በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 36

መዝሙር 89 ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ

“ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ”

“ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ”

“ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ . . . ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ።”ያዕ. 1:22

ዓላማ

ይህ የጥናት ርዕስ፣ የአምላክን ቃል በየዕለቱ ለማንበብ እንዲሁም ስላነበብነው ነገር ለማሰብና በሕይወታችን ይበልጥ ተግባራዊ ለማድረግ ያነሳሳናል።

1-2. የአምላክ አገልጋዮች ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው? (ያዕቆብ 1:22-25)

 ይሖዋ እና የሚወደው ልጁ ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋሉ። የመዝሙር 119:2 ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፦ “ማሳሰቢያዎቹን የሚጠብቁ፣ እሱን በሙሉ ልባቸው የሚፈልጉ ደስተኞች ናቸው።” ኢየሱስም “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” በማለት ተጨማሪ ማረጋገጫ ሰጥቷል።—ሉቃስ 11:28

2 እኛ የይሖዋ አገልጋዮች ደስተኛ ሕዝብ ነን። ለምን? ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ አንዱ ምክንያት ግን የአምላክን ቃል አዘውትረን ማንበባችንና የተማርነውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ማድረጋችን ነው።—ያዕቆብ 1:22-25ን አንብብ።

3. በአምላክ ቃል ላይ ያነበብነውን ነገር ተግባራዊ ማድረጋችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

3 ‘ቃሉን የምናደርግ መሆናችን’ በብዙ መንገዶች ይጠቅመናል። አንደኛ፣ ከአምላክ ቃል የተማርነውን ነገር ተግባራዊ ስናደርግ ይሖዋን እናስደስተዋለን። ይህን ማወቃችን ደግሞ እኛን ያስደስተናል። (መክ. 12:13) በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ላይ ያነበብነውን ነገር በተግባር ስናውል የቤተሰብ ሕይወታችን ይሻሻላል፤ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለን ወዳጅነትም ይጠናከራል። አንተም ይህን በሕይወትህ ተመልክተኸው ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ፣ የይሖዋን መመሪያዎች የማይከተሉ ሰዎች ከሚደርሱባቸው ብዙ ችግሮች እንጠበቃለን። ንጉሥ ዳዊት ከተናገረው ሐሳብ ጋር እንደምንስማማ ጥያቄ የለውም። ዳዊት በመዝሙሩ ላይ ስለ ይሖዋ ሕግ፣ መመሪያዎችና ፍርዶች ከጠቀሰ በኋላ “እነሱን መጠበቅ ትልቅ ወሮታ አለው” ብሏል።—መዝ. 19:7-11

4. የአምላክን ቃል ተግባራዊ ማድረግ ቀላል ያልሆነው ለምንድን ነው?

4 የአምላክን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ፣ ይሖዋ ከእኛ ምን እንደሚፈልግብን ለማወቅ በሚያስችል መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናት ይኖርብናል። ሆኖም ፕሮግራማችን የተጣበበ ስለሆነ ለዚህ የሚሆን ጊዜ ማግኘት ቀላል አይደለም። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ለማንበብ የሚረዱንን አንዳንድ ነጥቦች እንመልከት። በተጨማሪም ስላነበብነው ነገር ቆም ብለን ለማሰብ ምን ሊረዳን እንደሚችል እንዲሁም ያገኘነውን ትምህርት እንዴት በተግባር ማዋል እንደምንችል እንመረምራለን።

የአምላክን ቃል ለማንበብ ጊዜ መድብ

5. ጊዜ የሚጠይቁ ምን ምን ኃላፊነቶች አሉብን?

5 አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች ጊዜያቸው የተጣበበ ነው። ጊዜ የሚጠይቁ የተለያዩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶች አሉብን። ለምሳሌ አብዛኞቻችን ራሳችንንም ሆነ ቤተሰባችንን ለማስተዳደር ሰብዓዊ ሥራ እንሠራለን። (1 ጢሞ. 5:8) ብዙ ክርስቲያኖች የታመሙ ወይም በዕድሜ የገፉ የቤተሰባቸውን አባላት ይንከባከባሉ። እንዲሁም ሁላችንም የራሳችንን ጤና መንከባከብ አለብን፤ ይህም ጊዜ የሚጠይቅ ነገር ነው። ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች በተጨማሪ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶች አሉብን። በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል ትልቁ ኃላፊነታችን ነው። ታዲያ ይህ ሁሉ ኃላፊነት እያለብህ የአምላክን ቃል አዘውትረህ ለማንበብ፣ ለማሰላሰልና የተማርከውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ ልታገኝ የምትችለው እንዴት ነው?

6. ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ቅድሚያ ለመስጠት ምን ይረዳሃል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ለክርስቲያኖች ‘ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች’ መካከል አንዱ ነው፤ ስለዚህ ቅድሚያ ልንሰጠው ይገባል። (ፊልጵ. 1:10) የመጀመሪያው መዝሙር ስለ ደስተኛ ሰው ሲናገር “በይሖዋ ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል” ይላል። (መዝ. 1:1, 2) ይህ ጥቅስ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጊዜ መመደብ እንዳለብን በግልጽ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ የትኛው ነው? መልሱ ከሰው ሰው የተለያየ ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር፣ አዘውትረን ለማንበብ የሚቀለንን ጊዜ መምረጣችን ነው። ቪክቶር የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን ጠዋት ላይ ማድረግ ደስ ይለኛል። እርግጥ የጠዋት ሰው አይደለሁም፤ ግን በዚህ ሰዓት ትኩረት የሚከፋፍሉ ብዙ ነገሮች የሉም። አእምሮዬ ነፃ ስለሚሆን ትኩረቴን መሰብሰብ እችላለሁ።” ይህ ሐሳብ ለአንተም ይሠራል? ‘ለእኔ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ የትኛው ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ የትኛው ነው? አዘውትረህ ለማንበብ የሚቀልህ መቼ ብታነብ ነው? (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)


ስለምታነበው ነገር አስብ

7-8. ከንባባችን የተሟላ ጥቅም እንዳናገኝ እንቅፋት ሊሆንብን የሚችለው ምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

7 በአብዛኛው እንደሚስተዋለው፣ መልእክቱን ከራሳችን ጋር ሳናዋህደው ረጅም ንባብ ልናነብ እንችላለን። አንድ ነገር አንብበህ ብዙም ሳይቆይ ያነበብከውን ነገር ማስታወስ አቅቶህ ያውቃል? ይህ ሁላችንንም የሚያጋጥመን ነገር ነው። ካልተጠነቀቅን ይህ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብም ሊከሰት ይችላል። ምናልባት በየቀኑ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎችን ለማንበብ ግብ አውጥተን ይሆናል። ይህ የሚበረታታ ነገር ነው። ግብ ማውጣትና ግባችን ላይ ለመድረስ መጣር አለብን። (1 ቆሮ. 9:26) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጥሩ እርምጃ ነው፤ ግን የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን የተሟላ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ ይኖርብናል።

8 ለንጽጽር ያህል አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በዝናብ መልክ የሚወርደው ውኃ ለሕይወት በጣም አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዘነበ መሬቱ ይጥለቀለቃል። እንዲህ ያለው ዝናብ ጠቃሚ ሊሆን አይችልም። ውኃው መሬት ውስጥ ሰርጎ እንዲገባና ተክሎችን መጥቀም እንዲችል ጊዜ ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በችኮላ ካነበብን መልእክቱን መረዳት፣ ማስታወስና በሥራ ላይ ማዋል እንቸገራለን።—ያዕ. 1:24

የዝናብ ውኃ አፈር ውስጥ ሰርጎ እንዲገባና ለተክሎች እንዲጠቅም ከተፈለገ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ሁሉ እኛም ከአምላክ ቃል ስላነበብነው ነገር ለማሰብና ተግባራዊ የምናደርግበትን አቅጣጫ ለማስተዋል ጊዜ ያስፈልገናል (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)


9. መጽሐፍ ቅዱስን በችኮላ የማንበብ ልማድ ካለን ምን ልናደርግ ይገባል?

9 አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን የምታነበው በችኮላ እንደሆነ አስተውለህ ይሆን? ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ቀስ በል። በምታነብበት ወቅት ወይም ካነበብክ በኋላ፣ ስላነበብከው ነገር ቆም ብለህ ለማሰብ ጥረት አድርግ። ይህ ብዙም ከባድ ነገር አይደለም። ‘ማሰላሰል’ የሚለው ቃል ከባድ ሆኖ እንዲታይህ የሚያደርግ ከሆነ ነገሩን ቀለል አድርገህ ተመልከተው፤ ማሰላሰል ማለት ስላነበብከው ነገር ማሰብ ማለት ብቻ ነው። ለማሰብ ወይም ለማሰላሰል እንዲያስችልህ የምታጠናበትን ጊዜ ረዘም ልታደርግ ትችል ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ የምታነበውን ነገር ቀነስ አድርገህ የቀረውን ጊዜ ለማሰላሰል ልትጠቀምበት ትችላለህ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቪክቶር እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤ ብዙም ረጅም አይደለም፤ ምናልባትም አንድ ምዕራፍ ብቻ ሊሆን ይችላል። የማነበው በማለዳ ስለሆነ ቀኑን ሙሉ ስላነበብኩት ነገር ማሰብ እችላለሁ።” አንተ የምትጠቀምበት ዘዴ ምንም ይሁን ምን፣ ቁም ነገሩ ካነበብከው ነገር የተሟላ ጥቅም ለማግኘት በሚያስችልህ ፍጥነት ማንበብህ ነው።—መዝ. 119:97፤ “ እነዚህን ጥያቄዎች አስብባቸው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

10. ያገኘኸውን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (1 ተሰሎንቄ 5:17, 18)

10 መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ማድረግ ያለብህ ሌላው ነገር ትምህርቱን ተግባራዊ የምታደርግባቸውን መንገዶች መፈለግ ነው። የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ካነበብክ በኋላ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በአሁኑ ወቅት ወይም በቅርቡ ይህን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ 1 ተሰሎንቄ 5:17, 18 ያካተተ ነው እንበል። (ጥቅሱን አንብብ።) ይህን ጥቅስ ካነበብክ በኋላ ስለ ጸሎት ልማድህ ቆም ብለህ ልታስብ ትችላለህ። ምን ያህል አዘውትረህ ትጸልያለህ? ጸሎትህስ ምን ያህል ጥልቀት ያለው ነው? ልታስብበት የምትችለው ሌላው ነገር ደግሞ ‘ስለ የትኞቹ ነገሮች አመስጋኝ መሆን እችላለሁ?’ የሚለው ነው። ምናልባት ሦስት ነገሮችን ጠቅሰህ ይሖዋን ለማመስገን ልትወስን ትችላለህ። ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ እንኳ ትኩረትህን ሰብስበህ ማሰብህ የአምላክን ቃል የምትሰማና የምታደርግ እንድትሆን የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ አስተዋልክ? በየዕለቱ ከምታደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጋር በተያያዘ ይህንኑ ብታደርግ ምን ያህል ልትጠቀም እንደምትችል እስቲ አስበው! አዎ፣ የአምላክን ቃል በማድረግ ረገድ እየተሻሻልክ ትሄዳለህ። ይሁንና ልትሠራባቸው የሚገቡ ብዙ ነጥቦች እንዳሉ ቢሰማህስ?

ምክንያታዊ ግቦች አውጣ

11. አንዳንድ ጊዜ ምን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሊያጋጥምህ ይችላል? ምሳሌ ስጥ።

11 መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብና ምክሩን ተግባራዊ ስለማድረግ ስታስብ አንዳንድ ጊዜ ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ለምሳሌ የዛሬው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ አድልዎን ስለማስወገድ የሚናገር ምክር የያዘ ይሆናል። (ያዕ. 2:1-8) ሌሎችን የምትይዝበትን መንገድ ማስተካከል እንደሚያስፈልግህ ትገነዘብና አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ ትወስናለህ። በጣም ጥሩ! የነገው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ደግሞ አንደበትን መቆጣጠር ስላለው አስፈላጊነት የሚያጎላ ነው። (ያዕ. 3:1-12) ንግግርህ በተወሰነ መጠን አሉታዊ እንደሆነ ትረዳ ይሆናል። ስለዚህ አነጋገርህ አዎንታዊና የሚያንጽ እንዲሆን ለማድረግ ግብ ታወጣለህ። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ የዓለም ወዳጅ መሆንን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ይዟል። (ያዕ. 4:4-12) በመዝናኛ ምርጫህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብህ ትገነዘባለህ። በአራተኛው ቀን፣ ልትሠራባቸው የሚገቡ ነጥቦችን ብዛት ስታስብ ሁኔታው ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል።

12. መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ በብዙ አቅጣጫዎች ማስተካከያ ማድረግ እንዳለብህ ከተገነዘብክ ተስፋ መቁረጥ የሌለብህ ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

12 በብዙ አቅጣጫዎች ማስተካከያ ማድረግ እንዳለብህ ከተሰማህ ተስፋ አትቁረጥ። ይህ ጥሩ የልብ ዝንባሌ እንዳለህ የሚጠቁም ነገር ነው። ትሑትና ለራሱ ሐቀኛ የሆነ ሰው ቅዱሳን መጻሕፍትን የሚያነበው ማሻሻያ ለማድረግ ብሎ ነው። a “አዲሱን ስብዕና” መልበስ ቀጣይ የሆነ ሂደት እንደሆነም አስታውስ። (ቆላ. 3:10) የአምላክን ቃል ማድረግህን ለመቀጠል ምን ሊረዳህ ይችላል?

13. ምክንያታዊ የሆኑ ግቦች ልታወጣ የምትችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 ያነበብከውን ነገር ሁሉ በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ጥቂት ግቦችን ብቻ አውጣ። (ምሳሌ 11:2) እንዲህ ልታደርግ ትችላለህ፦ ልትሠራባቸው የምትፈልጋቸውን ነገሮች ዘርዝረህ ጻፍ፤ ከዚያም አንዱን ወይም ሁለቱን ብቻ መርጠህ በመጀመሪያ በእነሱ ላይ ሥራ። የቀሩትን በጊዜ ሂደት ልትሠራባቸው ትችላለህ። ታዲያ ከየትኛው ብትጀምር ይሻላል?

ከመጽሐፍ ቅዱስ ያነበብከውን ነገር ሁሉ በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ለምን ምክንያታዊ ግቦች አታወጣም? ምናልባት በአንድ ወይም በሁለት ነጥቦች ላይ ልታተኩር ትችላለህ (አንቀጽ 13-14⁠ን ተመልከት)


14. ከየትኞቹ ግቦች መጀመር ትችላለህ?

14 በቀላሉ ከምትደርስበት ግብ ልትጀምር ትችላለህ። ወይም ይበልጥ ማሻሻያ ልታደርግበት በሚገባው ግብ ልትጀምር ትችላለህ። ልትሠራበት የምትፈልገውን ግብ ከመረጥክ በኋላ ስለ ጉዳዩ በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አድርግ፤ ምናልባትም የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍትን ወይም የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮችን ልትጠቀም ትችል ይሆናል። ስለ ግብህ ጸልይ፤ ‘ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎትም ሆነ ኃይል’ እንዲሰጥህ ይሖዋን ጠይቀው። (ፊልጵ. 2:13) ከዚያም የተማርከውን ተግባራዊ አድርግ። የመጀመሪያው ግብህ እንደተሳካልህ ስታይ በሌሎች ግቦችህ ላይ ለመሥራት ያለህ ፍላጎትም ይጨምራል። ደግሞም በአንድ የክርስቲያናዊ ሕይወት መስክ ወይም ባሕርይ ረገድ ማሻሻያ ስታደርግ በሌሎች አቅጣጫዎች ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እየቀለለህ ይሄዳል።

የአምላክ ቃል ‘በአንተ ላይ እንዲሠራ’ ፍቀድ

15. የይሖዋ ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያነቡ ሌሎች ብዙ ሰዎች የሚለዩት እንዴት ነው? (1 ተሰሎንቄ 2:13)

15 አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ደጋግመው እንዳነበቡት ይናገራሉ። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ያምናሉ ሊባል ይችላል? ምክሮቹን ተግባራዊ ያደርጋሉ? ወይም ቃሉ ሕይወታቸውን እንዲመራላቸው ፈቅደዋል? የሚያሳዝነው፣ በአብዛኛው ሁኔታው እንደዚህ አይደለም። የአምላክ ሕዝቦች ግን ከዚህ በጣም የተለዩ ናቸው። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን “እንደ አምላክ ቃል [አድርገን]” ተቀብለነዋል። ከዚህም ሌላ በእኛ ላይ እየሠራ እንደሆነ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን።—1 ተሰሎንቄ 2:13ን አንብብ።

16. ቃሉን የምናደርግ እንድንሆን ምን ይረዳናል?

16 የአምላክን ቃል ማንበብና ተግባራዊ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ለማንበብ የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ልንቸገር እንችላለን። ወይም በችኮላ የማንበብ ልማድ ይኖረን ይሆናል፤ ይህም መልእክቱ ወደ ልባችን ጠልቆ እንዳይገባ እንቅፋት ይሆንብናል። ወይም ማድረግ ስላለብን ማሻሻያዎች ስናስብ ሁኔታው ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ያጋጠመህ ፈታኝ ሁኔታ ምንም ዓይነት ቢሆን ልትወጣው የማትችለው አይደለም። በይሖዋ እርዳታ ልታሸንፈው ትችላለህ። የእሱን እርዳታ በመቀበል ቃሉን የምናደርግ እንጂ ሰምተን የምንረሳ እንዳንሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የአምላክን ቃል ባነበብንና በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ባደረግነው መጠን ይበልጥ ደስተኞች እንደምንሆን ምንም ጥርጥር የለውም።—ያዕ. 1:25

መዝሙር 94 ለአምላክ ቃል አመስጋኝ መሆን

a እኩዮችህ ምን ይላሉ?—መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የተሰኘውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት።