በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 29

መዝሙር 121 ራሳችንን መግዛት ያስፈልገናል

ከፈተና ራስህን ጠብቅ

ከፈተና ራስህን ጠብቅ

“ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ።”ማቴ. 26:41

ዓላማ

ከኃጢአት እንዲሁም ወደ ኃጢአት ከሚመሩት እርምጃዎች መራቅ ያለውን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ መርዳት።

1-2. (ሀ) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ ለድክመታቸው እጅ የሰጡት ለምንድን ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

 “መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” a (ማቴ. 26:41ለ) ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ፍጹማን አለመሆናችንን እንደሚረዳ ያሳያሉ። ሆኖም እነዚህ ቃላት ማስጠንቀቂያም ይዘዋል፦ ከልክ በላይ በራሳችሁ አትተማመኑ። በዚያ ምሽት ደቀ መዛሙርቱ ከጌታቸው ላለመለየት ቁርጠኛ እንደሆኑ በልበ ሙሉነት ገልጸው ነበር። (ማቴ. 26:35) ሐሳባቸው ጥሩ ነው። ያም ቢሆን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ በፍጥነት ሊዳከሙ እንደሚችሉ አልተገነዘቡም። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው፦ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ።”—ማቴ. 26:41ሀ

2 የሚያሳዝነው፣ ደቀ መዛሙርቱ ነቅተው ሳይጠብቁ ቀርተዋል። ኢየሱስ በተያዘበት ወቅት ከእሱ ጎን ቆሙ? ወይስ ለፈተና እጅ በመስጠት ጥለውት ሸሹ? ደቀ መዛሙርቱ ነቅተው ስላልጠበቁ ፈጽሞ እንደማያደርጉ የተናገሩትን ነገር አደረጉ፤ ኢየሱስን ጥለውት ሸሹ።—ማቴ. 26:56

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ንቁ እንዲሆኑና ከፈተና ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧቸዋል፤ እነሱ ግን ጥለውት ሸሹ (አንቀጽ 1-2⁠ን ተመልከት)


3. (ሀ) ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት መጠበቅ ከፈለግን ከልክ በላይ በራሳችን ከመተማመን መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ከልክ በላይ በራሳችን መተማመን የለብንም። እርግጥ ነው፣ ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቀን ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። ያም ቢሆን ፍጹማን ስላልሆንን በፈተና ልንሸነፍ እንችላለን። (ሮም 5:12፤ 7:21-23) ሳናስበው፣ የተሳሳተ ጎዳና መከተል አጓጊ መስሎ እንዲታየን የሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ለይሖዋና ለልጁ ያለንን ታማኝነት መጠበቅ ከፈለግን ኢየሱስ በኃጢአት ፈተና እንዳንወድቅ ራሳችንን እንድንጠብቅ የሰጠውን ምክር መከተል ይኖርብናል። ይህ ርዕስ እንዲህ ለማድረግ ይረዳናል። በመጀመሪያ፣ መጠንቀቅ ያለብን በተለይ በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚያም ከፈተና ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። በመጨረሻም ምንጊዜም ነቅተን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን።

ነቅተህ ጠብቅ—በየትኞቹ አቅጣጫዎች?

4-5. ቀላል ከሚመስሉ ኃጢአቶችም እንኳ መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?

4 በአንጻራዊ ሁኔታ ቀላል የሚመስሉ ኃጢአቶችም እንኳ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያዳክሙት ይችላሉ። በተጨማሪም ይበልጥ ከባድ የሆኑ ኃጢአቶችን ወደመፈጸም ሊመሩን ይችላሉ።

5 ሁላችንም ኃጢአት የመፈጸም ዝንባሌ ይፈታተነናል። ሆኖም እያንዳንዳችን ደካማ የሆንበት አቅጣጫ ይለያያል፤ ስለዚህ የሚፈትነን ነገር የተለያየ ነው። ለምሳሌ አንዳንዶች እንደ ፆታ ብልግና ያለ ከባድ ኃጢአት ለመፈጸም ከሚያድርባቸው ግፊት ጋር ይታገላሉ። ሌሎች ደግሞ እንደ ማስተርቤሽን ወይም ፖርኖግራፊ እንደመመልከት ያሉ ርኩስ ልማዶችን ለመፈጸም ይፈተናሉ። ሰውን እንደመፍራት፣ በራስ እንደመመራት ወይም እንደ ቁጣ ካሉ ዓለማዊ አስተሳሰቦች ጋር የሚታገሉም አሉ። ያዕቆብ እንዳለው “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል።”—ያዕ. 1:14

6. ስለ ምን ጉዳይ ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል?

6 አንተ በቀላሉ የምትፈተነው በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ ታውቃለህ? ድክመቶቻችንን ችላ በማለት ወይም በመንፈሳዊ ጠንካራ ስለሆንን ኃጢአት ልንፈጽም እንደማንችል በማሰብ ራሳችንን ማታለላችን አይጠቅመንም። (1 ዮሐ. 1:8) ደግሞም ጳውሎስ እንደተናገረው ‘መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው’ ሰዎችም እንኳ ካልተጠነቀቁ ለፈተና እጅ ሊሰጡ ይችላሉ። (ገላ. 6:1) ራሳችንን በሐቀኝነት በመመርመር ጠንካራ ያልሆንባቸውን አቅጣጫዎች አምነን መቀበል ይኖርብናል።—2 ቆሮ. 13:5

7. ለየትኛው ነገር ለየት ያለ ትኩረት ልንሰጥ ይገባል? በምሳሌ አስረዳ።

7 ለፈተና ተጋላጭ የሆንባቸውን አቅጣጫዎች ለይተን ካወቅን በኋላ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የመከላከል አቅማችንን ማጠናከር ይኖርብናል! ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የአንዲት ከተማ ቅጥር ይበልጥ ለጥቃት ተጋላጭ የሚሆነው በሮቹ ላይ ነበር። በመሆኑም ከየትኛውም የቅጥሩ ክፍል ይበልጥ ብዙ ጠባቂዎች የሚመደቡት በሮቹ ላይ ነው። እኛም በተመሳሳይ ደካማ ለሆንባቸው አቅጣጫዎች ለየት ያለ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል።—1 ቆሮ. 9:27

ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

8-9. በምሳሌ ምዕራፍ 7 ላይ የተጠቀሰው ወጣት ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም ሊቆጠብ የሚችለው ምን ቢያደርግ ነበር? (ምሳሌ 7:8, 9, 13, 14, 21)

8 ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? በምሳሌ ምዕራፍ 7 ላይ ከተጠቀሰው ወጣት ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት። ይህ ወጣት ከአንዲት ባለጌ ሴት ጋር የፆታ ብልግና ፈጽሟል። ቁጥር 22 ወጣቱ ይህችን ሴት “በድንገት” እንደተከተላት ይናገራል። ሆኖም ያለፉት ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ቀስ በቀስ ወደ ኃጢአት የመሩት ከዚያ በፊት የወሰዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች ናቸው።

9 ይህ ወጣት ኃጢአት ከመፈጸሙ በፊት የትኞቹን ነገሮች አድርጓል? በመጀመሪያ፣ ምሽት ላይ በዚህች ሴትዮ ቤት ‘አቅራቢያ በሚገኝ መታጠፊያ አልፏል።’ ከዚያም ወደ ቤቷ አቅጣጫ አመራ። (ምሳሌ 7:8, 9ን አንብብ።) ቀጥሎም ሴትየዋን ሲያያት አካባቢውን ጥሎ አልሄደም። ከዚህ ይልቅ እንድትስመው ፈቀደላት፤ እንዲሁም ስላቀረበችው የኅብረት መሥዋዕት ስትናገር አዳመጣት፤ ይህን ያለችው መጥፎ ሰው እንዳልሆነች እንዲሰማው ለማድረግ ብላ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 7:13, 14, 21ን አንብብ።) ወጣቱ ወደ ኃጢአት ከመሩት አደገኛ ሁኔታዎች ቢርቅ ኖሮ በፈተና ከመውደቅና ኃጢአት ከመፈጸም ራሱን መጠበቅ ይችል ነበር።

10. በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰውን ወጣት ዓይነት ስህተት ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው?

10 ሰለሞን የጻፈው ዘገባ ማንኛውም የይሖዋ አገልጋይ ምን ሊያጋጥመው እንደሚችል ያሳያል። ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ ሁሉም ነገር “በድንገት” እንደተከሰተ ሊሰማው ይችላል። ወይም ደግሞ “ሳላስበው ነው የሆነው” ይል ይሆናል። ያም ቢሆን፣ ቆም ብሎ ካሰበበት ኃጢአት ወደመፈጸም የመራው ጥበብ የጎደላቸውን አንዳንድ እርምጃዎች መውሰዱ እንደሆነ መገንዘቡ አይቀርም። ምናልባትም ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ገጥሞ፣ ጤናማ ባልሆነ መዝናኛ መካፈል ጀምሮ ወይም በአካልም ሆነ በኢንተርኔት አማካኝነት አጠያያቂ የሆኑ ቦታዎችን ማዘውተር ጀምሮ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ መጸለዩን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቡን፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘቱን ወይም በአገልግሎት መካፈሉን አቁሞ ሊሆን ይችላል። በምሳሌ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው ወጣት ሁሉ እሱም ኃጢአት የፈጸመው “በድንገት” ላይሆን ይችላል።

11. በኃጢአት እንዳንወድቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

11 ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከኃጢአት ብቻ ሳይሆን ወደ ኃጢአት ከሚመሩት እርምጃዎችም መራቅ ይኖርብናል። ሰለሞን ስለ ወጣቱና ስለ ባለጌዋ ሴት የሚገልጸውን ታሪክ ከተናገረ በኋላ ይህን ነጥብ ግልጽ አድርጓል። ስለ ሴትየዋ ሲናገር “መንገድ ስታችሁ ወደ ጎዳናዋ አትግቡ” ብሏል። (ምሳሌ 7:25) በተጨማሪም እንዲህ ስላለችው ጋጠወጥ ሴት ሲናገር “ከእሷ ራቅ፤ ወደ ቤቷም ደጃፍ አትቅረብ” ብሏል። (ምሳሌ 5:3, 8) አዎ፣ ከኃጢአት ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው ወደ ኃጢአት ከሚመሩት ሁኔታዎች በደንብ በመራቅ ነው። b ይህም በጥቅሉ ለክርስቲያኖች የተከለከሉ ባይሆኑም ወደ ፈተና ሊመሩን እንደሚችሉ ከምናውቃቸው አንዳንድ ሁኔታዎችና እንቅስቃሴዎች መራቅን ሊጨምር ይችላል።—ማቴ. 5:29, 30

12. ኢዮብ ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል? ይህስ ከፈተና ለመራቅ የሚረዳው እንዴት ነው? (ኢዮብ 31:1)

12 ወደ ኃጢአት ከሚመሩ ሁኔታዎች መራቅ ከፈለግን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። ኢዮብም ያደረገው ይህንኑ ነው። ሌሎች ሴቶችን በፍትወት ዓይን ላለመመልከት ‘ከዓይኑ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል።’ (ኢዮብ 31:1ን አንብብ።) ይህን ቁርጥ አቋም ማክበሩ መቼም ቢሆን ምንዝር ለመፈጸም አደጋ እንዳይጋለጥ ይረዳዋል። እኛም ወደ ፈተና ሊመራን ከሚችል ከማንኛውም ነገር ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን።

13. አስተሳሰባችንን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

13 ከዚህም ሌላ አስተሳሰባችንን መጠበቅ ይኖርብናል። (ዘፀ. 20:17) አንዳንዶች፣ አንድ ሰው ኃጢአት እስካልፈጸመ ድረስ በመጥፎ ምኞቶች ላይ ማውጠንጠኑ ምንም ስህተት እንደሌለው ይሰማቸዋል። ሆኖም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው። በመጥፎ ምኞቶች ላይ የሚያውጠነጥን ሰው ምኞቱ እንዲባባስ ያደርጋል። በሌላ አባባል በራሱ ላይ ፈተና ይፈጥራል። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ይህን ፈተና ለማሸነፍ መታገል ይኖርበታል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳቱ ሐሳቦች ወደ አእምሯችን ሊመጡ ይችላሉ። ዋናው ነገር እነዚህን ሐሳቦች ወዲያውኑ ማስወገዳችንና አእምሯችንን በጥሩ ሐሳቦች መሙላታችን ነው። እንዲህ ካደረግን የተሳሳቱ ሐሳቦች አድገው ለመቋቋም የሚያስቸግር ኃይለኛ ምኞት እንዳይሆኑ፣ ይባስ ብሎም ከባድ ኃጢአት ወደመፈጸም እንዳይመሩን መከላከል እንችላለን።—ፊልጵ. 4:8፤ ቆላ. 3:2፤ ያዕ. 1:13-15

ወደ ፈተና ሊመራን ከሚችል ከማንኛውም ነገር መራቅ ይኖርብናል (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)


14. ከፈተና ራሳችንን ለመጠበቅ የሚረዳን ሌላው ነገር ምንድን ነው?

14 ራሳችንን ከፈተና ለመጠበቅ ሌላስ ምን ማድረግ እንችላለን? የይሖዋን ሕጎች መታዘዛችን ምንጊዜም ጥቅም እንደሚያስገኝልን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ አስተሳሰባችንንና ምኞታችንን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ማስማማት ሊያታግለን ይችላል። ሆኖም ይህን ስናደርግ የምናገኘው የአእምሮ ሰላም ምንም ያህል ጥረት ቢደረግለት አያስቆጭም።

15. ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት ማዳበራችን ራሳችንን ከፈተና ለመጠበቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

15 ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት ማዳበር ይኖርብናል። ‘ክፉ የሆነውን ከጠላን እንዲሁም መልካም የሆነውን ከወደድን’ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግና ወደ ኃጢአት ከሚመሩ ሁኔታዎች ለመራቅ ያለን ቁርጠኝነት ይጠናከራል። (አሞጽ 5:15) ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት ማዳበራችን ባልጠበቅነው ወይም ልንከላከለው በማንችለው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ብንገባም እንኳ ጽኑ አቋማችንን ለመጠበቅ ይረዳናል።

16. መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ራሳችንን ለመጠበቅ የሚረዱን እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

16 ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? በተቻለን መጠን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መጠመድ ይኖርብናል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወይም በአገልግሎት ላይ ስንሆን መጥፎ ነገር ለማድረግ በቀላሉ አንፈተንም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ለማስደሰት ያለንን ፍላጎት እናጠናክራለን። (ማቴ. 28:19, 20፤ ዕብ. 10:24, 25) የአምላክን ቃል በማንበብና በማጥናት እንዲሁም ባነበብነው ላይ በማሰላሰል መልካም ለሆነው ነገር ያለንን ፍቅር እንዲሁም ክፉ ለሆነው ነገር ያለንን ጥላቻ ማጠናከር እንችላለን። (ኢያሱ 1:8፤ መዝ. 1:2, 3፤ 119:97, 101) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ‘ወደ ፈተና እንዳትገቡ ሳታሰልሱ ጸልዩ’ እንዳላቸው አስታውስ። (ማቴ. 26:41) ወደ ሰማዩ አባታችን በመጸለይ ከእሱ ጋር ጊዜ ስናሳልፍ የእሱን እርዳታ እናገኛለን፤ እንዲሁም እሱን ለማስደሰት ያለን ቁርጠኝነት ይጠናከራል።—ያዕ. 4:8

ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ፈተናዎችን እንድንቋቋም ብርታት ይሰጠናል (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት) c


ምንጊዜም ነቅተህ ጠብቅ

17. ጴጥሮስ በተደጋጋሚ በየትኛው ድክመት ተሸንፏል?

17 አንዳንድ ድክመቶቻችንን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ እንችል ይሆናል። ይሁንና ሌሎች ዝንባሌዎች በቀጣይነት ሊያታግሉን ይችላሉ። የሐዋርያው ጴጥሮስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስን ሦስት ጊዜ የካደው ለሰው ፍርሃት እጅ በመስጠቱ ነው። (ማቴ. 26:69-75) ጴጥሮስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በድፍረት ምሥክርነት በሰጠበት ወቅት ፍርሃቱን ማሸነፍ የቻለ ይመስል ነበር። (ሥራ 5:27-29) ይሁንና ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ “ከተገረዙት ወገን የሆኑትን በመፍራት” ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከአሕዛብ ክርስቲያኖች ጋር መብላት አቁሞ ነበር። (ገላ. 2:11, 12) ጴጥሮስ ፍርሃቱ አገርሽቶበታል። ምናልባት ቀድሞውንም ይህን ድክመት ሙሉ በሙሉ አላሸነፈው ይሆናል።

18. ከአንዳንድ መጥፎ ዝንባሌዎች ጋር በተያያዘ ምን ሊያጋጥመን ይችላል?

18 እኛም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። እንዴት? እንዳሸነፍነው የሚሰማን ድክመት በድጋሚ ሊፈትነን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ወንድም እንዲህ ሲል በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “የፖርኖግራፊ ሱሴ ለአሥር ዓመት ያህል ሳያገረሽብኝ ስለቆየ ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንዳሸነፍኩት ተሰምቶኝ ነበር። ለካስ ሱሱ አመቺ ጊዜ ሲያገኝ ብቅ ለማለት ተደብቆ እያደባ ነበር።” ጥሩነቱ ወንድማችን ተስፋ አልቆረጠም። ይህን ሱስ ለማሸነፍ በየቀኑ ምናልባትም እስከዚህ ሥርዓት መጨረሻ ድረስ ትግል ማድረጉን መቀጠል እንደሚያስፈልገው ተገነዘበ። በባለቤቱና በጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ የፖርኖግራፊ ሱሱን ለማሸነፍ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን ወሰደ።

19. አሁንም እየታገለን ያለ ዝንባሌ ካለ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 አሁንም እያታገለን ያለ ዝንባሌ ካለ በፈተናው እንዳንሸነፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ኢየሱስ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት የሰጠውን ምክር መከተል ይኖርብናል። ጠንካራ እንደሆንክ በሚሰማህ ጊዜም ጭምር ወደ ፈተና ሊመሩህ ከሚችሉ ሁኔታዎች መራቅህን ቀጥል። (1 ቆሮ. 10:12) እንዲሳካልህ የረዱህን ዘዴዎች በሥራ ላይ ማዋልህን አታቋርጥ። ምሳሌ 28:14 “ምንጊዜም ተጠንቅቆ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው” ይላል።—2 ጴጥ. 3:14

ነቅቶ መጠበቅ የሚያስገኛቸው በረከቶች

20-21. (ሀ) ከፈተና ራሳችንን ከጠበቅን የትኞቹን በረከቶች እናገኛለን? (ለ) እኛ የበኩላችንን ድርሻ ከተወጣን ይሖዋ ምን እንደሚያደርግልን ቃል ገብቷል? (2 ቆሮንቶስ 4:7)

20 ከፈተና ራሳችንን ለመጠበቅ የምናደርገው ጥረት የሚክስ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኃጢአት “ጊዜያዊ ደስታ” ሊያስገኝ ቢችልም በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት ከዚህ እጅግ የላቀ ደስታ ያስገኝልናል። (ዕብ. 11:25፤ መዝ. 19:8) ምክንያቱም የተፈጠርነው በይሖዋ መሥፈርቶች እንድንመራ ተደርገን ነው። (ዘፍ. 1:27) በመሆኑም ንጹሕ ሕሊና እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይኖረናል።—1 ጢሞ. 6:12፤ 2 ጢሞ. 1:3፤ ይሁዳ 20, 21

21 እውነት ነው፣ ‘ሥጋ ደካማ ነው።’ ሆኖም ይህ ሲባል ፈተናዎችን ማሸነፍ አንችልም ማለት አይደለም። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ኃይል ሊሰጠን ዝግጁ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:7ን አንብብ።) ይሁንና አምላክ የሚሰጠን ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል እንደሆነ ልብ በል። ሰብዓዊ ኃይላችንን መጠቀም ማለትም ከፈተና ራሳችንን ለመጠበቅ በየዕለቱ ጥረት ማድረግ የእኛ ኃላፊነት ነው። እኛ የበኩላችንን ድርሻ ከተወጣን በሚያስፈልገን ጊዜ ተጨማሪ ኃይል እንዲሰጠን የምናቀርበውን ጸሎት ይሖዋ እንደሚመልስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (1 ቆሮ. 10:13) አዎ፣ በይሖዋ እርዳታ ከፈተና ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን።

መዝሙር 47 በየዕለቱ ወደ ይሖዋ መጸለይ

a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በማቴዎስ 26:41 ላይ የተጠቀሰው “መንፈስ” አንድን ነገር እንድናደርግ ወይም አንድ ስሜት እንዲሰማን የሚያነሳሳንን ውስጣዊ ግፊት ያመለክታል። “ሥጋ” የሚለው ቃል ደግሞ አለፍጽምናችንን ያመለክታል። ስለዚህ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ከልባችን ብንፈልግም እንኳ ካልተጠነቀቅን ለፈተና እጅ በመስጠት መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት እንደሆነ የሚናገረውን ነገር ልናደርግ እንችላለን።

b ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ሰው ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 57 ከነጥብ 1-3 እንዲሁም በኅዳር 2020 መጠበቂያ ግንብ ላይ በሚገኘው “የወደፊቱን ጊዜ ‘በትኩረት ተመልከት’” በሚለው ርዕስ ከገጽ 27-29 ከአን. 12-17 ላይ ጠቃሚ ሐሳብ ማግኘት ይችላል።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ጠዋት ላይ የዕለቱን ጥቅስ ያነብባል፤ በምሳ እረፍቱ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ ያነብባል፤ እንዲሁም ምሽት ላይ በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ይገኛል