የጥናት ርዕስ 37
መዝሙር 118 “እምነት ጨምርልን”
እስከ መጨረሻው ለመጽናት የሚረዳን ደብዳቤ
“በመጀመሪያ የነበረንን ትምክህት እስከ መጨረሻው አጽንተን [እንያዝ]።”—ዕብ. 3:14
ዓላማ
ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ከተጻፈው ደብዳቤ የምናገኛቸው ጠቃሚ ትምህርቶች እስከዚህ ሥርዓት መጨረሻ ድረስ በታማኝነት ለመጽናት ይረዱናል።
1-2. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈላቸው ወቅት በይሁዳ ያለው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? (ለ) ይህ ደብዳቤ ወቅታዊ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የሚኖሩ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ባሉት ዓመታት ብዙ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል። የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ ብዙም ሳይቆይ በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ስደት ተነሳ። (ሥራ 8:1) ከ20 ዓመታት ገደማ በኋላ ደግሞ የክርስቶስ ተከታዮች ቀደም ሲል በተከሰተው ረሃብ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም ለአስከፊ ድህነት ተዳረጉ። (ሥራ 11:27-30) ይሁንና በ61 ዓ.ም. ገደማ ክርስቲያኖች አንጻራዊ ሰላም አገኙ። በዚያ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ደብዳቤ ጻፈላቸው። ይህ ደብዳቤ በጣም ወቅታዊ ነበር።
2 ለዕብራውያን የተላከው ደብዳቤ ወቅታዊ ነበር የምንለው ክርስቲያኖች በወቅቱ ያገኙት ሰላም ስላልዘለቀ ነው። ጳውሎስ በቅርቡ የሚጠብቃቸውን መከራ በጽናት እንዲቋቋሙ የሚረዳ ተግባራዊ ምክር ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ በትንቢት የተናገረለት የአይሁድ ሥርዓት ጥፋት እየቀረበ ነበር። (ሉቃስ 21:20) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስም ሆነ በይሁዳ የነበሩት ክርስቲያኖች ጥፋቱ የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ አያውቁም። ያም ቢሆን የቀረውን ጊዜ ተጠቅመው እንደ እምነትና ጽናት ያሉትን ባሕርያት በማዳበር ራሳቸውን ማዘጋጀት ይችላሉ።—ዕብ. 10:25፤ 12:1, 2
3. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ለዕብራውያን መጽሐፍ ትኩረት መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው?
3 እኛም ዕብራውያን ክርስቲያኖች ካጋጠማቸው እጅግ የከፋ መከራ ከፊታችን ይጠብቀናል። (ማቴ. 24:21፤ ራእይ 16:14, 16) እንግዲያው፣ ይሖዋ ለእነዚያ ክርስቲያኖች ከሰጣቸው ተግባራዊ ምክሮች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት፤ እነዚህ ምክሮች እኛንም ይጠቅሙናል።
“ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር”
4. አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ምን ፈተና አጋጥሟቸዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
4 ከአይሁድ እምነት የመጡ ክርስቲያኖች ትልቅ ፈተና ነበረባቸው። በአንድ ወቅት አይሁዳውያን ይሖዋ የመረጣቸው ሕዝቦች ነበሩ። ኢየሩሳሌም የአምላክን መንግሥት የሚወክሉት ነገሥታት መቀመጫ ነበረች፤ ቤተ መቅደሱ ደግሞ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ነበር። ሁሉም ታማኝ አይሁዳውያን የሙሴን ሕግ እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎቻቸው በዚህ ሕግ ላይ ተመሥርተው ያወጧቸውን ደንቦች ይከተሉ ነበር። እነዚህ ደንቦች አመጋገብን፣ የግርዘትን ጉዳይ አልፎ ተርፎም ከአሕዛብ ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ግንኙነት የሚነኩ ነበሩ። ይሁንና ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ይሖዋ በአይሁድ ሥርዓት መሠረት የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች መቀበሉን አቆመ። ይህም ሕጉን ሲከተሉ ለኖሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ትልቅ ፈተና ነው። (ዕብ. 10:1, 4, 10) እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ያሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንኳ ከእነዚህ ለውጦች አንዳንዶቹን መቀበል ከብዷቸው ነበር። (ሥራ 10:9-14፤ ገላ. 2:11-14) እነዚህ ክርስቲያኖች በአዲሱ እምነታቸው የተነሳ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች የስደት ዒላማ ሆኑ።
5. ክርስቲያኖች ምን ተጽዕኖ ነበረባቸው?
5 ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከሁለት አቅጣጫ ተቃውሞ ይደርስባቸው ነበር። በአንድ በኩል፣ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች እንደ ከሃዲ ይቆጥሯቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያን ነን ከሚሉ አንዳንድ ሰዎች የሚመጣባቸው ጫና አለ። እነዚህ ሰዎች ስደትን በመፍራት ሳይሆን አይቀርም የክርስቶስ ተከታዮች የሙሴን ሕግ መከተላቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩ ነበር። (ገላ. 6:12) ታዲያ ታማኝ ክርስቲያኖች እውነትን አጥብቀው እንዲይዙ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
6. ጳውሎስ የእምነት አጋሮቹን ምን እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል? (ዕብራውያን 5:14–6:1)
6 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የእምነት አጋሮቹ የአምላክን ቃል በጥልቀት እንዲቆፍሩ አበረታቷቸዋል። (ዕብራውያን 5:14–6:1ን አንብብ።) ጳውሎስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጠቀም የክርስትና የአምልኮ ሥርዓት ከአይሁድ እምነት ያለውን ብልጫ አብራርቶላቸዋል። a ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች እውቀታቸውንና ግንዛቤያቸውን ማሳደጋቸው እንደሚጠቅማቸው ያውቅ ነበር። ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋቸው ከእውነት ጎዳና ስተው እንዲወጡ የሚያደርጉ የሐሰት ትምህርቶችን ለይተው እንዲያውቁና ከእነዚህ ትምህርቶች እንዲርቁ ይረዳቸዋል።
7. በዛሬው ጊዜ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥመናል?
7 እንደ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር የሚጻረሩ መረጃዎችና ትምህርቶች ይዥጎደጎዱብናል። በምንከተላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የሥነ ምግባር ደንቦች የተነሳ ተቃዋሚዎች ጨካኞች እንደሆንን እና ጠባብ አስተሳሰብ እንዳለን አድርገው ይቆጥሩናል። የዓለም አመለካከትና ዝንባሌ ፍጹም ከሆነው የአምላክ አመለካከት ከዕለት ወደ ዕለት እየራቀ ነው። (ምሳሌ 17:15) እንግዲያው ተቃዋሚዎች እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ ወይም ከእውነት ለማራቅ የሚጠቀሙባቸውን የሐሰት ትምህርቶች ለይተን እንድናውቅና በእነሱ እንዳንወሰድ ራሳችንን ማስታጠቅ ይኖርብናል።—ዕብ. 13:9
8. ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ለመድረስ መጣጣር የምንችለው እንዴት ነው?
8 ጳውሎስ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ለመድረስ እንዲጣጣሩ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የሰጣቸውን ምክር ልብ ማለት ይኖርብናል። ይህም ስለ እውነት ጠለቅ ብሎ ማወቅን እንዲሁም የይሖዋን አስተሳሰብ ማዳበርን ይጨምራል። ይህ ሂደት ራሳችንን ወስነን ከተጠመቅን በኋላም የሚቀጥል ነው። እውነት ውስጥ የኖርንበት ዘመን ምንም ያህል ቢሆን ሁላችንም የአምላክን ቃል አዘውትረን ማንበብና ማጥናት ይኖርብናል። (መዝ. 1:2) ጥሩ የግል ጥናት ልማድ እምነታችንን ለማጠናከር ይረዳናል፤ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለዚህ ባሕርይ ጎላ አድርጎ ገልጿል።—ዕብ. 11:1, 6
‘በሕይወት የሚያኖር እምነት ይኑራችሁ’
9. ዕብራውያን ክርስቲያኖች ጠንካራ እምነት ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?
9 ዕብራውያን ክርስቲያኖች በይሁዳ ላይ ከሚመጣው መከራ በሕይወት ለመትረፍ ጠንካራ እምነት ያስፈልጋቸው ነበር። (ዕብ. 10:37-39) ኢየሱስ፣ ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ሲያዩ ወደ ተራሮች እንዲሸሹ ተከታዮቹን አሳስቧቸዋል። ምክሩ በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥም ሆነ በገጠር ለሚኖሩት ክርስቲያኖች ይሠራል። (ሉቃስ 21:20-24) በዚያ ዘመን፣ ሰዎች ወራሪ ሠራዊት ሲመጣባቸው ጥበቃ ለማግኘት እንደ ኢየሩሳሌም ወዳሉ የተመሸጉ ከተሞች መሸሻቸው የተለመደ ነበር። ወደ ተራሮች መሸሽ ምክንያታዊ እርምጃ አይመስልም። እንዲህ ማድረግ ትልቅ እምነት ይጠይቃል።
10. ጠንካራ እምነት ክርስቲያኖችን ምን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል? (ዕብራውያን 13:17)
10 ዕብራውያን ክርስቲያኖች፣ ኢየሱስ ጉባኤውን ለመምራት እየተጠቀመባቸው ባሉት ወንድሞችም መተማመን ነበረባቸው። አመራር የሚሰጡት ወንድሞች፣ በጉባኤው ውስጥ ያሉት ክርስቲያኖች በሙሉ የኢየሱስን መመሪያ ተከትለው መቼና እንዴት መሸሽ እንዳለባቸው ዝርዝር መመሪያዎችን ሰጥተው መሆን አለበት። (ዕብራውያን 13:17ን አንብብ።) ዕብራውያን 13:17 ላይ “ታዘዙ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አምኖበት የሚታዘዝን ሰው ያመለክታል። እንዲህ ያለው ሰው የሚታዘዘው መመሪያውን የሚሰጠው ሰው ሥልጣን ስላለው ብቻ ሳይሆን ስለሚተማመንበትም ነው። ስለዚህ ዕብራውያን ክርስቲያኖች መከራው ከመምጣቱ በፊት አመራር በሚሰጡት ወንድሞች ላይ እምነት ማዳበር አለባቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች በሰላሙ ጊዜ አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች የሚታዘዙ ከሆነ በመከራ ጊዜ እንዲህ ማድረግ ቀላል ይሆንላቸዋል።
11. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ጠንካራ እምነት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
11 ጳውሎስ ደብዳቤ እንደጻፈላቸው ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም በዛሬው ጊዜ እምነት ያስፈልገናል። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ሥርዓት መጨረሻ አስመልክቶ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ይላሉ፤ እንዲያውም በዚህ በማመናችን ያፌዙብናል። (2 ጴጥ. 3:3, 4) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ታላቁ መከራን አስመልክቶ አንዳንድ መረጃዎችን ቢሰጠንም ብዙ የማናውቃቸው ነገሮች አሉ። የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ይሖዋ በወሰነው ጊዜ እንደሚመጣ እንዲሁም በዚያ ጊዜ ይሖዋ እንደሚንከባከበን ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል።—ዕን. 2:3
12. ከታላቁ መከራ ለመትረፍ ምን ይረዳናል?
12 ከዚህም ሌላ ይሖዋ እኛን ለመምራት በሚጠቀምበት ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ይኖርብናል። (ማቴ. 24:45) በሮም ወረራ ወቅት እንደነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ታላቁ መከራ ሲጀምር ሕይወት አድን የሆኑ ዝርዝር መመሪያዎች ሊሰጡን ይችላሉ። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በሚሰጡን መመሪያ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ያለብን አሁን ነው። ዛሬ እነሱን መታዘዝ የሚከብደን ከሆነ በታላቁ መከራ ወቅት የሚሰጡንን መመሪያ በሙሉ ልብ መታዘዝ ቀላል እንደማይሆንልን የታወቀ ነው።
13. በዕብራውያን 13:5 ላይ የሚገኘው ምክር አስፈላጊ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
13 ዕብራውያን ክርስቲያኖች የሚሸሹበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ “ከገንዘብ ፍቅር” በመራቅ አኗኗራቸውን ቀላል ማድረግ ነበረባቸው። (ዕብራውያን 13:5ን አንብብ።) አንዳንዶቹ በሕይወታቸው ውስጥ ረሃብና ድህነት አሳልፈዋል። (ዕብ. 10:32-34) ቀደም ሲል ለምሥራቹ ሲሉ መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ የነበሩ ቢሆንም አንዳንዶቹ ሀብት ጥበቃ እንደሚያስገኝ ማሰብ ጀምረው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ምንም ያህል ገንዘብ ቢኖራቸው ከመጪው ጥፋት ሊያድናቸው አይችልም። (ያዕ. 5:3) እንዲያውም ለቁሳዊ ነገሮች ፍቅር ያላቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሸሽ ሊከብዳቸው ይችላል።
14. ጠንካራ እምነት ከቁሳዊ ነገሮች ጋር በተያያዘ የምናደርገውን ውሳኔ የሚነካው እንዴት ነው?
14 የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በቅርቡ እንደሚመጣ ጠንካራ እምነት ካለን ከፍቅረ ነዋይ ለመራቅ እንነሳሳለን። ሰዎች “በይሖዋ የቁጣ ቀን ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው” እንደማይችል ስለሚገነዘቡ “ብራቸውን በየጎዳናው ይጥላሉ።” (ሕዝ. 7:19) የምንችለውን ያህል ብዙ ገንዘብ በማከማቸት ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ቀላል ሆኖም ሚዛናዊ ሕይወት ለመምራት የሚረዱንን ውሳኔዎች ማድረግ ይኖርብናል። ለምሳሌ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ከመግባት ወይም የእኛን ጊዜና እንክብካቤ የሚፈልጉ ብዙ ቁሳዊ ነገሮችን ከመሰብሰብ እንቆጠባለን። አሁን ላሉን ቁሳዊ ንብረቶችም ከመጠን ያለፈ ፍቅር እንዳይኖረን እንጠነቀቃለን። (ማቴ. 6:19, 24) የዚህን ሥርዓት መጨረሻ በምንጠባበቅበት ወቅት ከቁሳዊ ነገሮችም ሆነ ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ እምነታችን ሊፈተን ይችላል።
“መጽናት ያስፈልጋችኋል”
15. ዕብራውያን ክርስቲያኖች ጽናት ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?
15 በይሁዳ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ሲሄድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች የእምነት ፈተናዎችን ለመቋቋም ጽናት ያስፈልጋቸዋል። (ዕብ. 10:36) አንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከባድ ስደት ያሳለፉ ቢሆንም ብዙዎቹ ክርስትናን የተቀበሉት አንጻራዊ ሰላም በነበረበት ጊዜ ነው። ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች ከባድ የእምነት ፈተናዎችን በጽናት የተቋቋሙ ቢሆንም የኢየሱስን ያህል ማለትም እስከ ሞት ድረስ እንዳልተፈተኑ ገልጿል። (ዕብ. 12:4) ሆኖም ክርስትና እየተስፋፋ ሲሄድ አይሁዳውያን ተቃዋሚዎች ጥላቻቸውና ጽንፈኝነታቸው እየጨመረ መጣ። ጳውሎስ ደብዳቤውን ከመጻፉ ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢየሩሳሌም ውስጥ በመገኘቱ ትልቅ ረብሻ ተነስቶ ነበር። ከ40 የሚበልጡ አይሁዳውያን ጳውሎስን “እስኪገድሉ ድረስ እህል ውኃ ላለመቅመስ” ተማምለው ነበር። (ሥራ 22:22፤ 23:12-14) እነዚህ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ሃይማኖታዊ ጥላቻና ጽንፈኝነት በሰፈነበት አካባቢ ለአምልኮ መሰብሰብ፣ ምሥራቹን መስበክ እንዲሁም እምነታቸውን ጠብቀው መኖር ይጠበቅባቸዋል።
16. ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፈው ደብዳቤ ለስደት ትክክለኛው አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው? (ዕብራውያን 12:7)
16 ዕብራውያን ክርስቲያኖች የሚያጋጥማቸውን ተቃውሞ በጽናት ለመቋቋም ምን ሊረዳቸው ይችላል? ለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ትክክለኛው አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጳውሎስ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም አምላክ አንድ ክርስቲያን ሥልጠና እንዲያገኝ ሲል የእምነት ፈተናዎች እንዲደርሱበት ሊፈቅድ እንደሚችል ጳውሎስ አብራራላቸው። (ዕብራውያን 12:7ን አንብብ።) እንዲህ ያለው ሥልጠና ግለሰቡ ወሳኝ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንዲያዳብርና እንዲያሻሽል ይረዳዋል። ዕብራውያን ክርስቲያኖች ፈተናዎቹ በሚያስገኙት ውጤት ላይ ማተኮራቸው መጽናት ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል።—ዕብ. 12:11
17. ጳውሎስ ስደትን በጽናት ከመቋቋም ጋር በተያያዘ ምን ያውቃል?
17 ዕብራውያን ክርስቲያኖች ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም ይበልጥ ቁርጠኛ እንዲሆኑ ጳውሎስ አሳስቧቸዋል። ደግሞም ስደትን በጽናት ስለመቋቋም ከተነሳ ጳውሎስ ብዙ የሚያውቀው ነገር አለ። ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ ስለነበር የሚጋፈጡት ስደት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያውቃል። ስደትን በጽናት መቋቋም የሚቻለው እንዴት እንደሆነም ያውቃል። ምክንያቱም ክርስቲያን ከሆነ በኋላ የተለያየ ዓይነት ተቃውሞ ደርሶበታል። (2 ቆሮ. 11:23-25) በመሆኑም ጳውሎስ ለመጽናት ምን እንደሚያስፈልግ በእርግጠኝነት መናገር ይችላል። ለእነዚያ ክርስቲያኖች እንዳሳሰባቸው ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም ከፈለጉ በራሳቸው ሳይሆን በይሖዋ መታመን አለባቸው። ጳውሎስ በልበ ሙሉነት “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም” ማለት የቻለው ይህን በማድረጉ ነው።—ዕብ. 13:6
18. ስደትን በጽናት ለመቋቋም የሚረዳን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ማወቃችን ነው?
18 አንዳንድ ወንድሞቻችን በአሁኑ ወቅት ስደትን በጽናት እየተቋቋሙ ይገኛሉ። ስለ እነሱ በመጸለይ በታማኝነት ልንደግፋቸው እንችላለን፤ አንዳንድ ጊዜም ተግባራዊ እርዳታ ልንሰጣቸው እንችል ይሆናል። (ዕብ. 10:33) መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚናገረው ግን “የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።” (2 ጢሞ. 3:12) በመሆኑም ሁላችንም ከፊታችን ለሚጠብቀን አስቸጋሪ ጊዜ መዘጋጀት ይኖርብናል። በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመናችንን እንቀጥል፤ ይሖዋ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና በጽናት ለመቋቋም እንደሚረዳን እርግጠኞች እንሁን። እሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለታማኝ አገልጋዮቹ በሙሉ እረፍት ይሰጣቸዋል።—2 ተሰ. 1:7, 8
19. ለታላቁ መከራ ለመዘጋጀት የትኞቹን ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
19 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈላቸው ደብዳቤ ወደፊት ለሚጠብቃቸው መከራ እንዳዘጋጃቸው ምንም ጥያቄ የለውም። ጳውሎስ ጥልቅ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት እንዲኖራቸው ወንድሞቹን አበረታቷቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው እምነታቸውን የሚያዳክሙ ትምህርቶችን ለይተው እንዲያውቁና ከእነዚህ ትምህርቶች እንዲርቁ ይረዳቸዋል። የኢየሱስንም ሆነ በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች መመሪያ በፍጥነት መታዘዝ ይችሉ ዘንድ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ አበረታቷቸዋል። በተጨማሪም ለፈተና ትክክለኛውን አመለካከት በመያዝ ጽናትን እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። ፈተናዎችን በአፍቃሪ አባታቸው ለመሠልጠን የሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገው እንዲመለከቷቸው ነግሯቸዋል። እኛም በመንፈስ መሪነት የተሰጠውን ይህን ምክር እንከተል። እንዲህ ካደረግን እስከ መጨረሻው በታማኝነት መጽናት እንችላለን።—ዕብ. 3:14
መዝሙር 126 ነቅተህ ኑር፣ ጸንተህ ቁም፣ በርታ
a ጳውሎስ የክርስትና የአምልኮ ሥርዓት ከአይሁድ እምነት የላቀ መሆኑን ለማስረዳት በመጀመሪያው ምዕራፍ ውስጥ ብቻ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቢያንስ ሰባት ጥቅሶችን ጠቅሷል።—ዕብ. 1:5-13