በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 38

“ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ”

“ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ”

“እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ።”—ማቴ. 11:28

መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”

ማስተዋወቂያ *

1. በማቴዎስ 11:28-30 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ኢየሱስ ምን ተስፋ ሰጥቷል?

ኢየሱስ ተሰብስቦ ያዳምጠው ለነበረው ሕዝብ አንድ አስደሳች ተስፋ ሰጠ። “ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ” በማለት ተናገረ። (ማቴዎስ 11:28-30ን አንብብ።) ይህ እንዲሁ ባዶ ተስፋ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በአስከፊ ሕመም ትሠቃይ ለነበረች አንዲት ሴት ምን እንዳደረገላት እንመልከት።

2. ኢየሱስ ለአንዲት የታመመች ሴት ምን አደረገላት?

2 ይህች ሴት ያለችበት ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነበር። ከሕመሟ ፈውስ ለማግኘት ስትል ብዙ ሐኪሞች ጋ ሄዳለች። ለ12 ዓመት ያህል በከባድ ሕመም ብትሠቃይም ምንም መፍትሔ ማግኘት አልቻለችም። ሴትየዋ በሕጉ መሠረት እንደ ርኩስ ትቆጠር ነበር። (ዘሌ. 15:25) ከጊዜ በኋላ ግን ኢየሱስ የታመሙትን እንደሚፈውስ ሰማች። በመሆኑም እሱን ፍለጋ ሄደች። ባገኘችው ጊዜ ሄዳ የልብሱን ዘርፍ ነካች፤ ወዲያውኑም ከሕመሟ ተፈወሰች! ሆኖም ኢየሱስ ሴትየዋ አካላዊ ፈውስ እንድታገኝ በማድረግ ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ ሰብዓዊ ክብሯንም መልሳ እንድታገኝ ረድቷታል። ለምሳሌ ከእሷ ጋር ሲያወራ አክብሮትና ወዳጃዊ ስሜት የሚንጸባረቅበትን “ልጄ ሆይ” የሚለውን አገላለጽ ተጠቅሟል። ይህች ሴት ምንኛ ተበረታታና እረፍት አግኝታ ይሆን!—ሉቃስ 8:43-48

3. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 ሴትየዋ ከሕመሟ ፈውስ ለማግኘት ቅድሚያውን ወስዳ ወደ ኢየሱስ እንደሄደች ልብ በሉ። በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ እኛ ራሳችን ቅድሚያውን መውሰድ አለብን። በዘመናችን ኢየሱስ ወደ እሱ የሚመጡትን ሰዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከአካላዊ ሕመማቸው አይፈውሳቸውም። ሆኖም “ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ” የሚል ግብዣ አቅርቦልናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን አምስት ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ ወደ ኢየሱስ መሄድ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “ቀንበሬን ተሸከሙ” ሲል ምን ማለቱ ነው? ከኢየሱስ ምን እንማራለን? ኢየሱስ የሰጠን ሥራ እረፍት ይሰጣል የምንለው ለምንድን ነው? በኢየሱስ ቀንበር ሥር ምንጊዜም እረፍት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

“ወደ እኔ ኑ”

4-5. ወደ ኢየሱስ የምንሄድባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

4 ወደ ኢየሱስ የምንሄድበት አንዱ መንገድ እሱ ስለተናገራቸውና ስላደረጋቸው ነገሮች የቻልነውን ያህል በመማር ነው። (ሉቃስ 1:1-4) በእኛ ምትክ ይህን ሊያደርግልን የሚችል ሌላ ሰው የለም፤ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩትን ዘገባዎች እኛ ራሳችን ልናጠናቸው ይገባል። በተጨማሪም ለመጠመቅና የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ውሳኔ በማድረግ ወደ ኢየሱስ መሄድ እንችላለን።

5 ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ” በማለት ያቀረበውን ግብዣ የምንቀበልበት ሌላው መንገድ ደግሞ እርዳታ ሲያስፈልገን ወደ ጉባኤ ሽማግሌዎች መሄድ ነው። ኢየሱስ በጎቹን ለመንከባከብ እነዚህን ‘ስጦታ የሆኑ ሰዎች’ ይጠቀማል። (ኤፌ. 4:7, 8, 11፤ ዮሐ. 21:16፤ 1 ጴጥ. 5:1-3) ቅድሚያውን ወስደን የእነሱን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አለብን። ሽማግሌዎች ልባችንን አንብበው ምን እንደሚያስፈልገን እንዲያውቁ ልንጠብቅ አንችልም። ጁሊየን የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በጤና እክል ምክንያት ከቤቴል ለመውጣት በተገደድኩ ጊዜ አንድ ጓደኛዬ ሽማግሌዎች እረኝነት እንዲያደርጉልኝ እንድጠይቅ አበረታታኝ። መጀመሪያ ላይ እረኝነት እንደሚያስፈልገኝ አልተሰማኝም ነበር። በኋላ ላይ ግን የሽማግሌዎችን እርዳታ ጠየቅኩ። እነሱ ያደረጉልኝ የእረኝነት ጉብኝት እስከዛሬ ከተቀበልኳቸው ልዩ ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው።” ለጁሊየን እረኝነት እንዳደረጉለት ሁለት ወንድሞች ያሉ ታማኝ ሽማግሌዎች ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ እንድናውቅ ማለትም የእሱን አመለካከት እንድንረዳና አርዓያውን እንድንከተል ያግዙናል። (1 ቆሮ. 2:16፤ 1 ጴጥ. 2:21) በእርግጥም ይህ ከእነሱ ልንቀበለው የምንችለው ከሁሉ የላቀ ስጦታ ነው።

“ቀንበሬን ተሸከሙ”

6. ኢየሱስ “ቀንበሬን ተሸከሙ” ሲል ምን ማለቱ ሊሆን ይችላል?

6 ኢየሱስ “ቀንበሬን ተሸከሙ” ሲል “ሥልጣኔን ተቀበሉ” ማለቱ ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ “ከእኔ ጋር በአንድ ቀንበር ሥር ሆነን ለይሖዋ እንሥራ” ማለቱ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ቀንበሩን መሸከም ሥራ ይጠይቃል።

7. በማቴዎስ 28:18-20 መሠረት ምን ሥራ ተሰጥቶናል? ስለ ምን ነገርስ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

7 ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ስንጠመቅ የኢየሱስን ግብዣ እንቀበላለን። ይህ ግብዣ ለሁሉም ክፍት ነው። ኢየሱስ ከልቡ አምላክን ማገልገል የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው ከመቀበል ወደኋላ አይልም። (ዮሐ. 6:37, 38) ሁሉም የክርስቶስ ተከታዮች ይሖዋ ለኢየሱስ በሰጠው ሥራ የመካፈል መብት ተሰጥቷቸዋል። ይህን ሥራ ስናከናውን ኢየሱስ ሁሌም ከጎናችን ሆኖ እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን።—ማቴዎስ 28:18-20ን አንብብ።

‘ከእኔ ተማሩ’

ልክ እንደ ኢየሱስ ለሌሎች የእረፍት ምንጭ ሁኑ (ከአንቀጽ 8-11⁠ን ተመልከት) *

8-9. ትሑት የሆኑ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መቅረብ ይቀላቸው የነበረው ለምንድን ነው? የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል?

8 ትሑት የሆኑ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መቅረብ ይቀላቸው ነበር። (ማቴ. 19:13, 14፤ ሉቃስ 7:37, 38) ለምን? በኢየሱስና በፈሪሳውያን መካከል ያለውን ልዩነት እስቲ እንመልከት። የሃይማኖት መሪዎች የነበሩት ፈሪሳውያን ጨካኝና ኩሩ ነበሩ። (ማቴ. 12:9-14) ኢየሱስ ግን አፍቃሪና ትሑት ነበር። ፈሪሳውያን ከሌሎች ልቀው ለመታየት ይጣጣሩ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በማኅበረሰቡ ውስጥ በነበራቸው ከፍተኛ ቦታ ይኩራሩ ነበር። ኢየሱስ ግን ከሌሎች ልቆ ለመታየት የመፈለግ ዝንባሌን ያወገዘ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ ራሳቸውን እንደ ተራ አገልጋይ እንዲቆጥሩ አስተምሯል። (ማቴ. 23:2, 6-11) ፈሪሳውያን ሕዝቡን በማስፈራራትና በማሸማቀቅ እንዲገዛላቸው ያደርጉ ነበር። (ዮሐ. 9:13, 22) ኢየሱስ ግን ፍቅርና ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት በመናገር ለሌሎች የእረፍት ምንጭ ሆኗል።

9 እናንተስ በዚህ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ታደርጋላችሁ? ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ሌሎች የሚመለከቱኝ ገርና ትሑት እንደሆንኩ አድርገው ነው? ሌሎችን ለማገልገል ስል ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቃደኛ ነኝ? ለሰዎች ደግነት አሳያለሁ?’

10. ከኢየሱስ ጋር መሥራት ምን ይመስል ነበር?

10 ኢየሱስ ተከታዮቹ ከእሱ ጋር ሲሠሩ ሰላምና ደስታ እንዲያገኙ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ እነሱን ማሠልጠን ያስደስተው ነበር። (ሉቃስ 10:1, 19-21) ደቀ መዛሙርቱን ጥያቄ እንዲጠይቁ ያበረታታቸው የነበረ ሲሆን እነሱ የሚሰጡትን ሐሳብ የመስማት ፍላጎትም ነበረው። (ማቴ. 16:13-16) በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ አመቺ በሆነ ቦታ ላይ እንደተተከለ ተክል ሊያብቡ ችለዋል። ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶች በሚገባ ስለቀሰሙ መልካም ሥራዎችን በመሥራት ፍሬ ለማፍራት በቅተዋል።

አፍቃሪና የምትቀረቡ ሁኑ

ንቁና ቀናተኛ ሁኑ

ትሑትና ትጉ ሁኑ *

11. የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል?

11 ኃላፊነት ያለህ ሰው ነህ? ከሆነ ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ ‘አብረውኝ የሚሠሩትን ሰዎች ወይም የቤተሰቤን አባላት የምይዘው እንዴት ነው? ሰላማዊ ሁኔታ እንዲሰፍን አደርጋለሁ? ሌሎች ጥያቄ እንዲጠይቁ አበረታታለሁ? እነሱ የሚሰጡትን ሐሳብ ለመስማትስ ፈቃደኛ ነኝ?’ ጥያቄ የሚጠይቋቸውን ሰዎች የሚጠሉትንና ከእነሱ የተለየ ሐሳብ የሚሰነዝሩ ሰዎችን እንደ ጠላት አድርገው የሚመለከቱትን ፈሪሳውያንን መምሰል ፈጽሞ እንደማንፈልግ የታወቀ ነው።—ማር. 3:1-6፤ ዮሐ. 9:29-34

“እረፍት ታገኛላችሁ”

12-14. ኢየሱስ የሰጠን ሥራ እረፍት የሚያስገኝ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ኢየሱስ የሰጠንን ሥራ መሥራት እረፍት ያስገኝልናል የምንለው ለምንድን ነው? ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት።

13 ከሁሉ የተሻሉ አሠሪዎች አሉን። ዋነኛው አሠሪያችን ይሖዋ ምስጋና ቢስ ወይም ጨካኝ አለቃ አይደለም። የምናከናውነውን ሥራ ያደንቃል። (ዕብ. 6:10) በተጨማሪም የኃላፊነት ሸክማችንን ለመሸከም የሚያስፈልገንን ኃይል ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 4:7፤ ገላ. 6:5) ንጉሣችን ኢየሱስ ደግሞ የሚመራን እሱ ራሱ ምሳሌ በመሆን ነው። (ዮሐ. 13:15) እንዲንከባከቡን የተሾሙት ሽማግሌዎችም “ታላቅ የበጎች እረኛ” የሆነውን ኢየሱስን ለመምሰል ይጣጣራሉ። (ዕብ. 13:20፤ 1 ጴጥ. 5:2) መንጋውን የመመገብና የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ደግ፣ ደፋርና ሌሎችን የሚያበረታቱ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ።

14 ከሁሉ የተሻሉ የሥራ ባልደረቦች አሉን። በዓለም ላይ የእኛን ያህል ትልቅ ዓላማ ያለው ሥራ የሚያከናውንና በፍቅር የተሳሰረ ሕዝብ የለም። እስቲ አስቡት፦ ከሁሉ የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ከሚከተሉ ሆኖም ራሳቸውን ከማያመጻድቁ ሰዎች ጋር አብረን የመሥራት መብት አግኝተናል። እነዚህ ሰዎች በሥራቸው የተካኑ ቢሆኑም ትሑት ናቸው፤ እንዲሁም ሌሎች ከእነሱ የተሻሉ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። እኛን የሚመለከቱን እንደ ሥራ ባልደረባቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ወዳጃቸው አድርገው ነው። ከእኛ ጋር ያላቸው ወዳጅነት በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ሕይወታቸውንም ጭምር ለእኛ ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው!

15. እየሠራን ላለነው ሥራ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

15 ከሁሉ የተሻለ ሥራ አለን። ሰዎች ስለ ይሖዋ እውነቱን እንዲያውቁ እንረዳለን፤ እንዲሁም የዲያብሎስን ውሸቶች እናጋልጣለን። (ዮሐ. 8:44) ሰይጣን በሰዎች ላይ ሊሸከሙት የማይችሉት ሸክም ይጭንባቸዋል። ለምሳሌ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንደማይለንና ፈጽሞ ሊወደን እንደማይችል እንድናምን ይፈልጋል። ይህ ውሸት ከባድ ሸክም ከመሆኑም ሌላ ስሜት የሚደቁስ ነው! ክርስቶስ “ወደ እኔ ኑ” በማለት ያቀረበልንን ግብዣ ስንቀበል የኃጢአት ይቅርታ እናገኛለን። እንደ እውነቱ ከሆነ ደግሞ ይሖዋ ሁላችንንም በጣም ይወደናል። (ሮም 8:32, 38, 39) ሰዎች በይሖዋ እንዲታመኑና ሕይወታቸውን እንዲለውጡ መርዳት እንዴት ያለ እርካታ የሚሰጥ ሥራ ነው!

በኢየሱስ ቀንበር ሥር ምንጊዜም እረፍት ማግኘት

16. ኢየሱስ እንድንሸከመው የነገረን ሸክም፣ ልንሸከማቸው ከሚገቡን ሌሎች ሸክሞች የሚለየው እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ እንድንሸከመው የነገረን ሸክም፣ ልንሸከማቸው ከሚገቡን ሌሎች ሸክሞች የተለየ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች በሥራ ሲደክሙ ውለው ማታ ላይ ኃይላቸው የሚሟጠጥ ከመሆኑም በላይ ከሥራቸው ምንም እርካታ አያገኙም። በተቃራኒው ግን ይሖዋንና ክርስቶስን ስናገለግል ከቆየን በኋላ ከፍተኛ እርካታ ይሰማናል። አንዳንዴ ከሥራ በኋላ በጣም ስለሚደክመን ምሽት ላይ በጉባኤ ስብሰባ ለመገኘት ራሳችንን ማስገደድ ይጠይቅብን ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ከስብሰባ የምንመለሰው ታድሰንና ተበረታተን ነው። አገልግሎት ለመውጣትና መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን ለማጥናት ከምናደርገው ጥረት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ የምናገኘው በረከት ከምንከፍለው መሥዋዕት እጅግ የላቀ ነው!

17. እውነታውን አምነን መቀበልና ጠንቃቃ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

17 ይሁንና እውነታውን አምነን መቀበል ይኖርብናል። ሁላችንም ያለን ኃይል ውስን ነው። በመሆኑም ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ለማድረግ እንዳንሞክር መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለምሳሌ ቁሳዊ ሀብት ለማካበት ስንል ብዙ በመድከም ኃይላችንን እናባክን ይሆናል። ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” በማለት ለጠየቀው ሀብታም ወጣት ምን መልስ እንደሰጠው ልብ በሉ። ይህ ወጣት ቀድሞውንም ሕጉን ይጠብቅ ነበር። የማርቆስ ወንጌል ኢየሱስ ወጣቱን ‘እንደወደደው’ ስለሚናገር ይህ ወጣት ጥሩ ሰው መሆን አለበት። ኢየሱስ ለዚህ ወጣት ገዢ አንድ ግብዣ አቀረበለት። “ሂድና ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ . . . ተከታዬ ሁን” አለው። ይህ ሰው በቀረበለት ግብዣ ምክንያት ልቡ ቢከፈልም ያለውን “ብዙ ንብረት” ለመተው ፈቃደኛ አልሆነም። (ማር. 10:17-22) በዚህም የተነሳ የኢየሱስን ቀንበር ለመሸከም እንቢተኛ በመሆን “ለሀብት” ባሪያ ሆኖ መገዛቱን ቀጠለ። (ማቴ. 6:24) አንተ ብትሆን ምን ውሳኔ ታደርግ ነበር?

18. አልፎ አልፎ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

18 በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ እየሰጠናቸው ያሉትን ነገሮች በየጊዜው መለስ ብለን መገምገማችን አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን ኃይላችንን በጥበብ እየተጠቀምንበት መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ያስችለናል። ማርክ የተባለ ወጣት እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “ለብዙ ዓመታት፣ ቀላል ሕይወት እየመራሁ እንዳለሁ ይሰማኝ ነበር። አቅኚ የነበርኩ ቢሆንም ሁሌም የማስበው ገንዘብ ስለ ማግኘትና የተደላደለ ኑሮ ስለ መምራት ነበር። ‘ሕይወቴ ይህን ያህል በውጥረት የተሞላው ለምንድን ነው?’ ብዬ አስብ ነበር። ከዚያም በዋነኝነት እያተኮርኩ ያለሁት በራሴ ፍላጎት ላይ እንደሆነና ለይሖዋ እየሰጠሁ ያለሁት ከራሴ የተረፈውን ጊዜና ጉልበት እንደሆነ ተገነዘብኩ።” ማርክ አስተሳሰቡንና አኗኗሩን በማስተካከል በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ተሳትፎ ለማድረግ ራሱን አቀረበ። እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ገንዘብ የምጨነቅባቸው ጊዜያት አሉ። ሆኖም በይሖዋና በኢየሱስ እርዳታ፣ ተፈታታኝ የሆኑብኝን ነገሮች መወጣት ችያለሁ።”

19. ትክክለኛውን አመለካከት መያዝ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

19 በኢየሱስ ቀንበር ሥር ምንጊዜም እረፍት ማግኘት ከፈለግን ሦስት ነገሮች ማድረግ ያስፈልገናል። አንደኛ፣ ትክክለኛውን አመለካከት መያዝ። የምንሠራው የይሖዋን ሥራ ስለሆነ ሥራውን በእሱ መንገድ መሥራት አለብን። እኛ ሠራተኞች፣ ይሖዋ ደግሞ አሠሪያችን ነው። (ሉቃስ 17:10) የይሖዋን ሥራ በራሳችን መንገድ ለመሥራት መሞከር ከቀንበሩ ጋር እንደ መታገል ይቆጠራል። ጠንካራ የሆነ በሬም እንኳ በተደጋጋሚ በራሱ አቅጣጫ በመሄድ ጌታው ከሚቆጣጠረው ቀንበር ጋር የሚታገል ከሆነ ራሱን ሊጎዳና ሊያደክም ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋን አመራር የምንከተል ከሆነ የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን እንኳ ማከናወንና ማንኛውንም እንቅፋት መወጣት እንችላለን። የይሖዋ ፈቃድ እንዳይፈጸም ሊያግድ የሚችል ማንም እንደሌለ እናስታውስ!—ሮም 8:31፤ 1 ዮሐ. 4:4

20. የኢየሱስን ቀንበር ለመሸከም የሚያነሳሳን ውስጣዊ ግፊት ምን መሆን አለበት?

20 ሁለተኛ፣ በትክክለኛው ውስጣዊ ግፊት ተነሳስቶ መሥራት። ግባችን አፍቃሪ የሆነውን አባታችንን ይሖዋን ማስከበር ነው። በስግብግብነት ወይም በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ክርስቶስን ይከተሉ የነበሩ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ሰዎች ብዙም ሳይቆይ ደስታቸውን ያጡ ሲሆን የኢየሱስን ቀንበር መሸከማቸውን አቁመዋል። (ዮሐ. 6:25-27, 51, 60, 66፤ ፊልጵ. 3:18, 19) በተቃራኒው ግን ለአምላክና ለሰዎች ባላቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ተነሳስተው ክርስቶስን የተከተሉ ሰዎች በምድራዊ ሕይወታቸው በሙሉ ቀንበሩን በደስታ መሸከማቸውን ቀጥለዋል፤ ወደፊትም ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት መብት ያገኛሉ። እኛም በትክክለኛው ውስጣዊ ግፊት ተነሳስተን የክርስቶስን ቀንበር መሸከማችን ምንጊዜም ደስተኛ ለመሆን ያስችለናል።

21. በማቴዎስ 6:31-33 መሠረት ይሖዋ ምን እንደሚያደርግልን መጠበቅ እንችላለን?

21 ሦስተኛ፣ በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን። የመረጥነው ሕይወት የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግንና ጠንክሮ መሥራትን ይጠይቃል። ኢየሱስ ስደት እንደሚደርስብን አስጠንቅቆናል። ሆኖም ይሖዋ ማንኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጠን መጠበቅ እንችላለን። ፈተናዎችን በጽናት በተወጣን ቁጥር ይበልጥ ጠንካሮች እየሆንን እንሄዳለን። (ያዕ. 1:2-4) በተጨማሪም ይሖዋ እንደሚንከባከበን፣ ኢየሱስ እንደ እረኛ እንደሚጠብቀን እንዲሁም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደሚያበረታቱን ልንጠብቅ እንችላለን። (ማቴዎስ 6:31-33ን አንብብ፤ ዮሐ. 10:14፤ 1 ተሰ. 5:11) ታዲያ ከዚህ በላይ ምን እንፈልጋለን?

22. አመስጋኝ የሆንነው ለየትኛው ነገር ነው?

22 ኢየሱስ የፈወሳት ሴት ከሕመሟ በተፈወሰችበት በዚያኑ ዕለት እረፍት አግኝታለች። ለዘላለም እረፍት ማግኘት የምትችለው ግን ታማኝ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ከሆነች ብቻ ነው። ይህች ሴት ምን ውሳኔ አድርጋ ይሆን? የኢየሱስን ቀንበር ለመሸከም መርጣ ከሆነ እንዴት ያለ አስደናቂ ሽልማት እንደሚጠብቃት አስቡት፤ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር አብራ የማገልገል መብት ታገኛለች! ክርስቶስን ለመከተል ስትል የምትከፍለው የትኛውም መሥዋዕት ከዚህ በረከት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ ሊባል አይችልም። ተስፋችን በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር፣ ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ” በማለት ያቀረበውን ግብዣ በመቀበላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ

^ አን.5 ኢየሱስ ወደ እሱ እንድንመጣ ጋብዞናል። ይህን ግብዣ መቀበል ምን ነገሮችን ይጨምራል? ይህ ርዕስ የዚህን ጥያቄ መልስ ይዟል፤ እንዲሁም ከክርስቶስ ጋር አብረን በመሥራት እረፍት ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ በተለያዩ መንገዶች ለሌሎች የእረፍት ምንጭ ሆኗል።

^ አን.66 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በተለያዩ መንገዶች ለሌሎች የእረፍት ምንጭ ለመሆን ጥረት ሲያደርግ።