የጥናት ርዕስ 35
ታማኝ አረጋውያንን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው
“ሽበት . . . የውበት ዘውድ ነው።”—ምሳሌ 16:31
መዝሙር 138 ሽበት ያለው ውበት
ማስተዋወቂያ *
1-2. (ሀ) በምሳሌ 16:31 መሠረት ለታማኝ አረጋውያን ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን?
በአርከንሶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አልማዝ መሬት ላይ ማንም ሰው ሊያየው በሚችለው ሁኔታ የሚገኝበት አንድ ፓርክ አለ። ሆኖም እዚያ የሚገኘው አልማዝ ተቆርጦና ተሞርዶ የተስተካከለ አይደለም። በመሆኑም ብዙ ጎብኚዎች አልማዙን ቢያዩትም ምን እንደሆነ ስለማይገነዘቡ እንደ ተራ ነገር ቆጥረው አልፈውት ሊሄዱ ይችላሉ።
2 ታማኝ አረጋውያን እንደነዚህ አልማዞች ውድ ሀብት ናቸው። የአምላክ ቃል የአረጋውያንን ሽበት ከዘውድ ጋር ያመሳስለዋል። (ምሳሌ 16:31ን አንብብ፤ 20:29) ሆኖም አረጋውያን ውድ ሀብት መሆናቸውን ላናስተውል እንችላለን። አረጋውያን ያላቸውን ዋጋ የሚገነዘቡ ወጣቶች ከቁሳዊ ሀብት የሚበልጥ ውድ ነገር ያገኛሉ። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሦስት ጥያቄዎችን መልስ እንመለከታለን፦ ይሖዋ ታማኝ አረጋውያንን እንደ ውድ ሀብት አድርጎ የሚመለከታቸው ለምንድን ነው? ታማኝ አረጋውያን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ምን ቦታ አላቸው? ከእነሱ ምሳሌ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለውስ እንዴት ነው?
ይሖዋ ታማኝ አረጋውያንን እንደ ውድ ሀብት አድርጎ የሚመለከታቸው ለምንድን ነው?
3. በመዝሙር 92:12-15 መሠረት ታማኝ አረጋውያን በይሖዋ ዓይን ውድ የሆኑት ለምንድን ነው?
3 ታማኝ አረጋውያን ለይሖዋ አምላክ ውድ ናቸው። ይሖዋ ውስጣዊ ማንነታቸውን ያያል፤ እንዲሁም ግሩም ባሕርያታቸውን ያደንቃል። አረጋውያን እሱን ለረጅም ዘመን በታማኝነት በማገልገል ያካበቱትን ጥበብ ለወጣቶች ሲያካፍሉ በጣም ይደሰታል። (ኢዮብ 12:12፤ ምሳሌ 1:1-4) በተጨማሪም ይሖዋ አረጋውያን የሚያሳዩትን ጽናት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (ሚል. 3:16) አረጋውያን በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል፤ ሆኖም በይሖዋ ላይ ያላቸው እምነት አልተናወጠም። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያላቸው ተስፋ እውነትን በሰሙበት ጊዜ ከነበረው ይበልጥ ብሩህ ነው። ደግሞም “ባረጁ ጊዜም እንኳ” የይሖዋን ስም ማወጃቸውን ስለቀጠሉ ይሖዋ በጣም ይወዳቸዋል።—መዝሙር 92:12-15ን አንብብ።
4. አረጋውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምን ማሰባቸው ሊያጽናናቸው ይችላል?
4 አንተም ዕድሜህ እየገፋ ከሆነ ይሖዋ ከዚህ ቀደም ያከናወንከውን ሥራ እንደማይረሳው እርግጠኛ ሁን። (ዕብ. 6:10) የስብከቱን ሥራ በቅንዓት ደግፈሃል፤ ይህም የሰማዩን አባታችንን ያስደስተዋል። ቅስም የሚሰብሩ ችግሮችን ጨምሮ ብዙ ፈተናዎችን በጽናት ተቋቁመሃል፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ የጽድቅ መሥፈርቶች ጎን ቆመሃል፤ ከባድ ኃላፊነቶችን ተወጥተሃል፤ እንዲሁም ሌሎችን አሠልጥነሃል። በፍጥነት ከሚጓዘው የይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል ለመሄድ አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርገሃል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ክርስቲያኖችን ደግፈሃል እንዲሁም አበረታተሃል። ለምታሳየው ታማኝነት ይሖዋ አምላክ በጣም ይወድሃል። ይሖዋ ‘ታማኝ አገልጋዮቹን እንደማይተዋቸው’ ቃል ገብቷል! (መዝ. 37:28) ለአረጋውያን “ፀጉራችሁ እስኪሸብትም ድረስ እሸከማችኋለሁ” የሚል ዋስትና ሰጥቷል። (ኢሳ. 46:4) እንግዲያው ዕድሜህ ስለገፋ ብቻ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ጠቃሚ ሥራ ማከናወን እንደማትችል ሊሰማህ አይገባም። አሁንም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ ማበርከት ትችላለህ!
አረጋውያን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ጠቃሚ ቦታ አላቸው
5. አረጋውያን ምን ማስታወስ አለባቸው?
5 አረጋውያን ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ማከናወን ይችላሉ። በአንድ ወቅት የነበራቸውን ያህል ጉልበት ባይኖራቸውም እንኳ በረጅም ዘመናት ያካበቱት ብዙ ልምድ አላቸው። ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች በእነሱ መጠቀሙን ሊቀጥል ይችላል። በጥንት ዘመንም ሆነ በዘመናችን የኖሩ አንዳንድ አረጋውያን ምሳሌ ይህን ያሳያል።
6-7. ይሖዋ እሱን በታማኝነት ያገለገሉ አረጋውያንን እንደባረካቸው የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
6 ዕድሜያቸው ከገፋም በኋላ ይሖዋን በትጋት ማገልገላቸውን የቀጠሉ ታማኝ ሰዎችን ግሩም ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ የይሖዋ ነቢይና የእስራኤል ብሔር መሪ ሆኖ ማገልገል በጀመረበት ወቅት ዕድሜው 80 ዓመት ገደማ ነበር።
ዳንኤል ካረጀም በኋላ፣ ምናልባትም ዕድሜው 90 ዓመት ካለፈም በኋላ ጭምር ይሖዋ እሱን ቃል አቀባዩ አድርጎ መጠቀሙን ቀጥሏል። ሐዋርያው ዮሐንስም የራእይ መጽሐፍን በመንፈስ መሪነት የጻፈው በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ሳይሆን አይቀርም።7 ያን ያህል ታዋቂ ያልነበሩ ሌሎች በርካታ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም አሉ፤ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች በሌሎች ዘንድ እምብዛም ትኩረት አልተሰጣቸው ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች ትኩረት ሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ለታማኝነታቸው ወሮታ ከፍሏቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ “ጻድቅና ለአምላክ ያደረ ሰው” ስለነበረው ስለ ስምዖን መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ሐሳብ በጣም ጥቂት ነው። ሆኖም ይሖዋ ይህን ሰው በደንብ ያውቀው ነበር፤ በተጨማሪም ሕፃኑን ኢየሱስን የማየት እንዲሁም ስለ እሱና ስለ እናቱ ትንቢት የመናገር መብት ሰጥቶታል። (ሉቃስ 2:22, 25-35) መበለት የነበረችውን የነቢይቷን የሐናን ምሳሌም እንመልከት። ሐና 84 ዓመቷ ቢሆንም “ከቤተ መቅደስ ፈጽሞ አትጠፋም ነበር።” እሷም አዘውትራ በቤተ መቅደስ በመገኘቷ ሕፃኑን ኢየሱስን የማየት ልዩ በረከት አግኝታለች። ስምዖንም ሆነ ሐና በይሖዋ ዓይን ውድ ነበሩ።—ሉቃስ 2:36-38
8-9. መበለቶች ምን ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ?
8 በዘመናችንም ለወጣቶች ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ታማኝ አረጋውያን አሉ። የእህት ሎይስ ዲደርን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሎይስ በካናዳ በልዩ አቅኚነት ማገልገል በጀመረችበት ወቅት ገና 21 ዓመቷ ነበር። በኋላም እሷና ባለቤቷ ጆን በጉብኝት ሥራ ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል። በኋላም በካናዳ ቤቴል ከ20 ዓመታት በላይ አገልግለዋል። ሎይስ 58 ዓመት ሲሆናት እሷና ጆን በዩክሬን እንዲያገለግሉ ግብዣ ቀረበላቸው። ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን? ዕድሜያቸው ስለገፋ በሌላ አገር ማገልገል እንደማይችሉ ይሰማቸው ይሆን? በፍጹም። የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበሉ፤ ጆንም እዚያ በቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ እንዲያገለግል ተሾመ። ጆን ከሰባት ዓመት በኋላ ሕይወቱ ቢያልፍም ሎይስ በአገልግሎት ምድቧ ለመቀጠል ወሰነች። ሎይስ አሁን 81 ዓመቷ ሲሆን በዩክሬን ቤቴል ውስጥ በታማኝነት እያገለገለች ነው፤ የቤቴል ቤተሰቡ አባላትም በጣም ይወዷታል።
9 እንደ ሎይስ ያሉ መበለቶች፣ የትዳር ጓደኛቸው በሕይወት ሳለ የነበረውን ያህል ትኩረት አይሰጣቸው ይሆናል፤ ያም ቢሆን መበለት መሆናቸው ዋጋቸውን አይቀንሰውም። የትዳር ጓደኛቸውን ለበርካታ ዓመታት ሲደግፉ የቆዩ እንዲሁም አሁንም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን የቀጠሉ እህቶችን ይሖዋ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (1 ጢሞ. 5:3) በተጨማሪም እነዚህ አረጋውያን እህቶች በዕድሜ ከእነሱ የሚያንሱትን በእጅጉ ያበረታታሉ።
10. ቶኒ ምን ግሩም ምሳሌ ትቶልናል?
10 በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ የሚኖሩት ወይም ከቤታቸው መውጣት የማይችሉት በርካታ ታማኝ አረጋውያንም ውድ ሀብት ናቸው። ቶኒ የተባለን ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ቶኒ የሚኖረው በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ ነው። ነሐሴ 1942 በፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በ20 ዓመቱ ተጠመቀ። ብዙም ሳይቆይ በገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት ፈተና ገጠመው፤ በዚህም የተነሳ ለሁለት ዓመት ተኩል ታስሯል።
እሱና ባለቤቱ ሂልዳ ሁለት ልጆቻቸውን እውነት ውስጥ አሳድገዋል። ባለፉት ዓመታት ውስጥ ቶኒ በሦስት ጉባኤዎች ውስጥ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች (አሁን የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ይባላል) እንዲሁም የወረዳ ስብሰባ የበላይ ተመልካች ሆኖ አገልግሏል። በማረሚያ ቤት ውስጥ የጉባኤ ስብሰባዎችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራ ነበር። ቶኒ አሁን 98 ዓመቱ ቢሆንም ጠንክሮ መሥራቱን አላቆመም። አቅሙ በፈቀደ መጠን ይሖዋን ለማገልገል እንዲሁም ከጉባኤው ጋር ተባብሮ ለመሥራት ጥረት ያደርጋል!11. በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ የሚኖሩ ወይም ከቤታቸው መውጣት የማይችሉ አረጋውያንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከታቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
11 በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ ለሚኖሩ ወይም ከቤታቸው መውጣት ለማይችሉ አረጋውያን አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ሽማግሌዎች እነዚህ አረጋውያን በተቻለ መጠን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ እንዲሁም በአገልግሎት እንዲካፈሉ ሊረዷቸው ይችላሉ። እኛም እነሱን ሄደን በመጠየቅ አሊያም ደግሞ በስልክ ወይም በቪዲዮ ጥሪ አማካኝነት በማነጋገር ትኩረት እንደምንሰጣቸው ማሳየት እንችላለን። በተለይም ከጉባኤያቸው ርቆ በሚገኝ ተቋም ውስጥ ለሚኖሩ አረጋውያን ልዩ ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል። እነዚህን አረጋውያን ችላ እንዳንላቸው መጠንቀቅ ይኖርብናል። አንዳንድ አረጋውያን ስለ ራሳቸው ማውራት ሊከብዳቸው ወይም ሊያሳፍራቸው ይችላል። ሆኖም ጊዜ ወስደን ጥያቄዎችን ከጠየቅናቸው እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ሲካፈሉ ያገኟቸውን አስደሳች ተሞክሮዎች ሲነግሩን ካዳመጥናቸው ትልቅ ጥቅም እናገኛለን።
12. በራሳችን ጉባኤ ውስጥ ምን ልናገኝ እንችላለን?
12 በራሳችን ጉባኤ ውስጥም ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ታማኝ አረጋውያንን ማግኘት እንችላለን። ሃሪየት የተባለች እህት በኒው ጀርሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ጉባኤዋ ውስጥ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት ይሖዋን አገልግላለች። በኋላ ግን ከልጇ ጋር ለመኖር ወደ ሌላ አካባቢ ተዛወረች። በአዲሱ ጉባኤዋ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች እሷን በደንብ ለማወቅ ጥረት አደረጉ፤ እንዲህ በማድረጋቸውም ለጉባኤው ውድ ሀብት እንደሆነች ተገነዘቡ። ሃሪየት እውነትን በሰማችበት ወቅት ማለትም በ1920ዎቹ ዓመታት ያጋጠሟትን የአገልግሎት ተሞክሮዎች በመንገር አበረታታቻቸው። በወቅቱ አገልግሎት ስትወጣ በድንገት ተይዛ ልትታሰር እንደምትችል ስለምትጠብቅ ሁልጊዜ የጥርስ ብሩሽ ትይዝ ነበር። ደግሞም በ1933 ሁለት ጊዜ ለአንድ ሳምንት ያህል ታስራለች። ባለቤቷ የይሖዋ ምሥክር ባይሆንም ይደግፋት ነበር፤ በታሰረችባቸው ወቅቶች ሦስት ትናንሽ ልጆቻቸውን ሲንከባከብ ቆይቷል። በእርግጥም እንደ ሃሪየት ያሉ ታማኝ አረጋውያን እንደ ውድ ሀብት ሊታዩ ይገባል!
13. አረጋውያን በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ ያላቸውን ቦታ በተመለከተ ምን ትምህርት አግኝተናል?
13 አረጋውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ ጠቃሚ ሚና ይጫወታሉ። ይሖዋ ድርጅቱንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ እነሱን በተለያየ መንገድ የባረካቸው እንዴት እንደሆነ ተመልክተዋል። ከሠሯቸው ስህተቶች ጠቃሚ ትምህርቶችን አግኝተዋል። እነዚህን ክርስቲያኖች “የጥበብ ምንጭ” እንደሆኑ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው፤ እንዲሁም ከእነሱ ተሞክሮ ተማሩ። (ምሳሌ 18:4) ጊዜ ወስዳችሁ እነሱን በደንብ ለማወቅ ጥረት ካደረጋችሁ እምነታችሁ ይጠናከራል፤ እንዲሁም ብዙ ትምህርት ታገኛላችሁ።
ከአረጋውያን ምሳሌ የተሟላ ጥቅም አግኙ
14. ዘዳግም 32:7 ወጣቶች ምን እንዲያደርጉ ያበረታታል?
14 ቅድሚያውን ወስዳችሁ አረጋውያንን አነጋግሯቸው። (ዘዳግም 32:7ን አንብብ።) እርግጥ ነው በአሁኑ ወቅት ዓይናቸው ደካማ፣ እርምጃቸው አዝጋሚ፣ ድምፃቸውም ዝግ ያለ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ልባቸው አሁንም ወጣት ነው፤ ደግሞም በይሖዋ ፊት “ጥሩ ስም” አትርፈዋል። (መክ. 7:1) ይሖዋ እነሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው ለምን እንደሆነ አስታውሱ። ምንጊዜም አክብሮት አሳዩአቸው። ልክ እንደ ኤልሳዕ ሁኑ። ኤልሳዕ ከኤልያስ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን ላይ ከእሱ ላለመለየት ቆርጦ ነበር። ኤልሳዕ ሦስት ጊዜ ኤልያስን “ከአንተ አልለይም” ብሎታል።—2 ነገ. 2:2, 4, 6
15. አረጋውያንን የትኞቹን ጥያቄዎች ልንጠይቃቸው እንችላለን?
15 አረጋውያንን በደግነት አንዳንድ ጥያቄዎችን በመጠየቅ፣ በሌላ አባባል ውስጣቸው ያለውን ቀድተን በማውጣት ትኩረት እንደምንሰጣቸው ማሳየት እንችላለን። (ምሳሌ 1:5፤ 20:5፤ 1 ጢሞ. 5:1, 2) እንደሚከተለው ያሉ ጥያቄዎችን ልንጠይቃቸው እንችላለን፦ “ወጣት ሳለህ እውነትን እንዳገኘህ እርግጠኛ እንድትሆን ያደረገህ ምንድን ነው?” “በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠሙህ ነገሮች ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ የረዱህ እንዴት ነው?” “በይሖዋ አገልግሎት ምንጊዜም ደስተኛ ሆኖ ለመኖር ቁልፉ ምንድን ነው ትላለህ?” (1 ጢሞ. 6:6-8) ከዚያም ታሪካቸውን ሲነግሩን በጥሞና ማዳመጥ ይኖርብናል።
16. ወጣቶችና አረጋውያን እርስ በርስ መጨዋወታቸው ሁለቱንም የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
16 ወጣቶችና አረጋውያን እርስ በርስ መጨዋወታቸው ሁለቱንም ይጠቅማቸዋል። (ሮም 1:12) እንዲህ ያለው ጭውውት፣ ወጣቶቹ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ምንጊዜም እንደማይጥል እንዲተማመኑ ያደርጋቸዋል፤ አረጋውያኑን ደግሞ እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው ያደርጋል። አረጋውያን በሕይወታቸው ውስጥ የይሖዋን በረከት ያዩት እንዴት እንደሆነ መናገር ያስደስታቸዋል።
17. ታማኝ የሆኑ አረጋውያን ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይበልጥ ውብ ይሆናሉ የምንለው ለምንድን ነው?
17 ውጫዊ ውበት በአብዛኛው ዕድሜ ሲጨምር እየደበዘዘ ይሄዳል፤ ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ግን ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በይሖዋ ዓይን ይበልጥ ውብ ይሆናሉ። (1 ተሰ. 1:2, 3) ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በይሖዋ አገልግሎት ባሳለፏቸው ዓመታት የአምላክ መንፈስ እንዲቀርጻቸውና እንዲያጠራቸው ፈቅደዋል። ታማኝ የሆኑ አረጋውያን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይበልጥ ባወቅናቸው፣ ባከበርናቸውና ከእነሱ በተማርን መጠን እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንመለከታቸዋለን!
18. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
18 ጉባኤው እንዲጠናከር የሚያደርገው ወጣቶች አረጋውያንን ውድ አድርገው መመልከታቸው ብቻ አይደለም፤ አረጋውያንም ወጣቶችን ከፍ አድርገው መመልከት አለባቸው። አረጋውያን በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ከፍ አድርገው እንደሚመለከቷቸው ማሳየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
መዝሙር 144 ዓይንህ ሽልማቱ ላይ ያተኩር!
^ አን.5 ታማኝ አረጋውያን ውድ ሀብት ናቸው። ይህ ርዕስ ለእነሱ ያለንን አድናቆት እንድናሳድግ ያበረታታናል፤ እንዲሁም ከእነሱ ጥበብና ተሞክሮ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። ከዚህም ሌላ፣ አረጋውያን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ አስፈላጊ ቦታ እንዳላቸው እንዲተማመኑ ይረዳቸዋል።