ኅዳር  13-19, 2023 ባለው ሳምንት የሚጠና።"/>

በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 38

ወጣቶች—የወደፊት ሕይወታችሁ ምን ይመስል ይሆን?

ወጣቶች—የወደፊት ሕይወታችሁ ምን ይመስል ይሆን?

“ጥልቅ ግንዛቤ . . . ይጋርድሃል።”—ምሳሌ 2:11

መዝሙር 135 የይሖዋ ፍቅራዊ ግብዣ፦ ‘ልጄ ሆይ፣ ጥበበኛ ሁን’

ማስተዋወቂያ a

1. ኢዮዓስ፣ ዖዝያ እና ኢዮስያስ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል?

 በልጅነትህ የአምላክ ሕዝቦች ንጉሥ ሆነህ ብትሾም ምን ይሰማሃል? ሥልጣንህን እንዴት ትጠቀምበታለህ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ የይሁዳ ነገሥታት የሆኑ በርካታ ወጣቶችን ታሪክ ይዟል። ለምሳሌ ኢዮዓስ የነገሠው በ7 ዓመቱ፣ ዖዝያ በ16 ዓመቱ፣ ኢዮስያስ ደግሞ በ8 ዓመቱ ነበር። እነዚህ ወጣቶች ምን ያህል ጫና ሊበዛባቸው እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። የነበሩበት ሁኔታ ከባድ ቢሆንም ሁሉም ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋምና ፍሬያማ ሕይወት ለመምራት የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ አግኝተዋል።

2. የኢዮዓስን፣ የዖዝያንና የኢዮስያስን ምሳሌ መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?

2 እርግጥ እኛ ነገሥታት አይደለንም። ሆኖም ከእነዚህ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በሕይወታቸው ውስጥ ጥሩም ሆነ መጥፎ ውሳኔ አድርገዋል። ጥሩ ጓደኞች መምረጥ፣ ምንጊዜም ትሑት መሆን እንዲሁም ይሖዋን መፈለጋችንን መቀጠል ያለብን ለምን እንደሆነ ከእነሱ ምሳሌ እንማራለን።

ጥሩ ጓደኞች ምረጥ

ጥሩ ጓደኞች የሚሰጡንን ምክር በመስማት የኢዮዓስን ምሳሌ መከተል እንችላለን (አንቀጽ 3, 7⁠ን ተመልከት) c

3. ንጉሥ ኢዮዓስ፣ ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ ለሰጠው ትምህርት ምን ምላሽ ሰጥቷል?

3 የኢዮዓስን ጥሩ ውሳኔዎች ኮርጅ። ንጉሥ ኢዮዓስ በልጅነቱ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አድርጓል። ኢዮዓስ አባት ባይኖረውም ታማኝ ሊቀ ካህናት የሆነው ዮዳሄ የሰጠውን አመራር ተቀብሏል። ዮዳሄ ኢዮዓስን ልክ እንደ ገዛ ልጁ አስተምሮታል። ኢዮዓስም በምላሹ ንጹሑን አምልኮ ለማራመድና ይሖዋን ለማገልገል ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አደረገ። እንዲያውም ኢዮዓስ የይሖዋ ቤተ መቅደስ እንዲጠገን ዝግጅት አደረገ።—2 ዜና 24:1, 2, 4, 13, 14

4. የይሖዋን ትእዛዛት እንደ ውድ ሀብት የምንመለከታቸው ከሆነ ምን ጥቅም እናገኛለን? (ምሳሌ 2:1, 10-12)

4 ወላጆችህ ወይም ሌሎች ሰዎች ይሖዋን እንድትወድና በእሱ መሥፈርቶች እንድትመራ እያስተማሩህ ከሆነ ውድ ስጦታ ሰጥተውሃል። (ምሳሌ 2:1, 10-12ን አንብብ።) ወላጆች በተለያየ መንገድ ሥልጠና መስጠት ይችላሉ። ካትያ የተባለች እህት ጥሩ ውሳኔዎችን እንድታደርግ አባቷ የረዳት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። በየቀኑ አባቷ ትምህርት ቤት ሲወስዳት በዕለቱ ጥቅስ ላይ ይወያዩ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ውይይቶች በቀኑ ውስጥ የሚያጋጥሙኝን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም ረድተውኛል።” ይሁንና ወላጆችህ የሚሰጡህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ ነፃነትህን እንደሚገድብብህ ቢሰማህስ? መመሪያዎቹን ለመቀበል ምን ይረዳሃል? አናስታሲያ የተባለች እህት፣ ወላጆቿ አንዳንድ ደንቦችን ያወጡበትን ምክንያት ጊዜ ወስደው እንደሚያብራሩላት ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ ማድረጋቸው፣ ያወጧቸውን ሕጎች ነፃነቴን እንደሚያሳጡኝ ገደቦች ሳይሆን ጥበቃ እንደሚያስገኙልኝ ፍቅራዊ መመሪያዎች አድርጌ እንድመለከታቸው ረድቶኛል።”

5. የምታደርገው ነገር በወላጆችህና በይሖዋ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? (ምሳሌ 22:6፤ 23:15, 24, 25)

5 የሚሰጥህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ ስታደርግ ወላጆችህን ታስደስታለህ። ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክን ታስደስተዋለህ፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ትመሠርታለህ። (ምሳሌ 22:6፤ 23:15, 24, 25ን አንብብ።) ይህ፣ ኢዮዓስ በልጅነቱ የተወውን ምሳሌ ለመከተል የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት አይደለም?

6. ኢዮዓስ የማንን ምክር መስማት ጀመረ? ይህስ ምን ውጤት አስከተለበት? (2 ዜና መዋዕል 24:17, 18)

6 ከኢዮዓስ መጥፎ ውሳኔዎች ተማር። ዮዳሄ ከሞተ በኋላ ኢዮዓስ መጥፎ ጓደኞችን መረጠ። (2 ዜና መዋዕል 24:17, 18ን አንብብ።) ይሖዋን የማይወዱትን የይሁዳ መኳንንት ለመስማት ወሰነ። ኢዮዓስ ከእነዚህ መጥፎ ሰዎች መራቅ ነበረበት ቢባል አትስማማም? (ምሳሌ 1:10) እሱ ግን ጓደኛ ተብዬዎቹን ለመስማት መረጠ። እንዲያውም የአክስቱ ልጅ የሆነው ዘካርያስ እርማት ሲሰጠው ኢዮዓስ አስገደለው። (2 ዜና 24:20, 21፤ ማቴ. 23:35) እንዴት ያለ ሞኝነትና ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ድርጊት ነው! ኢዮዓስ በልጅነቱ ጥሩ ውሳኔዎችን አድርጓል፤ የሚያሳዝነው ግን በኋላ ላይ ከሃዲና ነፍሰ ገዳይ ሆነ። በመጨረሻም የገዛ አገልጋዮቹ ገደሉት። (2 ዜና 24:22-25) ይሖዋንና እሱን የሚወዱትን ሰዎች መስማቱን ቢቀጥል ኖሮ ሕይወቱ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር! አንተስ ከኢዮዓስ ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

7. ምን ዓይነት ጓደኞች መምረጥ ይኖርብሃል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 ኢዮዓስ ካደረገው መጥፎ ውሳኔ የምናገኘው አንዱ ትምህርት፣ ይሖዋን የሚወዱና እሱን ማስደሰት የሚፈልጉ ጓደኞችን መምረጥ እንዳለብን ነው። እንዲህ ያሉ ጓደኞች በጎ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። ጓደኛ የምናደርገው የግድ እኩዮቻችንን መሆን የለበትም። ኢዮዓስ ከጓደኛው ከዮዳሄ በዕድሜ በጣም ያንስ እንደነበር አስታውስ። ጓደኛ አድርገህ ከምትመርጣቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት እንዳጠናክር ይረዱኛል? በአምላክ መሥፈርቶች እንድመራ ያበረታቱኛል? ስለ ይሖዋና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት እውነቶች ያወራሉ? ለአምላክ መሥፈርቶች አክብሮት ያሳያሉ? የሚነግሩኝ መስማት የምፈልገውን ነገር ብቻ ነው ወይስ ትክክል ያልሆነ ነገር ሳደርግ በድፍረት እርማት ይሰጡኛል?’ (ምሳሌ 27:5, 6, 17) እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ጓደኞችህ ይሖዋን የማይወዱ ከሆነ ለአንተም አይበጁህም። ይሖዋን የሚወዱ ጓደኞች ካሉህ ግን አጥብቀህ ያዛቸው፤ ይጠቅሙሃል!—ምሳሌ 13:20

8. ማኅበራዊ ሚዲያ የምንጠቀም ከሆነ ምን ነገር ከግምት ማስገባት ይኖርብናል?

8 ማኅበራዊ ሚዲያ ከቤተሰቦቻችንና ከጓደኞቻችን ጋር ለመገናኘት ሊጠቅመን ይችላል። ይሁንና ብዙዎች ማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙት የገዟቸውንና ያደረጓቸውን ነገሮች የሚያሳዩ ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን በመለጠፍ ሌሎችን ለማስደመም ነው። አንተም ማኅበራዊ ሚዲያ የምትጠቀም ከሆነ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ዓላማዬ ሌሎችን ማስደመም ነው? የምፈልገው ሌሎችን ማነጽ ነው ወይስ የሌሎችን አድናቆት ማትረፍ? ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የማገኛቸው ሰዎች በአስተሳሰቤ፣ በአነጋገሬና በምግባሬ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ እየፈቀድኩ ነው?’ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ናታን ኖር እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “ጥረታችሁ ሰዎችን ማስደሰት መሆን የለበትም። ይህ ከሆነ በመጨረሻ ማንንም ሳታስደስቱ ትቀራላችሁ። ይሖዋን የምታስደስቱ ከሆነ ግን እሱን የሚወዱትን ሁሉ ማስደሰት ትችላላችሁ።”

ምንጊዜም ትሑት የመሆን አስፈላጊነት

9. ይሖዋ ዖዝያን ምን እንዲያደርግ ረድቶታል? (2 ዜና መዋዕል 26:1-5)

9 የዖዝያን ጥሩ ውሳኔዎች ኮርጅ። ንጉሥ ዖዝያ ወጣት ሳለ ትሑት ነበር። “እውነተኛውን አምላክ መፍራት” ተምሯል። ዖዝያ 68 ዓመት የኖረ ሲሆን በአብዛኛው የሕይወቱ ክፍል ይሖዋ ባርኮታል። (2 ዜና መዋዕል 26:1-5ን አንብብ።) ዖዝያ ብዙዎቹን የይሁዳ ጠላቶች ድል ያደረገ ከመሆኑም ሌላ የኢየሩሳሌምን መከላከያዎች አጠናክሯል። (2 ዜና 26:6-15) ዖዝያ በአምላክ እርዳታ ባከናወናቸው ነገሮች በጣም እንደተደሰተ ምንም ጥያቄ የለውም።—መክ. 3:12, 13

10. ዖዝያ ምን ደረሰበት?

10 ከዖዝያ መጥፎ ውሳኔዎች ተማር። ዖዝያ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሁልጊዜ ለሌሎች ትእዛዝ ያስተላልፍ ነበር። ይህ መሆኑ፣ የፈለገውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደሚችል እንዲሰማው አድርጎት ይሆን? አንድ ቀን ዖዝያ በትዕቢት ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ገብቶ በመሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ሞከረ፤ ነገሥታት ይህን ማድረግ አይፈቀድላቸውም ነበር። (2 ዜና 26:16-18) ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ ሊያስቆመው ሞክሮ ነበር፤ ዖዝያ ግን በጣም ተበሳጨ። የሚያሳዝነው፣ ዖዝያ ያስመዘገበውን የታማኝነት ታሪክ አበላሸ፤ ይሖዋም በሥጋ ደዌ መታው። (2 ዜና 26:19-21) ዖዝያ እስከ መጨረሻው ትሑት ሆኖ ቢኖር ኖሮ ሕይወቱ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር!

ባገኘናቸው ስኬቶች የተነሳ ጉራ ከመንዛት ይልቅ ማከናወን ለቻልነው ነገር ይሖዋን ልናመሰግን ይገባል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) d

11. ትሑት መሆናችንን የሚያሳየው ምን ሊሆን ይችላል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 ዖዝያ በበረታ ጊዜ የብልጽግናውና የብርታቱ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን ዘነጋ። እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ያሉን በረከቶችና መብቶች ከይሖዋ የተገኙ መሆናቸውን ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል። ባገኘናቸው ስኬቶች የተነሳ ጉራ ከመንዛት ይልቅ ላከናወንነው ነገር ይሖዋን ልናመሰግን ይገባል። b (1 ቆሮ. 4:7) ፍጹማን እንዳልሆንንና ተግሣጽ እንደሚያስፈልገን በትሕትና አምነን መቀበል ይኖርብናል። በ60ዎቹ ዕድሜ የሚገኝ አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለራሴ ከፍ ያለ አመለካከት ሊኖረኝ እንደማይገባ ተምሬያለሁ። አንዳንድ ጊዜ በሠራኋቸው የሞኝነት ስህተቶች የተነሳ ተግሣጽ ሲሰጠኝ ማሻሻያ ለማድረግና ወደፊት መግፋቴን ለመቀጠል ጥረት አደርጋለሁ።” እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይሖዋን የምንፈራና ለራሳችን ትሕትና የሚንጸባረቅበት አመለካከት የምናዳብር ከሆነ ሕይወታችን የተሻለ ይሆናል።—ምሳሌ 22:4

ይሖዋን መፈለግህን ቀጥል

12. ኢዮስያስ ወጣት ሳለ ይሖዋን የፈለገው እንዴት ነው? (2 ዜና መዋዕል 34:1-3)

12 የኢዮስያስን ጥሩ ውሳኔዎች ኮርጅ። ኢዮስያስ ይሖዋን መፈለግ የጀመረው ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ ነው። ስለ ይሖዋ መማርና የእሱን ፈቃድ ማድረግ ይፈልግ ነበር። ያም ቢሆን፣ ለዚህ ወጣት ንጉሥ ሕይወት ቀላል አልነበረም። የሐሰት አምልኮ በተስፋፋበት ዘመን ከንጹሑ አምልኮ ጎን መቆም ነበረበት። ያደረገውም ይህንኑ ነው! ኢዮስያስ ገና 20 ዓመት ሳይሞላው በፊት የሐሰት አምልኮን ከይሁዳ ማስወገድ ጀመረ።—2 ዜና መዋዕል 34:1-3ን አንብብ።

13. ራስህን ለይሖዋ መወሰንህ በሕይወትህ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

13 ገና ልጅ ብትሆንም እንኳ ይሖዋን በመፈለግና ስለ ባሕርያቱ በመማር የኢዮስያስን ምሳሌ መከተል ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ራስህን ለእሱ ለመወሰን ያነሳሳሃል። ራስህን ለይሖዋ መወሰንህ በዕለት ተዕለት ሕይወትህ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? በ14 ዓመቱ የተጠመቀው ሉክ እንዲህ ብሏል፦ “ከአሁን ጀምሮ በሕይወቴ ውስጥ የይሖዋን አገልግሎት አስቀድማለሁ፤ እሱን ለማስደሰትም ጥረት አደርጋለሁ።” (ማር. 12:30) አንተም እንዲህ ማድረግ የምትፈልግ ከሆነ ትልቅ በረከት ታገኛለህ!

14. አንዳንድ ወጣቶች የንጉሥ ኢዮስያስን ምሳሌ እየተከተሉ ያሉት እንዴት ነው?

14 ወጣት የይሖዋ አገልጋዮች የትኞቹ ፈተናዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ? በ12 ዓመቱ የተጠመቀው ጆሃን፣ አብረውት የሚማሩት ልጆች ኤሌክትሮኒክ ሲጋራ እንዲያጨስ ጫና እንደሚያሳድሩበት ተናግሯል። ጆሃን ኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ማጨሱ በጤንነቱም ሆነ ከይሖዋ ጋር ባለው ወዳጅነት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ማሰቡ ይህን ጫና ለመቋቋም ረድቶታል። በ14 ዓመቷ የተጠመቀችው ሬቸል በትምህርት ቤት ውስጥ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች ለመቋቋም የረዳት ምን እንደሆነ ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “የማየውን ነገር ሁሉ ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር ለማያያዝ እሞክራለሁ። ለምሳሌ በትምህርት ቤት ታሪክ ስማር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ወይም ትንቢት ወደ አእምሮዬ ይመጣል። ወይም ደግሞ አብረውኝ ከሚማሩ ልጆች ጋር ሳወራ የትኛውን ጥቅስ ላካፍላቸው እንደምችል አስባለሁ።” አንተን የሚያጋጥሙህ ፈተናዎች ንጉሥ ኢዮስያስን ካጋጠሙት ፈተናዎች የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም እንደ እሱ ጥበበኛና ታማኝ መሆን ትችላለህ። በወጣትነትህ ፈተናዎችን መቋቋምህ በመጪዎቹ ዓመታት ለሚያጋጥሙህ ፈተናዎች ያዘጋጅሃል።

15. ኢዮስያስ ይሖዋን በታማኝነት እንዲያገለግል የረዳው ምንድን ነው? (2 ዜና መዋዕል 34:14, 18-21)

15 ንጉሥ ኢዮስያስ አዋቂ ከሆነ በኋላ ቤተ መቅደሱን ማደስ ጀመረ። በእድሳቱ ወቅት ‘በሙሴ በኩል የተሰጠው የይሖዋ ሕግ መጽሐፍ’ ተገኘ። ንጉሡ የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ ከሰማ በኋላ የሰማውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ እርምጃ ወሰደ። (2 ዜና መዋዕል 34:14, 18-21ን አንብብ።) አንተስ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ማንበብ ትፈልጋለህ? አሁንም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ እየሞከርክ ከሆነ ደግሞ ንባብህ እንዴት እየሄደልህ ነው? ለግል ሕይወትህ የሚጠቅሙህን ጥቅሶች ለማስታወስ ትሞክራለህ? ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሉክ፣ ያገኛቸውን ትኩረት የሚስቡ ነጥቦች በማስታወሻ ደብተሩ ላይ ያሰፍራል። አንተም ተመሳሳይ ነገር ማድረግህ ትኩረትህን የሳቡትን ነጥቦች ወይም ጥቅሶች ለማስታወስ ሊረዳህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ስታውቅና ስትወደው ይሖዋን ለማገልገል ያለህ ፍላጎት ይጨምራል። በተጨማሪም እንደ ንጉሥ ኢዮስያስ የአምላክ ቃል እርምጃ ለመውሰድ ያነሳሳሃል።

16. ኢዮስያስ ከባድ ስህተት የሠራው ለምንድን ነው? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

16 ከኢዮስያስ መጥፎ ውሳኔ ተማር። ኢዮስያስ 39 ዓመት ገደማ ሲሆነው የሠራው ስህተት ሕይወቱን አሳጥቶታል። የይሖዋን አመራር ከመጠየቅ ይልቅ በራሱ ታመነ። (2 ዜና 35:20-25) እኛም ከዚህ የምናገኘው ትምህርት አለ። ዕድሜያችን ወይም መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ያሳለፍነው ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን ይሖዋን መፈለጋችንን መቀጠል ይኖርብናል። ይህም የእሱን አመራር ለማግኘት አዘውትሮ መጸለይን፣ ቃሉን ማጥናትን እንዲሁም የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚሰጡንን ምክር መቀበልን ይጨምራል። እንዲህ ካደረግን ትላልቅ ስህተቶችን የመሥራታችን አጋጣሚ ይቀንሳል፤ ደስተኛ የመሆናችን አጋጣሚ ደግሞ ይጨምራል።—ያዕ. 1:25

ወጣቶች—አስደሳች ሕይወት መምራት ትችላላችሁ

17. ከሦስቱ የይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ምን እንማራለን?

17 ወጣትነት ብዙ ነገሮችን ማድረግ የሚቻልበት ጊዜ ነው። የኢዮዓስ፣ የዖዝያና የኢዮስያስ ታሪክ ወጣቶች ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ማድረግና ይሖዋን የሚያስደስት አካሄድ መከተል እንደሚችሉ ያሳያል። እርግጥ እስካሁን እንደተመለከትነው ሁልጊዜ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ይቻላል ማለት አይደለም። ያም ቢሆን፣ እነዚህ ነገሥታት ያደረጓቸውን መልካም ነገሮች መኮረጅ እንዲሁም ስህተታቸውን ከመድገም መቆጠብ እንችላለን። እንዲህ ካደረግን አስደሳች ሕይወት እንመራለን።

ዳዊት በወጣትነቱ ወደ ይሖዋ ቀርቧል። የእሱን ሞገስ አግኝቷል፤ እንዲሁም አስደሳች ሕይወት መምራት ችሏል (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)

18. አስደሳች ሕይወት መምራት እንደምትችል የሚያሳዩት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

18 መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ይሖዋ የቀረቡ፣ የእሱን ሞገስ ያገኙና አስደሳች ሕይወት መምራት የቻሉ ሌሎች ወጣቶችን ታሪክም ይዟል። ከእነዚህ ወጣቶች አንዱ ዳዊት ነው። ዳዊት በወጣትነቱ ከይሖዋ ጎን ለመቆም መርጧል፤ በኋላም ታማኝ ንጉሥ ሆኗል። እርግጥ ስህተት የሠራባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ በጥቅሉ ሲታይ ግን የአምላክን ሞገስ አግኝቷል። (1 ነገ. 3:6፤ 9:4, 5፤ 14:8) ስለ ዳዊት ሕይወት እንዲሁም በታማኝነት ስላቀረበው አገልግሎት ማጥናትህ ሊያበረታታህና ለሥራ ሊያነሳሳህ ይችላል። አሊያም ደግሞ ስለ ማርቆስ ወይም ስለ ጢሞቴዎስ ሕይወት ማጥናት ትችላለህ። እነዚህ ሰዎች ከልጅነታቸው አንስቶ ሕይወታቸውን በሙሉ ይሖዋን በማገልገላቸው የእሱን ሞገስ ማግኘትና አስደሳች ሕይወት መምራት እንደቻሉ ትገነዘባለህ።

19. ምን ዓይነት ሕይወት መምራት ትችላለህ?

19 የወደፊት ሕይወትህ የተመካው በአሁኑ ጊዜ ሕይወትህን በምትጠቀምበት መንገድ ላይ ነው። በይሖዋ ከታመንክና በገዛ ራስህ ማስተዋል ካልተመካህ እሱ አካሄድህን ይመራልሃል። (ምሳሌ 20:24) ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት መምራት ትችላለህ። ይሖዋ ለእሱ ስትል የምታደርገውን ነገር ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው አትዘንጋ። አፍቃሪ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን ከማገልገል ሌላ ሕይወትህን ልትጠቀም የምትችልበት ምን የተሻለ መንገድ አለ?

መዝሙር 144 ዓይንህ ሽልማቱ ላይ ያተኩር!

a ወጣቶች፣ ይሖዋ ከእሱ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሟችሁ ያውቃል። ታዲያ የሰማዩን አባታችሁን የሚያስደስቱ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የይሁዳ ነገሥታት የሆኑ ሦስት ወጣቶችን ምሳሌ እንመለከታለን። እነሱ ካደረጓቸው ውሳኔዎች ምን ትምህርት እንደምታገኙ ልብ በሉ።

b jw.org ላይ በወጣው “ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን “በትሕትና ጉራ አትንዙ” የሚል ሣጥን ተመልከት።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት የጎለመሰች እህት ለአንዲት ወጣት እህት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ስትሰጥ።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ በወረዳ ስብሰባ ላይ ክፍል የምታቀርብ አንዲት እህት በይሖዋ ትታመናለች፤ እንዲሁም እሱን ታመሰግናለች።