በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 30

ፍቅርህ እያደገ ይሂድ

ፍቅርህ እያደገ ይሂድ

“በሁሉም ነገር . . . በፍቅር እንደግ።”—ኤፌ. 4:15

መዝሙር 2 ስምህ ይሖዋ ነው

ማስተዋወቂያ a

1. መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና የትኞቹን እውነቶች ተምረሃል?

 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመርክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? አምላክ ስም እንዳለው ስታውቅ በጣም ተገርመህ ሊሆን ይችላል። አምላክ ሰዎችን በገሃነመ እሳት እንደማያሠቃይ ስትማር እፎይታ ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። በሞት ያጣሃቸውን የምትወዳቸውን ሰዎች ዳግመኛ እንደምታገኛቸውና ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም አብረሃቸው የመኖር ተስፋ እንዳለህ ስታውቅ ደግሞ በጣም ተደስተህ መሆን አለበት።

2. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከመማር ባለፈ ምን እድገት አደረግህ? (ኤፌሶን 5:1, 2)

2 የአምላክን ቃል እያጠናህ ስትሄድ ለይሖዋ ያለህ ፍቅርም እያደገ ሄደ። ይህ ፍቅር ደግሞ የተማርከውን በተግባር እንድታውል አነሳሳህ። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተህ የተሻሉ ውሳኔዎችን ማድረግ ጀመርክ። አምላክን ማስደሰት ስለፈለግህ በአመለካከትህና በምግባርህም ላይ ለውጥ አደረግህ። አንድ ልጅ የሚወደውን ወላጁን እንደሚኮርጅ ሁሉ አንተም በሰማይ ያለውን አባትህን መምሰል ጀመርክ።—ኤፌሶን 5:1, 2ን አንብብ።

3. ራሳችንን ምን እያልን መጠየቅ እንችላለን?

3 ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ክርስቲያን ስሆን ከነበረበት ጨምሯል? ከተጠመቅሁበት ጊዜ ወዲህ በአስተሳሰቤና በድርጊቴ ይሖዋን ይበልጥ እየመሰልኩት ነው? ለምሳሌ ለወንድሞቼና ለእህቶቼ ፍቅር በማሳየት ረገድ እንዴት ነኝ?’ ‘መጀመሪያ ላይ የነበረህ ፍቅር’ በተወሰነ ደረጃ ተቀዛቅዞ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ነገር አጋጥሟቸዋል። ሆኖም ኢየሱስ ተስፋ አልቆረጠባቸውም፤ በእኛም ተስፋ አይቆርጥብንም። (ራእይ 2:4, 7) እውነትን ስንሰማ የነበረንን ፍቅር መልሰን ማቀጣጠል እንደምንችል ያውቃል።

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

4 ይህ ርዕስ ለይሖዋና ለሌሎች ያለንን ፍቅር እንዴት ማሳደግ እንደምንችል ያብራራል። ከዚያም ፍቅራችንን ማሳደጋችን ለእኛም ሆነ ለሌሎች የሚያስገኘውን በረከት እንመለከታለን።

ለይሖዋ ያለህን ፍቅር አሳድግ

5-6. ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን ሲያከናውን ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር? ይሖዋን ማገልገሉን እንዲቀጥል ያነሳሳውስ ምንድን ነው?

5 ሐዋርያው ጳውሎስ በይሖዋ አገልግሎት አስደሳች ሕይወት አሳልፏል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖለታል ማለት አይደለም። ጳውሎስ ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ብዙ ጊዜ ተጉዟል፤ በዚያ ዘመን ደግሞ ጉዞ ማድረግ ቀላል አልነበረም። ጳውሎስ በጉዞው ላይ “በወንዝ ሙላት ለሚመጣ አደጋ” እንዲሁም “ዘራፊዎች ለሚያደርሱት አደጋ” የተጋለጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። በተቃዋሚዎች እጅ ተደብድቧል እንዲሁም እንግልት ደርሶበታል። (2 ቆሮ. 11:23-27) ክርስቲያን ወንድሞቹም ቢሆኑ ለእነሱ ሲል ብዙ መድከሙን ያላደነቁበት ጊዜ አለ።—2 ቆሮ. 10:10፤ ፊልጵ. 4:15

6 ታዲያ ጳውሎስ በይሖዋ አገልግሎት እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? ጳውሎስ ከቅዱሳን መጻሕፍትና ከራሱ ተሞክሮ ስለ ይሖዋ ባሕርያት ብዙ ተምሯል። ጳውሎስ ይሖዋ አምላክ እንደሚወደው እርግጠኛ ነበር። (ሮም 8:38, 39፤ ኤፌ. 2:4, 5) እሱም ይሖዋን በጣም ይወደው ነበር። ይህ ፍቅር ‘ቅዱሳንን እንዲያገለግልና ወደፊትም ማገልገሉን እንዲቀጥል’ አነሳስቶታል።—ዕብ. 6:10

7. ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ የሚረዳን አንዱ ነገር ምንድን ነው?

7 እኛም ለአምላክ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ የሚረዳን አንዱ ነገር ቃሉን በትጋት ማጥናት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ እያንዳንዱ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምርህ ለማስተዋል ሞክር። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ይህ ዘገባ ይሖዋ እንደሚወደኝ የሚጠቁመው እንዴት ነው? ይሖዋን እንድወደው የሚያነሳሳ ምን ምክንያትስ ይዟል?’

8. ጸሎት ለይሖዋ ያለን ፍቅር እንዲያድግ የሚረዳን እንዴት ነው?

8 ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ አዘውትረን መጸለይና ልባችንን በፊቱ ማፍሰስ ነው። (መዝ. 25:4, 5) ይህንን ስናደርግ ይሖዋም ጸሎታችንን ይመልስልናል። (1 ዮሐ. 3:21, 22) በእስያ የምትኖር ካን የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ ይሖዋን እንድወደው ያነሳሳኝ ስለ እሱ የተማርኩት ነገር ነበር። ጸሎቴን እንዴት እንደመለሰልኝ ሳይ ደግሞ ለእሱ ያለኝ ፍቅር ይበልጥ እያደገ ሄደ። ይህም እሱን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ለማድረግ አነሳሳኝ።” b

ለሌሎች ያለህን ፍቅር አሳድግ

9. ጢሞቴዎስ ለሌሎች ፍቅር ከማሳየት ጋር በተያያዘ እድገት እንዳደረገ የሚያሳየው ምንድን ነው?

9 ጳውሎስ ክርስትናን ከተቀበለ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ጢሞቴዎስ ከተባለ ግሩም ወጣት ጋር ተገናኘ። ጢሞቴዎስ ይሖዋንም ሰዎችንም ይወድ ነበር። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች “ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ [ጢሞቴዎስ] ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝም” ሲል ጽፏል። (ፊልጵ. 2:20) ጳውሎስ እዚህ ላይ ያደነቀው የጢሞቴዎስን የማደራጀት ወይም የንግግር ችሎታ አይደለም። ጳውሎስን ያስደነቀው ጢሞቴዎስ ለወንድሞችና ለእህቶች ያለው ፍቅር እንደሆነ ግልጽ ነው። ጢሞቴዎስ የጎበኛቸው ጉባኤዎችም የእሱን መምጣት በጉጉት ይጠባበቁ እንደነበረ ጥርጥር የለውም።—1 ቆሮ. 4:17

10. አናና ባለቤቷ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ያላቸውን ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?

10 እኛም ክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመርዳት አጋጣሚ እንፈልጋለን። (ዕብ. 13:16) ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው አና ያደረገችውን እንመልከት። በአካባቢያቸው ውድመት ያደረሰ ኃይለኛ ዝናብ ተከስቶ ነበር። በኋላ ላይ እሷና ባለቤቷ አንድ ቤተሰብ ለመጠየቅ ሄዱ፤ የዚህ ቤተሰብ ቤት ጣሪያው እንደተነደለና በዚህም ምክንያት ልብሶቻቸው ሁሉ እንደቆሸሹባቸው አስተዋሉ። አና እንዲህ ብላለች፦ “ልብሳቸውን ወሰድንና አጥበን፣ ተኩሰንና አጣጥፈን መለስንላቸው። ይህ ለእኛ ምንም ማለት አልነበረም። ሆኖም ከዚህ ቤተሰብ ጋር እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረት ችለናል።” አናና ባለቤቷ ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅር፣ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያደርጉላቸው አነሳስቷቸዋል።—1 ዮሐ. 3:17, 18

11. (ሀ) ፍቅር ለማሳየት የምናደርገው ጥረት በሌሎች ላይ ምን ስሜት ሊፈጥር ይችላል? (ለ) ምሳሌ 19:17 እንደሚያሳየው ይሖዋ ፍቅር ስናሳይ ምን ያደርጋል?

11 ፍቅርና ደግነት ስናሳይ ይሖዋን በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ለመምሰል የምናደርገውን ጥረት ሌሎች ማስተዋላቸው አይቀርም። እኛ ከምናስበው በላይ ደግነታችንን ያደንቁ ይሆናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካን እገዛ ያደረጉላትን ሰዎች ሁሌም በመልካም ታስታውሳቸዋለች። እንዲህ ብላለች፦ “አገልግሎት ይዘውኝ ይወጡ ለነበሩት እህቶች በጣም አመስጋኝ ነኝ። ከቤቴ መጥተው ይወስዱኛል፣ ሻይ ቡና ወይም ምሳ ይጋብዙኛል፣ ከዚያም ቤቴ ድረስ ይሸኙኛል። አሁን ሳስበው ለእኔ ብዙ እንደደከሙ ይሰማኛል። ይህንንም ያደረጉት በደስታ ነው።” እርግጥ ነው፣ ላደረግነው ነገር የሚያመሰግነን ሁሉም ሰው አይደለም። ካን ያገዟትን ሰዎች በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “ላሳዩኝ ደግነት ውለታቸውን ብመልስ ደስ ይለኝ ነበር። ሆኖም የማናቸውንም የመኖሪያ አድራሻ አላውቅም፤ ይሖዋ ግን ያውቃል። ስለዚህ ብድራታቸውን እንዲመልስላቸው እጸልያለሁ።” ካን የተናገረችው ነገር እውነት ነው። ይሖዋ ለሌሎች የምናሳየውን ትንሿን ደግነት እንኳ ያስተውላል። ውድ ዋጋ እንዳለው መሥዋዕት አድርጎ ይመለከተዋል፤ ለእሱ እንዳበደርነው አድርጎም ይቆጥረዋል።ምሳሌ 19:17ን አንብብ።

አንድ ሰው መንፈሳዊ እድገት ሲያደርግ ሌሎችን ለመርዳት አጋጣሚ ይፈልጋል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. ወንድሞች ለጉባኤው ፍቅር ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

12 ወንድም ከሆንክ ለሌሎች ፍቅር ማሳየትና ለመልካም ሥራ መጣጣር የምትችለው እንዴት ነው? ጆርዳን የተባለ አንድ ወጣት ወንድም ጉባኤውን ለማገዝ ምን ተጨማሪ ነገር ማድረግ እንደሚችል አንድን ሽማግሌ አማከረው። ሽማግሌውም እስካሁን ስላደረገው እድገት ካመሰገነው በኋላ ተጨማሪ ነገር ማድረግ ስለሚችልባቸው አቅጣጫዎች ምክር ሰጠው። ለምሳሌ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ቀደም ብሎ እንዲመጣና ሰላም እንዲል፣ በስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ፣ ከአገልግሎት ቡድኑ ጋር አዘውትሮ እንዲያገለግል እንዲሁም ሌሎችን መርዳት የሚችልባቸውን አጋጣሚዎች እንዲፈልግ አበረታታው። ለጆርዳን ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁ ክህሎቶችን የመማር ጉዳይ አልነበረም። ይህ ሽማግሌ፣ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ያለውን ፍቅር እንዲያሳድግ ጆርዳንን እያበረታታው ነበር። ጆርዳን እንደተረዳው፣ አንድ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ ሲሆን አይደለም ወንድሞቹን መርዳት የሚጀምረው፤ ከዚህ ይልቅ ወንድሞቹን ለመርዳት ቀድሞውንም ያደርግ የነበረውን ጥረት ይቀጥልበታል።1 ጢሞ. 3:8-10, 13

13. ክርስቲያን የተባለ አንድ ወንድም እንደገና በሽምግልና እንዲያገለግል ፍቅር ያነሳሳው እንዴት ነው?

13 የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነህ የማገልገል መብትህን አጥተህ ከሆነስ? ይሖዋ ያከናወንከውን ሥራና ይህን ለማድረግ ያነሳሳህን ፍቅር እንደማይረሳ አስታውስ። (1 ቆሮ. 15:58) አሁን እያሳየህ ያለኸውንም ፍቅር ያስተውላል። ክርስቲያን የተባለ ወንድም ከሽምግልና ሲወርድ ተከፍቶ ነበር። ሆኖም ምን ብሎ እንደወሰነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “መብት ኖረኝም አልኖረኝ፣ በፍቅር ተነሳስቼ ይሖዋን ለማገልገል ቆረጥኩ።” ከጊዜ በኋላ ሽማግሌ ሆኖ እንደገና ተሾመ። ክርስቲያን እንዲህ ሲል ስሜቱን በግልጽ ተናግሯል፦ “እንደገና በሽምግልና ስለማገልገል ሳስብ ትንሽ ስጋት አድሮብኝ ነበር። ሆኖም ይሖዋ በምሕረቱ በድጋሚ ሽማግሌ ሆኜ እንዳገለግል ከፈቀደልኝ ኃላፊነቱን ለመቀበል ወሰንኩ። ይህን የማደርገው ይሖዋን እንዲሁም ወንድሞቼንና እህቶቼን ስለምወድ ነው።”

14. በጆርጂያ የምትኖር እህት ከተናገረችው ሐሳብ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

14 የይሖዋ አገልጋዮች ለሌሎች ሰዎችም ፍቅራቸውን ማሳየት ይፈልጋሉ። (ማቴ. 22:37-39) በጆርጂያ የምትኖረውን የኤሌናን ምሳሌ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ ለመስበክ የሚያነሳሳኝ ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ብቻ ነበር። ለሰማዩ አባቴ ያለኝ ፍቅር እያደገ ሲሄድ ግን ለሰዎች ያለኝ ፍቅርም ጨመረ። ምን ዓይነት ችግሮች እያጋጠሟቸው እንዳለና የትኛው ርዕሰ ጉዳይ ልባቸውን እንደሚነካው ማሰብ ጀመርኩ። በዚህ መንገድ ችግራቸውን ለመረዳት ጥረት ባደረግሁ ቁጥር እነሱን ለመርዳት ያለኝ ፍላጎትም እየጨመረ ሄደ።”—ሮም 10:13-15

ለሌሎች ፍቅር ማሳየት የሚያስገኘው በረከት

በፍቅር ተነሳስተን ያደረግነው አንድ ነገር በረከቱ ለብዙዎች ይተርፋል (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት)

15-16. በሥዕሎቹ ላይ በትወና መልክ እንደቀረበው ለሌሎች ፍቅር ማሳየት ምን በረከት ያስገኛል?

15 ለወንድሞቻችን ፍቅር ስናሳይ የሚጠቀሙት እነሱ ብቻ አይደሉም። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲጀምር ፓውሎና ባለቤቱ፣ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻቸውን ለአገልግሎት እንዴት እንደሚጠቀሙ ብዙ አረጋውያን እህቶችን አሠለጠኑ። መጀመሪያ ላይ በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ መጠቀም ተቸግራ የነበረች አንዲት እህት በኋላ ላይ ተሳካላት። በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ብዙ ዘመዶቿን መጋበዝም ቻለች። ስልሳ የሚሆኑት በዓሉን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተከታተሉ! ፓውሎና ባለቤቱ ያደረጉት ጥረት እህታችንን ብቻ ሳይሆን ዘመዶቿንም ጠቅሟቸዋል። እህታችን ለፓውሎ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “እኛን አረጋውያንን ስላስተማርከን በጣም እናመሰግናለን። የይሖዋን አሳቢነትና አንተም ሳትታክት የሰጠኸንን እርዳታ መቼም አልረሳውም።”

16 እንደነዚህ ያሉት ተሞክሮዎች ለፓውሎ አንድ ወሳኝ ነገር አስገንዝበውታል። ፍቅር ከእውቀት ወይም ከተፈጥሮ ችሎታ የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን አስተውሏል። እንዲህ ብሏል፦ “የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገለግል ነበር። አሁን እንደገባኝ ግን ወንድሞች ከሰጠኋቸው ንግግሮች ይበልጥ የሚያስታውሱት ያደረግኩላቸውን ነገሮች ነው።”

17. ለሌሎች ፍቅር ማሳየታችን ማንንም ይጠቅማል?

17 ለሌሎች ፍቅር ስናሳይ እኛም ባልጠበቅነው መንገድ እንጠቀማለን። በኒው ዚላንድ የሚኖረው ጆናታን ይህን ተመልክቷል። አንድ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ አንድ አቅኚ መንገድ ላይ በፀሐይ ሲያገለግል ተመለከተ። ጆናታን ከዚያ በኋላ ቅዳሜ ቅዳሜ ከሰዓት አብሮት ለማገልገል ወሰነ። በደግነት ተነሳስቶ ያደረገው ነገር ምን ያህል እንደሚጠቅመው የገባው በኋላ ላይ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “በዚያ ወቅት አገልግሎት ብዙም ደስ አይለኝም ነበር። አቅኚው የሚያስተምርበትን መንገድና በአገልግሎት ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ስመለከት ግን ለዚህ ሥራ ያለኝ ፍቅር ተቀጣጠለ። ይህ ወንድም ጥሩ ወዳጅም ሆኖልኛል። መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ፣ አገልግሎትን እንድወድና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድቀርብ ረድቶኛል።”

18. ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል?

18 ይሖዋ ሁላችንም ለእሱም ሆነ ለሌሎች ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ይፈልጋል። በዚህ ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ቃሉን በማንበብና በማሰላሰል እንዲሁም አዘውትረን ወደ እሱ በመጸለይ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳደግ እንችላለን። አጋጣሚዎች ፈልገን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በማገዝ ለእነሱ ያለንን ፍቅር ማሳደግ እንችላለን። ፍቅራችን እያደገ ሲሄድ ወደ ይሖዋም ሆነ ወደ መንፈሳዊ ቤተሰባችን ይበልጥ እንቀርባለን። ይህ ወዳጅነት ደግሞ ለዘላለም ይዘልቃል!

መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ

a በቅርቡ እውነትን የሰማንም ሆንን ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ስናገለግል የቆየን፣ ሁላችንም እድገት ማድረጋችንን መቀጠል ያስፈልገናል። ይህ ርዕስ እንዲህ ማድረግ የምንችልበትን አንድ አስፈላጊ መንገድ ያብራራል፤ ይህም ለይሖዋና ለሌሎች ያለንን ፍቅር ማሳደግ ነው። በዚህ ርዕስ ላይ ስታሰላስል እስካሁን ያደረግኸውን እድገት ገምግም፤ እንዲሁም ተጨማሪ እድገት ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።