የአንባቢያን ጥያቄዎች
በምድር ላይ ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ናቸው? የሚያገኙትስ ምን ዓይነት ትንሣኤ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንመልከት።
የሐዋርያት ሥራ 24:15 “ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ከሞት እንደሚነሱ” ይናገራል። “ጻድቃን” የተባሉት ከመሞታቸው በፊት አምላክን ይታዘዙ የነበሩ ሰዎች ናቸው፤ ስለዚህ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሯል። (ሚል. 3:16) “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ከተባሉት መካከል ስለ ይሖዋ ለመማር በቂ አጋጣሚ ሳያገኙ የሞቱ ሰዎች ይገኙበታል፤ ስለዚህ የእነዚህ ሰዎች ስም በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ አልሰፈረም።
ዮሐንስ 5:28, 29 በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ ስለተጠቀሱት ሁለት ቡድኖች ይናገራል። ኢየሱስ “መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ” እንደሚወጡ ተናግሯል። “ጻድቃን” የተባሉት ሰዎች ከመሞታቸው በፊት መልካም ሠርተዋል። የእነዚህ ሰዎች ስም አሁንም በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኝ ለሕይወት ትንሣኤ ይወጣሉ። ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች የተባሉት ግን ከመሞታቸው በፊት ክፉ ሠርተዋል። እነዚህ ሰዎች ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ። ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ገና አልሰፈረም። ስለዚህ የፍርድ ወይም የግምገማ ጊዜ ይጠብቃቸዋል። በዚያ ጊዜ ውስጥ ስለ ይሖዋ የሚማሩበትና ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የሚሰፍርበት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።
ራእይ 20:12, 13 ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች በሙሉ ‘በጥቅልሎቹ ውስጥ የተጻፉትን ነገሮች’ ማለትም በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖሩትን አዳዲስ ሕጎች ማክበር እንደሚጠበቅባቸው ይገልጻል። እነዚህን ሕጎች የማይታዘዙ ሰዎች ይጠፋሉ።—ኢሳ. 65:20
ዳንኤል 12:2 በሞት ካንቀላፉት መካከል “አንዳንዶቹ ለዘላለም ሕይወት፣ ሌሎቹ ደግሞ ለነቀፋና ለዘላለማዊ ውርደት” እንደሚነሱ ይገልጻል። ይህ ጥቅስ ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች የሚደርስባቸውን የመጨረሻ ዕጣ ይናገራል፤ ወይ ‘የዘላለም ሕይወት’ አሊያም “ዘላለማዊ ውርደት” ይጠብቃቸዋል። ስለዚህ በ1,000ው ዓመት መጨረሻ ላይ አንዳንዶች የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ዘላለማዊ ጥፋት ይደርስባቸዋል።—ራእይ 20:15፤ 21:3, 4
አንድ ምሳሌ እንመልከት። ትንሣኤ የሚያገኙት ሁለት ቡድኖች ሁኔታ በሌላ አገር ውስጥ መኖር ከሚፈልጉ የውጭ ዜጎች ሁኔታ ጋር ሊወዳደር ይችላል። “ጻድቃን” የተባሉት፣ የሥራ ቪዛ ወይም የመኖሪያ ፈቃድ ከሚሰጣቸው የውጭ ዜጎች ጋር ይመሳሰላሉ። እንዲህ ያለ ቪዛ የተሰጣቸው ሰዎች በተወሰነ መጠን እውቅናና ነፃነት ይኖራቸዋል። “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” የተባሉት ደግሞ ጊዜያዊ ወይም የቱሪስት ቪዛ ከሚሰጣቸው የውጭ ዜጎች ጋር ይመሳሰላሉ። እንዲህ ያለ ቪዛ የተሰጣቸው የውጭ ዜጎች በአዲሱ አገር ውስጥ መኖራቸውን እንዲቀጥሉ የሚፈቀድላቸው ብቁ መሆናቸውን ካስመሠከሩ በኋላ ነው። በተመሳሳይም ትንሣኤ የሚያገኙት ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች በገነት ውስጥ መኖራቸውን ለመቀጠል የይሖዋን ሕጎች መታዘዝና ጻድቃን መሆናቸውን ማስመሥከር ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም የውጭ ዜጎች ወደ ሌላ አገር ሲገቡ የሚሰጣቸው ቪዛ ምንም ይሁን ምን፣ አንዳንዶቹ ውሎ አድሮ ዜግነት ይሰጣቸዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ ከአገሪቱ ይባረራሉ። የመጨረሻው ውሳኔ የተመካው በአዲሱ አገር ውስጥ በሚያሳዩት ባሕርይና ምግባር ላይ ነው። በተመሳሳይም ትንሣኤ ያገኙት የሁሉም ሰዎች የመጨረሻ ዕጣ የሚመካው በአዲሱ ዓለም ውስጥ በሚያሳዩት ታማኝነትና ምግባር ላይ ነው።
ይሖዋ የፍቅር አምላክ ብቻ ሳይሆን የፍትሕም አምላክ ነው። (ዘዳ. 32:4፤ መዝ. 33:5) ጻድቃንንም ሆነ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት ፍቅሩን ያሳያል። ሆኖም ላቅ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹንም ያስከብራል። በአዲሱ ዓለም ውስጥ መኖራቸውን መቀጠል የሚፈቀድላቸው ለእሱ ፍቅር የሚያዳብሩና መሥፈርቶቹን የሚያከብሩ ሰዎች ብቻ ናቸው።