በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 37

ለይሖዋ በፈቃደኝነት ተገዙ

ለይሖዋ በፈቃደኝነት ተገዙ

“አባት ለሆነው ይበልጥ በፈቃደኝነት [ልንገዛ] አይገባም?”—ዕብ. 12:9

መዝሙር 9 ይሖዋ ንጉሣችን ነው!

ማስተዋወቂያ *

1. ለይሖዋ መገዛት ያለብን ለምንድን ነው?

ይሖዋ ፈጣሪያችን ስለሆነ ልንገዛለት * ይገባል። ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ለፍጥረታቱ መመሪያዎችን የማውጣት መብት አለው። (ራእይ 4:11) ሆኖም ለይሖዋ እንድንገዛ የሚገፋፋን ሌላም ምክንያት አለ፤ ይህም የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ መሆኑ ነው። በታሪክ ዘመናት ሁሉ በርካታ ሰብዓዊ ገዢዎች ሌሎች ሰዎችን ሲገዙ ቆይተዋል። ከእነዚህ ገዢዎች ጋር ሲነጻጸር ይሖዋ እጅግ ጥበበኛ፣ አፍቃሪ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ ገዢ ነው።—ዘፀ. 34:6፤ ሮም 16:27፤ 1 ዮሐ. 4:8

2. ዕብራውያን 12:9-11 ላይ በተገለጸው መሠረት ለይሖዋ እንድንገዛ የሚያነሳሱን ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

2 ይሖዋ ፈርተነው ሳይሆን ወደነውና እንደ አፍቃሪ አባታችን ተመልክተነው እንድንታዘዘው ይፈልጋል። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው፣ ለአባታችን ‘በፈቃደኝነት መገዛት’ ያለብን እሱ የሚያሠለጥነን “ለጥቅማችን” ስለሆነ ነው።—ዕብራውያን 12:9-11ን አንብብ።

3. (ሀ) ለይሖዋ እንደምንገዛ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 በሁሉም ነገር ይሖዋን ለመታዘዝ የቻልነውን ሁሉ በማድረግና በራሳችን ማስተዋል እንዳንመካ በመጠንቀቅ ለይሖዋ እንደምንገዛ ማሳየት እንችላለን። (ምሳሌ 3:5) ማራኪ ስለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት እያወቅን ስንሄድ ለእሱ መገዛት ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ባሕርያቱ ይሖዋ በሚያደርገው በማንኛውም ነገር ላይ በግልጽ ይታያሉ። (መዝ. 145:9) ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቅን ቁጥር ለእሱ ያለን ፍቅር እየጨመረ ይሄዳል። ለይሖዋ ፍቅር ካለን ደግሞ ማድረግ ስላለብንና ስለሌለብን ነገር የሚገልጹ ዝርዝር ሕጎች አያስፈልጉንም። አስተሳሰባችንንና ስሜታችንን ይሖዋ ከሚወዳቸው ነገሮች ጋር ለማስማማትና ክፉ ከሆኑ ነገሮች ለመራቅ ጥረት እናደርጋለን። (መዝ. 97:10) አንዳንድ ጊዜ ግን ይሖዋን መታዘዝ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ምክንያቱ ምንድን ነው? ሽማግሌዎች፣ አባቶችና እናቶች ከአገረ ገዢው ከነህምያ፣ ከንጉሥ ዳዊትና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? ይህ ርዕስ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ይዟል።

ለይሖዋ መገዛት ከባድ ሊሆንብን የሚችለው ለምንድን ነው?

4-5. በሮም 7:21-23 ላይ እንደተገለጸው ለይሖዋ መገዛት ከባድ ሊሆንብን የሚችለው ለምንድን ነው?

4 ለይሖዋ መገዛት ከባድ እንዲሆንብን ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ሁላችንም ኃጢአትንና አለፍጽምናን የወረስን መሆናችን ነው። ይህም የዓመፅ ዝንባሌ እንዲኖረን አድርጓል። አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ በማመፅና የተከለከለውን ፍሬ በመብላት የራሳቸውን መሥፈርት ለማውጣት መርጠዋል። (ዘፍ. 3:22) በዛሬው ጊዜም አብዛኛው የሰው ዘር ይሖዋን ችላ ለማለት እንዲሁም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በራሱ ለመወሰን መርጧል።

5 ይሖዋን የሚያውቁና የሚወዱ ሰዎችም እንኳ ለእሱ ሙሉ በሙሉ መገዛት ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያለ ችግር አጋጥሞት ነበር። (ሮም 7:21-23ን አንብብ።) እኛም ልክ እንደ ጳውሎስ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ እንፈልጋለን። ሆኖም መጥፎ የሆነውን ነገር እንድናደርግ ከሚገፋፋን ውስጣዊ ዝንባሌ ጋር ቀጣይ የሆነ ትግል ማድረግ አለብን።

6-7. ለይሖዋ መገዛት ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ሁለተኛው ምክንያት ምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

6 ለይሖዋ መገዛት ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ያደግንበት ባሕል የሚያሳድርብን ተጽዕኖ ነው። በርካታ ሰብዓዊ አስተሳሰቦች ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚጋጩ ሲሆን በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ካላቸው እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች ለመላቀቅ ቀጣይ ትግል ማድረግ ያስፈልገናል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

7 በአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቶች ገንዘብ በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት እንዲመሩ ከፍተኛ ጫና ይደረግባቸዋል። ሜሪ * የተባለች እህት እንዲህ ያለ ፈተና አጋጥሟት ነበር። እውነትን ከማወቋ በፊት በአገሪቱ ውስጥ አለ በሚባል ዩኒቨርሲቲ ተምራለች። ቤተሰቦቿ ዳጎስ ያለ ደሞዝ በሚያስገኝና በሌሎች ዘንድ ከፍ ተደርጎ በሚታይ የሥራ መስክ እንድትሰማራ ይገፏፏት ነበር። እሷም ብትሆን እንዲህ ያለ ሥራ መያዝ ትፈልግ ነበር። ስለ ይሖዋ ካወቀችና ለእሱ ፍቅር ካዳበረች በኋላ ግን ግቧን ለወጠች። ያም ሆኖ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኙ አጓጊ ሥራዎችን አገኛለሁ፤ ሆኖም እነዚህ ሥራዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች የማውለውን ጊዜ እንደሚሻሙብኝ አውቃለሁ። በአስተዳደጌ ምክንያት አሁንም ድረስ እነዚህን ሥራዎች አለመቀበል ይከብደኛል። በሙሉ ልብ ይሖዋን እንዳላገለግል እንቅፋት የሚሆኑብኝን ሥራዎች ለመቀበል እንዳልፈተን ይሖዋ እንዲረዳኝ መለመን አስፈልጎኛል።”—ማቴ. 6:24

8. ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?

8 ለይሖዋ መገዛታችን ራሳችንን ይጠቅመናል። ሆኖም እንደ ሽማግሌዎች፣ አባቶችና እናቶች ያሉ የተወሰነ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች የአምላክን መመሪያ ለመከተል የሚያነሳሳቸው ተጨማሪ ምክንያት ደግሞ እንዲህ ማድረጋቸው ሌሎች ሰዎችን የሚጠቅም መሆኑ ነው። የተሰጠንን ሥልጣን ይሖዋን ደስ በሚያሰኝ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

ሽማግሌዎች ከነህምያ ምን ትምህርት ያገኛሉ?

ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር በመገንባቱ ሥራ እንደተካፈለ ሁሉ የጉባኤ ሽማግሌዎችም የስብሰባ አዳራሹን በመጠገኑ ሥራ ይካፈላሉ (ከአንቀጽ 9-11⁠ን ተመልከት) *

9. ነህምያ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል?

9 ይሖዋ ለሽማግሌዎች ሕዝቡን እንደ እረኛ የመጠበቅ ከባድ ኃላፊነት በአደራ ሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥ. 5:2) ሽማግሌዎች ነህምያ የይሖዋን ሕዝቦች የያዘበትን መንገድ በመመርመር ትልቅ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ነህምያ የይሁዳ አገረ ገዢ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። (ነህ. 1:11፤ 2:7, 8፤ 5:14) እስቲ ያጋጠሙትን አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለማሰብ ሞክሩ። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን እንዳረከሱና ሌዋውያኑን በገንዘብ እንዲደግፉ የተሰጣቸውን ሕግ እንደጣሱ ተገንዝቦ ነበር። አይሁዳውያኑ የሰንበትን ሕግ የማያከብሩ ከመሆኑም ሌላ አንዳንዶቹ ወንዶች የባዕድ አገር ሴቶችን አግብተው ነበር። አገረ ገዢው ነህምያ ለዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍትሔ መስጠት ነበረበት።—ነህ. 13:4-30

10. ነህምያ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ምን አድርጓል?

10 ነህምያ የራሱን ሕጎች በአምላክ ሕዝቦች ላይ በመጫን ሥልጣኑን አላግባብ አልተጠቀመም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን አመራር ለማግኘት ልባዊ ጸሎት አቅርቧል፤ እንዲሁም የይሖዋን ሕግ ለሕዝቡ አስተምሯል። (ነህ. 1:4-10፤ 13:1-3) ከዚህም በተጨማሪ ነህምያ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከወንድሞቹ ጋር ሠርቷል፤ ሌላው ቀርቶ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አብሯቸው ገንብቷል።—ነህ. 4:15

11. በ1 ተሰሎንቄ 2:7, 8 መሠረት ሽማግሌዎች የጉባኤውን አባላት እንዴት ሊይዙ ይገባል?

11 ሽማግሌዎች ነህምያን ያጋጠሙት ዓይነት ችግሮች አያጋጥሟቸው ይሆናል፤ ሆኖም የእሱን ምሳሌ መከተል የሚችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ጠንክረው ይሠራሉ። እንዲሁም የተሰጣቸው ሥልጣን ከሌሎች የተሻሉ እንደሚያደርጋቸው አይሰማቸውም። ከዚህ ይልቅ ጉባኤውን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይይዛሉ። (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8ን አንብብ።) ለጉባኤው ያላቸው ፍቅርና ትሕትናቸው ሌሎችን በሚያናግሩበት መንገድ ላይ በግልጽ ይታያል። ለበርካታ ዓመታት በሽምግልና ያገለገለ አንድሩ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በጥቅሉ ሲታይ ሽማግሌዎች ደግና አፍቃሪ ከሆኑ የወንድሞችንና የእህቶችን ልብ በቀላሉ መንካት እንደሚችሉ አስተውያለሁ። እነዚህ ባሕርያት ጉባኤው ከሽማግሌዎች ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ያነሳሳሉ።” ቶኒ የተባለ ለብዙ ዓመታት በሽምግልና ያገለገለ ወንድምም እንዲህ ብሏል፦ “በፊልጵስዩስ 2:3 ላይ በሚገኘው ምክር መሠረት ሌሎች ከእኔ እንደሚበልጡ አድርጌ ለማሰብ ሁሌም ጥረት አደርጋለሁ። ይህም ፈላጭ ቆራጭ እንዳልሆን ረድቶኛል።”

12. የጉባኤ ሽማግሌዎች ትሑት መሆናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ሽማግሌዎች ልክ እንደ ይሖዋ ትሑት መሆን አለባቸው። ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ቢሆንም “ወደ ታች [አጎንብሶ] ችግረኛውን ከአፈር ያነሳል።” (መዝ. 18:35፤ 113:6, 7) በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ኩሩና እብሪተኛ ሰዎችን ይጸየፋል።—ምሳሌ 16:5

13. ሽማግሌዎች ‘አንደበታቸውን መግታት’ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

13 ለይሖዋ ሥልጣን የሚገዛ ሽማግሌ ‘አንደበቱን መግታት’ ይኖርበታል። አለዚያ ግን አንድ ሰው እንዳላከበረው ሲሰማው ግለሰቡን ደግነት በጎደለው መንገድ ሊናገረው ይችላል። (ያዕ. 1:26፤ ገላ. 5:14, 15) ቀደም ሲል የተጠቀሰው አንድሩ እንዲህ ብሏል፦ “አክብሮት ያላሳዩኝን ወንድሞች ደግነት በጎደለው መንገድ ለመናገር የምፈተንበት ጊዜ አለ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰሌ ግን ትሑትና ገር የመሆንን አስፈላጊነት እንድገነዘብ ረድቶኛል።” ሽማግሌዎች አብረዋቸው በሽምግልና የሚያገለግሉትን ወንድሞች ጨምሮ የጉባኤውን አባላት በሙሉ ፍቅር በሚንጸባረቅበትና ለዛ ባለው መንገድ በማናገር ለይሖዋ ሥልጣን እንደሚገዙ ያሳያሉ።—ቆላ. 4:6

አባቶች ከንጉሥ ዳዊት ምን ትምህርት ያገኛሉ?

14. ይሖዋ ለአባቶች ምን ሥልጣን ሰጥቷቸዋል? ምን እንዲያደርጉስ ይጠብቅባቸዋል?

14 ይሖዋ አባቶችን የቤተሰብ ራስ አድርጎ የሾማቸው ሲሆን ልጆቻቸውን እንዲያሠለጥኑና እንዲገሥጹ ይጠብቅባቸዋል። (1 ቆሮ. 11:3፤ ኤፌ. 6:4) ሆኖም የአባቶች ሥልጣን ገደብ አለው፤ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ስያሜ በሰጠው በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ናቸው። (ኤፌ. 3:14, 15) አባቶች ሥልጣናቸውን አምላክን በሚያስደስት መንገድ በመጠቀም ለይሖዋ እንደሚገዙ ያሳያሉ። የንጉሥ ዳዊትን ሕይወት በመመርመር በዚህ ረገድ ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ።

አንድ ክርስቲያን አባት የሚጸልይበት መንገድ ትሕትናውን የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት) *

15. ንጉሥ ዳዊት ለአባቶች ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

15 ይሖዋ ዳዊትን የቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን የመላው እስራኤል ብሔር ራስ አድርጎ ሾሞታል። ዳዊት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። ይህን ሥልጣኑን አላግባብ በመጠቀም ከባድ ስህተት የሠራባቸው ጊዜያት ነበሩ። (2 ሳሙ. 11:14, 15) ሆኖም የተሰጠውን ተግሣጽ በመቀበል ለይሖዋ እንደሚገዛ አሳይቷል። በጸሎት አማካኝነት የልቡን አውጥቶ ለይሖዋ ተናግሯል። እንዲሁም ይሖዋ የሰጠውን ምክር ለመታዘዝ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። (መዝ. 51:1-4) ከዚህም በተጨማሪ ትሑት በመሆን ከወንዶች ብቻ ሳይሆን ከሴቶችም ጭምር ምክር ተቀብሏል። (1 ሳሙ. 19:11, 12፤ 25:32, 33) ዳዊት ከስህተቱ የተማረ ሲሆን በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት መርቷል።

16. አባቶች ከዳዊት ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

16 አባቶች፣ ከንጉሥ ዳዊት የሚከተሉትን ትምህርቶች ማግኘት ትችላላችሁ፦ ይሖዋ የሰጣችሁን ሥልጣን አላግባብ አትጠቀሙበት። ስህተታችሁን አምናችሁ ተቀበሉ፤ እንዲሁም ሌሎች የሚሰጧችሁን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመስማት ፈቃደኞች ሁኑ። በዚህ መልኩ ትሕትና ማሳየታችሁ የቤተሰባችሁን አክብሮት ያተርፍላችኋል። ከቤተሰባችሁ ጋር ስትጸልዩ የልባችሁን አውጥታችሁ ለይሖዋ ተናገሩ፤ ቤተሰባችሁ ምን ያህል በይሖዋ እንደምትታመኑ እንዲያስተውሉ አድርጉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት ተጣጣሩ። (ዘዳ. 6:6-9) ለቤተሰባችሁ ልትሰጡ ከምትችሏቸው ውድ ስጦታዎች መካከል አንዱ የእናንተ መልካም ምሳሌነት ነው።

እናቶች ከማርያም ምን ትምህርት ያገኛሉ?

17. ይሖዋ ለእናቶች ምን ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል?

17 ይሖዋ ለእናቶች በቤተሰብ ውስጥ የተከበረ ቦታ ሰጥቷቸዋል፤ እናቶች በልጆቻቸው ላይ የተወሰነ ሥልጣን አላቸው። (ምሳሌ 6:20) እንዲያውም አንዲት እናት በልጆቿ ላይ የምታሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛና እስከ ዕድሜ ልክ የሚዘልቅ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 22:6) እናቶች ከኢየሱስ እናት ከማርያም ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ።

18-19. እናቶች ከማርያም ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

18 ማርያም ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቃ ታውቅ ነበር። ለይሖዋ ጥልቅ አክብሮት የነበራት ከመሆኑም ሌላ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርታ ነበር። መላ ሕይወቷን የሚነካባት ቢሆንም እንኳ ለይሖዋ አመራር ለመገዛት ፈቃደኛ ነበረች።—ሉቃስ 1:35-38, 46-55

እናቶች ድካም በሚሰማቸው ወይም የሚያበሳጭ ነገር በሚያጋጥማቸው ጊዜ ለቤተሰባቸው አባላት ፍቅራቸውን ለመግለጽ ከወትሮው የበለጠ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል (አንቀጽ 19⁠ን ተመልከት) *

19 እናቶች፣ የማርያምን ምሳሌ መከተል የምትችሉባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። አንደኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በግላችሁ በማጥናትና ብቻችሁን የምትጸልዩበት ጊዜ በመመደብ ከይሖዋ ጋር የመሠረታችሁትን የጠበቀ ወዳጅነት ይዛችሁ ቀጥሉ። ሁለተኛ፣ ይሖዋን ለማስደሰት ስትሉ በሕይወታችሁ ውስጥ ለውጦችን ለማድረግ ፈቃደኛ ሁኑ። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆቻችሁ በቀላሉ ቱግ የሚሉና ልጆቻቸውን ደግነት በጎደለው መንገድ የሚናገሩ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ማደጋችሁ ልጆችን እንዲህ ባለ መንገድ መያዝ ምንም ችግር እንደሌለው እንዲሰማችሁ አድርጓችሁ ይሆናል። የይሖዋን መሥፈርቶች ከተማራችሁ በኋላም እንኳ ልጆቻችሁን በተረጋጋ መንፈስ ማናገር ተፈታታኝ ሊሆንባችሁ ይችላል፤ በተለይ ደክሟችሁ ባለበት ሰዓት ልጆቻችሁ የሚያበሳጭ ነገር ሲያደርጉ እነሱን በትዕግሥት መያዝ ይበልጥ ከባድ እንደሚሆንባችሁ የታወቀ ነው። (ኤፌ. 4:31) እንዲህ ባሉ ጊዜያት ወደ ይሖዋ በመጸለይ የእሱን እርዳታ መጠየቃችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። ሊዲያ የተባለች እናት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ፣ ልጄ አልታዘዝ ሲለኝ በቁጣ ገንፍዬ እንዳልጮኽበት ወደ ይሖዋ አጥብቄ መጸለይ ያስፈልገኛል። እንዲያውም የጀመርኩትን ሐሳብ እንኳ ሳልጨርስ በልቤ ወደ ይሖዋ የጸለይኩባቸው ጊዜያት አሉ። ጸሎት እንድረጋጋ ይረዳኛል።”—መዝ. 37:5

20. አንዳንድ እናቶች ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? ይህን ሁኔታ መወጣት የሚችሉትስ እንዴት ነው?

20 አንዳንድ እናቶች የሚያጋጥማቸው ተፈታታኝ ሁኔታ ደግሞ ለልጆቻቸው ፍቅራቸውን መግለጽ የሚከብዳቸው መሆኑ ነው። (ቲቶ 2:3, 4) ምናልባትም አንዳንዶቹ ያደጉት በወላጆችና በልጆች መካከል ጥሩ ግንኙነት በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ሊሆን ይችላል። እናንተም ያደጋችሁት እንዲህ ባለ ቤተሰብ ውስጥ ከሆነ የወላጆቻችሁን ስህተት ላለመድገም ጥንቃቄ አድርጉ። ለይሖዋ ፈቃድ የምትገዛ እናት ለልጆቿ ፍቅር መግለጽን መማር ይኖርባታል። እርግጥ በውስጧ የሚሰማትን ስሜት እንዲሁም የምታስብበትንና ነገሮችን የምታከናውንበትን መንገድ መቀየር ይከብዳት ይሆናል። ሆኖም ይህ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር አይደለም። ደግሞም እነዚህን ለውጦች ማድረጓ ራሷንም ሆነ ቤተሰቧን ይጠቅማል።

ለይሖዋ መገዛታችሁን ቀጥሉ

21-22. በኢሳይያስ 65:13, 14 ላይ እንደተገለጸው ለይሖዋ መገዛት ምን በረከቶች ያስገኛል?

21 ንጉሥ ዳዊት ለይሖዋ መገዛት ምን ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የይሖዋ መመሪያዎች ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ የይሖዋ ትእዛዝ ንጹሕ ነው፤ ዓይንን ያበራል። ለአገልጋይህ ማስጠንቀቂያ ሆነውለታል፤ እነሱን መጠበቅ ትልቅ ወሮታ አለው።” (መዝ. 19:8, 11) በዛሬው ጊዜም ለይሖዋ ሥልጣን በሚገዙና የእሱን ፍቅራዊ ምክር ችላ በሚሉ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ይታያል። ለይሖዋ የሚገዙ ሰዎች “ከልባቸው ደስታ የተነሳ እልል ይላሉ።”—ኢሳይያስ 65:13, 14ን አንብብ።

22 ሽማግሌዎች፣ አባቶችና እናቶች ለይሖዋ በፈቃደኝነት ሲገዙ ሕይወታቸው ይሻሻላል፣ ቤተሰባቸው ይበልጥ ደስተኛ ይሆናል እንዲሁም በመላው ጉባኤ መካከል ያለው አንድነት ይጠናከራል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛሉ። (ምሳሌ 27:11) ከዚህ የበለጠ ደስታ የሚያስገኝ ምን ነገር ሊኖር ይችላል?

መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት

^ አን.5 ይህ ርዕስ ለይሖዋ መገዛት ያለብን ለምን እንደሆነ ያብራራል። በተጨማሪም ሽማግሌዎች፣ አባቶችና እናቶች ከይሖዋ የተሰጣቸውን የተወሰነ ሥልጣን በመጠቀም ረገድ ከአገረ ገዢው ከነህምያ፣ ከንጉሥ ዳዊትና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ምን ትምህርት እንደሚያገኙ ይገልጻል።

^ አን.1 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ መገዛት የሚለው ቃል፣ ተገደው ለሚታዘዙ ሰዎች አሉታዊ ትርጉም ያስተላልፋል። የአምላክ ሕዝቦች ግን አምላክን የሚታዘዙት በምርጫቸው ስለሆነ መገዛትን እንደ መጥፎ ነገር አይመለከቱትም።

^ አን.7 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.62 የሥዕሎቹ መግለጫ፦ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር በመገንባቱ ሥራ እንደተካፈለ ሁሉ አንድ የጉባኤ ሽማግሌም የስብሰባ አዳራሹን በመጠገኑ ሥራ ከልጁ ጋር ሲካፈል።

^ አን.64 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ አባት ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት ሲያቀርብ።

^ አን.66 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ልጅ ለበርካታ ሰዓታት የቪዲዮ ጌም ሲጫወት በመቆየቱ የታዘዘውን ሥራም ሆነ የተሰጠውን የቤት ሥራ ማጠናቀቅ አልቻለም። በሥራ ስትደክም የዋለች እናቱ ሳትጮኽበት ወይም ደግነት የጎደለው ንግግር ሳትናገረው በትዕግሥት እርማት ስትሰጠው።