በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 30

መዝሙር 36 ልባችንን እንጠብቅ

ከእስራኤል ነገሥታት የምናገኛቸው ጠቃሚ ትምህርቶች

ከእስራኤል ነገሥታት የምናገኛቸው ጠቃሚ ትምህርቶች

“በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ዳግመኛ ታያላችሁ።”ሚል. 3:18

ዓላማ

ይሖዋ ለእስራኤል ነገሥታት ስለነበረው አመለካከት መማራችን በዛሬው ጊዜ ካሉ አገልጋዮቹ ምን እንደሚጠብቅ ለማስተዋል ይረዳናል።

1-2. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንዳንዶቹ የእስራኤል ነገሥታት ምን ይነግረናል?

 መጽሐፍ ቅዱስ በእስራኤል ላይ ነገሥታት ሆነው ስለገዙ ከ40 የሚበልጡ ሰዎች ይናገራል። a ዘገባው አንዳንዶቹን ነገሥታት በተመለከተ ትኩረት የሚስቡ ዝርዝር መረጃዎችን ይሰጠናል። ለምሳሌ ጥሩዎቹ ነገሥታትም አንዳንድ መጥፎ ነገሮችን አድርገዋል። ጥሩ ንጉሥ የነበረውን ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይሖዋ ‘አገልጋዬ ዳዊት በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር ብቻ በማድረግ በሙሉ ልቡ ተከትሎኛል’ ብሏል። (1 ነገ. 14:8) ያም ቢሆን ዳዊት ባለትዳር ከሆነች ሴት ጋር የፆታ ብልግና ፈጽሟል፤ እንዲሁም ባሏ በጦርነት ላይ እንዲገደል ሴራ ጠንስሷል።—2 ሳሙ. 11:4, 14, 15

2 በሌላ በኩል ደግሞ ታማኝ ካልነበሩት ነገሥታት መካከል ብዙዎቹ አንዳንድ ጥሩ ነገሮችን አድርገዋል። ሮብዓምን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሮብዓም በይሖዋ ዓይን ‘ክፉ ነገር አድርጓል።’ (2 ዜና 12:14) ያም ቢሆን ሮብዓም፣ አምላክ አሥሩ ነገዶች ከመንግሥቱ እንዲገነጠሉ የሰጠውን ትእዛዝ አክብሯል። በተጨማሪም የተመሸጉ ከተሞችን በመገንባት ብሔሩን የሚጠቅም ነገር አድርጓል።—1 ነገ. 12:21-24፤ 2 ዜና 11:5-12

3. የትኛው ወሳኝ ጥያቄ ይነሳል? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ይህ አንድ ወሳኝ ጥያቄ ያስነሳል። የእስራኤል ነገሥታት ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገሮችን ካደረጉ ይሖዋ አንድን ንጉሥ በእሱ ዓይን ታማኝ አድርጎ የሚመለከተው ምንን መሠረት አድርጎ ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምን እንደሆነ ለማስተዋል ይረዳናል። ይሖዋ የእስራኤልን ነገሥታት ሲመዝን ከግምት ያስገባቸውን ሦስት ነገሮች እንመለከታለን፦ የልባቸውን ሁኔታ፣ ንስሐ መግባት አለመግባታቸውን እንዲሁም እውነተኛውን አምልኮ የሙጥኝ ማለታቸውን።

በሙሉ ልባቸው ይሖዋን አገልግለዋል

4. በታማኞቹና ታማኝ ባልሆኑት ነገሥታት መካከል ያለው አንዱ ልዩነት ምንድን ነው?

4 ይሖዋን ያስደሰቱት ነገሥታት እሱን በሙሉ ልባቸው b አገልግለውታል። ጥሩው ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ‘ይሖዋን በሙሉ ልቡ ፈልጓል።’ (2 ዜና 22:9) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢዮስያስ ሲናገር “በሙሉ ልቡ . . . ወደ ይሖዋ የተመለሰ እንደ እሱ ያለ ንጉሥ ከእሱ በፊት አልነበረም” ይላል። (2 ነገ. 23:25) በስተ እርጅናው መጥፎ ነገር ስለሠራው ስለ ሰለሞንስ ምን ማለት ይቻላል? “[ልቡ] በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ አልነበረም።” (1 ነገ. 11:4) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ንጉሥ ስላልነበረው ስለ አብያም ሲናገር “[ልቡ] በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ አልነበረም” ይላል።—1 ነገ. 15:3

5. ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገል ሲባል ምን ማለት እንደሆነ አብራራ።

5 ለመሆኑ ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገል ሲባል ምን ማለት ነው? ልቡ ሙሉ የሆነ ሰው ይሖዋን የሚያመልከው በዘልማድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክን የሚያገለግለው በፍቅርና በታማኝነት ተነሳስቶ ነው። በተጨማሪም በመላው ሕይወቱ ለይሖዋ ያለውን ፍቅርና ታማኝነት ይዞ ይቀጥላል።

6. ሙሉ ልብ ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 4:23፤ ማቴዎስ 5:29, 30)

6 የታማኞቹን ነገሥታት ምሳሌ በመከተል ሙሉ ልብ ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ከመጥፎ ተጽዕኖዎች በመራቅ ነው። ለምሳሌ ጤናማ ያልሆነ መዝናኛ ልባችንን ሊከፍለው ይችላል። መጥፎ ጓደኝነትና ፍቅረ ነዋይም ተመሳሳይ ውጤት ሊያስከትሉ ይችላሉ። አንድ ነገር ለይሖዋ ያለንን ፍቅር እያዳከመው እንዳለ ካስተዋልን ይህን ተጽዕኖ ለማስወገድ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።—ምሳሌ 4:23፤ ማቴዎስ 5:29, 30ን አንብብ።

7. ከመጥፎ ተጽዕኖዎች መራቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7 ልባችን እንዲከፈል ልንፈቅድ አይገባም። ካልተጠነቀቅን፣ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እስከተጠመድን ድረስ ከመጥፎ ተጽዕኖዎች መራቅ እንደማያስፈልገን በማሰብ ራሳችንን ልናታልል እንችላለን። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ኃይለኛ ነፋስና ብርድ ባለበት ቀን ወደ ደጅ ወጥተሃል እንበል። ቤት ስትገባ ማሞቂያ ታበራለህ። ይሁንና በሩን ክፍት ከተውከው ማሞቂያ ማብራትህ ምን ያህል ይጠቅምሃል? ቀዝቃዛው አየር ወዲያውኑ ቤትህን ይሞላዋል። ነጥቡ ምንድን ነው? ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት የሚያሞቅ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችን ብቻውን በቂ አይደለም። የዚህ ዓለም ቀዝቃዛ “አየር” ወይም ዓለማዊ ዝንባሌ ወደ ልባችን ገብቶ እንዳይከፍለው ለመጥፎ ተጽዕኖዎች ልባችንን መዝጋት ይኖርብናል።—ኤፌ. 2:2

ከኃጢአታቸው ንስሐ ገብተዋል

8-9. ንጉሥ ዳዊትና ንጉሥ ሕዝቅያስ ለተሰጣቸው ተግሣጽ ምን ምላሽ ሰጥተዋል? (ሥዕሉን ተመልከት።)

8 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ንጉሥ ዳዊት ከባድ ኃጢአት ፈጽሟል። ሆኖም በሠራው ኃጢአት ምክንያት ነቢዩ ናታን ሲገሥጸው በትሕትና ንስሐ ገባ። (2 ሳሙ. 12:13) በመዝሙር 51 ላይ የተናገራቸው ቃላት ንስሐ የገባው ከልቡ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ዳዊት ናታንን ለማታለል ወይም ከቅጣት ለማምለጥ ብሎ የተጸጸተ ለማስመሰል ከመሞከር ይልቅ ከልቡ ንስሐ ገብቷል።—መዝ. 51:3, 4, 17 እና አናት ላይ ያለው መግለጫ

9 ንጉሥ ሕዝቅያስም በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርቷል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቅያስ ልቡ ታብዮ ስለነበር [የአምላክ] ቁጣ በእሱ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ መጣ።” (2 ዜና 32:25) ሕዝቅያስ ልቡ የታበየው ለምንድን ነው? ሀብት በማካበቱ፣ በአሦራውያን ላይ ድል በመቀዳጀቱ ወይም ከሕመሙ በተአምራዊ መንገድ ፈውስ በማግኘቱ ተኩራርቶ ሊሆን ይችላል። ሀብቱን ለባቢሎናውያን ለማሳየት ያነሳሳው ኩራት ሊሆን ይችላል፤ በዚህም የተነሳ ነቢዩ ኢሳይያስ ገሥጾታል። (2 ነገ. 20:12-18) ሆኖም እንደ ዳዊት ሁሉ ሕዝቅያስም በትሕትና ንስሐ ገባ። (2 ዜና 32:26) ይሖዋም እሱን ‘በፊቱ ትክክል የሆነውን ነገር ያደረገ’ ታማኝ ንጉሥ አድርጎ ተመልክቶታል።—2 ነገ. 18:3

ንጉሥ ዳዊትና ንጉሥ ሕዝቅያስ በኃጢአታቸው የተነሳ ተግሣጽ ከተሰጣቸው በኋላ በትሕትና ንስሐ ገብተዋል (አንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)


10. ንጉሥ አሜስያስ እርማት ሲሰጠው ምን አደረገ?

10 በሌላ በኩል ደግሞ የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ትክክል የሆነውን ነገር ቢያደርግም “በሙሉ ልቡ አልነበረም።” (2 ዜና 25:2) ጥፋቱ ምንድን ነው? ይሖዋ ኤዶማውያንን ድል እንዲያደርግ ከረዳው በኋላ አሜስያስ ለአማልክታቸው ሰገደ። c ከዚያም የይሖዋ ነቢይ ተግሣጽ ሲሰጠው ንጉሡ ልቡን በማደንደን ነቢዩን አባረረው።—2 ዜና 25:14-16

11. በ2 ቆሮንቶስ 7:9, 11 መሠረት የይሖዋን ይቅርታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

11 ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን እንማራለን? ከኃጢአታችን ንስሐ መግባትና ስህተታችንን ላለመድገም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለብን። ይሁንና ቀላል በሚመስሉ ጉዳዮችም ቢሆን የጉባኤ ሽማግሌዎች ምክር ቢሰጡንስ? ይሖዋም ሆነ ሽማግሌዎች እንደማይወዱን ሊሰማን አይገባም። ጥሩዎቹ የእስራኤል ነገሥታትም እንኳ ምክርና ተግሣጽ ተሰጥቷቸዋል። (ዕብ. 12:6) እርማት ሲሰጠን (1) ምክሩን በትሕትና መቀበል፣ (2) አስፈላጊዎቹን ማስተካከያዎች ማድረግ እንዲሁም (3) በሙሉ ልባችን ይሖዋን ማገልገላችንን መቀጠል ይኖርብናል። ከኃጢአታችን ንስሐ ከገባን ይሖዋ ይቅር ይለናል።—2 ቆሮንቶስ 7:9, 11ን አንብብ።

እርማት ሲሰጠን (1) ምክሩን በትሕትና መቀበል፣ (2) አስፈላጊዎቹን ማስተካከያዎች ማድረግ እንዲሁም (3) በሙሉ ልባችን ይሖዋን ማገልገላችንን መቀጠል ይኖርብናል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) f


እውነተኛውን አምልኮ የሙጥኝ ብለዋል

12. ታማኞቹ ነገሥታት በዋነኝነት ተለይተው የሚታወቁት በምን ነበር?

12 ይሖዋ ታማኝ አድርጎ የቆጠራቸው ነገሥታት እውነተኛውን አምልኮ የሙጥኝ ብለዋል። ሕዝቡም እንዲሁ እንዲያደርግ አበረታተዋል። እርግጥ ነው፣ እስካሁን እንደተመለከትነው እነዚህ ነገሥታት አንዳንድ ስህተቶችን ሠርተዋል። ያም ቢሆን ይሖዋን ብቻ አምልከዋል፤ እንዲሁም የጣዖት አምልኮን ከምድሪቱ ለማስወገድ ከፍተኛ ትግል አድርገዋል። d

13. ይሖዋ ንጉሥ አክዓብን ታማኝ እንዳልሆነ አድርጎ የቆጠረው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ ታማኝ እንዳልሆኑ አድርጎ የቆጠራቸው ነገሥታትስ? ያደረጉት ነገር ሁሉ መጥፎ እንዳልነበር የታወቀ ነው። ክፉው ንጉሥ አክዓብም እንኳ በተወሰነ መጠን ትሕትና በማሳየት በናቡቴ ግድያ ለተጫወተው ሚና በመጠኑ ተጸጽቷል። (1 ነገ. 21:27-29) በተጨማሪም ከተሞችን የገነባ ከመሆኑም ሌላ እስራኤላውያን አንዳንድ ድሎችን እንዲያገኙ አድርጓል። (1 ነገ. 20:21, 29፤ 22:39) ያም ቢሆን አክዓብ በሚስቱ ተጽዕኖ ሥር ሆኖ የሐሰት አምልኮን በማስፋፋት ከባድ ኃጢአት ፈጽሟል። ለዚህ ኃጢአቱ ደግሞ ንስሐ አልገባም።—1 ነገ. 21:25, 26

14. (ሀ) ይሖዋ ንጉሥ ሮብዓምን ታማኝ እንዳልሆነ አድርጎ የቆጠረው ለምንድን ነው? (ለ) ታማኝ ያልሆኑት ነገሥታት ተለይተው የሚታወቁት በምን ነበር?

14 ታማኝ ካልነበሩት ነገሥታት መካከል የሮብዓምን ምሳሌም እንመልከት። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሮብዓም በግዛት ዘመኑ አንዳንድ መልካም ነገሮችን አድርጓል። ሆኖም ንግሥናው በጸና ጊዜ የይሖዋን ሕግ ትቶ በሐሰት አምልኮ መካፈል ጀመረ። (2 ዜና 12:1) ከዚያ በኋላም በእውነተኛው አምልኮና በሐሰት አምልኮ መካከል ሲወላውል ኖሯል። (1 ነገ. 14:21-24) ከእውነተኛው አምልኮ የራቁት ነገሥታት ሮብዓምና አክዓብ ብቻ አይደሉም። እንዲያውም ታማኝ ካልነበሩት ነገሥታት መካከል አብዛኞቹ በሆነ መንገድ የሐሰት አምልኮን ደግፈዋል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ አንድ ንጉሥ በይሖዋ ዓይን ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑ በዋነኝነት የሚወሰነው እውነተኛውን አምልኮ የሙጥኝ በማለቱ ነበር።

15. እውነተኛውን አምልኮ የሙጥኝ ማለት በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው?

15 ይሖዋ ለአምልኮ ጉዳይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ነገሥታቱ የአምላክ ሕዝቦች በእውነተኛው አምልኮ እንዲካፈሉ ግንባር ቀደም ሆነው የመርዳት ኃላፊነት ነበረባቸው። ከዚህም ሌላ፣ የሐሰት አምልኮ ወደ ሌሎች ኃጢአቶችና ኢፍትሐዊ ድርጊቶች መምራቱ አይቀርም። (ሆሴዕ 4:1, 2) ይህ ብቻ ሳይሆን ነገሥታቱና ተገዢዎቻቸው ለይሖዋ የተወሰኑ ሰዎች ነበሩ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎች በሐሰት አምልኮ መካፈላቸውን ከምንዝር ጋር ያመሳስለዋል። (ኤር. 3:8, 9) ቃል በቃል ምንዝር የሚፈጽም ሰው የትዳር አጋሩን በቀጥታ ይበድላል። በተመሳሳይም ለይሖዋ የተወሰነ አንድ ሰው በሐሰት አምልኮ ሲካፈል እሱን በቀጥታ ይበድለዋል። eዘዳ. 4:23, 24

16. በይሖዋ ዓይን በጻድቅና በክፉ ሰው መካከል ያለው ዋነኛ ልዩነት ምንድን ነው?

16 ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከሐሰት አምልኮ ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ እንዳለብን የታወቀ ነው። ግን ይህ ብቻ ሳይሆን እውነተኛውን አምልኮ የሙጥኝ ማለትና በእውነተኛው አምልኮ በቅንዓት ተሳትፎ ማድረግ ይኖርብናል። ነቢዩ ሚልክያስ አንድን ሰው በይሖዋ ዓይን ጥሩ ወይም መጥፎ የሚያስብለው ምን እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ዳግመኛ ታያላችሁ።” (ሚል. 3:18) በመሆኑም አለፍጽምናችንን እና ስህተቶቻችንን ጨምሮ ማንኛውም ነገር ተስፋ እንዲያስቆርጠንና አምላክን ማገልገላችንን እንድናቆም እንዲያደርገን መፍቀድ አይኖርብንም። ይሖዋን ማገልገላችንን ማቆም በራሱ ከባድ ኃጢአት ነው።

17. የትዳር ጓደኛ ምርጫችን ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ የሚነካው እንዴት ነው?

17 ለማግባት እያሰብክ ከሆነ፣ ሚልክያስ አምላክን ስለማገልገል የተናገረው ሐሳብ በትዳር ጓደኛ ምርጫህ ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ልብ ብለሃል? አንድ ሰው አንዳንድ መልካም ባሕርያት ሊኖሩት ይችላሉ። ይሁንና ይህ ሰው እውነተኛውን አምላክ የማያገለግል ከሆነ ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት በይሖዋ ዓይን ጻድቅ ተደርጎ ይቆጠራል? (2 ቆሮ. 6:14) እንዲህ ያለውን ሰው ብናገባ ግለሰቡ በመንፈሳዊነታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል? እስቲ አስበው፦ የንጉሥ ሰለሞን ሚስቶች አንዳንድ መልካም ባሕርያት ሊኖሯቸው ይችላሉ። ሆኖም የይሖዋ አገልጋዮች አልነበሩም፤ በመሆኑም የሰለሞን ልብ ቀስ በቀስ ወደ ሐሰት አምልኮ እንዲያዘነብል አድርገዋል።—1 ነገ. 11:1, 4

18. ወላጆች ለልጆቻቸው ምን ሊያስተምሯቸው ይገባል?

18 ወላጆች፣ ስለ ነገሥታት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ተጠቅማችሁ ልጆቻችሁ ለይሖዋ አምልኮ ቅንዓት እንዲያድርባቸው መርዳት ትችላላችሁ። ይሖዋ በዋነኝነት አንድን ንጉሥ ጥሩ ወይም መጥፎ አድርጎ የሚቆጥረው ‘እውነተኛውን አምልኮ አስፋፍቷል ወይ’ የሚለውን መሠረት አድርጎ እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዷቸው። መጽሐፍ ቅዱስን እንደማንበብ፣ በስብሰባዎች ላይ እንደመገኘትና በአገልግሎት እንደመካፈል ያሉ መንፈሳዊ ነገሮች ከሌሎች እንቅስቃሴዎች ሁሉ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ለልጆቻችሁ በንግግርም ሆነ በተግባር አስተምሯቸው። (ማቴ. 6:33) አለዚያ ልጆቻችሁ የይሖዋ ምሥክር መሆን ማለት እንዲሁ “የቤተሰባቸውን ሃይማኖት” መከተል እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። በዚህም የተነሳ ለእውነተኛው አምልኮ ሁለተኛ ቦታ ሊሰጡ ይባስ ብሎም ከናካቴው ሊተዉት ይችላሉ።

19. ይሖዋን ማገልገላቸውን ያቆሙ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው? (“ ወደ ይሖዋ መመለስ ትችላለህ!” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

19 አንድ ሰው ይሖዋን ማገልገሉን ካቆመ ምንም ተስፋ የለውም ማለት ነው? አይደለም። ምክንያቱም ንስሐ መግባትና በእውነተኛው አምልኮ መካፈሉን መቀጠል ይችላል። እንዲህ ማድረግ ከፈለገ ኩራቱን ዋጥ አድርጎ ከጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ መቀበል ያስፈልገው ይሆናል። (ያዕ. 5:14) የይሖዋን ሞገስ መልሶ ማግኘት ምንም ያህል ጥረት ቢደረግለት አያስቆጭም!

20. የታማኞቹን ነገሥታት ምሳሌ ከተከተልን ይሖዋ እንዴት አድርጎ ይመለከተናል?

20 እስካሁን ከእስራኤል ነገሥታት የትኞቹን ትምህርቶች አግኝተናል? ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደረ ልብ ካለን እንደ ታማኞቹ ነገሥታት መሆን እንችላለን። ከስህተታችን እንማር፤ ንስሐ እንግባ፤ እንዲሁም አስፈላጊውን ማስተካከያ እናድርግ። ከዚህም ሌላ፣ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆነውን የይሖዋን አምልኮ የሙጥኝ ማለት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ምንጊዜም እናስታውስ። ለይሖዋ ያለህን ታማኝነት ከጠበቅክ አንተንም በእሱ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር እንደምታደርግ አድርጎ ይመለከትሃል።

መዝሙር 45 በልቤ የማሰላስለው ነገር

a በዚህ ርዕስ ውስጥ “የእስራኤል ነገሥታት” የሚለው አገላለጽ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ የገዙትን ነገሥታት በሙሉ ያመለክታል። ይህም ሁለቱን ነገዶች ባቀፈው የይሁዳ መንግሥት፣ አሥሩን ነገዶች ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት እንዲሁም በ12ቱም ነገዶች ላይ የነገሡትን ነገሥታት ይጨምራል።

b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙውን ጊዜ “ልብ” የሚለው ቃል የአንድን ሰው ምኞት፣ አስተሳሰብ፣ ዝንባሌ፣ አመለካከት፣ ችሎታ፣ ተነሳሽነትና ግብ ጨምሮ ውስጣዊ ማንነቱን በሙሉ ለማመልከት ተሠርቶበታል።

c ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ አረማዊ ነገሥታት ድል ያደረጓቸውን ብሔራት አማልክት የማምለክ ልማድ ነበራቸው።

d ንጉሥ አሳ ከባድ ኃጢአቶችን ፈጽሟል። (2 ዜና 16:7, 10) ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሰው በአዎንታዊ መንገድ ነው። የተሰጠውን እርማት መጀመሪያ ላይ ባይቀበልም ከጊዜ በኋላ ንስሐ ገብቶ ሊሆን ይችላል። በጥቅሉ ሲታይ መልካም ባሕርያቱ ከስህተቶቹ ይበልጡ ነበር። አሳ ይሖዋን ብቻ ማምለኩን እንዲሁም ከመንግሥቱ የጣዖት አምልኮን ለማስወገድ ጥረት ማድረጉን ልብ ማለት ያስፈልጋል።—1 ነገ. 15:11-13፤ 2 ዜና 14:2-5

e ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል የመጀመሪያዎቹ ሁለት ትእዛዛት እስራኤላውያን ከይሖዋ በቀር ማንኛውንም አካል ወይም ማንኛውንም ነገር ማምለክ እንደሌለባቸው የሚገልጹ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።—ዘፀ. 20:1-6

f የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወጣት የጉባኤ ሽማግሌ ለአንድ ወንድም የመጠጥ ልማዱን አስመልክቶ ምክር ይሰጠዋል። ወንድም የተሰጠውን ምክር በትሕትና ይቀበላል፤ አስፈላጊውን ማስተካከያ ያደርጋል፤ እንዲሁም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን ይቀጥላል