በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 31

የጸሎት መብታችሁን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱት

የጸሎት መብታችሁን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱት

“ጸሎቴ በአንተ ፊት እንደተዘጋጀ ዕጣን ይሁን።”—መዝ. 141:2

መዝሙር 47 በየዕለቱ ወደ ይሖዋ መጸለይ

ማስተዋወቂያ *

1. ወደ ይሖዋ የመጸለይ መብታችንን እንዴት ልንመለከተው ይገባል?

 የሰማይና የምድር ፈጣሪ ወደሆነው አምላክ በጸሎት የመቅረብ አስደናቂ መብት አግኝተናል። ቀጠሮ መያዝ ሳያስፈልገን በማንኛውም ሰዓት፣ ማንኛውንም ቋንቋ ተጠቅመን ልባችንን ለይሖዋ ማፍሰስ እንችላለን። የሆስፒታል አልጋ ላይም እንሁን እስር ቤት ውስጥ፣ የሚወደን አባታችን እንደሚሰማን ተማምነን ወደ እሱ መጸለይ እንችላለን። ይህን መብት በፍጹም አቅልለን አንመለከተውም።

2. ንጉሥ ዳዊት የጸሎት መብቱን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ያሳየው እንዴት ነው?

2 ንጉሥ ዳዊት የጸሎት መብቱን ከፍ አድርጎ ይመለከተው ነበር። “ጸሎቴ በአንተ ፊት እንደተዘጋጀ ዕጣን ይሁን” በማለት ለይሖዋ ዘምሯል። (መዝ. 141:1, 2) በዳዊት ዘመን ካህናቱ ለእውነተኛው አምልኮ የሚጠቀሙበት ቅዱስ ዕጣን የሚዘጋጀው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነበር። (ዘፀ. 30:34, 35) ዳዊት ስለ ዕጣን መጥቀሱ ወደ ሰማዩ አባቱ ሲጸልይ ምን እንደሚል አስቀድሞ በጥንቃቄ እንደሚያስብበት ያመለክታል። የእኛም ልባዊ ፍላጎት ይኸው ነው። ጸሎታችን ይሖዋን የሚያስደስት እንዲሆን እንፈልጋለን።

3. በጸሎት ወደ ይሖዋ ስንቀርብ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል? ለምንስ?

3 ወደ ይሖዋ ስንጸልይ አክብሮት በጎደለው መንገድ እንዳንናገር መጠንቀቅ ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ወደ ይሖዋ የምንቀርበው በጥልቅ አክብሮት ሊሆን ይገባል። እስቲ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤልና ዮሐንስ ያዩአቸውን አስደናቂ ራእዮች ለማሰብ ሞክሩ። እነዚህ ራእዮች የተለያዩ ቢሆኑም የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ። በሁሉም ራእዮች ላይ ይሖዋ የተገለጸው ግርማ ሞገስ የተላበሰ ንጉሥ ተደርጎ ነው። ኢሳይያስ፣ ይሖዋ “በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ” ተመልክቷል። (ኢሳ. 6:1-3) ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ ‘እንደ ቀስተ ደመና ባለ ደማቅ ብርሃን ተከቦ’ በሰማያዊ ሠረገላው ላይ ተቀምጦ አይቷል። (ሕዝ. 1:26-28) ዳንኤል “ከዘመናት በፊት የነበረው” ነጭ ልብስ እንደለበሰና ከዙፋኑ የእሳት ነበልባል ይወጣ እንደነበር ተመልክቷል። (ዳን. 7:9, 10) ዮሐንስ ደግሞ ይሖዋ መረግድ በሚመስል ውብ ቀስተ ደመና በተከበበ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ተመልክቷል። (ራእይ 4:2-4) ወደር በሌለው የይሖዋ ክብር ላይ ስናሰላስል ወደ እሱ በጸሎት መቅረብ አስደናቂ መብት እንደሆነ እናስታውሳለን፤ እንዲሁም ወደ እሱ ስንጸልይ ጥልቅ አክብሮት ሊኖረን እንደሚገባ እንገነዘባለን። ይሁንና መጸለይ ያለብን እንዴት ነው?

“እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ”

4. በጸሎት ናሙናው ውስጥ ካሉት የመጀመሪያ ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? (ማቴዎስ 6:9, 10)

4 ማቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ደቀ መዛሙርቱ አምላክን በሚያስደስት መንገድ መጸለይ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አስተምሯቸዋል። ኢየሱስ “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ” ካለ በኋላ መጀመሪያ የጠቀሰው ከይሖዋ ዓላማ ጋር በቀጥታ የተያያዙ አስፈላጊ ጉዳዮችን ነው። እነሱም የስሙ መቀደስ፣ የአምላክን ተቃዋሚዎች በሙሉ የሚያጠፋው የመንግሥቱ መምጣት እንዲሁም አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ለማምጣት ያሰባቸው በረከቶች ናቸው። እነዚህን ጉዳዮች በጸሎታችን ውስጥ ማካተታችን ለአምላክ ፈቃድ ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ ያሳያል።

5. ስለ ግል ጉዳዮቻችን መጸለይ ተገቢ ነው?

5 በጸሎት ናሙናው ቀጣይ ክፍል ላይ ኢየሱስ ስለ ግል ጉዳዮቻችን መጸለይ ተገቢ እንደሆነ አስተምሯል። ይሖዋ የዕለቱን ምግባችንን እንዲሰጠን፣ በደላችንን ይቅር እንዲለን፣ ከፈተና እንዲጠብቀን እንዲሁም ከክፉው እንዲያድነን መጠየቅ እንችላለን። (ማቴ. 6:11-13) እነዚህን ነገሮች በተመለከተ ይሖዋን ስንጠይቀው የእሱ እርዳታ እንደሚያስፈልገን አምነን መቀበላችንን እንዲሁም የእሱን ሞገስ ማግኘት እንደምንፈልግ እናሳያለን።

አንድ ባል ከሚስቱ ጋር ሲጸልይ የትኞቹን ነገሮች መጥቀስ ይችላል? (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት) *

6. መጸለይ የምንችለው በጸሎት ናሙናው ውስጥ ስለተጠቀሱት ጉዳዮች ብቻ ነው? አብራራ።

6 ኢየሱስ ተከታዮቹ የጸሎት ናሙናውን ቃል በቃል እንዲደግሙ አልጠበቀባቸውም። ኢየሱስ በሌሎች ጊዜያት ባቀረባቸው ጸሎቶች ላይ በወቅቱ ያሳሰቡትን ሌሎች ጉዳዮች ጠቅሷል። (ማቴ. 26:39, 42፤ ዮሐ. 17:1-26) እኛም በተመሳሳይ ስለሚያሳስበን ስለ ማንኛውም ጉዳይ መጸለይ እንችላለን። ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገን ጥበብና ማስተዋል ለማግኘት መጸለይ እንችላለን። (መዝ. 119:33, 34) ከባድ ኃላፊነት ሲሰጠን ጥልቅ ግንዛቤ ለማግኘት መጸለይ እንችላለን። (ምሳሌ 2:6) ወላጆች ስለ ልጆቻቸው፣ ልጆች ደግሞ ስለ ወላጆቻቸው መጸለይ ይችላሉ። በተጨማሪም ሁላችንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንና ስለምንሰብክላቸው ሰዎች መጸለይ እንችላለን፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። እርግጥ በጸሎታችን ውስጥ መካተት ያለበት ልመና ብቻ አይደለም።

በጸሎታችን ላይ ይሖዋን ስለ የትኞቹ ነገሮች ልናወድሰውና ልናመሰግነው እንችላለን? (ከአንቀጽ 7-9⁠ን ተመልከት) *

7. በምንጸልይበት ወቅት ይሖዋን ማወደስ ያለብን ለምንድን ነው?

7 በጸሎታችን ላይ አስታውሰን ይሖዋን ማወደስ ይኖርብናል። የአምላካችንን ያህል ውዳሴ የሚገባው ማንም የለም። እሱ ‘ጥሩ ነው፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነው።’ በተጨማሪም ‘መሐሪና ሩኅሩኅ፣ ለቁጣ የዘገየ እንዲሁም ታማኝ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ አምላክ ነው።’ (መዝ. 86:5, 15) በእርግጥም ይሖዋን ስለ ባሕርያቱና ስለ ሥራዎቹ ለማወደስ የሚያነሳሱን ብዙ ምክንያቶች አሉን።

8. ይሖዋን ስለ የትኞቹ ነገሮች ማመስገን እንችላለን? (መዝሙር 104:12-15, 24)

8 በምንጸልይበት ወቅት ይሖዋን ከማወደስ በተጨማሪ ለሰጠን ግሩም ነገሮች እሱን ለማመስገንም እንነሳሳለን። ለምሳሌ በቀለማት ላሸበረቁት አበቦች፣ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ጣፋጭ ምግቦች እንዲሁም ከጓደኞቻችን ጋር ጊዜ በማሳለፍ ለምናገኘው ደስታ ልናመሰግነው እንችላለን። የሚወደን አባታችን እነዚህንና ሌሎችም ነገሮችን የሰጠን ደስተኛ እንድንሆን ስለሚፈልግ ነው። (መዝሙር 104:12-15, 24ን አንብብ።) ከዚህ ይበልጥ ደግሞ ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ስለሚያቀርብልን እንዲሁም ለወደፊቱ ጊዜ አስደናቂ ተስፋ ስለሰጠን ልናመሰግነው ይገባል።

9. አስታውሰን ይሖዋን ለማመስገን ምን ሊረዳን ይችላል? (1 ተሰሎንቄ 5:17, 18)

9 ይሖዋ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ቢያደርግልንም እሱን ማመስገን ልንረሳ እንችላለን። ታዲያ ለማስታወስ ምን ሊረዳን ይችላል? በጸሎት የጠየቅናቸውን የተለያዩ ነገሮች ዘርዝረን ከጻፍን በኋላ ይሖዋ እንዴት እንደመለሰልን ለማየት አልፎ አልፎ ዝርዝሩን መመልከት እንችላለን። ከዚያም ላደረገልን ነገር ይሖዋን በጸሎት እናመስግነው። (1 ተሰሎንቄ 5:17, 18ን አንብብ።) እስቲ አስቡት፦ ሌሎች ላደረግንላቸው ነገር ሲያመሰግኑን ደስ ይለናል። በተመሳሳይም ይሖዋ ጸሎታችንን ስለመለሰልን አስታውሰን ስናመሰግነው ልቡ ይደሰታል። (ቆላ. 3:15) ይሁንና አምላካችንን ለማመስገን የሚያነሳሳን ሌላው ወሳኝ ምክንያት ምንድን ነው?

ውድ ልጁን ስለላከልን ይሖዋን አመስግኑት

10. በ1 ጴጥሮስ 2:21 መሠረት ይሖዋ ኢየሱስን ወደ ምድር ስለላከልን ልናመሰግነው የሚገባው ለምንድን ነው?

10 አንደኛ ጴጥሮስ 2:21ን አንብብ። ይሖዋ ውድ ልጁን እንዲያስተምረን ስለላከልን ልናመሰግነው ይገባል። የኢየሱስን ሕይወት በመመርመር ስለ ይሖዋ እንዲሁም እሱን ማስደሰት ስለምንችልበት መንገድ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። በክርስቶስ መሥዋዕት ካመንን ከይሖዋ አምላክ ጋር በግለሰብ ደረጃ የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንዲሁም ከእሱ ጋር ያለንን ሰላም ጠብቀን መኖር እንችላለን።—ሮም 5:1

11. ወደ ይሖዋ ከምናቀርበው ጸሎት ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ምን ሚና ይጫወታል?

11 በልጁ አማካኝነት ወደ እሱ በጸሎት የመቅረብ መብት ስላገኘን ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን በኢየሱስ አማካኝነት ነው። ይሖዋ በኢየሱስ ስም የቀረቡ ጸሎቶችን ይሰማል እንዲሁም ይመልሳል። ኢየሱስ “አብ በወልድ አማካኝነት እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ” ብሏል።—ዮሐ. 14:13, 14

12. ይሖዋ ልጁን ስለሰጠን የምናመሰግንበት ሌላው ምክንያት ምንድን ነው?

12 ይሖዋ የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት በማድረግ ኃጢአታችንን ይቅር ይልልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “በሰማያት በግርማዊው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ . . . ሊቀ ካህናት” በማለት ይጠራዋል። (ዕብ. 8:1) ኢየሱስ ‘በአብ ዘንድ ያለን ረዳት’ ነው። (1 ዮሐ. 2:1) ይሖዋ ድክመታችንን የሚረዳልንና ‘ስለ እኛ የሚማልድ’ አዛኝ ሊቀ ካህናት ስለሰጠን በጣም እናመሰግነዋለን። (ሮም 8:34፤ ዕብ. 4:15) ፍጹማን እንዳለመሆናችን መጠን የኢየሱስ መሥዋዕት ባይኖር ኖሮ ወደ ይሖዋ በጸሎት መቅረብ አንችልም ነበር። በእርግጥም ይሖዋ ይህን ልዩ ስጦታ ማለትም ውድ ልጁን ስለሰጠን አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል!

ለወንድሞቻችሁና ለእህቶቻችሁ ጸልዩላቸው

13. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚወዳቸው ያሳየው እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ረጅም ጸሎት አቅርቧል፤ ‘ከክፉው እንዲጠብቃቸው’ አባቱን ለምኖታል። (ዮሐ. 17:15) ይህ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ ነው። ኢየሱስ እሱ ራሱ ከፍተኛ መከራ ከፊቱ የሚጠብቀው ቢሆንም ስለ ሐዋርያቱ ደህንነት ተጨንቋል።

ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በተያያዘ ስለ የትኞቹ ነገሮች መጸለይ እንችላለን? (ከአንቀጽ 14-16⁠ን ተመልከት) *

14. ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንደምንወዳቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በራሳችን ፍላጎት ላይ ብቻ ከማተኮር እንቆጠባለን። ከዚህ ይልቅ ስለ ወንድሞቻችንና ስለ እህቶቻችን አዘውትረን እንጸልያለን። እንዲህ ስናደርግ ኢየሱስ እርስ በርስ እንድንዋደድ የሰጠንን ትእዛዝ እንፈጽማለን። እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቻችንን ምን ያህል እንደምንወዳቸው ለይሖዋ እናሳየዋለን። (ዮሐ. 13:34) ስለ ወንድሞቻችንና ስለ እህቶቻችን መጸለያችን ለውጥ ያመጣል። የአምላክ ቃል “ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው” ይላል።—ያዕ. 5:16

15. የእምነት ባልንጀሮቻችን የእኛ ጸሎት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

15 የእምነት ባልንጀሮቻችን ብዙ ፈተናዎች ስለሚያጋጥሟቸው የእኛ ጸሎት ያስፈልጋቸዋል። ሕመምን፣ የተፈጥሮ አደጋን፣ የእርስ በርስ ጦርነትን፣ ስደትን ወይም ሌሎች ፈተናዎችን ለመቋቋም እንዲረዳቸው ይሖዋን ልንጠይቀው እንችላለን። በተጨማሪም የተቸገሩትን ለመርዳት ሲሉ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ለሚያደርጉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጸለይ እንችላለን። እንዲህ ዓይነት ፈተና ያጋጠማቸውን ወንድሞችና እህቶች በግል ታውቁ ይሆናል። ታዲያ ለምን ስማቸውን ጠቅሳችሁ አትጸልዩላቸውም? ይሖዋ መጽናት እንዲችሉ እንዲረዳቸው በመጸለይ እውነተኛ የወንድማማች ፍቅር እንዳለን እናሳያለን።

16. በመካከላችን ሆነው አመራር ለሚሰጡ ወንድሞች መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

16 በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡ ወንዶች ስንጸልይላቸው ደስ ይላቸዋል፤ ደግሞም ጸሎታችን በእጅጉ ይጠቅማቸዋል። ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በተያያዘ ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የምሥራቹን ቅዱስ ሚስጥር በድፍረት ለሌሎች ማሳወቅ እንድችል አፌን በምከፍትበት ጊዜ የምናገረው ቃል እንዲሰጠኝ ለእኔም ጸልዩልኝ።” (ኤፌ. 6:19) በዛሬው ጊዜም በመካከላችን ሆነው አመራር የሚሰጡ በርካታ ትጉ ወንድሞች አሉ። ይሖዋ ሥራቸውን እንዲባርክላቸው በመጸለይ ለእነሱ ያለንን ፍቅር እናሳያለን።

ሌሎችን ወክላችሁ ስትጸልዩ

17-18. ሌሎችን ወክለን እንድንጸልይ የምንጋበዘው መቼ ሊሆን ይችላል? የትኞቹን ነገሮችስ ማስታወስ ይኖርብናል?

17 አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን ወክለን እንድንጸልይ እንጋበዝ ይሆናል። ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምትመራ አንዲት እህት ጥናቱ ላይ የተገኘችን ሌላ እህት እንድትጸልይ ትጋብዛት ይሆናል። ጥናት የተጋበዘችው እህት ስለ ተማሪዋ ብዙም ላታውቅ ስለምትችል በጥናቱ መደምደሚያ ላይ ለመጸለይ ትመርጥ ይሆናል። እንዲህ ማድረጓ የተማሪዋን ሁኔታ ከግምት ያስገባ ጸሎት ለማቅረብ ያስችላታል።

18 አንድ ወንድም በመስክ ስምሪት ስብሰባ ወይም በጉባኤ ስብሰባ ላይ እንዲጸልይ ይጋበዝ ይሆናል። እንዲህ ያለ መብት ያገኙ ወንድሞች የስብሰባውን ዓላማ ሊዘነጉ አይገባም። በተጨማሪም ጉባኤውን ለመምከር ወይም ማስታወቂያ ለመናገር ጸሎትን መጠቀም ተገቢ አይደለም። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አብዛኛውን ጊዜ ለመዝሙርና ለጸሎት የሚመደበው በድምሩ አምስት ደቂቃ ነው። በመሆኑም ጸሎት የሚያቀርቡ ወንድሞች በተለይም በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ‘ቃላት ማብዛት’ የለባቸውም።—ማቴ. 6:7

በሕይወታችሁ ውስጥ ለጸሎት ትልቅ ቦታ ስጡ

19. ለይሖዋ የፍርድ ቀን ለመዘጋጀት ምን ይረዳናል?

19 ወደ ይሖዋ የፍርድ ቀን እየተቃረብን ስንሄድ በተለይ ለጸሎት ትልቅ ቦታ መስጠታችን አስፈላጊ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲያው መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማምለጥ . . . እንድትችሉ ሁልጊዜ ምልጃ እያቀረባችሁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።” (ሉቃስ 21:36) አዎ፣ አዘውትረን መጸለያችን የአምላክ ቀን ሳንዘጋጅ እንዳይደርስብን በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንድንጠብቅ ይረዳናል።

20. ጸሎታችን ጣፋጭ መዓዛ እንዳለው ዕጣን ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

20 እስካሁን ምን ተምረናል? የጸሎት መብታችንን እጅግ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። በዋነኝነት መጸለይ ያለብን ከይሖዋ ዓላማ ጋር በቀጥታ ስለተያያዙ ጉዳዮች ነው። በተጨማሪም ይሖዋን ስለ ውድ ልጁና ስለ መንግሥቱ እናመሰግነዋለን። ስለ እምነት ባልንጀሮቻችንም እንጸልያለን። እርግጥ ነው፣ ስለ ቁሳዊና ስለ መንፈሳዊ ፍላጎታችንም መጸለይ እንችላለን። በምንጸልይበት ጊዜ ስለምንናገረው ነገር በጥንቃቄ ካሰብን ይህን አስደናቂ መብት ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው እናሳያለን። ጸሎታችን ጣፋጭ መዓዛ እንዳለው ዕጣን ይሖዋን “ደስ ያሰኘዋል።”—ምሳሌ 15:8

መዝሙር 45 በልቤ የማሰላስለው ነገር

^ ወደ ይሖዋ በጸሎት የመቅረብ መብት በማግኘታችን እጅግ አመስጋኞች ነን። ጸሎታችን ጣፋጭ መዓዛ እንዳለው ዕጣን ይሖዋን የሚያስደስት እንዲሆን እንፈልጋለን። በጸሎታችን ውስጥ የትኞቹን ነገሮች ማካተት እንደምንችል በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። ሌሎችን ወክለን እንድንጸልይ ስንጋበዝ ከግምት ማስገባት ያለብንን አንዳንድ ነጥቦችም እናያለን።

^ የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ባል ከሚስቱ ጋር ሆኖ ስለ ልጃቸው የትምህርት ቤት ውሎ፣ ስለ አረጋውያን ወላጆቻቸው ጤንነት እንዲሁም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው እድገት ሲጸልይ።

^ የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወጣት ወንድም ይሖዋ የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት፣ ውብ የሆነችውን ምድር እንዲሁም ገንቢ ምግብ ስለሰጠን ሲያመሰግነው።

^ የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት ይሖዋ ለበላይ አካሉ መንፈሱን እንዲሰጠው እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋና ስደት የደረሰባቸውን ክርስቲያኖች እንዲረዳቸው ስትጸልይ።