በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 39

‘እነሆ፣ እጅግ ብዙ ሕዝብ’

‘እነሆ፣ እጅግ ብዙ ሕዝብ’

“እነሆ . . . አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ . . . በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር።”—ራእይ 7:9

መዝሙር 60 ስብከታችን ሰው ያድናል

ማስተዋወቂያ *

1. በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ የነበረበት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ አንድ የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ዮሐንስ በዚህ ወቅት በዕድሜ የገፋ ሲሆን ጳጥሞስ በተባለች ደሴት ላይ በእስር ይገኝ ነበር፤ ምናልባትም ከሐዋርያት መካከል በሕይወት ያለው እሱ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። (ራእይ 1:9) ተቃዋሚዎች ጉባኤዎችን እያሳሳቱና በወንድሞች መካከል ክፍፍል እየፈጠሩ እንዳሉ ማወቁ አስጨንቆታል። ጭል ጭል እያለ የነበረው የክርስትና ብርሃን ጨርሶ ሊጠፋ የተቃረበ ይመስል ነበር።—ይሁዳ 4፤ ራእይ 2:15, 20፤ 3:1, 17

ሐዋርያው ዮሐንስ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በራእይ ተመልክቷል፤ እነዚህ ሰዎች ነጭ ልብስ ለብሰውና የዘንባባ ዝንጣፊዎችን በእጆቻቸው ይዘው ነበር (አንቀጽ 2⁠ን ተመልከት)

2. በራእይ 7:9-14 ላይ እንደተገለጸው ዮሐንስ ምን አስደሳች ትንቢታዊ ራእይ ተመልክቷል? (ሽፋኑን ተመልከት።)

2 ዮሐንስ በዚህ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እያለ አንድ አስደሳች ትንቢታዊ ራእይ ተመለከተ። በራእዩ ላይ መላእክት፣ የአምላክን ባሪያዎች ያቀፈ አንድ ቡድን የመጨረሻው ማኅተም እስኪደረግበት ድረስ አውዳሚ የሆኑትን ነፋሳት አግደው እንዲይዙ ተነገራቸው። (ራእይ 7:1-3) ይህ ቡድን ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙትን 144,000 የአምላክ አገልጋዮች ያቀፈ ነው። (ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 7:4) ቀጥሎም ዮሐንስ ስለ አንድ ሌላ ቡድን ተናገረ፤ በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉት ሰዎች ብዛት ፈጽሞ ያልጠበቀው ስለሆነ ሳይሆን አይቀርም “እነሆ” የሚለውን አግራሞትን የሚያሳይ አገላለጽ ተጠቅሟል። ዮሐንስ የተመለከተው ምንድን ነው? “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ ነጭ ልብስ ለብሰው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር።” (ራእይ 7:9-14ን አንብብ።) ወደፊት ከእውነተኛው አምልኮ ጎን የሚሰለፉ እልፍ አእላፍ ሰዎች እንደሚኖሩ ሲያውቅ ዮሐንስ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን እስቲ አስቡት!

3. (ሀ) ዮሐንስ የተመለከተው ራእይ እምነታችንን ያጠናክርልናል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 ይህ ራእይ የዮሐንስን እምነት አጠናክሮለት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ራእዩ ፍጻሜውን እያገኘ ባለበት በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ደግሞ ይበልጥ እምነታችንን እንደሚያጠናክርልን ግልጽ ነው! ከታላቁ መከራ በሕይወት ተርፈው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሰበሰቡ በገዛ ዓይናችን የመመልከት አጋጣሚ አግኝተናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ይሖዋ ከ80 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የእጅግ ብዙ ሕዝብን ማንነት ለአገልጋዮቹ የገለጠው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚያም የዚህን ቡድን ሁለት ገጽታዎች ማለትም (1) ብዛቱን (2) ቡድኑ የተለያዩ ሰዎችን ያቀፈ መሆኑን እንመለከታለን። እነዚህን ነጥቦች በተመለከተ የምናገኘው ማብራሪያ ወደፊት ግሩም ተስፋ የተዘረጋላቸውን የዚህን ቡድን አባላት እምነት ያጠናክራል።

የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት የሚኖሩት የት ነው?

4. የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ያልተረዱት የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በዚህ ረገድ የተለዩ የሆኑትስ እንዴት ነው?

4 በጥቅሉ ሲታይ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ታዛዥ የሰው ልጆች ወደፊት በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አያስተምሩም። (2 ቆሮ. 4:3, 4) በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ጥሩ ሰዎች ሁሉ ሲሞቱ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ያስተምራሉ። በ1800ዎቹ መገባደጃ ላይ መጠበቂያ ግንብ የተባለውን መጽሔት ያዘጋጁ የነበሩት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት ነበራቸው። አምላክ በምድር ላይ ገነትን መልሶ እንደሚያቋቁምና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታዛዥ ሰዎች በሰማይ ላይ ሳይሆን በዚህችው ምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ ተገንዝበው ነበር። ሆኖም የእነዚህን ታዛዥ ሰዎች ማንነት በትክክል ለመረዳት የተወሰነ ጊዜ ወስዶባቸዋል።—ማቴ. 6:10

5. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ስለ 144,000ዎቹ ምን ተረድተው ነበር?

5 እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ‘ከምድር የተዋጁ’ የተወሰኑ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር በሰማይ እንደሚገዙም ከቅዱሳን መጻሕፍት ተረድተው ነበር። (ራእይ 14:3) ይህ ቡድን በምድር ላይ ሳሉ ራሳቸውን ወስነው አምላክን በቅንዓትና በታማኝነት ያገለገሉ 144,000 ክርስቲያኖችን ያቀፈ ነው። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላትን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?

6. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ስለ እጅግ ብዙ ሕዝብ ምን ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር?

6 ዮሐንስ በራእዩ ላይ ይህ ቡድን “በዙፋኑና በበጉ ፊት [ቆሞ]” ተመልክቷል። (ራእይ 7:9) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ከዚህ ራእይ በመነሳት ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ልክ እንደ 144,000ዎቹ ቅቡዓን በሰማይ ይኖራሉ’ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላትም ሆኑ 144,000ዎቹ ቅቡዓን በሰማይ የሚኖሩ ከሆነ አንዱ ቡድን ከሌላው የሚለየው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ራእዩ ላይ የተጠቀሰው እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ ምድር ላይ ሳሉ በተሟላ ሁኔታ ለአምላክ ታዛዥ ያልሆኑ ክርስቲያኖችን ያቀፈ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር። እነሱ እንደሚያስቡት እነዚህ ክርስቲያኖች በተወሰነ መጠንም ቢሆን በሥነ ምግባር ንጹሕ ሕይወት ቢመሩም አንዳንዶቹ ከሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች አልወጡ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ እነዚህ ሰዎች ቅንዓት ቢኖራቸውም ቅንዓታቸው ከኢየሱስ ጋር ለመግዛት የሚያበቃቸው እንዳልነበር ደምድመዋል። ለአምላክ ያላቸው ፍቅር የሚፈለገውን ያህል ጠንካራ ስላልነበር ወደ ሰማይ ሄደው በዙፋኑ ፊት መሆን ይችላሉ እንጂ በዙፋኖች ላይ መቀመጥ አይችሉም።

7. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በሺው ዓመት ግዛት ወቅት ምድር ላይ የሚኖሩት እነማን እንደሆኑ ያምኑ ነበር? በጥንት ዘመን ስለኖሩ ታማኝ ሰዎችስ ምን ብለው ያምኑ ነበር?

7 ታዲያ በምድር ላይ የሚኖሩት እነማን ናቸው? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ 144,000ዎቹና እጅግ ብዙ ሕዝብ ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች በምድር ላይ የመኖርና የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት የሚያመጣቸውን በረከቶች የማጣጣም አጋጣሚ እንደሚያገኙ ያምኑ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ እነዚህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የክርስቶስ ግዛት ከመጀመሩ በፊት የይሖዋ አገልጋዮች ይሆናሉ ብለው አይጠብቁም ነበር። ከዚህ ይልቅ ይህ ቡድን በሺው ዓመት ግዛት ወቅት የይሖዋን መንገዶች እንደሚማር ያስቡ ነበር። ከዚያ በኋላ የይሖዋን መሥፈርቶች የሚጠብቁ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ የሚሰጣቸው ሲሆን የሚያምፁት ደግሞ ይጠፋሉ። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ፣ ከሞት የተነሱትን “የጥንቶቹን ጻድቃን” ማለትም ከክርስቶስ በፊት የሞቱትን ታማኝ ሰዎች ጨምሮ በዚያ ወቅት በምድር ላይ “መኳንንት” ሆነው የሚያገለግሉ አንዳንድ ሰዎች በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ በሆነ መንገድ ሰማያዊ ሕይወት በማግኘት ወሮታ ሊከፈላቸው እንደሚችል ያምኑ ነበር።—መዝ. 45:16

8. በአምላክ ዓላማ ውስጥ ቦታ አላቸው ተብለው ይታሰቡ የነበሩት የትኞቹ ሦስት ቡድኖች ናቸው?

8 በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ሦስት የተለያዩ ቡድኖች እንዳሉ ያምኑ ነበር፦ (1) ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙት 144,000 ሰዎች (2) በቂ ቅንዓት ሳያሳዩ ከቀሩ ሰዎች የተውጣጣውና በኢየሱስ ዙፋን ፊት የሚቆመው እጅግ ብዙ ሕዝብ (3) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት እዚህ ምድር ላይ እየኖሩ ስለ ይሖዋ መንገዶች የሚማሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች። * ሆኖም ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በዚህ ጉዳይ ላይ የእውነት ብርሃን ይበልጥ በድምቀት መብራት ጀመረ።—ምሳሌ 4:18

የእውነት ብርሃን ይበልጥ በድምቀት በራ

በ1935 በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው በርካታ ሰዎች ተጠመቁ (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)

9. (ሀ) በምድር ላይ የሚኖረው እጅግ ብዙ ሕዝብ ‘በዙፋኑና በበጉ ፊት የሚቆመው’ እንዴት ነው? (ለ) ራእይ 7:9⁠ን በምንረዳበት መንገድ ላይ የተደረገው ማስተካከያ ምክንያታዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

9 በ1935፣ ዮሐንስ በራእይ ስለተመለከተው እጅግ ብዙ ሕዝብ ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ተደረገ። የይሖዋ ምሥክሮች እጅግ ብዙ ሕዝብ “በዙፋኑና በበጉ ፊት [ለመቆም]” ቃል በቃል በሰማይ መሆን እንደማያስፈልገው ከዚህ ይልቅ ይህ አገላለጽ ምሳሌያዊ እንደሆነ ተገነዘቡ። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት የሚኖሩት ምድር ላይ ቢሆንም የይሖዋን ሥልጣን በመቀበልና ለእሱ ሉዓላዊነት በመገዛት ‘በዙፋኑ ፊት እንደቆሙ’ ያሳያሉ። (ኢሳ. 66:1) እንዲሁም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን ‘በበጉ ፊት ይቆማሉ።’ በማቴዎስ 25:31, 32 ላይ ተመሳሳይ አገላለጽ እናገኛለን፤ በዚህ ጥቅስ ላይ ክፉዎችን ጨምሮ “ሕዝቦች ሁሉ” በክብራማ ዙፋኑ ላይ በተቀመጠው በኢየሱስ ‘ፊት እንደሚሰበሰቡ’ ተገልጿል። እነዚህ ሕዝቦች የሚሰበሰቡት ምድር ላይ እንጂ ሰማይ ላይ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። በዚህ ረገድ የተደረገው ማስተካከያ ምክንያታዊ ነው። ይህ ማስተካከያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ብዙ ሕዝብ ወደ ሰማይ እንደሚሄድ የማይናገረው ለምን እንደሆነ ግልጽ ያደርጋል። በሰማይ ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝ ቃል የተገባለት አንድ ቡድን ብቻ ነው፤ የዚህ ቡድን አባላት ከኢየሱስ ጋር ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው የሚገዙት’ 144,000 ሰዎች ናቸው።—ራእይ 5:10

10. የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት የሺህ ዓመቱ ግዛት ከመጀመሩ በፊት የይሖዋን መንገዶች መማር ያለባቸው ለምንድን ነው?

10 በመሆኑም ከ1935 አንስቶ የይሖዋ ምሥክሮች ዮሐንስ በራእይ የተመለከተው እጅግ ብዙ ሕዝብ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን ታማኝ ክርስቲያኖች ያቀፈ ቡድን እንደሆነ ተገነዘቡ። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ከታላቁ መከራ ለመትረፍ የሺህ ዓመቱ ግዛት ከመጀመሩ በፊት የይሖዋን መንገዶች መማር ይኖርባቸዋል። ወደፊት “መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች [ለማምለጥ]” የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ማሳየት አለባቸው።—ሉቃስ 21:34-36

11. አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ‘አንዳንዶች ከሺህ ዓመቱ ግዛት በኋላ ወደ ሰማይ ሊሄዱ ይችላሉ’ ብለው ያስቡ የነበረው ለምን ሊሆን ይችላል?

11 ‘እንደ ምሳሌ የሚታዩ በምድር ላይ የኖሩ አንዳንድ ሰዎች ከሺህ ዓመቱ ግዛት በኋላ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ’ የሚለውን እምነት በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? በየካቲት 15, 1913 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ ይህን የሚጠቁም ሐሳብ ወጥቶ ነበር። ይህ ሐሳብ (1) የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት የሚኖሩት በሰማይ ነው፣ (2) እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ በቂ ቅንዓት ሳያሳዩ ከቀሩ ክርስቲያኖች የተውጣጣ ነው ከሚሉት ሁለት የተሳሳቱ አመለካከቶች የመነጨ ነው። ሆኖም አንድ ሰው እንዲህ የሚል ጥያቄ ሊፈጠርበት ይችላል፦ ‘በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ ሰዎች ምድራዊ ውርሻ እንዲኖራቸው ተደርጎ ያን ያህል ቅንዓት ያላሳዩ ክርስቲያኖች ግን በሰማይ የመኖር ተስፋ የሚሰጣቸው ለምንድን ነው?’

12-13. ቅቡዓንም ሆኑ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ሽልማታቸውን በተመለከተ ምን ይገነዘባሉ?

12 ይሁንና ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከአርማጌዶን እንደሚተርፉ የተገለጹት ሰዎች ዮሐንስ በራእይ የተመለከተው እጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት እንደሆኑ ከ1935 አንስቶ በግልጽ ተረድተው ነበር። እነዚህ ሰዎች እዚሁ ምድር ላይ ‘ከታላቁ መከራ የሚያልፉ’ ሲሆን “[በታላቅ] ድምፅ እየጮኹ ‘መዳን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ ነው’” ይላሉ። (ራእይ 7:10, 14) ከዚህም በተጨማሪ ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ሕይወት የሚያገኙት ሰዎች በጥንት ዘመን ከኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች “የተሻለ ነገር” እንደሚያገኙ ቅዱሳን መጻሕፍት ያስተምራሉ። (ዕብ. 11:40) በ1935 የተገኘው ይህ አዲስ ግንዛቤ ወንድሞቻችን፣ የይሖዋ አገልጋዮች የሚሆኑና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ የሚያገኙ ሰዎችን በቅንዓት እንዲፈልጉ አነሳስቷቸዋል።

13 የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት በተዘረጋላቸው ተስፋ ደስተኞች ናቸው። ታማኝ አምላኪዎቹ የሚያገለግሉት በሰማይ ይሁን በምድር የሚወስነው ይሖዋ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ቅቡዓንም ሆኑ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ሽልማታቸውን ሊያገኙ የቻሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት በተገለጠው የይሖዋ ጸጋ የተነሳ እንደሆነ ይረዳሉ።—ሮም 3:24

ብዙ ሰዎች

14. ከ1935 በኋላ ብዙዎች ስለ እጅግ ብዙ ሕዝብ የሚናገረው ትንቢት የሚፈጸመው እንዴት እንደሆነ ያሳስባቸው የነበረው ለምንድን ነው?

14 በ1935 የይሖዋ ሕዝቦች ቀደም ሲል በነበራቸው ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ካደረጉ በኋላ ብዙዎች ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ቁጥር “እጅግ ብዙ” የሚሆነው እንዴት እንደሆነ ያሳስባቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሮናልድ ፓርኪን የእጅግ ብዙ ሕዝብ ማንነት ግልጽ በተደረገ ጊዜ የ12 ዓመት ልጅ ነበር። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያን ጊዜ በዓለም ዙሪያ የነበሩት አስፋፊዎች 56,000 ገደማ ነበሩ፤ ደግሞም በርካታ አስፋፊዎች፣ ምናልባትም አብዛኞቹ ቅቡዓን ናቸው። በመሆኑም የእጅግ ብዙ ሕዝብ ቁጥር ያን ያህል ብዙ አይመስልም ነበር።”

15. የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ቁጥር እየጨመረ የመጣው እንዴት ነው?

15 ሆኖም በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት ሚስዮናውያን ወደተለያዩ አገሮች የተላኩ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር እየጨመረ ሄደ። ከዚያም በ1968 ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ተጀመረ። መጽሐፉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ቀላል በሆነ መንገድ ስለሚያብራራ ቅን ልብ ያላቸውን በርካታ ሰዎች መማረክ ችሏል። በአራት ዓመት ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ተጠምቀዋል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በላቲን አሜሪካና በሌሎች አገሮች ላይ የምታሳድረው ተጽዕኖ እየቀነሰ ሲሄድ እንዲሁም በምሥራቅ አውሮፓና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በሥራችን ላይ የተጣለው ገደብ ቀስ በቀስ ሲነሳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ተጠመቁ። (ኢሳ. 60:22) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የይሖዋ ድርጅት፣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ የሚረዱ ተጨማሪ ውጤታማ መሣሪያዎችን አዘጋጅቷል። በእርግጥም በዛሬው ጊዜ ያሉትን ከስምንት ሚሊዮን የሚበልጡ አስፋፊዎች ስናይ በትንቢት እንደተነገረው እጅግ ብዙ ሕዝብ እየተሰበሰበ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ከተለያዩ ሕዝቦች የተውጣጡ

16. እጅግ ብዙ ሕዝብ ከእነማን የተውጣጣ ነው?

16 ዮሐንስ ራእዩን ሲጽፍ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ” እንደሆኑ ገልጿል። ነቢዩ ዘካርያስም ከዚያ በፊት ተመሳሳይ ነገር ተንብዮ ነበር፤ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያን ጊዜ ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ ‘አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን’ ይላሉ።”—ዘካ. 8:23

17. ከሁሉም ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሰዎችን ለመርዳት ምን እየተደረገ ነው?

17 የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከሁሉም ቋንቋዎች የተውጣጡ ሰዎች እንዲሰበሰቡ ከተፈለገ ምሥራቹ በብዙ ቋንቋዎች መሰበክ እንዳለበት ተገንዝበዋል። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎችን ከ130 ለሚበልጡ ዓመታት ሲተረጉሙ ቆይተዋል፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ጽሑፎቻችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች እየተተረጎሙ ነው። ይሖዋ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላትን ከሁሉም ብሔራት በመሰብሰብ በዘመናችን ድንቅ ተአምር እየፈጸመ እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል። መንፈሳዊ ምግብ የሚቀርብባቸው ቋንቋዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመሩ በመሄዳቸው ከተለያዩ ሕዝቦች የተውጣጣው ይህ ቡድን በአምልኮ አንድ ሊሆን ችሏል። ደግሞም የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ በቅንዓት በመካፈላቸውና የወንድማማች ፍቅር በማሳየታቸው ተለይተው ይታወቃሉ። ይህ እንዴት እምነት የሚያጠናክር ነው!—ማቴ. 24:14፤ ዮሐ. 13:35

ራእዩ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

18. (ሀ) በኢሳይያስ 46:10, 11 መሠረት ይሖዋ ስለ እጅግ ብዙ ሕዝብ የሚናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ማድረጉ የማያስገርመን ለምንድን ነው? (ለ) በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎች የሆነ ነገር እንደቀረባቸው የማይሰማቸው ለምንድን ነው?

18 ስለ እጅግ ብዙ ሕዝብ የሚናገረው ትንቢት በጣም አስደሳች ነው! ይሖዋ ይህ ትንቢት አስደናቂ በሆነ መንገድ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ማድረጉ አያስገርመንም። (ኢሳይያስ 46:10, 11ን አንብብ።) የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ይሖዋ ለሰጣቸው ተስፋ አመስጋኞች ናቸው። ከኢየሱስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ በአምላክ መንፈስ ስላልተቀቡ የሆነ ነገር እንደቀረባቸው አይሰማቸውም። ቅዱሳን መጻሕፍት መንፈስ ቅዱስ በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ይናገራሉ፤ ሆኖም እነዚህ ሰዎች የ144,000ዎቹ አባል አይደሉም። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ነው። (ማቴ. 11:11) ሌላው ደግሞ ዳዊት ነው። (ሥራ 2:34) እነዚህን ጨምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸው በርካታ ሰዎች ከሞት ተነስተው ገነት በሆነች ምድር ላይ ይኖራሉ። ሁሉም ከእጅግ ብዙ ሕዝብ ጋር በመሆን ለይሖዋ ታማኝ እንደሆኑና ሉዓላዊነቱን እንደሚደግፉ የሚያሳዩበት አጋጣሚ ያገኛሉ።

19. ዮሐንስ ስለ እጅግ ብዙ ሕዝብ የተመለከተው ራእይ ፍጻሜ የምንኖርበትን ዘመን አጣዳፊነት የሚያሳየው እንዴት ነው?

19 አምላክ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የአሁኑን ያህል ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድነት እሱን እንዲያመልኩ ያደረገበት ጊዜ የለም። ተስፋችን በሰማይ መኖርም ሆነ በምድር፣ የቻልነውን ያህል ብዙ ሰዎች ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆነው የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባል እንዲሆኑ መርዳት ይኖርብናል። (ዮሐ. 10:16) በቅርቡ ይሖዋ በትንቢት የተነገረውን ታላቁን መከራ ያመጣል፤ በዚያን ጊዜ በሰው ዘር ላይ መከራ ያስከተሉት መንግሥታትና ሃይማኖቶች ይጠፋሉ። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ይጠብቃቸዋል! ይሖዋን በምድር ላይ ለዘላለም የማገልገል አጋጣሚ ያገኛሉ።—ራእይ 7:14

መዝሙር 139 በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ

^ አን.5 ይህ ርዕስ ዮሐንስ ስለ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” መሰብሰብ ያየውን ትንቢታዊ ራእይ ያብራራል። የራእዩ ማብራሪያ የዚህ ግሩም ተስፋ ተካፋይ የሆኑትን ሰዎች እምነት እንደሚያጠናክር ምንም ጥርጥር የለውም።

^ አን.8 የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 159-163 ተመልከት።