በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 31

“ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ”

“ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ”

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ።”—1 ቆሮ. 15:58

መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!

ማስተዋወቂያ a

1-2. ክርስቲያኖች ከሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ጋር ሊመሳሰሉ የሚችሉት እንዴት ነው? (1 ቆሮንቶስ 15:58)

 በ1970ዎቹ መጨረሻ ቶኪዮ፣ ጃፓን ውስጥ ባለ 60 ፎቅ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ተገነባ። ሕንፃው በከተማዋ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ርዕደ መሬት መቋቋም መቻሉን የተጠራጠሩ ታዛቢዎች ነበሩ። ታዲያ ጸንቶ ለመቆሙ ሚስጥሩ ምንድን ነው? መሐንዲሶች ሕንፃውን የገነቡት ጠንካራ ሆኖም ንዝረትን ውጦ ለማስቀረት የሚያስችል የመለመጥ ባሕርይ እንዲኖረው አድርገው ነው። ክርስቲያኖች ከዚህ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። እንዴት?

2 እንደ ክርስቲያን መጠን ፍንክች አለማለትም ሆነ እንደአስፈላጊነቱ ሐሳብን መቀየር የሚያስፈልገን ጊዜ ይኖራል፤ በዚህ ረገድ ሚዛናችንን መጠበቅ አለብን። አንድ ክርስቲያን የይሖዋን ሕጎችና መሥፈርቶች ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ጽኑና የማይነቃነቅ አቋም ሊኖረው ይገባል። (1 ቆሮንቶስ 15:58ን አንብብ።) “ለመታዘዝ ዝግጁ” ነው፤ እንዲሁም አቋሙን ለድርድር አያቀርብም። በሌላ በኩል ደግሞ የሚቻል ወይም አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት “ምክንያታዊ” ወይም ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን አለበት። (ያዕ. 3:17) በዚህ ረገድ ሚዛኑን መጠበቅን የተማረ ክርስቲያን ወደ የትኛውም ጽንፍ አይሄድም፤ ከልክ በላይ ጥብቅም ልልም አይሆንም። በዚህ ርዕስ ውስጥ ንቅንቅ ማለት የሌለብን በየትኞቹ መንገዶች እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም ሰይጣን አቋማችንን ለማዳከም የሚሞክርባቸውን አምስት መንገዶችና ጥረቱን ማክሸፍ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን።

ጽኑ አቋም የምንይዘው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

3. ከሁሉ የላቀው ሕግ ሰጪ በሐዋርያት ሥራ 15:28, 29 ላይ የሰጣቸው ሕጎች የትኞቹ ናቸው?

3 የሁሉ የበላይ ሕግ አውጪ የሆነው ይሖዋ በዘመናት ሁሉ ለሕዝቡ ግልጽ ሕግጋትን ሲሰጥ ቆይቷል። (ኢሳ. 33:22) ለምሳሌ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል፣ ክርስቲያኖች ጽኑ አቋም ሊይዙባቸው የሚገቡ ሦስት አቅጣጫዎችን ጠቁሟል፤ እነሱም (1) ከጣዖት አምልኮ መራቅና ይሖዋን ብቻ ማምለክ፣ (2) ለደም ቅድስና አክብሮት ማሳየት እንዲሁም (3) የመጽሐፍ ቅዱስን የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መታዘዝ ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በእነዚህ ሦስት አቅጣጫዎች ጽኑ አቋም መያዝ የሚችሉት እንዴት ነው?

4. ይሖዋን ብቻ እንደምናመልክ የምናሳየው እንዴት ነው? (ራእይ 4:11)

4 ከጣዖት አምልኮ እንርቃለን፤ ይሖዋን ብቻ እናመልካለን። ይሖዋ እሱን ብቻ እንዲያመልኩ እስራኤላውያንን አዟቸዋል። (ዘዳ. 5:6-10) ኢየሱስም በዲያብሎስ በተፈተነበት ወቅት ልናመልክ የሚገባው ይሖዋን ብቻ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። (ማቴ. 4:8-10) ስለዚህ ጣዖት አናመልክም። ደግሞም ለየትኛውም ሰው አምልኮ አከል ክብር አንሰጥም፤ የሃይማኖት መሪዎችም ሆኑ ፖለቲከኞች ወይም የስፖርቱና የመዝናኛው ዓለም ኮከቦች ጣዖት እንዲሆኑብን አንፈቅድም። ከይሖዋ ጎን እንቆማለን፤ የምናመልከው ‘ሁሉንም ነገሮች የፈጠረውን’ እሱን ብቻ ነው።ራእይ 4:11ን አንብብ።

5. ይሖዋ ከሕይወትና ከደም ቅድስና ጋር በተያያዘ ያወጣውን ሕግ የምንታዘዘው ለምንድን ነው?

5 ይሖዋ ስለ ሕይወትና ስለ ደም ቅድስና የሰጠውን ሕግ እናከብራለን። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ እንደተናገረው ደም ከእሱ ያገኘነውን ውድ ስጦታ ይኸውም ሕይወትን ይወክላል። (ዘሌ. 17:14) ይሖዋ፣ ሰዎች እንስሳትን እንዲበሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈቅድ ደሙን እንዳይበሉ አዟቸዋል። (ዘፍ. 9:4) የሙሴን ሕግ ለእስራኤላውያን በሰጠበት ወቅትም ይህን ትእዛዝ ደግሞታል። (ዘሌ. 17:10) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ደግሞ በበላይ አካሉ አማካኝነት ለሁሉም ክርስቲያኖች ባስተላለፈው ውሳኔ ‘ከደም እንዲርቁ’ መመሪያ ሰጥቷል። (ሥራ 15:28, 29) የሕክምና ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ በዚህ ትእዛዝ ላይ አንደራደርም። b

6. በይሖዋ የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለመመራት ምን እናደርጋለን?

6 የይሖዋን የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጥብቅ እንከተላለን። (ዕብ. 13:4) ሐዋርያው ጳውሎስ የአካል ክፍሎቻችሁን “ግደሉ” በማለት ምስል ከሳች የሆነ አገላለጽ ተጠቅሟል፤ ይህ አገላለጽ መጥፎ የሥጋ ምኞቶችን ለማስወገድ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ያስታውሰናል። ወደ ፆታ ብልግና የሚመራ ማንኛውንም ነገር ከማየትም ሆነ ከማድረግ እንቆጠባለን። (ቆላ. 3:5፤ ኢዮብ 31:1) መጥፎ ነገር ለማድረግ ስንፈተን ሐሳቡን ወዲያውኑ ከአእምሯችን ለማውጣት እንጥራለን፤ ደግሞም ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ከሚያበላሽ ማንኛውም ድርጊት ወዲያውኑ እንርቃለን።

7. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል? ለምንስ?

7 ይሖዋ ‘ከልብ እንድንታዘዘው’ ይጠብቅብናል። (ሮም 6:17) መመሪያዎቹ ምንጊዜም ይጠቅሙናል፤ ሕግጋቱም ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም። (ኢሳ. 48:17, 18፤ 1 ቆሮ. 6:9, 10) ይሖዋን ለማስደሰት ስንል የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠናል። “ሥርዓትህን በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ እስከ መጨረሻው ለመጠበቅ ቆርጫለሁ” ብሎ እንደዘመረው መዝሙራዊ ይሰማናል። (መዝ. 119:112) ሆኖም ሰይጣን አቋማችንን ለማዳከም ይጥራል። የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው?

ሰይጣን አቋማችንን ለማዳከም የሚጥረው እንዴት ነው?

8. ሰይጣን አቋማችንን ለማዳከም ስደትን የሚጠቀመው እንዴት ነው?

8 ስደት። ዲያብሎስ አካላዊና ስሜታዊ ጥቃት በመሰንዘር አቋማችንን ለማዳከም ይጥራል። ዓላማው እኛን ‘መዋጥ’ ይኸውም ከይሖዋ ጋር ያለንን ግንኙነት ማበላሸት ነው። (1 ጴጥ. 5:8) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት ክርስቲያኖች ለአቋማቸው ቆራጥ በመሆናቸው ዛቻ ደርሶባቸዋል፣ ተደብድበዋል እንዲሁም ተገድለዋል። (ሥራ 5:27, 28, 40፤ 7:54-60) ሰይጣን በዛሬው ጊዜም ስደትን መሣሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው። በሩሲያና በሌሎች አገራት ያሉት ወንድሞቻችን የሚደርስባቸው ግፍ ይህንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በተጨማሪም ተቃዋሚዎች በግለሰብ ደረጃ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ነው።

9. ስውር ጫና ያለውን አደጋ በምሳሌ አስረዳ።

9 ስውር ጫና። ሰይጣን ፊት ለፊት ከሚሰነዝርብን ጥቃት በተጨማሪ “መሠሪ ዘዴዎች” ይጠቀማል። (ኤፌ. 6:11) ቦብ የተባለ ወንድም ያጋጠመውን እንመልከት። ከባድ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ሆስፒታል ገብቶ ነበር። ቦብ፣ ምንም ቢመጣ ደም እንደማይወስድ ለሐኪሞቹ አስረዳቸው። ቀዶ ጥገናውን የሚያደርገው ሐኪም ውሳኔውን ለማክበር ተስማማ። ሆኖም ማደንዘዣ የሚሰጠው ሐኪም ከቀዶ ሕክምናው በፊት ባለው ምሽት የቦብ ቤተሰቦች ወደ ቤት ከሄዱ በኋላ መጣ። ደም መስጠት የሚጠይቅ ሁኔታ በአብዛኛው እንደማይፈጠር፣ ምናልባት ከተፈጠረ ግን ደም አዘጋጅተው እንደሚጠብቁ ለቦብ ነገረው። ሐኪሙ፣ ቦብ ቤተሰቡ በሌሉበት ሐሳቡን ሊቀይር እንደሚችል ሳይሰማው አልቀረም። ቦብ ግን ከአቋሙ ንቅንቅ አላለም፤ ምንም ሆነ ምን ደም እንዲሰጠው እንደማይፈልግ ገለጸ።

10. ሰብዓዊ አስተሳሰብ ወጥመድ የሆነው ለምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 3:19, 20)

10 ሰብዓዊ አስተሳሰብ። ነገሮችን በሰብዓዊ ዓይን መመልከት ከጀመርን ይሖዋንና መሥፈርቶቹን ችላ ልንል እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 3:19, 20ን አንብብ።) “የዚህ ዓለም ጥበብ” በአብዛኛው ለኃጢአተኛው ሥጋችን የሚማርክ ነው። አንዳንድ የጴርጋሞንና የትያጥሮን ክርስቲያኖች በከተሞቹ በተስፋፋው ጣዖት አምልኮና የብልግና አኗኗር ተስበው ነበር። የፆታ ብልግናን በቸልታ በማለፋቸው ኢየሱስ ለሁለቱም ጉባኤዎች ጠንከር ያለ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ራእይ 2:14, 20) በዛሬው ጊዜም የዓለምን የተሳሳተ አመለካከት እንድንቀበል ጫና ይደረግብናል። የቤተሰባችን አባላትና የምናውቃቸው ሰዎች ሊያባብሉንና አቋማችንን እንድናላላ ሊያሳምኑን ይሞክሩ ይሆናል። ለምሳሌ፣ ለምኞታችን እጅ መስጠት ምንም ችግር እንደሌለው ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጊዜ ያለፈባቸው እንደሆኑ ይናገሩ ይሆናል።

11. በአቋማችን መጽናት ቢኖርብንም ምን ልናደርግ አይገባም?

11 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የይሖዋ መመሪያዎች በበቂ መጠን ግልጽ እንዳልሆኑ እናስብ ይሆናል። ይባስ ብሎም ‘ከተጻፈው ለማለፍ’ ልንፈተን እንችላለን። (1 ቆሮ. 4:6) በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ዓይነት ስህተት ሠርተዋል። ሰው ያወጣቸውን ደንቦች በሕጉ ውስጥ በማካተት በሕዝቡ ላይ ከባድ ሸክም ጭነዋል። (ማቴ. 23:4) ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ግልጽ የሆነ መመሪያ ይሰጠናል። ታዲያ እሱ በሰጠን መመሪያ ላይ የራሳችንን የምናክልበት ምን ምክንያት አለ? (ምሳሌ 3:5-7) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው አልፈን መሄድ ወይም ለምርጫ ከተተዉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ የራሳችንን ደንቦች ማውጣት አንፈልግም።

12. ሰይጣን “ከንቱ ማታለያ” የሚጠቀመው እንዴት ነው?

12 ማታለያዎች። ሰይጣን “ከንቱ ማታለያ” እንዲሁም ‘የዓለምን መሠረታዊ ነገሮች’ በመጠቀም ሰዎችን ለማሳሳትና ለመከፋፈል ይሞክራል። (ቆላ. 2:8) ለምሳሌ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሰብዓዊ አመለካከት ላይ የተመሠረቱ ፍልስፍናዎችን፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ የአይሁድ ትምህርቶችን እንዲሁም ‘ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ ሊያከብሩ ይገባል’ የሚለውን ትምህርት ተጠቅሟል። እነዚህ ትምህርቶች ማታለያ ነበሩ፤ ምክንያቱም የሰዎችን ትኩረት በመስረቅ የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ዘወር እንዳይሉ አድርገዋል። በዛሬው ጊዜም ሰይጣን የመገናኛ ብዙኃንንና የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይጠቀማል፤ እነዚህ ሚዲያዎች የሴራ ትንታኔዎችንና ፖለቲከኞች የሚነዟቸውን የሐሰት ዘገባዎች ያሰራጫሉ። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ይህን በደንብ አይተናል። c የድርጅቱን መመሪያ የታዘዙ የይሖዋ ምሥክሮች የተዛባ መረጃ መስማት ከሚያስከትለው አላስፈላጊ ጭንቀት ድነዋል።—ማቴ. 24:45

13. ማዘናጊያዎች ወጥመድ እንዳይሆኑብን መጠንቀቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

13 ማዘናጊያዎች። ትኩረታችን ሊያርፍ የሚገባው “ይበልጥ አስፈላጊ [በሆኑት] ነገሮች” ላይ ነው። (ፊልጵ. 1:9, 10) ማዘናጊያዎች ይበልጥ ጠቃሚ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ የምናውለውን ጊዜና ትኩረት ይሻሙብናል። እንደ ምግብ፣ መጠጥ፣ መዝናኛና ሥራ የመሳሰሉት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ እንዲይዙ ከፈቀድንላቸው ማዘናጊያ ሊሆኑብን ይችላሉ። (ሉቃስ 21:34, 35) ከዚህም ሌላ ስለ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውዝግቦች የሚገልጹ ዜናዎች በየዕለቱ ይዥጎደጎዱብናል። እነዚህ ውዝግቦች ማዘናጊያ እንዲሆኑብን ልንፈቅድ አይገባም። አለዚያ በውስጣችን አንዱን ቡድን መደገፍ ልንጀምር እንችላለን። ሰይጣን ከላይ የተዘረዘሩትን ዘዴዎች የሚጠቀምበት ዓላማ ግልጽ ነው። ትክክል የሆነውን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ማዳከም ይፈልጋል። እንግዲያው የእሱን ጥረት ማክሸፍና ጸንተን መቀጠል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

በአቋማችን ለመጽናት ምን ይረዳናል?

በአቋምህ ለመጽናት የሚረዱህ ነገሮች፦ ራስህን ወስነህ ለመጠመቅ ያደረግኸውን ውሳኔ መለስ ብለህ ማሰብ፣ የአምላክን ቃል ማጥናትና ማሰላሰል፣ ልብህን ማጽናትና በይሖዋ መታመን (ከአንቀጽ 14-18⁠ን ተመልከት)

14. ከይሖዋ ጎን ለመቆም ባደረግነው ውሳኔ እንድንጸና የሚረዳን አንዱ ነገር ምንድን ነው?

14 ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ያደረግኸውን ውሳኔ መለስ ብለህ አስብ። እነዚህን እርምጃዎች የወሰድከው ከይሖዋ ጎን መቆም ስለፈለግህ ነው። እውነትን እንዳገኘህ እርግጠኛ እንድትሆን ያስቻሉህን ነገሮች መለስ ብለህ አስብ። በቅድሚያ ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት ቀሰምክ። ይህ ደግሞ ለሰማዩ አባትህ ያለህ ፍቅርና አክብሮት እያደገ እንዲሄድ አደረገ። እምነትህ እየጨመረ ሄደ፤ በመሆኑም ንስሐ ለመግባት ተነሳሳህ። ከመጥፎ ድርጊቶች ለመራቅና በአምላክ ፈቃድ መሠረት ለመኖር ቆረጥክ። (መዝ. 32:1, 2) የአምላክን ይቅርታ ስታገኝ ትልቅ እፎይታ ተሰማህ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም የተማርካቸውን አስደሳች ነገሮች ለሌሎች ማካፈል ጀመርክ። አሁን ደግሞ ራስህን ወስነህ የተጠመቅህ ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን በሕይወት ጎዳና ላይ እየተጓዝክ ነው፤ ከዚህ መንገድ ፈጽሞ ላለመውጣት ቆርጠሃል።—ማቴ. 7:13, 14

15. ጥናትና ማሰላሰል ጠቃሚ የሆኑት ለምንድን ነው?

15 የአምላክን ቃል አጥና እንዲሁም አሰላስልበት። ሥር የሰደደ ዛፍ ጸንቶ እንደሚቆም ሁሉ እኛም እምነታችን በአምላክ ቃል ላይ ሥር የሰደደ ከሆነ ጸንተን መቆም እንችላለን። አንድ ዛፍ እያደገ ሲሄድ ይበልጥ ሥር እየሰደደ ይሄዳል። ስናጠናና ስናሰላስል እምነታችን ይጠናከራል፤ እንዲሁም የአምላክ መንገዶች ከሁሉ የተሻሉ እንደሆኑ ይበልጥ እርግጠኛ እንሆናለን። (ቆላ. 2:6, 7) ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ከይሖዋ ትምህርት፣ መመሪያና ጥበቃ እንዴት እንደተጠቀሙ ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ ሕዝቅኤል በራእይ አንድ ቤተ መቅደስ ተመልክቶ ነበር፤ መልአኩ እያንዳንዱን ነገር ሲለካ ሕዝቅኤል በትኩረት ተመልክቷል። ራእዩ የሕዝቅኤልን እምነት አጠናክሮለታል፤ ለእኛም ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣውን መሥፈርት እንዴት መጠበቅ እንደምንችል ጠቃሚ ትምህርት ይዞልናል። d (ሕዝ. 40:1-4፤ 43:10-12) በእርግጥም ጊዜ መድበን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ ነገሮች ስናጠናና ስናሰላስልባቸው እንጠቀማለን።

16. ቦብ ልቡ ጽኑ መሆኑ የጠቀመው እንዴት ነው? (መዝሙር 112:7)

16 ልብህን አጽና። ንጉሥ ዳዊት ለይሖዋ ያለውን የማይናወጥ ፍቅር ሲገልጽ “አምላክ ሆይ፣ ልቤ ጽኑ ነው” ሲል ዘምሯል። (መዝ. 57:7) እኛም በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ጽኑ ልብ እንዲኖረን ማድረግ እንችላለን። (መዝሙር 112:7ን አንብብ።) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቦብ ይህን ማድረጉ እንዴት እንደረዳው እንመልከት። ለምናልባቱ ካስፈለገ ደም እንደሚቀመጥለት ሲነገረው ምላሽ የሰጠው ወዲያውኑ ነው። ምንም ሆነ ምን፣ ደም የመስጠት ሐሳብ ካላቸው ወዲያውኑ ሆስፒታሉን ለቆ እንደሚወጣ ገለጸ። ቦብ “አንዳች ጥርጣሬም ሆነ ስጋት አልነበረኝም” ሲል በኋላ ላይ ተናግሯል።

መንፈሳዊ መሠረታችን ጠንካራ ከሆነ ምንም ዓይነት ፈተና ቢመጣ በአቋማችን እንጸናለን (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

17. ከቦብ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

17 ቦብ ሆስፒታል ከመግባቱ ከረጅም ጊዜ በፊት በአቋሙ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ ባያደርግ ኖሮ እንዲህ ዓይነት ጥንካሬ አይኖረውም ነበር። በመጀመሪያ፣ ይሖዋን የማስደሰት ፍላጎት እንዲያድርበት አድርጓል። ሁለተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ስለ ሕይወትና ስለ ደም ቅድስና የሚናገሩትን ነገር በጥልቀት አጥንቷል። ሦስተኛ፣ የይሖዋን መመሪያ መከተል ውሎ አድሮ ዘላቂ ጥቅም እንደሚያስገኝ ራሱን አሳምኗል። እኛም ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን እንዲህ ዓይነት ጽኑ ልብ ሊኖረን ይችላል።

ባርቅና ወታደሮቹ የሲሳራን ሠራዊት ሲያሳድዱ (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)

18. የባርቅ ታሪክ በይሖዋ እንድንታመን የሚያስተምረን እንዴት ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

18 በይሖዋ ታመን። ባርቅ፣ ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መታመኑ ውጤታማ ለመሆን የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ከእስራኤላውያን መካከል ጋሻም ሆነ ጦር ያለው ሰው አልነበረም። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ ሲሳራ ከሚመራው በሚገባ የታጠቀ የከነአናውያን ሠራዊት ጋር እንዲዋጋ መመሪያ ሰጠው። (መሳ. 5:8) ነቢዪቱ ዲቦራ፣ ባርቅ ከተራራው ወደ ሜዳው ወርዶ ሲሳራንና 900 የጦር ሠረገሎቹን እንዲገጥም ነገረችው። ሜዳ ላይ መዋጋት ስልታዊ ጠቀሜታ የሚያስገኘው ለሠረገሎቹ ቢሆንም ባርቅ ታዟል። ወታደሮቹ ከታቦር ተራራ ሲወርዱ ይሖዋ ዶፍ ዝናብ እንዲጥል አደረገ። በመሆኑም የሲሳራ ሠረገሎች በጭቃ ተያዙ፤ ይሖዋ ባርቅን ድል አጎናጸፈው። (መሳ. 4:1-7, 10, 13-16) እኛም በተመሳሳይ በይሖዋና ተወካዮቹ በሚሰጡን መመሪያ የምንታመን ከሆነ ድል እናደርጋለን።—ዘዳ. 31:6

በአቋምህ ለመጽናት ቁረጥ

19. በአቋምህ ለመጽናት የቆረጥከው ለምንድን ነው?

19 በዚህ ሥርዓት እስከኖርን ድረስ በአቋማችን ለመጽናት የምናደርገው ፍልሚያ አያቆምም። (1 ጢሞ. 6:11, 12፤ 2 ጴጥ. 3:17) እንግዲያው ስደት፣ ስውር ጫና፣ ሰብዓዊ አስተሳሰብ፣ ማታለያዎችና ማዘናጊያዎች አቋማችንን እንዳያናጉት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ኤፌ. 4:14) ከዚህ ይልቅ ጸንተን እንቁም፤ ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ ጽኑ፣ ሕግጋቱን በመታዘዝ ረገድ ደግሞ የማንነቃነቅ እንሁን። በሌላ በኩል ደግሞ ምክንያታዊ መሆን አለብን። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይሖዋና ኢየሱስ ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ፍጹም ምሳሌ የሚሆኑን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን

a ሰይጣን ከአዳምና ከሔዋን ዘመን አንስቶ ሲያስፋፋ የቆየው አንድ ሐሳብ አለ፤ ይህም ‘ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በራሳቸው የመወሰን መብት አላቸው’ የሚል ነው። እኛም ከይሖዋ ሕጎችና ከድርጅቱ ከሚሰጠን ማንኛውም መመሪያ ጋር በተያያዘ እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንድናዳብር ይፈልጋል። ይህ ርዕስ የሰይጣን ዓለም የሚያስፋፋውን በራስ የመመራት መንፈስ ለመዋጋት ይረዳናል። ከይሖዋ ጎን ለመቆም ያለንን ቁርጠኝነትም ያጠናክርልናል።

b አንድ ክርስቲያን አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ እንዴት መታዘዝ እንደሚችል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 39 ተመልከት።

c jw.org ላይ የወጣውን “ከተሳሳተ መረጃ ራስህን ጠብቅ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።