል? እስከዚያው ድረስ ግን ይህ ክፉ ዓለምም ሆነ ዓለም ሊሰጠን የሚችለው እውቅና እንደሚያልፉ በማስታወስ የሚደርስብንን ማንኛውንም ችግርና ፈተና በጽናት እንቋቋም። (1 ዮሐ. 2:17) አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ ‘የምናከናውነውን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።’ (ዕብ. 6:10) አዎ፣ ሞገሱን ያሳየናል! ምናልባትም ይህን የሚያደርገው አሁን ፈጽሞ ልንገምተው በማንችለው መንገድ ሊሆን ይችላል።