በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ደፋር . . . ሁን፤ ሥራህንም ጀምር”

“ደፋር . . . ሁን፤ ሥራህንም ጀምር”

“ደፋርና ብርቱ ሁን፤ ሥራህንም ጀምር። አትፍራ ወይም አትሸበር፤ . . . ይሖዋ አምላክ ከአንተ ጋር ነውና።”—1 ዜና 28:20

መዝሙሮች፦ 38, 34

1, 2. (ሀ) ሰለሞን ምን ከባድ ኃላፊነት ተሰጥቶታል? (ለ) የሰለሞን ሁኔታ ዳዊትን ያሳሰበው ለምንድን ነው?

ሰለሞን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ የመገንባቱን ሥራ በበላይነት የመከታተል ኃላፊነት ተሰጥቶታል፤ ይህ ሥራ በታሪክ ዘመናት ከተከናወኑት የግንባታ ሥራዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ምክንያቱም ሕንፃው “እጅግ የሚያምር ከመሆኑ የተነሳ ዝናውም ሆነ ውበቱ በመላው ምድር የታወቀ ይሆናል።” ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ ሕንፃ “የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ ቤት” ነው። ይሖዋ፣ ሰለሞን ይህን የግንባታ ሥራ በበላይነት እንዲከታተል መመሪያ ሰጥቷል።—1 ዜና 22:1, 5, 9-11

2 ንጉሥ ዳዊት፣ ሰለሞን የአምላክ ድጋፍ እንደማይለየው እርግጠኛ ነበር፤ ሆኖም ሰለሞን “ገና ወጣት” ከመሆኑም ሌላ ‘ተሞክሮ አልነበረውም።’ ታዲያ ደፋር በመሆን ይህን ኃላፊነት ይቀበል ይሆን? ወጣትና ተሞክሮ የሌለው መሆኑ እንቅፋት ይፈጥርበት ይሆን? ሰለሞን እንዲሳካለት ከፈለገ ደፋር መሆንና ሥራውን መጀመር ነበረበት።

3. ሰለሞን ድፍረት ማሳየትን በተመለከተ ከአባቱ ምን ሊማር ይችላል?

3 ሰለሞን ድፍረት ማሳየትን በተመለከተ ከአባቱ ከዳዊት ብዙ ነገር እንደተማረ ምንም ጥርጥር የለውም። ዳዊት ልጅ ሳለ የአባቱን በጎች ከነጣቂ አውሬዎች በድፍረት ያስጥል ነበር። (1 ሳሙ. 17:34, 35) በተጨማሪም ከፍተኛ የጦር ልምድ ያለውን ግዙፍ ሰው ፊት ለፊት በመግጠም አስገራሚ ድፍረት አሳይቷል። ዳዊት አምላክ ስለረዳው በአንዲት ድቡልቡል ድንጋይ ጎልያድን ድል ማድረግ ችሏል።—1 ሳሙ. 17:45, 49, 50

4. ሰለሞን ደፋር መሆን የነበረበት ለምንድን ነው?

4 በእርግጥም ዳዊት ሰለሞንን ደፋር እንዲሆንና ቤተ መቅደሱን እንዲገነባ ያበረታታው ለምን እንደሆነ መገመት አያዳግትም! (1 ዜና መዋዕል 28:20ን አንብብ።) ሰለሞን ደፋር ካልሆነ በፍርሃት ሊሽመደመድና ሥራውን ከመጀመር ወደኋላ ሊል ይችላል፤ ሥራውን ጨርሶ አለመጀመር ደግሞ ከሁሉ የከፋ ነው፤ ከዚህ ይልቅ ጀምሮ ሳይሳካለት ቢቀር ይሻላል።

5. ደፋር መሆን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

5 እኛም ልክ እንደ ሰለሞን ደፋር ለመሆን የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል፤ ይህም እሱ የሰጠንን ሥራ ለማከናወን ያስችለናል። በጥንት ዘመን የኖሩ ድፍረት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ታሪክ እስቲ እንመርምር። ከዚያም ደፋር መሆንና ሥራችንን ማከናወን የምንችልባቸውን አቅጣጫዎች እንመለከታለን።

ድፍረት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች

6. ዮሴፍ ስላሳየው ድፍረት ስታስብ አንተን የሚያስደንቅህ ምንድን ነው?

6 ዮሴፍ፣ የጶጢፋር ሚስት የፆታ ብልግና እንዲፈጽም በወተወተችው ጊዜ ያሳየውን ድፍረት እንደ ምሳሌ እንመልከት። የእሷን ጥያቄ አለመቀበሉ ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትልበት ተገንዝቦ መሆን አለበት። ያም ቢሆን ለእሷ ውትወታ እጅ ከመስጠት ይልቅ ደፋር በመሆን ቆራጥ እርምጃ ወስዷል።—ዘፍ. 39:10, 12

7. ረዓብ ደፋር መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

7 ረዓብም ድፍረት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትሆነናለች። እስራኤላውያን ሰላዮች በኢያሪኮ ወዳለው ቤቷ በመጡ ጊዜ በፍርሃት ልትሸነፍና እነሱን ከመቀበል ወደኋላ ልትል ትችል ነበር። ሆኖም በይሖዋ በመታመን ሁለቱን ሰዎች ቤቷ የደበቀቻቸው ከመሆኑም ሌላ በሰላም ከከተማው እንዲወጡ ረድታቸዋለች፤ በዚህ መንገድ ደፋር መሆኗን አሳይታለች። (ኢያሱ 2:4, 5, 9, 12-16) ረዓብ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ እንደሆነና ምድሪቱን ለእስራኤላውያን መስጠቱ እንደማይቀር ሙሉ እምነት ነበራት። የኢያሪኮን ንጉሥና የላካቸውን ሰዎች ጨምሮ የማንኛውም ሰው ፍርሃት እንዲያሽመደምዳት አልፈቀደችም። ከዚህ ይልቅ የኋላ ኋላ የእሷንም ሆነ የቤተሰቧን ሕይወት ሊያተርፍ የሚችል እርምጃ ወስዳለች።—ኢያሱ 6:22, 23

8. ኢየሱስ ያሳየው ድፍረት ሐዋርያቱን የረዳቸው እንዴት ነው?

8 ታማኝ የሆኑት ሐዋርያትም ድፍረት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። እነዚህ ሐዋርያት፣ ኢየሱስ ያሳየውን ድፍረት በገዛ ዓይናቸው የመመልከት አጋጣሚ አግኝተዋል፤ ይህም ድፍረት እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። (ማቴ. 8:28-32፤ ዮሐ. 2:13-17፤ 18:3-5) ሰዱቃውያን ከፍተኛ ተቃውሞ ቢያደርሱባቸውም በኢየሱስ ስም ከማስተማር ወደኋላ አላሉም።—ሥራ 5:17, 18, 27-29

9. በ2 ጢሞቴዎስ 1:7 መሠረት ዋነኛው የድፍረት ምንጭ ማን ነው?

9 ዮሴፍ፣ ረዓብ፣ ኢየሱስና ሐዋርያቱ መልካም ሥራ ለመሥራት የሚያነሳሳ ውስጣዊ ጥንካሬ እንዳላቸው አሳይተዋል። ደፋሮች የሆኑት ከልክ በላይ በራሳቸው ስለተማመኑ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ስለታመኑ ነው። እኛም ደፋር መሆንን የሚጠይቁ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። በእነዚህ ጊዜያት በራሳችን ከመተማመን ይልቅ በይሖዋ ልንታመን ይገባል። (2 ጢሞቴዎስ 1:7ን አንብብ።) እስቲ በሚከተሉት ሁለት መስኮች ማለትም በቤተሰብና በጉባኤ ውስጥ ድፍረት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ደፋር መሆንን የሚጠይቁ ሁኔታዎች

10. ክርስቲያን ወጣቶች ደፋር መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

10 ክርስቲያን ወጣቶች ይሖዋን ለማገልገል ሲሉ ድፍረት የሚጠይቁ በርካታ ሁኔታዎችን ይጋፈጣሉ። እነዚህ ወጣቶች ሰለሞን ከተወው ምሳሌ ትምህርት በማግኘት እሱ የወሰደው ዓይነት እርምጃ መውሰድ ይችላሉ፤ ሰለሞን የቤተ መቅደሱን ግንባታ ለማጠናቀቅ ሲል ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ በማድረግ ደፋር መሆኑን አሳይቷል። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያን ወጣቶች ከወላጆቻቸው መመሪያ ሊያገኙ ይችላሉ፤ ደግሞም የእነሱን መመሪያ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አለባቸው። ያም ቢሆን ወጣቶች በግላቸው ሊያደርጓቸው የሚገቡ አስፈላጊ ውሳኔዎች አሉ። (ምሳሌ 27:11) ጥሩ ጓደኞችንና ጤናማ መዝናኛን ከመምረጥ፣ የሥነ ምግባር ንጽሕናን ከመጠበቅ እንዲሁም ራስን ወስኖ ከመጠመቅ ጋር በተያያዘ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ማድረግ ደፋር መሆንን ይጠይቃል። ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን የሚያደርጉ ወጣቶች አምላክን የሚነቅፈው ሰይጣን ከሚፈልገው ነገር ጋር የሚቃረን እርምጃ እየወሰዱ ነው።

11, 12. (ሀ) ሙሴ ድፍረት በማሳየት ረገድ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል? (ለ) ወጣቶች ሙሴ የተወውን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

11 ወጣቶች ከሚያጋጥሟቸው ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ግብ ማውጣት ነው። በአንዳንድ አገሮች ወጣቶች ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉና ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ እንዲይዙ ጫና ይደረግባቸዋል። በሌሎች አገሮች ደግሞ፣ ካለው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የተነሳ ወጣቶች ቤተሰባቸውን በቁሳዊ ነገሮች በመደገፍ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይችላል። እናንት ወጣቶች፣ ያላችሁበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ሙሴ የተወውን ምሳሌ መመርመራችሁ ይጠቅማችኋል። ሙሴን ያሳደገችው የፈርዖን ሴት ልጅ እንደመሆኗ መጠን ሙሴ ከፍተኛ ሥልጣን በመያዝ አሊያም የተደላደለ ኑሮ በመምራት ላይ ያተኮረ ግብ ሊያወጣ ይችል ነበር። ግብፃውያን ቤተሰቦቹ፣ አስተማሪዎቹና አማካሪዎቹ እንዲህ ያለ ግብ እንዲከታተል ከፍተኛ ተጽዕኖ አድርገውበት ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም! ይሁንና ሙሴ በተጽዕኖው ከመሸነፍ ይልቅ ደፋር በመሆን ከንጹሕ አምልኮ ጎን ቆሟል። የግብፅን ሀብት ትቶ ከወጣ በኋላም ደፋር በመሆን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እንደሚታመን አሳይቷል። (ዕብ. 11:24-26) እንዲህ ማድረጉ በሕይወት ዘመኑ የይሖዋን በረከት አስገኝቶለታል፤ ወደፊት ደግሞ ብዙ በረከቶች እንደሚጠብቁት የታወቀ ነው።

12 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ደፋሮች በመሆን መንፈሳዊ ግቦችን የሚያወጡና በሕይወታቸው ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጡ ወጣቶችን ይባርካቸዋል። በተጨማሪም ቤተሰብ ከመሠረቱ በኋላ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶችም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደኖረው እንደ ወጣቱ ጢሞቴዎስ ሁሉ መንፈሳዊ ግቦችን በመከታተል ላይ ትኩረት ማድረግ ይችላሉ። *ፊልጵስዩስ 2:19-22ን አንብብ።

በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች ደፋር ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? (አንቀጽ 13-17⁠ን ተመልከት)

13. አንዲት ወጣት እህት ድፍረት ማዳበሯ ግቧ ላይ እንድትደርስ የረዳት እንዴት ነው?

13 በአላባማ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት እህት መንፈሳዊ ግቦችን ለማውጣት ድፍረት ማዳበር አስፈልጓታል። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ልጅ ሳለሁ በጣም ዓይናፋር ነበርኩ። ፈጽሞ የማላውቃቸውን ሰዎች በር ማንኳኳት ይቅርና በስብሰባ አዳራሽ የማገኛቸውን ሰዎችም እንኳ ማናገር ይከብደኝ ነበር።” ይህች ወጣት እህት ወላጆቿና ሌሎች የጉባኤው አባላት ባደረጉላት እርዳታ የዘወትር አቅኚነት ግቧ ላይ መድረስ ችላለች። እንዲህ ብላለች፦ “የሰይጣን ዓለም ከፍተኛ ትምህርትን፣ ዝነኝነትን እንዲሁም ገንዘብና ቁሳዊ ነገሮች ማካበትን እንደ ግብ አድርገን እንድንከታተል ያበረታታናል። እነዚህ ግቦች አብዛኛውን ጊዜ የማይደረስባቸው ከመሆናቸውም ሌላ ለጭንቀትና ለሐዘን የሚዳርጉ ናቸው። ይሖዋን ማገልገል ግን ከፍተኛ ደስታና እርካታ አስገኝቶልኛል።”

14. ክርስቲያን ወላጆች ደፋር መሆንን የሚጠይቁ ምን ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?

14 ክርስቲያን ወላጆችም ደፋሮች መሆን ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አሠሪህ ማታ ማታ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ትርፍ ሰዓት እንድትሠራ በተደጋጋሚ ይጠይቅህ ይሆናል፤ እነዚህ ጊዜያት ደግሞ የቤተሰብ አምልኮ የምታደርግባቸው፣ በመስክ አገልግሎት የምትካፈልባቸውና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምትገኝባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። አሠሪህ በተደጋጋሚ የሚያቀርብልህን እንዲህ ያለ ጥያቄ ላለመቀበልና በዚህ ረገድ ለልጆችህ ጥሩ ምሳሌ ሆነህ ለመገኘት ደፋር መሆን ያስፈልግሃል። ደፋር መሆንን የሚጠይቅ ሌላም ሁኔታ መጥቀስ እንችላለን። አንተ ልጆችህ እንዳያደርጉ የከለከልካቸውን ነገር በጉባኤህ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ይፈቅዱላቸው ይሆናል። እነዚህ ወላጆች፣ ልጆችህ እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች እንዳይካፈሉ የምትከለክላቸው ለምን እንደሆነ ሊጠይቁህ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ በድፍረት ሆኖም አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዲህ ያደረግክበትን ምክንያት ታስረዳቸዋለህ?

15. በመዝሙር 37:25 እና በዕብራውያን 13:5 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ወላጆችን የሚረዳቸው እንዴት ነው?

15 ወላጆች፣ ልጆቻቸው መንፈሳዊ ግቦች እንዲያወጡና ግቦቻቸው ላይ እንዲደርሱ ለመርዳት ደፋር መሆን ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን አቅኚ እንዲሆኑ፣ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደው እንዲያገለግሉ፣ ቤቴል እንዲገቡ ወይም በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲካፈሉ ከማበረታታት ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። እነዚህ ወላጆች እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ የሚሉት፣ ሲያረጁ የሚጦራቸው እንደሚያጡ ስለሚሰማቸው አሊያም ልጆቻቸው ወደፊት ራሳቸውን መደገፍ ይከብዳቸዋል የሚል ስጋት ስለሚያድርባቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ደፋሮች በመሆን ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ። (መዝሙር 37:25ን እና ዕብራውያን 13:5ን አንብብ።) ወላጆች በዚህ መንገድ በይሖዋ የሚታመኑና ደፋሮች እንደሆኑ የሚያሳዩ ከሆነ ልጆቻቸውም በይሖዋ ላይ ተመሳሳይ እምነት ለመጣል ይነሳሳሉ።—1 ሳሙ. 1:27, 28፤ 2 ጢሞ. 3:14, 15

16. አንዳንድ ወላጆች መንፈሳዊ ግቦችን እንዲያወጡ ልጆቻቸውን የረዷቸው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋቸውስ ምን ጥቅም አስገኝቷል?

16 በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ልጆቻቸው መንፈሳዊ ግቦችን እንዲያወጡ ረድተዋል። ባልየው እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ገና ከሕፃንነታቸው አንስቶ ለልጆቻችን አቅኚ መሆን እንዲሁም ጉባኤውን ማገልገል ስለሚያስገኘው ደስታ እንነግራቸው ነበር። አሁን እነሱ ራሳቸው ይህንኑ ግብ አውጥተዋል። ልጆቻችን መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣታቸውና እነዚህ ግቦች ላይ መድረሳቸው የሰይጣን ዓለም የሚያሳድርባቸውን ተጽዕኖ እንዲቋቋሙና እውን በሆነው አካል ማለትም በይሖዋ ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳቸዋል።” ሁለት ልጆች ያሉት አንድ ወንድም ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው እንደ ስፖርት፣ የትርፍ ጊዜ እንቅስቃሴዎችና ትምህርት ባሉ መስኮች ጥሩ ቦታ ላይ እንዲደርሱላቸው ሲሉ ብዙ የሚለፉ ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ወጪ ያወጣሉ። ከዚህ የበለጠ ሊደከምለት የሚገባው ጉዳይ ግን ልጆቻችን በይሖዋ ፊት ጥሩ አቋም እንዲኖራቸው የሚያስችሏቸውን ግቦች እንዲያወጡ መርዳት ነው። ልጆቻችን መንፈሳዊ ግቦቻቸው ላይ ሲደርሱ ማየት ከፍተኛ እርካታ አስገኝቶልናል፤ እኛም የደስታቸው ተካፋይ መሆን ችለናል።።” ወላጆች፣ ልጆቻቸው መንፈሳዊ ግቦችን እንዲያወጡና ግቦቻቸው ላይ እንዲደርሱ የሚረዷቸው ከሆነ አምላክ እንደሚባርካቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።

በጉባኤ ውስጥ ድፍረት ማሳየት

17. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ደፋር መሆንን የሚጠይቁ ምን ሁኔታዎች ይኖራሉ?

17 በጉባኤ ውስጥም ደፋር መሆንን የሚጠይቁ ሁኔታዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ ሽማግሌዎች ከፍርድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ሲመለከቱ አሊያም ድንገተኛና ከባድ የጤና ችግር የገጠማቸውን ወንድሞች ሲረዱ ደፋር መሆን ይኖርባቸዋል። እስር ቤት በመሄድ በዚያ የሚገኙ ግለሰቦችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ጥረት የሚያደርጉ ሽማግሌዎችም ደፋር መሆን ያስፈልጋቸዋል። ነጠላ እህቶችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? በዛሬው ጊዜ ነጠላ እህቶች አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚችሉባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ፤ በአቅኚነት አገልግሎት መካፈልን፣ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ ማገልገልን፣ በአካባቢ ንድፍና ግንባታ ፕሮግራም መካፈልንና በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት መማርን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። እንዲያውም አንዳንድ እህቶች ጊልያድ ትምህርት ቤት ገብተው የመማር አጋጣሚ አግኝተዋል።

18. በዕድሜ የገፉ እህቶች ደፋር እንደሆኑ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

18 በዕድሜ የገፉ እህቶች ለጉባኤው በረከት ናቸው። እነዚህን እህቶች በጣም እንወዳቸዋለን! አንዳንዶቹ በአምላክ አገልግሎት የቀድሞውን ያህል ብዙ ማከናወን አይችሉ ይሆናል፤ ይሁንና አሁንም ቢሆን ደፋሮች በመሆን የሚሠሩት ሥራ አለ። (ቲቶ 2:3-5ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት አረጋዊት እህት በአለባበስ ረገድ ልከኛ መሆንን በተመለከተ ለአንዲት ወጣት እህት ምክር እንዲሰጡ ሊጠየቁ ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ ደፋር መሆን ያስፈልጋቸዋል። እኚህ እህት ምክር የሚያስፈልጋትን እህት በሚያነጋግሩበት ጊዜ የአለባበስ ምርጫዋን በተመለከተ አይነቅፏትም፤ ከዚህ ይልቅ በዚህ ረገድ የምታደርገው ምርጫ በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል እንድታስብበት ይረዷታል። (1 ጢሞ. 2:9, 10) ፍቅርና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ የቀረበ እንዲህ ያለ ምክር ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።

19. (ሀ) የተጠመቁ ወንድሞች ደፋር እንደሆኑ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) በፊልጵስዩስ 2:13 እና 4:13 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ወንድሞች ድፍረት እንዲያዳብሩ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

19 የተጠመቁ ወንድሞችም ደፋር መሆንና ይሖዋ የሚጠብቅባቸውን ሥራ ማከናወን አለባቸው። ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኞች የሆኑ ደፋር ወንዶች ለጉባኤው በረከት ናቸው። (1 ጢሞ. 3:1) አንዳንድ ወንድሞች ግን ኃላፊነት ላይ ለመድረስ ከመጣጣር ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። ምናልባትም አንዳንዶች ከዚህ በፊት በፈጸሙት ኃጢአት ምክንያት የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነው ለማገልገል ብቁ እንዳልሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ አንድን ኃላፊነት ለመወጣት ችሎታው እንደሌላቸው ይሰማቸው ይሆናል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ድፍረት እንድታዳብር ሊረዳህ ይችላል። (ፊልጵስዩስ 2:13⁠ን እና 4:13ን አንብብ።) ሙሴም የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ብቁ እንዳልሆነ የተሰማው ወቅት እንደነበር አስታውስ። (ዘፀ. 3:11) ይሁንና ይሖዋ የረዳው ሲሆን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስፈልገውን ድፍረት በጊዜ ሂደት ማዳበር ችሏል። አንድ የተጠመቀ ወንድምም የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ልባዊ ጸሎት በማቅረብና በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ተመሳሳይ ድፍረት ማዳበር ይችላል። ድፍረት ስላሳዩ ሰዎች በሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ማሰላሰሉም ሊረዳው ይችላል። በተጨማሪም ሽማግሌዎች እንዲያሠለጥኑት በትሕትና መጠየቁና በተመደበበት ቦታ ሁሉ ለማገልገል ራሱን ማቅረቡ ጠቃሚ ነው። እናንት የተጠመቃችሁ ወንድሞች፣ ደፋሮች እንድትሆኑና ጉባኤውን ለማገልገል ጠንክራችሁ እንድትሠሩ እናበረታታችኋለን!

“ይሖዋ አምላክ ከአንተ ጋር ነው”

20, 21. (ሀ) ዳዊት ለሰለሞን ምን ማረጋገጫ ሰጥቶታል? (ለ) ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

20 ንጉሥ ዳዊት፣ ልጁን ሰለሞንን የቤተ መቅደሱ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ይሖዋ ከእሱ ጋር እንደሚሆን በመንገር አበረታቶታል። (1 ዜና 28:20) ሰለሞን አባቱ በሰጠው ምክር ላይ አሰላስሎ መሆን አለበት፤ ይህም ወጣትና ተሞክሮ የሌለው ቢሆንም ደፋር እንዲሆንና ሥራውን እንዲጀምር እንደረዳው ጥርጥር የለውም። ደግሞም ሰለሞን በይሖዋ እርዳታ እጅግ የሚያምረውን ቤተ መቅደስ በሰባት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ሊጨርስ ችሏል።

21 ይሖዋ ሰለሞንን እንደረዳው ሁሉ እኛንም በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ደፋር እንድንሆንና ሥራችንን እንድናከናውን ሊረዳን ይችላል። (ኢሳ. 41:10, 13) ከይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዘ ድፍረት የሚጠይቁ እርምጃዎችን ስንወስድ አሁንም ሆነ ወደፊት የይሖዋ በረከት እንደማይለየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ስለዚህ ደፋር በመሆን ይሖዋ የሰጠንን ሥራ እንጀምር።

^ አን.12 መንፈሳዊ ግቦችን ለማውጣት የሚረዱ አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮችን ለማግኘት ሐምሌ 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ፈጣሪህን ለማክበር መንፈሳዊ ግቦች አውጣ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።