በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

መንፈሳዊ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመሥራቴ ተባርኬያለሁ

መንፈሳዊ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመሥራቴ ተባርኬያለሁ

አባቴ ጄምስ ሲንክሌርና እናቴ ጄሲ ሲንክሌር በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ፣ ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ብሮንክስ ተዛውረው መኖር ጀመሩ። በዚያ ከተዋወቋቸው ሰዎች መካከል አንዱ ልክ እንደ እነሱ ከስኮትላንድ የመጣው ዊሊ ስኔደን ነው። በተዋወቁ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ወላጆቼና ዊሊ ስለ ቤተሰቦቻቸው ማውራት ጀመሩ። ይህ የሆነው እኔ ከመወለዴ ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው።

እናቴ ታላቁ ጦርነት (አንደኛው የዓለም ጦርነት) ከመጀመሩ ከጥቂት ጊዜ በፊት አባቷና ታላቅ ወንድሟ የዓሣ ማጥመጃ ጀልባቸው ሰሜን ባሕር ላይ ከተጠመደ ቦንብ ጋር በመጋጨቱ ሕይወታቸው እንዳለፈ ለዊሊ ነገረችው። ዊሊም “አባትሽ ሲኦል ገብቷል!” በማለት መለሰላት። ዊሊ የይሖዋ ምሥክር ነበር። እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማችው እንዲህ ባለ አስደንጋጭ ሁኔታ ነው።

ዊሊና ሊዝ ስኔደን

እናቴ፣ ዊሊ በተናገረው ነገር ተበሳጨች፤ ምክንያቱም አባቷ ጥሩ ሰው እንደነበር ታውቃለች። ዊሊም በመቀጠል “ኢየሱስም ሲኦል እንደገባ ማወቅሽ ለውጥ ያመጣ ይሆን?” አላት። በዚህ ጊዜ እናቴ ኢየሱስ ሲኦል እንደገባና በሦስተኛው ቀን እንደተነሳ በቤተ ክርስቲያን እንደተማረች አስታወሰች። በመሆኑም ‘ሲኦል ክፉዎች በእሳት የሚሠቃዩበት ቦታ ከሆነ ኢየሱስ ለምን ወደ ሲኦል ገባ?’ የሚል ጥያቄ ተፈጠረባት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እናቴ እውነትን የመማር ፍላጎት አደረባት። ስለዚህ በብሮንክስ ጉባኤ መሰብሰብ የጀመረች ሲሆን በ1940 ተጠመቀች።

ከእናቴ ጋር፣ በኋላም ከአባቴ ጋር

በወቅቱ ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተምሩ ያን ያህል ማበረታቻ አይሰጣቸውም ነበር። በመሆኑም ሕፃን ሳለሁ ቅዳሜና እሁድ እናቴ በጉባኤና በአገልግሎት ስትካፈል እኔ ከአባቴ ጋር ቤት እውል ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ እኔና አባቴም ከእናቴ ጋር በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። እናቴ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት ትካፈል የነበረ ሲሆን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ነበሯት። እንዲያውም የተወሰኑ ሰዎችን አንድ ላይ የምታስጠናበት ጊዜ ነበር፤ ምክንያቱም አንዳንድ ጥናቶቿ የሚኖሩበት አካባቢ ተቀራራቢ ነበር። ትምህርት ሲዘጋ ከእሷ ጋር አብሬ አገልግሎት እወጣ ነበር። ይህም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳውቅና መልእክቱን ለሰዎች ማስተማር ስለሚቻልበት መንገድ እንድማር ረድቶኛል።

የሚያሳዝነው፣ ልጅ ሳለሁ ለእውነት ብዙም አድናቆት አልነበረኝም። የምማረውን ነገር ያን ያህል በቁም ነገር አልመለከተውም ነበር። አሥራ ሁለት ዓመት ገደማ ሳለሁ ግን አስፋፊ ሆንኩ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመስክ አገልግሎት አዘውትሬ መካፈል ጀመርኩ። ሐምሌ 24, 1954 በ16 ዓመቴ ቶሮንቶ፣ ካናዳ ውስጥ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ራሴን ለይሖዋ ወስኜ ተጠመቅኩ።

በቤቴል ማገልገል

በጉባኤያችን ውስጥ፣ ቤቴላውያን የሆኑ ወይም በአንድ ወቅት በቤቴል ያገለገሉ አንዳንድ ወንድሞች ይገኙ ነበር። እነዚህ ወንድሞች ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረውብኛል። የንግግር ችሎታቸውና ለሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚያብራሩበት መንገድ በጣም ይማርከኝ ነበር። አስተማሪዎቼ ዩኒቨርሲቲ እንድገባ ይፈልጉ የነበረ ቢሆንም የእኔ ግብ ግን በቤቴል ማገልገል ነበር። በመሆኑም ቀደም ብዬ በጠቀስኩት በቶሮንቶ በተደረገው ስብሰባ ላይ ቤቴል ለመግባት አመለከትኩ። ከዚያም በ1955 ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ በያንኪ ስታዲየም በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ በድጋሚ አመለከትኩ። ብዙም ሳይቆይ መስከረም 19, 1955 በብሩክሊን ቤቴል እንዳገለግል መጋበዜን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ፤ በወቅቱ 17 ዓመቴ ነበር። ቤቴል በገባሁ በሁለተኛው ቀን 117 አዳምስ ጎዳና በሚገኘው መጠረዣ ክፍል ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። የምሠራበት ማሽን የአንድን መጽሐፍ 32 ገጾች አንድ ላይ በማድረግ ገጾቹን ለሚሰፋው ማሽን የሚያቀብል ነበር።

በ17 ዓመቴ በብሩክሊን ቤቴል ማገልገል ጀመርኩ

በመጠረዣ ክፍል ውስጥ ለአንድ ወር ገደማ ከሠራሁ በኋላ ወደ መጽሔት ክፍል ተዛወርኩ፤ ምክንያቱም ታይፕ ማድረግ እችል ነበር። በዚያን ወቅት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ለማግኘት የተመዘገቡ አዳዲስ ሰዎች አድራሻ በስቴንስል (ትንሽ ጠፍጣፋ ብረት) ላይ ይጻፍ ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ በጽሑፍ መላኪያ ክፍል ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። የጽሑፍ መላኪያ ክፍል የበላይ ተመልካች የሆነው ክላውስ ጄንሰን ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚላኩ ጽሑፎችን የያዙ ካርቶኖችን በመኪና ጭኖ ወደ ወደብ ከሚወስደው ወንድም ጋር አብሬ መሥራት እችል እንደሆነ ጠየቀኝ። ሥራው በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ወዳሉ ጉባኤዎች የሚላኩ መጽሔቶችን ወደ ፖስታ ቤት ማድረስንም ይጨምራል። ወንድም ጄንሰን አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ በሚጠይቅ ሥራ ላይ መካፈሌ እንደሚጠቅመኝ ተሰምቶት ነበር። ምክንያቱም በጣም ቀጭን ከመሆኔ የተነሳ የምመዝነው 57 ኪሎ ገደማ ብቻ ነበር። ወደ ወደቦችና ወደ ፖስታ ቤት በተደጋጋሚ ጉዞ ማድረጌ አካላዊ ጥንካሬ እንዳገኝ ረድቶኛል። በእርግጥም ወንድም ጄንሰን ትክክል ነበር!

የመጽሔት ክፍሉ የጉባኤዎችን የመጽሔት ትእዛዞችም ይሞላ ነበር። በመሆኑም በብሩክሊን ቤቴል ውስጥ መጽሔቶቻችን ስለሚታተሙባቸው የተለያዩ ቋንቋዎች የማወቅ አጋጣሚ አግኝቼ ነበር፤ እነዚህ መጽሔቶች በብሩክሊን ታትመው በመላው ዓለም ይሰራጫሉ። አብዛኞቹን ቋንቋዎች ከዚያ በፊት ሰምቻቸው እንኳ የማላውቅ ቢሆንም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ መጽሔቶች እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ ሰዎች ወደሚኖሩባቸው ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች እንደሚደርሱ ማወቄ ያስደስተኝ ነበር። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል አብዛኞቹን የመጎብኘት መብት አግኝቻለሁ፤ እርግጥ በዚያን ወቅት ይህ እንደሚሆን ጨርሶ አላሰብኩም።

ከሮበርት ዎለን፣ ቻርልስ ሞሎሃንና ዶን አዳምስ ጋር

በ1961 በገንዘብ ያዥ ቢሮ ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ፤ የበላይ ተመልካቹ ወንድም ግራንት ሱተር ነበር። በዚያ ለጥቂት ዓመታት ከሠራሁ በኋላ በወቅቱ ዓለም አቀፉን ሥራ በበላይነት ይከታተል ወደነበረው ወደ ወንድም ኖር ቢሮ ተጠራሁ። ወንድም ኖር፣ በእሱ ዲፓርትመንት ውስጥ ከሚሠሩት ወንድሞች መካከል አንዱ ለአንድ ወር ያህል በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ሊሠለጥን እንደሆነና ትምህርቱን ሲጨርስ በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ እንዲያገለግል እንደተመደበ ነገረኝ። በመሆኑም የዚህን ወንድም ቦታ ተክቼ እንድሠራ ተመደብኩ፤ በዚህ ዲፓርትመንት ውስጥ የምሠራው ከዶን አዳምስ ጋር ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በ1955 በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ የቤቴል ማመልከቻዬን የተቀበለኝ ዶን ነበር። ሮበርት ዎለን እና ቻርልስ ሞሎሃን የተባሉት ወንድሞችም በዚያ ዲፓርትመንት ውስጥ ይሠሩ ነበር። አራታችን ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት አብረን ሠርተናል። መንፈሳዊና ታማኝ ከሆኑት ከእነዚህ ወንድሞች ጋር አብሮ መሥራት በጣም አስደሳች ነበር!—መዝ. 133:1

በ1970 በቬኔዙዌላ የመጀመሪያ የዞን ጉብኝቴን ሳደርግ

በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሥር ያሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በየዓመቱ ወይም በየሁለት ዓመቱ ለጥቂት ሳምንታት እንድጎበኝ ከ1970 ጀምሮ ተመደብኩ፤ እንዲህ ያለው ጉብኝት በወቅቱ የዞን ጉብኝት በመባል ይታወቅ ነበር። ይህ ጉብኝት በዓለም ዙሪያ ያሉ የቤቴል ቤተሰብ አባላትንና ሚስዮናውያንን መጎብኘትንና መንፈሳዊ ማበረታቻ መስጠትን እንዲሁም የቅርንጫፍ ቢሮ መዝገቦችን መመርመርን ይጨምራል። ከጊልያድ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ክፍሎች የተመረቁና በተመደቡበት የውጭ አገር ምድብ አሁንም ድረስ በታማኝነት እያገለገሉ ያሉ ወንድሞችን ማግኘት በጣም ያስደስታል! ከዚህ የሥራ ምድብ ጋር በተያያዘ፣ ከ90 የሚበልጡ አገሮችን መጎብኘት መቻሌ ትልቅ መብት ነው።

ከ90 በሚበልጡ አገሮች የሚገኙ ወንድሞችን መጎብኘት በጣም አስደሳች ነበር!

ታማኝ አጋር አገኘሁ

የብሩክሊን ቤቴል ቤተሰብ አባላት በሙሉ የተመደቡት በኒው ዮርክ ሲቲ አካባቢ በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ ነበር። እኔ የተመደብኩበት ጉባኤ የሚገኘው በብሮንክስ ነው። በብሮንክስ የነበረው የመጀመሪያው ጉባኤ እድገት በማድረጉ የተከፈለ ሲሆን አንደኛው ጉባኤ አፐር ብሮንክስ ተብሎ መጠራት ጀመረ፤ እኔ የተመደብኩት በዚህ ጉባኤ ውስጥ ነበር።

ከላትቪያ የመጣ አንድ ቤተሰብ በደቡብ ብሮንክስ እውነትን ሰማ፤ ይህ ቤተሰብ በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ወደ ጉባኤያችን ተዛውሮ መጣ። የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ የሆነችው ሊቪያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች አቅኚ ሆነች። ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ ማሳቹሴትስ ተዛውራ ማገልገል ጀመረች። እኔም በጉባኤያችን ውስጥ የተከናወኑ አዳዲስ ነገሮችን ደብዳቤ በመጻፍ እነግራት ነበር፤ እሷም በቦስተን አካባቢ ስታገለግል ያገኘቻቸውን ጥሩ ተሞክሮዎች ትጽፍልኛለች።

ከሊቪያ ጋር

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሊቪያ ልዩ አቅኚ ሆና ተመደበች። በይሖዋ አገልግሎት አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ትፈልግ ስለነበር ቤቴል ለመግባት አመለከተች፤ ከዚያም በ1971 በቤቴል እንድታገለግል ተጠራች። በዚህ ጊዜ ይሖዋ አንድ ዓይነት ፍንጭ እንደሰጠኝ ሆኖ ተሰማኝ! ጥቅምት 27, 1973 ከሊቪያ ጋር ተጋባን፤ የጋብቻ ንግግራችንን የሰጠን ወንድም ኖር መሆኑ በጣም አስደስቶናል። ምሳሌ 18:22 “ጥሩ ሚስት ያገኘ ጥሩ ነገር አግኝቷል፤ የይሖዋንም ሞገስ ያገኛል” ይላል። እኔና ሊቪያም በቤቴል በማገልገል ባሳለፍናቸው ከ40 የሚበልጡ ዓመታት የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ችለናል። አሁንም ድረስ በብሮንክስ አካባቢ በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ አብረን በማገልገል ላይ እንገኛለን።

ከክርስቶስ ወንድሞች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ማገልገል

ከወንድም ኖር ጋር መሥራት በጣም አስደሳች ነበር። ወንድም ኖር ለእውነት ድጋፍ ለማድረግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የሚሠራ ከመሆኑም ሌላ በዓለም ዙሪያ ላሉ ሚስዮናውያን ከፍተኛ አድናቆት ነበረው። ከእነዚህ ሚስዮናውያን መካከል አብዛኞቹ የተመደቡት ምንም የይሖዋ ምሥክር በሌለባቸው አካባቢዎች ነው። በ1976 ወንድም ኖር በካንሰር በሽታ ተይዞ ሲሠቃይ ማየት በጣም ያሳዝን ነበር። ወንድም ኖር ታሞ ተኝቶ ባለበት ወቅት፣ ለሕትመት በመዘጋጀት ላይ ያለ አንድ ጽሑፍ እንዳነብለት ጠይቆኝ ነበር። የሚነበበውን ነገር እንዲያዳምጥ ወንድም ፍሬድሪክ ፍራንዝንም እንድጠራው ነገረኝ። ከጊዜ በኋላ እንደተረዳሁት፣ የወንድም ፍራንዝ ዓይን እየደከመ ስለነበር ወንድም ኖር ለሕትመት በመዘጋጀት ላይ ያሉ ጽሑፎችን ጊዜ መድቦ ያነብለት ነበር።

በ1977 ከዳንኤልና ከማሪና ሲድሊክ ጋር የዞን ጉብኝት ስናደርግ

ወንድም ኖር በ1977 ሕይወቱ አለፈ፤ ሆኖም እሱን የሚያውቁትና የሚወዱት ሰዎች ምድራዊ ሕይወቱን በታማኝነት እንዳጠናቀቀ በማወቃቸው ተጽናንተዋል። (ራእይ 2:10) ከዚያም ወንድም ፍራንዝ ሥራውን በበላይነት መከታተል ጀመረ።

በዚያን ወቅት፣ ከወንድም ኖር ጋር ለአሥርተ ዓመታት አብሮ የሠራው የወንድም ሚልተን ሄንሼል ጸሐፊ ነበርኩ። ወንድም ሄንሼል፣ አሁን በቤቴል ያለኝ ዋነኛው ኃላፊነት ወንድም ፍራንዝን በሚያስፈልገው መንገድ ሁሉ መርዳት እንደሆነ ነገረኝ። በመሆኑም ለሕትመት በመዘጋጀት ላይ ያሉ ጽሑፎችን ለወንድም ፍራንዝ አዘውትሬ አነብለት ነበር። ወንድም ፍራንዝ አስገራሚ የማስታወስ ችሎታ ያለው ከመሆኑም ሌላ በሚነበበው ነገር ላይ ሙሉ በሙሉ ትኩረት ማድረግ ይችል ነበር። ታኅሣሥ 1992 ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ እሱን በዚህ መንገድ መርዳት መቻሌ በጣም አስደስቶኛል!

ለአሥርተ ዓመታት የሠራሁበት 124 ኮሎምቢያ ሃይትስ

በቤቴል ያሳለፍኳቸው 61 ዓመታት እንዴት በፍጥነት እንዳለፉ ሳስብ ይገርመኛል። ወላጆቼ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ለይሖዋ ታማኝ ነበሩ፤ እነሱን ከአሁኑ እጅግ በተሻለ ዓለም ውስጥ የምቀበልበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ። (ዮሐ. 5:28, 29) በዓለም ዙሪያ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች በመወከል፣ ታማኝ ከሆኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሮ መሥራት ይህ አሮጌ ሥርዓት ከሚያቀርበው ከማንኛውም ነገር ጋር ጨርሶ ሊወዳደር አይችልም። እኔም ሆንኩ ሊቪያ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍናቸው ዓመታት ሁሉ ‘የይሖዋ ደስታ ምሽጋችን እንደነበር’ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን።—ነህ. 8:10

የይሖዋ ድርጅት ሕልውና በማንም ሰው ላይ የተመካ አይደለም፤ በማንኛውም ሁኔታ ሥር የመንግሥቱ የስብከት ሥራ መከናወኑን ይቀጥላል። ባለፉት ዓመታት ውስጥ፣ ጠንካራና ታማኝ ከሆኑ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ጋር የመሥራት መብት በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። አብሬያቸው እሠራ ከነበሩ ቅቡዓን ወንድሞች መካከል አብዛኞቹ ምድራዊ ሕይወታቸውን አጠናቀዋል። ሆኖም ከእነዚህ ታማኝና መንፈሳዊ ወንድሞች ጋር በአንድ ወቅት አብሬ መሥራት በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ።