በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 32

ይሖዋን ምሰሉ—ምክንያታዊ ሁኑ

ይሖዋን ምሰሉ—ምክንያታዊ ሁኑ

“ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።”—ፊልጵ. 4:5

መዝሙር 89 ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ

ማስተዋወቂያ a

መሆን የምትፈልገው የትኛውን ዓይነት ዛፍ ነው? (አንቀጽ 1⁠ን ተመልከት)

1. ክርስቲያኖች ከዛፍ ጋር የሚመሳሰሉት በምን መንገድ ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

 “ነፋስን ዘንበል ብሎ ያሳለፈ ዛፍ አይሰበርም።” ይህ አባባል ከአንዳንድ ዛፎች ጽናት በስተ ጀርባ ያለውን ሚስጥር ያጎላል፤ ይህም እንደአስፈላጊነቱ ዘንበል የማለት ችሎታ ነው። ክርስቲያኖችም በመንፈሳዊ ሁኔታ በተተከሉበት ለመጽናት እንደአስፈላጊነቱ ዘንበል ማለት ወይም ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። እንዴት? በግል ሕይወታቸው ለውጥ ሲያጋጥማቸው ከአዲሱ ሁኔታ ጋር በመላመድ እንዲሁም የሌሎችን አመለካከትና ውሳኔ በማክበር ነው።

2. ለውጥ ሲያጋጥመን የትኞቹ ባሕርያት ይረዱናል? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 እኛ የይሖዋ አገልጋዮች ምክንያታዊ መሆን እንፈልጋለን። ትሑትና ሩኅሩኅ መሆንም እንፈልጋለን። አንዳንድ ክርስቲያኖች እነዚህን ባሕርያት ማዳበራቸው ለውጥ ሲያጋጥማቸው የረዳቸው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። እነዚህ ባሕርያት እኛን የሚጠቅሙን እንዴት እንደሆነም እናያለን። በቅድሚያ ግን የምክንያታዊነት ፍጹም ምሳሌ ከሆኑት ከይሖዋና ከኢየሱስ የምናገኘውን ትምህርት እንመልከት።

ይሖዋና ኢየሱስ ምክንያታዊ ናቸው

3. ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

3 ይሖዋ ጽኑና የማይነቃነቅ በመሆኑ “ዓለት” ተብሎ ተጠርቷል። (ዘዳ. 32:4) በሌላ በኩል ግን ምክንያታዊም ነው። ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው የማስተናገድ ችሎታ አለው። ይሖዋ በመልኩ ለፈጠራቸው የሰው ልጆች ለውጥን የመልመድ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። ምንም ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥመን እንደአመጣጡ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ ግልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ሰጥቶናል። ይሖዋ ራሱ ከተወው ምሳሌም ከሆነ ከሰጣቸው መመሪያዎች እንደምንረዳው “ዓለት” የሆነው አምላክ ምክንያታዊም ነው።

4. ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑን የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ። (ዘሌዋውያን 5:7, 11)

4 የይሖዋ መንገዶች ፍጹምና ምክንያታዊ ናቸው። ይሖዋ ከሰዎች በሚጠብቀው ነገር ረገድ ድርቅ ያለ አይደለም። ለምሳሌ ለአንዳንድ እስራኤላውያን ምክንያታዊነት ያሳየው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ድሆች ከሀብታሞች እኩል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ አልጠበቀባቸውም። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ግለሰቦች አቅማቸው በሚፈቅድላቸው መጠን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ፈቅዶላቸው ነበር።ዘሌዋውያን 5:7, 11ን አንብብ።

5. የይሖዋን ትሕትና እና ርኅራኄ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

5 ይሖዋ ምክንያታዊ እንዲሆን የሚያነሳሳው ትሕትናውና ርኅራኄው ነው። ለምሳሌ፣ ክፉ የሆኑትን የሰዶም ነዋሪዎች ለማጥፋት በወሰነበት ወቅት ትሕትናው በግልጽ ታይቷል። ይሖዋ መላእክቱን ልኮ፣ ወደ ተራራማው አካባቢ እንዲሸሽ ለጻድቁ ሎጥ መመሪያ ሰጠው። ሎጥ ግን እዚያ መሄድ ፈራ። በመሆኑም ከቤተሰቡ ጋር ወደ ዞአር ለመሸሽ እንዲፈቀድለት ለመነ፤ ዞአር ይሖዋ ለጥፋት ካሰባቸው ከተሞች አንዷ ነበረች። ይሖዋ ሎጥን ‘አንዴ ብያለሁ፣ የተባልከውን አድርግ’ ማለት ይችል ነበር። ሆኖም ልመናውን ሰማው፤ ቀድሞ ያሰበው ባይሆንም ዞአርን ላለማጥፋት ወሰነ። (ዘፍ. 19:18-22) ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ ይሖዋ ለነነዌ ነዋሪዎች ርኅራኄ አሳይቷል። በከተማዋና ክፉ በሆኑት ነዋሪዎቿ ላይ የሚመጣውን ጥፋት እንዲያውጅ ነቢዩ ዮናስን ላከው። ነዋሪዎቿ ንስሐ ሲገቡ ግን ይሖዋ አዘነላቸው፤ ከተማዋንም ሳያጠፋት ቀረ።—ዮናስ 3:1, 10፤ 4:10, 11

6. ኢየሱስ እንደ ይሖዋ ምክንያታዊነት ያሳየው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስም እንደ ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑን አሳይቷል። ወደ ምድር የተላከው “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች” ለመስበክ ነው። ሆኖም ይህን ኃላፊነቱን ሲወጣ ምክንያታዊነት አሳይቷል። በአንድ ወቅት፣ እስራኤላዊት ያልሆነች አንዲት ሴት ‘ጋኔን ክፉኛ የሚያሠቃያትን’ ልጇን እንዲፈውስላት ለመነችው። ኢየሱስ ለሴትየዋ ስለራራላት ጥያቄዋን ተቀብሎ ልጇን ፈወሰላት። (ማቴ. 15:21-28) ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። ኢየሱስ “የሚክደኝን ሁሉ [እኔም] እክደዋለሁ” ብሎ ነበር። (ማቴ. 10:33) ታዲያ ሦስት ጊዜ የካደውን ጴጥሮስን ክዶታል? በፍጹም። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ከልቡ መጸጸቱንና ለእሱ ያለውን ታማኝነት አይቷል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለጴጥሮስ ተገልጦለታል፤ በዚህ አጋጣሚ ይቅር እንዳለውና እንደሚወደው አረጋግጦለት መሆን አለበት።—ሉቃስ 24:33, 34

7. በፊልጵስዩስ 4:5 መሠረት ምን ዓይነት ስም ማትረፍ እንፈልጋለን?

7 ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያታዊ እንደሆኑ ተመልክተናል። እኛስ? ይሖዋ ምክንያታዊ እንድንሆን ይጠብቅብናል። (ፊልጵስዩስ 4:5ን አንብብ።) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ጥቅስ “ምክንያታዊ ነው የሚል ስም አትርፉ” በማለት አስቀምጦታል። እንግዲያው ራሳችንን እንዲህ ብለን እንጠይቅ፦ ‘ሰዎች ምክንያታዊ፣ እሺ ባይና ሰው የሚለኝን የምሰማ እንደሆንኩ ይሰማቸዋል? ወይስ ድርቅ ያልኩ፣ ግትርና አልሰማም ባይ አድርገው ይመለከቱኛል? ሌሎች እኔ ትክክለኛ ብዬ የማስበውን አሠራር እንዲከተሉ ጫና አደርጋለሁ? ወይስ ሌሎችን ለማዳመጥ፣ የሚቻል ከሆነም ሐሳባቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ?’ ይበልጥ ምክንያታዊ በሆንን መጠን ይሖዋንና ኢየሱስን ይበልጥ እንመስላለን። ከዚህ ቀጥሎ ምክንያታዊነት የሚጠይቁ ሁለት አቅጣጫዎችን እንመለከታለን፤ ያለንበት ሁኔታ ሲቀየር እንዲሁም የሌሎች አመለካከትና ውሳኔ ከእኛ የተለየ ሲሆን።

ሁኔታዎች ሲለወጡ ምክንያታዊ ሁኑ

8. ሁኔታዎች ሲለወጡ ምክንያታዊ ለመሆን ምን ይረዳናል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

8 ምክንያታዊ መሆን፣ ለውጦች ሲያጋጥሙን ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው ለማስተናገድ ያስችለናል። አንዳንድ ጊዜ ለውጦች ባልጠበቅነው አቅጣጫ ሕይወታችንን ሊያከብዱብን ይችላሉ። በድንገት ከባድ የጤና ችግር ሊያጋጥመን ይችላል፤ ወይም በምንኖርበት አካባቢ በኢኮኖሚው አሊያም በፖለቲካው ሥርዓት ላይ ድንገተኛ ለውጥ ተከስቶ ኑሯችን ሊመሰቃቀልብን ይችላል። (መክ. 9:11፤ 1 ቆሮ. 7:31) የአገልግሎት ምድብ ለውጥ እንኳ ፈተና የሚሆንበት ጊዜ አለ። ለውጡ ምንም ይሁን ምን የሚከተሉትን አራት እርምጃዎች ከወሰድን አዲሱን ሁኔታ መልመድ ቀላል ይሆንልናል፦ (1) እውነታውን መቀበል፣ (2) ነገን አሻግሮ ማየት፣ (3) በጎ በጎውን ማሰብ እንዲሁም (4) ሌሎችን መርዳት። b እነዚህን እርምጃዎች መውሰድ እንዴት እንደሚጠቅመን የሚያሳዩ እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎችን እስቲ እንመልከት።

9. ሚስዮናዊ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ያጋጠሟቸውን ያልተጠበቁ ፈተናዎች መወጣት የቻሉት እንዴት ነው?

9 እውነታውን ተቀበል። ኤማንዌሌ እና ፍራንቼስካ በሌላ አገር ሚስዮናዊ ሆነው እንዲያገለግሉ ተመድበው ነበር። የአካባቢውን ቋንቋ መማርና ጉባኤውን መላመድ እንደጀመሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከሰተ፤ በመሆኑም በአካል መገናኘት ቀረ። ከዚያ ደግሞ የፍራንቼስካ እናት በድንገት አረፉ። በዚህ ወቅት ፍራንቼስካ ከቤተሰቧ ጋር መሆን በጣም ፈልጋ ነበር፤ ሆኖም በወረርሽኙ ምክንያት መጓዝ አልቻለችም። ታዲያ እነዚህን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች እንድትቋቋም የረዳት ምንድን ነው? አንደኛ፣ ኤማንዌሌ እና ፍራንቼስካ ከዕለቱ አልፈው ለነገ ላለመጨነቅ ጥበብ እንዲሰጣቸው ይሖዋን በጸሎት ይለምኑት ነበር። ይሖዋም ወቅታዊ በሆኑ መንፈሳዊ ዝግጅቶች አማካኝነት ለጸሎታቸው ምላሽ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ በአንድ ወንድም የቃለ መጠይቅ ቪዲዮ ላይ የተጠቀሰ ሐሳብ አበረታቷቸዋል። ወንድም እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አዲሱን ሁኔታችንን ቶሎ አምነን ከተቀበልን . . . ደስታችን ቶሎ ይመለስልናል፤ ይህ ደግሞ ያለንበትን ሁኔታ በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት ያስችለናል።” c ሁለተኛ፣ በስልክ ምሥክርነት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ጥረት ማድረግ ጀመሩ፤ ተሳክቶላቸውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ቻሉ። ሦስተኛ፣ የጉባኤያቸው ወንድሞች በፍቅር ተነሳስተው የሚሰጧቸውን ማበረታቻና ድጋፍ በአድናቆት ተቀበሉ። አሳቢ የሆነች አንዲት እህት ለአንድ ዓመት ያህል በየቀኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አያይዛ አጭር መልእክት ትልክላቸው ነበር። እኛም አዲሱን ሁኔታችንን ከተቀበልነው ማድረግ በምንችለው ነገር እርካታ እናገኛለን።

10. አንዲት እህት በሕይወቷ ውስጥ ያጋጠማትን ትልቅ ለውጥ ያስተናገደችው እንዴት ነው?

10 ነገን አሻግረህ ተመልከት፤ በጎ በጎውን አስብ። ክርስቲና በጃፓን የምትኖር ሩማንያዊት እህት ናት። እሷ የምትሄድበት እንግሊዝኛ ጉባኤ ሲፈርስ አዝና ነበር። ይሁንና ያለፈውን እያሰበች አልቆዘመችም። በአካባቢዋ ባለው የጃፓንኛ ጉባኤ ውስጥ የምትችለውን ሁሉ ለማድረግና በጃፓንኛ የአገልግሎት ክልል በትጋት ለመስበክ ወሰነች። የቀድሞ የሥራ ባልደረባዋን በቋንቋ እንድታግዛት ጠየቀቻት። ሴትየዋም ክርስቲናን ጃፓንኛ ስታስተምር በመጽሐፍ ቅዱስና ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው ብሮሹር ለመጠቀም ተስማማች። በውጤቱም ክርስቲናም ሴትየዋም ተጠቅመዋል፤ ክርስቲና የጃፓንኛ ቋንቋ ችሎታዋን አሻሻለች፤ ሴትየዋ ደግሞ እውነትን ለመማር ፍላጎት አደረባት። ከትናንቱ ይልቅ ነገን አሻግረን ከተመለከትንና አዎንታዊ ከሆንን ድንገተኛ ለውጦች ያልጠበቅናቸውን በረከቶች ያስገኙልናል።

11. አንድ ባልና ሚስት የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥማቸው ምን አደረጉ?

11 ሌሎችን እርዳ። ሥራችን በታገደበት አገር የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሲወድቅ የገንዘብ ችግር ገጠማቸው። ታዲያ ሁኔታውን ለመልመድ ምን አደረጉ? በመጀመሪያ ኑሯቸውን ቀላል አደረጉ። ቀጥሎም በችግሮቻቸው ላይ ከመብሰልሰል ይልቅ ሌሎችን በመርዳት ላይ ለማተኮር ወሰኑ፤ በመሆኑም በስብከቱ ሥራ ራሳቸውን አስጠመዱ። (ሥራ 20:35) ባልየው እንዲህ ብሏል፦ “በአገልግሎት ስለተጠመድን መጥፎ መጥፎውን ለማሰብ ጊዜ የለንም። ትኩረታችን ሁሉ ያረፈው የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ነው።” ያለንበት ሁኔታ ሲቀየር፣ ሌሎችን መርዳት በተለይም በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን መበርታት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን መርሳት የለብንም።

12. የሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ በአገልግሎት ላይ የተለያዩ ሰዎችን ስናነጋግር የሚጠቅመን እንዴት ነው?

12 በአገልግሎታችን ላይ ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው የማስተናገድ ችሎታ ይጠቅመናል። የተለያየ እምነትና አመለካከት እንዲሁም አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር እንገናኛለን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደአስፈላጊነቱ ለውጥ የሚያደርግ ሰባኪ ነበር፤ ከእሱ የምናገኘው ብዙ ትምህርት አለ። ኢየሱስ ጳውሎስን ‘ለአሕዛብ የተላከ ሐዋርያ’ እንዲሆን ሾሞታል። (ሮም 11:13) ጳውሎስ ይህን ተልእኮውን ሲወጣ አይሁዳውያን፣ ግሪካውያን፣ የተማሩ ሰዎች፣ ተራ ገበሬዎች፣ ሹሞችና ነገሥታት አጋጥመውታል። ጳውሎስ የእነዚህን ሁሉ ሰዎች ልብ ለመንካት “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር” ሆኗል። (1 ቆሮ. 9:19-23) የአድማጮቹን ባሕል፣ አስተዳደግና ሃይማኖታዊ አመለካከት ለማስተዋል ጥረት አድርጓል፤ አቀራረቡንም እንደሁኔታው አስተካክሏል። እኛም በአገልግሎታችን ዘዴኞች በመሆንና አቀራረባችንን እንደ አድማጮቻችን ሁኔታ በመቀየር ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንችላለን።

የሌሎችን አመለካከት አክብሩ

ምክንያታዊ ከሆንን የሌሎችን አመለካከት እናከብራለን (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. የሌሎችን አመለካከት የምናከብር ከሆነ በ1 ቆሮንቶስ 8:9 ላይ የተጠቀሰውን የትኛውን አደጋ ማስቀረት እንችላለን?

13 ምክንያታዊነት የሌሎችን አመለካከት እንድናከብርም ይረዳናል። ለምሳሌ አንዳንድ እህቶች መኳኳያ መጠቀም ይወዳሉ፤ ሌሎች ደግሞ አይወዱም። አንዳንድ ክርስቲያኖች በልክ መጠጣት ያስደስታቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ጨርሶ ላለመጠጣት ወስነዋል። ሁሉም ክርስቲያኖች ጤናማ መሆን ይፈልጋሉ፤ ጤንነታቸውን የሚንከባከቡበት ዘዴ ግን እንደ ምርጫቸው ይለያያል። የእኛ ምርጫ ብቻ ትክክል እንደሆነ በማሰብ ሌሎችን የምንጫን ከሆነ በጉባኤ ውስጥ ማሰናከያ ልንሆንና ክፍፍል ልንፈጥር እንችላለን። ይህ እንዲሆን ጨርሶ አንፈልግም! (1 ቆሮንቶስ 8:9⁠ን አንብብ፤ 10:23, 24) ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች ሚዛናዊ ለመሆንና ሰላም ለመፍጠር የሚረዱን እንዴት እንደሆነ የሚያጎሉ ሁለት ምሳሌዎች እስቲ እንመልከት።

ምክንያታዊ ከሆንን የሌሎችን አመለካከት እናከብራለን (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. ከአለባበስና ከፀጉር ስታይል ጋር በተያያዘ ምን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተሰጥተዋል?

14 አለባበስና የፀጉር ስታይል። ይሖዋ ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ዝርዝር ደንቦች ከማውጣት ይልቅ ልንከተላቸው የሚገቡ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰጥቶናል። አለባበሳችን ለአምላክ አገልጋዮች የሚመጥን እንዲሁም ምክንያታዊነት፣ ልከኝነትና “ማስተዋል” የተንጸባረቀበት ሊሆን ይገባል። (1 ጢሞ. 2:9, 10፤ 1 ጴጥ. 3:3) ስለዚህ አለባበሳችን ወደ ራሳችን አላስፈላጊ ትኩረት የሚስብ ሊሆን አይገባም። ሽማግሌዎችም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተላቸው ከአለባበስና ከፀጉር ስታይል ጋር በተያያዘ የራሳቸውን ደንብ እንዳያወጡ ይረዳቸዋል። በአንድ ጉባኤ ውስጥ የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። በዚያ ጉባኤ ያሉ አንዳንድ ወጣት ወንድሞች በአካባቢያቸው ያለውን የፀጉር ፋሽን መከተል ጀመሩ፤ የፀጉር ስታይሉ አጭር ቢሆንም የተንጨባረረ ነበር። ሽማግሌዎቹ የራሳቸውን ደንብ ሳያወጡ እነዚህን ወጣቶች መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ወጣቶቹን እንዲህ እንዲሏቸው ለሽማግሌዎቹ ነገራቸው፦ “መድረክ ላይ ስትሆኑ አድማጮቻችሁ ንግግራችሁን መስማት ትተው በውጫዊ ገጽታችሁ ላይ ትኩረት ካደረጉ አለባበሳችሁና የፀጉር ስታይላችሁ የሆነ ችግር አለው ማለት ነው።” ሽማግሌዎቹ ይህንን ቀላል ነጥብ በማንሳት ብቻ ጉዳዩን መፍታት ቻሉ፤ የራሳቸውን ደንብ ማውጣትም አላስፈለጋቸውም። d

ምክንያታዊ ከሆንን የሌሎችን አመለካከት እናከብራለን (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. ጤንነትን ከመንከባከብ ጋር በተያያዘ የትኞቹ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ተሰጥተውናል? (ሮም 14:5)

15 ጤናን መንከባከብ። ‘ጤናዬን እንዴት ልንከባከብ?’ የሚለው ጉዳይ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የተተወ ውሳኔ ነው። (ገላ. 6:5) የአንድን ክርስቲያን የሕክምና ምርጫ የሚነኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ቀጥተኛ ሕጎች ጥቂት ናቸው፤ እነሱም ከደምና ከመናፍስታዊ ድርጊቶች እንድንርቅ የተሰጡት ሕጎች ናቸው። (ሥራ 15:20፤ ገላ. 5:19, 20) ከዚህ ውጭ ያለው ሁሉ ለግለሰቡ ምርጫ የተተወ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ዘመናዊ ሕክምናን ይመርጣሉ፤ ሌሎች ደግሞ አማራጭ የሚባሉ የሕክምና ዘዴዎችን መሞከር ይፈልጋሉ። ለእኛ ይበጀናል ብለን የመረጥነው የሕክምና ዓይነት ምንም ይሁን ምን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የራሳቸውን የሕክምና ምርጫ የማድረግ መብት እንዳላቸው ልንገነዘብ ይገባል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ነጥቦች ማስታወስ ይኖርብናል፦ (1) የተሟላና ዘላቂ ፈውስ የሚያስገኘው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። (ኢሳ. 33:24) (2) እያንዳንዱ ክርስቲያን ይበጀኛል ብሎ የመረጠው ሕክምና “ሙሉ በሙሉ ያመነበት” ሊሆን ይገባል። (ሮም 14:5ን አንብብ።) (3) በሌሎች ላይ መፍረድ ወይም የሚያሰናክል ነገር ማስቀመጥ አይኖርብንም። (ሮም 14:13) (4) ክርስቲያኖች ለሌሎች ፍቅር ያሳያሉ፤ የግል ምርጫ ከማድረግ መብታቸው የሚበልጥባቸው የጉባኤው አንድነት ነው። (ሮም 14:15, 19, 20) እነዚህን ነጥቦች ካስታወስን ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት አይሻክርም፤ ለጉባኤው ሰላምም አስተዋጽኦ እናደርጋለን።

ምክንያታዊ ከሆንን የሌሎችን አመለካከት እናከብራለን (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

16. አንድ ሽማግሌ ከሌሎች ሽማግሌዎች ጋር ባለው ግንኙነት ምክንያታዊነት የሚያሳየው እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

16 ሽማግሌዎች ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል። (1 ጢሞ. 3:2, 3) ለምሳሌ አንድ ሽማግሌ በዕድሜ ከሌሎቹ ሽማግሌዎች ስለሚበልጥ ብቻ ሁልጊዜ የእሱን ሐሳብ መቀበል እንዳለባቸው ሊሰማው አይገባም። የይሖዋ መንፈስ በሽማግሌዎች አካል ውስጥ ባለ በየትኛውም ወንድም እንደሚጠቀምና ለውሳኔ የሚረዳ ጠቃሚ ሐሳብ እንዲናገር ሊመራው እንደሚችል ይገነዘባል። ደግሞም የእሱ ምርጫ ምንም ይሁን ምን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ የሽማግሌዎች አካል በአብላጫ ድምፅ የሚያደርገውን ውሳኔ ይደግፋል።

ምክንያታዊ መሆን የሚያስገኛቸው በረከቶች

17. ምክንያታዊ የሆኑ ክርስቲያኖች ምን በረከት ያገኛሉ?

17 ምክንያታዊ የሆኑ ክርስቲያኖች ብዙ በረከቶችን ያገኛሉ። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ጥሩ ወዳጅነት ይኖረናል። ጉባኤውም ሰላማዊ ይሆናል። አንድነት ባላቸው የይሖዋ አገልጋዮች መካከል ያለው የባሕርይና የባሕል ልዩነት የደስታ ምክንያት ይሆንልናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ምክንያታዊ የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን እንደመሰልነው ስለምናውቅ ልባችን በእርካታ ይሞላል።

መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ

a ይሖዋና ኢየሱስ ምክንያታዊ ናቸው፤ እኛም ይህ ባሕርይ እንዲኖረን ይፈልጋሉ። በሕይወታችን ውስጥ ከጤንነታችን ወይም ከኢኮኖሚ ሁኔታችን ጋር በተያያዘ ለውጥ የሚያጋጥመን ጊዜ ይኖራል። ምክንያታዊነት አዲሱን ሁኔታ መላመድ ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል። ለጉባኤው ሰላምና አንድነትም አስተዋጽኦ ያደርጋል።

b በቁጥር 4 2016 ንቁ! ላይ የወጣውን “ለውጥን ማስተናገድ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c ከወንድም ዲሚትሪ ሚኻይሎቭ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ይህ ቪዲዮ በመጋቢት-ሚያዝያ 2021 ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ “ይሖዋ ስደትን ወደ ምሥክርነት ይቀይራል” ከሚለው ርዕስ ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል።

d ስለ አለባበስና የፀጉር ስታይል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 52 ተመልከት።