በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 36

ሰው አጥማጅ ለመሆን ዝግጁ ነህ?

ሰው አጥማጅ ለመሆን ዝግጁ ነህ?

“አይዞህ አትፍራ፤ ከአሁን ጀምሮ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ።”—ሉቃስ 5:10

መዝሙር 73 ድፍረት ስጠን

ማስተዋወቂያ *

1. ኢየሱስ ለአራት ዓሣ አጥማጆች ምን ግብዣ አቅርቧል? እነሱስ ምን ምላሽ ሰጡ?

ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የተባሉት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መተዳደሪያቸው ዓሣ ማጥመድ ነበር። ኢየሱስ “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” የሚል ግብዣ ሲያቀርብላቸው ተገርመው እንደሚሆን መገመት ይቻላል። * ታዲያ ምን ምላሽ ሰጡ? መጽሐፍ ቅዱስ “ወዲያውኑ መረቦቻቸውን ትተው ተከተሉት” ይላል። (ማቴ. 4:18-22) ይህ በሕይወታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ውሳኔ ነበር። እነዚህ ሰዎች ዓሣ ከማጥመድ ይልቅ ‘ሰውን ማጥመድ’ ይጀምራሉ። (ሉቃስ 5:10) በዛሬው ጊዜም ኢየሱስ እውነትን ለሚወዱ ቅን ሰዎች ይህንኑ ግብዣ እያቀረበ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) አንተስ የኢየሱስን ግብዣ በመቀበል ሰው አጥማጅ ሆነሃል?

2. ሰው አጥማጆች ለመሆን የምናደርገውን ውሳኔ በቁም ነገር ልናስብበት የሚገባው ለምንድን ነው? ወደዚህ ውሳኔ ምን ሊመራን ይችላል?

2 ምናልባት አንተ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ገፍተህ እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ማስተካከያዎችን አድርገህ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም የምሥራቹ አስፋፊ ስለ መሆን የምታስብበት ጊዜ አሁን ነው። የኢየሱስን ግብዣ መቀበል ከብዶህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ይህን ውሳኔ ለማድረግ ማመንታትህ በራሱ የውሳኔው ክብደት እንደገባህ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ጴጥሮስና ጓደኞቹ መረቦቻቸውን የተዉት “ወዲያውኑ” ነበር። ይሁንና ይህን ውሳኔ ያደረጉት ምንም ሳያስቡበት አልነበረም። ኢየሱስን ካወቁትና መሲሕ መሆኑን ካመኑ ከስድስት ወር በላይ ሆኗቸው ነበር። (ዮሐ. 1:35-42) አንተም ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ እስካሁን ብዙ ነገር ተምረህ ሊሆን ይችላል፤ በመንፈሳዊ እድገት ማድረግህን መቀጠልም ትፈልግ ይሆናል። ይሁን እንጂ ወጪህን ሳታሰላ ይህን ውሳኔ ማድረግ የለብህም። ጴጥሮስ፣ እንድርያስና ሌሎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ውሳኔ እንዲያደርጉ የረዳቸው ምን ነበር?

3. የኢየሱስን ግብዣ ለመቀበል ያለህ ፍላጎት እንዲጨምር የሚረዱህ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

3 የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሥራ ተነሳሽነትና በቂ እውቀት የነበራቸው እንዲሁም ደፋሮችና ራሳቸውን የሚገሥጹ ሰዎች ነበሩ። ሰው ከማጥመድ ሥራቸው ጋር በተያያዘም እነዚህ ባሕርያት ውጤታማ እንዲሆኑ እንደረዷቸው አያጠራጥርም። አንተም ውጤታማ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንድትሆን እነዚህን ባሕርያት ማዳበር የምትችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

ለሥራው ተነሳሽነትህ እንዲጨምር አድርግ

ጴጥሮስና ሌሎች ደቀ መዛሙርት ሰው አጥማጆች ሆነዋል። ይህ አስፈላጊ ሥራ በዘመናችንም ቀጥሏል (ከአንቀጽ 4-5⁠ን ተመልከት)

4. ጴጥሮስ ዓሣ አጥማጅ እንዲሆን ያነሳሳው ምን ነበር?

4 ጴጥሮስ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ዓሣ በማጥመድ ነበር። ሆኖም ይህን ሥራውን ከመተዳደሪያነት ባለፈም ይወደው የነበረ ይመስላል። (ዮሐ. 21:3, 9-15) በኋላ ላይም ሰው የማጥመድ ሥራውን ወዶታል። ደግሞም በይሖዋ እርዳታ ጴጥሮስ በዚህ ሥራ ውጤታማ መሆን ችሏል።—ሥራ 2:14, 41

5. ከሉቃስ 5:8-11 መረዳት እንደምንችለው ጴጥሮስን ያስፈራው ምን ነበር? እኛስ የፍርሃት ስሜትን ለማሸነፍ ምን ይረዳናል?

5 የምንሰብከው ይሖዋን ስለምንወደው ነው፤ በዚህ ሥራ ለመካፈል የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ይህ ነው። ለይሖዋ ያለን ፍቅር ‘ብቃት የለኝም’ የሚለውን ስሜት ለማሸነፍ ይረዳናል። ኢየሱስ ጴጥሮስን ሰው አጥማጅ እንዲሆን በጋበዘው ወቅት “አይዞህ አትፍራ” ብሎት ነበር። (ሉቃስ 5:8-11ን አንብብ።) ጴጥሮስን ያስፈራው ‘ደቀ መዝሙር ብሆን ምን ያጋጥመኛል?’ የሚለው ስጋት አልነበረም። ኢየሱስ፣ እሱንና የሥራ ባልደረቦቹን ብዙ ዓሣ እንዲይዙ በተአምር በረዳቸው ወቅት ጴጥሮስ በጣም ተደንቆ ነበር፤ በመሆኑም እንዲህ ያለ ተአምር ከፈጸመው ከኢየሱስ ጋር መሥራት የሚገባው ሰው እንደሆነ አልተሰማውም። በሌላ በኩል ግን አንተን የሚያስፈራህ፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ነገሮችን እንደሚጨምር መገንዘብህ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ለይሖዋ፣ ለኢየሱስና ለባልንጀራህ ያለህ ፍቅር እንዲጨምር ጥረት አድርግ፤ ይህን ስታደርግ ኢየሱስ ሰው አጥማጅ እንድትሆን ያቀረበልህን ግብዣ ለመቀበል ትነሳሳለህ።—ማቴ. 22:37, 39፤ ዮሐ. 14:15

6. ለመስበክ የሚያነሳሱን ሌሎች ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

6 ለመስበክ የሚያነሳሱንን ሌሎች ምክንያቶችም እንመልከት። ኢየሱስ “ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ማክበር እንፈልጋለን። (ማቴ. 28:19, 20) በተጨማሪም ሰዎች ‘ተገፈዋል እንዲሁም ተጥለዋል’፤ በመሆኑም ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን እውነት ማወቅ በጣም ያስፈልጋቸዋል። (ማቴ. 9:36) ይሖዋ፣ ሁሉም ዓይነት ሰዎች የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙና እንዲድኑ ይፈልጋል።—1 ጢሞ. 2:4

7. ሮም 10:13-15 የስብከቱ ሥራ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

7 የስብከቱ ሥራችን ሊያስገኝ የሚችለውን ውጤት ስናስብ በዚህ ሕይወት አድን ሥራ ለመካፈል ይበልጥ እንነሳሳለን። አንድ ዓሣ አጥማጅ፣ ዓሣ የሚያጠምደው ዓሦቹን ለመሸጥ አሊያም ለመመገብ ነው፤ እኛ ግን ሰዎችን ‘የምናጠምደው’ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ነው።ሮም 10:13-15ን አንብብ፤ 1 ጢሞ. 4:16

እውቀትህን አሳድግ

8-9. ዓሣ አጥማጆች ምን ማወቅ ይኖርባቸዋል? ለምንስ?

8 በኢየሱስ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን ዓሣ አጥማጆች፣ የትኞቹን የዓሣ ዓይነቶች ማጥመድ እንደሚችሉ ማወቅ ነበረባቸው። (ዘሌ. 11:9-12) ዓሦቹ የሚገኙበትን ቦታም ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ዓሦች ብዙውን ጊዜ የሚገኙት ውኃው በሚስማማቸውና ብዙ ምግብ በሚያገኙበት አካባቢ ነው። አንድ ዓሣ አጥማጅ ሥራውን የሚያከናውንበት ጊዜስ ለውጥ ያመጣል? በፓስፊክ ደሴት የሚኖር አንድ ሚስዮናዊ፣ ዓሣ ከማጥመድ ጋር በተያያዘ ጊዜ መምረጥ እንደሚያስፈልግ ተገንዝቧል። በአካባቢው የሚኖር አንድ ወንድም ይህን ሚስዮናዊ አብሮት ዓሣ እንዲያጠምድ ጋብዞት ነበር። ሚስዮናዊው “ነገ ጠዋት ሦስት ሰዓት ላይ እንገናኝ” አለው። የጋበዘው ወንድም ግን “ያልገባህ ነገር አለ። ዓሣ ለማጥመድ የምንሄደው ለእኛ በሚመቸን ጊዜ ሳይሆን ዓሦቹ በሚገኙበት ጊዜ ነው” ብሎ መለሰለት።

9 በተመሳሳይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሰው አጥማጆች፣ “ዓሦች” በሚገኙበት ቦታ እና ሰዓት ለመስበክ ጥረት ያደርጉ ነበር። ለምሳሌ የኢየሱስ ተከታዮች በቤተ መቅደስ፣ በምኩራቦች፣ ከቤት ወደ ቤት እንዲሁም በገበያ ስፍራ ይሰብኩ ነበር። (ሥራ 5:42፤ 17:17፤ 18:4) እኛም በክልላችን ውስጥ ስላሉት ሰዎች ማወቅ ይኖርብናል። ፕሮግራማችንን እንደ ሁኔታው ለማስተካከል ፈቃደኛ መሆናችን እንዲሁም ሰዎችን በምናገኝበት ቦታና ጊዜ መስበካችን አስፈላጊ ነው።—1 ቆሮ. 9:19-23

የተዋጣላቸው ዓሣ አጥማጆች . . . 1. ዓሦች ሊያገኙ በሚችሉበት ቦታና ሰዓት ይሠራሉ (ከአንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)

10. የይሖዋ ድርጅት የትኞቹን መሣሪያዎች አዘጋጅቶልናል?

10 ዓሣ አጥማጆች ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን መሣሪያ መያዝ እንዲሁም አጠቃቀሙን ማወቅ ይኖርባቸዋል። እኛም ለሥራችን የሚያስፈልጉት መሣሪያዎች ሊኖሩን ይገባል። መሣሪያዎቹን እንዴት እንደምንጠቀም ማወቅም ይኖርብናል። ኢየሱስ፣ ሰዎችን እንዴት ማጥመድ እንደሚቻል ለደቀ መዛሙርቱ ግልጽ መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል። ምን መያዝ፣ የት መስበክና ምን ማለት እንዳለባቸው ነግሯቸዋል። (ማቴ. 10:5-7፤ ሉቃስ 10:1-11) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ድርጅት በሥራችን ውጤታማ እንድንሆን ለመርዳት ሲል የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችንን አዘጋጅቶልናል። * በተጨማሪም እነዚህን መሣሪያዎች እንዴት እንደምንጠቀም እንማራለን። ይህ ሥልጠና ልበ ሙሉ እንድንሆንና ክህሎታችንን እንድናሻሽል ስለሚረዳን በሥራችን ውጤታማ ለመሆን ያስችለናል።—2 ጢሞ. 2:15

የተዋጣላቸው ዓሣ አጥማጆች . . . 2. ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን መሣሪያ አጠቃቀም ያውቃሉ (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

ድፍረት አዳብር

11. ሰው አጥማጆች ደፋሮች መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

11 ዓሣ አጥማጆች ደፋር መሆን ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ባሕር ላይ ያልጠበቁት ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ የሚሠሩት በምሽት ሲሆን ባሕሩ ላይ ድንገተኛ ማዕበል ሊነሳ ይችላል። ሰው አጥማጆችም ድፍረት ያስፈልጋቸዋል። መስበክ ስንጀምርና የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ስንናገር የቤተሰባችን አባላት ሊቃወሙን፣ ሌሎች የምናውቃቸው ሰዎች ሊያፌዙብን እንዲሁም ሰዎች መልእክታችንን ለመቀበል እንቢተኞች ሊሆኑ ይችላሉ፤ እነዚህ ሁኔታዎች ከማዕበል ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች የሚያጋጥሙን መሆኑ ግን አያስገርመንም። ኢየሱስ ተከታዮቹን የሚልካቸው ወደ ተቃዋሚዎቻቸው እንደሆነ አስጠንቅቋል።—ማቴ. 10:16

12. በኢያሱ 1:7-9 መሠረት ድፍረት ለማዳበር ምን ሊረዳን ይችላል?

12 ድፍረት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ ይህን ሥራ ከሰማይ ሆኖ መምራቱን እንደቀጠለ እርግጠኛ ሁን። (ዮሐ. 16:33፤ ራእይ 14:14-16) ሁለተኛ፣ ይሖዋ እንደሚንከባከብህ በገባው ቃል ላይ ያለህን እምነት አጠናክር። (ማቴ. 6:32-34) እምነትህ እየተጠናከረ በሄደ መጠን ይበልጥ ደፋር ትሆናለህ። ጴጥሮስና ጓደኞቹ ኢየሱስን ለመከተል ሲሉ መተዳደሪያቸውን በመተው ትልቅ እምነት አሳይተዋል። አንተም በተመሳሳይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት እንደጀመርክ ለምታውቃቸው ሰዎችና ለቤተሰብህ አባላት ስትናገር ትልቅ እምነት አሳይተሃል! የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ለመከተል ስትል በምግባርህና በባሕርይህ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዳደረግክም ጥያቄ የለውም። ይህም ቢሆን እምነትና ድፍረት ጠይቆብሃል። ድፍረት ማዳበርህን ስትቀጥል “አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር [እንደሚሆን]” መተማመን ትችላለህ።ኢያሱ 1:7-9ን አንብብ።

የተዋጣላቸው ዓሣ አጥማጆች . . . 3. በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም በድፍረት መሥራታቸውን ይቀጥላሉ (ከአንቀጽ 11-12⁠ን ተመልከት)

13. ማሰላሰልና ጸሎት ድፍረት ለማዳበር የሚረዳህ እንዴት ነው?

13 ድፍረት ለማዳበር ሌላስ ምን ማድረግ ትችላለህ? ድፍረት እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። (ሥራ 4:29, 31) ይሖዋ የጠየቅከውን ይሰጥሃል፤ ደግሞም አንተን መደገፉን አያቆምም። ምንጊዜም ከጎንህ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ከዚህ ቀደም አገልጋዮቹን የታደገው እንዴት እንደሆነ ማሰላሰልህ ይጠቅምሃል። አንተ ራስህ ያጋጠሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድትወጣ የረዳህና በሕይወትህ ውስጥ ለውጥ እንድታደርግ ኃይል የሰጠህ እንዴት እንደሆነም አስብ። ሕዝቡን እየመራ ቀይ ባሕርን ያሻገረው አምላክ አንተንም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንድትሆን መርዳት አይሳነውም። (ዘፀ. 14:13) “ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” ብሎ እንደዘመረው መዝሙራዊ ዓይነት እምነት ይኑርህ።—መዝ. 118:6

14. ማሳዬ እና ቶሞዮ ካጋጠማቸው ሁኔታ ምን እንማራለን?

14 ድፍረት ለማዳበር የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ ይሖዋ በተፈጥሯቸው ዓይናፋር የሆኑ ሰዎችን ደፋር እንዲሆኑ እንዴት እንደረዳቸው ማወቃችን ነው። ማሳዬ የተባለችውን እህት ተሞክሮ እንመልከት። ይህች እህት በጣም ዓይናፋር ስለሆነች መቼም ቢሆን ስለ እምነቷ መስበክ እንደማትችል ይሰማት ነበር። የማታውቃቸውን ሰዎች ማነጋገር የሚለው ሐሳብ በራሱ የማይገፋ ተራራ ሆኖ ይታያት ነበር። ስለዚህ ለአምላክና ለሰዎች ያላትን ፍቅር ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመረች። በአሁኑ ወቅት የስብከቱ ሥራ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ በደንብ አሰበችበት፤ በተጨማሪም የመስበክ ፍላጎቷን ለማሳደግ እንዲረዳት ወደ ይሖዋ ጸለየች። በመሆኑም ፍርሃቷን ማሸነፍ ቻለች፤ እንዲያውም የዘወትር አቅኚ ሆና አገልግላለች። ይሖዋ አዳዲስ አስፋፊዎችንም “ደፋር” መሆን እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ቶሞዮ የተባለች እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ቶሞዮ ከቤት ወደ ቤት መስበክ በጀመረችበት ወቅት መጀመሪያ ያገኘቻት ሴት “የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር አልፈልግም!” ብላ ከጮኸችባት በኋላ በሩን ላይዋ ላይ ዘጋችባት። ቶሞዮ በዚህ አልተደናገጠችም፤ እንዲያውም ለአገልግሎት ጓደኛዋ “አይገርምም? አንዲት ቃል እንኳ ሳልተነፍስ የይሖዋ ምሥክር መሆኔን አውቃለች። ደስ አይልም?” አለቻት። በአሁኑ ወቅት ቶሞዮ የዘወትር አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው።

ራስን የመገሠጽ ችሎታ አዳብር

15. ራስን መገሠጽ ሲባል ምን ማለት ነው? ይህ ችሎታ ለክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

15 የተዋጣላቸው ዓሣ አጥማጆች ራሳቸውን የመገሠጽ ችሎታ አላቸው። ራስን መገሠጽ የሚለው አገላለጽ “መደረግ ያለበትን ነገር ለማድረግ ራስን የማስገደድ ችሎታ” ተብሎ ሊፈታ ይችላል። ዓሣ አጥማጆች ጎህ ሳይቀድ ለመነሳት፣ ሥራቸውን ሳያጠናቅቁ ላለመሄድ እንዲሁም መጥፎ የአየር ጠባይን ተቋቁመው ለመሥራት ራሳቸውን መገሠጽ ያስፈልጋቸዋል። እኛም ለመጽናትና ሥራችንን ለማጠናቀቅ ራሳችንን መገሠጽ ይኖርብናል።—ማቴ. 10:22

16. ራስን የመገሠጽ ችሎታ ለማዳበር ምን ይረዳናል?

16 ራስን የመገሠጽ ችሎታ በውርስ የሚገኝ ነገር አይደለም። እንዲያውም በተፈጥሯችን የሚቀናን ብዙም ጥረት የማይጠይቅብንን ነገር ማድረግ ነው። ራስን የመገሠጽ ችሎታ ለማዳበር ራስን መግዛት ያስፈልጋል። በመሆኑም የሚከብዱንን ነገሮች ለማድረግ ራሳችንን ማሠልጠን እንድንችል እርዳታ ያስፈልገናል። ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይህን እርዳታ ይሰጠናል።—ገላ. 5:22, 23

17. ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱን ለመገሠጽ ያደረገውን ጥረት በ1 ቆሮንቶስ 9:25-27 ላይ የገለጸው እንዴት ነው?

17 ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱን የሚገሥጽ ሰው ነበር። ጳውሎስ፣ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ‘ሰውነቱን መጎሰም’ እንዳስፈለገው በሐቀኝነት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 9:25-27ን አንብብ።) ሐዋርያው፣ ሌሎችም ራሳቸውን እንዲገሥጹ እንዲሁም ሁሉን ነገር “በአግባብና በሥርዓት” እንዲያከናውኑ አሳስቧል። (1 ቆሮ. 14:40) እኛም ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዘን ለመቀጠል ራሳችንን መገሠጽ ይኖርብናል፤ እንዲህ ያለው ልማድ በምሳሌያዊው የዓሣ አጥማጅነት ሥራ አዘውትሮ መካፈልን ይጨምራል።—ሥራ 2:46

አትዘግይ

18. ይሖዋ ስኬታማ እንደሆንን አድርጎ እንዲመለከተን የሚያደርገው ምንድን ነው?

18 ዓሣ አጥማጆች ስኬታቸውን የሚለኩት በያዙት ዓሣ ብዛት ነው። እኛ ግን ስኬታማነታችንን የምንለካው ወደ አምላክ ድርጅት ባመጣናቸው ሰዎች ብዛት አይደለም። (ሉቃስ 8:11-15) ምሥራቹን በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ከጸናን ይሖዋ ስኬታማ አድርጎ ይቆጥረናል። ለምን? እሱንና ልጁን ስለታዘዝን ነው።—ማር. 13:10፤ ሥራ 5:28, 29

19-20. በአሁኑ ወቅት ለመስበክ የሚያነሳሳ ምን ልዩ ምክንያት አለን?

19 በአንዳንድ አገሮች ዓሣ ማጥመድ የሚፈቀደው በዓመቱ ውስጥ በተወሰኑ ወራት ላይ ብቻ ነው። እንዲህ ባሉት አገሮች የሚኖሩ ዓሣ አጥማጆች እነዚህ ወራት የሚያበቁበት ጊዜ ሲቃረብ በጥድፊያ ስሜት ለመሥራት ይነሳሳሉ። እኛም ሰው አጥማጆች እንደመሆናችን መጠን በአሁኑ ወቅት እንድንሰብክ የሚያነሳሳን ተጨማሪ ምክንያት አለን፦ ይህም የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በጣም መቅረቡ ነው! በዚህ ሕይወት አድን ሥራ ለመካፈል ያለን ጊዜ በጣም አጭር ነው። እንግዲያው አትዘግይ፤ በዚህ አስፈላጊ ሥራ ለመካፈል ሁኔታዎች ሁሉ እስኪመቻቹልህም አትጠብቅ።—መክ. 11:4

20 ተነሳሽነትህ እንዲጨምር ለማድረግ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትህን ለማሳደግ እንዲሁም ድፍረትና ራስህን የመገሠጽ ችሎታ ለማዳበር አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ። ከስምንት ሚሊዮን ከሚበልጡት ሰው አጥማጆች ጋር ተባብረህ ለመሥራት መወሰንህ የይሖዋን ደስታ ለመቅመስ ያስችልሃል። (ነህ. 8:10) በዚህ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግና ሥራው እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ሰው አጥማጆች በመሆን በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ለመጽናት ያደረግነውን ውሳኔ ለማጠናከር የሚረዱንን ሦስት ነገሮች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

መዝሙር 66 ምሥራቹን አውጁ

^ አን.5 ኢየሱስ፣ ትሑትና ታታሪ የሆኑ ዓሣ አጥማጆችን የእሱ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ጋብዟቸዋል። በዛሬው ጊዜም ኢየሱስ እንዲህ ያሉ ባሕርያት ያሏቸውን ሰዎች፣ ሰው አጥማጆች እንዲሆኑ መጋበዙን ቀጥሏል። ይህ ርዕስ ኢየሱስ ያቀረበውን ግብዣ ለመቀበል የሚያመነቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያብራራል።

^ አን.1 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “ሰው አጥማጆች” የሚለው አገላለጽ ምሥራቹን የሚሰብኩና ሌሎችን በማስተማር የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ የሚረዱ ሰዎችን ሁሉ ያመለክታል።

^ አን.10 በጥቅምት 2018 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 11-16 ላይ የወጣውን “እውነትን አስተምሩ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።