በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ያደረግኩት ላደርገው የሚገባኝን ነገር ነው

ያደረግኩት ላደርገው የሚገባኝን ነገር ነው

ዶናልድ ሪድሊ ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ጠበቃ ሆኖ አገልግሏል። ታካሚዎች ያለደም ሕክምና የማግኘት መብታቸው እንዲከበር በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ዶናልድ ያከናወነው ሥራ የይሖዋ ምሥክሮች በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ድል እንዲያገኙ አስችሏል። ጓደኞቹ ዶን ብለው የሚጠሩት ይህ ወንድም ትጉ፣ ትሑትና የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ሰው ነበር።

በ2019 ዶን በማይድን የነርቭ በሽታ እንደተያዘ ታወቀ። ሕመሙ በፍጥነት እየተባባሰ በመምጣቱ ነሐሴ 16, 2019 ሕይወቱ አልፏል። የሕይወት ታሪኩ ይህን ይመስላል።

የተወለድኩት በ1954 በሴንት ፖል፣ ሚኒሶታ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነው፤ ቤተሰቤ የሮም ካቶሊክ እምነት ተከታዮች ሲሆኑ መካከለኛ ገቢ ነበራቸው። ከአምስት ልጆች መካከል ሁለተኛ ነኝ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በካቶሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር፤ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም አገለግል ነበር። ያም ቢሆን የነበረኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በጣም ትንሽ ነበር። ሁሉንም ነገር የፈጠረ አምላክ እንዳለ ባምንም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያለኝ እምነት ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ነበር።

እውነትን ተማርኩ

በዊልያም ሚቼል የሕግ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሳለሁ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቴ መጡ። በወቅቱ ልብሴን እያጠብኩ ስለነበር ባልና ሚስቱ ሌላ ጊዜ እንደሚመለሱ በደግነት ገለጹልኝ። ተመልሰው ሲመጡ ሁለት ጥያቄዎች አቀረብኩላቸው፤ “ጥሩ ሰዎች የማይሳካላቸው ለምንድን ነው?” እና “እውነተኛ ደስታ የሚገኘው እንዴት ነው?” ብዬ ጠየቅኳቸው። እነሱም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የሚለውን መጽሐፍና ትኩረት የሚስብ አረንጓዴ ቀለም ያለውን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ሰጡኝ። እኔም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማሁ። ጥናቱ ዓይኔን ገለጠልኝ። የአምላክ መንግሥት ሰዎችን የሚያስተዳድርበት ቀን እንደሚመጣ ሳውቅ በጣም ተደነቅኩ። ሰዎች ራሳቸውን ለመምራት ያደረጉት ጥረት በሰው ልጆች ላይ መከራ፣ ሥቃይ፣ ግፍና ሐዘን ከማስከተል ውጭ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ማስተዋል ችዬ ነበር።

በ1982 መጀመሪያ አካባቢ ራሴን ከወሰንኩ በኋላ በዚያው ዓመት በሴንት ፖል በሚገኝ አንድ አዳራሽ ውስጥ “የመንግሥቱ እውነት” በሚል ጭብጥ በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ ተጠመቅኩ። በቀጣዩ ሳምንት በዚያው አዳራሽ የሚኒሶታ ግዛት ያዘጋጀውን የጠበቃነት ማረጋገጫ ፈተና ተፈተንኩ። ጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ ፈተናውን በማለፌ ጠበቃ ሆኜ ለመሥራት ተፈቀደልኝ።

“የመንግሥቱ እውነት” በተባለው ስብሰባ ላይ በብሩክሊን ቤቴል ከሚያገለግለው ከማይክ ሪቻርድሰን ጋር ተገናኝተን ነበር፤ እሱም በዋናው መሥሪያ ቤት ውስጥ የሕግ ክፍል እንደተቋቋመ ነገረኝ። በሐዋርያት ሥራ 8:36 ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የተናገረው ነገር ትዝ አለኝና ‘እኔስ በሕግ ክፍል ውስጥ እንዳላገለግል የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?’ ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። ስለዚህ ቤቴል ለማገልገል ማመልከቻ አስገባሁ።

ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ አልተደሰቱም። አባቴ ለመጠበቂያ ግንብ ድርጅት መሥራቴ ለሕግ ሙያዬ ምን ጥቅም እንዳለው ጠይቆኝ ነበር። እኔም የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት እንደምሰጥና በወር 75 ዶላር እንደሚሰጠኝ ነገርኩት፤ በወቅቱ የቤቴላውያን ወርሃዊ ወጪ መሸፈኛ ይህ ነበር።

በጀመርኩት ሥራ ላይ የነበሩብኝን ግዴታዎች ከተወጣሁ በኋላ በ1984 በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የቤቴል አገልግሎቴን ጀመርኩ። በሕግ ክፍል እንዳገለግል ተመደብኩ። የቤቴል አገልግሎቴን የጀመርኩት በጣም ጥሩ ጊዜ ላይ ነበር።

የስታንሊ ቲያትር ቤት እድሳት

የስታንሊ ቲያትር ቤት በተገዛበት ወቅት

በጀርሲ ሲቲ፣ ኒው ጀርሲ የሚገኘው የስታንሊ ቲያትር ቤት የተገዛው ኅዳር 1983 ነበር። ወንድሞች የሕንፃውን የኤሌክትሪክና የቧንቧ መስመር ለማደስ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ወንድሞች ቲያትር ቤቱን ለሃይማኖታዊ ስብሰባዎች ሊጠቀሙበት እንዳሰቡ ለአካባቢው ባለሥልጣናት ገለጹላቸው። ባለሥልጣናቱ ግን ይህን ሐሳብ አልተቀበሉትም። በከተማዋ ሕግ መሠረት የአምልኮ ሕንፃዎች መገኘት ያለባቸው በመኖሪያ ሰፈሮች ብቻ ነበር። የስታንሊ ቲያትር ቤት ግን የሚገኘው በከተማዋ የንግድ ማዕከል ውስጥ ስለሆነ ባለሥልጣናቱ ፈቃዱን ለመስጠት አልተስማሙም። ወንድሞች ይግባኝ ቢጠይቁም ይግባኙ ውድቅ ተደረገ።

ቤቴል በገባሁበት ሳምንት ላይ ድርጅቱ ፈቃድ መከልከላችንን አስመልክቶ በፌዴራል የአውራጃ ፍርድ ቤት ክስ መሠረተ። ቤቴል ከመግባቴ በፊት በሴንት ፖል፣ ሚኒሶታ በሚገኘው የፌዴራል የአውራጃ ፍርድ ቤት ለሁለት ዓመታት ስለሠራሁ በፍርድ ቤቱ ስለሚቀርቡት ክርክሮች ብዙ እውቀት ነበረኝ። አንደኛው ጠበቃችን የስታንሊ ቲያትር ቤት፣ ፊልሞችንና የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሕዝባዊ ፕሮግራሞችን እንደሚያስተናግድ ከገለጸ በኋላ ‘ታዲያ ሃይማኖታዊ ስብሰባ ማዘጋጀት ሕገ ወጥ የሚሆነው ለምንድን ነው?’ በማለት ጠየቀ። የፌዴራል የአውራጃ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ የጀርሲ ሲቲ የከተማ አስተዳደር ሃይማኖታዊ ነፃነታችንን እንደተጋፋ ገለጸ። ፍርድ ቤቱ የከተማው አስተዳደር አስፈላጊውን ፈቃድ እንዲሰጥ አዘዘ፤ እኔም ድርጅቱ ሕጋዊ አሠራር ተጠቅሞ ሥራውን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት ይሖዋ እንዴት እንደሚባርከው አስተዋልኩ። በዚህ ሥራ መካፈል በመቻሌ በጣም ተደስቼ ነበር።

ወንድሞች መጠነ ሰፊ የእድሳት ሥራ አከናወኑ፤ ከዚያም የእድሳት ሥራው ከጀመረ ዓመት እንኳ ሳይሞላው የ79ኛው የጊልያድ ክፍል ምርቃት መስከረም 8, 1985 በጀርሲ ሲቲ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ተካሄደ። በሕግ ክፍሉ ውስጥ ሆኜ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የማራመድ መብት በማግኘቴ ከፍተኛ ደስታ ተሰማኝ፤ ቤቴል ከመግባቴ በፊት የሕግ ባለሙያ ሆኜ በሠራሁባቸው ጊዜያት በሙሉ እንዲህ ያለ እርካታ አግኝቼ አላውቅም። ይሖዋ እንዲህ ያለ አርኪ ሥራ በተደጋጋሚ እንደሚሰጠኝ በወቅቱ አላወቅኩም ነበር።

ያለደም ሕክምና የማግኘት መብትን ማስከበር

በ1980ዎቹ ሐኪሞችና ሆስፒታሎች አዋቂ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ያለደም ሕክምና ለማግኘት የሚያቀርቡትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው የተለመደ ነገር ነበር። በተለይ ነፍሰ ጡር ሴቶች ከዚህ ጋር በተያያዘ ከበድ ያለ ፈተና ያጋጥማቸው ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ዳኞች፣ እናትየዋ ደም ካልወሰደች ሕፃኑ ያለእናት ሊቀር ስለሚችል ነፍሰ ጡር ሴቶች ደም ላለመውሰድ የመምረጥ መብት እንደሌላቸው ይገልጹ ነበር።

ታኅሣሥ 29, 1988 እህት ዴኒስ ኒኮሎ ወንድ ልጅ ከተገላገለች በኋላ ብዙ ደም ፈሰሳት። የሂሞግሎቢኗ መጠን ከ5.0 በታች ወርዶ ነበር፤ ስለዚህ ሐኪሟ ደም ለመውሰድ እንድትስማማ ጠየቃት። እህት ኒኮሎ ግን ፈቃደኛ አልሆነችም። የሆስፒታሉ ሠራተኞች እህት ኒኮሎ ደም ሊሰጣት እንደሚገባ ስላመኑ ደም ለመስጠት የሚያስችል ፈቃድ ለማግኘት በማግስቱ ጠዋት ለፍርድ ቤት አመለከቱ። ዳኛውም የእህት ኒኮሎን ሐሳብ ሳይጠይቁ፣ ሌላው ቀርቶ ለእሷም ሆነ ለባለቤቷ ጉዳዩን ሳያሳውቁ ሆስፒታሉ ደም እንዲሰጣት የሚያዝዝ ውሳኔ አስተላለፉ።

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 30 የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለእህት ኒኮሎ ደም ሰጧት፤ ባለቤቷም ሆነ አብረዋት የነበሩ ሌሎች የቤተሰቧ አባላት ቢቃወሙም ሠራተኞቹ ደም ከመስጠት ወደኋላ አላሉም። በርካታ የቤተሰቧ አባላትና ጥቂት ሽማግሌዎች እህት ኒኮሎን ከበው ደም እንዳይሰጣት ለመከላከል በመሞከራቸው በዚያ ምሽት ተይዘው ታሰሩ። ቅዳሜ ጠዋት፣ ታኅሣሥ 31 የኒው ዮርክ ሲቲና የሎንግ አይላንድ የዜና ማሰራጫዎች ስለ እስራቱ ሲዘግቡ ነበር።

ከፊሊፕ ብረምሊ ጋር፣ ወጣት ሳለን

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ዋና ዳኛ ከሆኑት ከሚልተን ሞለን ጋር ሰኞ ጠዋት ተነጋገርኩ። ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ሰጠኋቸው፤ እንዲሁም ደም እንዲሰጥ የወሰኑት ዳኛ ውሳኔውን ያስተላለፉት ታካሚዋን ሳያነጋግሩ እንደሆነ ጎላ አድርጌ ገለጽኩላቸው። ሚልተን ሞለን የተባሉት ዳኛም ከሰዓት በኋላ ወደ ቢሯቸው በመምጣት ስለ ጉዳዩና ተያያዥነት ስላላቸው ሕጎች እንድንነጋገር ጠየቁኝ። በቤቴል የሥራ ኃላፊዬ የሆነው ፊሊፕ ብረምሊም አብሮኝ ወደ ዳኛው ቢሮ ሄደ። ዳኛው በውይይቱ ላይ የሆስፒታሉ ጠበቃም እንዲገኝ ጠርተውት ነበር። ውይይታችን እየተጋጋለ ሄደ። እንዲያውም የሆነ ሰዓት ላይ ወንድም ብረምሊ በማስታወሻ ደብተሩ ላይ “ተረጋጋ” ብሎ ጽፎ አሳየኝ። አሁን ሳስበው ጥሩ ምክር እንደሰጠኝ ይሰማኛል፤ ምክንያቱም የጠበቃውን ሐሳብ ውድቅ ለማድረግ በጣም በግለት እየተከራከርኩ ነበር።

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ሪቻርድ ሞኬ፣ ግሪጎሪ ኦልድስ፣ ፖል ፖሊዶሮ፣ ፊሊፕ ብረምሊ፣ እኔ እና ማሪዮ ሞሬኖ—ከሳሽ “መጠበቂያ ግንብ” ተከሳሽ “የስትራተን መንደር” በተባለው ክስ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት መከራከሪያችንን ባቀረብንበት ዕለት።—የጥር 2003 ንቁ! መጽሔትን ተመልከት

ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ዳኛው፣ በማግስቱ ጠዋት ፍርድ ቤት የሚታየው የመጀመሪያው ጉዳይ ይህ ክስ እንደሚሆን ነገሩን። ከቢሯቸው እየወጣን ሳለ ዳኛው የሆስፒታሉ ጠበቃ “ነገ ከባድ ሥራ” እንደሚጠብቀው ተናገሩ። ይህም ጠበቃው ለሆስፒታሉ ጥብቅና መቆም ቀላል እንደማይሆንለት የሚጠቁም ንግግር ነበር። ይሖዋ የማሸነፍ አጋጣሚያችን ከፍተኛ እንደሆነ እያረጋገጠልኝ እንደሆነ ተሰማኝ። ይሖዋ ፈቃዱን ለማስፈጸም እየተጠቀመብን መሆኑን ማወቄ ልቤን ነካው።

በዚያ ሌሊት በቀጣዩ ቀን ለሚኖረን ክርክር ስንዘጋጅ ቆየን። ፍርድ ቤቱ የሚገኘው በብሩክሊን ቤቴል አቅራቢያ ስለነበር በሕግ ክፍል ውስጥ ያለን አብዛኞቻችን ወደ ፍርድ ቤቱ በእግር ሄድን። አራት ዳኞችን ያቀፈው ችሎት ክርክሩን ካዳመጠ በኋላ እህት ኒኮሎ ደም እንዲሰጣት የተደረገው ውሳኔ ተገቢ እንዳልነበር ገለጸ። ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ለእህት ኒኮሎ የፈረደላት ከመሆኑም ሌላ በወቅቱ በፍርድ ቤቶች ውስጥ ይተገበር የነበረው ሰዎች አቋማቸውን የሚገልጹበት አጋጣሚ ሳያገኙ ውሳኔ የማስተላለፍ ልማድ የሰዎቹን መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚጥስ እንደሆነ ገለጸ።

በመጨረሻም የኒው ዮርክ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እህት ኒኮሎ ያለደም ሕክምና የማግኘት መብት እንዳላት አረጋገጠ። እኔ ከተካፈልኩባቸው ከደም ጋር የተያያዙ አራት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዮች መካከል ይህ የመጀመሪያው ነው። (“ በተለያዩ ግዛቶች በጠቅላይ ፍርድ ቤት ያገኘናቸው ድሎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በተጨማሪም በቤቴል ካሉ ሌሎች ጠበቆች ጋር ሆኜ ልጅ ከማሳደግ መብት፣ ከፍቺ እንዲሁም ከመሬትና ከሕንፃ ይዞታ ጋር በተያያዙ የሕግ ጉዳዮች ላይ ተካፍያለሁ።

ትዳሬና ቤተሰቤ

ከባለቤቴ ከዶውን ጋር

ከባለቤቴ ከዶውን ጋር በተዋወቅንበት ወቅት ዶውን ከባሏ ተፋታ ሦስት ልጆቿን ብቻዋን ታሳድግ ነበር። ቤተሰቧን እያስተዳደረች በአቅኚነት ታገለግል ነበር። አስቸጋሪ ሕይወት አሳልፋለች። ይሖዋን ለማገልገል ያላት ቁርጠኝነት በጣም ማረከኝ። በ1992 በኒው ዮርክ ሲቲ በተካሄደው “ብርሃን አብሪዎች” የተባለ አውራጃ ስብሰባ ላይ ተገናኝተን ነበር፤ በዚህ ወቅት እንድንጠናና ጠየቅኳት። ከአንድ ዓመት በኋላ ተጋባን። ይሖዋ መንፈሳዊና ተጫዋች የሆነች ሚስት ስለሰጠኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። ዶውን አብረን ባሳለፍነው ዘመን ሁሉ መልካም ነገር አድርጋልኛለች።—ምሳሌ 31:12

በተጋባንበት ወቅት የልጆቹ ዕድሜ 11፣ 13 እና 16 ዓመት ነበር። ጥሩ አባት ልሆንላቸው ፈልጌ ስለነበር የእንጀራ አባት ስለመሆን የሚናገሩ በጽሑፎቻችን ላይ የወጡ ርዕሶችን በሙሉ በጥንቃቄ አንብቤ ተግባራዊ ለማድረግ እሞክር ነበር። ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ተፈታታኝ ነገሮች አጋጥመውናል፤ ሆኖም ልጆቹ እንደ ታማኝ ወዳጅና እንደ አፍቃሪ አባት አድርገው ስለተቀበሉኝ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለልጆቻችን ጓደኞች በራችን ምንጊዜም ክፍት ነበር፤ ቤታችን ተጫዋች በሆኑ ወጣቶች መሞላቱ ያስደስተን ነበር።

በ2013 እኔና ዶውን በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችንን ለመንከባከብ ወደ ዊስኮንሰን ተዛወርን። የሚገርመው የቤቴል አገልግሎቴ ያኔም አላቆመም። ጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኜ ለድርጅታችን ሕግ ነክ እርዳታ እንዳበረክት ተጋበዝኩ።

ድንገተኛ ለውጥ

መስከረም 2018 ላይ ጉሮሮዬን በተደጋጋሚ መጥረግ እንደሚያስፈልገኝ ስላስተዋልኩ ሁኔታው አሳሰበኝ። በአካባቢያችን ያለ አንድ ሐኪም መረመረኝ፤ ሆኖም የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ ማወቅ አልቻለም። በኋላ ግን አንድ ሌላ ሐኪም የነርቭ ስፔሻሊስት እንዳማክር ሐሳብ አቀረበልኝ። ጥር 2019 የነርቭ ስፔሻሊስቱ ምርመራ ካደረገልኝ በኋላ ፕሮግረሲቭ ሱፕራኒዩክሊያር ፓልሲ የተባለ እምብዛም የማይታወቅ የነርቭ ሕመም ሊኖርብኝ እንደሚችል ነገረኝ።

ከሦስት ቀን በኋላ በምወደው ስፖርታዊ ጨዋታ እየተካፈልኩ ሳለ ወድቄ ቀኝ እጄ ተሰበረ። ዕድሜ ልኬን ይህን ስፖርት ስሠራ ኖሬያለሁ። ስለዚህ ጡንቻዎቼን የመቆጣጠር ችሎታዬ እየተዳከመ እንደሆነ አስተዋልኩ። የነርቭ ሕመሙ በፍጥነት እየተባባሰ ስለሄደ መናገር፣ መንቀሳቀስና ምግብ መዋጥ እየከበደኝ ሄደ።

የጠበቃነት ሙያዬን ተጠቅሜ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማራመድ የበኩሌን አነስተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። በተጨማሪም በብዙ መጽሔቶች ላይ ከሙያዬ ጋር የተያያዙ ጽሑፎችን የማቅረብ እንዲሁም በመላው ዓለም በተካሄዱ ከሕክምናና ከሕግ ጋር የተያያዙ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቼ የይሖዋ ምሥክሮች ያለደም ሕክምናና ቀዶ ጥገና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው የመሟገት አጋጣሚ አግኝቻለሁ። ያም ቢሆን ሉቃስ 17:10 እንደሚናገረው ‘ምንም የማልጠቅም ባሪያ ነኝ። ያደረግኩት ላደርገው የሚገባኝን ነገር ነው።’