በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 27

መዝሙር 73 ድፍረት ስጠን

እንደ ሳዶቅ ደፋር ሁን

እንደ ሳዶቅ ደፋር ሁን

‘ሳዶቅ ኃያልና ደፋር ወጣት ነበር።’1 ዜና 12:28

ዓላማ

የሳዶቅ ምሳሌ ደፋሮች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

1-2. ሳዶቅ ማን ነበር? (1 ዜና መዋዕል 12:22, 26-28)

 የሚከተለውን ሁኔታ በምናብህ ለመሣል ሞክር። ከ340,000 የሚበልጡ ሰዎች ዳዊትን በመላው እስራኤል ላይ ለማንገሥ ተሰብስበዋል። እነዚህ ሰዎች ለሦስት ቀን ያህል በኬብሮን አቅራቢያ በሚገኙት ዓለታማ ኮረብቶች ላይ ተሰብስበው ሞቅ ያለ ጭውውት ሲያደርጉ፣ ሲሳሳቁና በደስታ የውዳሴ መዝሙር ሲዘምሩ ቆይተዋል። (1 ዜና 12:39) ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሳዶቅ የተባለ ወጣትም ይገኝበታል። ከሕዝቡ ብዛት አንጻር ሳዶቅ እዚያ መኖሩን ማንም ልብ ላይል ይችላል። ሆኖም ይሖዋ፣ ሳዶቅ እዚያ መኖሩን እንድናውቅ አድርጓል። (1 ዜና መዋዕል 12:22, 26-28ን አንብብ።) ሳዶቅ ማን ነበር?

2 ሳዶቅ ከሊቀ ካህናቱ ከአብያታር ጋር በቅርበት የሚሠራ ካህን ነበር። በተጨማሪም ሳዶቅ የአምላክን ፈቃድ የማስተዋል ችሎታና አስደናቂ ጥበብ ያለው ባለራእይ ነበር። (2 ሳሙ. 15:27) ሰዎች ጥሩ ምክር ማግኘት ሲፈልጉ ሳዶቅን ያማክሩት ነበር። ከዚህም ሌላ ሳዶቅ ደፋር ሰው ነበር። በዚህ ርዕስ ውስጥ የምናተኩረው በዚህ ባሕርይው ላይ ነው።

3. (ሀ) የይሖዋ አገልጋዮች ደፋር መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት አፋፍሟል። (1 ጴጥ. 5:8) ይሖዋ ሰይጣንን እና ክፉ ሥርዓቱን እስኪያጠፋ በምንጠብቅበት ወቅት ደፋር መሆን ያስፈልገናል። (መዝ. 31:24) የሳዶቅን ድፍረት መኮረጅ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ከአምላክ መንግሥት ጎን ቁም

4. የይሖዋ ሕዝቦች ከአምላክ መንግሥት ጎን ለመቆም ድፍረት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን በሙሉ ልባችን ከአምላክ መንግሥት ጎን እንቆማለን። ሆኖም ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረግ ድፍረት ይጠይቃል። (ማቴ. 6:33) ለምሳሌ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ በይሖዋ መሥፈርቶች ለመመራትና የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ድፍረት ያስፈልገናል። (1 ተሰ. 2:2) በተጨማሪም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በፖለቲካዊ ጉዳዮች በተከፋፈለው በዚህ ዓለም ውስጥ ገለልተኝነታችንን መጠበቅ ድፍረት ይጠይቃል። (ዮሐ. 18:36) በፖለቲካዊ ወይም በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ የገንዘብ ኪሳራ የደረሰባቸው፣ አካላዊ ጥቃት የተሰነዘረባቸው አልፎ ተርፎም የታሰሩ በርካታ የይሖዋ ሕዝቦች አሉ።

ሌሎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ወገንተኛ ሲሆኑ ምን ታደርጋለህ? (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)


5. ሳዶቅ ከዳዊት ጎን ለመቆም ድፍረት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

5 ሳዶቅ ወደ ኬብሮን የሄደው ዳዊት በመንገሡ ደስታውን ለመግለጽ ብቻ አልነበረም። ወደዚያ የሄደው መሣሪያ ታጥቆና ለጦርነት ተዘጋጅቶ ነው። (1 ዜና 12:38) ዳዊትን ተከትሎ ለመዋጋትና እስራኤልን ከጠላቶቹ ለመታደግ ፈቃደኛ ነበር። ሳዶቅ የውጊያ ተሞክሮ ሊጎድለው ቢችልም አስደናቂ ድፍረት ነበረው።

6. ዳዊት በድፍረት ረገድ ለሳዶቅ ግሩም ምሳሌ የተወለት እንዴት ነው? (መዝሙር 138:3)

6 ሳዶቅ ካህን ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ያለ አስደናቂ ድፍረት ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? በዙሪያው የነበሩት ሰዎች ጠንካራና ደፋር ነበሩ። ከእነሱ ምሳሌ እንደተጠቀመ ምንም ጥያቄ የለውም። ለምሳሌ ዳዊት “እስራኤል ወደ ጦርነት ሲወጣ” በድፍረት ሕዝቡን በመምራት ረገድ የተወው ምሳሌ ሁሉም እስራኤላውያን በሙሉ ልባቸው እንዲደግፉት አነሳስቷቸዋል። (1 ዜና 11:1, 2) ዳዊት ምንጊዜም ጠላቶቹን ለማሸነፍ የይሖዋን እርዳታ በመጠየቅ በእሱ ይታመን ነበር። (መዝ. 28:7፤ መዝሙር 138:3ን አንብብ።) ሳዶቅ ሌሎች ግሩም ምሳሌዎችም ነበሩት፤ ከእነዚህ መካከል ዮዳሄና ተዋጊ የነበረው ልጁ በናያህ እንዲሁም ከዳዊት ጎን የቆሙት 22 አለቆች ይገኙበታል። (1 ዜና 11:22-25፤ 12:26-28) እነዚህ ሰዎች በሙሉ የዳዊትን ንግሥና ለመደገፍ ቆራጥ እርምጃ ወስደዋል።

7. (ሀ) በዘመናችን ከእነማን የድፍረት ምሳሌ መማር እንችላለን? (ለ) በቪዲዮው ላይ ከተጠቀሰው ከወንድም ንሲሉ ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

7 በድፍረት ከይሖዋ አገዛዝ ጎን የቆሙ ሰዎችን ምሳሌ መመርመራችን ብርታትና ድፍረት ይሰጠናል። ንጉሣችን ክርስቶስ ኢየሱስ በሰይጣን ፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የተደረገበትን ጫና በጽናት ተቋቁሟል። (ማቴ. 4:8-11፤ ዮሐ. 6:14, 15) ብርታት ለማግኘት ምንጊዜም በይሖዋ ይታመን ነበር። በዘመናችንም በወታደራዊ አገልግሎት ወይም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በድፍረት የገለጹ በርካታ ወጣት ወንድሞች ምሳሌ አለን። ተሞክሯቸውን jw.org ላይ እንድታነብ እናበረታታሃለን። a

ወንድሞችህን እርዳ

8. ሽማግሌዎች ለወንድሞቻቸው ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት ድፍረት የሚያስፈልጋቸው መቼ ሊሆን ይችላል?

8 የይሖዋ ሕዝቦች እርስ በርስ መረዳዳት ያስደስታቸዋል። (2 ቆሮ. 8:4) ይሁንና አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ማድረግ ድፍረት ይጠይቃል። ለምሳሌ ጦርነት በሚቀሰቀስበት ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ማበረታቻ፣ ድጋፍ እንዲሁም መንፈሳዊ ምግብና ቁሳዊ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ይገነዘባሉ። ሽማግሌዎች ለመንጋው ፍቅር ስላላቸው የራሳቸውን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል ቢጠይቅባቸውም እንኳ ወንድሞቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያቀርባሉ። (ዮሐ. 15:12, 13) በዚህ ረገድ ሳዶቅ የተወውን የድፍረት ምሳሌ ይከተላሉ።

9. ሁለተኛ ሳሙኤል 15:27-29 እንደሚገልጸው ዳዊት ሳዶቅን ምን እንዲያደርግ አዘዘው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

9 የዳዊት ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል። ልጁ አቢሴሎም መንግሥቱን ከእሱ ለመንጠቅ ቆርጦ ተነስቷል። (2 ሳሙ. 15:12, 13) ዳዊት ወዲያውኑ ኢየሩሳሌምን ለቆ መውጣት አለበት። አገልጋዮቹን “ተነሱ፣ እንሽሽ፤ አለዚያ አንዳችንም ከአቢሴሎም እጅ አናመልጥም” አላቸው። (2 ሳሙ. 15:14) አገልጋዮቹ እየወጡ ሳሉ ዳዊት አንድ ሰው ኢየሩሳሌም ቀርቶ የአቢሴሎምን ዕቅድ ሊያሳውቀው እንደሚገባ ተገነዘበ። ስለዚህ ሰላዮች እንዲሆኑ ሳዶቅንና ሌሎቹን ካህናት ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ ላካቸው። (2 ሳሙኤል 15:27-29ን አንብብ።) እነዚህ ሰዎች በጣም መጠንቀቅ ነበረባቸው። ዳዊት ለእነዚህ ካህናት የሰጣቸው ሥራ አደገኛ አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን ሊያሳጣቸው የሚችል ነበር። ትዕቢተኛ፣ ቂመኛና ከሃዲ የሆነው አቢሴሎም፣ ሳዶቅና ሌሎቹ ካህናት ለዳዊት ወግነው እየሰለሉት እንደሆነ ቢያውቅ ምን ሊያደርግ እንደሚችል እስቲ አስበው!

ዳዊት ለሳዶቅ አደገኛ ተልእኮ ሰጥቶታል (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)


10. ሳዶቅና አብረውት የነበሩት ሰዎች የዳዊትን ሕይወት የታደጉለት እንዴት ነው?

10 ዳዊት ከሳዶቅና ከሌላ ታማኝ ወዳጁ ከኩሲ ጋር በመተባበር አንድ ዕቅድ አወጣ። (2 ሳሙ. 15:32-37) በዚህ ዕቅድ መሠረት ኩሲ አቢሴሎምን የሚደግፍ መስሎ በመቅረብ ዳዊትን ለማጥቃት የሚያስችል ወታደራዊ ምክረ ሐሳብ አቀረበ፤ ይህ ስልት ዳዊት ቅድመ ዝግጅት የሚያደርግበት ጊዜ ይሰጠዋል። ቀጥሎም ኩሲ ዕቅዱን ለሳዶቅና ለአብያታር ነገራቸው። (2 ሳሙ. 17:8-16) ሁለቱ ሰዎች ደግሞ ለዳዊት መልእክት ላኩበት። (2 ሳሙ. 17:17) በይሖዋ እርዳታ ሳዶቅና ሌሎቹ ካህናት የዳዊትን ሕይወት ለመታደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።—2 ሳሙ. 17:21, 22

11. ወንድሞቻችንን በምንረዳበት ጊዜ የሳዶቅን ድፍረት መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

11 በአደገኛ ወቅት ወንድሞቻችንን እንድንረዳ ከተጠየቅን እንደ ሳዶቅ ዓይነት ድፍረት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (1) መመሪያ ተከተል። እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን አንድነታችንን መጠበቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከቅርንጫፍ ቢሮው ያገኘኸውን መመሪያ ተከተል። (ዕብ. 13:17) ሽማግሌዎች ለአደጋ ከመዘጋጀት እንዲሁም አደጋ ሲከሰት መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች ጋር በተያያዘ ያሉትን መመሪያዎች አዘውትረው መከለስ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮ. 14:33, 40) (2) ደፋር ሆኖም ጠንቃቃ ሁን። (ምሳሌ 22:3) የማመዛዘን ችሎታህን ተጠቀም። ሳያስፈልግ ራስህን አደጋ ላይ አትጣል። (3) በይሖዋ ታመን። ይሖዋ የአንተም ሆነ የወንድሞችህ ደህንነት በጥልቅ እንደሚያሳስበው አስታውስ። ደህንነትህን አደጋ ላይ ሳትጥል ወንድሞችህን እንድትደግፍ ሊረዳህ ይችላል።

12-13. ከቪክቶር እና ከቪታሊ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 በዩክሬን ጦርነት ወቅት ለእምነት አጋሮቻቸው ምግብና ውኃ ለማድረስ ተግተው ይሠሩ የነበሩ ቪክቶር እና ቪታሊ የተባሉ ሁለት ወንድሞችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ቪክቶር እንዲህ ብሏል፦ “ምግብ ለማግኘት ያልፈለግንበት ቦታ አልነበረም። ብዙ ጊዜ በዙሪያችን ተኩስ እንሰማ ነበር። አንድ ወንድም አስቀድሞ ያከማቸውን ምግብ በልግስና ሰጠ። በዚህ ስጦታ ምክንያት በርካታ አስፋፊዎች ለተወሰነ ጊዜ የሚበቃቸውን ምግብ ማግኘት ችለዋል። አንዳንድ ቁሳቁሶችን ወደ መኪናችን እየጫንን ሳለ እኛ ካለንበት 20 ሜትር ርቀት ላይ ቦምብ ፈነዳ። በዚያ ዕለት፣ ወንድሞችን መርዳቴን ለመቀጠል የሚያስችል ድፍረት እንዲሰጠኝ ቀኑን ሙሉ ወደ ይሖዋ ስጸልይ ዋልኩ።”

13 ቪታሊ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታው በጣም ድፍረት የሚጠይቅ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረግኩት ጉዞ 12 ሰዓት ፈጅቶብኛል። መንገዱን ሙሉ ወደ ይሖዋ ስጸልይ ነበር።” ቪታሊ ደፋር ቢሆንም ጠንቃቃም ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ጥበበኛ መሆንና ልኬን ማወቅ እንድችል እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር። የምነዳው ባለሥልጣናቱ በፈቀዷቸው መንገዶች ላይ ብቻ ነው። ወንድሞችና እህቶች ተባብረው የሚሠሩበትን መንገድ በዓይኔ በማየቴ በጣም ተበረታትቻለሁ። ከመንገድ ላይ እንቅፋቶችን ያነሱልን፣ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ይሰበስቡና ይጭኑ እንዲሁም መንገድ ላይ የምንመገበው ምግብና የምናርፍበት ቦታ ያዘጋጁልን ነበር።”

በአደገኛ ወቅት ወንድሞችህን ስትረዳ ደፋር ሆኖም ጠንቃቃ ሁን (አንቀጽ 12-13⁠ን ተመልከት)


ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ ሁን

14. የቤተሰባችን አባል ወይም የቅርብ ጓደኛችን ይሖዋን ሲተው ምን ሊሰማን ይችላል?

14 በሕይወታችን ውስጥ ሊያጋጥሙን ከሚችሉት በጣም ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎች አንዱ የቤተሰባችን አባል ወይም የቅርብ ጓደኛችን ይሖዋን ሲተው ማየት ነው። (መዝ. 78:40፤ ምሳሌ 24:10) ከግለሰቡ ጋር በጣም የምንቀራረብ ከሆነ ደግሞ ሁኔታውን መቀበል የዚያኑ ያህል ከባድ ይሆንብናል። አንተም እንዲህ ያለ ከባድ ፈተና አጋጥሞህ ከሆነ የሳዶቅ የታማኝነት ምሳሌ ሊያበረታታህ ይችላል።

15. ሳዶቅ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ለመቀጠል ድፍረት ያስፈለገው ለምንድን ነው? (1 ነገሥት 1:5-8)

15 ሳዶቅ የቅርብ ጓደኛው አብያታር ታማኝነቱን ባጓደለበት ወቅት ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ሁኔታው የተፈጠረው በዳዊት የግዛት ዘመን መገባደጃ አካባቢ ነው። ይሖዋ ዳዊትን ተክቶ እንዲነግሥ የመረጠው ሰለሞንን ቢሆንም ዳዊት መሞቻው በተቃረበበት ወቅት ልጁ አዶንያስ ዙፋኑን ለመውሰድ አሰበ። (1 ዜና 22:9, 10) አብያታር አዶንያስን ለመደገፍ መረጠ። (1 ነገሥት 1:5-8ን አንብብ።) አብያታር እንዲህ ማድረጉ ለዳዊት ብቻ ሳይሆን ለይሖዋም ታማኝ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። ሳዶቅ ይህን ሲያይ ምን ያህል አዝኖ እንደሚሆን መገመት ትችላለህ? እሱና አብያታር ከ40 ዓመት በላይ አብረው በክህነት አገልግለዋል። (2 ሳሙ. 8:17) ‘ከእውነተኛው አምላክ ታቦት’ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አብረው ያከናውኑ ነበር። (2 ሳሙ. 15:29) ሁለቱም መጀመሪያ ላይ የዳዊትን ንግሥና ደግፈዋል፤ ሌሎች ብዙ ነገሮችንም አብረው አከናውነዋል።—2 ሳሙ. 19:11-14

16. ሳዶቅ ታማኝነቱን እንዲጠብቅ የረዳው ምን ሊሆን ይችላል?

16 አብያታር ታማኝነቱን ቢያጓድልም ሳዶቅ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ዳዊት የሳዶቅን ታማኝነት ተጠራጥሮ አያውቅም። የአዶንያስ ሴራ ሲጋለጥ ዳዊት ሰለሞንን ንጉሥ አድርገው እንዲቀቡት ሳዶቅን፣ ናታንን እና በናያህን ጠየቃቸው። (1 ነገ. 1:32-34) ሳዶቅ እንደ ናታን እና እንደ ሌሎቹ የንጉሥ ዳዊት ደጋፊዎች ካሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር አብሮ መሆኑ አጠናክሮትና አበረታቶት መሆን አለበት። (1 ነገ. 1:38, 39) ሰለሞን ንጉሥ ከሆነ በኋላ “በአብያታር ቦታ . . . ካህኑን ሳዶቅን ሾመው።”—1 ነገ. 2:35

17. አንድ የምትቀርበው ሰው ይሖዋን ለመተው ከመረጠ የሳዶቅን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?

17 አንተስ የሳዶቅን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? አንድ የምትቀርበው ሰው ይሖዋን ለመተው ከመረጠ አንተ ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን መምረጥህን በግልጽ አሳይ። (ኢያሱ 24:15) ይሖዋ የሚያስፈልግህን ብርታትና ድፍረት ይሰጥሃል። ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ እንዲሁም ከሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር ተቀራረብ። ይሖዋ ታማኝነትህን ከፍ አድርጎ ይመለከታል፤ ወሮታህንም ይከፍልሃል።—2 ሳሙ. 22:26

18. ከማርኮ እና ከሲድሴ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

18 የማርኮን እና የባለቤቱን የሲድሴን ምሳሌ እንመልከት። ሁለት ሴቶች ልጆቻቸው ራሳቸውን ከቻሉ በኋላ ይሖዋን ማገልገላቸውን አቆሙ። ማርኮ እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆች ልጆቻቸው ከተወለዱበት ዕለት አንስቶ በጣም ይወዷቸዋል። ልጆቻቸውን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲሉ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው። ስለዚህ ልጆቻቸው ይሖዋን ለመተው ሲመርጡ ቅስማቸው ይሰበራል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ሆኖም ይሖዋ ከጎናችን አልተለየም። እኔ በምደክምበት ጊዜ ባለቤቴ ጠንካራ እንድትሆን፣ እሷ በምትደክምበት ጊዜ ደግሞ እኔ ጠንካራ እንድሆን አድርጓል።” ሲድሴ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የሚያስፈልገንን ጥንካሬ ባይሰጠን ኖሮ መጽናት አንችልም ነበር። ልጆቻችን ይሖዋን የተዉት በእኔ ጥፋት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፤ ስለዚህ ስሜቴን ለይሖዋ ነገርኩት። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለበርካታ ዓመታት አግኝቻት የማላውቃት አንዲት እህት ወደ እኔ መጥታ እጇን ትከሻዬ ላይ አደረገችና ዓይን ዓይኔን እያየች ‘ሲድሴ አስታውሺ፣ የአንቺ ጥፋት አይደለም’ አለችኝ። በይሖዋ እርዳታ ደስታዬን ጠብቄ እሱን ማገልገል ችያለሁ።”

19. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

19 ይሖዋ ሁሉም አገልጋዮቹ እንደ ሳዶቅ ደፋር እንዲሆኑ ይፈልጋል። (2 ጢሞ. 1:7) ይሁንና በራሳችን ብርታት እንድንታመን አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ በእሱ እንድንታመን ይፈልጋል። እንግዲያው ድፍረት የሚጠይቅ ሁኔታ ሲያጋጥምህ የይሖዋን እርዳታ ጠይቅ። እንደ ሳዶቅ ደፋር እንድትሆን እንደሚረዳህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ!—1 ጴጥ. 5:10

መዝሙር 126 ነቅተህ ኑር፣ ጸንተህ ቁም፣ በርታ