የጥናት ርዕስ 39
ስማችሁ “በሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ ተጽፏል?
“ይሖዋንም ለሚፈሩ . . . በፊቱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።”—ሚል. 3:16
መዝሙር 61 እናንተ ምሥክሮች ወደፊት ግፉ!
ማስተዋወቂያ *
1. በሚልክያስ 3:16 መሠረት ይሖዋ የትኛውን መጽሐፍ ሲጽፍ ቆይቷል? መጽሐፉስ ምን ይዟል?
በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይሖዋ አንድ ልዩ መጽሐፍ ሲጽፍ ቆይቷል። ይህ መጽሐፍ የስም ዝርዝር ይዟል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስሙ የተጻፈው የመጀመሪያ ሰው፣ የመጀመሪያው ታማኝ ምሥክር የሆነው አቤል ነው። * (ሉቃስ 11:50, 51) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ይሖዋ በመጽሐፉ ውስጥ ተጨማሪ ስሞችን ሲያሰፍር ቆይቷል። በዛሬው ጊዜ ይህ መጽሐፍ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስሞችን ይዟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ መጽሐፍ “የመታሰቢያ መጽሐፍ፣” “የሕይወት መጽሐፍ” እንዲሁም “የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል” ተብሎ ተጠርቷል። በዚህ ርዕስ ውስጥ “የሕይወት መጽሐፍ” የሚለውን አጠራር እንጠቀማለን።—ሚልክያስ 3:16ን አንብብ፤ ራእይ 3:5፤ 17:8
2. በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የእነማን ስም ነው? ስማችን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንዲጻፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
2 ይህ ልዩ መጽሐፍ ይሖዋን በፍርሃት ወይም በጥልቅ አክብሮት የሚያመልኩ እንዲሁም ስሙን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎችን ስም በሙሉ ይዟል። እነዚህ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ አላቸው። በዛሬው ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና ከመሠረትን ስማችን በዚህ መጽሐፍ ላይ ሊጻፍ ይችላል። (ዮሐ. 3:16, 36) ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ይሁን በምድር ላይ መኖር ሁላችንም ስማችን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንዲገኝ እንፈልጋለን።
3-4. (ሀ) በአሁኑ ወቅት ስማችን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ መስፈሩ የዘላለም ሕይወት እንደምናገኝ ዋስትና ይሆናል? አብራራ። (ለ) በዚህና በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
3 ታዲያ ይህ ሲባል ስማቸው በዚህ መጽሐፍ ላይ የሰፈረ ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ዋስትና አላቸው ማለት ነው? በዘፀአት 32:33 ላይ ይሖዋ ለሙሴ የተናገረው ሐሳብ የዚህን ጥያቄ መልስ ይሰጠናል፤ ይሖዋ “በእኔ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሁሉ ከመጽሐፌ ላይ እደመስሰዋለሁ” ብሏል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በዚህ መጽሐፍ ላይ የሰፈሩ ስሞች ሊደመሰሱ ወይም ሊሰረዙ ይችላሉ። ይሖዋ ስሞቹን መጀመሪያ ላይ የሚጽፈው በእርሳስ ነው ሊባል ይችላል። (ራእይ 3:5 ግርጌ) ስማችን በምሳሌያዊ ሁኔታ በብዕር በቋሚነት እስኪጻፍ ድረስ ከዚህ መጽሐፍ ሳይሰረዝ እንዲቆይ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።
4 ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ስለተጻፈና ስላልተጻፈ ሰዎች ምን ይላል? ስማቸው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት መቼ ነው? ይሖዋን የማወቅ አጋጣሚ ሳያገኙ ስለሞቱ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ ሊጻፍ ይችላል? በዚህና በቀጣዩ ርዕስ ላይ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን።
መጽሐፉ የእነማንን ስም ይዟል?
5-6. (ሀ) ፊልጵስዩስ 4:3 እንደሚገልጸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የእነማን ስም ይገኛል? (ለ) እነዚህ ሰዎች ስማቸው በቋሚነት በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የሚጻፈው መቼ ነው?
5 በዚህ ምሳሌያዊ መጽሐፍ ላይ የእነማን ስም ተጽፏል? ይህን ጥያቄ ለመመለስ አምስት ቡድኖችን እንመለከታለን። ከእነዚህ ቡድኖች መካከል አንዳንዶቹ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፏል፤ የሌሎቹ ደግሞ አልተጻፈም።
6 የመጀመሪያው ቡድን በሰማይ ላይ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ የተመረጡትን ሰዎች ያቀፈ ነው። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፏል? አዎ። ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚገኙ ‘የሥራ ባልደረቦቹ’ ከጻፈው ሐሳብ እንደምንማረው ከኢየሱስ ጋር አብረው ለመግዛት የተመረጡት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስማቸው በአሁኑ ወቅት በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል። (ፊልጵስዩስ 4:3ን አንብብ።) ሆኖም ስማቸው በዚህ ምሳሌያዊ መጽሐፍ ውስጥ እንዲቆይ ታማኝነታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ከዚያም ከመሞታቸው በፊት ወይም ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት የመጨረሻው ማኅተም ሲደረግባቸው ስማቸው በቋሚነት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ይጻፋል።—ራእይ 7:3
7. የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ በቋሚነት የሚጻፍበትን ጊዜ በተመለከተ ከራእይ 7:16, 17 ምን እንማራለን?
7 ሁለተኛው ቡድን የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑትን እጅግ ብዙ ሕዝብ ያቀፈ ነው። የእነዚህ ሰዎች ስም በአሁኑ ወቅት በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል? አዎ። አርማጌዶንን በሕይወት ካለፉ በኋላም ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይኖራል? አዎ። (ራእይ 7:14) ኢየሱስ እነዚህ በግ መሰል ሰዎች “ወደ ዘላለም ሕይወት” እንደሚሄዱ ተናግሯል። (ማቴ. 25:46) ሆኖም ከአርማጌዶን በሕይወት የሚያልፉት እነዚህ ሰዎች ወዲያውኑ የዘላለም ሕይወት አያገኙም። ስማቸው በምሳሌያዊ ሁኔታ በእርሳስ እንደተጻፈ ይቆያል። በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት ኢየሱስ “እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም ይመራቸዋል።” የክርስቶስን አመራር የሚከተሉና በመጨረሻው ፍርድ ወቅት ለይሖዋ ታማኝ ሆነው የሚገኙ ሰዎች ስማቸው በቋሚነት በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይጻፋል።—ራእይ 7:16, 17ን አንብብ።
8. በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የማይገኘው የእነማን ስም ነው? እነሱስ ምን ይጠብቃቸዋል?
8 ሦስተኛው ቡድን በአርማጌዶን የሚጠፉትን ፍየሎች የያዘ ነው። የእነዚህ ሰዎች ስም በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ አይገኝም። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች “ወደ ዘላለም ጥፋት” እንደሚሄዱ ተናግሯል። (ማቴ. 25:46) ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ “[እነዚህ ሰዎች] ዘላለማዊ ጥፋት ተፈርዶባቸው ከጌታ ፊት ይወገዳሉ” በማለት ጽፏል። (2 ተሰ. 1:9፤ 2 ጴጥ. 2:9) ባለፉት ዘመናት ሆን ብለው በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት የሠሩ ሰዎችም የሚደርስባቸው ዕጣ ተመሳሳይ ነው። እነሱም የሚጠብቃቸው የዘላለም ሕይወት ሳይሆን የዘላለም ጥፋት ነው። ትንሣኤ እንደማያገኙ ምንም ጥያቄ የለውም። (ማቴ. 12:32፤ ማር. 3:28, 29፤ ዕብ. 6:4-6) እስቲ አሁን ደግሞ በምድር ላይ ትንሣኤ የሚያገኙትን ሁለት ቡድኖች እንመልከት።
ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች
9. የሐዋርያት ሥራ 24:15 እንደሚገልጸው በምድር ላይ ትንሣኤ የሚያገኙት ሁለት ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነትስ ምንድን ነው?
9 መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት ተነስተው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ የሚያገኙ ሁለት ቡድኖች እንዳሉ ይናገራል፤ እነሱም “ጻድቃን” እና “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 24:15ን አንብብ።) “ጻድቃን” የተባሉት በሕይወት በነበሩበት ወቅት ይሖዋን በታማኝነት ያገለገሉ ሰዎች ናቸው። “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” የተባሉት ግን ይሖዋን በታማኝነት አላገለገሉም። እንዲያውም አብዛኞቹ ምግባራቸው ከጽድቅ ፈጽሞ የራቀ ነበር። ይሁንና ሁለቱም ቡድኖች ትንሣኤ የሚያገኙ መሆኑ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ እንደተጻፈ የሚጠቁም ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ሁለቱንም ቡድኖች በየተራ እንመልከት።
10. “ጻድቃን” ትንሣኤ የሚያገኙት ለምንድን ነው? ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ ምን መብት ያገኛሉ? (በተጨማሪም በዚህ መጽሔት ውስጥ የሚገኘውን ስለ ምድራዊ ትንሣኤ የሚገልጸውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።)
10 አራተኛው ቡድን “ጻድቃን” የተባሉትን ያቀፈ ነው። እነዚህ ሰዎች ከመሞታቸው በፊት ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ነበር። ታዲያ ሲሞቱ ስማቸው ከዚህ መጽሐፍ ላይ ተሰርዟል? በፍጹም። ምክንያቱም ከይሖዋ አመለካከት አንጻር አሁንም ‘ሕያዋን’ ናቸው። ይሖዋ “የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸውና።” (ሉቃስ 20:38) ከዚህ አንጻር ጻድቃን በምድር ላይ ትንሣኤ ሲያገኙ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ እንደተጻፈ ይገኛል። እርግጥ መጀመሪያ ላይ ስማቸው የሚገኘው በምሳሌያዊ ሁኔታ “በእርሳስ” ተጽፎ ነው። (ሉቃስ 14:14) ትንሣኤ ከሚያገኙት ጻድቃን መካከል አንዳንዶቹ “በምድር ሁሉ ላይ መኳንንት” ሆነው የማገልገል መብት እንደሚያገኙ ምንም ጥያቄ የለውም።—መዝ. 45:16
11. ከሞት የሚነሱት “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ከመጻፉ በፊት ምን መማር ያስፈልጋቸዋል?
11 በመጨረሻም አምስተኛውን ቡድን እንመልከት፤ ይህ ቡድን ‘ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎችን’ ያቀፈ ነው። እነዚህ ሰዎች ከመሞታቸው በፊት የጽድቅ ጎዳና አይከተሉም ነበር፤ ምናልባትም ይህ የሆነው የይሖዋን መሥፈርቶች ስላላወቁ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ አልተጻፈም። ሆኖም አምላክ እነሱን ከሞት በማስነሳት ከጊዜ በኋላ ስማቸው በዚያ መጽሐፍ ላይ እንዲሰፍር አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። እነዚህ “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ብዙ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ በቀድሞ ሕይወታቸው እጅግ አስከፊ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር። በመሆኑም በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች መሠረት ሕይወታቸውን መምራት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር ያስፈልጋቸዋል። ለዚህም ሲባል የአምላክ መንግሥት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ መጠነ ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር ያዘጋጃል።
12. (ሀ) ጻድቃን ያልሆኑትን ሰዎች የሚያስተምራቸው ማን ነው? (ለ) የተሰጣቸውን ትምህርት ለመቀበል ፈቃደኛ የማይሆኑ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል?
12 ጻድቃን ያልሆኑትን ሰዎች የሚያስተምራቸው ማን ነው? እጅግ ብዙ ሕዝብና ከሞት የተነሱት ጻድቃን ናቸው። እነዚህ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ እንዲጻፍ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና መመሥረትና ራሳቸውን ለእሱ መወሰን አለባቸው። ኢየሱስ ክርስቶስና ቅቡዓኑ እነዚህ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ለሚሰጣቸው ትምህርት የሚሰጡትን ምላሽ በትኩረት ይከታተላሉ። (ራእይ 20:4) ለሚሰጣቸው እርዳታ በጎ ምላሽ የማይሰጡ ሰዎች በሙሉ 100 ዓመት ቢሆናቸው እንኳ ይጠፋሉ። (ኢሳ. 65:20) የሰዎችን ልብ ማንበብ የሚችሉት ይሖዋና ኢየሱስ ማንም ሰው በአዲሱ ዓለም ውስጥ ችግር እንዲፈጥር አይፈቅዱም።—ኢሳ. 11:9፤ 60:18፤ 65:25፤ ዮሐ. 2:25
የሕይወት ትንሣኤ እና የፍርድ ትንሣኤ
13-14. (ሀ) ከዚህ ቀደም፣ በዮሐንስ 5:29 ላይ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ የምንረዳው እንዴት ነበር? (ለ) እነዚህን ቃላት በተመለከተ ምን ነገር ልብ ማለት ይኖርብናል?
13 ኢየሱስም በምድር ላይ ትንሣኤ ስለሚያገኙ ሰዎች ተናግሯል። ለምሳሌ እንዲህ ብሏል፦ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣልና፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።” (ዮሐ. 5:28, 29) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
14 ከዚህ ቀደም፣ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ከሞት ከተነሱ በኋላ የሚያደርጉትን ነገር እንደሚያመለክት እናስብ ነበር፤ ይህም ሲባል አንዳንዶች ከሞት ተነስተው መልካም እንደሚሠሩ፣ ሌሎች ደግሞ ከሞት ተነስተው ክፉ እንደሚሠሩ እናስብ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ከመታሰቢያ መቃብር የወጡ ሰዎች መልካም እንደሚሠሩ ወይም ክፉ እንደሚሠሩ እንዳልተናገረ ልብ በሉ። ከዚህ ይልቅ የተጠቀመበት ግስ አላፊ ጊዜን የሚያመለክት ነው። “መልካም የሠሩ” እና “ክፉ የሠሩ” በማለት ተናግሯል። ይህም፣ መልካም ወይም ክፉ የሠሩት ከመሞታቸው በፊት እንደሆነ ይጠቁማል። ይህ ሐሳብ ምክንያታዊ አይደለም? ደግሞም ማንም ሰው በአዲሱ ዓለም ውስጥ ክፉ እንዲሠራ አይፈቀድለትም። ስለዚህ ትንሣኤ ያገኙት ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ክፉ የሠሩት ከመሞታቸው በፊት መሆን አለበት። ታዲያ ኢየሱስ ስለ “ሕይወት ትንሣኤ” እና ስለ “ፍርድ ትንሣኤ” የተናገረውን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል?
15. ‘የሕይወት ትንሣኤ’ የሚያገኙት እነማን ናቸው? ለምንስ?
15 ከመሞታቸው በፊት መልካም የሠሩ ጻድቃን ‘የሕይወት ትንሣኤ’ ያገኛሉ፤ ምክንያቱም ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሯል። ይህም ሲባል በዮሐንስ 5:29 መሠረት ትንሣኤ የሚያገኙት “መልካም የሠሩ” ሰዎችና በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ የተጠቀሱት ትንሣኤ የሚያገኙ “ጻድቃን” አንድ ዓይነት ናቸው። ይህ ማብራሪያ በሮም 6:7 ላይ ካለው ሐሳብ ጋር ይስማማል፤ ጥቅሱ “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል” ይላል። እነዚህ ጻድቃን ሲሞቱ ኃጢአታቸው ተሰርዞላቸዋል፤ ያስመዘገቡት የታማኝነት ታሪክ ግን አልተሰረዘም። (ዕብ. 6:10) እርግጥ ትንሣኤ ያገኙት ጻድቃን ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ እንደተጻፈ እንዲቀጥል ከፈለጉ ታማኝነታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
16. ‘የፍርድ ትንሣኤ’ ምን ያመለክታል?
16 ከመሞታቸው በፊት ክፉ ስለሠሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ሲሞቱ ኃጢአታቸው የተሰረዘላቸው ቢሆንም የታማኝነት ታሪክ አላስመዘገቡም። ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ አልተጻፈም። በመሆኑም ትንሣኤ የሚያገኙት “ክፉ የሠሩ” ሰዎች በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ ከተጠቀሱት ትንሣኤ የሚያገኙ “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ጋር አንድ ዓይነት ናቸው። እነዚህ ሰዎች የሚያገኙት ትንሣኤ ‘የፍርድ ትንሣኤ’ ይሆናል። * ይህም ሲባል ኢየሱስ እነዚህን ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ይገመግማቸዋል ማለት ነው። (ሉቃስ ) ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ መጻፍ የሚገባው መሆኑን ለመወሰን ጊዜ ይወስዳል። እነዚህ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የሚጻፈው የቀድሞውን ክፉ አኗኗራቸውን ከተዉና ራሳቸውን ለይሖዋ ከወሰኑ ብቻ ነው። 22:30
17-18. በምድር ላይ ትንሣኤ የሚያገኙ ሁሉ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? ራእይ 20:12, 13 “እንደየሥራቸው” ሲል ምን ማለቱ ነው?
17 ከመሞታቸው በፊት ጻድቃን የነበሩም ሆኑ ያልነበሩ ሰዎች ትንሣኤ ካገኙ በኋላ በሺው ዓመት ውስጥ በሚከፈቱት ጥቅልሎች ውስጥ ያሉትን ሕጎች መታዘዝ ይጠበቅባቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ያየውን ነገር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ የመጽሐፍ ጥቅልሎችም ተከፈቱ። ሌላም ጥቅልል ተከፈተ፤ ይህም የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል ነው። ሙታን በጥቅልሎቹ ውስጥ በተጻፉት ነገሮች መሠረት እንደየሥራቸው ፍርድ ተሰጣቸው።”—ራእይ 20:12, 13
18 ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች “እንደየሥራቸው” ፍርድ ይሰጣቸዋል ሲባል ምን ማለት ነው? የሚፈረድባቸው ከመሞታቸው በፊት በሠሩት ሥራ መሠረት ነው? አይደለም! ሲሞቱ ኃጢአታቸው እንደተሰረዘላቸው አስታውሱ። ከዚህ አንጻር “እንደየሥራቸው” የሚለው ቃል ከመሞታቸው በፊት የሠሩትን ሥራ የሚያመለክት ሊሆን አይችልም። ከዚህ ይልቅ በአዲሱ ሥርዓት ሥልጠና ካገኙ በኋላ የሚሠሩትን ሥራ የሚያመለክት መሆን አለበት። እንደ ኖኅ፣ ሳሙኤል፣ ዳዊትና ዳንኤል ያሉ ታማኝ ሰዎች እንኳ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መማርና በእሱ መሥዋዕት ማመን ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች እንኳ ይህን ሁሉ ነገር መማር የሚጠበቅባቸው ከሆነ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎችማ ብዙ ትምህርት እንደሚያስፈልጋቸው ምንም ጥያቄ የለውም!
19. ይህን ግሩም አጋጣሚ የማይቀበሉ ሰዎች ምን ይጠብቃቸዋል?
19 ይህን ግሩም አጋጣሚ የማይቀበሉ ሰዎች ምን ይጠብቃቸዋል? ራእይ 20:15 “በሕይወት መጽሐፍ ላይ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳቱ ሐይቅ ተወረወረ” ይላል። አዎ፣ ዘላለማዊ ጥፋት ይደርስባቸዋል። እንግዲያው ስማችን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ እንዲሰፍርና ሳይሰረዝ እንዲቆይ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
20. በሺው ዓመት ግዛት ወቅት የትኛው አስደናቂ ሥራ ይካሄዳል? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)
20 የሺው ዓመት ግዛት ምንኛ አስደናቂ ጊዜ ይሆናል! በዚያ ወቅት በምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ መጠነ ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር ይዘረጋል። በተጨማሪም ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ሥራቸው የሚገመገምበት ጊዜ ይሆናል። (ኢሳ. 26:9፤ ሥራ 17:31) ይህ የትምህርት መርሐ ግብር የሚካሄደው እንዴት ነው? ቀጣዩ ርዕስ ስለዚህ ግሩም ዝግጅት እንድናውቅና አድናቆታችንን እንድናሳድግ ይረዳናል።
መዝሙር 147 የዘላለም ሕይወት ተስፋ ተሰጥቶናል
^ ይህ ርዕስ ኢየሱስ በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ ስለ “ሕይወት ትንሣኤ” እና ስለ “ፍርድ ትንሣኤ” የተናገረውን ሐሳብ በምንረዳበት መንገድ ላይ የተደረገውን ማስተካከያ ያብራራል። እነዚህ ሁለት ትንሣኤዎች ምን እንደሚያመለክቱ እንዲሁም በእያንዳንዱ ትንሣኤ ውስጥ የሚካተቱት እነማን እንደሆኑ እንመለከታለን።
^ ይህ መጽሐፍ መጻፍ የጀመረው “ዓለም ከተመሠረተበት” ማለትም ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ተጠቃሚ የሚሆኑ ሰዎች ከኖሩበት ጊዜ አንስቶ ነው። (ማቴ. 25:34፤ ራእይ 17:8) በመሆኑም በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ስሙ የተጻፈው የመጀመሪያ ሰው ጻድቁ አቤል መሆን አለበት።
^ ከዚህ ቀደም፣ እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው “ፍርድ” የሚለው ቃል እነዚህ ሰዎች እንደሚፈረድባቸው ወይም አሉታዊ ፍርድ እንደሚሰጣቸው እንደሚያመለክት ገልጸን ነበር። እርግጥ “ፍርድ” የሚለው ቃል ይህን ትርጉም ሊያስተላልፍ ይችላል። ሆኖም በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ “ፍርድ” የሚለውን ቃል ጠቅለል ባለ መልኩ ማለትም የግምገማ ወይም የፈተና ሂደትን ለማመልከት የተጠቀመበት ይመስላል፤ አንድ የግሪክኛ መዝገበ ቃላት፣ ይህ ቃል ‘የአንድን ሰው ምግባር መፈተንን’ ሊያመለክት እንደሚችል ይገልጻል።