በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 26

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል ትችላለህ?

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል ትችላለህ?

“ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ኃይል እንድታገኙ [የሚያደርገው] አምላክ ነው።”—ፊልጵ. 2:13

መዝሙር 64 በመከሩ ሥራ በደስታ መካፈል

ማስተዋወቂያ *

1. ይሖዋ ምን አድርጎልሃል?

የይሖዋ ምሥክር የሆንከው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ‘ምሥራቹን’ ሰማህ፤ ምናልባትም የሰማኸው ከወላጆችህ፣ ከሥራ ባልደረባህ፣ አብሮህ ከሚማር ልጅ አሊያም ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት አማካኝነት ሊሆን ይችላል። (ማር. 13:10) ከዚያም አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን አስጠናህ፤ ይህን ለማድረግ ብዙ ጊዜና ጥረት ጠይቆበት ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ይሖዋን መውደድ ጀመርክ፤ እሱ እንደሚወድህም ተማርክ። በዚህ መንገድ ይሖዋ ወደ እውነት ስቦሃል፤ አሁን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ስለሆንክ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለህ። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ አንድን ሰው ተጠቅሞ እውነትን ስላስተማረህ እንዲሁም እንደ አገልጋዩ አድርጎ ስለተቀበለህ አመስጋኝ እንደሆንክ ምንም ጥያቄ የለውም።

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 እውነትን ስላወቅን ሌሎችም አብረውን በሕይወት መንገድ ላይ እንዲጓዙ የመርዳት መብት አግኝተናል። ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ብዙም አይከብደን ይሆናል፤ ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርና መምራት በጣም ከባድ ሊሆንብን ይችላል። አንተስ እንዲህ ይሰማሃል? ከሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት ሐሳቦች ሊጠቅሙህ ይችላሉ። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ለመካፈል የሚያነሳሳን ምን እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመምራት ወደኋላ እንድንል ሊያደርጉን የሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። በመጀመሪያ ግን የምሥራቹ ሰባኪዎች ብቻ ሳይሆን አስተማሪዎችም መሆን ያለብን ለምን እንደሆነ እንመልከት።

ኢየሱስ እንድንሰብክ እና እንድናስተምር አዞናል

3. የምንሰብከው ለምንድን ነው?

3 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ለተከታዮቹ ድርብ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። በመጀመሪያ የመንግሥቱን ምሥራች እንዲሰብኩ የነገራቸው ሲሆን ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳይቷቸዋል። (ማቴ. 10:7፤ ሉቃስ 8:1) ለምሳሌ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ምላሽ ሲሰጡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 9:2-5) ምሥራቹ ምን ያህል በስፋት እንደሚሰበክም ገልጾላቸዋል፤ ተከታዮቹ “ለብሔራት ሁሉ” ምሥክርነት እንደሚሰጡ ተናግሯል። (ማቴ. 24:14፤ ሥራ 1:8) ሰዎች ለስብከቱ ሥራ የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ አምላክ መንግሥትና መንግሥቱ ስለሚያከናውነው ነገር መስበክ ይጠበቅባቸው ነበር።

4. በማቴዎስ 28:18-20 መሠረት ስለ መንግሥቱ ከመስበክ በተጨማሪ ምን ማድረግ አለብን?

4 ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጠው ተልእኮ ሁለተኛ ክፍል ምንድን ነው? የእሱ ደቀ መዛሙርት ለሚሆኑ ሰዎች እሱ ያዘዘውን ነገር ሁሉ እንዲጠብቁ ማስተማር ነው። ይሁንና አንዳንዶች እንደሚናገሩት ኢየሱስ የስብከቱን እና የማስተማሩን ተልእኮ የሰጠው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች ብቻ ነበር? አልነበረም፤ ኢየሱስ ይህ ወሳኝ ሥራ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ” ማለትም አሁን እስከምንኖርበት ዘመን ድረስ እንደሚቀጥል አመልክቷል። (ማቴዎስ 28:18-20ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ተልእኮ የሰጠው ከ500 ለሚበልጡ ደቀ መዛሙርቱ በተገለጠበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። (1 ቆሮ. 15:6) በተጨማሪም ኢየሱስ ለዮሐንስ ባሳየው ራእይ ላይ ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ የመርዳት ኃላፊነት እንዳለባቸው በማያሻማ መንገድ ጠቁሟል።—ራእይ 22:17

5. በ1 ቆሮንቶስ 3:6-9 መሠረት ጳውሎስ በመስበክ እና በማስተማር መካከል ያለውን ግንኙነት በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

5 ሐዋርያው ጳውሎስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ እርሻ ከማልማት ጋር አመሳስሎታል፤ ይህም ዘር ከመዝራት ያለፈ ነገር መሥራት እንደሚጠበቅብን ያመለክታል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ አጠጣ፤ . . . እናንተ በመልማት ላይ ያለ የአምላክ እርሻ ናችሁ” ብሏቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:6-9ን አንብብ።) ‘በአምላክ እርሻ’ ውስጥ ስንሠራ ዘር መዝራት ብቻ ሳይሆን ውኃ ማጠጣትና አዘውትረን የተክሉን እድገት መከታተል ይኖርብናል። (ዮሐ. 4:35) ያም ቢሆን ዘሩን የሚያሳድገው አምላክ እንደሆነ አንዘነጋም።

6. የማስተማሩ ሥራችን ምን ማድረግን ይጨምራል?

6 ዓላማችን “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎችን ማግኘት ነው። (ሥራ 13:48) እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማሩትን ነገር (1) እንዲረዱ፣ (2) እንዲቀበሉ እና (3) በሥራ ላይ እንዲያውሉ ልንረዳቸው ይገባል። (ዮሐ. 17:3፤ ቆላ. 2:6, 7፤ 1 ተሰ. 2:13) ሁሉም ወንድሞችና እህቶች ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ፍቅር በማሳየትና በስብሰባ ላይ ሲገኙ እንግድነት እንዳይሰማቸው በማድረግ ጥናቶችን ሊረዷቸው ይችላሉ። (ዮሐ. 13:35) በተጨማሪም አስጠኚው፣ ጥናቱ እንደ “ምሽግ” ጠንካራ የሆኑ እምነቶችንና ልማዶችን እንዲደረምስ ለመርዳት ብዙ ጊዜና ጉልበት ሊጠይቅበት ይችላል። (2 ቆሮ. 10:4, 5) አንድ ሰው እነዚህን እርምጃዎች ወስዶ ወደ ጥምቀት ደረጃ እንዲደርስ ለመርዳት ረጅም ጊዜ ሊያስፈልግ ይችላል። ሆኖም የምናደርገው ጥረት የሚክስ ነው።

ፍቅር ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንድንካፈል ያነሳሳናል

7. በስብከቱ እና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንድንካፈል የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

7 በስብከቱ እና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የምንካፈለው ለምንድን ነው? የመጀመሪያው ምክንያት ይሖዋን ስለምንወደው ነው። እንድንሰብክ እና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ትእዛዝ ለማክበር አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ስታደርግ ለአምላክ ያለህን ፍቅር ታሳያለህ። (1 ዮሐ. 5:3) እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ አነሳስቶሃል። ይህን ትእዛዝ መታዘዝ ቀላል ነበር? ላይሆን ይችላል። ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ወጥተህ የመጀመሪያውን በር ስታንኳኳ ፈርተህ ነበር? መሆን አለበት። ሆኖም ኢየሱስ ይህን ሥራ እንድታከናውን እንደሚፈልግ ስላወቅክ ትእዛዙን አክብረሃል። ደግሞም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በስብከቱ ሥራ መካፈል እየቀለለህ እንደመጣ ጥያቄ የለውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራትን በተመለከተስ ምን ይሰማሃል? ስታስበው እንኳ ይጨንቅሃል? ሊሆን ይችላል። ሆኖም ፍርሃትህን ለማሸነፍ እንዲረዳህና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚያስችል ድፍረት እንዲሰጥህ ይሖዋን ከጠየቅከው እሱ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የመካፈል ፍላጎትህ እንዲያድግ ይረዳሃል።

8. በማርቆስ 6:34 መሠረት ሰዎችን ለማስተማር የሚያነሳሳን ሁለተኛው ምክንያት ምንድን ነው?

8 ሁለተኛ፣ ለሰዎች ያለን ፍቅር እውነትን እንድናስተምራቸው ያነሳሳናል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ለረጅም ሰዓት ሲሰብኩ ከቆዩ በኋላ በጣም ደክሟቸው ነበር። ስለዚህ ለማረፍ ወደ ሌላ ቦታ ሄዱ፤ ሆኖም እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተላቸው። ኢየሱስ ለሰዎቹ በጣም ስላዘነላቸው “ብዙ ነገር” ያስተምራቸው ጀመር። (ማርቆስ 6:34ን አንብብ።) ኢየሱስ ቢደክመውም ሰዎቹን አስተምሯቸዋል። ለምን? ኢየሱስ ራሱን በሰዎቹ ቦታ አስቀምጦ ነበር። እነዚህ ሰዎች ብዙ መከራ እንደደረሰባቸውና ተስፋ በጣም እንደሚያስፈልጋቸው ተመልክቶ ነበር፤ ስለዚህ ሊረዳቸው ፈልጓል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች የሚገኙበት ሁኔታም በኢየሱስ ዘመን ከነበሩት ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው። ከውጭ ሲታዩ ደስተኛ ቢመስሉም ብዙ ችግሮች አሉባቸው፤ እንዲሁም ተስፋ ያስፈልጋቸዋል። የሚመራቸው እረኛ እንደሌላቸው በጎች እየተቅበዘበዙ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያሉት ሰዎች “ያለተስፋና ያለአምላክ” እንደሆኑ ገልጿል። (ኤፌ. 2:12) ‘ወደ ጥፋት በሚወስደው መንገድ’ ላይ እየተጓዙ ነው። (ማቴ. 7:13) በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለሚገኙበት መንፈሳዊ ሁኔታ ማሰባችን እንድንወዳቸውና እንድናዝንላቸው ያደርገናል፤ ይህም እነሱን ለመርዳት ያነሳሳናል። እነሱን መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ መጋበዝ ነው።

9. በፊልጵስዩስ 2:13 መሠረት ይሖዋ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

9 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከማስጀመር ወደኋላ የምትለው ለጥናቱ መዘጋጀትና ጥናት መምራት ረጅም ጊዜ እንደሚጠይቅ ስለተገነዘብክ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ስሜትህን ለይሖዋ ንገረው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማግኘትና የመምራት ፍላጎት ለማዳበር እንዲረዳህ ጠይቀው። (ፊልጵስዩስ 2:13ን አንብብ።) አምላክ ከፈቃዱ ጋር የሚስማሙ ጸሎቶችን እንደሚመልስ ሐዋርያው ዮሐንስ አረጋግጦልናል። (1 ዮሐ. 5:14, 15) ስለዚህ ይሖዋ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የመካፈል ፍላጎት ለማዳበር እንደሚረዳህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣት

10-11. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመምራት ወደኋላ እንድንል የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል?

10 ሰዎችን እንድናስተምር የተሰጠንን ተልእኮ በቁም ነገር እንመለከተዋለን፤ ሆኖም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የምንፈልገውን ያህል እንዳንካፈል የሚያግዱን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ከእነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? ልንወጣቸው የምንችለውስ እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።

11 ያለንበት ሁኔታ እንደሚገድበን ይሰማን ይሆናል። ለምሳሌ አንዳንድ አስፋፊዎች ከዕድሜ መግፋት ወይም ከጤና ችግር ጋር ይታገላሉ። አንተም እንዲህ ዓይነት ችግር አጋጥሞሃል? ከሆነ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ያገኘነውን ትምህርት አስብ። በስልክ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት እንደሚቻል ተምረናል! ስለዚህ ከቤትህ ሳትወጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርና መምራት ትችል ይሆናል። በስልክ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት ጥናት መምራት ሌላ ጥቅምም አለው። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ቢፈልጉም አብዛኞቹ ወንድሞች አገልግሎት በሚወጡበት ሰዓት ማጥናት አይመቻቸው ይሆናል። ሆኖም ማለዳ ወይም ምሽት ላይ ማጥናት ይችሉ ይሆናል። ታዲያ በዚያ ሰዓት ጥናት መምራት ትችል ይሆን? ኢየሱስ ኒቆዲሞስን በሚመቸው ሰዓት ማለትም ማታ ላይ አስተምሮታል።—ዮሐ. 3:1, 2

12. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመምራት ብቃት እንዳለን እንድንተማመን የሚረዱን የትኞቹ ነጥቦች ናቸው?

12 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ብቃቱ እንደሌለን ይሰማን ይሆናል። ምናልባትም አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት በቂ እውቀትና ችሎታ እንደሌለን ሊሰማን ይችላል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ጥናት መምራት እንደምትችል እንድትተማመን የሚረዱ ሦስት ነጥቦችን እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ፣ ይሖዋ ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱ እንዳለህ አድርጎ ይመለከትሃል። (2 ቆሮ. 3:5) ሁለተኛ፣ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” የተሰጠው ኢየሱስ እንድታስተምር አዞሃል፤ ይህም እንደሚተማመንብህ ያሳያል። (ማቴ. 28:18) ሦስተኛ፣ ይሖዋ እና ወንድሞችህ ይረዱሃል። ይሖዋ ለኢየሱስ ምን መናገር እንዳለበት አስተምሮታል፤ አንተንም ሊያስተምርህ ይችላል። (ዮሐ. 8:28፤ 12:49) ከዚህም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርና ለመምራት እንዲረዳህ የመስክ አገልግሎት ቡድንህን የበላይ ተመልካች፣ ጥሩ ችሎታ ያለውን አንድ አቅኚ ወይም ተሞክሮ ያለውን አስፋፊ መጠየቅ ትችላለህ። ጥሩ አስተማሪ ለመሆን የሚረዳህ አንዱ ነገር እነዚህ አስፋፊዎች ጥናት ሲመሩ አብረሃቸው መገኘት ነው።

13. አዳዲስ ዘዴዎችን ለመልመድ ፈቃደኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

13 አዳዲስ ዘዴዎችንና መሣሪያዎችን መልመድ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የምንመራበት መንገድ ተቀይሯል። ሰዎችን ለማስጠናት በዋነኝነት የምንጠቀመው ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ጽሑፍ በመሆኑ ለጥናቱ የምንዘጋጅበት እንዲሁም ጥናቱን የምንመራበት መንገድ ከቀድሞው የተለየ ነው። የምናነባቸው አንቀጾች ጥቂት ብቻ ናቸው፤ በዋነኝነት የምናተኩረው ከጥናቱ ጋር በመወያየት ላይ ነው። በምናስጠናበት ጊዜ ብዙ ቪዲዮዎችን እንዲሁም ድረ ገጻችን እና JW Library® ላይ የሚገኙ ሌሎች መሣሪያዎችን እንጠቀማለን። እነዚህን መሣሪያዎች መጠቀም ከከበደህ አንድ የእምነት ባልንጀራህ አጠቃቀሙን እንዲያሳይህ ጠይቅ። ሰዎች ስንባል ነገሮችን በለመድነው መንገድ ማከናወን ይቀናናል። አዲስ ዘዴ መልመድ ይከብደናል። ሆኖም ይሖዋና ወንድሞችህ ስለሚረዱህ አዲሶቹን ዘዴዎች መልመድ ትችላለህ፤ በዚህ መንገድ ሰዎችን ማስጠናትም ይበልጥ አስደሳች ይሆንልሃል። አንድ አቅኚ እንደገለጸው ይህ የማስጠኛ ዘዴ “ለተማሪውም ሆነ ለአስተማሪው በጣም አስደሳች ነው።”

14. ጥናቶች ማግኘት ከባድ በሆነበት ክልል ውስጥ ስናገለግል ምን ማስታወስ ይኖርብናል? አንደኛ ቆሮንቶስ 3:6, 7 የሚያበረታታንስ እንዴት ነው?

14 የምናገለግለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ከባድ በሆነበት ክልል ሊሆን ይችላል። ሰዎች ለመልእክታችን ግድየለሾች ይሆኑ አልፎ ተርፎም ይቃወሙን ይሆናል። በእንዲህ ዓይነት ክልል ውስጥ ስናገለግል አዎንታዊ ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል? በዚህ ተነዋዋጭ ዓለም ውስጥ የሰዎች ሁኔታ በቅጽበት ሊቀየር እንደሚችል አስታውስ፤ ቀደም ሲል ለመልእክታችን ፍላጎት ያልነበራቸው ሰዎችም መንፈሳዊ ፍላጎት ሊያዳብሩ ይችላሉ። (ማቴ. 5:3) ቀደም ሲል ጽሑፎቻችንን ለመቀበል ጨርሶ ፈቃደኛ ያልነበሩ ሰዎች በኋላ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ፈቃደኛ ሆነዋል። በተጨማሪም የመከሩ ሥራ ኃላፊ ይሖዋ እንደሆነ እናውቃለን። (ማቴ. 9:38) ይሖዋ መትከላችንን እና ውኃ ማጠጣታችንን እንድንቀጥል ይፈልጋል፤ ሆኖም የሚያሳድገው እሱ ነው። (1 ቆሮ. 3:6, 7) ከዚህም ሌላ በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ባይኖረንም እንኳ ይሖዋ ወሮታችንን የሚከፍለን በጥረታችን ላይ እንጂ ባገኘነው ውጤት ላይ ተመሥርቶ አለመሆኑን ማወቃችን በጣም ያበረታታናል! *

ደቀ መዛሙርት ማድረግ የሚያስገኘውን ደስታ አጣጥም

የስብከቱ እና የማስተማሩ ሥራችን የአንድን ሰው ሕይወት የሚለውጠው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 15-17⁠ን ተመልከት) *

15. አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና እንዲሁም የተማረውን ነገር በሥራ ላይ ሲያውል ይሖዋ ምን ይሰማዋል?

15 አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲቀበልና ይህን እውነት ለሌሎች ሲያካፍል ይሖዋ በጣም ይደሰታል። (ምሳሌ 23:15, 16) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚከናወነውን ሥራ ሲያይ ምንኛ ይደሰት ይሆን! ለምሳሌ ያህል በ2020 የአገልግሎት ዓመት ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ የነበረ ቢሆንም እንኳ 7,705,765 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተመርተዋል፤ ይህም 241,994 ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው እንዲጠመቁ አስችሏል። እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትም በበኩላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት ተጨማሪ ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ያደርጋሉ። (ሉቃስ 6:40) በእርግጥም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስንካፈል ይሖዋን እናስደስተዋለን።

16. ምን ግብ ማውጣት እንችላለን?

16 ደቀ መዛሙርት ማድረግ ጥረት ይጠይቃል፤ ሆኖም ይሖዋ ስለሚረዳን አዲሶች የሰማዩን አባታችንን እንዲወዱ በማስተማሩ ሥራ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። ቢያንስ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርና ለመምራት ግብ ማውጣት እንችል ይሆን? አመቺ አጋጣሚዎችን ሁሉ ተጠቅመን ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ብንጋብዝ አስገራሚ ውጤት እናገኝ ይሆናል። ይሖዋ ጥረታችንን እንደሚባርክልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

17. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ምን ያስገኝልናል?

17 ለሌሎች እውነትን መስበክ እና ማስተማር እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው! ይህ ሥራ እውነተኛ ደስታ ያስገኝልናል። በተሰሎንቄ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ የረዳው ሐዋርያው ጳውሎስ ስሜቱን በዚህ መንገድ ገልጾታል፦ “ጌታችን ኢየሱስ በሚገኝበት ጊዜ በእሱ ፊት ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም የሐሴታችን አክሊል ምንድን ነው? እናንተ አይደላችሁም? በእርግጥም እናንተ ክብራችንና ደስታችን ናችሁ።” (1 ተሰ. 2:19, 20፤ ሥራ 17:1-4) በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙዎችም እንዲህ ተሰምቷቸዋል። ስቴፋኒ እና ባለቤቷ በርካታ ሰዎች እንዲጠመቁ ረድተዋል፤ ስቴፋኒ እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ ከመርዳት የበለጠ ደስታ የሚያስገኝ ምንም ነገር የለም።”

መዝሙር 57 ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መስበክ

^ አን.5 ይሖዋ ለሌሎች የመስበክ ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ ያዘዘውን ነገር በሙሉ እንዲጠብቁ የማስተማር መብትም ሰጥቶናል። ሌሎችን ለማስተማር የሚያነሳሳን ምንድን ነው? በስብከቱ እና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስንካፈል የትኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል? እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት የምንችለውስ እንዴት ነው? ይህ ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

^ አን.14 ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ሁላችንም አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በመጋቢት 2021 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት አድርገው እንዲጠመቁ በጉባኤ ደረጃ መርዳት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.53 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ ሕይወቱን እንዴት እንደሚለውጠው እንመልከት፦ መጀመሪያ ላይ ሰውየው ሕይወቱ ዓላማ እንደሌለው ተሰምቶታል፤ ይሖዋንም አያውቅም። ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮች ሲሰብኩ አገኙት፤ እሱም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። የተማረው ነገር ራሱን እንዲወስንና እንዲጠመቅ አነሳሳው። ከጊዜ በኋላ እሱም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል ጀመረ። በመጨረሻ ሁሉም በገነት ውስጥ በደስታ እየኖሩ ነው።