የጥናት ርዕስ 37
ወንድሞቻችሁን ማመን ትችላላችሁ
“ፍቅር . . . ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል።”—1 ቆሮ. 13:4, 7
መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን
ማስተዋወቂያ *
1. በዚህ ዓለም ውስጥ መተማመን የሌለ መሆኑ የማያስገርመን ለምንድን ነው?
በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ማንን ማመን እንደሚችሉ ግራ ይገባቸዋል። በንግዱ ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች በሚያደርጉት ነገር ብዙ ጊዜ ቅር ይሰኛሉ። እንዲያውም ብዙዎች ጓደኞቻቸውን፣ ጎረቤቶቻቸውን አልፎ ተርፎም የቤተሰባቸውን አባላት ማመን እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። እርግጥ ይህ መሆኑ አያስገርመንም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በመጨረሻዎቹ ቀናት ሰዎች ታማኝ ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎችና ከዳተኞች’ እንደሚሆኑ ይናገራል። በሌላ አባባል፣ ሰዎች የዚህ ዓለም አምላክ የሆነውን የሰይጣንን ባሕርይ ያንጸባርቃሉ፤ ሰይጣን ደግሞ ጨርሶ እምነት የሚጣልበት አይደለም።—2 ጢሞ. 3:1-4፤ 2 ቆሮ. 4:4
2. (ሀ) ሙሉ በሙሉ መተማመን የምንችለው በማን ነው? (ለ) አንዳንዶች ምን ብለው ያስቡ ይሆናል?
2 እኛ ክርስቲያኖች ግን በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመን እንደምንችል እናውቃለን። (ኤር. 17:7, 8) እሱ እንደሚወደንና ወዳጆቹን ‘ፈጽሞ እንደማይተዋቸው’ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 9:10) ክርስቶስ ኢየሱስንም ማመን እንችላለን፤ ምክንያቱም ለእኛ ሲል ሕይወቱን ሰጥቷል። (1 ጴጥ. 3:18) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መመሪያ እንደያዘ በሕይወታችን ተመልክተናል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) በይሖዋ፣ በኢየሱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል እንደምንችል እርግጠኞች ነን። ይሁንና አንዳንዶች ‘በእርግጥ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ሁልጊዜ ማመን እንችላለን?’ ብለው ያስቡ ይሆናል። የዚህ ጥያቄ መልስ ‘አዎ’ ከሆነ፣ ወንድሞቻችንን ልናምናቸው የምንችለው ለምንድን ነው?
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያስፈልጉናል
3. ምን አስደናቂ መብት አግኝተናል? (ማርቆስ 10:29, 30)
3 ይሖዋ አገልጋዮቹን ያቀፈው ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ አባል እንድንሆን መርጦናል። ይህ ልዩ መብት ነው፤ ብዙ በረከቶችንም ያስገኛል! (ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ።) በዓለም ዙሪያ እንደ እኛ ይሖዋን የሚወዱና በእሱ መሥፈርቶች ለመመራት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉ ወንድሞችና እህቶች አሉን። ቋንቋችን፣ ባሕላችንና አለባበሳችን የተለያየ ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ ስናገኛቸው እንኳ በደንብ እንደምናውቃቸው ይሰማናል። በተለይ አብረናቸው ሆነን የሚወደንን ሰማያዊ አባታችንን ስናወድስና ስናመልክ በጣም ደስ ይለናል።—መዝ. 133:1
4. ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው?
4 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያለንን አንድነት መጠበቅ ያስፈልገናል። አንዳንድ ጊዜ ወንድሞቻችን ሸክማችንን ለመሸከም ያግዙናል። (ሮም 15:1፤ ገላ. 6:2) በተጨማሪም ይሖዋን በቅንዓት ማገልገላችንን እንድንቀጥልና በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድንሆን ያበረታቱናል። (1 ተሰ. 5:11፤ ዕብ. 10:23-25) የጋራ ጠላቶቻችን የሆኑትን ሰይጣን ዲያብሎስንና በሥሩ ያለውን ክፉ ዓለም ለመቋቋም የጉባኤው ጥበቃ ባይኖረን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር! ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎች በቅርቡ በአምላክ አገልጋዮች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። በዚያ ወቅት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከጎናችን በመኖራቸው በጣም አመስጋኞች እንደምንሆን ምንም ጥያቄ የለውም።
5. አንዳንዶች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ማመን የሚከብዳቸው ለምን ሊሆን ይችላል?
5 ይሁንና አንዳንዶች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ማመን ይከብዳቸዋል። ምናልባትም እንዲህ የሚሰማቸው አንድ የእምነት ባልንጀራቸው ሚስጥራቸውን ስላወጣባቸው ወይም የገባውን ቃል ሳይጠብቅ ስለቀረ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ አንድ ክርስቲያን የተናገረው ወይም ያደረገው ነገር በጥልቅ ጎድቷቸው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለ ነገር ያጋጠማቸው ክርስቲያኖች ሌሎችን ማመን ሊከብዳቸው ይችላል። ታዲያ በእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ እምነት ለመገንባት ምን ሊረዳን ይችላል?
ፍቅር በሌሎች ላይ እምነት ለመገንባት ይረዳናል
6. ፍቅር በሌሎች ላይ እምነት ለመገንባት የሚረዳን እንዴት ነው? (1 ቆሮንቶስ 13:4-8)
6 መተማመን የሚመሠረተው በፍቅር ላይ ነው። አንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 በሌሎች ላይ እምነት ለመገንባት ወይም እምነታችንን ለማደስ የሚረዱ የተለያዩ የፍቅር ገጽታዎችን ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 13:4-8ን አንብብ።) ለምሳሌ ቁጥር 4 “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው” ይላል። ይሖዋ በእሱ ላይ ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜም ጭምር በትዕግሥት ይይዘናል። ታዲያ እኛስ ወንድሞቻችን የሚያበሳጭ ወይም የሚጎዳ ነገር ሲናገሩ ወይም ሲያደርጉብን በትዕግሥት ልንይዛቸው አይገባም? ቁጥር 5 “[ፍቅር] በቀላሉ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም” ይላል። እኛም “የበደል መዝገብ” መያዝ፣ ማለትም ወንድሞቻችን የፈጸሙብንን በደል ሁልጊዜ እያስታወስን መኖር የለብንም። መክብብ 7:9 ‘ለቁጣ መቸኮል’ እንደሌለብን ይናገራል። ከዚህ ይልቅ “ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ” የሚለውን በኤፌሶን 4:26 ላይ የሚገኘውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጋችን ምንኛ የተሻለ ነው!
7. በማቴዎስ 7:1-5 ላይ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች እምነት ለመገንባት የሚረዱን እንዴት ነው?
7 በሌሎች ላይ እምነት ለመገንባት የሚረዳን ሌላው ነገር ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን የይሖዋን ዓይነት አመለካከት ማዳበር ነው። አምላክ ይወዳቸዋል፤ እንዲሁም ኃጢአታቸውን አይከታተልም። እኛም በዚህ ረገድ አምላክን መምሰል ይኖርብናል። (መዝ. 130:3) በድክመታቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ መልካም ጎናቸውንና እምቅ አቅማቸውን ለማስተዋል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ማቴዎስ 7:1-5ን አንብብ።) አንድ ነገር ለማድረግ የሚያነሳሳቸውን ውስጣዊ ግፊት አንጠራጠርም፤ ምክንያቱም ፍቅር “ሁሉን ያምናል።” (1 ቆሮ. 13:7) እርግጥ እንዲህ ሲባል ይሖዋ ሌሎችን በጭፍን እንድናምን ይጠብቅብናል ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሌሎች እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ካስመሠከሩ እንድናምናቸው ይጠብቅብናል። *
8. በወንድሞቻችሁ ላይ እምነት መገንባት የምትችሉት እንዴት ነው?
8 በወንድሞቻችን ላይ እምነት መጣል ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው። ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እነሱን በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስትገናኙ ከእነሱ ጋር ተነጋገሩ። አብራችኋቸው አገልግሉ። በትዕግሥት ያዟቸው፤ እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ ስጧቸው። እርግጥ ነው፣ በቅርቡ ለተዋወቃችሁት አንድ ክርስቲያን ሁሉንም የግል ጉዳዮቻችሁን አትነግሩት ይሆናል። ቅርበታችሁ እየጨመረ ሲሄድ ግን ስሜታችሁን አውጥታችሁ መናገር ይበልጥ ቀላል ሊሆንላችሁ ይችላል። (ሉቃስ 16:10) ይሁንና አንድ ወንድም የእናንተን አመኔታ ቢያጓድልስ? በእሱ ላይ ተስፋ ለመቁረጥ አትቸኩሉ። ከዚህ ይልቅ ለጉዳዩ ጊዜ ስጡት። በተጨማሪም የጥቂቶች ምግባር በወንድሞቻችሁ ላይ ያላችሁን እምነት እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ። በዚህ ረገድ የአንዳንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችን ምሳሌ እንመለከታለን። እነዚህ ሰዎች፣ አንዳንዶች እምነት ቢያጓድሉባቸውም ሌሎችን ማመናቸውን ቀጥለዋል።
ሌሎችን ማመናቸውን ከቀጠሉ ሰዎች ተማሩ
9. (ሀ) አንዳንድ የአምላክ ወኪሎች ስህተት ቢሠሩም እንኳ ሐና በይሖዋ ዝግጅት ላይ እምነት መጣሏን የቀጠለችው እንዴት ነው? (ለ) በይሖዋ ዝግጅት ላይ እምነት መጣልን በተመለከተ ከሐና ታሪክ ምን ትምህርት አግኝተሃል? (ሥዕሉን ተመልከት።)
9 ኃላፊነት ያለው አንድ ወንድም ባደረገው ነገር የተነሳ ቅር ተሰኝታችሁ ታውቃላችሁ? ከሆነ የሐናን ምሳሌ መመርመራችሁ ይጠቅማችኋል። በወቅቱ እስራኤል ውስጥ በይሖዋ አምልኮ ግንባር ቀደም ቦታ የነበረው ሊቀ ካህናቱ ኤሊ ነበር። ሆኖም ኤሊ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ቤተሰብ አልነበረውም። በኃላፊነት ቦታ ላይ ያገለግሉ የነበሩት ልጆቹ አሳፋሪ የሆነ የሥነ ምግባር ብልግና አዘውትረው ይፈጽሙ ነበር። አባታቸውም እነሱን ለማረም ተገቢውን እርምጃ አልወሰደም። ይሖዋ ኤሊን ወዲያውኑ ከኃላፊነት ቦታው አላነሳውም። ያም ቢሆን ሐና ‘ኤሊ ሊቀ ካህናት ሆኖ እስካገለገለ ድረስ ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ሄጄ አምልኮ አላቀርብም’ በማለት ለአምላክ ዝግጅት ጀርባዋን አልሰጠችም። ኤሊ፣ ሐና በከፍተኛ ጭንቀት ተውጣ ስትጸልይ ሲመለከት እንደሰከረች በማሰብ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደረሰ። እውነታውን ለማጣራት ከመሞከር ይልቅ በሐዘን የተዋጠችውን ይህችን ሴት ተቆጣት። (1 ሳሙ. 1:12-16) ሆኖም ሐና ወንድ ልጅ ከተሰጣት ልጇ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ እንዲያገለግል እንደምታመጣው ተስላ ነበር፤ ልጇ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ የሚያገለግለው በኤሊ ሥልጣን ሥር ቢሆንም እንኳ ስዕለቷን ከመፈጸም ወደኋላ አላለችም። (1 ሳሙ. 1:11) የኤሊ ልጆች የሚፈጽሙት ምግባር መታረም ይገባው ነበር? ምንም ጥያቄ የለውም! ደግሞም ይሖዋ ከጊዜ በኋላ እርምጃ ወስዷል። (1 ሳሙ. 4:17) እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ ለሐና ወንድ ልጅ ማለትም ሳሙኤልን በመስጠት ባርኳታል።—1 ሳሙ. 1:17-20
10. ንጉሥ ዳዊት ክህደት ቢደርስበትም እንኳ ሌሎችን ማመኑን የቀጠለው እንዴት ነው?
10 የቅርብ ጓደኛችሁ እንደከዳችሁ ተሰምቷችሁ ያውቃል? ከሆነ፣ የንጉሥ ዳዊትን ምሳሌ አስቡ። ዳዊት፣ አኪጦፌል የሚባል ጓደኛ ነበረው። ሆኖም የዳዊት ልጅ አቢሴሎም ንግሥናውን ከዳዊት ለመንጠቅ በሞከረበት ወቅት አኪጦፌል ከአቢሴሎም ጋር በዓመፁ ተባበረ። ዳዊት በልጁና እንደ ጓደኛ ይቆጥረው በነበረው ሰው በአንድ ጊዜ ሲከዳ ምንኛ ተጎድቶ ይሆን! ሆኖም ዳዊት፣ የደረሰበት ክህደት በሌሎች ላይ ያለውን እምነት እንዲያሳጣው አልፈቀደም። በዓመፁ ለመተባበር ፈቃደኛ ያልሆነውን ሌላ ታማኝ ጓደኛውን ኩሲን ማመኑን ቀጥሏል። ዳዊት ኩሲን በማመኑ አልከሰረም። ኩሲ ጥሩ ጓደኛ መሆኑን አስመሥክሯል፤ ዳዊትን ለመርዳት ሲል ሕይወቱን እንኳ አደጋ ላይ ጥሏል።—2 ሳሙ. 17:1-16
11. የናባል አገልጋይ በአቢጋኤል እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው?
11 የናባል አገልጋይ የተወውን ምሳሌም እንመልከት። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በደግነት ተነሳስተው ናባል ለተባለ አንድ እስራኤላዊ አገልጋዮች ጥበቃ አድርገውላቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ዳዊት አብረውት ላሉት ሰዎች የቻለውን ያህል ምግብ እንዲሰጣቸው ባለጸጋውን ናባልን ጠየቀው። ናባል ይህን ምክንያታዊ ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ዳዊት በጣም ተበሳጭቶ በናባል ቤት ውስጥ ያሉትን ወንዶች በሙሉ ለመግደል ወሰነ። ከናባል አገልጋዮች አንዱ ሁኔታውን ለናባል ሚስት ለአቢጋኤል ነገራት። ይህ አገልጋይ በናባል ቤት ውስጥ ካሉት ወንዶች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ሕይወቱ መትረፉ የተመካው በአቢጋኤል ላይ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ከመሸሽ ይልቅ አቢጋኤል ለጉዳዩ መፍትሔ እንደምታገኝለት ተማምኗል። ይህ ሰው በአቢጋኤል ሊተማመንባት የቻለው አቢጋኤል አስተዋይ ሴት በመሆኗ ትታወቅ ስለነበረ ነው። ደግሞም ቀጥሎ የሆነው ነገር በእሷ መተማመኑ ተገቢ እንደነበር ያሳያል። አቢጋኤል ዳዊትን ለማስቆም ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ወሰደች። (1 ሳሙ. 25:2-35) ዳዊት ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ ተማምና ነበር።
12. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስህተት ቢሠሩም እንኳ እንደሚተማመንባቸው ያሳየው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስህተት ቢሠሩም እንኳ ይተማመንባቸው ነበር። (ዮሐ. 15:15, 16) ያዕቆብና ዮሐንስ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ልዩ ቦታ እንዲሰጣቸው ኢየሱስን በጠየቁበት ወቅት ኢየሱስ ይሖዋን የሚያገለግሉበትን ዓላማ አልተጠራጠረም፤ ወይም ከሐዋርያነት አልሻራቸውም። (ማር. 10:35-40) በኋላም ኢየሱስ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ምሽት ላይ ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ጥለውት ሸሽተዋል። (ማቴ. 26:56) ያም ቢሆን ኢየሱስ በእነሱ ላይ ያለውን እምነት አላጣም። ድክመቶቻቸውን በደንብ ያውቅ ነበር። ያም ቢሆን ‘እስከ መጨረሻው ወዷቸዋል።’ (ዮሐ. 13:1) እንዲያውም ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለ11 ታማኝ ሐዋርያቱ፣ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ የመምራትና ውድ በጎቹን የመንከባከብ ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ዮሐ. 21:15-17) ኢየሱስ በእነዚህ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች መተማመኑ ተገቢ መሆኑ ታይቷል። ሁሉም እስከ ሕይወታቸው ማብቂያ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል። በእርግጥም ሐና፣ ዳዊት፣ የናባል አገልጋይ፣ አቢጋኤልና ኢየሱስ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን በማመን ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትተውልናል።
በሌሎች ላይ ያለንን እምነት ማደስ
13. ሌሎችን እንዳናምን እንቅፋት የሚሆንብን ምን ሊሆን ይችላል?
13 ለአንድ ወንድም ሚስጥራችሁን ከነገራችሁት በኋላ ሚስጥራችሁን አውጥቶባችሁ ያውቃል? ይህ ሁኔታ በእጅጉ ስሜት ይጎዳል። በአንድ ወቅት አንዲት እህት ለአንድ የጉባኤ ሽማግሌ የግል ጉዳይዋን በሚስጥር ነገረችው። በቀጣዩ ቀን የሽማግሌው ሚስት እህትን ለማበረታታት ደወለችላት፤ በመሆኑም እህታችን ሽማግሌው ለሚስቱ ሚስጥሯን እንደነገረባት አወቀች። በዚህም የተነሳ እህታችን በሽማግሌው ላይ ያላት እምነት ተናጋ። ደስ የሚለው ግን እህት እርዳታ ጠየቀች። አንድን ሌላ ሽማግሌ ቀርባ አነጋገረችው። እሱም በሽማግሌዎች ላይ ያላትን እምነት እንድታድስ ረዳት።
14. አንድ ወንድም እምነቱን እንዲያድስ የረዳው ምንድን ነው?
14 አንድ ወንድም በሁለት የጉባኤ ሽማግሌዎች ላይ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ቅሬታ አድሮበት ነበር። እነዚህን ሽማግሌዎች ሊያምናቸው እንደማይችል ይሰማው ነበር። ሆኖም በጣም የሚያከብረው አንድ ወንድም ስለተናገረው ነገር ማሰብ ጀመረ። ይህ ወንድም “ጠላታችን ሰይጣን እንጂ ወንድሞቻችን አይደሉም” ብሎ ነበር። ወንድማችን ይህን ጉዳይ በጸሎት አሰበበት። ውሎ አድሮም ከሁለቱም ሽማግሌዎች ጋር ሰላም መፍጠር ችሏል።
15. እምነትን ማደስ ጊዜ ሊወስድ የሚችለው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።
15 የአገልግሎት መብታችሁን አጥታችሁ ታውቃላችሁ? ይህ ስሜት የሚጎዳ ነገር ነው። ግሬተ እና እናቷ በ1930ዎቹ በናዚ ጀርመን ሥራችን በታገደበት ወቅት ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ግሬተ የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን ለእምነት ባልንጀሮቿ የመገልበጥ መብት ነበራት። ሆኖም ወንድሞች የግሬተ አባት ተቃዋሚ መሆኑን ሲያውቁ የጉባኤውን መረጃ ለባለሥልጣናቱ ሊያጋልጥ ይችላል ብለው በመፍራት ይህን መብት ከግሬተ ወሰዱባት። የግሬተ ፈተና በዚህ አላበቃም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወንድሞች ለግሬተና ለእናቷ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎችን አይሰጧቸውም ነበር። መንገድ ላይ ሲያገኟቸውም ቢሆን አያነጋግሯቸውም። ይህ ስሜታቸውን በጥልቅ ጎድቶት ነበር። በመሆኑም ግሬተ እነዚህን ወንድሞች ይቅር ለማለትና በእነሱ ላይ መልሳ እምነት ለመጣል ረጅም ጊዜ እንደወሰደባት ተናግራለች። ውሎ አድሮ ግን ይሖዋ ይቅር እንዳላቸውና እሷም ይቅር ልትላቸው እንደሚገባ አምና ተቀበለች። *
“ጠላታችን ሰይጣን እንጂ ወንድሞቻችን አይደሉም”
16. ሌሎችን ለማመን እንቅፋት የሚሆኑብንን ነገሮች መወጣት ያለብን ለምንድን ነው?
16 እናንተም እንዲህ ያለ ስሜት የሚጎዳ ነገር አጋጥሟችሁ ከሆነ እምነታችሁን ለማደስ ጥረት አድርጉ። ይህን ማድረግ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ሆኖም የምታደርጉት ጥረት አያስቆጭም። ለምሳሌ ያህል፣ የምግብ መመረዝ አጋጥሞን የሚያውቅ ከሆነ በአመጋገባችን ረገድ ይበልጥ ጠንቃቃ መሆናችን አይቀርም። ሆኖም በአንድ ወቅት የበላነው ምግብ ስለተመረዘ ብቻ ምግብ መብላታችንን እንደማናቆም የታወቀ ነው። በተመሳሳይም በአንድ ወቅት ስሜት የሚጎዳ ነገር ስላጋጠመን ብቻ በሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ያለንን እምነት ማጣት የለብንም። ደግሞም ፍጹም የሆነ ሰው እንደሌለ እናውቃለን። በሌሎች ላይ ያለንን እምነት ስናድስ ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን፤ እንዲሁም በጉባኤያችን ውስጥ የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።
17. መተማመን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
17 በሰይጣን ዓለም ውስጥ መተማመን ጠፍቷል። ሆኖም በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን ውስጥ በፍቅር ላይ የተመሠረተ የመተማመን መንፈስ ሰፍኗል። እንዲህ ያለው የመተማመን መንፈስ በአሁኑ ወቅት ለደስታችንና ለአንድነታችን አስተዋጽኦ ያበረክታል። ወደፊት ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ጥበቃ ያስገኝልናል። ይሁንና ሌሎች ሰዎች እምነት በማጓደላቸው የተነሳ ስሜታችሁ ተጎድቶ ከሆነስ? ለሁኔታው የይሖዋን ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት አድርጉ፤ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ አውሉ፤ ለወንድሞቻችሁ ጥልቅ ፍቅር አዳብሩ፤ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ተማሩ። ከደረሰብን የስሜት ቁስል ማገገምና በሌሎች ላይ ያለንን እምነት ማደስ እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ‘ከወንድም ይበልጥ የሚቀርቡ’ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጓደኞች እናገኛለን። (ምሳሌ 18:24) ይሁንና መተማመን በአንድ ወገን ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። እምነት የሚጣልብን ሰዎች መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
መዝሙር 99 እልፍ አእላፋት ወንድሞች
^ ወንድሞቻችንን ማመን ይኖርብናል። እርግጥ ይህን ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ወንድሞቻችን እንደጠበቅነው ሳይሆኑ ይቀራሉ። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችንና በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ ማሰላሰላችን በእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ እምነት ለመገንባት ወይም አሳዝነውን ከሆነ በእነሱ ላይ ያለንን እምነት ለማደስ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
^ መጽሐፍ ቅዱስ በጉባኤው ውስጥ እምነት ሊጣልባቸው የማይገባ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃል። (ይሁዳ 4) አልፎ አልፎ ሐሰተኛ ወንድሞች “ጠማማ ነገር” በመናገር ሌሎችን ለማሳሳት ይሞክሩ ይሆናል። (ሥራ 20:30) እንዲህ ያሉ ሰዎችን ላለማመንና እነሱን ላለመስማት እንመርጣለን።
^ የግሬተን ተሞክሮ ለማንበብ የ1974 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 129-131ን ተመልከት።