በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 39

የቤተሰባችሁ አባል ይሖዋን ሲተው

የቤተሰባችሁ አባል ይሖዋን ሲተው

“ብዙ ጊዜ ስሜቱን ጎዱት!”—መዝ. 78:40

መዝሙር 102 ‘ደካማ የሆኑትን እርዱ’

ማስተዋወቂያ *

1. አንዳንዶች የቤተሰባቸው አባል ሲወገድ ምን ሊሰማቸው ይችላል?

ከቤተሰባችሁ አባላት አንዱ ከጉባኤ ተወግዷል? ይህ ሁኔታ ልብ እንደሚሰብር ምንም ጥያቄ የለውም። ሂልዳ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ለ41 ዓመታት አብሮኝ የኖረው ባለቤቴ ሲሞት ከዚህ የከፋ ነገር ሊገጥመኝ እንደማይችል አስቤ ነበር። * ሆኖም ልጄ እውነትን ሲተው እንዲሁም ባለቤቱንና ልጆቹን ጥሎ ሲሄድ ከባለቤቴ ሞት በእጅጉ የከፋ ሐዘን ደርሶብኛል።”

የቤተሰባችሁ አባል እውነትን ሲተው ምን ያህል እንደምታዝኑ ይሖዋ ይረዳል (ከአንቀጽ 2-3⁠ን ተመልከት) *

2-3. በመዝሙር 78:40, 41 መሠረት ይሖዋ አገልጋዮቹ ሲተዉት ምን ይሰማዋል?

2 ይሖዋ የቤተሰቡ አባላት የነበሩት መላእክት ጀርባቸውን ሲሰጡት ምን ያህል አዝኖ እንደሚሆን እስቲ አስቡት! (ይሁዳ 6) በተጨማሪም የሚወዳቸው ሕዝቦቹ የነበሩት እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ሲያምፁበት ስሜቱ ምን ያህል ተጎድቶ እንደሚሆን አስቡት። (መዝሙር 78:40, 41ን አንብብ።) አፍቃሪው የሰማዩ አባታችን የእናንተም ቤተሰብ አባል እሱን ሲተወው በጣም እንደሚያዝን አትጠራጠሩ። ይሖዋ የሚሰማችሁን ሐዘን ይረዳል። እንዲሁም የሚያስፈልጋችሁን ማበረታቻና ድጋፍ በርኅራኄ ይሰጣችኋል።

3 የቤተሰባችን አባል አምላክን ማገልገሉን ሲተው የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንደምንችል በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በጉባኤያችን ውስጥ እንዲህ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጠማቸው ክርስቲያኖች ካሉ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነም እንመረምራለን። በመጀመሪያ ግን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን የትኛውን አሉታዊ አመለካከት ማስወገድ እንዳለብን እንመልከት።

ራሳችሁን አትውቀሱ

4. በርካታ ወላጆች ልጃቸው ይሖዋን ሲተው ምን ይሰማቸዋል?

4 ወላጆች የሚወዱት ልጃቸው ይሖዋን ሲተው ‘እንዲህ ባደርግ ኖሮ ልጄ ከእውነት አይወጣም ነበር’ በማለት ራሳቸውን ይወቅሱ ይሆናል። ሉክ የተባለ ወንድም ልጁ በመወገዱ የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ራሴን እወቅስ ነበር። ጉዳዩ ሌሊት እንኳ ያቃዠኝ ነበር። አንዳንዴ በጣም አለቅስ ነበር፤ ልቤ ተሰብሮ ነበር።” ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠማት ኤሊዛቤት የተባለች እህትም እንዲህ ብላለች፦ “‘የእናትነት ኃላፊነቴን በሚገባ አልተወጣሁ ይሆን?’ ብዬ አስብ ነበር። በልጄ ልብ ውስጥ እውነትን ለመትከል ማድረግ ያለብኝን ያህል እንዳላደረግኩ ተሰማኝ።”

5. አንድ ሰው እውነትን ሲተው ተጠያቂው ማን ነው?

5 ይሖዋ ለሁላችንም የመምረጥ ነፃነት እንደሰጠን ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም እሱን ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ መምረጥ እንችላለን። አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ባይሆኑላቸውም እንኳ ይሖዋን ለማገልገል መርጠዋል፤ እንዲሁም ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ቀጥለዋል። ሌሎች ልጆች ደግሞ ወላጆቻቸው እነሱን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት ለማሳደግ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ቢያደርጉም ካደጉ በኋላ እውነትን ለመተው መርጠዋል። ከዚህ መመልከት እንደምንችለው ይሖዋን ማገልገል እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ የምናደርገው ውሳኔ ነው። (ኢያሱ 24:15) እንግዲያው ልጃቸው እውነትን በመተዉ ያዘኑ ወላጆች ሁኔታው የእነሱ ጥፋት እንደሆነ ሊሰማቸው አይገባም።

6. ልጆች ወላጆቻቸው እውነትን ሲተዉ ምን ሊሰማቸው ይችላል?

6 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወላጆች እውነትን ይተዉ፣ ሌላው ቀርቶ ቤተሰባቸውንም ጥለው ይሄዱ ይሆናል። (መዝ. 27:10) ይህ ሁኔታ ወላጆቻቸውን እንደ ምሳሌ ሲመለከቱ የኖሩትን ልጆች ቅስማቸውን ሊሰብረው ይችላል። የኤስተርን ምሳሌ እንመልከት፤ ኤስተር አባቷ በተወገደበት ወቅት ምን እንደተሰማት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ጊዜ አለቅስ ነበር፤ ምክንያቱም አባቴ ከእውነት የራቀው ሳያስበው እንዳልሆነ ገብቶኝ ነበር። ይሖዋን የተወው ሆን ብሎ ነው። አባቴን እወደዋለሁ፤ ስለዚህ ከተወገደ በኋላም ሁልጊዜ ደህንነቱ ያሳስበኝ ነበር። በጭንቀት የምዋጥባቸው ጊዜያት ነበሩ።”

7. ይሖዋ ወላጆቻቸው የተወገዱባቸውን ወጣቶች በተመለከተ ምን ይሰማዋል?

7 ወጣቶች፣ አባታችሁ ወይም እናታችሁ ተወግደው ከሆነ ሐዘናችሁ ይሰማናል። ይሖዋም ሥቃያችሁን በሚገባ እንደሚረዳው አትጠራጠሩ። ይሖዋ ይወዳችኋል፤ እንዲሁም የምታሳዩትን ታማኝነት ያደንቃል፤ እኛ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁም እንደዚያው። በተጨማሪም ለወላጆቻችሁ ውሳኔ እናንተ ተጠያቂ እንዳልሆናችሁ አስታውሱ። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ ለእያንዳንዱ ሰው የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷል። ራሱን ወስኖ የተጠመቀ እያንዳንዱ ክርስቲያን “የራሱን የኃላፊነት ሸክም” መሸከም አለበት።—ገላ. 6:5

8. የቤተሰባቸው አባል የተወገደባቸው ክርስቲያኖች ግለሰቡ ወደ ይሖዋ እስኪመለስ በሚጠብቁበት ወቅት ምን ማድረግ ይችላሉ? ( “ወደ ይሖዋ ተመለስ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

8 የቤተሰባችሁ አባል ይሖዋን ሲተው ግለሰቡ አንድ ቀን ወደ ይሖዋ እንደሚመለስ ተስፋ ማድረጋችሁ አይቀርም። ታዲያ ይህ እስኪሆን ድረስ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? የራሳችሁን መንፈሳዊነት መንከባከብ ትችላላችሁ። እንዲህ ስታደርጉ ለሌሎቹ የቤተሰባችሁ አባላት፣ ምናልባትም ለተወገደው ሰውም ጭምር ጥሩ ምሳሌ ትሆናላችሁ። እንዲሁም የሚሰማችሁን ሐዘን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ታገኛላችሁ። ልትወስዷቸው የምትችሏቸውን አንዳንድ እርምጃዎች እስቲ እንመልከት።

በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆናችሁ ለመቀጠል ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

9. ከይሖዋ ብርታት ማግኘት የምትችሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው? (“ የቤተሰባችሁ አባል ይሖዋን ሲተው ሊያጽናኗችሁ የሚችሉ ጥቅሶች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

9 አዘውትራችሁ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላችሁን ቀጥሉ። የራሳችሁንም ሆነ የሌሎቹን የቤተሰባችሁን አባላት መንፈሳዊነት ማጠናከራችሁን መቀጠላችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? አዘውትራችሁ የአምላክን ቃል በማንበብና ባነበባችሁት ላይ በማሰላሰል እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ከይሖዋ ብርታት አግኙ። የጆአናን ምሳሌ እንመልከት፤ ጆአና አባቷና እህቷ እውነትን ትተዋል፤ እንዲህ ብላለች፦ “እንደ አቢጋኤል፣ አስቴር፣ ኢዮብ፣ ዮሴፍና ኢየሱስ ስላሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ሳነብ ውስጤ ይረጋጋል። የእነሱ ምሳሌ ያበረታታኛል፤ እንዲሁም አዎንታዊ አመለካከት እንድይዝ ይረዳኛል። ኦሪጅናል መዝሙሮቻችንም በእጅጉ ያበረታቱኛል።”

10. የሚሰማንን ጭንቀት መቋቋም የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ መዝሙር 32:6-8 ምን ይነግረናል?

10 የሚያሳስባችሁን ነገር በሙሉ ለይሖዋ ንገሩት። በጭንቀት በምትዋጡበት ጊዜም ወደ እሱ ከመጸለይ ወደኋላ አትበሉ። አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ሁኔታውን ከእሱ አመለካከት አንጻር ለማየት እንዲረዳችሁ እንዲሁም ‘ጥልቅ ማስተዋል እንዲሰጣችሁና ልትሄዱበት የሚገባውን መንገድ እንዲያስተምራችሁ’ ለምኑት። (መዝሙር 32:6-8ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ የሚሰማችሁን ሁሉ ግልጥልጥ አድርጋችሁ ለይሖዋ መናገሩ በጣም ይረብሻችሁ ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ የሚሰማችሁን ሥቃይ ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳ አስታውሱ። ይሖዋ በጣም ይወዳችኋል፤ እንዲሁም ልባችሁን በፊቱ እንድታፈሱ ጋብዟችኋል።—ዘፀ. 34:6፤ መዝ. 62:7, 8

11. በዕብራውያን 12:11 መሠረት ፍቅር በሚንጸባረቅበት የይሖዋ እርማት መተማመን ያለብን ለምንድን ነው? (“ ውገዳ—ፍቅር የሚንጸባረቅበት የይሖዋ ተግሣጽ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

11 የሽማግሌዎችን ውሳኔ ደግፉ። ውገዳ የይሖዋ ዝግጅት ነው። ፍቅር የሚንጸባረቅበት የይሖዋ እርማት ኃጢአት የሠራውን ግለሰብ ጨምሮ ሁሉንም ሰው ይጠቅማል። (ዕብራውያን 12:11ን አንብብ።) በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንዳንዶች፣ ሽማግሌዎች ትክክለኛውን ውሳኔ እንዳላደረጉ ይናገሩ ይሆናል፤ ሆኖም እንዲህ ያሉት ሰዎች ኃጢአት የሠራው ግለሰብ የፈጸማቸውን ስህተቶች ለመሸፋፈን ይሞክራሉ። ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ እንደሌለን ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም ውሳኔውን ያደረጉት ሽማግሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተልና “ለይሖዋ” ለመፍረድ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እንዳደረጉ መተማመናችን ጥበብ ይሆናል።—2 ዜና 19:6

12. አንዳንዶች የይሖዋን ተግሣጽ በመደገፋቸው ምን ጥቅም አግኝተዋል?

12 ሽማግሌዎች የቤተሰባችሁ አባል ከጉባኤው እንዲወገድ ያደረጉትን ውሳኔ መደገፋችሁ ግለሰቡ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ሊረዳው ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤሊዛቤት እንዲህ ብላለች፦ “ለአካለ መጠን ከደረሰው ልጃችን ጋር የነበረንን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ በጣም ከብዶን ነበር። ሆኖም ልጃችን ወደ ይሖዋ ከተመለሰ በኋላ፣ ያኔ መወገዱ ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር ተናግሯል። ከጊዜ በኋላ እንደተናገረው በጣም ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶች አግኝቷል። ይህም የይሖዋ ተግሣጽ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ አስተምሮኛል።” ባለቤቷ ማርክ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ልጃችን ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ያነሳሳው አንዱ ነገር፣ ከእሱ ጋር የነበረንን ግንኙነት ማቋረጣችን እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ነግሮኛል። ይሖዋ ታዛዦች እንድንሆን ስለረዳን በጣም ደስተኛ ነኝ።”

13. የደረሰባችሁን የስሜት ሥቃይ ለመቋቋም ምን ሊረዳችሁ ይችላል?

13 ለቅርብ ወዳጆቻችሁ ስሜታችሁን አካፍሏቸው። አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር ሊረዷችሁ ከሚችሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር ተቀራረቡ። (ምሳሌ 12:25፤ 17:17) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጆአና እንዲህ ብላለች፦ “ብቻዬን እንደሆንኩ ተሰምቶኝ ነበር። ሆኖም ለማምናቸው ጓደኞቼ ስሜቴን ማካፈሌ ሁኔታውን ለመቋቋም ረድቶኛል።” ይሁንና በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ይባስ እንዲከፋችሁ የሚያደርግ ነገር ቢናገሩስ?

14. ‘እርስ በርስ መቻቻላችንንና በነፃ ይቅር መባባላችንን መቀጠል’ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

14 ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በትዕግሥት ያዟቸው። ሁሉም ሰው ሁልጊዜ ትክክለኛውን ነገር ይናገራል ብለን መጠበቅ አንችልም። (ያዕ. 3:2) ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም አንዳንዶች ምን ማለት እንዳለባቸው ግራ ቢገባቸው ይባስ ብሎም የሚጎዳችሁን ነገር ሳያስቡት ቢናገሩ ልትገረሙ አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” በማለት የሰጠውን ምክር አስታውሱ። (ቆላ. 3:13) የቤተሰቧ አባል ተወግዶባት የነበረ አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ሊያበረታቱኝ አስበው የሚጎዳኝ ነገር የተናገሩ ወንድሞችን ይቅር እንድላቸው ይሖዋ ረድቶኛል።” ታዲያ የቤተሰባቸው አባል የተወገደባቸውን ታማኝ ክርስቲያኖች ለመርዳት ጉባኤው ምን ማድረግ ይችላል?

ጉባኤው ምን እርዳታ ማበርከት ይችላል?

15. የቤተሰባቸው አባል በቅርቡ የተወገደባቸውን ክርስቲያኖች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

15 ታማኝ የሆኑት የቤተሰብ አባላት ወደ ስብሰባ ሲመጡ ሞቅ አድርጋችሁ ተቀበሏቸው። ሚርያም የተባለች እህት ወንድሟ ከተወገደ በኋላ ወደ ስብሰባ መሄድ ጨንቋት እንደነበረ ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “‘ሌሎች ምን ይሉ ይሆን’ የሚለው አሳስቦኝ ነበር። ሆኖም በርካታ ግሩም ወዳጆቼ ሐዘኔን እንደሚጋሩ አሳይተውኛል፤ እንዲሁም ስለተወገደው ወንድሜ ምንም አሉታዊ ነገር አልተናገሩም። እነሱ ከጎኔ መሆናቸው በሐዘን በተዋጥኩበት በዚህ ወቅት ብቻዬን እንዳልሆንኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።” ሌላ እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ልጃችን ከተወገደ በኋላ ጓደኞቻችን ሊያጽናኑን መጡ። አንዳንዶቹ ምን ብለው እንደሚያጽናኑን ግራ እንደገባቸው ነግረውን ነበር። አብረውኝ ያለቀሱ እንዲሁም የሚያጽናና ደብዳቤ የጻፉልኝ ወንድሞችና እህቶች ነበሩ። እነሱ ያደረጉልኝ ነገር በእጅጉ ረድቶኛል!”

16. ጉባኤው ድጋፍ ማድረጉን መቀጠል የሚችለው እንዴት ነው?

16 ታማኝ የሆኑትን የቤተሰብ አባላት ማበረታታታችሁን አታቋርጡ። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በዚህ ወቅት የእናንተ ፍቅርና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። (ዕብ. 10:24, 25) የቤተሰባቸው አባል የተወገደባቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ጉባኤው እነሱንም ጭምር እንዳገለላቸው የተሰማቸው ጊዜ አለ። እነዚህ ክርስቲያኖች እንዲህ እንዲሰማቸው ልናደርግ አይገባም። በተለይም እውነትን የተዉ ወላጆች ያሏቸው ወጣቶች ምስጋናና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ማሪያ ባለቤቷ የተወገደ ከመሆኑም ሌላ ቤተሰቡን ጥሎ ሄዷል፤ ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጓደኞቼ ወደ ቤቴ መጥተው ምግብ ያበስሉ እንዲሁም አብረውን የቤተሰብ ጥናት ያደርጉ ነበር። ሐዘኔን ተጋርተውኛል፤ እንዲሁም አብረውኝ አልቅሰዋል። ስለ እኔ አሉባልታ ሲናፈስ ጥብቅና ቆመውልኛል። እነዚህ ወዳጆቼ በእጅጉ አበረታተውኛል!”—ሮም 12:13, 15

ጉባኤው ታማኝ ለሆኑት የቤተሰብ አባላት ፍቅራዊ ድጋፍ መስጠት ይችላል (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት) *

17. ሽማግሌዎች በሐዘን የተዋጡ ክርስቲያኖችን ማበረታታት የሚችሉት እንዴት ነው?

17 ሽማግሌዎች፣ የቤተሰባቸው አባል የተወገደባቸውን ክርስቲያኖች ያገኛችሁትን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅማችሁ አበረታቷቸው። ይሖዋን የተወ የቤተሰብ አባል ያላቸውን የእምነት ባልንጀሮቻችሁን የማጽናናት ልዩ ኃላፊነት አለባችሁ። (1 ተሰ. 5:14) ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በፊትና በኋላ እነሱን ለማበረታታት ቅድሚያውን ውሰዱ። ቤታቸው ሄዳችሁ ጠይቋቸው፤ እንዲሁም ጸልዩላቸው። አብራችኋቸው አገልግሉ፤ አልፎ አልፎ ደግሞ በቤተሰብ አምልኳችሁ ላይ ጋብዟቸው። መንፈሳዊ እረኞች በሐዘን ለተዋጡ የይሖዋ በጎች የሚያስፈልጋቸውን ርኅራኄና ፍቅር የማሳየት እንዲሁም ለእነሱ ትኩረት የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው።—1 ተሰ. 2:7, 8

ተስፋ ማድረጋችሁንና በይሖዋ መታመናችሁን ቀጥሉ

18. በ2 ጴጥሮስ 3:9 መሠረት አምላክ ኃጢአተኞች ምን እንዲያደርጉ ይፈልጋል?

18 ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ” አይፈልግም። (2 ጴጥሮስ 3:9ን አንብብ።) አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምም እንኳ ሕይወቱ በአምላክ ዓይን ውድ ነው። ይሖዋ የኃጢአተኞችን ሕይወት ለማዳን ሲል ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንደከፈለ አስቡት፤ የሚወደውን ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። ይሖዋ በርኅራኄ ተነሳስቶ ኃጢአተኞች ወደ እሱ እንዲመለሱ ሊረዳቸው ይጥራል። ኢየሱስ ስለጠፋው ልጅ ከተናገረው ምሳሌ እንደምንማረው ይሖዋ እንዲህ ያሉ ሰዎች ወደ እሱ እንደሚመለሱ ተስፋ ያደርጋል። (ሉቃስ 15:11-32) እውነትን ትተው የነበሩ ብዙ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ወደ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታቸው ተመልሰዋል። ጉባኤውም እጁን ዘርግቶ ተቀብሏቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤሊዛቤት ልጇ በመመለሱ በጣም ተደስታለች። ሁኔታውን መለስ ብላ ስታስታውስ “ብዙዎች ተስፋ እንዳንቆርጥ ስላበረታቱን በጣም አመስጋኝ ነኝ” ብላለች።

19. ምንጊዜም በይሖዋ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

19 ምንጊዜም በይሖዋ መተማመን እንችላለን። ይሖዋ የሚሰጠን መመሪያ ሁሉ ለጥቅማችን ነው። ይሖዋ ለሚወዱትና ለሚያመልኩት ሰዎች ሁሉ ጥልቅ ፍቅር ያለው ለጋስና ሩኅሩኅ አባት ነው። ይሖዋ በሐዘን በተዋጣችሁበት ጊዜ እንደማይተዋችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ። (ዕብ. 13:5, 6) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ማርክ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ መቼም ቢሆን ትቶን አያውቅም። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ምንጊዜም ከጎናችን ነው።” ይሖዋ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ ይሰጣችኋል። (2 ቆሮ. 4:7) አዎ፣ የቤተሰባችሁ አባል ይሖዋን ቢተውም እንኳ እናንተ በታማኝነት መጽናት እንዲሁም ግለሰቡ እንደሚመለስ ተስፋ ማድረግ ትችላላችሁ።

መዝሙር 44 የተቸገረ ሰው ጸሎት

^ አን.5 አንድ የቤተሰባችን አባል ይሖዋን ሲተው በእጅጉ እንደምናዝን የታወቀ ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን አምላካችን ምን እንደሚሰማው በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም ታማኝ የሆኑት የቤተሰብ አባላት ይህ ሁኔታ የሚያስከትለውን ሥቃይ ለመቋቋምና ጠንካራ መንፈሳዊነት ይዘው ለመቀጠል ምን ማድረግ እንደሚችሉ እንመለከታለን። ከዚህም ሌላ፣ በጉባኤው ውስጥ ያሉ በሙሉ ለቤተሰቡ ማጽናኛና ድጋፍ መስጠት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይህ ርዕስ ያብራራል።

^ አን.1 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.79 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ቤተሰቡንና ይሖዋን መተዉ ሚስቱንና ልጆቹን በጣም ጎድቷቸዋል።

^ አን.81 የሥዕሉ መግለጫ፦ ሁለት ሽማግሌዎች በጉባኤያቸው ውስጥ ያለን አንድ ቤተሰብ ሄደው ሲያበረታቱ።