በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 29

በራስህ መንፈሳዊ እድገት ተደሰት!

በራስህ መንፈሳዊ እድገት ተደሰት!

“እያንዳንዱ ሰው . . . ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላ. 6:4

መዝሙር 34 በንጹሕ አቋም መመላለስ

ማስተዋወቂያ *

1. ይሖዋ ከሌሎች ጋር የማያወዳድረን ለምንድን ነው?

ይሖዋ ልዩነት የሚወድ አምላክ ነው። የሰው ልጆችን ጨምሮ አስደናቂ በሆኑት ፍጥረታቱ መካከል የሚታየው ልዩነት ይህን ያረጋግጣል። እያንዳንዳችን ልዩ ነን። በመሆኑም ይሖዋ በፍጹም ከሌሎች ጋር አያወዳድርህም። ልብህን ማለትም ውስጣዊ ማንነትህን ይመረምራል። (1 ሳሙ. 16:7) በተጨማሪም ጥንካሬህን፣ ድክመትህን እና አስተዳደግህን ግምት ውስጥ ያስገባል። እንዲሁም ከአቅምህ በላይ አይጠብቅብህም። እኛም ስለ ራሳችን የይሖዋ ዓይነት አመለካከት በማዳበር እሱን መምሰል ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን “ጤናማ አስተሳሰብ” ይኖረናል፤ በሌላ አባባል ራሳችንን ከልክ በላይ ከፍም ሆነ ዝቅ አድርገን አንመለከትም።—ሮም 12:3

2. ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደራችን ጥሩ ያልሆነው ለምንድን ነው?

2 እርግጥ ነው፣ ከሌሎች መልካም አርዓያነት መማር እንችላለን። ለምሳሌ በአገልግሎቱ ውጤታማ የሆነ ታማኝ ክርስቲያን እናውቅ ይሆናል። (ዕብ. 13:7) ከእሱ ምሳሌ፣ በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። (ፊልጵ. 3:17) ይሁንና የአንድን ሰው መልካም ምሳሌ በመከተልና ራሳችንን ከግለሰቡ ጋር በማወዳደር መካከል ልዩነት አለ። በዚህ መልኩ ከሌሎች ጋር ራሳችንን ማወዳደራችን እንድንቀና፣ ተስፋ እንድንቆርጥ ይባስ ብሎም የከንቱነት ስሜት እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። በተጨማሪም ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር መፎካከራችን መንፈሳዊነታችንን ይጎዳዋል። በመሆኑም ይሖዋ እንደሚከተለው የሚል ፍቅር የሚንጸባረቅበት ምክር ሰጥቶናል፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላ. 6:4

3. በየትኞቹ አቅጣጫዎች እድገት በማድረግህ መደሰት ትችላለህ?

3 ይሖዋ በራስህ መንፈሳዊ እድገት እንድትደሰት ይፈልጋል። ለምሳሌ የተጠመቅክ ክርስቲያን ከሆንክ እዚህ ግብ ላይ በመድረስህ ልትደሰት ይገባሃል! ይህን ውሳኔ ያደረግከው አንተው ራስህ ነህ። ይህን ውሳኔ ለማድረግ ያነሳሳህ ለአምላክ ያለህ ፍቅር ነው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ያደረግከውን እድገት አስብ። ለምሳሌ፣ ለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ጥናት ያለህ ፍቅር ጨምሯል? የምታቀርበው ጸሎት ይበልጥ ትርጉም ያለውና ከልብ የመነጨ ሆኗል? (መዝ. 141:2) በአገልግሎት ላይ ውይይት በመጀመር ወይም የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችንን በመጠቀም ረገድ ክህሎትህን አሳድገሃል? ቤተሰብ ካለህ ደግሞ በይሖዋ እርዳታ የተሻለ የትዳር ጓደኛ ወይም ወላጅ መሆን ችለሃል? በእነዚህ ሁሉ አቅጣጫዎች እድገት በማድረግህ ከልብህ ልትደሰት ይገባሃል።

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

4 ሌሎች በራሳቸው መንፈሳዊ እድገት እንዲደሰቱ ልንረዳቸው እንችላለን። ራሳቸውን ከሌሎች ጋር ከማወዳደር እንዲቆጠቡም ልንረዳቸው እንችላለን። በዚህ ረገድ ወላጆች ልጆቻቸውን መርዳት፣ የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው መረዳዳት እንዲሁም ሽማግሌዎችና ሌሎች ክርስቲያኖች ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን መርዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም ከራሳችን ችሎታና ካለንበት ሁኔታ ጋር የሚስማሙ ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦችን ለማውጣት የሚረዱንን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመለከታለን።

ወላጆችና የትዳር አጋሮች ምን ማድረግ ይችላሉ?

ወላጆች፣ እያንዳንዱ ልጃችሁ የሚያደርገውን ጥረት አድንቁ (ከአንቀጽ 5-6⁠ን ተመልከት) *

5. በኤፌሶን 6:4 መሠረት ወላጆች ምን ላለማድረግ መጠንቀቅ አለባቸው?

5 ወላጆች አንዱን ልጃቸውን ከሌላው ጋር ላለማወዳደር መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም ልጃቸውን ከአቅሙ በላይ ሊጠብቁበት አይገባም። እንዲህ ማድረግ ልጃቸውን ተስፋ ሊያስቆርጠው ይችላል። (ኤፌሶን 6:4ን አንብብ።) ሳቺኮ * የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “አስተማሪዎቼ አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች የተሻለ ውጤት እንዳመጣ ይጠብቁብኝ ነበር። እናቴም ለአስተማሪዬና የይሖዋ ምሥክር ላልሆነው አባቴ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት እንድችል ጎበዝ ተማሪ እንድሆን ትጠብቅብኝ ነበር። እንዲያውም በሁሉም ፈተናዎቼ መቶ ከመቶ እንዳመጣ ትፈልግ ነበር፤ ይህን ማድረግ ደግሞ አልቻልኩም። ትምህርት ከጨረስኩ ብዙ ዓመት አልፎኛል፤ አሁንም ግን ለይሖዋ ምርጤን ብሰጥም እንኳ ‘እሱ ይደሰትብኝ ይሆን?’ የሚለውን እጠራጠራለሁ።”

6. ወላጆች ከመዝሙር 131:1, 2 ምን ይማራሉ?

6 ወላጆች ከመዝሙር 131:1, 2 ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። (ጥቅሱን አንብብ።) ንጉሥ ዳዊት “እጅግ ታላላቅ ነገሮችን” ወይም ከአቅሙ በላይ የሆኑ ነገሮችን እንደማይመኝ ተናግሯል። ትሑትና ልኩን የሚያውቅ መሆኑ ‘እንዲረጋጋ’ እና ሰላም እንዲያገኝ አድርጎታል። ወላጆች ዳዊት ከተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? ወላጆች ትሑት መሆናቸው ከራሳቸው ብቻ ሳይሆን ከልጆቻቸውም ከልክ በላይ እንዳይጠብቁ ያደርጋቸዋል። ወላጆች፣ ልጃቸው ጥንካሬውንና ድክመቱን እንዲያውቅ እንዲሁም ሊደርስባቸው የሚችሉ ግቦች እንዲያወጣ በመርዳት ለራሱ ጥሩ ግምት እንዲኖረው ሊረዱት ይችላሉ። ማሪና የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ከሦስቱ ወንድሞቼም ሆነ ከሌሎች ልጆች ጋር ፈጽሞ አወዳድራኝ አታውቅም። ሁሉም ሰው የተለያየ ስጦታ እንዳለው እንዲሁም ሁላችንም በይሖዋ ዓይን ውድ እንደሆንን አስተምራኛለች። እሷ እንዲህ አድርጋ ስላሳደገችኝ አሁንም ቢሆን ራሴን ከሌሎች ጋር ለማወዳደር አልፈተንም።”

7-8. አንድ ባል ሚስቱን ማክበር የሚችለው እንዴት ነው?

7 አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱን በአክብሮት ሊይዛት ይገባል። (1 ጴጥ. 3:7) እንዲህ ማድረግ የሚችልበት አንዱ መንገድ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጣት በማሳየት ነው። ማድረግ ከምትችለው በላይ አይጠብቅባትም። እንዲሁም ከሌሎች ሴቶች ጋር ጨርሶ አያወዳድራትም። አንድ ባል ሚስቱን ከሌሎች ሴቶች ጋር ቢያወዳድራት ምን ሊሰማት ይችላል? ሮዛ የተባለችን እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባሏ ከሌሎች ሴቶች ጋር ብዙ ጊዜ ያወዳድራታል። ባለቤቷ የሚናገረው ቅስም የሚሰብር ንግግር ሮዛ ለራሷ ዝቅተኛ አመለካከት እንዲያድርባትና ማንም እንደማይወዳት እንድታስብ አድርጓት ነበር። “ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከተኝ መሆኑን ስለምጠራጠር ሁልጊዜ ‘ይሖዋ ይወድሻል’ ብሎ የሚያስታውሰኝ ያስፈልገኛል” በማለት ተናግራለች። አንድ ክርስቲያን ባል ግን ሚስቱን ያከብራታል። ይህን ማድረጉ ከእሷ ጋርም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና እንደሚነካው ያውቃል። *

8 ሚስቱን የሚያከብር ባል እንደሚወዳት ይገልጽላታል፣ ያሞግሳታል እንዲሁም በሰዎች ፊት ያመሰግናታል። (ምሳሌ 31:28) ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ካታሪና ራሷን ዝቅ አድርጋ የመመልከት አዝማሚያዋን እንድታሸንፍ ባለቤቷ የረዳት በዚህ መንገድ ነው። ካታሪና ልጅ እያለች እናቷ ታንቋሽሻት እንዲሁም ብዙ ጊዜ ከጓደኞቿ እና ከሌሎች ልጆች ጋር ታወዳድራት ነበር። በዚህም ምክንያት ካታሪና ራሷን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ዝንባሌ ተጠናወታት፤ ወደ እውነት ከመጣች በኋላም ጭምር እንዲህ ማድረጓን አላቆመችም። ሆኖም ክርስቲያን የሆነው ባለቤቷ ይህን ዝንባሌ እንድታሸንፍና ስለ ራሷ ይበልጥ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንድታዳብር ረድቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ይወደኛል፤ ለማደርጋቸው መልካም ነገሮች ያመሰግነኛል እንዲሁም ይጸልይልኛል። ከዚህም ሌላ የይሖዋን ግሩም ባሕርያት እንዳስታውስና አሉታዊ አስተሳሰቤን እንዳስተካክል ይረዳኛል።”

አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎችና ሌሎች ክርስቲያኖች ምን ማድረግ ይችላሉ?

9-10. አንዲት እህት ራሷን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ዝንባሌዋን እንድታሸንፍ አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች የረዷት እንዴት ነው?

9 ሽማግሌዎች፣ ራሳቸውን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ዝንባሌ ያላቸውን ክርስቲያኖች መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? ሀኑኒ የተባለችን እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ሀኑኒ በልጅነቷ ማንም አመስግኗት አያውቅም ማለት ይቻላል። እንዲህ ብላለች፦ “ዓይናፋር ነበርኩ፤ እንዲሁም ሌሎች ልጆች ከእኔ እንደሚበልጡ ይሰማኝ ነበር። ከልጅነቴ አንስቶ ራሴን ከሌሎች ጋር አወዳድር ነበር።” ሀኑኒ ወደ እውነት ከመጣችም በኋላ ራሷን ከሌሎች ጋር ማወዳደሯን አላቆመችም። በዚህም ምክንያት በጉባኤ ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንደምታበረክት አይሰማትም ነበር። አሁን ግን ደስተኛ ሆና በአቅኚነት እያገለገለች ነው። አመለካከቷን እንድትቀይር የረዳት ምንድን ነው?

10 ሀኑኒ አሳቢ የሆኑ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንደረዷት ተናግራለች። ሽማግሌዎቹ በጉባኤው ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳላት ያረጋግጡላት እንዲሁም ጥሩ ምሳሌ በመሆኗ ያመሰግኗት ነበር። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ሽማግሌዎቹ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን እህቶች እንዳበረታታ አልፎ አልፎ ይጠይቁኝ ነበር። እንዲህ ዓይነት ኃላፊነት ሲሰጠኝ ተፈላጊ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። አሳቢ የሆኑት ሽማግሌዎቻችን በአንድ ወቅት ለአንዳንድ ወጣት እህቶች ለሰጠሁት ማበረታቻ ካመሰገኑኝ በኋላ 1 ተሰሎንቄ 1:2, 3⁠ን አነበቡልኝ። ይህ በጣም አስደሰተኝ! ለእነዚህ ግሩም እረኞች ምስጋና ይግባቸውና አሁን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንደማበረክት ይሰማኛል።”

11. ‘የተሰበረ ልብ ያላቸውንና መንፈሳቸው የተደቆሰውን’ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 57:15)

11 ኢሳይያስ 57:15ን አንብብ። ይሖዋ ‘የተሰበረ ልብ ላላቸውና መንፈሳቸው ለተደቆሰ’ ሰዎች በጥልቅ ያስብላቸዋል። ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም እነዚህን ውድ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ማበረታታት እንችላለን። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ለእነሱ ልባዊ አሳቢነት በማሳየት ነው። ይሖዋ እሱ ምን ያህል እንደሚወዳቸው እንድናሳያቸው ይፈልጋል። (ምሳሌ 19:17) ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መርዳት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ትሑቶችና ልካችንን የምናውቅ በመሆን ነው። ወደ ራሳችን ትኩረት የሚስብ ነገር በማድረግ ሌሎችን ማስቀናት አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ችሎታችንን እና እውቀታችንን ሌሎችን ለማበረታታት እንጠቀምበታለን።—1 ጴጥ. 4:10, 11

ኢየሱስ ራሱን ከፍ ከፍ ስላላደረገ ደቀ መዛሙርቱ ከእሱ ጋር መሆን ይቀልላቸው ነበር። ኢየሱስ ከወዳጆቹ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተው ነበር (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. ተራ ሰዎች ኢየሱስን ይወዱት የነበረው ለምንድን ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

12 ኢየሱስ ተከታዮቹን የያዘበትን መንገድ በመመርመር እኛም ሌሎችን እንዴት መያዝ እንዳለብን መማር እንችላለን። ኢየሱስ እስከ ዛሬ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው ነበር። ያም ቢሆን ‘ገርና በልቡ ትሑት’ ነበር። (ማቴ. 11:28-30) የላቀ የማሰብ ችሎታና እውቀት ቢኖረውም ይህን ለማሳየት አልሞከረም። ቀለል ያለ ቋንቋና ማራኪ ምሳሌዎችን በመጠቀም የተራ ሰዎችን ልብ በሚነካ መንገድ አስተምሯል። (ሉቃስ 10:21) በዘመኑ ከነበሩት ትዕቢተኛ የሃይማኖት መሪዎች በተለየ መልኩ ኢየሱስ፣ ሰዎች በአምላክ ዓይን ምንም ቦታ እንደሌላቸው እንዲሰማቸው አድርጎ አያውቅም። (ዮሐ. 6:37) ከዚህ ይልቅ ተራ ሰዎችን በአክብሮት ይዟቸዋል።

13. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበት መንገድ ደግነቱን እና ፍቅሩን የሚያሳየው እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበት መንገድ ደግነቱን እና ፍቅሩን ያሳያል። ችሎታቸው እና ያሉበት ሁኔታ እንደሚለያይ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ሁሉም ተመሳሳይ ኃላፊነት መሸከም ወይም በአገልግሎት ላይ እኩል ውጤት ማግኘት እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ያም ቢሆን እያንዳንዳቸው በሙሉ ነፍስ ያደረጉትን ጥረት አድንቋል። ኢየሱስ ስለ ታላንቱ የተናገረው ምሳሌ እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳለው ያሳያል። በምሳሌው ላይ ጌታው ለባሪያዎቹ ሥራ የሰጠው “ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው” ነው። በትጋት ከሠሩት ሁለት ባሪያዎች አንዱ ከሌላኛው የበለጠ ትርፍ አግኝቷል። ያም ቢሆን ጌታው ሁለቱንም ያመሰገናቸው ተመሳሳይ የአድናቆት ቃላት በመጠቀም ነው፤ “ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ!” ብሏቸዋል።—ማቴ. 25:14-23

14. ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ እኛንም ደግነት እና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይይዘናል። ችሎታችን እና ያለንበት ሁኔታ እንደሚለያይ ያውቃል፤ እንዲሁም ምርጣችንን ስንሰጥ ይደሰታል። እኛም ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ጠቃሚ ነው። አንድ የእምነት ባልንጀራችን የሌሎችን ያህል ማከናወን ባለመቻሉ ምክንያት እንዲሸማቀቅ ወይም የከንቱነት ስሜት እንዲሰማው ማድረግ በፍጹም አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለይሖዋ ምርጣቸውን በመስጠታቸው ምንጊዜም እናመስግናቸው።

ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦች አውጣ

ልትደርሱባቸው የምትችሏቸው ግቦች በማውጣትና እነዚህ ግቦች ላይ በመድረስ ተደሰቱ (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት) *

15-16. አንዲት እህት ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦች በማውጣቷ የተጠቀመችው እንዴት ነው?

15 መንፈሳዊ ግቦች ሕይወታችን አቅጣጫ እንዲይዝና ዓላማ እንዲኖረው ይረዱናል። ሆኖም ግብ ማውጣት ያለብን ሌሎችን በማየት ሳይሆን የራሳችንን ችሎታና ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። እንዲህ ማድረጋችን ከሐዘንና ተስፋ ከመቁረጥ ይጠብቀናል። (ሉቃስ 14:28) ሚዶሪ የተባለችን አቅኚ እንደ ምሳሌ እንመልከት።

16 የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው የሚዶሪ አባት፣ ልጅ እያለች ከወንድሟ እና ከእህቷ እንዲሁም አብረዋት ከሚማሩ ልጆች ጋር በማወዳደር ያሸማቅቃት ነበር። ሚዶሪ “ምንም ዋጋ እንደሌለኝ ይሰማኝ ነበር” ብላለች። ሆኖም ሚዶሪ እያደገች ስትሄድ በራስ የመተማመን ስሜቷ እየጨመረ ሄደ። “መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቤ ውስጣዊ ሰላም እንዳገኝ እና ይሖዋ እንደሚወደኝ እንድገነዘብ ረድቶኛል” በማለት ተናግራለች። በተጨማሪም ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦች አወጣች፤ እንዲሁም እነዚህ ግቦች ላይ መድረስ እንድትችል ጸለየች። በውጤቱም ሚዶሪ በራሷ መንፈሳዊ እድገት መደሰት ችላለች።

ለይሖዋ ምርጥህን መስጠትህን ቀጥል

17. ‘አእምሯችንን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ እንዲሄድ’ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችንስ ምን ውጤት ያስገኛል?

17 ያሉብንን አሉታዊ ስሜቶች በአንድ ጀምበር ማስወገድ አንችል ይሆናል። ይሖዋ “አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ” የሚል ምክር የሰጠን ለዚህ ነው። (ኤፌ. 4:23, 24) ይህን ለማድረግ መጸለይ፣ የአምላክን ቃል ማጥናትና ማሰላሰል እንዳለብን የታወቀ ነው። እነዚህን ነገሮች አዘውትረህ አድርግ፤ እንዲሁም ይሖዋ ብርታት እንዲሰጥህ ጠይቀው። የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ራስህን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ዝንባሌህን ለማሸነፍ ይረዳሃል። በተጨማሪም በልብህ ውስጥ ምቀኝነት ወይም ተገቢ ያልሆነ ኩራት እያቆጠቆጠ ከሆነ ይሖዋ እነዚህን መጥፎ ዝንባሌዎች ለማስተዋልና ለማስወገድ ይረዳሃል።

18. በ2 ዜና መዋዕል 6:29, 30 ላይ የሚገኘው ሐሳብ የሚያጽናናህ እንዴት ነው?

18 ሁለተኛ ዜና መዋዕል 6:29, 30ን አንብብ። ይሖዋ ልባችንን ያውቃል። በተጨማሪም ከዓለም መንፈስና ከራሳችን አለፍጽምና ጋር የምናደርገውን ትግል ያውቃል። ይሖዋ እነዚህን አሉታዊ ተጽዕኖዎች ለመቋቋም የምናደርገውን ከፍተኛ ጥረት ሲያይ ለእኛ ያለው ፍቅር ይጨምራል።

19. ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማስረዳት የትኛውን ምሳሌ ተጠቅሟል?

19 ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማስረዳት እናት ለሕፃን ልጇ ያላትን ፍቅር እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። (ኢሳ. 49:15) ሬቸል የተባለችን እናት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ልጄ ስቴፋኒ የተወለደችው ጊዜዋ ሳይደርስ ነበር። ልክ እንደተወለደች ሳያት ትንሽዬና ምስኪን ነበረች። ያለጊዜያቸው የተወለዱ ሕፃናት በሚቆዩበት ክፍል ውስጥ ለአንድ ወር በቆየችበት ወቅት በየቀኑ እየገባሁ እንዳቅፋት ሐኪሞች ፈቅደውልኝ ነበር። በዚያ ወቅት ከልጄ ጋር ጠንካራ ትስስር መመሥረት ችያለሁ። አሁን ልጄ ስድስት ዓመቷ ነው። እርግጥ በእሷ ዕድሜ ካሉ ሌሎች ልጆች አነስ ያለች ናት። ያም ቢሆን በሕይወት ለመቆየት ያደረገችው ከፍተኛ ትግል እንዲሁም በሕይወቴ ላይ የጨመረችው ታላቅ ደስታ ይበልጥ እንድወዳት አድርጎኛል!” ይሖዋ እሱን በሙሉ ነፍሳችን ለማገልገል የምናደርገውን ከፍተኛ ጥረት ሲያይ ለእኛ እንዲህ ያለ ጥልቅ ፍቅር እንደሚሰማው ማወቃችን በጣም ያጽናናናል!

20. ራስህን የወሰንክ የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን ለመደሰት የሚያበቃ ምን ምክንያት አለህ?

20 የይሖዋ አገልጋይ በመሆንህ ልዩና ውድ የሆንክ የቤተሰቡ አባል ነህ። ይሖዋ ወደ ራሱ የሳበህ ከሌሎች ሰዎች የተሻልክ ስለሆንክ አይደለም። ወደ ራሱ የሳበህ ልብህን ስለመረመረና ትሑት እንዲሁም ለመማርና ለመቀረጽ ፈቃደኛ ሰው እንደሆንክ ስላየ ነው። (መዝ. 25:9) እሱን ለማገልገል አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ስታደርግ በጣም እንደሚደሰት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። የምታሳየው ጽናትና ታማኝነት ‘መልካምና ጥሩ ልብ’ እንዳለህ ያሳያል። (ሉቃስ 8:15) እንግዲያው ለይሖዋ ምርጥህን መስጠትህን ቀጥል። እንዲህ ካደረግክ ‘ከራስህ ጋር ብቻ በተያያዘ’ የምትደሰትበት ነገር ታገኛለህ።

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

^ አን.5 ይሖዋ ከሌሎች ጋር አያወዳድረንም። ያም ቢሆን አንዳንዶቻችን ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ይቀናን ይሆናል፤ በዚህም ምክንያት ለራሳችን ዝቅተኛ አመለካከት እናዳብር ይሆናል። ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ጎጂ የሆነው ለምን እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም የቤተሰባችን አባላት እንዲሁም በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ስለ ራሳቸው የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

^ አን.5 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.7 እነዚህ ነጥቦች በባሎች ላይ የሚያተኩሩ ቢሆንም ብዙዎቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሚስቶች ጋር በተያያዘም ይሠራሉ።

^ አን.58 የሥዕሉ መግለጫ፦ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ወላጆች እያንዳንዱ ልጃቸው የኖኅን መርከብ ለመሥራት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እንደሚያደንቁ ሲያሳዩ።

^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ ትንሽ ልጇን ብቻዋን የምታሳድግ አንዲት እናት ረዳት አቅኚ ለመሆን ፕሮግራም ስታወጣ፤ ግቧ ላይ ለመድረስ በመቻሏ ተደስታለች።