የጥናት ርዕስ 38
እምነት የሚጣልባችሁ መሆናችሁን አስመሥክሩ
“እምነት የሚጣልበት ሰው . . . ሚስጥር ይጠብቃል።”—ምሳሌ 11:13
መዝሙር 101 በአንድነት አብሮ መሥራት
ማስተዋወቂያ *
1. እምነት የሚጣልበት ሰው ምን ዓይነት ሰው ነው?
እምነት የሚጣልበት ሰው የገባውን ቃል ለመጠበቅ ጥረት ያደርጋል፤ እንዲሁም እውነቱን ይናገራል። (መዝ. 15:4) ሰዎች ይተማመኑበታል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስለ እኛ እንደዚያ እንዲሰማቸው እንፈልጋለን። ታዲያ የእነሱን አመኔታ ለማትረፍ ምን ይረዳናል?
2. እምነት የሚጣልብን መሆናችንን ማስመሥከር የምንችለው እንዴት ነው?
2 ሌሎች እንዲያምኑን ማስገደድ አንችልም። እንዲያምኑን ከፈለግን አመኔታቸውን ማትረፍ ይኖርብናል። አመኔታ እንደ ገንዘብ ነው ሲባል እንሰማለን። ማትረፍ ከባድ ነው፤ ማጣት ግን ቀላል ነው። ይሖዋ የሕዝቦቹን አመኔታ አትርፏል። መቼም ቢሆን በእሱ ላይ ያለንን እምነት የምናጣበት ምክንያት የለም። ምክንያቱም “[ሥራው] ሁሉ እምነት የሚጣልበት ነው።” (መዝ. 33:4) እኛም እሱን እንድንመስለው ይጠብቅብናል። (ኤፌ. 5:1) የሰማዩን አባታቸውን በመምሰል እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ያስመሠከሩ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮችን ምሳሌ እንመልከት። እምነት የሚጣልብን ሰዎች ለመሆን የሚረዱንን አምስት ባሕርያትም እንመለከታለን።
እምነት ከሚጣልባቸው የይሖዋ አገልጋዮች ተማሩ
3-4. ነቢዩ ዳንኤል እምነት የሚጣልበት መሆኑን ያስመሠከረው እንዴት ነው? ይህስ ራሳችንን ምን ብለን እንድንጠይቅ ያነሳሳናል?
3 ነቢዩ ዳንኤል እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ባቢሎናውያን በግዞት ቢወስዱትም ብዙም ሳይቆይ እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆን ረገድ ጥሩ ስም አተረፈ። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ያያቸውን ሕልሞች በይሖዋ እርዳታ በፈታበት ወቅት ደግሞ የሌሎችን አመኔታ ይበልጥ አተረፈ። በአንድ ወቅት ዳንኤል ለንጉሡ ይሖዋ እንዳዘነበት መናገር አስፈልጎት ነበር፤ የትኛውም ንጉሥ እንዲህ ያለ መልእክት መስማት እንደማይፈልግ የታወቀ ነው። በተለይ ናቡከደነጾር ቁጡ ሰው ስለነበር ዳንኤል ይህን መልእክት ለመናገር ድፍረት ጠይቆበታል። (ዳን. 2:12፤ 4:20-22, 25) ከበርካታ ዓመታት በኋላ ዳንኤል በባቢሎን በቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ የታየውን ሚስጥራዊ መልእክት በትክክል በፈታበት ወቅት እምነት የሚጣልበት መሆኑን በድጋሚ አስመሠከረ። (ዳን. 5:5, 25-29) ከጊዜ በኋላም ሜዶናዊው ዳርዮስና ባለሥልጣናቱ፣ ዳንኤል “ልዩ የሆነ መንፈስ” እንዳለው አስተውለዋል። ዳንኤል ‘እምነት የሚጣልበት እንደሆነና ምንም ዓይነት እንከንና ጉድለት እንደሌለበት’ ተናግረዋል። (ዳን. 6:3, 4) በእርግጥም አረማዊ መሪዎችም እንኳ ይህ የይሖዋ አገልጋይ እምነት የሚጣልበት መሆኑን አስተውለዋል።
4 የዳንኤልን ምሳሌ በአእምሯችን ይዘን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ ምን ዓይነት ስም አትርፌያለሁ? የምታወቀው ኃላፊነቱን በሚገባ የሚወጣና እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆኔ ነው?’ ስለ እነዚህ ጥያቄዎች ማሰብ ያለብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም እምነት የሚጣልብን ሰዎች ከሆንን ለይሖዋ ውዳሴ እናመጣለን።
5. ሃናንያህ እምነት የሚጣልበት ሰው ለመሆን የረዳው ምንድን ነው?
5 በ455 ዓ.ዓ. ገዢው ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ ከገነባ በኋላ ከተማዋን በሚገባ የሚንከባከቡ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎችን ማግኘት ፈልጎ ነበር። ነህምያ ከመረጣቸው ሰዎች መካከል የምሽጉ አለቃ የሆነው ሃናንያህ ይገኝበታል። መጽሐፍ ቅዱስ ሃናንያህ “እምነት የሚጣልበትና ከሌሎቹ ሁሉ ይበልጥ እውነተኛውን አምላክ የሚፈራ ሰው” እንደሆነ ይገልጻል። (ነህ. 7:2) ሃናንያህ ለይሖዋ ፍቅር የነበረው ከመሆኑም ሌላ እሱን ማሳዘን ያስፈራው ነበር፤ ይህም የተሰጠውን ማንኛውንም ኃላፊነት በቁም ነገር እንዲመለከት አነሳስቶታል። እኛም እነዚህን ባሕርያት ማዳበራችን ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት እምነት የሚጣልብን እንድንሆን ይረዳናል።
6. ቲኪቆስ ለሐዋርያው ጳውሎስ እምነት የሚጣልበት ወዳጅ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
6 እምነት የሚጣልበት የጳውሎስ ወዳጅ የሆነውን ቲኪቆስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጳውሎስ በቁም እስር ላይ በነበረበት ወቅት በቲኪቆስ ላይ ይተማመን ነበር፤ “ታማኝ አገልጋይ” በማለት ጠርቶታል። (ኤፌ. 6:21, 22) ጳውሎስ በኤፌሶንና በቆላስይስ ላሉ ወንድሞች ደብዳቤ እንዲያደርስ ብቻ ሳይሆን እነሱን እንዲያበረታታና እንዲያጽናናም አደራ ጥሎበታል። ቲኪቆስ በዛሬው ጊዜ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ተግተው የሚሠሩትን ታማኝና እምነት የሚጣልባቸው ወንድሞች ያስታውሰናል።—ቆላ. 4:7-9
7. እምነት የሚጣልባችሁ ሰዎች መሆንን በተመለከተ በጉባኤያችሁ ካሉት ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ምን ትማራላችሁ?
7 በዛሬው ጊዜም እምነት የሚጣልባቸው ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ስላሉን በጣም አመስጋኞች ነን። እነዚህ ወንድሞች እንደ ዳንኤል፣ ሃናንያህና ቲኪቆስ ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር ይመለከቱታል። ለምሳሌ በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ስንገኝ ሁሉም ክፍሎች መመደባቸውን አንጠራጠርም። ክፍል የተሰጣቸው አስፋፊዎችም እምነት የሚጣልባቸው በመሆን ክፍላቸውን ተዘጋጅተው ሲያቀርቡ ሽማግሌዎች በጣም ይደሰታሉ። እስቲ አስቡት! ወንድሞች የሕዝብ ተናጋሪ መጋበዝ ረስተው ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ጥናቶቻችንን በጉባኤ ላይ እንዲገኙ ከመጋበዝ ወደኋላ እንደማንል የታወቀ ነው። በተጨማሪም ለአገልግሎት የሚያስፈልጉንን ጽሑፎች እንደምናገኝ እንተማመናለን። እነዚህ ታማኝ ወንድሞች በደንብ ይንከባከቡናል። እነሱን ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን! ይሁንና እምነት የሚጣልብን መሆናችንን ማስመሥከር የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
ሚስጥር በመጠበቅ እምነት የሚጣልባችሁ ሁኑ
8. ለሌሎች ትኩረት መስጠት ቢኖርብንም በዚህ ረገድ ሚዛናዊ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 11:13)
8 ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንወዳቸዋለን፤ ያሉበት ሁኔታም ያሳስበናል። ሆኖም ሚዛናዊ መሆንና በግል ጉዳያቸው ላለመግባት መጠንቀቅ ይኖርብናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንዶች “ማውራት ስለማይገባቸው ነገሮች እያወሩ ሐሜተኞችና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ” ነበሩ። (1 ጢሞ. 5:13) እንደ እነሱ መሆን እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ይሁንና አንድ ሰው ሌሎች እንዲያውቁት የማይፈልገውን የግል ጉዳዩን ነገረን እንበል። ለምሳሌ አንዲት እህት ስላጋጠማት የጤና እክል ወይም ስለደረሰባት አንድ ፈተና ከነገረችን በኋላ ጉዳዩን በሚስጥር እንድንይዘው ትጠይቀን ይሆናል። በዚህ ጊዜ ሚስጥሯን ልንጠብቅላት ይገባል። * (ምሳሌ 11:13ን አንብብ።) አሁን ደግሞ ሚስጥር መጠበቅን የሚጠይቁ ሌሎች ሁኔታዎችን እስቲ እንመልከት።
9. የቤተሰብ አባላት እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ማስመሥከር የሚችሉት እንዴት ነው?
9 በቤተሰብ ውስጥ። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አንዳንድ የቤተሰብ ጉዳዮችን በሚስጥር የመያዝ ኃላፊነት አለበት። ለምሳሌ አንዲት ክርስቲያን ሚስት እንግዳ ልማድ ይኖራት ይሆናል። ባሏ ስለዚህ ጉዳይ ለሌሎች በመናገር ያሳፍራታል? በፍጹም እንደዚህ አያደርግም! ሚስቱን ይወዳታል፤ እሷን የሚጎዳ ምንም ነገር ማድረግ አይፈልግም። (ኤፌ. 5:33) በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች በአክብሮት መያዝ ይፈልጋሉ። ወላጆች ይህን መገንዘባቸው ጠቃሚ ነው። ልጆቻቸው የሠሯቸውን ስህተቶች ለሌሎች በመናገር ሊያሳፍሯቸው አይገባም። (ቆላ. 3:21) ልጆችም ሚስጥር ጠባቂነትን መማር አለባቸው፤ የቤተሰባቸውን አባላት ሊያሳፍሩ የሚችሉ ጉዳዮችን ለሌሎች ሰዎች መናገር የለባቸውም። (ዘዳ. 5:16) እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የቤተሰቡን ሚስጥር ለመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ ከሆነ በቤተሰቡ መካከል ያለው ጥምረት ይጠናከራል።
10. እውነተኛ ወዳጅ መሆን ምን ይጨምራል? (ምሳሌ 17:17)
10 ከጓደኞቻችን ጋር። አብዛኞቻችን ስሜታችንን አውጥተን ለጓደኞቻችን መናገር የምንፈልግበት ጊዜ ይኖራል። አንዳንድ ጊዜ ግን እንዲህ ማድረግ ሊከብደን ይችላል። ስሜታችንን አውጥተን ለሌሎች መናገር አልለመድን ይሆናል። ጓደኛችን ሚስጥራችንን ለሌላ ሰው እንደተናገረብን ካወቅን ደግሞ በጣም እንደምናዝን ጥያቄ የለውም። በሌላ በኩል ግን ሚስጥር ጠባቂ የሆኑ ጓደኞች ካሉን በጣም አመስጋኝ እንሆናለን! እንዲህ ያሉ ሰዎች “እውነተኛ ወዳጅ” ናቸው።—ምሳሌ 17:17ን አንብብ።
11. (ሀ) ሽማግሌዎችና ሚስቶቻቸው እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) የጉባኤ ጉዳዮችን ለቤተሰቡ ካልተናገረው ሽማግሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሉን ተመልከት።)
11 በጉባኤ ውስጥ። ሚስጥር ጠባቂ በመሆናቸው የሚታወቁ ሽማግሌዎች ለወንድሞቻቸው “ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ” ናቸው። (ኢሳ. 32:2) እነዚህ ወንድሞች ሚስጥራችንን እንደሚጠብቁልን በመተማመን በነፃነት ልናነጋግራቸው እንችላለን። በሚስጥር ሊያዙ የሚገባቸውን ነገሮች እንዲነግሩን አንጎተጉታቸውም። በተጨማሪም የሽማግሌ ሚስቶች ከባሎቻቸው ሚስጥራዊ መረጃ ለማወጣጣት ስለማይሞክሩ በጣም እናደንቃቸዋለን። ደግሞም የሽማግሌ ሚስቶች ስለ ወንድሞቻቸውና ስለ እህቶቻቸው ሚስጥራዊ መረጃ አለመስማታቸው ይጠቅማቸዋል። የአንድ ሽማግሌ ሚስት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ እረኝነት ስለሚያደርግላቸው ወይም መንፈሳዊ እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው ወንድሞች ሚስጥራዊ መረጃ ስለማይነግረኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ ስማቸውን እንኳ የማይነግረኝ መሆኑ ጠቅሞኛል። ምንም ማድረግ ስለማልችልበት ጉዳይ አለመጨነቄ ሸክም ያቀልልኛል። በተጨማሪም ከሁሉም የጉባኤው አስፋፊዎች ጋር በነፃነት መቀራረብ እችላለሁ። እንዲሁም ለባለቤቴ ስለ ስሜቴ ወይም ስለ ችግሬ ስነግረው ሚስጥሬን እንደሚጠብቅልኝ እርግጠኛ ነኝ።” ሁላችንም እምነት የሚጣልብን በመሆን ረገድ ጥሩ ስም ማትረፍ እንፈልጋለን። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚረዱን የትኞቹ ባሕርያት ናቸው? እስቲ አምስቱን እንመልከት።
እምነት የሚጣልባችሁ ለመሆን የሚረዷችሁን ባሕርያት አዳብሩ
12. የመተማመን መሠረቱ ፍቅር ነው የምንለው ለምንድን ነው? አብራራ።
12 የመተማመን መሠረቱ ፍቅር ነው። ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጡት ሁለት ትእዛዛት ይሖዋን መውደድና ባልንጀራችንን መውደድ እንደሆኑ ተናግሯል። (ማቴ. 22:37-39) ለይሖዋ ያለን ፍቅር እምነት የሚጣልበት በመሆን ረገድ የተወልንን ፍጹም ምሳሌ እንድንከተል ያነሳሳናል። ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር የግል ጉዳያቸውን በሚስጥር እንድንይዝ ይገፋፋናል። ሊጎዳቸው፣ ሊያሳፍራቸው ወይም ሊያሳዝናቸው የሚችል መረጃ ማውጣት አንፈልግም።—ዮሐ. 15:12
13. ትሕትና እምነት የሚጣልብን ለመሆን የሚረዳን እንዴት ነው?
13 ትሕትና እምነት የሚጣልብን ለመሆን ይረዳናል። ትሑት የሆነ ክርስቲያን አንድን መረጃ ለመናገር የመጀመሪያው ሰው በመሆን ሌሎችን ለማስደመም አይሞክርም። (ፊልጵ. 2:3) ወይም ደግሞ ለሌሎች መናገር የማይችለው መረጃ እንዳለው በመጠቆም በጣም ተፈላጊ ሰው መስሎ ለመታየት አይሞክርም። በተጨማሪም ትሕትና በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ውስጥ ማብራሪያ ስላልተሰጠባቸው ጉዳዮች ግምታዊ ሐሳብ ከማሰራጨት እንድንቆጠብ ያነሳሳናል።
14. ማስተዋል እምነት የሚጣልብን ለመሆን የሚረዳን እንዴት ነው?
14 ማስተዋል አንድ ክርስቲያን ‘መቼ ዝም ማለት፣ መቼ ደግሞ መናገር’ እንዳለበት ለይቶ እንዲያውቅ ይረዳዋል። (መክ. 3:7) “ዝምታ ወርቅ ነው፤ መናገር ብር ነው” ሲባል እንሰማለን። ይህም ሲባል ከመናገር ይልቅ ዝም ማለት የሚሻልበት ጊዜ አለ ማለት ነው። ምሳሌ 11:12 “ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰው . . . ዝም ይላል” የሚለው ለዚህ ነው። አንድ ምሳሌ እንመልከት። ተሞክሮ ያለው አንድ ሽማግሌ፣ ሌሎች ጉባኤዎች ውስብስብ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው እንዲረዳ ብዙ ጊዜ ይጠየቃል። አብሮት የሚያገለግል አንድ ሽማግሌ ስለዚህ ወንድም ሲናገር “ስለ ሌሎች ጉባኤዎች ሚስጥራዊ መረጃ ላለማውጣት ሁሌም ይጠነቀቃል” ብሏል። ይህ ወንድም አስተዋይ መሆኑ በጉባኤው ውስጥ አብረውት የሚያገለግሉትን ሽማግሌዎች አክብሮት እንዲያተርፍ ረድቶታል። እነዚህ ወንድሞች የእነሱን ሚስጥራዊ መረጃ ለሌሎች እንደማይናገርባቸው እርግጠኞች ናቸው።
15. ሐቀኛ መሆን የሌሎችን አመኔታ ለማትረፍ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
15 እምነት የሚጣልብን ለመሆን የሚረዳን ሌላው ባሕርይ ሐቀኝነት ነው። ሐቀኛ ሰው ሁልጊዜ እውነቱን እንደሚናገር ስለምናውቅ እናምነዋለን። (ኤፌ. 4:25፤ ዕብ. 13:18) ለምሳሌ የማስተማር ችሎታችሁን ለማሻሻል ፈልጋችኋል እንበል። ስለዚህ አንድ ሰው ክፍል ስታቀርቡ አዳምጦ በየትኞቹ አቅጣጫዎች ማሻሻል እንደሚያስፈልጋችሁ ሐሳብ እንዲሰጣችሁ ትጠይቃላችሁ። በሐቀኝነት ምክር እንደሚሰጣችሁ የምትተማመኑት በምን ዓይነት ሰው ነው? መስማት የምትፈልጉትን ነገር በሚነግራችሁ ሰው ነው ወይስ በደግነት እውነቱን በሚነግራችሁ ሰው? መልሱ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከተሰወረ ፍቅር ይልቅ የተገለጠ ወቀሳ ይሻላል። የወዳጅ ማቁሰል ከታማኝነት የሚመነጭ ነው” ይላል። (ምሳሌ 27:5, 6) አንድ ጓደኛችን በሐቀኝነት የሚሰጠን ሐሳብ መጀመሪያ ላይ ቅር ቢያሰኘንም እንኳ ለወደፊቱ ይጠቅመናል።
16. ምሳሌ 10:19 ራስን የመግዛትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው?
16 የሌሎችን አመኔታ ማትረፍ ከፈለግን ራስን መግዛት የግድ ያስፈልገናል። በሚስጥር የተነገረንን ነገር ለማውራት ስንፈተን ይህ ባሕርይ አንደበታችንን ለመቆጣጠር ይረዳናል። (ምሳሌ 10:19ን አንብብ።) ማኅበራዊ ሚዲያ በምንጠቀምበት ጊዜ ራስን የመግዛት ባሕርያችን ሊፈተን ይችላል። ካልተጠነቀቅን ሳናስበው ሚስጥራዊ የሆኑ መረጃዎችን ለብዙ ሰዎች ልናሰራጭ እንችላለን። አንድን መረጃ ኢንተርኔት ላይ ካወጣነው በኋላ መረጃው በምን መልኩ ጥቅም ላይ እንደሚውል ወይም ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ መቆጣጠር አንችልም። ከዚህም ሌላ ራስን መግዛት ተቃዋሚዎች ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን አደጋ ላይ የሚጥል መረጃ ለማወጣጣት በሚሞክሩበት ወቅት ዝም እንድንል ይረዳናል። በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ገደብ በተጣለባቸው አገሮች ውስጥ ፖሊሶች ምርመራ ሲያደርጉብን እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። በእነዚህም ሆነ በሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‘አፋችንን ለመጠበቅ ልጓም ማስገባት’ ይኖርብናል። (መዝ. 39:1) ከቤተሰቦቻችን፣ ከጓደኞቻችን፣ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ሰው ጋር ባለን ግንኙነት እምነት የሚጣልብን መሆን ይኖርብናል። እምነት የሚጣልብን ለመሆን ደግሞ ራሳችንን መግዛት ያስፈልገናል።
17. በጉባኤያችን ውስጥ የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?
17 ይሖዋ አፍቃሪና እምነት የሚጣልባቸውን ሰዎች ወዳቀፈው የወንድማማች ማኅበር ስለሳበን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ሁላችንም የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን አመኔታ የማትረፍ ኃላፊነት አለብን። እያንዳንዳችን ፍቅር፣ ትሕትና፣ ማስተዋል፣ ሐቀኝነትና ራስን መግዛት ለማንጸባረቅ ጥረት ስናደርግ በጉባኤው ውስጥ የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን። የሌሎችን አመኔታ ማትረፍ ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው። እንግዲያው አምላካችንን ይሖዋን በመምሰል እምነት የሚጣልብን ሰዎች እንደሆንን ማስመሥከራችንን እንቀጥል።
መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት
^ ሌሎች እንዲያምኑን ከፈለግን እምነት የሚጣልብን መሆናችንን ማስመሥከር ይኖርብናል። መተማመን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንዲሁም እምነት የሚጣልብን ሰዎች ለመሆን የሚረዱን ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።
^ በጉባኤው ውስጥ ያለ አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ካወቅን የሽማግሌዎችን እርዳታ እንዲጠይቅ ልናሳስበው ይገባል። እንዲህ ካላደረገ ግን ለይሖዋና ለክርስቲያን ጉባኤው ያለን ታማኝነት ጉዳዩን ለመንፈሳዊ እረኞች እንድንናገር ያነሳሳናል።
^ የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ሽማግሌ የተሳተፈበትን ሚስጥራዊ የጉባኤ ጉዳይ ለቤተሰቡ አይናገርም።