ኅዳር  27–​ታኅሣሥ 3, 2023 ባለው ሳምንት የሚጠና።"/>

በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 40

እንደ ጴጥሮስ መጽናት ትችላላችሁ

እንደ ጴጥሮስ መጽናት ትችላላችሁ

“ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ስለሆንኩ ከእኔ ራቅ።”—ሉቃስ 5:8

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

ማስተዋወቂያ a

1. ጴጥሮስ በተአምር ብዙ ዓሣ በያዘ ጊዜ ምን ተሰማው?

 ጴጥሮስ ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ቢሞክርም አንድም ዓሣ አልያዘም። ኢየሱስ ግን ያልተጠበቀ መመሪያ ሰጠው፤ “ጥልቅ ወደሆነው አካባቢ ፈቀቅ በልና መረቦቻችሁን ጥላችሁ አጥምዱ” አለው። (ሉቃስ 5:4) ጴጥሮስ ዓሣ መገኘቱን ተጠራጥሮ ነበር፤ ሆኖም ልክ እንደታዘዘው አደረገ። በዚህ ጊዜ በጣም ብዙ ዓሣ ከመያዙ የተነሳ መረቦቹ መበጣጠስ ጀመሩ። ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት ዓሣ አጥማጆች ኢየሱስ ተአምር እንደፈጸመ ሲያስተውሉ ‘በጣም ተደነቁ።’ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ስለሆንኩ ከእኔ ራቅ” በማለት ተናገረ። (ሉቃስ 5:6-9) ጴጥሮስ ከኢየሱስ አጠገብ መቆም እንኳ እንደማይገባው ተሰምቶት ነበር።

2. የጴጥሮስን ምሳሌ መመርመራችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

2 በእርግጥም ጴጥሮስ “ኃጢአተኛ” ሰው ነበር። ጴጥሮስ በኋላ ላይ የተጸጸተባቸውን ነገሮች እንደተናገረና እንዳደረገ የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አሉ። አንተስ እንደ ጴጥሮስ ተሰምቶህ ያውቃል? ነጋ ጠባ የሚያታግልህ መጥፎ ባሕርይ ወይም የኃጢአት ዝንባሌ አለ? ከሆነ የጴጥሮስን ታሪክ ማጥናትህ ሊያጽናናህ ይችላል። እንዴት? እስቲ አስበው፦ ይሖዋ፣ ጴጥሮስ የሠራቸው ስህተቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳይጻፉ ማድረግ ይችል ነበር። ያም ቢሆን ትምህርት እንድናገኝባቸው ሲል እንዲጻፉልን አድርጓል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ልክ እንደ እኛ ያሉ ድክመቶችና ስሜቶች ስላሉት ስለዚህ ሰው መማራችን ይሖዋ ከእኛ ፍጽምና እንደማይጠብቅ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ይሖዋ ድክመት ቢኖርብንም እንድንጸና ማለትም ለመሻሻል ጥረት ማድረጋችንን እንድንቀጥል ይፈልጋል።

3. መጽናት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

3 መጽናታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድን ነገር ደጋግመን ስናደርገው ችሎታችን እየተሻሻለ እንደሚሄድ የታወቀ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው አንድን የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ለመቻል ብዙ ዓመት ሊፈጅበት ይችላል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በጣም ብዙ ስህተት መሥራቱ አይቀርም። ግን ልምምዱን ከቀጠለ እየተሻሻለ ይሄዳል። እርግጥ የተዋጣለት ሙዚቀኛ ከሆነ በኋላም እንኳ አልፎ አልፎ ስህተት ሊሠራ ይችላል። ያም ቢሆን ተስፋ አይቆርጥም። ክህሎቱን ለማሻሻል ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል። እኛም በተመሳሳይ አንድን ድክመት እንዳሸነፍነው ከተሰማን በኋላም እንኳ ችግሩ ሊያገረሽብን ይችላል። ሆኖም ለመሻሻል ጥረት ማድረጋችንን አናቆምም። ሁላችንም በኋላ ላይ የምንጸጸትበትን ነገር እናደርጋለን ወይም እንናገራለን፤ ያም ቢሆን ተስፋ ካልቆረጥን ይሖዋ ለውጥ ማድረጋችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። (1 ጴጥ. 5:10) ጴጥሮስ በጽናት ረገድ የተወውን ምሳሌ እስቲ እንመርምር። ጴጥሮስ ስህተት ቢሠራም ኢየሱስ ርኅራኄ እንዳሳየው መገንዘባችን እኛም ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል።

ጴጥሮስ ያደረገው ትግልና ያገኘው በረከት

ጴጥሮስ ያጋጠመው ነገር ቢያጋጥምህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)

4. በሉቃስ 5:5-10 ላይ ጴጥሮስ ስለ ራሱ ምን ብሏል? ሆኖም ኢየሱስ ምን ብሎ አጽናናው?

4 ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ጴጥሮስ ራሱን “ኃጢአተኛ” ብሎ የጠራው ለምን እንደሆነ ወይም የትኞቹን ኃጢአቶች በአእምሮው ይዞ እንደሆነ አይገልጹልንም። (ሉቃስ 5:5-10ን አንብብ።) ሆኖም ከባድ ስህተቶችን ፈጽሞ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ፍርሃት እንደተሰማው ተገንዝቦ ነበር፤ ምናልባትም ፍርሃቱ የመነጨው ‘ብቁ አይደለሁም’ ከሚል ስሜት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ታማኝነቱን መጠበቅ እንደሚችልም ያውቃል። በመሆኑም ኢየሱስ ጴጥሮስን በደግነት “አይዞህ አትፍራ” አለው። ኢየሱስ የተማመነበት መሆኑ የጴጥሮስን ሕይወት ቀይሮታል። ከጊዜ በኋላ ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን በመተው ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው መሲሑን መከተል ጀመሩ። ይህ ውሳኔያቸው አስደናቂ በረከቶች አስገኝቶላቸዋል።—ማር. 1:16-18

5. ጴጥሮስ ፍርሃቱን በማሸነፉና የኢየሱስን ግብዣ በመቀበሉ የትኞቹን በረከቶች አግኝቷል?

5 ጴጥሮስ የክርስቶስ ተከታይ በመሆኑ በርካታ አስደናቂ ተሞክሮዎችን አግኝቷል። ኢየሱስ የታመሙትን ሲፈውስ፣ አጋንንትን ሲያስወጣ አልፎ ተርፎም ሙታንን ሲያስነሳ ተመልክቷል። b (ማቴ. 8:14-17፤ ማር. 5:37, 41, 42) በተጨማሪም ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ወደፊት ንጉሥ ሲሆን የሚኖረውን ክብር በራእይ ተመልክቷል፤ ይህ ራእይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። (ማር. 9:1-8፤ 2 ጴጥ. 1:16-18) ጴጥሮስ ኢየሱስን ባይከተል ኖሮ እነዚህን ሁሉ አስደናቂ ነገሮች የማየት አጋጣሚ አያገኝም ነበር። ስለ ራሱ የነበረው አሉታዊ አመለካከት እነዚህን በረከቶች እንዲያሳጣው ባለመፍቀዱ ምንኛ ተደስቶ ይሆን!

6. ጴጥሮስ ድክመቶቹን በአንድ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል? አብራራ።

6 ጴጥሮስ እነዚህን ሁሉ አስደናቂ ነገሮች ያየና የሰማ ቢሆንም አሁንም ከድክመቱ ጋር መታገል አስፈልጎታል። ይህን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት እንደሚሠቃይና እንደሚሞት ሲናገር ጴጥሮስ ገሠጸው። (ማር. 8:31-33) ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ከሁሉም የሚበልጠው ማን እንደሆነ በተደጋጋሚ ይከራከሩ ነበር። (ማር. 9:33, 34) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ጴጥሮስ የአንድን ሰው ጆሮ ቆርጧል። (ዮሐ. 18:10) በዚያው ምሽት ጴጥሮስ በፍርሃት ተሸንፎ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ክዶታል። (ማር. 14:66-72) በዚህም የተነሳ ጴጥሮስ ምርር ብሎ አልቅሷል።—ማቴ. 26:75

7. ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ጴጥሮስ ምን አጋጣሚ አገኘ?

7 ኢየሱስ ቅስሙ በተሰበረው ሐዋርያው ላይ ተስፋ አልቆረጠበትም። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ጴጥሮስ ለእሱ ያለውን ፍቅር እንዲገልጽ አጋጣሚ ሰጠው። ኢየሱስ የበጎቹ እረኛ ሆኖ በትሕትና እንዲያገለግል ጴጥሮስን ጋበዘው። (ዮሐ. 21:15-17) ጴጥሮስም ግብዣውን ተቀብሏል። ጴጥሮስ በጴንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም በመገኘት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉት የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መካከል ለመሆን በቅቷል።

8. ጴጥሮስ በአንጾኪያ ምን ከባድ ስህተት ፈጸመ?

8 ጴጥሮስ በመንፈስ ከተቀባ በኋላም እንኳ ከድክመቶቹ ጋር መታገል ነበረበት። በ36 ዓ.ም. ካልተገረዙ አሕዛብ ወገን የሆነው ቆርኔሌዎስ በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት ጊዜ ጴጥሮስ እዚያ ነበር። ይህ አጋጣሚ “አምላክ እንደማያዳላ” እና አሕዛብም የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን እንደሚችሉ በግልጽ አሳይቷል። (ሥራ 10:34, 44, 45) ከዚያ ጊዜ በኋላ ጴጥሮስ ከአሕዛብ ጋር አብሮ መብላት ጀመረ፤ በፊት ቢሆን ይህን ፈጽሞ አያደርግም ነበር። (ገላ. 2:12) ነገር ግን አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ አይሁዳውያንና አሕዛብ አብረው መብላት እንደሌለባቸው ይሰማቸው ነበር። እንዲህ ያለ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ወደ አንጾኪያ ሲመጡ ጴጥሮስ ከአሕዛብ ወንድሞቹ ጋር መብላቱን አቆመ፤ ይህን ያደረገው አይሁዳውያን ክርስቲያኖችን እንዳያስቀይም ፈርቶ ሳይሆን አይቀርም። ሐዋርያው ጳውሎስ የጴጥሮስን ግብዝነት ሲመለከት በሁሉም ፊት ገሠጸው። (ገላ. 2:13, 14) ጴጥሮስ እንዲህ ያለ ስህተት ቢሠራም በጽናት ቀጥሏል። እንዲህ ለማድረግ የረዳው ምንድን ነው?

ጴጥሮስን እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው?

9. ዮሐንስ 6:68, 69 የጴጥሮስን ታማኝነት የሚያሳየው እንዴት ነው?

9 ጴጥሮስ ታማኝ ነበር፤ ምንም ነገር ኢየሱስን መከተሉን እንዲያስቆመው አልፈቀደም። በአንድ ወቅት ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ደቀ መዛሙርቱ መረዳት ባቃታቸው ጊዜ ጴጥሮስ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። (ዮሐንስ 6:68, 69ን አንብብ።) ብዙዎች፣ ኢየሱስ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ሳይጠብቁም ሆነ ሳይጠይቁ እሱን መከተላቸውን አቆሙ። ጴጥሮስ ግን እንደዚያ አላደረገም። “የዘላለም ሕይወት ቃል” ያለው ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።

ኢየሱስ በጴጥሮስ መተማመኑ የሚያበረታታን እንዴት ነው? (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. ኢየሱስ በጴጥሮስ እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

10 ኢየሱስ ጴጥሮስን አልተወውም። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ትተውት እንደሚሄዱ አውቆ ነበር። ያም ቢሆን ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ እንደሚመለስና ታማኝ ሆኖ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነበር። (ሉቃስ 22:31, 32) ኢየሱስ “መንፈስ ዝግጁ . . . ሥጋ ግን ደካማ” እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ማር. 14:38) በመሆኑም ጴጥሮስ ከካደው በኋላም እንኳ ኢየሱስ ተስፋ አልቆረጠበትም። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለጴጥሮስ ተገለጠለት፤ በዚህ ወቅት ጴጥሮስ ብቻውን ሳይሆን አይቀርም። (ማር. 16:7፤ ሉቃስ 24:34፤ 1 ቆሮ. 15:5) ቅስሙ የተሰበረው ይህ ሐዋርያ በዚህ ምንኛ ተጽናንቶ ይሆን!

11. ኢየሱስ ለጴጥሮስ ይሖዋ እንደሚደግፈው ያረጋገጠለት እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ለጴጥሮስ ይሖዋ እንደሚደግፈው አረጋግጦለታል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በድጋሚ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት በተአምር ብዙ ዓሣ እንዲያጠምዱ አድርጓቸዋል። (ዮሐ. 21:4-6) ይህ ተአምር፣ ጴጥሮስ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ሁሉ ይሖዋ በቀላሉ ሊሰጠው እንደሚችል አረጋግጦለት እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። በዚህ ወቅት ጴጥሮስ ‘ከሁሉ አስቀድመው መንግሥቱን ለሚፈልጉ’ ሁሉ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያሟላላቸው ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አስታውሶ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 6:33) በዚህም የተነሳ ጴጥሮስ ዓሣ ከማጥመድ ሥራው ይልቅ ለአገልግሎቱ ቅድሚያ መስጠት ጀመረ። በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት በድፍረት ምሥክርነት በመስጠት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹን እንዲቀበሉ ረድቷል። (ሥራ 2:14, 37-41) በኋላ ደግሞ ሳምራውያንና አሕዛብ ክርስቶስን እንዲቀበሉ ረድቷል። (ሥራ 8:14-17፤ 10:44-48) በእርግጥም ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ወደ ጉባኤው ለማምጣት ጴጥሮስን አስደናቂ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

12. ከአንድ ድክመት ጋር ለረጅም ጊዜ ስንታገል ከቆየን የጴጥሮስ ታሪክ የሚረዳን እንዴት ነው?

12 ይሖዋ እንድንጸና ሊረዳን ይችላል። በተለይ ከአንድ ድክመት ጋር ለረጅም ጊዜ ስንታገል ከቆየን መጽናት ከባድ ሊሆንብን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የእኛ ድክመት ከጴጥሮስ ድክመት አንጻር ከባድ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ ተስፋ እንዳንቆርጥ ብርታት ሊሰጠን ይችላል። (መዝ. 94:17-19) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም እውነትን ከመስማቱ በፊት ለበርካታ ዓመታት ግብረ ሰዶማዊ ነበር። በኋላ ግን ሥነ ምግባር የጎደለውን አኗኗሩን ሙሉ በሙሉ ተወ። ይሁንና ከመጥፎ ምኞቶች ጋር አልፎ አልፎ ይታገል ነበር። ታዲያ እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ያጠናክረናል። የይሖዋ መንፈስ እስከረዳኝ ድረስ . . . በእውነት መንገድ ላይ መጓዜን [መቀጠል] እንደምችል ተምሬያለሁ። . . . ይሖዋ አሁንም እየተጠቀመብኝ ነው። ድክመት ቢኖርብኝም እንኳ ምንጊዜም ያጠናክረኛል።”

ሆርስት ሄንሸል የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመረው ጥር 1, 1950 ነው። ሕይወቱን ይሖዋን ለማገልገል በማዋሉ የተቆጨ ይመስልሃል? (አንቀጽ 13, 15⁠ን ተመልከት) d

13. በሐዋርያት ሥራ 4:13, 29, 31 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የጴጥሮስ ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ጴጥሮስ በሰው ፍርሃት በተደጋጋሚ ተሸንፏል። ሆኖም ጴጥሮስ የይሖዋን እርዳታ በመጠየቁ በድፍረት መናገር ችሏል። (የሐዋርያት ሥራ 4:13, 29, 31ን አንብብ።) እኛም ፍርሃታችንን ማሸነፍ እንችላለን። በናዚ ጀርመን ይኖር የነበረ ሆርስት የተባለ ወጣት ወንድም ያጋጠመውን እስቲ እንመልከት። ሆርስት በተደጋጋሚ፣ በትምህርት ቤት ለሚደርስበት ጫና ተሸንፎ “ሃይል ሂትለር!” ብሏል። ወላጆቹ እሱን ከመቆጣት ይልቅ አብረውት በመጸለይ ድፍረት እንዲሰጠው ይሖዋን ለመኑት። ሆርስት ከወላጆቹ እርዳታ በማግኘቱና በይሖዋ በመታመኑ ውሎ አድሮ በአቋሙ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት አግኝቷል። ሆርስት ከጊዜ በኋላ “ይሖዋ ፈጽሞ አልተወኝም” በማለት ተናግሯል። c

14. አሳቢ የሆኑ እረኞች ተስፋ የቆረጡትን ማጽናናት የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ይሖዋና ኢየሱስ ተስፋ አይቆርጡብንም። ጴጥሮስ ክርስቶስን ከካደው በኋላ ትልቅ ውሳኔ ከፊቱ ተደቅኖ ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሆኖ ይጸናል? ወይስ እሱን መከተሉን ያቆማል? ኢየሱስ የጴጥሮስ እምነት እንዳይጠፋ ወደ ይሖዋ ምልጃ አቅርቦ ነበር። ኢየሱስ ለጴጥሮስ ስለዚህ ጸሎት የነገረው ከመሆኑም ሌላ ጴጥሮስ በኋላ ላይ ወንድሞቹን እንደሚያበረታ እምነት እንዳለው ገለጸለት። (ሉቃስ 22:31, 32) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር መለስ ብሎ ሲያስብ ምንኛ ተጽናንቶ ይሆን! በሕይወታችን ውስጥ ከባድ ውሳኔ ሲደቀንብን ይሖዋ አፍቃሪ የሆኑ እረኞችን በመጠቀም ታማኝ ሆነን እንድንጸና ብርታት ሊሰጠን ይችላል። (ኤፌ. 4:8, 11) ለረጅም ጊዜ በሽምግልና ያገለገለ ፖል የተባለ ወንድም እንዲህ ያለ ማበረታቻ ለመስጠት ጥረት ያደርጋል። ተስፋ ሊቆርጡ ከተቃረቡ ወንድሞች ጋር ሲነጋገር ይሖዋ መጀመሪያ ላይ ወደ እውነት የሳባቸው እንዴት እንደሆነ እንዲያስታውሱ ያበረታታቸዋል። ከዚያም ይሖዋ ለእነሱ ታማኝ ፍቅር ስላለው ተስፋ እንደማይቆርጥባቸው ይነግራቸዋል። እንዲህ ብሏል፦ “ተስፋ የቆረጡ ብዙ ክርስቲያኖች በይሖዋ እርዳታ ሲጸኑ ማየት ችያለሁ።”

15. የጴጥሮስና የሆርስት ምሳሌ የማቴዎስ 6:33⁠ን እውነተኝነት የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

15 ይሖዋ ለጴጥሮስና ለሌሎቹ ሐዋርያት በቁሳዊ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዳሟላላቸው ሁሉ እኛም የይሖዋን አገልግሎት በሕይወታችን ካስቀደምን የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች ያሟላልናል። (ማቴ. 6:33) ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሆርስት አቅኚ ለመሆን አሰበ። ሆኖም በጣም ድሃ ስለነበር ራሱን እያስተዳደረ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል መቻሉን ተጠራጥሮ ነበር። ታዲያ ሆርስት ምን አድርጎ ይሆን? የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በሚጎበኝበት ጊዜ ሙሉውን ሳምንት በአገልግሎት በማሳለፍ ይሖዋን ለመፈተን ወሰነ። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ አንድ ፖስታ ሲሰጠው በጣም ደነገጠ። ፖስታው ውስጥ ገንዘብ የነበረ ሲሆን ሆርስት የላኪውን ማንነት አያውቅም። ገንዘቡ በአቅኚነት እያገለገለ ለበርካታ ወራት የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የሚበቃ ነበር። ሆርስት ይህን ስጦታ፣ ይሖዋ የሚያስፈልገውን ነገር ምንጊዜም እንደሚያሟላለት የሚያሳይ ማረጋገጫ አድርጎ ተመልክቶታል። ቀሪውን ሕይወቱን በሙሉ መንግሥቱን ማስቀደሙን ቀጥሏል።—ሚል. 3:10

16. ለጴጥሮስ ተሞክሮና ለጻፋቸው ደብዳቤዎች ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?

16 ጴጥሮስ ከእሱ እንዲርቅ ኢየሱስን ቢጠይቀውም ኢየሱስ ይህን ባለማድረጉ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ክርስቶስ ጴጥሮስን በቀጣይነት በማሠልጠን ታማኝ ሐዋርያና ለክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ እንዲሆን ረድቶታል። ስለዚህ ሥልጠና የሚናገረው ዘገባ ለሁላችንም የሚጠቅሙ ግሩም ትምህርቶች ይዟል። ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ጉባኤዎች በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው ሁለት ደብዳቤዎች ላይ እነዚህንና ሌሎች ነጥቦችን ጠቅሷል። ቀጣዩ ርዕስ፣ በእነዚህ ደብዳቤዎች ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ማሳሰቢያዎችን ያብራራል፤ እንዲሁም በዛሬው ጊዜ እንዴት ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንደምንችል ይገልጻል።

መዝሙር 126 ነቅተህ ኑር፣ ጸንተህ ቁም፣ በርታ

a ይህ ርዕስ የተዘጋጀው ከድክመቶቻቸው ጋር የሚታገሉ ክርስቲያኖች ድክመቶቻቸውን ማሸነፍና ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ሆነው መጽናት እንደሚችሉ ዋስትና ለመስጠት ነው።

b በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚገኙት ብዙዎቹ ጥቅሶች የተወሰዱት ከማርቆስ ወንጌል ነው። ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው እነዚህን ክንውኖች በዓይኑ ከተመለከተው ከጴጥሮስ በሰማው ነገር ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን አይቀርም።

c jw.org ላይ የሚገኘውን ሆርስት ሄንሸል፦ ይሖዋ ጽኑ ግንብ ሆኖልኛል የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ የሆርስት ሄንሸል ወላጆች አብረውት ሲጸልዩና በአቋሙ እንዲጸና ሲያበረታቱት የሚያሳይ ትወና።