በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ የጌታ ራትን ሲያቋቁም ቀደም ሲል ለስብከት ልኳቸው የነበሩት 70 ደቀ መዛሙርት የት ነበሩ? ጥለውት ሄደው ነበር?

ሰባዎቹ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የጌታ ራትን ባቋቋመበት ጊዜ አብረውት ስላልነበሩ ብቻ ተቀባይነት እንዳጡ ወይም ጥለውት እንደሄዱ ማሰብ አይኖርብንም። ይህ የሆነው፣ ኢየሱስ በወቅቱ ከሐዋርያቱ ጋር መሆን ስለፈለገ ብቻ ነው።

ሰባዎቹ ደቀ መዛሙርት እንደ 12ቱ ሐዋርያት ሁሉ በኢየሱስ ዘንድ ተቀባይነት ነበራቸው። በመጀመሪያ ኢየሱስ ብዙ ቁጥር ከነበራቸው ደቀ መዛሙርቱ መካከል 12ቱን መረጠ፤ ሐዋርያት ብሎም ሰየማቸው። (ሉቃስ 6:12-16) ኢየሱስ “አሥራ ሁለቱን አንድ ላይ ጠርቶ” “የአምላክን መንግሥት እንዲሰብኩና የታመሙትን እንዲፈውሱ” የላካቸው በገሊላ እያለ ነው። (ሉቃስ 9:1-6) ከጊዜ በኋላ በይሁዳ ‘ሌሎች 70 ሰዎችን ሾሞ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው።’ (ሉቃስ 9:51፤ 10:1) በመሆኑም ኢየሱስ በተለያዩ አካባቢዎች ስለ እሱ የሚሰብኩ ተከታዮች ነበሩት።

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ አይሁዳውያን በዚያ ዓመት ዓመታዊውን የፋሲካ በዓል እንደሚያከብሩ ግልጽ ነው፤ ምናልባትም የሚያከብሩት ከቤተሰባቸው ጋር ሳይሆን አይቀርም። (ዘፀ. 12:6-11, 17-20) ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ ከሐዋርያቱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። ሆኖም በይሁዳ፣ በገሊላና በፔሪያ የሚኖሩ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ አንድ ላይ ተሰብስበው የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ ዝግጅት አላደረገም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ኢየሱስ የፈለገው ከሐዋርያቱ ጋር መሆን ነበር። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር።”—ሉቃስ 22:15

ለዚህ በቂ ምክንያት ነበረው። ኢየሱስ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ” ሆኖ የሚሞትበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። (ዮሐ. 1:29) ይህ የሚሆነው ደግሞ ለረጅም ጊዜ ለአምላክ መሥዋዕት ይቀርብባት በነበረችው በኢየሩሳሌም ነው። የፋሲካው በግ ለእስራኤላውያን ይሖዋ ከግብፅ ነፃ ያወጣቸውን ጊዜ ያስታውሳቸዋል። የኢየሱስ ሞት ግን ከዚህ እጅግ የላቀ ነፃነት ያስገኛል። (1 ቆሮ. 5:7, 8) ኢየሱስ ያደረገው ነገር፣ 12ቱ ሐዋርያት የክርስቲያን ጉባኤ መሠረት እንዲሆኑ ያስችላል። (ኤፌ. 2:20-22) ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም “የ12ቱ የበጉ ሐዋርያት 12 ስሞች” የተጻፉባቸው “12 የመሠረት ድንጋዮች” ያሏት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። (ራእይ 21:10-14) አዎ፣ ታማኞቹ ሐዋርያት በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል። ከዚህ አንጻር፣ ኢየሱስ ለመጨረሻው የፋሲካ በዓል እንዲሁም ቀጥሎ ላቋቋመው የጌታ ራት አብረውት እንዲሆኑ መፈለጉ የሚያስገርም አይደለም።

ሰባዎቹና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱ በዚያ ወቅት ከኢየሱስ ጋር አልነበሩም። ያም ሆኖ፣ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ኢየሱስ ካቋቋመው የጌታ ራት ጥቅም ያገኛሉ። ከጊዜ በኋላ ቅቡዓን የሆኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ኢየሱስ በዚያ ምሽት የጠቀሰው የመንግሥት ቃል ኪዳን ክፍል ይሆናሉ።—ሉቃስ 22:29, 30