የጥናት ርዕስ 37
“ብሔራትንም ሁሉ አናውጣለሁ”
“ብሔራትንም ሁሉ አናውጣለሁ፤ በብሔራትም ሁሉ መካከል ያሉ የከበሩ ነገሮች ይመጣሉ።”—ሐጌ 2:7
መዝሙር 24 ኑ! ወደ ይሖዋ ተራራ
ማስተዋወቂያ *
1-2. በዘመናችን ምን ዓይነት ምሳሌያዊ ነውጥ እንደሚኖር በትንቢት ተነግሯል?
“ሱቆችና ረጅም ዘመን የኖሩ ሕንፃዎች በጥቂት ደቂቃ ውስጥ የፍርስራሽ ክምር ሆኑ።” “ሁሉም ሰው ተሸብሮ ነበር፤ . . . ብዙ ሰዎች መናወጡ የቆየው ለሁለት ደቂቃ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። እኔ ግን ለረጅም ጊዜ የቆየ ነበር የመሰለኝ።” እነዚህን ሐሳቦች የተናገሩት በ2015 በኔፓል ከተከሰተው የምድር መናወጥ የተረፉ ሰዎች ናቸው። እንዲህ ዓይነት አስፈሪ አደጋ ቢያጋጥምህ ሁኔታውን መቼም ቢሆን እንደማትረሳው የታወቀ ነው።
2 በዛሬው ጊዜ ከዚህ በጣም የተለየ መናወጥ ሲከሰት እየተመለከትን ነው፤ ይህ ነውጥ በአንድ ከተማ ወይም በአንድ አገር ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ብሔራትን ሁሉ የሚነካ ሲሆን ነውጡ ከጀመረ በርካታ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። ነቢዩ ሐጌ ስለዚህ ነውጥ ትንቢት ተናግሮ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደገና ሰማያትን፣ ምድርን፣ ባሕርንና የብስን አናውጣለሁ።’”—ሐጌ 2:6
3. ምሳሌያዊው ነውጥ ከምድር መናወጥ የሚለየው እንዴት ነው?
3 ሐጌ በትንቢቱ ላይ የገለጸው ነውጥ ከምድር መናወጥ የተለየ ነው፤ ምክንያቱም የምድር መናወጥ ውጤቱ ውድመት ብቻ ነው። ሐጌ የተናገረለት መናወጥ ግን መልካም ውጤት ያስገኛል። ይሖዋ ራሱ እንዲህ ብሏል፦ “ብሔራትንም ሁሉ አናውጣለሁ፤ በብሔራትም ሁሉ መካከል ያሉ የከበሩ ነገሮች ይመጣሉ፤ ደግሞም ይህን ቤት በክብር እሞላዋለሁ።” (ሐጌ 2:7) ይህ ትንቢት በሐጌ ዘመን ለኖሩት ሰዎች ምን ትርጉም ነበረው? በዛሬው ጊዜ ላለነውስ ምን ትርጉም አለው? በዚህ ርዕስ ውስጥ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን። በተጨማሪም ብሔራትን ሁሉ እያናወጠ ባለው ሥራ መካፈል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን።
በሐጌ ዘመን የተነገረ የሚያበረታታ መልእክት
4. ይሖዋ ነቢዩ ሐጌን ወደ ሕዝቡ የላከው ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ ለነቢዩ ሐጌ ወሳኝ ተልእኮ ሰጥቶት ነበር። እስቲ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ሐጌ በ537 ዓ.ዓ. ከባቢሎን ግዞት ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱት አይሁዳውያን አንዱ ሳይሆን አይቀርም። እነዚህ ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች ኢየሩሳሌም ከደረሱ ብዙም ሳይቆይ የይሖዋን ቤት ወይም ቤተ መቅደስ መሠረት ጣሉ። (ዕዝራ 3:8, 10) ብዙም ሳይቆይ ግን የሚያሳዝን ሁኔታ ተፈጠረ። ሕዝቡ በተስፋ መቁረጥና በተቃውሞ ተሸንፈው ሥራውን አቆሙ። (ዕዝራ 4:4፤ ሐጌ 1:1, 2) በመሆኑም ይሖዋ ሕዝቡ ቅንዓታቸውን እንዲያቀጣጥሉና የቤተ መቅደሱን ግንባታ እንዲያጠናቅቁ ለማነሳሳት በ520 ዓ.ዓ. ሐጌን ላከው። *—ዕዝራ 6:14, 15
5. ሐጌ የተናገረው መልእክት የአምላክን ሕዝብ አበረታቷቸው መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው?
5 የሐጌ መልእክት ዓላማ ሕዝቡ በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ መርዳት ነበር። ነቢዩ ተስፋ ለቆረጡት አይሁዳውያን የሚከተለውን መልእክት በድፍረት ነገራቸው፦ “‘እናንተም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ፣ በርቱና ሥሩ’ ይላል ይሖዋ። ‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።” (ሐጌ 2:4) “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” የሚለው አገላለጽ ሕዝቡን አበረታቷቸው መሆን አለበት። ይሖዋ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መላእክትን ያቀፈ ሠራዊት አለው፤ ስለዚህ አይሁዳውያኑ እንዲሳካላቸው ከፈለጉ በእሱ መታመን ይኖርባቸዋል።
6. ሐጌ በትንቢት የተናገረለት ነውጥ ምን ውጤት ያስገኛል?
6 ሐጌ፣ ይሖዋ ብሔራትን ሁሉ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደሚያናውጣቸው የሚገልጽ መልእክት በመንፈስ መሪነት ተናግሯል። ይህ መልእክት ተስፋ ቆርጠው ቤተ መቅደሱን መገንባት ያቆሙትን አይሁዳውያን አበረታቷቸዋል፤ ምክንያቱም መልእክቱ በዘመኑ የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረውን ፋርስን ይሖዋ እንደሚያናውጠው የሚያሳይ ነው። ታዲያ ይህ ነውጥ ምን ውጤት ያስገኛል? በመጀመሪያ የአምላክ ሕዝብ ቤተ መቅደሱን ገንብተው ይጨርሳሉ። ከዚያም አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ ከአይሁዳውያን ጋር ሆነው እንደገና በተገነባው በዚያ ቤተ መቅደስ ውስጥ ይሖዋን ያመልካሉ። ይህ መልእክት የአምላክን ሕዝብ ምንኛ አበረታቷቸው ይሆን!—ዘካርያስ 8:9
በዘመናችን እየተከናወነ ያለ ምድርን የሚያናውጥ ሥራ
7. በዛሬው ጊዜ በየትኛው የሚያናውጥ ሥራ እየተካፈልን ነው? አብራራ።
7 የሐጌ ትንቢት በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ይሖዋ በድጋሚ ብሔራትን ሁሉ እያናወጠ ሲሆን በዚህ ዘመን ለሚከናወነው ነውጥ እኛም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ በ1914 ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን የሰማያዊ መንግሥቱ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። (መዝ. 2:6) የዚህ መንግሥት መቋቋም ለዓለም መሪዎች መጥፎ ዜና ነው። ምክንያቱም የዚህ መንግሥት መቋቋም “የአሕዛብ ዘመናት” ይኸውም በምድር ላይ ይሖዋን በቀጥታ የሚወክል ገዢ የማይኖርበት ዘመን መፈጸሙን ወይም ማብቃቱን ያመለክታል። (ሉቃስ 21:24) የይሖዋ ሕዝቦች ይህንን እውነታ ስለተገነዘቡ ለሰው ልጆች ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት መሆኑን በተለይ ከ1919 ወዲህ ሲያውጁ ቆይተዋል። ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በመስበክ ያከናወኑት ይህ ሥራ መላውን ዓለም አናውጦታል።—ማቴ. 24:14
8. መዝሙር 2:1-3 እንደሚጠቁመው አብዛኞቹ ብሔራት ለምንሰብከው መልእክት ምን ምላሽ ሰጥተዋል?
8 ሰዎች ለዚህ መልእክት ምን ምላሽ ሰጥተዋል? አብዛኞቹ ሰዎች በመልእክቱ አልተደሰቱም። (መዝሙር 2:1-3ን አንብብ።) ብሔራት ይህን መልእክት ሲሰሙ ታውከዋል። ይሖዋ የሾመውን ገዢ ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። የምንሰብከውን የመንግሥቱን መልእክት እንደ “ምሥራች” አድርገው አልተመለከቱትም። እንዲያውም አንዳንድ መንግሥታት የስብከቱን ሥራ አግደውታል። የብዙዎቹ ብሔራት ገዢዎች አምላክን እናገለግላለን ቢሉም ሥልጣናቸውን ማስረከብ አይፈልጉም። በመሆኑም በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት ገዢዎች ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ገዢዎችም በኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች ላይ ጥቃት በመሰንዘር፣ ይሖዋ የቀባውን ንጉሥ እየተቃወሙ ነው።—ሥራ 4:25-28
9. ብሔራት መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑም ይሖዋ ምን አድርጓል?
9 ብሔራት መልእክቱን መቀበል ባይፈልጉም ይሖዋ ምን አድርጓል? መዝሙር 2:10-12 መልሱን ይሰጠናል፤ እንዲህ ይላል፦ “እንግዲህ እናንተ ነገሥታት አስተውሉ፤ እናንተ የምድር ፈራጆች እርማት ተቀበሉ። ይሖዋን በፍርሃት አገልግሉ፤ ለእሱ በመንቀጥቀጥም ሐሴት አድርጉ። ልጁን አክብሩ፤ አለዚያ አምላክ ይቆጣል፤ ከመንገዱም ትጠፋላችሁ፤ ቁጣው ፈጥኖ ይነድዳልና። እሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።” እነዚህ ተቃዋሚዎች አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ይሖዋ በደግነት ጊዜ ሰጥቷቸዋል። አሁንም ቢሆን አመለካከታቸውን ለውጠው የይሖዋን መንግሥት መቀበል ይችላሉ። ይሁንና የቀራቸው ጊዜ አጭር ነው። የምንኖረው በዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞ. 3:1፤ ኢሳ. 61:2) ሰዎች እውነትን አውቀው ትክክለኛ ውሳኔ ማድረጋቸው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጣዳፊ ነው።
ለነውጡ በጎ ምላሽ የሰጡ ሰዎች
10. ሐጌ 2:7-9 እንደሚናገረው አንዳንዶች ለነውጡ ምን በጎ ምላሽ ይሰጣሉ?
10 አንዳንድ ሰዎች ሐጌ በትንቢት ለተናገረለት ነውጥ በጎ ምላሽ ሰጥተዋል። ሐጌ በዚህ ነውጥ የተነሳ “በብሔራትም ሁሉ መካከል ያሉ የከበሩ ነገሮች” ማለትም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ይሖዋን ለማምለክ ‘እንደሚመጡ’ ተናግሯል። * (ሐጌ 2:7-9ን አንብብ።) ኢሳይያስ እና ሚክያስም “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” እንዲህ ዓይነት ነገር እንደሚከናወን ትንቢት ተናግረዋል።—ኢሳ. 2:2-4 ግርጌ፤ ሚክ. 4:1, 2 ግርጌ
11. አንድ ወንድም የመንግሥቱን ምሥራች ለመጀመሪያ ጊዜ በሰማበት ወቅት ምን እርምጃ ወሰደ?
11 በዋናው መሥሪያ ቤት የሚያገለግል ኬን የተባለ አንድ ወንድም፣ ምድርን የሚያናውጠውን መልእክት
በሰማበት ወቅት ምን እንደተሰማው እስቲ እንመልከት። የዛሬ 40 ዓመት የመንግሥቱን ምሥራች ለመጀመሪያ ጊዜ በሰማበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ትናንት የሆነ ያህል ያስታውሰዋል። ኬን እንዲህ ብሏል፦ “በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰማሁበት ወቅት፣ የምንኖረው በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ መሆኑን በመማሬ ደስ ብሎኝ ነበር። የአምላክን ሞገስ እና የዘላለም ሕይወት ማግኘት ከፈለግኩ አስተማማኝ ካልሆነው ከዚህ ዓለም መውጣትና ከይሖዋ ጎን መቆም እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ወደ ይሖዋ ከጸለይኩ በኋላ ወዲያውኑ ይህንን እርምጃ ወሰድኩ። ይህን ዓለም በመተው፣ ፈጽሞ ሊናወጥ ከማይችለው የአምላክ መንግሥት ጎን ቆምኩ።”12. በመጨረሻዎቹ ቀናት የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በክብር የተሞላው እንዴት ነው?
12 ይሖዋ ሕዝቡን እየባረከ እንደሆነ በግልጽ መመልከት ይቻላል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። በ1914 የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ብቻ ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን ከስምንት ሚሊዮን የሚበልጡ የአምላክ አገልጋዮች አሉ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ የመታሰቢያውን በዓል አብረውን ያከብራሉ። በመሆኑም የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ (ማለትም ለንጹሕ አምልኮ ያደረገው ዝግጅት) ምድራዊ አደባባይ፣ ‘በብሔራት ሁሉ መካከል ባሉ የከበሩ ነገሮች’ ተሞልቷል። እነዚህ ሰዎች አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ሲሉ የሚያደርጉት ለውጥም ለይሖዋ ስም ክብር አምጥቷል።—ኤፌ. 4:22-24
13. የተገኘው አስደሳች እድገት የትኞቹ ሌሎች ትንቢቶች እንዲፈጸሙ አድርጓል? (ሽፋኑን ተመልከት።)
13 ይህ አስደሳች እድገት ሌሎች ትንቢቶችም ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አድርጓል፤ በኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ላይ የሚገኘውን ትንቢት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ቁጥር 22 እንዲህ ይላል፦ “ጥቂት የሆነው ሺህ፣ ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል። እኔ ይሖዋ፣ ይህን በራሱ ጊዜ አፋጥነዋለሁ።” የይሖዋ እውነተኛ አገልጋዮች ወደ ቤቱ በብዛት በመጉረፋቸው አስደናቂ ነገር ተፈጽሟል። እነዚህ “የከበሩ ነገሮች” የተለያየ ብቃትና ችሎታ አላቸው፤ እንዲሁም ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በመስበኩ ሥራ ለመካፈል ፈቃደኞች ናቸው። በመሆኑም ኢሳይያስ እንደገለጸው የይሖዋ ሕዝቦች “የብሔራትን ወተት” እየጠጡ ነው። (ኢሳ. 60:5, 16) እነዚህ ውድ ወንዶችና ሴቶች በሚያደርጉት እገዛ ምሥራቹ በ240 አገራት ሊሰበክ ችሏል፤ ጽሑፎቻችንም ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች እየተዘጋጁ ነው።
የውሳኔ ጊዜ
14. በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች ምን ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል?
14 በምንኖርበት በመጨረሻው ዘመን፣ የብሔራት መናወጥ ሰዎች ውሳኔ እንዲያደርጉ እያስገደዳቸው ነው። በሁሉም ሰው ፊት የተደቀነ ውሳኔ አለ፦ የአምላክን መንግሥት መደገፍ አሊያም በዚህ ዓለም መንግሥታት መተማመን። የይሖዋ ሕዝቦች የሚኖሩበትን አገር ሕግጋት የሚያከብሩ ቢሆንም ከዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ናቸው። (ሮም 13:1-7) ለሰው ልጆች ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያውቃሉ። ይህ መንግሥት የዓለም ክፍል አይደለም።—ዮሐ. 18:36, 37
15. የራእይ መጽሐፍ የአምላክ ሕዝቦች ምን ከባድ የታማኝነት ፈተና እንደሚያጋጥማቸው ይገልጻል?
15 የራእይ መጽሐፍ፣ የአምላክ ሕዝቦች በመጨረሻዎቹ ቀናት የታማኝነት ፈተና እንደሚገጥማቸው ይናገራል። በዚህ የታማኝነት ፈተና ምክንያት ከባድ ተቃውሞና ስደት ይደርስብናል። የዚህ ዓለም መንግሥታት እንድናመልካቸው ይጠብቃሉ፤ እንዲሁም እነሱን ለመደገፍ ፈቃደኛ ባልሆኑት ላይ ስደት ያደርሳሉ። (ራእይ 13:12, 15) መንግሥታት “ሰዎች ሁሉ ማለትም ታናናሾችና ታላላቆች፣ ሀብታሞችና ድሆች እንዲሁም ነፃ ሰዎችና ባሪያዎች በቀኝ እጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምልክት እንዲደረግባቸው [ያስገድዳሉ]።” (ራእይ 13:16) በጥንት ዘመን የነበሩ ባሪያዎች የማን ንብረት መሆናቸውን ለማሳወቅ ቋሚ ምልክት ይደረግባቸው ነበር። በተመሳሳይም በዘመናችን የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ በእጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምሳሌያዊ ምልክት እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም ሰው ከዚህ ዓለም መንግሥታት ጎን እንደሚቆምና እንደሚደግፋቸው በአስተሳሰቡና በድርጊቱ እንዲያሳይ ይጠበቅበታል።
16. በአሁኑ ወቅት ለይሖዋ የማይናወጥ ታማኝነት ማዳበራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
16 እኛስ ይህን ምሳሌያዊ ምልክት ተቀብለን ከፖለቲካዊ መንግሥታት ጎን እንቆም ይሆን? ይህን ምልክት ለመቀበል ፈቃደኛ የማይሆኑ ሁሉ አስቸጋሪና አደገኛ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። የራእይ መጽሐፍ “ምልክቱ . . . ካለው ሰው በስተቀር ማንም መግዛት ወይም መሸጥ” እንደማይችል ይናገራል። (ራእይ 13:17) ይሁን እንጂ የአምላክ ሕዝቦች፣ በራእይ 14:9, 10 ላይ የተገለጸውን ምልክት በሚቀበሉ ሰዎች ላይ ይሖዋ ምን እርምጃ እንደሚወስድባቸው ያውቃሉ። በመሆኑም ይህንን ምልክት ከመቀበል ይልቅ በምሳሌያዊ መንገድ በእጃቸው ላይ “የይሖዋ ነኝ” ብለው ይጽፋሉ። (ኢሳ. 44:5) ለይሖዋ ያለን ታማኝነት የማይናወጥ መሆኑን ለማረጋገጥ ጊዜው አሁን ነው። የማይናወጥ ታማኝነት ካለን ይሖዋም በደስታ ንብረቱ አድርጎ ይቀበለናል!
የመጨረሻ ነውጥ
17. ከይሖዋ ትዕግሥት ጋር በተያያዘ ልናስታውሰው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
17 ይሖዋ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ታላቅ ትዕግሥት አሳይቷል። ይሖዋ ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9) በመሆኑም ሁሉም ሰው ንስሐ መግባትና ትክክለኛውን ውሳኔ ማድረግ እንዲችል አጋጣሚ ሰጥቷል። ይሁንና የይሖዋ ትዕግሥት ገደብ አለው። ይሖዋ በሰጣቸው አጋጣሚ ለመጠቀም ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የፈርዖን ዕጣ ይደርስባቸዋል። ይሖዋ በሙሴ ዘመን ለኖረው ፈርዖን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “እስካሁን እጄን ዘርግቼ አንተንም ሆነ ሕዝብህን አጥፊ በሆነ መቅሰፍት በመታኋችሁ ነበር፤ አንተም ከምድር ገጽ ተጠራርገህ በጠፋህ ነበር። ሆኖም ኃይሌን እንዳሳይህና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ስል በሕይወት አቆይቼሃለሁ።” (ዘፀ. 9:15, 16) ይዋል ይደር እንጂ፣ ብሔራት ሁሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ይሖዋ መሆኑን ለማወቅ ይገደዳሉ። (ሕዝ. 38:23) ይህ የሚሆነው እንዴት ነው?
18. (ሀ) በሐጌ 2:6, 20-22 ላይ ምን ሌላ ዓይነት ነውጥ ተገልጿል? (ለ) ሐጌ የተናገረው ሐሳብ ወደፊት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እንዴት እናውቃለን?
በሐጌ 2:6, 20-22 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ወደፊት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ጥቅሱን አንብብ።) ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ግን ‘ምድርን ብቻ ሳይሆን ሰማይን ጭምር እንደገና አናውጣለሁ’ ሲል ቃል ገብቷል። እንግዲህ ‘እንደገና’ የሚለው አባባል የማይናወጡት ነገሮች ጸንተው ይኖሩ ዘንድ የሚናወጡት ይኸውም የተሠሩት ነገሮች የሚወገዱ መሆናቸውን ያመለክታል።” (ዕብ. 12:26, 27) ይሄኛው ነውጥ በሐጌ 2:7 ላይ ከተገለጸው ነውጥ የተለየ ነው። ይሄኛው ነውጥ፣ እንደ ፈርዖን የይሖዋን የመግዛት መብት የማይቀበሉ ሰዎች የሚደርስባቸውን ዘላለማዊ ጥፋት ያመለክታል።
18 ሐጌ ከኖረ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ19. የማይናወጠው ምንድን ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?
19 ታዲያ የማይናወጠው ወይም የማይጠፋው ምንድን ነው? ጳውሎስ ቀጥሎ እንዲህ ብሏል፦ “እኛ ሊናወጥ የማይችል መንግሥት ልንቀበል እንደሆነ ስለምናውቅ ጸጋውን መቀበላችንን እንቀጥል፤ ይህም በጸጋው አማካኝነት በአምላካዊ ፍርሃትና በጥልቅ አክብሮት፣ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ እንችል ዘንድ ነው።” (ዕብ. 12:28) ከዚህ የመጨረሻ ታላቅ መናወጥ በኋላ ሳይናወጥ ባለበት የሚቀረው የአምላክ መንግሥት ብቻ ይሆናል። የአምላክ መንግሥት ጸንቶ ይቆማል!—መዝ. 110:5, 6፤ ዳን. 2:44
20. ሰዎች ምን ምርጫ ተደቅኖባቸዋል? እኛስ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
20 የሚባክን ጊዜ የለም! ሰዎች ምርጫ ማድረግ አለባቸው፦ ይህንን ዓለም መደገፋቸውን ለመቀጠል ከመረጡ ጥፋት ይጠብቃቸዋል። በሌላ በኩል ግን ይሖዋን ለማገልገል እንዲሁም የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ከመረጡ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (ዕብ. 12:25) የምናከናውነው የስብከት ሥራ ሰዎች በዚህ አስፈላጊ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት ምርጫ እንደሚያደርጉ ለመወሰን ይረዳቸዋል። እንደከበሩ ነገሮች የሆኑ በርካታ ሰዎች ከአምላክ መንግሥት ጎን እንዲቆሙ ለመርዳት ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥል። ጌታችን ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብም ምንጊዜም እናስታውስ፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴ. 24:14
መዝሙር 40 የማን ንብረት ነን?
^ አን.5 ይህ ርዕስ ሐጌ 2:7ን በተመለከተ ባለን ግንዛቤ ላይ የተደረገውን ማስተካከያ ያብራራል። ብሔራትን ሁሉ እያናወጠ ባለው ትኩረት የሚስብ ሥራ እኛም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። በተጨማሪም ብሔራትን ለሚያናውጠው ለዚህ ሥራ አንዳንዶች በጎ ሌሎች ደግሞ መጥፎ ምላሽ የሚሰጡት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
^ አን.4 የሐጌ ተልእኮ ስኬታማ ሆኗል፤ የቤተ መቅደሱ ግንባታ በ515 ዓ.ዓ. መጠናቀቁ ይህን ያሳያል።
^ አን.10 ይህ ሐሳብ ቀደም ሲል የነበረንን ግንዛቤ የሚያስተካክል ነው። ከዚህ ቀደም፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ይሖዋ የሚሳቡት ብሔራት ሁሉ ስለሚናወጡ እንዳልሆነ የተናገርንባቸው ጊዜያት ነበሩ። በግንቦት 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።
^ አን.63 የሥዕሉ መግለጫ፦ ሐጌ የአምላክ ሕዝቦች ቤተ መቅደሱን በቅንዓት እንዲገነቡ አበረታቷቸዋል፤ በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች የአምላክን መልእክት በቅንዓት እያወጁ ነው። አንድ ባልና ሚስት ወደፊት ስለሚመጣው የመጨረሻው ነውጥ በመስበክ፣ ምድርን በሚያናውጠው ሥራ ሲካፈሉ።