በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

መክብብ 5:8 የሚናገረው ስለ ሰብዓዊ ገዢዎች ነው? ወይስ ስለ ይሖዋም ይናገራል?

ይህ ትኩረት የሚስብ ጥቅስ እንዲህ ይላል፦ “በምትኖርበት ግዛት ውስጥ በድሃ ላይ ግፍ ሲፈጸም፣ ፍትሕ ሲጓደልና ጽድቅ ወደ ጎን ገሸሽ ሲደረግ ብታይ በዚህ ጉዳይ አትገረም። ይህን ባለሥልጣን፣ ከእሱ ከፍ ያለ ቦታ ያለው ይመለከተዋልና፤ ከእነሱም በላይ የሆኑ ሌሎች አሉ።”—መክ. 5:8

ይሖዋ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት ከግምት ካላስገባን ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ሰብዓዊ መንግሥታት ብቻ ሊመስል ይችላል። ሆኖም ይህ ጥቅስ ስለ ይሖዋም የሚያስተምረን እውነታ አለ፤ ይህም ማጽናኛና ዋስትና የሚሰጥ እውነታ ነው።

በመክብብ 5:8 ላይ በድሃ ላይ ግፍ ስለሚፈጽምና ፍትሕ ስለሚያጓድል ገዢ ተጠቅሷል። ይህ ገዢ ከእሱ የበለጠ ቦታ ወይም ሥልጣን ያለው ሰው እየተመለከተው ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ያስፈልገዋል። እንዲያውም የእሱ የበላይ የሆነው ሰውም የበላዮች ሊኖሩት ይችላሉ። የሚያሳዝነው በሰብዓዊ መንግሥታት ውስጥ በተለያየ የሥልጣን ተዋረድ ያሉት ገዢዎች ሁሉ ምግባረ ብልሹ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በመሆኑም ተራው ሕዝብ የተለያየ የሥልጣን እርከን ላይ ባሉ ሰዎች የፍትሕ መጓደል ሊፈጸምበት ይችላል።

ሁኔታዎች ምንም ያህል ተስፋ አስቆራጭ ቢመስሉ፣ ይሖዋ ‘ከፍ ያለ ቦታ ያላቸውን’ ባለሥልጣናት እንኳ እንደሚመለከታቸው ማወቃችን ያጽናናናል። አምላክ እንዲረዳን መለመንና ሸክማችንን በእሱ ላይ መጣል እንችላለን። (መዝ. 55:22፤ ፊልጵ. 4:6, 7) “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ [እንደሚመላለሱ]” እናውቃለን።—2 ዜና 16:9

ነጥቡን ስናጠቃልለው መክብብ 5:8 በሰው ልጆች መንግሥታት ውስጥ የሚታየውን ሁኔታ የሚገልጽ ነው፤ ባለሥልጣን የሆነው አካልም ምንጊዜም ቢሆን የበላይ አለው። ከዚህም ሌላ ጥቅሱ፣ የሁሉ የበላይ የሆነው ባለሥልጣን ይሖዋ መሆኑን እንድናስታውስ ይረዳናል። በአሁኑ ወቅት ይሖዋ የመንግሥቱ ንጉሥ አድርጎ በሾመው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት እየገዛ ነው። ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ እይታ የሚያመልጥ ነገር የለም፤ እሱም ሆነ ልጁ ፈጽሞ ፍትሕ አያጓድሉም።