በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የይሖዋ ምሥክሮች፣ ትዳር ፈላጊዎችን የሚያገናኙ ድረ ገጾችን ስለመጠቀም ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

ይሖዋ ትዳር የሚመሠርቱ ሰዎች ደስተኞች እንዲሆኑ እንዲሁም ዘላቂና ጠንካራ ወዳጅነት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። (ማቴ. 19:4-6) አንተም ማግባት የምትፈልግ ከሆነ ጥሩ የትዳር አጋር ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ሥርዓታማ በሆነ መልኩ ለመጠናናት እንዲሁም የተሳካ ትዳር ለመመሥረት ምን ማድረግ እንዳለብን ያውቃል። በመሆኑም እሱ የሰጠንን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ የምታውል ከሆነ እውነተኛ ደስታ ማግኘት ትችላለህ። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።

በመጀመሪያ፣ ራሳችንን በተመለከተ አንድ እውነታ መረዳት ያስፈልገናል፤ “ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም።” (ኤር. 17:9) ማግባት የሚፈልጉ ሁለት ሰዎች መጠናናት ሲጀምሩ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ስሜት ቶሎ እያደገ ሊሄድ ይችላል፤ ይህም ማስተዋል የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እንዳያደርጉ ሊያግዳቸው ይችላል። ሰዎች ትዳር ለመመሥረት የሚወስኑት በዋነኝነት በስሜት ተገፋፍተው ከሆነ ብዙውን ጊዜ ለሐዘን መዳረጋቸው አይቀርም። (ምሳሌ 28:26) የሚጠናኑ ሰዎች በደንብ ከመተዋወቃቸው በፊት ፍቅራቸውን መገላለጻቸው ወይም ቃል መገባባታቸው ጥበብ ያልሆነው ለዚህ ነው።

ምሳሌ 22:3 እንዲህ ይላል፦ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።” ትዳር ፈላጊዎችን የሚያገናኙ ድረ ገጾችን መጠቀም አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? ከማያውቁት ሰው ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት መጠናናት የጀመሩ አንዳንዶች፣ ግለሰቡ በስሜታቸው ላይ እንደተጫወተ ውሎ አድሮ ተገንዝበዋል፤ ይህ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! በተጨማሪም አንዳንድ አጭበርባሪዎች እነዚህ ድረ ገጾች ላይ የውሸት አካውንት በመክፈት፣ ያልጠረጠሩ ሰዎችን ገንዘብ አጭበርብረዋቸዋል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት የማጭበርበር ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር መስለው የቀረቡ ናቸው።

ሌላ አደጋም አለ። ትዳር ፈላጊዎችን የሚያገናኙ አንዳንድ ድረ ገጾች፣ የሚጣጣሙ ሰዎችን ለማገናኘት የሒሳብ ስሌቶችን ይጠቀማሉ። ሆኖም እንዲህ ያለው ዘዴ ስኬታማ ትዳር ለመመሥረት እንደሚያስችል የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። የኮምፒውተር ፕሮግራም ትዳርን የሚያክል ትልቅ ውሳኔ እንዲያደርግልን መምረጥ ጥበብ ይሆናል? የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ጨርሶ ሊወዳደሩ አይችሉም።—ምሳሌ 1:7፤ 3:5-7

ምሳሌ 14:15 “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” የሚል መሠረታዊ ሥርዓት ይዟል። አንድ ሰው ጥሩ የትዳር አጋር እንደሚሆናችሁ ከመወሰናችሁ በፊት ግለሰቡን በደንብ ማወቅ ይኖርባችኋል። ሆኖም በኢንተርኔት ብቻ እየተገናኙ ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ግለሰቡ ኢንተርኔት ላይ ያወጣውን መረጃ ስላያችሁ ወይም ኢንተርኔት ላይ ረጅም ሰዓት ስላወራችሁ ብቻ ግለሰቡን በደንብ አውቃችሁታል ማለት ይቻላል? የሚሆናቸውን ሰው እንዳገኙ የተሰማቸው አንዳንድ ሰዎች ግለሰቡን በአካል ሲያገኙት ባዩት ነገር በጣም ደንግጠዋል።

መዝሙራዊው “አታላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር አልቀራረብም፤ ማንነታቸውን ከሚደብቁም እርቃለሁ” ብሏል። (መዝ. 26:4) ብዙዎች፣ ትዳር ፈላጊዎችን በሚያገናኙ ድረ ገጾች ላይ ማራኪ ሆነው ለመታየት ሲሉ ስለ ራሳቸው የውሸት መረጃ ማስፈራቸው የተለመደ ነው። እውነተኛ ማንነታቸውን ሆን ብለው ሊደብቁ ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ በኢንተርኔት ሐሳብ በሚለዋወጡበት ወቅት መጥፎ ባሕርያቸው ግልጽ ሆኖ ላይታይ ይችላል። በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰባችን አስፈላጊ ነው፦ ግለሰቡ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ ቢናገርም በእርግጥ የተጠመቀ ክርስቲያን ነው? በመንፈሳዊ ጎልማሳ ነው? ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና አለው? በጉባኤው ውስጥ የሌሎችን አክብሮት ያተረፈ ነው? ወይስ ጥሩ ምሳሌ እንዳልሆነ ይባስ ብሎም ‘መጥፎ ጓደኛ’ እንደሆነ ተደርጎ የሚቆጠር ነው? (1 ቆሮ. 15:33፤ 2 ጢሞ. 2:20, 21) ከቅዱሳን መጻሕፍት አንጻር ለማግባት ነፃ ነው? እነዚህን ነገሮች ማወቃችሁ አስፈላጊ ነው። ሆኖም ግለሰቡን በደንብ የሚያውቁ የይሖዋ ምሥክሮች ካልረዷችሁ በቀር የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቅ ከባድ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 15:22) በተጨማሪም ታማኝ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ከማያምን ሰው ጋር “አቻ ባልሆነ መንገድ” ለመጠመድ ማሰብ እንኳ እንደሌለባቸው ግልጽ ነው።—2 ቆሮ. 6:14፤ 1 ቆሮ. 7:39

ትዳር ፈላጊዎችን የሚያገናኙ ድረ ገጾችን መጠቀም ካሉት አደጋዎች አንጻር የትዳር አጋር ለመፈለግና ለመጠናናት እንዲሁም ክብር ያለው ትዳር ለመመሥረት ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀም የተሻለ ነው። ታዲያ የትዳር አጋር ሊሆናችሁ የሚችል ሰው ማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው? አንድ ላይ መሰብሰብ በማይከለከልባቸው ሁኔታዎች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንዲሁም በሌሎች ወቅቶች ከተለያዩ ሰዎች ጋር በአካል ተገናኝተው የመተዋወቅ አጋጣሚ ያገኛሉ።

አብራችሁ ጊዜ ስታሳልፉ ግቦቻችሁና እሴቶቻችሁ ተመሳሳይ መሆናቸውን በግልጽ ማየት ትችላላችሁ

አንድ ላይ መሰብሰብ በማይፈቀድበት ጊዜ፣ ለምሳሌ ያህል በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የጉባኤ ስብሰባዎችን ለማድረግ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን እንጠቀማለን፤ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ከሌሎች ያላገቡ ክርስቲያኖች ጋር በደንብ ለመተዋወቅ የሚያስችል አጋጣሚ ማግኘት ይቻላል። በስብሰባዎች ላይ ክፍል ሲያቀርቡ እንዲሁም ሐሳብ በሚሰጡበት ወቅት እምነታቸውን ሲገልጹ መስማት ይቻላል። (1 ጢሞ. 6:11, 12) በተጨማሪም ከስብሰባው በኋላ ብሬክአውት ሩም ውስጥ ማውራት ትችላላችሁ። ከዚህም ሌላ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ላይ ለመጨዋወት በሚያደርጓቸው የቪዲዮ ኮንፈረንሶች ላይ ግለሰቡ ሌሎች ሰዎችን የሚይዝበትን መንገድ በደንብ ማየት ትችላላችሁ፤ ይህም የግለሰቡን እውነተኛ ማንነት ለማወቅ ይረዳችኋል። (1 ጴጥ. 3:4) በጊዜ ሂደት በደንብ እየተዋወቃችሁ ስትሄዱ ግቦቻችሁና እሴቶቻችሁ ተመሳሳይ መሆናቸውን እንዲሁም የምትጣጣሙ መሆናችሁን ማወቅ ትችላላችሁ።

ያላገቡ ክርስቲያኖች የትዳር አጋር ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ከሆነ የሚከተለው ምሳሌ ያለውን እውነተኝነት የማየታቸው አጋጣሚ ከፍ ያለ ይሆናል፦ “ጥሩ ሚስት ያገኘ [ባል ያገኘች] ጥሩ ነገር አግኝቷል [አግኝታለች]፤ የይሖዋንም ሞገስ ያገኛል [ታገኛለች]።”—ምሳሌ 18:22