በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 37

“እጅህ ሥራ አይፍታ”

“እጅህ ሥራ አይፍታ”

“በማለዳ ዘርህን ዝራ፤ እስከ ምሽትም ድረስ እጅህ ሥራ አይፍታ።”—መክ. 11:6

መዝሙር 68 የመንግሥቱን ዘር መዝራት

ማስተዋወቂያ *

1-2. መክብብ 11:6 ከመንግሥቱ የስብከት ሥራ ጋር ምን ግንኙነት አለው?

በአንዳንድ አገሮች ያሉ ሰዎች ምሥራቹ ሲሰበክላቸው በጉጉት ያዳምጣሉ! ሲፈልጉት የቆዩትን እውነት እንዳገኙ ይሰማቸዋል። በሌሎች አገሮች ግን ብዙ ሰዎች ስለ አምላክም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት የላቸውም። አንተ በምትኖርበት አካባቢ አብዛኞቹ ሰዎች ለምሥራቹ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው? የሰዎች ምላሽ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ሥራው አብቅቷል እስኪለን ድረስ መስበካችንን እንድንቀጥል ይጠብቅብናል።

2 ይሖዋ በወሰነው ጊዜ የስብከቱ ሥራ ያበቃል፤ ከዚያም “መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴ. 24:14, 36) እስከዚያው ድረስ ግን “እጅህ ሥራ አይፍታ” * የሚለውን ትእዛዝ ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?መክብብ 11:6ን አንብብ።

3. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

3 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ውጤታማ “ሰው አጥማጆች” ለመሆን ልናደርጋቸው የሚገቡ አራት ነገሮችን ተመልክተናል። (ማቴ. 4:19) በዚህ ርዕስ ላይ ደግሞ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ያለንን ቁርጠኝነት ለማጠናከር የሚረዱንን ሦስት ነገሮች እንመለከታለን። (1) በሥራው ላይ ትኩረት ማድረግ፣ (2) ታጋሾች መሆን፣ (3) እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እናያለን።

በሥራው ላይ ትኩረት አድርጉ

4. ይሖዋ በሰጠን ሥራ ላይ ምንጊዜም ትኩረት ለማድረግ መጣር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

4 ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን በዓለም ላይ የሚፈጸሙ ክንውኖችንና በሰዎች ባሕርይ ላይ የሚታየውን ለውጥ ለደቀ መዛሙርቱ አስቀድሞ ተናግሯል፤ እነዚህ ሁኔታዎች ተከታዮቹ በስብከቱ ሥራ ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ እንቅፋት ሊሆኑባቸው እንደሚችሉ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱን “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” ሲል መክሯቸዋል። (ማቴ. 24:42) በኖኅ ዘመን ሰዎች፣ ኖኅ ለሚሰብከው ማስጠንቀቂያ ትኩረት እንዳይሰጡ ያደረጓቸው ነገሮች ነበሩ፤ በዛሬው ጊዜም እነዚህ ነገሮች ትኩረታችንን ሊከፋፍሉብን ይችላሉ። (ማቴ. 24:37-39፤ 2 ጴጥ. 2:5) እንግዲያው ይሖዋ በሰጠን ሥራ ላይ ምንጊዜም ትኩረት ለማድረግ እንጣር።

5. የሐዋርያት ሥራ 1:6-8 የስብከቱ ሥራ ምን ያህል በስፋት እንደሚከናወን የሚጠቁመው እንዴት ነው?

5 በዛሬው ጊዜ ለመንግሥቱ የስብከት ሥራ ሙሉ ትኩረት መስጠታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ይህ ሥራ እየሰፋ እንደሚሄድና እሱ ከሞተ በኋላም ለረጅም ጊዜ እንደሚቀጥል አስቀድሞ ተናግሯል። (ዮሐ. 14:12) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ ዓሣ ወደ ማጥመድ ሥራቸው ተመልሰው ነበር። ከሞት ከተነሳ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን በተአምር ብዙ ዓሣ እንዲይዙ ረዳቸው። ከዚያም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም፣ ሰው አጥማጆች የመሆን ሥራቸው ከየትኛውም ሥራ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ አስገነዘባቸው። (ዮሐ. 21:15-17) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሊያርግ ሲል ደግሞ እሱ የጀመረው የስብከት ሥራ ከእስራኤል ውጭ ርቀው በሚገኙ ቦታዎችም እንደሚከናወን ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። (የሐዋርያት ሥራ 1:6-8ን አንብብ።) ከበርካታ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ‘በጌታ ቀን’ * ስለሚከናወነው ነገር ለሐዋርያው ዮሐንስ ራእይ አሳይቶት ነበር። ዮሐንስ በራእይ ካያቸው ነገሮች መካከል የሚከተለው አስደናቂ ክንውን ይገኝበታል፦ ‘የዘላለሙ ምሥራች’ በመላእክት አመራር ‘ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ’ ይሰበካል። (ራእይ 1:10፤ 14:6) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ፈቃድ፣ ይህ ታላቅ የስብከት ሥራ እስኪያበቃ ድረስ በሥራው እንድንካፈል ነው።

6. በስብከቱ ሥራ ላይ ምንጊዜም ትኩረት ለማድረግ ምን ይረዳናል?

6 ይሖዋ እኛን ለመርዳት ያደረጋቸውን ነገሮች ማሰባችን ምንጊዜም በስብከቱ ሥራ ላይ ትኩረት ለማድረግ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበልን ነው፤ ታትመው በሚወጡና በኤሌክትሮኒክ ፎርማት በሚዘጋጁ ጽሑፎች፣ በድምፅና በቪዲዮ በተቀዱ ነገሮች እንዲሁም በኢንተርኔት በሚተላለፉ የብሮድካስት ፕሮግራሞች አማካኝነት ይመግበናል። እስቲ አስበው፦ በሕጋዊ ድረ ገጻችን ላይ ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። (ማቴ. 24:45-47) በፖለቲካ፣ በሃይማኖት እንዲሁም በኑሮ ደረጃ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ከስምንት ሚሊዮን የሚበልጡ የአምላክ አገልጋዮች አንድነት ባለው ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ታቅፈዋል። ለምሳሌ ዓርብ፣ ሚያዝያ 19, 2019 በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ የዕለቱን ጥቅስ የሚያብራራ ቪዲዮ ተመልክተዋል። በዚያ ዕለት ምሽት 20,919,041 ሰዎች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በዓል ለማክበር ተሰባስበው ነበር። በዘመናችን እየተፈጸመ ያለውን ይህን ተአምር የመመልከትና የዚህ ተአምር ተካፋዮች የመሆን መብት እንዳገኘን ስናስብ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ላይ ምንጊዜም ትኩረት ለማድረግ እንነሳሳለን።

ኢየሱስ ምንም ነገር ትኩረቱን እንዲከፋፍልበትና ስለ እውነት ከመመሥከር እንዲያግደው አልፈቀደም (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ምንጊዜም በሥራው ላይ ትኩረት ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው?

7 በስብከቱ ሥራ ላይ ምንጊዜም ትኩረት ለማድረግ የሚረዳን ሌላው ነገር የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ነው። ኢየሱስ ምንም ነገር ትኩረቱን እንዲከፋፍልበትና ስለ እውነት ከመመሥከር እንዲያግደው አልፈቀደም። (ዮሐ. 18:37) ሰይጣን “የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን” እንደሚሰጠው ያቀረበለት ግብዣ ኢየሱስን አላጓጓውም፤ ሰዎች ሊያነግሡት በሞከሩበት ወቅትም ቢሆን ይህን ለመቀበል አልተፈተነም። (ማቴ. 4:8, 9፤ ዮሐ. 6:15) ቁሳዊ ሀብት አላማለለውም፤ ለከባድ ተቃውሞም አልተበገረም። (ሉቃስ 9:58፤ ዮሐ. 8:59) እኛም እምነታችንን የሚፈትኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ማስታወሳችን ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ይረዳናል። ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምሳሌ መከተላቸው ‘እንዳይደክሙና ተስፋ እንዳይቆርጡ’ እንደሚረዳቸው ተናግሯል።—ዕብ. 12:3

ታጋሾች ሁኑ

8. ትዕግሥት ምንድን ነው? በተለይ በአሁኑ ጊዜ ይህ ባሕርይ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

8 ትዕግሥት፣ አንድ ሁኔታ እስኪቀየር ድረስ በእርጋታ የመጠበቅ ችሎታ ነው። የማንፈልገው ሁኔታ እስኪወገድም ሆነ ለረጅም ጊዜ የጓጓንለት ነገር እስኪፈጸም ስንጠብቅ ትዕግሥት ያስፈልገናል። ነቢዩ ዕንባቆም በይሁዳ የነበረው ግፍ የሚወገድበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። (ዕን. 1:2) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የአምላክ መንግሥት ‘ወዲያውኑ እንደሚገለጥ’ እና ከሮም ጭቆና ነፃ እንደሚያወጣቸው ተስፋ አድርገው ነበር። (ሉቃስ 19:11) እኛ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ክፋትን አስወግዶ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም የሚያመጣበትን ጊዜ እንናፍቃለን። (2 ጴጥ. 3:13) ይሁንና ትዕግሥት ማዳበርና ይሖዋ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ይኖርብናል። ይሖዋ ትዕግሥት እንድናዳብር የሚረዳን በየትኞቹ መንገዶች እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

9. የይሖዋን ትዕግሥት የሚያሳዩ ሁኔታዎችን ጥቀስ።

9 ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ፍጹም ምሳሌ የሚሆነን ይሖዋ ነው። ይሖዋ፣ ኖኅ መርከቡን ለመገንባትና “የጽድቅ ሰባኪ” ሆኖ ለማገልገል የሚያስችል በቂ ጊዜ እንዲያገኝ አድርጓል። (2 ጴጥ. 2:5፤ 1 ጴጥ. 3:20) ክፉ የሆኑትን የሰዶምና ገሞራ ነዋሪዎች ለማጥፋት ስላደረገው ውሳኔ አብርሃም በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብለት ይሖዋ አዳምጦታል። (ዘፍ. 18:20-33) ይሖዋ ዓመፀኛ የሆነውን የእስራኤል ብሔር ለበርካታ ዘመናት ብዙ ታግሦታል። (ነህ. 9:30, 31) ዛሬም ይሖዋ ወደ ራሱ የሚስባቸው ሰዎች ሁሉ ‘ለንስሐ እንዲበቁ’ ጊዜ መስጠቱ ትዕግሥቱን ያሳያል። (2 ጴጥ. 3:9፤ ዮሐ. 6:44፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4) ይሖዋ የተወው ምሳሌ እኛም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ስንካፈል ትዕግሥት ማሳየታችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ትዕግሥተኛ እንድንሆን የሚያስተምር አንድ ምሳሌ በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል።

ታታሪና ትዕግሥተኛ እንደሆነ ገበሬ ሁሉ እኛም የሥራችንን ውጤት በትዕግሥት እንጠብቃለን (ከአንቀጽ 10-11⁠ን ተመልከት)

10. በያዕቆብ 5:7, 8 ላይ የተጠቀሰው የገበሬው ምሳሌ ምን ያስተምረናል?

10 ያዕቆብ 5:7, 8ን አንብብ። የገበሬው ምሳሌ ትዕግሥት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል። በእርግጥ አንዳንድ ተክሎች ቶሎ ይደርሳሉ። አብዛኞቹ ተክሎች በተለይ ደግሞ ፍሬ የሚያፈሩ ዕፀዋት ግን ለመድረስ ጊዜ ይወስድባቸዋል። በጥንቷ እስራኤል ዘር ተዘርቶ እህል እስኪሰበሰብ ድረስ ስድስት ወር ገደማ ይወስድ ነበር። አንድ ገበሬ ዘር የሚዘራው ከፊተኛው ዝናብ በኋላ ሲሆን ሰብሉን የሚሰበስበው ደግሞ ከኋለኛው ዝናብ በኋላ ነበር። (ማር. 4:28) እኛም እንደ ገበሬው ትዕግሥት ማሳየታችን የጥበብ እርምጃ ነው። ሆኖም ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም።

11. ትዕግሥት ማዳበራችን በአገልግሎታችን ምን ይጠቅመናል?

11 ፍጹም ያልሆኑት የሰው ልጆች የሥራቸውን ውጤት ቶሎ ማየት ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ተክል ተክለን ሲያፈራ ማየት ከፈለግን የማያቋርጥ እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልገናል፤ ይኸውም መሬቱን መቆፈር፣ መትከል እንዲሁም አረሙን መንቀልና ውኃ ማጠጣት ይኖርብናል። ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራም የማያቋርጥ ጥረት ይጠይቃል። የምናስተምራቸው ሰዎች ጭፍን ጥላቻንና ለሌሎች ግድየለሽ የመሆን ዝንባሌን ከልባቸው ነቅለው እንዲያወጡ መርዳት ጊዜ ይወስዳል። ትዕግሥት ሰዎች መልእክታችንን ለመስማት ፈቃደኛ በማይሆኑበት ጊዜ ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ በሚሰጡበት ጊዜም ትዕግሥተኛ መሆን ያስፈልገናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ጠንካራ እምነት እንዲያዳብር ልናስገድደው አንችልም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም እንኳ እሱ ያስተማራቸውን ነገር ለመረዳት ጊዜ ወስዶባቸው ነበር። (ዮሐ. 14:9) እኛ ብንተክልና ብናጠጣም የሚያሳድገው አምላክ እንደሆነ አንርሳ።—1 ቆሮ. 3:6

12. ለማያምኑ የቤተሰባችን አባላት ስንመሠክር ትዕግሥት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

12 ትዕግሥት ማሳየት ከባድ እንዲሆንብን ከሚያደርጉ ሁኔታዎች አንዱ ለማያምኑ የቤተሰባችን አባላት መመሥከር ነው። በዚህ ረገድ በመክብብ 3:7 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ይጠቅመናል። ጥቅሱ “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። በምናሳየው መልካም ምግባር፣ ያለቃል ግሩም ምሥክርነት መስጠት እንችላለን፤ ሆኖም እውነትን ለመናገር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በንቃት መከታተል የለብንም ማለት አይደለም። (1 ጴጥ. 3:1, 2) ምሥራቹን በቅንዓት ስንሰብክና ስናስተምር የቤተሰባችንን አባላት ጨምሮ ሁሉንም ሰው በትዕግሥት ለመያዝ እንጥራለን።

13-14. የትዕግሥት ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ጥቀስ።

13 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተጠቀሱም ሆነ በዘመናችን ካሉ ታማኝ ሰዎች ስለ ትዕግሥት መማር እንችላለን። ዕንባቆም ክፋት የሚወገድበትን ጊዜ ለማየት ይጓጓ ነበር፤ ያም ቢሆን “በንቃት እጠባበቃለሁ” በማለት ያን ጊዜ በትዕግሥት እንደሚጠባበቅ አሳይቷል። (ዕን. 2:1) ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን ‘ለማጠናቀቅ’ ከልቡ እንደሚፈልግ ገልጿል። ይሁንና ታጋሽ በመሆን ‘ምሥራቹን በተሟላ ሁኔታ መመሥከሩን’ ቀጥሏል።—ሥራ 20:24

14 ከጊልያድ የተመረቁ አንድ ባልና ሚስትን ተሞክሮ እንመልከት፤ እነዚህ ባልና ሚስት በተመደቡበት አገር ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጥቂት ሲሆኑ የአገሪቱ ዋነኛ ሃይማኖትም ክርስትና አይደለም። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፍላጎት አልነበራቸውም። በጊልያድ አብረዋቸው የተማሩና በሌሎች አገሮች የተመደቡ ክርስቲያኖች ግን እድገት የሚያደርጉ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዳሏቸው የሚገልጹ አስደሳች ተሞክሮዎችን ይነግሯቸው ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት በክልላቸው ያሉ ሰዎች ለመልእክቱ ፍላጎት ባይኖራቸውም በትዕግሥት ማገልገላቸውን ቀጠሉ። ፍሬያማ በማይመስል ክልል ውስጥ ለስምንት ዓመት ከሰበኩ በኋላ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ሲጠመቅ ለማየት በቁ። በጥንት ዘመን የነበሩትንም ሆነ በዘመናችን ያሉትን እነዚህን የአምላክ አገልጋዮች የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ዳተኞች አልሆኑም ወይም እጃቸው ሥራ አልፈታም፤ ይሖዋም ለትዕግሥታቸው ወሮታ ከፍሏቸዋል። እኛም “አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት የሚወርሱትን” እንምሰል።—ዕብ. 6:10-12

እምነታችሁ ምንጊዜም ጠንካራ ይሁን

15. እምነት ለመስበክ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያጠናክርበት አንዱ መንገድ የቱ ነው?

15 በምንሰብከው መልእክት ላይ እምነት ስላለን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ይህን መልእክት ለመስበክ እንጓጓለን። ምክንያቱም በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት ተስፋዎች ላይ እምነት አለን። (መዝ. 119:42፤ ኢሳ. 40:8) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ትንቢቶች በዘመናችን ሲፈጸሙ ተመልክተናል። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምሩ ሕይወታቸው ምን ያህል እንደተሻሻለም አይተናል። እነዚህ ነገሮች፣ የመንግሥቱ ምሥራች ሁሉም ሰው ሊሰማው የሚገባ መልእክት እንደሆነ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል።

16. መዝሙር 46:1-3 እንደሚያሳየው በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ለመስበክ ያለንን ቁርጠኝነት የሚያጠናክርልን እንዴት ነው? በኢየሱስ ላይ ያለን እምነትስ የሚረዳን እንዴት ነው?

16 የመልእክታችን ባለቤት በሆነው በይሖዋ ላይም እምነት አለን፤ ይሖዋ የመንግሥቱ ንጉሥ አድርጎ በሾመው በኢየሱስም እናምናለን። (ዮሐ. 14:1) ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ይሖዋ ምንጊዜም “መጠጊያችንና ብርታታችን” ነው። (መዝሙር 46:1-3ን አንብብ።) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ይሖዋ የሰጠውን ኃይልና ሥልጣን ተጠቅሞ የስብከቱን ሥራ ከሰማይ እየመራ እንዳለ እርግጠኞች ነን።—ማቴ. 28:18-20

17. መስበካችንን መቀጠል ያለብን ለምን እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

17 እምነት፣ ይሖዋ ጥረታችንን እንደሚባርክልን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል፤ አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ይህን የሚያደርገው ባልጠበቅነው መንገድ ነው። (መክ. 11:6) ለምሳሌ ያህል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጽሑፍ ማሳያዎቻችንን እና ጋሪዎቻችንን በምናስቀምጥባቸው ቦታዎች በየዕለቱ ይተላለፋሉ። ይህ የስብከት ዘዴ ውጤታማ ነው? በሚገባ! በኅዳር 2014 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የአንዲት የኮሌጅ ተማሪ ተሞክሮ ተጠቅሷል፤ ይህች ወጣት በይሖዋ ምሥክሮች ዙሪያ ጥናት በማካሄድ አንድ ጽሑፍ ማዘጋጀት ፈለገች። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮችን የስብሰባ አዳራሽ ማግኘት አልቻለችም፤ በምትማርበት ኮሌጅ ውስጥ ግን ጽሑፎቻችን የተደረደሩበት ጠረጴዛ አየች፤ በዚያም ለጥናታዊ ጽሑፏ የሚሆን መረጃ አገኘች። ይህች ወጣት ከጊዜ በኋላ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር የሆነች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የዘወትር አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው። እንዲህ ያሉት ተሞክሮዎች አሁንም የመንግሥቱን መልእክት መስማት የሚገባቸው ሰዎች እንዳሉ ያስገነዝቡናል፤ ይህም መስበካችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል።

እጃችሁ ሥራ እንዳይፈታ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ

18. የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ይሖዋ በወሰነለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

18 የመንግሥቱ የስብከት ሥራ የሚጠናቀቀው ይሖዋ ከወሰነለት ጊዜ አንዳች ሳይዘገይ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በኖኅ ዘመን የተፈጸመውን ሁኔታ እንመልከት። ይሖዋ፣ ከወሰነው ጊዜ ዝንፍ እንደማይል አሳይቷል። ይሖዋ የጥፋት ውኃው የሚጀምርበትን ጊዜ የወሰነው ከ120 ዓመት ገደማ በፊት ነበር። ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ኖኅን መርከብ እንዲሠራ አዘዘው። ምናልባትም የጥፋት ውኃው ከመጀመሩ በፊት ባሉት 40 ወይም 50 ዓመታት በሙሉ ኖኅ ሥራውን በትጋት አከናውኗል። በዘመኑ የነበሩት ሰዎች መልእክቱን ለመስማት ፈቃደኛ ባይሆኑም ኖኅ የማስጠንቀቂያ መልእክቱን ማወጁን ቀጥሎ ነበር፤ ይሖዋ እንስሳቱን ወደ መርከቡ እንዲያስገባ እስኪነግረው ድረስ በዚህ ሥራ ተካፍሏል። ይሖዋ፣ ልክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ‘በሩን ዘጋው።’—ዘፍ. 6:3፤ 7:1, 2, 16

19. እጃችን ሥራ እንዲፈታ ካልፈቀድን የትኛው ተስፋ ሲፈጸም እናያለን?

19 በቅርቡ ይሖዋ የመንግሥቱ የስብከት ሥራ እንዲጠናቀቅ ያደርጋል፤ በሰይጣን ሥርዓት ላይ ‘በሩን ይዘጋበታል’፤ ከዚያም ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ያመጣል። እስከዚያው ድረስ ግን እንደ ኖኅና ዕንባቆም ያሉ እጃቸው ሥራ እንዲፈታ ያልፈቀዱ የአምላክ አገልጋዮችን ምሳሌ እንከተል። በሥራው ላይ ትኩረት እናድርግ፣ ታጋሾች እንሁን እንዲሁም በይሖዋና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ምንጊዜም ጠንካራ እምነት ይኑረን።

መዝሙር 75 “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!”

^ አን.5 እድገት እያደረጉ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ኢየሱስ ሰው አጥማጆች እንዲሆኑ ለተከታዮቹ ያቀረበውን ግብዣ እንዲቀበሉ የሚያበረታቱ ሐሳቦችን ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ተመልክተናል። ይህ ርዕስ ደግሞ አዲሶችም ሆኑ ተሞክሮ ያካበቱ አስፋፊዎች፣ ይሖዋ በቃ እስከሚልበት ጊዜ ድረስ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ለመካፈል ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማጠናከር ማድረግ የሚችሏቸውን ሦስት ነገሮች ያብራራል።

^ አን.2 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “እጅህ ሥራ አይፍታ” የሚለው አገላለጽ በዚህ ርዕስ ውስጥ የተሠራበት፣ ይሖዋ በቃ እስኪለን ድረስ ምሥራቹን መስበካችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ እንዳለብን ለማመልከት ነው።

^ አን.5 ‘የጌታ ቀን’ የጀመረው ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሲሆን ነው፤ የሚያበቃው ደግሞ በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ነው።