በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 39

መዝሙር 125 “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው”

በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ አጣጥም

በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ አጣጥም

“ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”ሥራ 20:35

ዓላማ

በመስጠት መደሰት፣ እንዲያውም ደስታችንን መጨመር የምንችልባቸውን መንገዶች እንመለከታለን።

1-2. ይሖዋ ከመቀበል ይልቅ በመስጠት የበለጠ ደስታ እንድናገኝ አድርጎ የፈጠረን መሆኑ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

 ይሖዋ ሰዎችን የፈጠራቸው ከመቀበል ይልቅ በመስጠት የበለጠ ደስታ እንዲያገኙ አድርጎ ነው። (ሥራ 20:35) ይሁንና ይህ ሲባል መቀበል ምንም ደስታ አያስገኝም ማለት ነው? አይደለም። ሁላችንም ከተሞክሮ እንደምናውቀው ስጦታ ሲሰጠን ደስ ይለናል። የበለጠ የምንደሰተው ግን ለሌሎች በምንሰጥበት ጊዜ ነው። ደግሞም ይሖዋ በዚህ መንገድ የፈጠረን መሆኑ ይጠቅመናል። እንዴት?

2 ይሖዋ በዚህ መልኩ ስለፈጠረን ደስታችን በተወሰነ መጠንም ቢሆን በእኛው እጅ ነው። ለሌሎች ለመስጠት የሚያስችሉ ተጨማሪ አጋጣሚዎችን በመፈለግ ደስታችንን ማሳደግ እንችላለን። ይሖዋ በዚህ መልኩ የፈጠረን መሆኑ አስደናቂ አይደለም?—መዝ. 139:14

3. ይሖዋ “ደስተኛው አምላክ” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?

3 ቅዱሳን መጻሕፍት መስጠት ደስታ እንደሚያስገኝ ይናገራሉ፤ በመሆኑም ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ደስተኛው አምላክ” ተብሎ መጠራቱ አያስገርምም። (1 ጢሞ. 1:11) የመጀመሪያውም ሆነ ከሁሉ የላቀው ሰጪ እሱ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው።” (ሥራ 17:28) በእርግጥም “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” ከይሖዋ ነው።—ያዕ. 1:17

4. በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ይበልጥ ለማጣጣም ምን ይረዳናል?

4 ሁላችንም በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ይበልጥ ማጣጣም እንደምንፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። የይሖዋን ልግስና መኮረጃችን ይህን ለማድረግ ይረዳናል። (ኤፌ. 5:1) በዚህ ርዕስ ውስጥ የይሖዋን ግሩም ምሳሌ እንመለከታለን። በተጨማሪም ላደረግነው መልካም ነገር ባንመሰገን ምን ማድረግ እንደምንችል እናያለን። እነዚህ ማሳሰቢያዎች፣ በመስጠት ደስታ ለማግኘት አልፎ ተርፎም ደስታችንን ለማሳደግ ይረዱናል።

የይሖዋን ልግስና ኮርጅ

5. ይሖዋ የትኞቹን ቁሳዊ ነገሮች ይሰጠናል?

5 ይሖዋ ልግስና የሚያሳየው እንዴት ነው? አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ቁሳዊ ነገሮችን ይሰጠናል። የተንደላቀቀ ሕይወት ባንመራም እንኳ ይሖዋ የሚያስፈልጉን ነገሮች እንዲሟሉልን ያደርጋል። ለምሳሌ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንድናገኝ ይረዳናል። (መዝ. 4:8፤ ማቴ. 6:31-33፤ 1 ጢሞ. 6:6-8) ይሖዋ የሚያስፈልገንን ቁሳዊ ነገር የሚያሟላልን ግዴታ እንዳለበት ስለሚሰማው ብቻ ነው? በፍጹም! ታዲያ ለምንድን ነው?

6. ከማቴዎስ 6:25, 26 ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች የሚያሟላልን ስለሚወደን ነው። ኢየሱስ በማቴዎስ 6:25, 26 ላይ ምን እንዳለ ልብ በል። (ጥቅሱን አንብብ።) በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ ተፈጥሮን እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። ስለ ወፎች ሲናገር “አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም” ብሏል። ሆኖም ቀጥሎ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል።” ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ በማለት ጠየቀ፦ “ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?” ነጥቡ ምንድን ነው? ለይሖዋ አገልጋዮቹ ከእንስሳት እጅግ ይበልጡበታል። ይሖዋ እንስሳት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያሟላላቸው ከሆነ ለእኛማ እንዴት አብልጦ አያደርግ! አሳቢ የሆኑ አባቶች እንደሚያደርጉት ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ቤተሰቡን ይንከባከባል።—መዝ. 145:16፤ ማቴ. 6:32

7. የይሖዋን ልግስና መኮረጅ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 እኛም እንደ ይሖዋ በፍቅር ተነሳስተን ለሌሎች ቁሳዊ ነገሮችን መስጠት እንችላለን። ለምሳሌ ምግብ ወይም ልብስ የሚያስፈልገው ክርስቲያን ታውቃለህ? ይሖዋ ይህ አገልጋዩ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ሊጠቀምብህ ይችላል። የይሖዋ ሕዝቦች በተለይ አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ ልግስና በማሳየታቸው ይታወቃሉ። ለምሳሌ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ወንድሞችና እህቶች ለተቸገሩ ወንድሞቻቸው ምግብ፣ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶችን ሰጥተዋል። በተጨማሪም ብዙዎች ለዓለም አቀፉ ሥራ በልግስና መዋጮ አድርገዋል። ይህ መዋጮ በዓለም ዙሪያ የእርዳታ ሥራ ለማከናወን አስችሏል። እነዚህ ለጋስ ወንድሞችና እህቶች በዕብራውያን 13:16 ላይ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ አውለዋል፦ “መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታልና።”

ሁላችንም የይሖዋን የልግስና ምሳሌ መኮረጅ እንችላለን (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)


8. ይሖዋ ኃይል በመስጠት የሚረዳን እንዴት ነው? (ፊልጵስዩስ 2:13)

8 ይሖዋ ኃይል ይሰጣል። ይሖዋ ገደብ የለሽ ኃይሉን ታማኝ አገልጋዮቹን ለማበርታት ሲጠቀምበት ደስ ይለዋል። (ፊልጵስዩስ 2:13ን አንብብ።) አንድን ፈተና ለማሸነፍ ወይም አንድን መከራ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንዲሰጥህ ጸልየህ ታውቃለህ? አንዳንድ ጊዜ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን እንኳ ብርታት ያስፈልግህ ይሆናል። ኃይል ለማግኘት ያቀረብከው ጸሎት ሲመለስልህ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል፤ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”—ፊልጵ. 4:13

9. ኃይላችንን በምንጠቀምበት መንገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

9 እኛ የሰው ልጆች እንደ ይሖዋ ገደብ የለሽ ኃይል ባይኖረንም እንኳ ኃይላችንን በልግስና በመጠቀም ረገድ እሱን መምሰል እንችላለን። ለሌሎች ቃል በቃል ኃይል ወይም ብርታት መስጠት አንችልም። ሆኖም ኃይላችንን እነሱን ለመርዳት ልንጠቀምበት እንችላለን። ለምሳሌ በዕድሜ ለገፉ ወይም ለታመሙ ክርስቲያኖች ልንላላክላቸው ወይም የቤት ውስጥ ሥራ በመሥራት ልናግዛቸው እንችላለን። ሁኔታችን የሚፈቅድልን ከሆነ ደግሞ በስብሰባ አዳራሽ ጽዳት ወይም ጥገና ሥራ ለመካፈል ራሳችንን ማቅረብ እንችል ይሆናል። ኃይላችንን በእነዚህ መንገዶች መጠቀማችን ሌሎች የይሖዋ አገልጋዮችን ይጠቅማል።

ኃይላችንን ተጠቅመን ሌሎችን መርዳት እንችላለን (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)


10. ሌሎችን በንግግራችን ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ቃላትም ኃይል እንዳላቸው አትዘንጋ። አንድን ወንድም ወይም አንዲትን እህት ከልብ በማመስገን ልታበረታታቸው ትችል ይሆን? ማጽናኛ የሚያስፈልገው ሰው ታውቃለህ? ከሆነ፣ ቅድሚያውን ወስደህ ግለሰቡን ለማነጋገር ለምን አትሞክርም? በአካል ልትጠይቀው፣ ስልክ ልትደውልለት አሊያም ደግሞ ፖስት ካርድ፣ ኢሜይል ወይም የጽሑፍ መልእክት ልትልክለት ትችላለህ። የምትናገረው ነገር በደንብ የተቀነባበረ መሆን አያስፈልገውም። የእምነት አጋርህ ታማኝነቱን ጠብቆ ያንን ቀን እንዲያልፍ ወይም ስላለበት ሁኔታ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረው ለመርዳት ከልብ የመነጩ ጥቂት ቃላት ብቻ እንኳ በቂ ሊሆኑ ይችላሉ።—ምሳሌ 12:25፤ ኤፌ. 4:29

11. ይሖዋ ጥበቡን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

11 ይሖዋ ጥበብ ይሰጣል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ አምላክ ስህተት ሳይፈላልግ ለሁሉም በልግስና ይሰጣልና።” (ያዕ. 1:5 ግርጌ) እነዚህ ቃላት እንደሚያሳዩት ይሖዋ ጥበቡን አይሰስትም። ከዚህ ይልቅ ለሌሎች በልግስና ያካፍላል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ጥበብን የሚሰጠው “ማንንም ሳይነቅፍ” ወይም “ስህተት ሳይፈላልግ” እንደሆነ ልብ በል። የእሱ አመራር እንደሚያስፈልገን አምነን በመቀበላችን የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን አይፈልግም። እንዲያውም የእሱን አመራር እንድንጠይቅ አበረታቶናል።—ምሳሌ 2:1-6

12. ለሌሎች ጥበባችንን ለማካፈል የሚያስችል ምን አጋጣሚ አለን?

12 እኛስ ጥበባችንን ለሌሎች በማካፈል የይሖዋን ምሳሌ መከተል እንችል ይሆን? (መዝ. 32:8) የይሖዋ ሕዝቦች የተማሩትን ነገር ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችል ብዙ አጋጣሚ አላቸው። ለምሳሌ አዳዲስ አስፋፊዎችን በአገልግሎት ለማሠልጠን ብዙ አጋጣሚ እናገኛለን። ሽማግሌዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮችንና የተጠመቁ ወንድሞችን በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነት እንዴት መወጣት እንደሚችሉ በትዕግሥት ያሠለጥናሉ። በግንባታና በጥገና ሥራ ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያኖች ደግሞ እምብዛም ተሞክሮ የሌላቸውን ወንድሞች በቲኦክራሲያዊ ፕሮጀክቶች ላይ ያሠለጥናሉ።

13. ሌሎችን በምናሠለጥንበት ጊዜ ይሖዋ ጥበቡን የሚያካፍልበትን መንገድ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ሥልጠና የሚሰጡ ወንድሞች፣ ይሖዋ ጥበቡን የሚያካፍልበትን መንገድ መኮረጃቸው ጠቃሚ ነው። ይሖዋ ጥበብን የሚሰጠው በልግስና እንደሆነ አስታውስ። እኛም በተመሳሳይ ለምናሠለጥናቸው ሰዎች እውቀታችንን እና ተሞክሯችንን በልግስና ማካፈል ይኖርብናል። የምናሠለጥነው ሰው ሥራችንን እንዳይወስድብን በመስጋት እውቀታችንን መቆጠብ የለብንም። ወይም ደግሞ ‘እኔን ያሠለጠነኝ ማንም ሰው የለም። እሱም በራሱ ይማር!’ አንልም። እንዲህ ያለው አመለካከት በይሖዋ ሕዝቦች መሃል ቦታ የለውም። ከዚህ ይልቅ ለምናሠለጥናቸው ሰዎች እውቀታችንን ብቻ ሳይሆን “ራሳችንን ጭምር” በደስታ እንሰጣለን። (1 ተሰ. 2:8) እነሱም “በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱን [እንደሚያሟሉ]” ተስፋ እናደርጋለን። (2 ጢሞ. 2:1, 2) በዚህ መንገድ የማያቋርጥ የልግስና ዑደት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ እናበረክታለን፤ ይህ ደግሞ ለብዙዎች ደስታ ያስገኛል።

ለልግስናችን እንዳልተመሰገንን ሲሰማን

14. ብዙዎች ለልግስናችን ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣሉ?

14 በተለይ ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ልግስና ስናሳይ በአብዛኛው እነሱም በምላሹ አድናቆታቸውን ይገልጻሉ። የምስጋና ደብዳቤ ሊልኩልን ወይም በሌላ መንገድ ምስጋናቸውን ሊገልጹልን ይችላሉ። (ቆላ. 3:15) እንዲህ ያለው ምስጋና፣ በመስጠት ለምናገኘው ደስታ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

15. አንዳንዶች ለልግስናችን ባያመሰግኑን ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

15 እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ላያመሰግኑን ይችላሉ። ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ገንዘባችንን ተጠቅመን አንድን ሰው ለመርዳት ጥረት ካደረግን በኋላ ግለሰቡ ከቁብ እንዳልቆጠረው ሊሰማን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ደስታችንን እንዳናጣ ምን ይረዳናል? የጭብጡ ጥቅሳችን በሆነው በሐዋርያት ሥራ 20:35 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አስታውስ። በመስጠት የምናገኘው ደስታ የተመካው ተቀባዩ በሚሰጠው ምላሽ ላይ አይደለም። ሌሎች ባያመሰግኑንም እንኳ በመስጠት ደስታ ለማግኘት መምረጥ እንችላለን። እንዴት? አንዳንድ መንገዶችን እስቲ እንመልከት።

16. ለሌሎች በምንሰጥበት ጊዜ በምን ላይ ማተኮር ይኖርብናል?

16 ይሖዋን በመምሰል ላይ አተኩር። ይሖዋ ለሚያመሰግኑም ለማያመሰግኑም ሰዎች መልካም ነገሮችን ይሰጣል። (ማቴ. 5:43-48) ይሖዋ እኛም “በምላሹ ምንም [ሳንጠብቅ]” ለሰዎች ከሰጠን ‘ሽልማታችን ታላቅ እንደሚሆን’ ቃል ገብቶልናል። (ሉቃስ 6:35) “ምንም ሳትጠብቁ” የሚለው ሐሳብ ምስጋናንም ሊጨምር ይችላል። ሰዎች አመሰገኑንም አላመሰገኑን ይሖዋ በደስታ በመስጠታችን ብቻ ላደረግነው መልካም ነገር ወሮታችንን ይከፍለናል።—ምሳሌ 19:17፤ 2 ቆሮ. 9:7

17. የትኩረት አቅጣጫችንን ለማስተካከል ምን ይረዳናል? (ሉቃስ 14:12-14)

17 በሉቃስ 14:12-14 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት የትኩረት አቅጣጫችንን ለማስተካከል ይረዳናል። (ጥቅሱን አንብብ።) በምላሹ አንድ ነገር ሊያደርጉልን የሚችሉ ሰዎችን ቤታችን ብንጋብዝ ወይም በሌላ መንገድ ለእነሱ ልግስና ብናሳይ ምንም ስህተት የለውም። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ለሌሎች የምንሰጠው በምላሹ የሆነ ነገር መቀበል ፈልገን እንደሆነ ብናስተውልስ? ኢየሱስ የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ማዋላችን ይጠቅመናል። በምላሹ ምንም ነገር ሊሰጠን እንደማይችል ለምናውቀው ሰው ልግስና ማሳየት እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ይሖዋን እየመሰልን እንደሆነ ስለምናውቅ ደስተኞች እንሆናለን። እንዲህ ያለውን አመለካከት መያዛችን ሌሎች በማያመሰግኑን ጊዜም ደስታችንን ለመጠበቅ ይረዳናል።

18. ምን ብለን መደምደም አይኖርብንም? ለምንስ?

18 ሌሎች አመስጋኝ አይደሉም ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። (1 ቆሮ. 13:7) ሌሎች ባያመሰግኑን እንዲህ እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በእርግጥ ግለሰቡ አመስጋኝ ስላልሆነ ነው? ወይስ ማመስገን ስለረሳ ነው?’ ግለሰቡ የጠበቅነውን ምላሽ ያልሰጠበት ሌላም ምክንያት ሊኖር ይችላል። አንዳንዶች በልባቸው የአመስጋኝነት ስሜት ቢኖራቸውም ስሜታቸውን መግለጽ ሊከብዳቸው ይችላል። በተለይ ቀደም ሲል ሌሎችን የመርዳት ልማድ ከነበራቸው እርዳታ መቀበል ሊያሳፍራቸው ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ለሌሎች ክርስቲያናዊ ፍቅር ካለን ስለ እነሱ ቀና ቀናውን ማሰብ ይቀለናል፤ እንዲሁም በመስጠት ደስታ ማግኘት እንችላለን።—ኤፌ. 4:2

19-20. ለሌሎች በምንሰጥበት ጊዜ ትዕግሥት ማሳየት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

19 ታጋሽ ሁን። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን ልግስና ከማሳየት ጋር በተያያዘ እንዲህ ብሏል፦ “ቂጣህን በውኃ ላይ ጣል፤ ከብዙ ቀናት በኋላ መልሰህ ታገኘዋለህና።” (መክ. 11:1) እነዚህ ቃላት እንደሚያሳዩት አንዳንዶች ልግስና ካሳየናቸው “ከብዙ ቀናት በኋላ” ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። ይህን ነጥብ የሚያጎላ አንድ ተሞክሮ እንመልከት።

20 ከበርካታ ዓመታት በፊት፣ የአንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሚስት በቅርቡ ለተጠመቀች አንዲት እህት ደብዳቤ ጽፋላት ነበር፤ በደብዳቤዋ ላይ ታማኝነቷን እንድትጠብቅ አበረታታቻት። ከስምንት ዓመት ገደማ በኋላ እህት መልሳ ደብዳቤ ጻፈችላት፤ ደብዳቤው እንዲህ ይላል፦ “ደብዳቤ የጻፍኩልሽ፣ አንቺ ባታውቂውም ባለፉት ዓመታት ምን ያህል እንደረዳሽኝ ልነግርሽ ስለፈለግኩ ነው።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “[የጻፍሽልኝ ደብዳቤ] የሚያበረታታ ነበር፤ ግን ልቤን የነካው የጠቀስሽው ጥቅስ ነው። ጥቅሱ ከአእምሮዬ ወጥቶ አያውቅም።” a እህት ያጋጠሟትን አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ከጠቀሰች በኋላ እንዲህ አለች፦ “ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጌ መተው ያሰኘኝ ጊዜ ነበር፤ እውነትን፣ ኃላፊነቶቼን፣ ብቻ ሁሉንም ነገር! ግን የጠቀስሽልኝ ጥቅስ ወደ ልቦናዬ እንድመለስ ይረዳኛል፤ . . . በዚህ ምክንያት መጽናት ችያለሁ። ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ የዚህን ያህል የረዳኝ ነገር የለም።” “ከብዙ ቀናት በኋላ” ቢሆንም እንኳ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሚስት ይህ ደብዳቤ ሲደርሳት ምን ያህል እንደተደሰተች መገመት ትችላለህ? እኛም ምስጋና የሚደርሰን ልግስና ካሳየን ከረጅም ጊዜ በኋላ ሊሆን ይችላል።

ልግስና ካሳየን ከረጅም ጊዜ በኋላ ምስጋና ሊደርሰን ይችላል (አንቀጽ 20⁠ን ተመልከት) b


21. የይሖዋን ልግስና መኮረጅህን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ያደረግከው ለምንድን ነው?

21 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ የፈጠረን ልዩ ችሎታ ሰጥቶ ነው። መቀበል የሚያስደስተን ቢሆንም ስንሰጥ የበለጠ ደስታ እናገኛለን። የእምነት አጋሮቻችንን ስንረዳ ደስ ይለናል። ምስጋናቸውን ሲገልጹልንም እንደሰታለን። ይሁንና ልግስና ያሳየናቸው ሰዎች ቢያመሰግኑንም ባያመሰግኑንም ትክክል የሆነውን ነገር በማድረጋችን መደሰት እንችላለን። ለሌሎች የምትሰጠው ነገር ምንም ይሁን ምን “ይሖዋ ከዚህ እጅግ የሚበልጥ ሊሰጥህ [እንደሚችል]” ፈጽሞ አትርሳ። (2 ዜና 25:9) መቼም ቢሆን ይሖዋ ከሚሰጠን ይበልጥ መስጠት አንችልም! ደግሞም በይሖዋ ከመካስ የበለጠ አስደሳች ነገር የለም። እንግዲያው ለጋስ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን መምሰላችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”

a ለእህት የጠቀሰችላት ጥቅስ 2 ዮሐንስ 8 ነው፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ሙሉ ሽልማት እንድታገኙ እንጂ የደከምንባቸውን ነገሮች እንዳታጡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።”

b የሥዕሉ መግለጫ፦ ሥዕሉ በአንቀጽ 20 ላይ የተጠቀሰውን ተሞክሮ ያሳያል፤ የአንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሚስት፣ ለአንዲት እህት የሚያበረታታ ደብዳቤ ትጽፍላታለች። ከዓመታት በኋላ የምስጋና ደብዳቤ ደረሳት።