የጥናት ርዕስ 37
እንደ ሳምሶን በይሖዋ ታመኑ
“ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ አስበኝ፤ . . . ብርታት ስጠኝ።”—መሳ. 16:28
መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ
ማስተዋወቂያ a
1-2. የሳምሶንን ታሪክ ማጥናታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
ሳምሶን የሚለውን ስም ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አስደናቂ ጥንካሬ የነበረው ሰው መሆኑን ታስታውስ ይሆናል። ደግሞም እውነት ነው። ይሁንና ሳምሶን አስከፊ መዘዝ ያስከተለ መጥፎ ውሳኔም አድርጓል። ያም ቢሆን ይሖዋ ያተኮረው ሳምሶን በሕይወት ዘመኑ ባሳየው ታማኝነት ላይ ነው። ይህ ታሪክ ለእኛ ጥቅም ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተትልን አድርጓል።
2 ይሖዋ የተመረጡ ሕዝቦቹ የሆኑትን እስራኤላውያንን ለመርዳት ሲል አስደናቂ ነገሮችን እንዲፈጽም ሳምሶንን ተጠቅሞበታል። ሳምሶን ከሞተ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ሐዋርያው ጳውሎስን በመንፈሱ በመምራት የሳምሶንን ስም አስደናቂ እምነት ባሳዩ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲያካትት አድርጓል። (ዕብ. 11:32-34) የሳምሶን ምሳሌ ሊያበረታታን ይችላል። አስቸጋሪ ነገሮች ሲያጋጥሙትም ጭምር በይሖዋ ታምኗል። ከሳምሶን ታሪክ የምናገኘውን ማበረታቻና ጠቃሚ ትምህርት እስቲ እንመልከት።
ሳምሶን በይሖዋ ታምኗል
3. ሳምሶን ምን ኃላፊነት ተሰጥቶታል?
3 ሳምሶን በተወለደ ጊዜ እስራኤላውያን በፍልስጤማውያን ግዛት ሥር ነበሩ፤ እነሱም ይጨቁኗቸው ነበር። (መሳ. 13:1) ጭካኔ በተሞላበት አገዛዛቸው የተነሳ እስራኤላውያን ለከፍተኛ ሥቃይ ተዳርገዋል። ይሖዋ “እስራኤልን ከፍልስጤማውያን እጅ በማዳን ረገድ ግንባር ቀደም” እንዲሆን ሳምሶንን መረጠው። (መሳ. 13:5) እንዴት ያለ ከባድ ኃላፊነት ነው! ሳምሶን ይህን ተፈታታኝ ኃላፊነት ለመወጣት በይሖዋ መታመን ነበረበት።
4. ሳምሶን ራሱን ከፍልስጤማውያን እንዲያድን ይሖዋ የረዳው እንዴት ነው? (መሳፍንት 15:14-16)
4 ሳምሶን በይሖዋ እንደታመነና እሱም እንደረዳው የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በአንድ ወቅት የፍልስጤም ሠራዊት ሳምሶንን ለመያዝ ወደ ሊሃይ መጥቶ ነበር፤ ሊሃይ የምትገኘው ይሁዳ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። የይሁዳ ሰዎች ስለፈሩ ሳምሶንን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑ። የገዛ ወገኖቹ ሳምሶንን በሁለት አዳዲስ ገመዶች ጥፍር አድርገው አስረው ወደ ፍልስጤማውያን አመጡት። (መሳ. 15:9-13) ነገር ግን “የይሖዋ መንፈስ ኃይል ሰጠው”፤ ሳምሶንም ገመዶቹን በጣጠሳቸው። ከዚያም “በቅርቡ የሞተ የአንድ አህያ መንጋጋ አገኘ”፤ መንጋጋውንም አንስቶ በእሱ 1,000 ፍልስጤማውያንን ገደለ።—መሳፍንት 15:14-16ን አንብብ።
5. ሳምሶን የአህያ መንጋጋ መጠቀሙ በይሖዋ መታመኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?
5 ሳምሶን የአህያ መንጋጋ የተጠቀመው ለምንድን ነው? የአህያ መንጋጋ የጦር መሣሪያ አይደለም! ሳምሶን ድል ማግኘቱ የተመካው በይሖዋ ላይ እንጂ በሚጠቀምበት መሣሪያ ላይ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። ይህ ታማኝ ሰው ቅርቡ ያገኘውን መሣሪያ በመጠቀም የይሖዋን ፈቃድ ፈጽሟል። ሳምሶን በይሖዋ በመታመኑ ስኬታማ ሆኗል።
6. ከቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶቻችን ጋር በተያያዘ ከሳምሶን ምን እንማራለን?
6 ይሖዋ ለእኛም ከባድ ኃላፊነቶችን ጨምሮ ማንኛውንም ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። ይህንንም የሚያደርገው ባልተጠበቀ መንገድ ሊሆን ይችላል። ለሳምሶን ኃይል የሰጠው ይሖዋ፣ በእሱ እስከታመንክ ድረስ ፈቃዱን እንድታደርግ አንተንም ሊረዳህ ይችላል።—ምሳሌ 16:3
7. የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።
7 በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የሚካፈሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች በይሖዋ እንደሚታመኑ አሳይተዋል። ቀደም ሲል የአብዛኞቹን የስብሰባ አዳራሾችና ሌሎች ሕንፃዎች ንድፍ የሚያወጡትም ሆነ የሚገነቡት ወንድሞች ነበሩ። ውሎ አድሮ ግን የይሖዋ ድርጅት እድገት በማድረጉ የተነሳ ማስተካከያ ማድረግ አስፈለገ። ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የይሖዋን አመራር በመጠየቅ አዳዲስ ዘዴዎችን መሞከር ጀመሩ። ከእነዚህ ዘዴዎች መካከል ሕንፃዎችን ገዝቶ ማደስ ይገኝበታል። ባለፉት ዓመታት በዓለም ዙሪያ በተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ የተሳተፈው ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ ይህን አዲስ አሠራር መልመድ ለአንዳንዶች ቀላል አልነበረም። ለዓመታት እንከተል ከነበረው አሠራር በጣም የተለየ ነው። ሆኖም ወንድሞች ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች ነበሩ። ይሖዋም እነዚህን ዝግጅቶች እየባረካቸው እንዳለ ግልጽ ሆነ።” ይህ ተሞክሮ፣ ይሖዋ ሕዝቦቹ ፈቃዱን እንዲፈጽሙ የሚመራቸው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ብቻ ነው። አልፎ አልፎ ሁላችንም እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘የይሖዋን መመሪያ ለማስተዋል ጥረት አደርጋለሁ? ለእሱ በማቀርበው አገልግሎት ረገድ ማስተካከያ ለማድረግስ ፈቃደኛ ነኝ?’
ሳምሶን የይሖዋን ዝግጅቶች ጥሩ አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል
8. በአንድ ወቅት ሳምሶን በጣም በተጠማበት ጊዜ ምን አደረገ?
8 ሳምሶን አስደናቂ ነገሮች ያደረገባቸውን ሌሎች ዘገባዎችም አንብበህ ሊሆን ይችላል። ብቻውን አንበሳ ገድሏል። በኋላ ላይ ደግሞ የፍልስጤም ከተማ በሆነችው በአስቀሎን 30 ሰዎችን ገድሏል። (መሳ. 14:5, 6, 19) ሳምሶን ያለይሖዋ እርዳታ ይህን ሁሉ ነገር ማድረግ እንደማይችል ያውቅ ነበር። በአንድ ወቅት 1,000 ፍልስጤማውያንን ከገደለ በኋላ ውኃ ሲጠማው ያደረገው ነገር ይህን ያሳያል። በዚህ ወቅት በራሱ ታምኖ የሚጠጣ ውኃ ከመፈለግ ይልቅ ይሖዋ እንዲረዳው ጠይቋል።—መሳ. 15:18
9. ይሖዋ የሳምሶንን ልመና የመለሰለት እንዴት ነው? (መሳፍንት 15:19 እና የግርጌ ማስታወሻ)
9 ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ ውኃ በማፍለቅ የሳምሶንን ልመና መለሰለት። ሳምሶን ከውኃው ሲጠጣ “ጥንካሬው ተመለሰ፤ ብርታትም አገኘ።” (መሳፍንት 15:19ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው፣ ነቢዩ ሳሙኤል ከዓመታት በኋላ የመሳፍንት መጽሐፍን በመንፈስ መሪነት በጻፈበት ወቅትም ይህ ምንጭ ነበር። ይህን ውኃ የተመለከቱ እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ እስከታመኑበት ድረስ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሁሉ እንደሚረዳቸው አስታውሰው መሆን አለበት።
10. የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
10 እኛም ምንም ያህል ችሎታ ወይም ተሰጥኦ ቢኖረን አሊያም በይሖዋ አገልግሎት ምንም ያህል ስኬት ብናገኝ ምንጊዜም የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ ይኖርብናል። ልካችንን ማወቅ እንዲሁም እውነተኛ ስኬት የሚገኘው በይሖዋ በመታመን ብቻ እንደሆነ አምነን መቀበል ይኖርብናል። ሳምሶን ይሖዋ ያዘጋጀለትን ውኃ በጠጣ ጊዜ ጥንካሬ እንዳገኘ ሁሉ እኛም ይሖዋ ባደረገልን ዝግጅቶች በሙሉ ስንጠቀም በመንፈሳዊ እንጠናከራለን።—ማቴ. 11:28
11. ይሖዋ ከሚሰጠን እርዳታ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
11 በሩሲያ ከባድ ስደት እየተቋቋመ ያለውን አሌክሲ የተባለ ወንድማችንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመጽናት የረዳው ምንድን ነው? እሱና ባለቤቱ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ አላቸው። እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ የግል ጥናት ልማድ እንዲኖረኝ ጥረት አደርጋለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስንም በየዕለቱ አነባለሁ። እኔና ባለቤቴ ጠዋት ጠዋት የዕለት ጥቅስ ካነበብን በኋላ ወደ ይሖዋ አብረን እንጸልያለን።” ከዚህ ምን እንማራለን? በራሳችን ከመታመን ይልቅ በይሖዋ ልንታመን ይገባል። እንዴት? አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል እምነታችንን ልናጠናክር ይገባል። ይሖዋም በምላሹ እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት አብዝቶ ይባርክልናል። ይሖዋ ሳምሶንን እንዳበረታው ሁሉ እኛንም ያለጥርጥር ያበረታናል።
ሳምሶን ተስፋ አልቆረጠም
12. ሳምሶን ምን መጥፎ ውሳኔ አደረገ? ከደሊላ ጋር የነበረው ግንኙነት የተለየ የሆነውስ እንዴት ነው?
12 ሳምሶን እንደ እኛው ፍጽምና የጎደለው ሰው ነበር፤ ስለዚህ የተሳሳተ ውሳኔ ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ። በተለይ በአንድ ወቅት ያደረገው ውሳኔ አስከፊ መዘዝ አስከትሎበታል። ሳምሶን ለተወሰነ ጊዜ መስፍን ሆኖ ካገለገለ በኋላ “በሶረቅ ሸለቆ የምትገኝ ደሊላ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ።” (መሳ. 16:4) ቀደም ሲል ሳምሶን አንዲት ፍልስጤማዊት አጭቶ ነበር። ሆኖም ይህ ጥምረት ‘ከይሖዋ ነበር’፤ ይሖዋ “ከፍልስጤማውያን ጋር ግጭት የሚፈጠርበትን አጋጣሚ እየፈለገ” ነበር። በኋላ ላይ ሳምሶን፣ ጋዛ በተባለችው የፍልስጤም ከተማ ውስጥ በአንዲት ዝሙት አዳሪ ቤት አድሯል። በዚያ ወቅት ሳምሶን የከተማዋን በሮች ነቅሎ እንዲወስድ አምላክ ኃይል ሰጥቶታል፤ ይህም ከተማዋን አዳክሟታል። (መሳ. 14:1-4፤ 16:1-3) የደሊላ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ደሊላ እስራኤላዊት ሳትሆን አትቀርም።
13. ደሊላ ሳምሶንን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የከተተችው እንዴት ነው?
13 ደሊላ ከፍልስጤማውያን ብዙ ገንዘብ በመቀበል ሳምሶንን ለእነሱ አሳልፋ ለመስጠት ተስማማች። ሳምሶን ለደሊላ ባለው ፍቅር ከመታወሩ የተነሳ ምን ለማድረግ እንዳሰበች ማስተዋል ተስኖት ይሆን? ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ደሊላ ከፍተኛ ጥንካሬ የሰጠው ምን እንደሆነ እንዲነግራት ሳምሶንን ወተወተችው። እሱም በስተ መጨረሻ ሚስጥሩን ነገራት። የሚያሳዝነው፣ ሳምሶን የሠራው ስህተት ጥንካሬውንና በይሖዋ ፊት ያለውን ሞገስ ለተወሰነ ጊዜ እንዲያጣ አደረገው።—መሳ. 16:16-20
14. ሳምሶን ደሊላን ማመኑ ምን መዘዝ አስከተለበት?
14 ሳምሶን ከይሖዋ ይልቅ ደሊላን ማመኑ አስከፊ መዘዝ አስከትሎበታል። ፍልስጤማውያን ሳምሶንን ይዘው ዓይኑን አሳወሩት። ሳምሶን ቀደም ሲል በሮቿን በገነጠለባት በጋዛ ታሰረ፤ እዚያም እህል ፈጪ ሆነ። ከዚያም ፍልስጤማውያን በዓል ለማክበር በተሰበሰቡበት ጊዜ አዋረዱት። ሳምሶንን በእጃቸው እንደሰጣቸው በመግለጽ ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት አቀረቡ። ከዚያም ሳምሶን “እንዲያዝናናቸው” ከእስር ቤት አውጥተው ሊቀልዱበት ወደ ግብዣው አመጡት።—መሳ. 16:21-25
15. ሳምሶን በድጋሚ በይሖዋ እንደሚታመን ያሳየው እንዴት ነው? (መሳፍንት 16:28-30) (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)
15 ሳምሶን ከባድ ስህተት ቢሠራም ተስፋ አልቆረጠም። አምላክ ፍልስጤማውያንን እንዲወጋ የሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም የሚያስችል አጋጣሚ ፈልጓል። (መሳፍንት 16:28-30ን አንብብ።) ሳምሶን “እባክህ . . . ፍልስጤማውያንን ልበቀላቸው” በማለት ይሖዋን ለመነው። እውነተኛው አምላክ የሳምሶንን ልመና በመስማት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ጥንካሬውን መለሰለት። በመሆኑም ሳምሶን በዚያ ዕለት፣ ከዚያ በፊት ከገደለው ይበልጥ ብዙ ፍልስጤማውያንን መግደል ቻለ።
16. ከሳምሶን ስህተት ምን ትምህርት እናገኛለን?
16 ሳምሶን የሠራው ስህተት ከባድ መዘዝ ቢያስከትልበትም የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ መሞከሩን አላቆመም። እኛም በሠራነው ስህተት የተነሳ ወቀሳ ቢሰጠን ወይም ያለንን መብት ብናጣም እንኳ ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም። ይሖዋ ተስፋ እንደማይቆርጥብን ማስታወስ ይኖርብናል። (መዝ. 103:8-10) እንደ ሳምሶን ሁሉ እኛም ስህተት ብንሠራም እንኳ ይሖዋ ሊጠቀምብን ይችላል።
17-18. ከማይክል ተሞክሮ ምን የሚያበረታታ ሐሳብ አግኝተሃል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 ማይክል የተባለ ወጣት ወንድም ያጋጠመውን እንመልከት። የጉባኤ አገልጋይና የዘወትር አቅኚ በመሆኑ በተለያዩ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ይካፈል ነበር። የሚያሳዝነው ግን ስህተት በመሥራቱ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን መብቶች አጣ። እንዲህ ብሏል፦ “እስከዚህ ወቅት ድረስ ሕይወቴ በይሖዋ አገልግሎት የተሞላ ነበር። አሁን ግን በይሖዋ አገልግሎት ምንም ነገር ማድረግ እንደማልችል ተሰማኝ። ይሖዋ ትቶኛል ብዬ አስቤ አላውቅም፤ ሆኖም ከእሱ ጋር ያለኝ ዝምድና እንደ በፊቱ መሆን መቻሉን ወይም እንደ ቀድሞው ጉባኤውን በተሟላ ሁኔታ ማገልገል መቻሌን ተጠራጥሬ ነበር።”
18 ደስ የሚለው፣ ማይክል ተስፋ አልቆረጠም። እንዲህ ብሏል፦ “አዘውትሬ ልቤን በጸሎት ለይሖዋ በማፍሰስ፣ በማጥናትና በማሰላሰል ከእሱ ጋር ያለኝን ዝምድና ለማደስ ጥረት አደረግኩ።” ውሎ አድሮ ማይክል በጉባኤ ውስጥ የነበሩትን መብቶች መልሶ አገኘ። አሁን የጉባኤ ሽማግሌና የዘወትር አቅኚ ሆኖ እያገለገለ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “በተለይ ከጉባኤ ሽማግሌዎች ያገኘሁት ድጋፍና ማበረታቻ ይሖዋ አሁንም እንደሚወደኝ አስገንዝቦኛል። ንጹሕ ሕሊና ኖሮኝ ጉባኤ ውስጥ በድጋሚ ማገልገል ችያለሁ። ያጋጠመኝ ነገር፣ ይሖዋ ማንኛውም ሰው ከልቡ ንስሐ እስከገባ ድረስ ይቅር እንደሚለው አስተምሮኛል።” እኛም ስህተት ብንሠራም እንኳ አካሄዳችንን ለማስተካከል የቻልነውን ሁሉ እስካደረግንና በይሖዋ መታመናችንን እስከቀጠልን ድረስ ይሖዋ በእኛ መጠቀሙን እንደሚቀጥልና እንደሚባርከን መተማመን እንችላለን።—መዝ. 86:5፤ ምሳሌ 28:13
19. የሳምሶን ምሳሌ ያበረታታህ እንዴት ነው?
19 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ሳምሶንን ያጋጠሙትን አንዳንድ አስደናቂ ክንውኖች ተመልክተናል። እርግጥ ሳምሶን ፍጹም አልነበረም። ሆኖም ከደሊላ ጋር በተያያዘ ስህተት ከሠራ በኋላም እንኳ ተስፋ ቆርጦ ይሖዋን ለማገልገል ጥረት ማድረጉን አላቆመም። ይሖዋም ተስፋ አልቆረጠበትም። በድጋሚ ሳምሶንን አስደናቂ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። ይሖዋ አሁንም የእምነት ሰው እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ከተዘረዘሩት ታማኝ ሰዎች መካከል አካቶታል። በተለይ በምንደክምበት ጊዜ እኛን ለማጠናከር የሚጓጓ አፍቃሪ አባት የምናገለግል መሆኑን ማወቃችን ምንኛ የሚያበረታታ ነው! እንግዲያው እኛም ልክ እንደ ሳምሶን ይሖዋን “እባክህ አስበኝ፤ . . . ብርታት ስጠኝ” ብለን እንለምነው።—መሳ. 16:28
መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን
a ሳምሶን—የዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ስም ብዙዎች ያውቁታል። እምብዛም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የሌላቸው ሰዎችም እንኳ ስለ ሳምሶን ሰምተው ያውቃሉ። የእሱን ታሪክ የያዙ በርካታ ቲያትሮች፣ ዘፈኖችና ፊልሞች አሉ። ሆኖም ታሪኩ ተረት አይደለም። ከዚህ የእምነት ሰው ብዙ የምንማረው ነገር አለ።