የጥናት ርዕስ 39
ገር በመሆን ጥንካሬያችሁን አሳዩ
“የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውምና፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር . . . ሊሆን ይገባዋል።”—2 ጢሞ. 2:24
መዝሙር 120 እንደ ክርስቶስ ገር መሆን
ማስተዋወቂያ a
1. በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ምን ዓይነት ጥያቄ ሊቀርብልን ይችላል?
የሥራ ባልደረባህ ወይም አብሮህ የሚማር ልጅ ስለ እምነትህ ሲጠይቅህ ምን ይሰማሃል? ፍርሃት ፍርሃት ይልሃል? ብዙዎቻችን እንደዚያ ይሰማናል። ይሁንና እንዲህ ያለው ጥያቄ ስለ ግለሰቡ አስተሳሰብ ወይም እምነት እንድናውቅ ሊረዳን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ምሥራቹን ለመናገር የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትልናል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ጥያቄ የሚያነሱት የማወቅ ፍላጎት ኖሯቸው ሳይሆን እኛን ለማፋጠጥ ብለው ነው። ይህ መሆኑ ሊያስገርመን አይገባም። ምክንያቱም አንዳንዶች ስለ እምነታችን የተሳሳተ መረጃ ሰምተዋል። (ሥራ 28:22) በተጨማሪም የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ ነው፤ በዚህ ዘመን የሚኖሩ ብዙዎቹ ሰዎች ደግሞ “ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ” አልፎ ተርፎም “ጨካኞች” ናቸው።—2 ጢሞ. 3:1, 3
2. ገርነት አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ‘አንድ ሰው የማምንባቸውን ነገሮች በተመለከተ በጥያቄ ቢያፋጥጠኝ በደግነትና በዘዴ ምላሽ መስጠት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። በዚህ ረገድ ገርነት ይረዳሃል። ገር የሆነ ሰው የሚያስቆጣ ሁኔታ ሲያጋጥመው ወይም ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት እንዳለበት ግራ ሲገባው በቀላሉ አይበሳጭም፤ ከዚህ ይልቅ ራሱን መቆጣጠር ይችላል። (ምሳሌ 16:32) ነገር ግን ይህን ማድረግ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም። ታዲያ ገርነትን ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? አንድ ሰው እምነትህን በተመለከተ በጥያቄ ሲያፋጥጥህ በገርነት ምላሽ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው? ወላጅ ከሆንክ ደግሞ፣ ልጆችህ በገርነት ለእምነታቸው ጥብቅና እንዲቆሙ ልታሠለጥናቸው የምትችለው እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እስቲ እንመልከት።
ገርነትን ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?
3. ገርነት የጥንካሬ እንጂ የድክመት ምልክት አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25)
3 ገርነት የጥንካሬ እንጂ የድክመት ምልክት አይደለም። በሚፈታተን ሁኔታ ውስጥ መረጋጋት ውስጣዊ ጥንካሬ ይጠይቃል። ገርነት “የመንፈስ ፍሬ” አንዱ ገጽታ ነው። (ገላ. 5:22, 23) “ገርነት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ከተገራ ፈረስ ጋር በተያያዘም ተሠርቶበታል። አንድ የዱር ፈረስ ሲገራ ውጤቱ ምን እንደሚሆን ለማሰብ ሞክር። ጠንካራ ሆኖም ገራም ይሆናል። እኛ ሰዎችስ ገርም ጠንካራም መሆን የምንችለው እንዴት ነው? በራሳችን ጥረት እንዲህ ማድረግ አንችልም። አምላክ መንፈሱን እንዲሰጠን እንዲሁም ይህን ግሩም ባሕርይ ለማዳበር እንዲረዳን መጸለይ ይኖርብናል። ገርነትን ማዳበር እንደሚቻል ተሞክሮዎች ያሳያሉ። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ተቃዋሚዎች ሲያጋጥሟቸው በገርነት ምላሽ መስጠት ችለዋል፤ ይህም ሁኔታውን ለተመለከቱ ሰዎች ምሥክርነት ለመስጠት አስችሏል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25ን አንብብ።) አንተስ ገርነትን ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?
4. ገርነትን በተመለከተ ከይስሐቅ ታሪክ ምን እንማራለን?
4 መጽሐፍ ቅዱስ የገርነትን ጥቅም የሚያሳዩ በርካታ ዘገባዎችን ይዟል። የይስሐቅን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይስሐቅ የፍልስጤማውያን ክልል በሆነው በጌራራ መኖር በጀመረበት ወቅት ጎረቤቶቹ ስለቀኑበት የአባቱ አገልጋዮች የቆፈሯቸውን የውኃ ጉድጓዶች ደፈኑ። ይስሐቅ መብቱን ለማስከበር ከመታገል ይልቅ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ሌሎች የውኃ ጉድጓዶችን ቆፈረ። (ዘፍ. 26:12-18) ይሁንና ፍልስጤማውያን ይሄኛውም ውኃ የእነሱ እንደሆነ ተናገሩ። ያም ቢሆን ይስሐቅ ሰላማዊ መሆኑን አሳይቷል። (ዘፍ. 26:19-25) ይስሐቅ ሌሎች ሆን ብለው የሚያበሳጭ ነገር ቢያደርጉበትም ገርነት እንዲያሳይ የረዳው ምንድን ነው? ወላጆቹ ከተዉት ምሳሌ እንደተማረ ምንም ጥያቄ የለውም። አብርሃም ያሳየውን ሰላማዊነትና ሣራ ያሳየችውን “የሰከነና ገር መንፈስ” ኮርጇል።—1 ጴጥ. 3:4-6፤ ዘፍ. 21:22-34
5. ክርስቲያን ወላጆች የገርነትን ጥቅም ለልጆቻቸው ማስተማር እንደሚችሉ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
5 ክርስቲያን ወላጆች፣ እናንተም ገርነት ያለውን ጥቅም ለልጆቻችሁ ማስተማር ትችላላችሁ። የ17 ዓመቱን ማክስን b እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በትምህርት ቤትም ሆነ በአገልግሎት ላይ ብስጩ ሰዎች ያጋጥሙት ነበር። ሆኖም ወላጆቹ ገርነትን እንዲያዳብር በትዕግሥት ረዱት። እንዲህ ብለዋል፦ “ማክስ የሚያበሳጭ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ በቁጣ ምላሽ ከመስጠት ወይም የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ራስን መቆጣጠር ይበልጥ ጥንካሬ እንደሚጠይቅ ተገንዝቧል።” ደስ የሚለው፣ ማክስ ገርነትን ማዳበር ችሏል።
6. ጸሎት ገርነት በማሳየት ረገድ ማሻሻያ እንድናደርግ የሚረዳን እንዴት ነው?
6 የሚፈታተን ሁኔታ ሲያጋጥመን ምን ማድረግ እንችላለን? ለምሳሌ አንድ ሰው ስለ አምላካችን መጥፎ ነገር ቢናገር ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ቢያጣጥል ምን እናደርጋለን? ይሖዋ መንፈሱን እንዲሁም በገርነት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል። ይሁንና ምላሽ የሰጠንበት መንገድ ጥሩ እንዳልነበረ በኋላ ላይ ብንገነዘብስ? ስለ ጉዳዩ በድጋሚ መጸለይ እንዲሁም ሌላ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ምላሽ መስጠት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማሰብ እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ቁጣችንን መቆጣጠርና ገርነት ማሳየት እንድንችል ቅዱስ መንፈሱን ይሰጠናል።
7. አንዳንድ ጥቅሶችን ማስታወሳችን በተፈታታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ራሳችንን ለመቆጣጠር የሚረዳን እንዴት ነው? (ምሳሌ 15:1, 18)
7 ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን አንደበታችንን እንድንቆጣጠር የሚረዱን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። የአምላክ መንፈስ እነዚህን ጥቅሶች እንድናስታውስ ሊረዳን ይችላል። (ዮሐ. 14:26) ለአብነት ያህል፣ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ገር እንድንሆን ይረዱናል። (ምሳሌ 15:1, 18ን አንብብ።) የምሳሌ መጽሐፍ በሚፈታተኑ ሁኔታዎች ውስጥ ራሳችንን መቆጣጠራችን ያለውን ጥቅምም ይገልጻል።—ምሳሌ 10:19፤ 17:27፤ 21:23፤ 25:15
ጥልቅ ማስተዋል ገርነት እንድናሳይ የሚረዳን እንዴት ነው?
8. አንድ ሰው ስለምናምንበት ነገር ጥያቄ እንዲጠይቅ ያነሳሳው ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰባችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
8 ገርነት እንድናሳይ የሚረዳን ሌላው ነገር ጥልቅ ማስተዋል ነው። (ምሳሌ 19:11) ጥልቅ ማስተዋል ያለው ሰው ሌሎች እምነቱን በተመለከተ በጥያቄ ሲያፋጥጡት ራሱን ይቆጣጠራል። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜ ከጥያቄያቸው በስተ ጀርባ ሌላ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ምላሽ ከመስጠታችን በፊት ግለሰቡ ያንን ጥያቄ እንዲጠይቅ ያነሳሳውን ምክንያት ላናውቅ እንደምንችል መገንዘብ ይኖርብናል።—ምሳሌ 16:23
9. ጌድዮን ለኤፍሬም ሰዎች ምላሽ በሰጠበት ወቅት ጥልቅ ማስተዋል እንዳለውና ገር እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?
9 ጌድዮን ለኤፍሬም ሰዎች የሰጠውን ምላሽ እንደ ምሳሌ እንመልከት። የኤፍሬም ሰዎች ጌድዮን ከአምላክ ጠላቶች ጋር ለመዋጋት ሲወጣ ያልጠራቸው ለምን እንደሆነ በቁጣ ጠየቁት። ይሁንና ይህን ያህል የተበሳጩት ለምንድን ነው? ክብራቸው እንደተነካ ስለተሰማቸው ይሆን? ያም ሆነ ይህ፣ ጌድዮን ስሜታቸውን ለመረዳት ጥረት በማድረግ በገርነት ምላሽ ሰጥቷቸዋል። ውጤቱስ ምን ሆነ? “ቁጣቸው በረደ።”—መሳ. 8:1-3
10. ስለ እምነታችን ጥያቄ ለሚያነሱ ሰዎች እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለብን ለመወሰን የሚረዳን ምንድን ነው? (1 ጴጥሮስ 3:15)
10 ለምሳሌ አንድ የሥራ ባልደረባችን ወይም አብሮን የሚማር ልጅ ከምንከተላቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር በተያያዘ ጥያቄ አነሳ እንበል። የግለሰቡን አመለካከት እንደምናከብር በሚያሳይ መንገድ ለእምነታችን ጥብቅና ለመቆም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። (1 ጴጥሮስ 3:15ን አንብብ።) ጥያቄውን እንደ ትችት ከመቁጠር ይልቅ የግለሰቡን አመለካከት ለማወቅ እንደሚረዳን መንገድ አድርገን መመልከታችን ብዙውን ጊዜ ሊጠቅመን ይችላል። ግለሰቡ ጥያቄውን ያነሳበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን በገርነትና በደግነት ምላሽ መስጠታችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ያለ ምላሽ መስጠታችን አመለካከቱን መለስ ብሎ እንዲያጤን ሊያነሳሳው ይችላል። የሚያነጋግረን ትሕትና በጎደለው ወይም አሽሙር በሚንጸባረቅበት መንገድ ቢሆንም እንኳ ምንጊዜም በደግነት ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።—ሮም 12:17
11-12. (ሀ) አንድን አስቸጋሪ ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ምን ነገሮችን ከግምት ልናስገባ እንችላለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) ሌሎች የሚያነሱት ጥያቄ ለውይይት በር ሊከፍት እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
11 ለምሳሌ የሥራ ባልደረባችን ልደት የማናከብረው ለምን እንደሆነ ቢጠይቀን ከጥያቄው በስተ ጀርባ ያለው ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? መዝናናት እንደማይፈቀድልን አስቦ ይሆን? ወይም ደግሞ ልደት አለማክበራችን በሥራ ቦታችን ያለውን የወዳጅነት መንፈስ እንደሚያደፈርስ ተሰምቶት ይሆን? በመጀመሪያ ግለሰቡ ለሥራ ባልደረቦቹ አሳቢነት በማሳየቱ ልናመሰግነው እንዲሁም በሥራ ቦታችን የወዳጅነት መንፈስ እንዲሰፍን እንደምንፈልግ ልንነግረው እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን አእምሮውን ክፍት አድርጎ እንዲያዳምጠንና መጽሐፍ ቅዱስ ከልደት ጋር በተያያዘ ምን እንደሚል ጥሩ ውይይት እንድናደርግ መንገድ ሊከፍት ይችላል።
12 ሌሎች አከራካሪ ጉዳዮች በሚነሱበት ጊዜም ተመሳሳይ ዘዴ ልንጠቀም እንችላለን። ለምሳሌ አብሮን የሚማር ልጅ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ግብረ ሰዶም ያላቸውን አመለካከት መቀየር እንዳለባቸው ይናገር ይሆናል። ይህን ያለው ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳተ አመለካከት ስላለው ይሆን? ወይም ደግሞ ግብረ ሰዶማዊ የሆነ ጓደኛ ወይም ዘመድ ይኖረው ይሆን? ግብረ ሰዶማዊ ለሆኑ ሰዎች ጥላቻ እንዳለን አስቦ ይሆን? ለሁሉም ሰዎች ፍቅር እንዳለን እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ያለውን የራሱን ምርጫ የማድረግ መብት እንደምናከብር ለልጁ ብንገልጽለት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። c (1 ጴጥ. 2:17) ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መከተል ስላለው ጥቅም ልንነግረው እንችል ይሆናል።
13. አንድ ሰው በአምላክ ማመን ሞኝነት እንደሆነ ቢናገር እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?
13 አንድ ሰው ስለ አንድ ጉዳይ ሽንጡን ገትሮ ቢከራከረን ግለሰቡ ምን ብሎ እንደሚያምን እናውቃለን ብለን ለመደምደም መቸኮል የለብንም። (ቲቶ 3:2) ለምሳሌ አብሮህ የሚማር ልጅ በአምላክ ማመን ሞኝነት እንደሆነ ቢናገርስ? ልጁ በዝግመተ ለውጥ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለውና ስለ ዝግመተ ለውጥ ብዙ እንደሚያውቅ ልታስብ ይገባል? እንደ እውነቱ ከሆነ ስለ ጉዳዩ እምብዛም አስቦበት አያውቅ ይሆናል። ስለ ሳይንስ ክርክር ከመጀመር ይልቅ ልጁ በኋላ ላይ የሚያስብበት ነገር ጣል ልታደርግ ትችል ይሆናል። ምናልባትም ከjw.org ላይ ስለ ፍጥረት የሚናገር ሐሳብ እንዲመለከት ልትጋብዘው ትችላለህ። ከጊዜ በኋላ፣ እዚያ ላይ በሚገኝ ቪዲዮ ወይም ርዕስ ላይ ለመወያየት ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም አክብሮት በተሞላበት መንገድ መናገርህ አመለካከቱን መለስ ብሎ እንዲያጤን ሊያነሳሳው ይችላል።
14. ኒል አብሮት የሚማር ልጅ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያለውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያርም ለመርዳት ድረ ገጻችንን ጥሩ አድርጎ የተጠቀመበት እንዴት ነው?
14 ኒል የተባለ ወጣት ሌሎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያርሙ ለመርዳት ድረ ገጻችንን ተጠቅሞበታል። እንዲህ ብሏል፦ “ክፍሌ ውስጥ ያለ አንድ ልጅ በሳይንስ እንደማላምን ከዚህ ይልቅ በተረት የተሞላ መጽሐፍ እንደማምን ይናገር ነበር።” ኒል ስለ እምነቱ ሊያስረዳው ቢሞክርም ልጁ እሱን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም። በመሆኑም ኒል፣ ልጁ jw.org ላይ የሚገኘውን “ሳይንስ እና መጽሐፍ ቅዱስ” የሚለውን ክፍል እንዲመለከት ጋበዘው። በኋላ ላይ ኒል፣ ልጁ ድረ ገጻችንን እንደተመለከተ የሚጠቁም ነገር አስተዋለ፤ በተጨማሪም ልጁ ስለ ሕይወት አመጣጥ ለመወያየት ፈቃደኛ ሆነ። አንተም ተመሳሳይ ውጤት ታገኝ ይሆናል።
በቤተሰብ ደረጃ ተዘጋጁ
15. ልጆች በገርነት ምላሽ እንዲሰጡ ማሠልጠን የሚቻለው እንዴት ነው?
15 ልጆች አንድ ሰው የሚያምኑበትን ነገር በተመለከተ በጥያቄ ቢያፋጥጣቸው በገርነት መልስ መስጠት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ወላጆቻቸው ሊያሠለጥኗቸው ይችላሉ። (ያዕ. 3:13) አንዳንድ ወላጆች በቤተሰብ አምልኮ ወቅት የልምምድ ፕሮግራም ያካሂዳሉ። በትምህርት ቤት ውስጥ ሊነሱ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ይመርጣሉ፤ መልስ መስጠት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ይወያያሉ እንዲሁም ይለማመዳሉ፤ በተጨማሪም ልጆቻቸው ገርነት በሚንጸባረቅበትና ማራኪ በሆነ መንገድ መናገር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ያሠለጥኗቸዋል።—“ የልምምድ ፕሮግራም ቤተሰባችሁን ሊጠቅመው ይችላል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
16-17. የልምምድ ፕሮግራም ወጣቶችን ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው?
16 ክርስቲያኖች ልምምድ ማድረጋቸው አሳማኝ የሆኑ ማስረጃዎችን ለማቅረብ እንዲሁም የሚያምኑባቸው ነገሮች ጠንካራ መሠረት እንዳላቸው ራሳቸውን ለማሳመን ይረዳቸዋል። jw.org ላይ “የወጣቶች ጥያቄ” የሚል ዓምድና ለወጣቶች የተዘጋጁ የመልመጃ ሣጥኖች አሉ። እነዚህ መልመጃዎች የተዘጋጁት ወጣቶች እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ እንዲሁም በራሳቸው አባባል መልስ ለመስጠት እንዲዘጋጁ ለመርዳት ታስበው ነው። በቤተሰብ ደረጃ ይህን ክፍል ማጥናታችን ሁላችንም ገርነት በሚንጸባረቅበትና ማራኪ በሆነ መንገድ ለእምነታችን ጥብቅና እንድንቆም ሊረዳን ይችላል።
17 ማቲው የተባለ ወጣት እንዲህ ያሉት የልምምድ ፕሮግራሞች የረዱት እንዴት እንደሆነ ተናግሯል። ማቲውና ወላጆቹ በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ ትምህርት ቤት ውስጥ ሊነሱ ስለሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ምርምር ያደርጋሉ። ማቲው እንዲህ ብሏል፦ “ምን ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመኝ እንደሚችል እናስባለን። ከዚያም ባደረግነው ምርምር ላይ ተመሥርተን ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት እንደምችል እንለማመዳለን። አንድን አቋም እንድይዝ ያደረጉኝን ምክንያቶች በግልጽ ማወቄ ድፍረት እንዲኖረኝ ይረዳኛል፤ እንዲሁም ለሌሎች በገርነት ምላሽ መስጠት ቀላል እንዲሆንልኝ ያደርጋል።”
18. ቆላስይስ 4:6 የምንን አስፈላጊነት ይናገራል?
18 እርግጥ ነው፣ አሳማኝ ማስረጃ ብናቀርብም እንኳ አንዳንዶቹ አድማጮች ላይቀበሉን ይችላሉ። ያም ቢሆን በዘዴና በገርነት መናገራችን ጠቃሚ ነው። (ቆላስይስ 4:6ን አንብብ።) ስለ እምነታችን መናገር ኳስ ከመወርወር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ኳሱን ቀስ ብለን ልናቀብል ወይም በኃይል ልንወረውር እንችላለን። ኳሱን ቀስ አድርገን ከወረወርነው ሌላኛው ተጫዋች ኳሱን ተቀብሎ ጨዋታውን የመቀጠሉ አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። በተመሳሳይም በዘዴና በገርነት የምንናገር ከሆነ ሰዎች እኛን ለማዳመጥና ውይይቱን ለመቀጠል ይበልጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ፍላጎቱ በክርክር ማሸነፍ ወይም በእምነታችን ላይ ማሾፍ ብቻ ከሆነ ለግለሰቡ ምላሽ የመስጠት ግዴታ የለብንም። (ምሳሌ 26:4) ይሁንና እንዲህ የሚያደርጉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። አንዳንዶች ምናልባትም ብዙዎች ለመስማት ፈቃደኛ መሆናቸው አይቀርም።
19. ለእምነታችን ጥብቅና በምንቆምበት ጊዜ ገርነት እንድናሳይ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
19 በእርግጥም ገርነትን ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ ነው። አከራካሪ ጥያቄ ሲቀርብልህ ወይም ተገቢ ያልሆነ ትችት ሲሰነዘርብህ ገር ለመሆን የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ገርነት ማሳየትህ የአመለካከት ልዩነቶች ወደ ጭቅጭቅ እንዳይሻገሩ ሊያደርግ እንደሚችል አስታውስ። በተጨማሪም ገርነትና አክብሮት የሚንጸባረቅበት ምላሽ መስጠትህ አንዳንድ ሰዎች ስለ እኛም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ስለ እምነትህ ‘መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ሁን፤ ይህን ስታደርግ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።’ (1 ጴጥ. 3:15) እንግዲያው፣ ገር በመሆን ጥንካሬህን አሳይ!
መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ
a ሌሎች የሚያበሳጭ ነገር ሲናገሩን ወይም በጥያቄ ሲያፋጥጡን በገርነት ለእምነታችን ጥብቅና መቆም የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይህ ርዕስ ያብራራል።
b ስሙ ተቀይሯል።
c ጠቃሚ ሐሳቦችን ለማግኘት በ2016 ንቁ! ቁጥር 4 ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም ምን ይላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d jw.org ላይ “የወጣቶች ጥያቄ” እና “ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች” በሚሉት ዓምዶች ሥር ጠቃሚ ሐሳቦችን ማግኘት ትችላላችሁ።