በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 28

የፉክክር መንፈስ አታነሳሱ፤ ሰላም አስፍኑ

የፉክክር መንፈስ አታነሳሱ፤ ሰላም አስፍኑ

“በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።”—ገላ. 5:26

መዝሙር 101 በአንድነት አብሮ መሥራት

ማስተዋወቂያ *

1. የፉክክር መንፈስ ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል?

በዛሬው ጊዜ ራስ ወዳድነትና የፉክክር መንፈስ በብዙዎች ዘንድ ይታያል። ለምሳሌ፣ አንድ ነጋዴ ከተፎካካሪዎቹ ይበልጥ ትርፋማ ለመሆን ሲል ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ከማድረግ ላይመለስ ይችላል። አንድ ስፖርተኛ በውድድሩ ለማሸነፍ ሲል በተቃራኒው ቡድን ያለውን ተጫዋች ሆን ብሎ ይጎዳው ይሆናል። ወይም ደግሞ ታዋቂ ወደሆነ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት እየተወዳደረ ያለ ተማሪ የመግቢያውን ፈተና ለማለፍ ያጭበረብር ይሆናል። እኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉት ድርጊቶች ስህተት እንደሆኑና “የሥጋ ሥራዎች” ከተባሉት መካከል እንደሚመደቡ እናውቃለን። (ገላ. 5:19-21) ይሁንና አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ሳያውቁት በጉባኤው ውስጥ የፉክክር መንፈስ ሊያነሳሱ ይችሉ ይሆን? የፉክክር መንፈስ የወንድማማች ማኅበራችንን አንድነት ስለሚያናጋ ይህን ጥያቄ ልናስብበት ይገባል።

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 ከወንድሞቻችን ጋር እንድንፎካከር ሊያደርጉን የሚችሉት መጥፎ ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ለፉክክር መንፈስ እጅ ያልሰጡ ታማኝ ወንዶችንና ሴቶችን ምሳሌ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን ውስጣዊ ዝንባሌያችንን እንዴት መመርመር እንደምንችል እንመልከት።

ውስጣዊ ዝንባሌያችሁን መርምሩ

3. ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል?

3 ውስጣዊ ዝንባሌያችንን አልፎ አልፎ መመርመራችን አስፈላጊ ነው። ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ለራሴ ጥሩ ግምት የሚኖረኝ ከሌሎች የተሻልኩ እንደሆንኩ ሲሰማኝ ብቻ ነው? አንድን ሥራ ለማከናወን የሚያነሳሳኝ፣ ከሁሉም ሰው ሌላው ቢቀር ከአንድ ወንድም ወይም ከአንዲት እህት በልጬ ለመገኘት ያለኝ ፍላጎት ነው? ወይስ ጠንክሬ የምሠራው ለይሖዋ ምርጤን መስጠት ስለምፈልግ ነው?’ ራሳችንን እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው? የአምላክ ቃል ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል እንመልከት።

4. ገላትያ 6:3, 4 እንደሚለው ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር የሌለብን ለምንድን ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ከማወዳደር እንድንቆጠብ ያሳስበናል። (ገላትያ 6:3, 4ን አንብብ።) ለምን? ከወንድማችን የተሻልን እንደሆንን ከተሰማን ኩራት ሊያድርብን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ስናወዳድር እነሱ የተሻሉ እንደሆኑ ከተሰማን ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ሁለቱም ቢሆኑ “ጤናማ አስተሳሰብ” አይደሉም። (ሮም 12:3) ካታሪና * የተባለች በግሪክ የምትኖር እህት እንዲህ ብላለች፦ “ከእኔ ይበልጥ ቆንጆ፣ በአገልግሎት ውጤታማና ተግባቢ ከሆኑ እህቶች ጋር ራሴን አወዳድር ነበር። ይህም የከንቱነት ስሜት እንዲሰማኝ አደረገኝ።” ይሖዋ ወደ ራሱ የሳበን ቆንጆ፣ አንደበተ ርቱዕ ወይም በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ ስለሆንን እንዳልሆነ ልናስታውስ ይገባል፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የሳበን እሱን ለመውደድና ልጁን ለመስማት ፈቃደኛ መሆናችንን ስላየ ነው።—ዮሐ. 6:44፤ 1 ቆሮ. 1:26-31

5. ህዮን ከተባለው ወንድም ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

5 ራሳችንን ልንጠይቅ የምንችለው ሌላው ጥያቄ ደግሞ ይህ ነው፦ ‘በሌሎች ዘንድ የምታወቀው ሰላም ፈጣሪ በመሆኔ ነው? ወይስ ብዙ ጊዜ ከሌሎች ጋር እጋጫለሁ?’ በደቡብ ኮሪያ የሚኖርን ህዮን የተባለ ወንድም እንደ ምሳሌ እንመልከት። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ኃላፊነት ያላቸው አንዳንድ ወንድሞችን እንደ ተቀናቃኞቹ አድርጎ ይመለከታቸው ነበር። “እነዚህን ወንድሞች እተች እንዲሁም የሚሰጡትን ሐሳብ ብዙ ጊዜ እቃወም ነበር” ብሏል። ታዲያ ይህ ምን አስከተለ? ህዮን “እንዲህ ያለ አመለካከት መያዜ በጉባኤ ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር አደረገ” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ሆኖም አንዳንድ ጓደኞቹ ይህን ችግሩን እንዲያስተውል ረዱት። ህዮን አስፈላጊውን ማስተካከያ አደረገ፤ በአሁኑ ወቅት ጥሩ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው። ሰላም እንዲሰፍን ከማድረግ ይልቅ የፉክክር መንፈስ የማነሳሳት አዝማሚያ እንዳለን ካስተዋልን አፋጣኝ እርምጃ ልንወስድ ይገባል።

ከትምክህተኝነትና ከምቀኝነት ራቁ

6. በገላትያ 5:26 መሠረት የፉክክር መንፈስ እንድናዳብር ሊያደርጉን የሚችሉት መጥፎ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

6 ገላትያ 5:26ን አንብብ። ከሌሎች ጋር እንድንፎካከር ሊያደርጉን የሚችሉት መጥፎ ባህርያት የትኞቹ ናቸው? አንዱ ባሕርይ ትምክህተኝነት ነው። ትምክህተኛ የሆነ ሰው ኩሩና ራስ ወዳድ ነው። ሌላው መጥፎ ባሕርይ ደግሞ ምቀኝነት ነው። ምቀኛ የሆነ ሰው ሌሎች ያሏቸውን ነገሮች ከመመኘት ባለፈ ሰዎቹ እነዚያን ነገሮች እንዲያጡ ይፈልጋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ምቀኝነት የጥላቻ መገለጫ ነው። በእርግጥም እነዚህን መጥፎ ባሕርያት እንደ ተላላፊ በሽታ ልንርቃቸው ይገባል።

7. ትምክህተኝነትና ምቀኝነት የሚያስከትሉትን ጉዳት በምሳሌ አስረዳ።

7 ትምክህተኝነትና ምቀኝነት የአውሮፕላንን ነዳጅ ከሚበክሉ ባዕድ ነገሮች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። አውሮፕላኑ ከመሬት መነሳትና መብረር ይችል ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህ ባዕድ ነገሮች የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሮቹን ስለሚዘጓቸው ልክ ከማረፉ በፊት ሞተሩ መሥራት ሊያቆምና አውሮፕላኑ ሊከሰከስ ይችላል። በተመሳሳይም ትምክህተኛና ምቀኛ የሆነ ሰው ለተወሰነ ጊዜ ይሖዋን ማገልገል ይችል ይሆናል። ሆኖም ውሎ አድሮ ለጥፋት መዳረጉ አይቀርም። (ምሳሌ 16:18) ይሖዋን ማገልገሉን ያቆማል፤ እንዲሁም በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት ያስከትላል። ታዲያ ከትምክህተኝነትና ከምቀኝነት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

8. ትምክህተኝነትን ለማሸነፍ ምን ይረዳናል?

8 ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የሰጠውን የሚከተለውን ምክር በተግባር ማዋላችን ትምክህተኝነትን ለማሸነፍ ይረዳናል፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ።” (ፊልጵ. 2:3) ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ የምናስብ ከሆነ በተሰጥኦዋቸው ወይም በችሎታቸው ከሚበልጡን ሰዎች ጋር አንፎካከርም። ከዚህ ይልቅ አብረናቸው እንደሰታለን። በተለይ ደግሞ ችሎታቸውን የሚጠቀሙበት ይሖዋን ለማገልገልና ለማወደስ ከሆነ ልንደሰት ይገባል። ጥሩ ችሎታ ያላቸው ወንድሞችና እህቶችም በበኩላቸው የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ እኛ ባሉን መልካም ባሕርያት ላይ ያተኩራሉ። በዚህ መንገድ ሁላችንም ለጉባኤው ሰላምና አንድነት አስተዋጽኦ እናበረክታለን።

9. የምቀኝነትን ዝንባሌ ለማስወገድ ምን ሊረዳን ይችላል?

9 የምቀኝነትን ዝንባሌ ለማሸነፍ የሚረዳን ልክን ማወቅ ነው፤ ልካችንን የምናውቅ ከሆነ የማንችላቸው ነገሮች እንዳሉ እንገነዘባለን። በመሆኑም ከሌሎች የበለጠ ብቃትና ችሎታ እንዳለን ለማሳየት አንሞክርም። ከዚህ ይልቅ ከእኛ የበለጠ ችሎታ ካላቸው ሰዎች ለመማር እንጥራለን። ለምሳሌ በጉባኤያችን ያለ አንድ ወንድም ግሩም የሕዝብ ንግግር ያቀርባል እንበል። ንግግሩን የሚዘጋጀው እንዴት እንደሆነ ልንጠይቀው እንችላለን። ጣት የሚያስቆረጥም ምግብ የምትሠራ እህትን ደግሞ ሙያዋን እንድታጋራን ልንጠይቃት እንችላለን። ጓደኛ ለማፍራት የሚቸገር ወጣት ክርስቲያንም ተግባቢ የሆነን ወንድም ምክር መጠየቅ ይችላል። በዚህ መንገድ ምቀኝነትን ማስወገድና የራሳችንን ችሎታ ማሻሻል እንችላለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ምሳሌዎች ትምህርት ውሰዱ

ጌድዮን ትሑት ስለነበር ከኤፍሬማውያን ጋር ሰላም ፈጥሯል (ከአንቀጽ 10-12⁠ን ተመልከት)

10. ጌድዮን ምን ፈተና አጋጠመው?

10 ከምናሴ ነገድ በሆነው በጌድዮን እና በኤፍሬም ሰዎች መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጌድዮን እና ከእሱ ጋር የነበሩት 300 ሰዎች በይሖዋ እርዳታ ታላቅ ድል አግኝተው ነበር፤ በዚህም ሊኮሩ ይችሉ ነበር። የኤፍሬም ሰዎች ግን ጌድዮንን ከማመስገን ይልቅ ሊጣሉት መጡ። የኤፍሬም ሰዎች፣ ጌድዮን የአምላክን ጠላቶች ለመዋጋት ሲሄድ ስላልጠራቸው ክብራቸው እንደተነካ ተሰምቷቸው የነበረ ይመስላል። በዋነኝነት ያሳሰባቸው የነገዳቸውን ክብር ማስጠበቃቸው ነበር፤ በመሆኑም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ጌድዮን የይሖዋን ስም ማስከበሩና የአምላክን ሕዝብ ከጠላት እጅ መታደጉ እንደሆነ ሳያስተውሉ ቀሩ።—መሳ. 8:1

11. ጌድዮን ለኤፍሬም ሰዎች ምን ምላሽ ሰጣቸው?

11 ጌድዮን “እናንተ ካደረጋችሁት ጋር ሲነጻጸር እኔ ምን አደረግኩ?” በማለት ለኤፍሬም ሰዎች በትሕትና መለሰላቸው። ከዚያም አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወነውን ታላቅ ሥራ የሚያሳይ ምሳሌ ጠቀሰላቸው። በዚህ ጊዜ “ቁጣቸው በረደ።” (መሳ. 8:2, 3) ጌድዮን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሰላም ለማስፈን ሲል ትሕትና ለማሳየት ፈቃደኛ ነበር።

12. ከኤፍሬማውያን እና ከጌድዮን ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከኤፍሬማውያን እንደምንማረው ይበልጥ ሊያሳስበን የሚገባው የይሖዋ እንጂ የራሳችን ክብር አይደለም። የቤተሰብ ራሶችና ሽማግሌዎች ከጌድዮን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። አንድ ሰው ባደረግነው ነገር ከተበሳጨብን ጉዳዩን ከእሱ አመለካከት አንጻር ለማየት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በተጨማሪም ግለሰቡ ያከናወናቸውን መልካም ነገሮች ጠቅሰን ልናመሰግነው እንችላለን። እርግጥ ይህን ማድረግ ትሕትና ይጠይቅብናል፤ በተለይ ደግሞ ጥፋተኛው ግለሰቡ ከሆነ እሱን ማመስገን ቀላል አይሆንም። ሆኖም ከእኛ ክብር ይበልጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ከወንድሞቻችን ጋር ያለን ሰላም ነው።

ሐና ይሖዋ ነገሮችን እንደሚያስተካክል ስለተማመነች ሰላሟን መልሳ ማግኘት ችላለች (ከአንቀጽ 13-14⁠ን ተመልከት)

13. ሐና ምን ፈታኝ ሁኔታ አጋጠማት? ሁኔታውን የተወጣችውስ እንዴት ነው?

13 የሐናን ምሳሌም እንመልከት። ሐና፣ ሕልቃና የተባለ ሌዋዊ አግብታ ነበር፤ እሱም በጣም ይወዳት ነበር። ይሁንና ሕልቃና፣ ፍናና የተባለች ሌላም ሚስት ነበረችው። ሕልቃና ሐናን ከፍናና አስበልጦ ይወዳት ነበር፤ ሆኖም “ፍናና ልጆች ነበሯት፤ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም።” በዚህም የተነሳ ፍናና “[ሐናን] ለማበሳጨት ዘወትር ትሳለቅባት ነበር።” ታዲያ ሐና ምን ተሰማት? ሐና “እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ” ታዝን ነበር! (1 ሳሙ. 1:2, 6, 7) ያም ቢሆን ሐና፣ ፍናናን ለመበቀል ጥረት እንዳደረገች የሚገልጽ ዘገባ የለም። ይልቁንም ሐና የልቧን አውጥታ ለይሖዋ ነገረችው፤ እሱ ነገሮችን እንደሚያስተካክል በመተማመን ጉዳዩን ለእሱ ተወችው። ታዲያ ፍናና፣ ሐናን የምትይዝበት መንገድ ተለወጠ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ነገር የለም። ሆኖም ሐና ውስጣዊ ሰላሟን መልሳ እንዳገኘችና ሰላሟን ጠብቃ መኖር እንደቻለች እናውቃለን። “ዳግመኛም በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።”—1 ሳሙ. 1:10, 18

14. ከሐና ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 ከሐና ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንድ ሰው ከአንተ ጋር እየተፎካከረ እንደሆነ ብታስተውልስ? የምትሰጠውን ምላሽ የምትወስነው አንተ እንደሆንክ አስታውስ። አንተም መልሰህ መፎካከር አያስፈልግህም። ክፉን በክፉ ከመመለስ ይልቅ ከግለሰቡ ጋር ሰላም ለመፍጠር ጥረት አድርግ። (ሮም 12:17-21) ግለሰቡ ጥሩ ምላሽ ባይሰጥም እንኳ ውስጣዊ ሰላምህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ።

አጵሎስና ጳውሎስ ሥራቸውን የሚባርከው ይሖዋ እንደሆነ ስለተገነዘቡ አንዳቸው ሌላውን እንደ ተቀናቃኝ አልተመለከቱም (ከአንቀጽ 15-18⁠ን ተመልከት)

15. አጵሎስን እና ጳውሎስን የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?

15 በመጨረሻም ከደቀ መዝሙሩ አጵሎስ እና ከሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት። ሁለቱም የቅዱሳን መጻሕፍት ጥልቅ እውቀት ነበራቸው። ሁለቱም በብዙዎች ዘንድ የታወቁ ግሩም አስተማሪዎች ነበሩ። እንዲሁም ሁለቱም ብዙ ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ረድተዋል። ሆኖም አንዳቸው ሌላውን እንደ ተቀናቃኝ አልተመለከቱም።

16. አጵሎስ ምን ዓይነት ሰው ነበር?

16 አጵሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የትምህርት ማዕከል የነበረችው “የእስክንድርያ ተወላጅ” ነው። አጵሎስ አንደበተ ርቱዕ ከመሆኑም ሌላ “ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው” ነበር። (ሥራ 18:24) አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ወቅት አንዳንድ የጉባኤው አባላት ከጳውሎስና ከሌሎች ወንድሞች ይልቅ እሱ እንደሚበልጥባቸው በግልጽ አሳይተው ነበር። (1 ቆሮ. 1:12, 13) አጵሎስ ይህን የሚከፋፍል ሐሳብ ደግፏል? እንዲህ አድርጓል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። እንዲያውም አጵሎስ ከቆሮንቶስ ከሄደ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጳውሎስ ወደዚያ እንዲመለስ ለምኖታል። (1 ቆሮ. 16:12) ጳውሎስ፣ አጵሎስ ጉባኤውን እየከፋፈለ እንደሆነ ቢሰማው ኖሮ ይህን እንደማያደርግ የታወቀ ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አጵሎስ ስጦታውን የተጠቀመበት ለትክክለኛው ዓላማ ይኸውም ምሥራቹን ለማስፋፋትና ወንድሞቹን ለማበረታታት ነው። አጵሎስ ትሑት ሰው እንደነበርም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ለምሳሌ አቂላና ጵርስቅላ “የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል” ባብራሩለት ወቅት አጵሎስ ክብሩ እንደተነካ እንደተሰማው የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም።—ሥራ 18:24-28

17. ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው እንዴት ነው?

17 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አጵሎስ ጥሩ ሥራ እንዳከናወነ ያውቅ ነበር። ሆኖም እንደሚቀናቀነው አልተሰማውም። ጳውሎስ ትሑት፣ ልኩን የሚያውቅና ምክንያታዊ ሰው እንደነበር ለቆሮንቶስ ጉባኤ ከሰጠው ምክር መገንዘብ ይቻላል። አንዳንዶች “እኔ የጳውሎስ ነኝ” በማለታቸው ከመደሰት ይልቅ ክብር ሊሰጥ የሚገባው ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ተናግሯል።—1 ቆሮ. 3:3-6

18. በ1 ቆሮንቶስ 4:6, 7 መሠረት ከአጵሎስና ከጳውሎስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

18 ከአጵሎስና ከጳውሎስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? በይሖዋ አገልግሎት ብዙ ነገር እናከናውን እንዲሁም ብዙዎች እድገት አድርገው እንዲጠመቁ እንረዳ ይሆናል። ያም ቢሆን በሥራችን ስኬታማ መሆን የቻልነው ይሖዋ ስለባረከን ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን። ከአጵሎስና ከጳውሎስ ምሳሌ ሌላም ትምህርት እናገኛለን፤ በጉባኤ ውስጥ ያለን ኃላፊነት በጨመረ መጠን ሰላም ለማስፈን ማድረግ የምንችለው ነገርም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። የተሾሙ ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት ለማስፈን ጥረት ሲያደርጉ ደስ ይለናል፤ ይህን የሚያደርጉት የሚሰጡት ምክር በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ እንዲሁም በእነሱ ላይ ሳይሆን አርዓያችን በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ እንድናተኩር በመርዳት ነው።1 ቆሮንቶስ 4:6, 7ን አንብብ።

19. እያንዳንዳችን ምን ማድረግ እንችላለን? (“ የፉክክር መንፈስ አታነሳሱ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

19 ሁላችንም ከአምላክ ያገኘነው ተሰጥኦ ወይም ችሎታ አለን። ይህን ስጦታ አንዳችን “ሌላውን ለማገልገል” ልንጠቀምበት እንችላለን። (1 ጴጥ. 4:10) እርግጥ የምናበረክተው ድርሻ ትንሽ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ሆኖም ለአንድ ልብስ ጥንካሬ እያንዳንዱ ስፌት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሁሉ እያንዳንዳችን የምናከናውነው አነስተኛ ተግባርም ለአንድነታችን አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንግዲያው የፉክክር መንፈስን ከውስጣችን ነቅለን ለማውጣት ጥረት እናድርግ። በጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ኤፌ. 4:3

መዝሙር 80 “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም”

^ አን.5 የሸክላ ድስት ስንጥቅ ካለው በቀላሉ እንደሚሰበር ሁሉ በጉባኤ ውስጥም የፉክክር መንፈስ ካለ ጉባኤው ሊከፋፈል ይችላል። ጉባኤው ጠንካራ ካልሆነና አንድነት ከሌለው ይሖዋን ለማምለክ የሚያስችል ሰላማዊ ቦታ አይሆንም። ይህ ርዕስ፣ የፉክክር መንፈስ እንዳያድርብን ጥረት ማድረግ ያለብን ለምን እንደሆነ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ሰላም ለማስፈን ምን ማድረግ እንደምንችል ያብራራል።

^ አን.4 ስሞቹ ተቀይረዋል።