በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ለእኔም ሞቶልኛል?

ኢየሱስ ለእኔም ሞቶልኛል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት” ያላቸው ሰዎች የልባቸውን አውጥተው የገለጹባቸውን በርካታ ሐሳቦች እናገኛለን። (ያዕ. 5:17) ለምሳሌ በሮም 7:21-24 ላይ ጳውሎስ ስለ ራሱ እንዲህ ሲል በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው። . . . እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ!” እኛም የጳውሎስን ስሜት እንጋራለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እንዲህ ያሉ ሐሳቦች ከአለፍጽምና ጋር በምንታገልበት ወቅት ያጽናኑናል።

በሌላ ጊዜ ደግሞ ጳውሎስ ከዚህ የተለየ ስሜት እንዳለው ገልጿል። ሐዋርያው በገላትያ 2:20 ላይ ኢየሱስ ‘እንደሚወደው’ እንዲሁም ‘ለእሱ ሲል ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ’ በልበ ሙሉነት ተናግሯል! እኛስ እንዲህ ይሰማናል? ምናልባት አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይሰማን ይሆናል።

ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ኃጢአቶች ምክንያት እንደማንረባ የሚሰማን ከሆነ ቤዛው በግለሰብ ደረጃ የተሰጠን ስጦታ እንደሆነ አድርገን ማሰብ ይቅርና ይሖዋ እንደሚወደንና ምሕረት እንዳደረገልን አምነን መቀበል እንኳ ይከብደን ይሆናል። ታዲያ ኢየሱስ ቤዛውን በግለሰብ ደረጃ እንደተሰጠን ስጦታ አድርገን እንድንመለከተው ይፈልጋል? ከሆነ እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንድናዳብር ምን ሊረዳን ይችላል? እስቲ የእነዚህን ሁለት ጥያቄዎች መልስ እንመርምር።

ኢየሱስ ስለ ቤዛዊ መሥዋዕቱ ያለው አመለካከት

ኢየሱስ ቤዛውን በግለሰብ ደረጃ እንደተሰጠን ስጦታ አድርገን እንድንመለከተው ይፈልጋል። ይህን እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን? በሉቃስ 23:39-43 ላይ የሚገኘውን ዘገባ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። አንድ ሰው ከኢየሱስ አጠገብ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሏል። ግለሰቡ፣ የፈጸመው ጥፋት እንዳለ በሐቀኝነት ተናገረ። ይህ ሰው ከባድ ወንጀል ሠርቶ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትል ቅጣት የሚበየነው አደገኛ በሆኑ ወንጀለኞች ላይ ነበር። ሰውየው በጭንቀት ተውጦ ኢየሱስን “ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” በማለት ለመነው።

ታዲያ ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠው? በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ቢሆንም እንኳ ሰውየውን ለማየት ቀስ ብሎ ፊቱን ሲያዞር ይታይህ። እንደ ምንም ብሎ ፈገግ በማለት “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎ ሰውየውን አጽናናው። ኢየሱስ ‘የሰው ልጅ የመጣው በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት’ እንደሆነ ሊገልጽለት ይችል ነበር። (ማቴ. 20:28) ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ እሱ የሚያቀርበው መሥዋዕት በግለሰብ ደረጃ ይህን ሰው እንደሚጠቅመው በደግነት መግለጹን ልብ እንበል። ‘አንተ’ እና ‘እኔ’ እያለ መናገሩ ወዳጃዊ ስሜት በማሳየት በግለሰብ ደረጃ ትኩረት እንደሰጠው ይጠቁማል። ኢየሱስ፣ መሥዋዕቱ ለሰውየው በግለሰብ ደረጃ የሚያስገኝለትን ጥቅም ይኸውም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር አጋጣሚ እንደሚያገኝም ነግሮታል።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ፣ እሱ የሚያቀርበውን መሥዋዕት ወንጀለኛው በግለሰብ ደረጃ ለራሱ እንደተሰጠ ስጦታ አድርጎ እንዲመለከተው ፈልጓል። ኢየሱስ፣ አምላክን ለማገልገል አጋጣሚ ያላገኘው ወንጀለኛ እንኳ እንዲህ እንዲሰማው ከፈለገ አምላክን እያገለገለ ያለ ክርስቲያንማ በዚህ ረገድ ይበልጥ እንዲተማመን እንደሚፈልግ ጥያቄ የለውም። እኛም ቀደም ሲል ምንም ዓይነት ኃጢአት ፈጽመን ቢሆን የኢየሱስ መሥዋዕት በግለሰብ ደረጃ እንደሚጠቅመን አምነን መቀበል እንድንችል ምን ይረዳናል?

ጳውሎስን የረዳው ምንድን ነው?

ጳውሎስ የተሰጠው አገልግሎት፣ ስለ ኢየሱስ መሥዋዕት በነበረው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። እንዴት? እንዲህ ብሏል፦ “ለአገልግሎቱ በመሾም ታማኝ አድርጎ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ፤ ምንም እንኳ ቀደም ሲል አምላክን የምሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ የነበርኩ ብሆንም ይህን አድርጎልኛል።” (1 ጢሞ. 1:12-14) ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ተልእኮ የተሰጠው መሆኑ፣ ኢየሱስ ምሕረት እንዳደረገለትና እንደሚወደው እንዲሁም በእሱ እንደሚተማመን እርግጠኛ እንዲሆን አድርጎታል። ኢየሱስ እኛም ምሥራቹን እንድንሰብክ በግለሰብ ደረጃ ተልዕኮ ሰጥቶናል። (ማቴ. 28:19, 20) ይህ ተልዕኮ እኛም እንደ ጳውሎስ ዓይነት ስሜት እንዲኖረን የሚያደርገው እንዴት ነው?

ከተወገደ ከ34 ዓመታት ገደማ በኋላ በቅርቡ ወደ ይሖዋ የተመለሰው አልበርት እንዲህ ብሏል፦ “ኃጢአቴ ሁልጊዜ ከአእምሮዬ አይጠፋም። ሆኖም አገልግሎት ላይ ስሆን ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ይህን ሥራ ለእኔ በአደራ እንደሰጠኝ ይሰማኛል። አገልግሎት ያበረታታኛል፤ ስለ ራሴ እንዲሁም ስለ አሁኑና ስለ ወደፊት ሕይወቴ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረኝ ይረዳኛል።”—መዝ. 51:3

ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ስታስጠና ኢየሱስ ምሕረት እንደሚያደርግላቸውና እንደሚወዳቸው አረጋግጥላቸው

እውነትን ከመስማቱ በፊት ወንጀለኛና ጠበኛ የነበረው አለን ደግሞ እንዲህ ሲል በግልጽ ተናግሯል፦ “በሰዎች ላይ ያደረስኩት ጉዳት አሁንም ድረስ ወደ አእምሮዬ ይመጣል። በዚህ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ በጭንቀት እዋጣለሁ። ይሖዋ እንደ እኔ ያለ ኃጢአተኛ ምሥራቹን ለሰዎች እንዲናገር እንደፈቀደ ሳስብ ግን ልቤ በአመስጋኝነት ይሞላል። ሰዎች ምሥራቹን ሲቀበሉ ስመለከት፣ ይሖዋ ምን ያህል ደግና አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ አስታውሳለሁ። እኔ የነበረኝ ዓይነት ሕይወት ያላቸውን ሰዎች እንድረዳ ይሖዋ እየተጠቀመብኝ እንደሆነ ይሰማኛል።”

አገልግሎታችን አዎንታዊ በሆኑ ድርጊቶችና ሐሳቦች ላይ እንድናተኩር አጋጣሚ ይፈጥርልናል። ኢየሱስ ምሕረት እንዳደረገልንና እንደሚወደን እንዲሁም በእኛ እንደሚተማመን እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል።

ይሖዋ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው

የሰይጣን ክፉ ሥርዓት እስከሚጠፋ ድረስ፣ ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ስህተቶች የተነሳ ልባችን ሊኮንነን ይችላል። እንዲህ ያለውን ስሜት ለማሸነፍ ምን ይረዳናል?

ወጣት እያለች ትመራው በነበረው ሁለት ዓይነት ሕይወት የተነሳ ብዙ ጊዜ ከጥፋተኝነት ስሜት ጋር የምትታገለው ጂን “‘አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ’ መሆኑ በጣም ያስደስተኛል” ብላለች። (1 ዮሐ. 3:19, 20) እኛም፣ ይሖዋና ኢየሱስ ስለ ኃጢአተኛው ሥጋችን ከእኛ የተሻለ ግንዛቤ እንዳላቸው ማወቃችን ያጽናናናል። ይሖዋና ኢየሱስ በፍቅር ተነሳስተው ቤዛውን ያዘጋጁት ንስሐ ለገቡ ኃጢአተኞች እንጂ ፍጹም ለሆኑ የሰው ልጆች እንዳልሆነ እናስታውስ።—1 ጢሞ. 1:15

ልባችን እንዲረጋጋ ለማድረግ ኢየሱስ ፍጹም ያልሆኑ የሰው ልጆችን በያዘበት መንገድ ላይ በጥልቅ ማሰላሰላችን እንዲሁም እሱ የሰጠንን አገልግሎት ለመፈጸም የምንችለውን ሁሉ ማከናወናችን ይጠቅመናል። እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ አንተም እንደ ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ‘እኔን ይወደኛል፤ ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል’ ማለት ትችላለህ።