በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ተግሣጽን ስሙ፤ ጥበበኞችም ሁኑ”

“ተግሣጽን ስሙ፤ ጥበበኞችም ሁኑ”

“ልጆቼ ሆይ፣ . . . ተግሣጽን ስሙ፤ ጥበበኞችም ሁኑ።”—ምሳሌ 8:32, 33

መዝሙሮች፦ 56, 89

1. ጥበብ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

ይሖዋ የጥበብ ምንጭ ሲሆን ይህን ጥበብ ለሌሎች በልግስና ይሰጣል። ያዕቆብ 1:5 እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣልና።” አምላክ የሚሰጠውን ጥበብ ማግኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ እሱ የሚሰጠንን ተግሣጽ በመቀበል ነው። ይህ ጥበብ ደግሞ ከሥነ ምግባራዊና ከመንፈሳዊ ጉዳት ይጠብቀናል። (ምሳሌ 2:10-12) ይህም ‘ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ በመኖር’ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል።—ይሁዳ 21

2. አምላክ ለሚሰጠን ተግሣጽ አድናቆት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

2 ሆኖም ወደ ኃጢአት ያዘነበለው ሥጋችን፣ አስተዳደጋችንና ሌሎች ምክንያቶች ተግሣጽን መቀበል ወይም ለተግሣጽ ትክክለኛውን አመለካከት መያዝ ተፈታታኝ እንዲሆንብን ሊያደርጉ ይችላሉ። ተግሣጽ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በገዛ ሕይወታችን ስንመለከት ግን አምላክ ምን ያህል እንደሚወደን እንገነዘባለን፤ ይህም ለተግሣጽ አድናቆት እንድናዳብር ይረዳናል። ምሳሌ 3:11, 12 “ልጄ ሆይ፣ የይሖዋን ተግሣጽ ለመቀበል እንቢተኛ አትሁን፤ . . . ይሖዋም የሚወዳቸውን ይወቅሳልና” ይላል። አዎ፣ ይሖዋ ለእኛ የሚበጀንን ነገር እንደሚያደርግ ፈጽሞ አንዘንጋ። (ዕብራውያን 12:5-11ን አንብብ።) ደግሞም አምላክ እኛን በሚገባ ስለሚያውቀን እሱ የሚሰጠን ተግሣጽ ምንጊዜም ትክክለኛና ከተገቢው መጠን የማያልፍ ነው። ከዚህ በመቀጠል አራት የተግሣጽ ገጽታዎችን እንመለከታለን፦ (1) ራስን መገሠጽ፣ (2) ወላጆች የሚሰጡት ተግሣጽ፣ (3) በጉባኤ ውስጥ የሚሰጥ ተግሣጽ፣ (4) ተግሣጽ ከሚያስከትለው ሕመም ይበልጥ ሊጎዳን የሚችል ነገር ናቸው።

ራሳችንን መገሠጻችን ጥበበኞች እንደሆንን ያሳያል

3. አንድ ልጅ ራስን የመገሠጽ ልማድ የሚያዳብረው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

3 ራስን መገሠጽ፣ በባሕርይና በአስተሳሰብ ረገድ ማሻሻያ ለማድረግ ሲባል ራስን መቆጣጠርን ይጨምራል። በተፈጥሯችን ራሳችንን የመገሠጽ ዝንባሌ የለንም፤ በመሆኑም እንዲህ ያለውን ልማድ ለማዳበር ሥልጠና ያስፈልገናል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ አንድ ወላጅ ልጁን ብስክሌት መንዳት ሲያስተምር መጀመሪያ ላይ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ለማድረግ ሲል ብስክሌቱን ይደግፍለታል። ሆኖም ልጁ ሚዛኑን መጠበቅ እየለመደ ሲመጣ ወላጁ አለፍ አለፍ እያለ ብስክሌቱን ለቀቅ ያደርገዋል። ልጁ በደንብ ሚዛኑን መጠበቅ ሲችል ደግሞ ሙሉ በሙሉ ይለቀዋል። በተመሳሳይም ወላጆች ልጆቻቸውን በትዕግሥትና ቀጣይነት ባለው መንገድ “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ሲያሠለጥኗቸው ልጆቻቸው ጥበብና ራስን የመገሠጽ ልማድ እንዲያዳብሩ እየረዷቸው ነው።—ኤፌ. 6:4

4, 5. (ሀ) ራስን መገሠጽ ‘የአዲሱ ስብዕና’ አስፈላጊ ገጽታ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ‘ሰባት ጊዜ ብንወድቅ እንኳ’ ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለምንድን ነው?

4 አዋቂ ከሆኑ በኋላ ስለ ይሖዋ ከተማሩ ሰዎች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ራሳቸውን የመገሠጽ ልማድ አዳብረው ሊሆን ይችላል። ሆኖም አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር በመንፈሳዊ ሁኔታ ሲታይ ገና ሕፃን ነው ሊባል ይችላል። ክርስቶስን የሚመስለውን “አዲሱን ስብዕና” መልበስን እየተማረ ሲሄድ ግን ቀስ በቀስ ወደ ጉልምስና ያድጋል። (ኤፌ. 4:23, 24) አንድ ሰው ወደ ጉልምስና ደረጃ ሲደርስ ከሚያዳብራቸው አስፈላጊ ነገሮች መካከል አንዱ ደግሞ ራስን የመገሠጽ ችሎታ ነው። ይህ ችሎታ “ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል ትተን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር ያሠለጥነናል።”—ቲቶ 2:12

5 እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። (መክ. 7:20) ሆኖም አንድ ሰው ስህተት ሠራ ማለት ግለሰቡ ምንም ተስፋ የለውም ወይም ራሱን በመገሠጽ ረገድ ከባድ ችግር አለበት ማለት አይደለም። ምሳሌ 24:16 “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ መልሶ ይነሳል” ይላል። እንዲህ ያለውን ሰው ስኬታማ እንዲሆን የሚረዳው ምንድን ነው? የራሱ ቆራጥነት ብቻ በቂ አይደለም፤ የግድ የአምላክ መንፈስ እርዳታ ያስፈልገዋል። (ፊልጵስዩስ 4:13ን አንብብ።) ከአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች መካከል ደግሞ ራስን መግዛት የሚገኝበት ሲሆን ይህ ባሕርይ ራስን ከመገሠጽ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።

6. ጥሩ የአምላክ ቃል ተማሪዎች በመሆን ረገድ ማሻሻያ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

6 በተጨማሪም ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረባችን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችንና ማሰላሰላችን ራሳችንን የመገሠጽ ችሎታ እንድናዳብር ይረዳናል። ይሁንና የአምላክን ቃል ማጥናት ተፈታታኝ ቢሆንብህስ? ምናልባትም ማጥናት አትወድ ይሆናል። ሆኖም እስከፈቀድክለት ድረስ ይሖዋ እንደሚረዳህና ለቃሉ ‘ጉጉት እንድታዳብር’ እንደሚያስችልህ አትዘንጋ። (1 ጴጥ. 2:2) በመጀመሪያ፣ ይሖዋ ራስን የመገሠጽ ችሎታ እንድታዳብርና ቃሉን የምታጠናበት ጊዜ እንድትመድብ እንዲረዳህ በጸሎት ጠይቀው። ከዚያም ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰድ፤ ምናልባትም አጠር ያለ የጥናት ፕሮግራም በማውጣት መጀመር ትችል ይሆናል። በጊዜ ሂደት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ቀላልና አስደሳች እየሆነልህ ይሄዳል! ፀጥ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሆነህ ውድ በሆኑት የይሖዋ ሐሳቦች ላይ የምታሰላስልበትን ጊዜ በናፍቆት መጠባበቅ ትጀምራለህ።—1 ጢሞ. 4:15

7. ራስን የመገሠጽ ችሎታ ማዳበራችን መንፈሳዊ ግባችን ላይ ለመድረስ የሚረዳን እንዴት ነው?

7 ራስን የመገሠጽ ችሎታ ማዳበራችን መንፈሳዊ ግቦቻችን ላይ እንድንደርስ ይረዳናል። በአንድ ወቅት ቅንዓቱ እየቀዘቀዘ እንዳለ ተሰምቶት የነበረን አንድ የቤተሰብ ራስ ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ወንድም ሁኔታው ስላሳሰበው የዘወትር አቅኚ የመሆን ግብ ያወጣ ከመሆኑም ሌላ አቅኚነትን በተመለከተ መጽሔቶቻችን ላይ የወጡ ርዕሶችን አነበበ፤ እንዲሁም ይሖዋ እንዲረዳው ጸለየ። ይህም በመንፈሳዊ እንዲበረታታና እንዲጠናከር ረድቶታል። በተጨማሪም ወንድም ሁኔታው በፈቀደለት መጠን ረዳት አቅኚ ለመሆን ዝግጅት አደረገ። ውጤቱ ምን ሆነ? ተፈታታኝ ነገሮች የነበሩበት ቢሆንም የዘወትር አቅኚነት ግቡ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ግቡ ላይ ሊደርስ ችሏል።

ልጆቻችሁን በይሖዋ ተግሣጽ አሳድጓቸው

ልጆች ትክክልና ስህተት የሆነውን የመለየት ችሎታ ይዘው አይወለዱም፤ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)

8-10. ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ በማሠልጠን ረገድ እንዲሳካላቸው ምን ሊረዳቸው ይችላል? በምሳሌ አስረዳ።

8 ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” የማሳደግ ውድ መብት አላቸው። (ኤፌ. 6:4) ይሁንና ይህ ኃላፊነት በተለይ ዛሬ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ በጣም ከባድ ነው። (2 ጢሞ. 3:1-5) ልጆች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ ይዘው አይወለዱም። እርግጥ ነው፣ በተፈጥሮ ያገኙት ሕሊና ይኖራቸዋል፤ ሆኖም ሕሊናቸው በትምህርት ወይም በሥልጠና መቀረጽ ያስፈልገዋል። (ሮም 2:14, 15) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ ጽሑፍ “ማሠልጠን” የሚለው የግሪክኛ ቃል “ልጅ ማሳደግ” ተብሎም ሊተረጎም እንደሚችል ይጠቁማል።

9 አብዛኛውን ጊዜ፣ ፍቅራዊ ተግሣጽ የሚሰጣቸው ልጆች የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል። ነፃነታቸው ገደብ እንዳለው እንዲሁም የሚያደርጉት ውሳኔም ሆነ ምግባራቸው ጥሩ አሊያም መጥፎ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ይማራሉ። እንግዲያው ክርስቲያን ወላጆች የይሖዋን አመራር ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! ልጆችን ማሳደግን በተመለከተ የሚሰነዘሩት ሐሳቦች ከባሕል ባሕል እንደሚለያዩና ዘዴዎቹም ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደሚለዋወጡ አትዘንጉ። ሆኖም ወላጆች የአምላክን ምክር የሚሰሙ ከሆነ ለራሳቸው ትክክል መስሎ በታያቸው መንገድ አሊያም በሰብዓዊ ተሞክሮ ወይም አስተሳሰብ ላይ ተመሥርተው ልጆቻቸውን አያሳድጉም።

10 የኖኅን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኖኅ መርከብ እንዲሠራ በታዘዘ ጊዜ በራሱ ተሞክሮ ሊታመን አይችልም ነበር። ምክንያቱም ከዚህ በፊት መርከብ ሠርቶ አያውቅም። በመሆኑም በይሖዋ በመታመን “ልክ እንደዚሁ” ማለትም ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው ማድረግ ነበረበት። (ዘፍ. 6:22) ውጤቱስ ምን ሆነ? ኖኅ ከዚህ በፊት ሠርቶ የማያውቀውን ነገር በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ችሏል። ይህ ደግሞ የራሱንና የቤተሰቡን ሕይወት ለማትረፍ አስችሎታል። በተጨማሪም ኖኅ የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ያለበትን ኃላፊነት በተሳካ መንገድ የተወጣ ሲሆን ለዚህም ቢሆን የረዳው በአምላክ ጥበብ መታመኑ ነው። በአምላክ መታመኑ ልጆቹን ጥሩ አድርጎ ለማስተማርና ለእነሱ ግሩም ምሳሌ ለመሆን ረድቶታል፤ ከጥፋት ውኃው በፊት በነበረው ክፉ ዓለም ውስጥ እንዲህ ማድረግ በጣም ተፈታታኝ ነበር።—ዘፍ. 6:5

11. ወላጆች ልጆችን በማሠልጠን ረገድ ይሖዋ የሚላቸውን መስማታቸው ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

11 እናንት ወላጆች፣ በአምላክ ፊት “ልክ እንደዚሁ” አድርጋችኋል ሊባልላችሁ የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ የሚላችሁን ስሙ። በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ስለ ልጆች አስተዳደግ የሚሰጣችሁን መመሪያ ተቀበሉ። ከጊዜ በኋላ ልጆቻችሁ እንዲህ በማድረጋችሁ ያመሰግኗችሁ ይሆናል! አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወላጆቼ ጥሩ አድርገው ስላሳደጉኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ልቤን ለመንካት የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። አሁን ላደረግኩት መንፈሳዊ እድገት በዋነኝነት ሊመሰገኑ የሚገባቸው እነሱ ናቸው።” እርግጥ ነው፣ ወላጆች የቻሉትን ያህል ጥረት ቢያደርጉም አንዳንድ ልጆች ይሖዋን ሊተዉ ይችላሉ። የሆነው ሆኖ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ እውነትን ለመቅረጽ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደረጉ ወላጆች ንጹሕ ሕሊና ይኖራቸዋል። በተጨማሪም ከእውነት መንገድ የራቀው ልጅ አንድ ቀን ወደ ይሖዋ እንደሚመለስ ተስፋ ማድረግ ይችላሉ።

12, 13. (ሀ) ክርስቲያን ወላጆች ልጃቸው በሚወገድበት ጊዜ አምላክን እንደሚታዘዙ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ቤተሰብ ይሖዋን በመታዘዙ የተጠቀመው እንዴት ነው?

12 አንዳንድ ወላጆች ከተወገደ ልጃቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ታዛዥነት ማሳየት በጣም ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። የተወገደች ልጇ ከቤት የወጣችን አንዲት እናት ምሳሌ እንመልከት። እናትየዋ እንዲህ ስትል በሐቀኝነት ተናግራለች፦ “ከልጄና ከልጅ ልጄ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ስል በጽሑፎቻችን ላይ ከወጡት ሐሳቦች መካከል ትንሽ ክፍተት የሚሰጠኝ ነገር ለማግኘት እሞክር ነበር።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ግን የልጃችን ጉዳይ ከእኛ እጅ እንደወጣና በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደሌለብን እንዳስተውል በደግነት ረድቶኛል።”

13 ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ልጃቸው ወደ ጉባኤ ተመለሰች። እናትየዋ እንዲህ ብላለች፦ “አሁን በየቀኑ ማለት ይቻላል፣ ስልክ ትደውልልኛለች ወይም መልእክት ትልክልኛለች! እኔና ባለቤቴ አምላክን እንደታዘዝን ስለምታውቅ ለእኛ ጥልቅ አክብሮት አላት። በአሁኑ ወቅት በመካከላችን በጣም ጥሩ ግንኙነት አለ።” እናንተም የተወገደ ልጅ ካላችሁ ‘በሙሉ ልባችሁ በይሖዋ ለመታመንና በገዛ ራሳችሁ ማስተዋል ላለመመካት’ ጥረት ታደርጋላችሁ? (ምሳሌ 3:5, 6) የይሖዋ ተግሣጽ የእሱን ወደር የለሽ ጥበብና ፍቅር እንደሚያንጸባርቅ አስታውሱ። በተጨማሪም ይሖዋ ለመላው የሰው ዘር ማለትም ለእናንተም ልጅ ጭምር ልጁን እንደሰጠ ፈጽሞ አትርሱ። አምላክ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም። (2 ጴጥሮስ 3:9ን አንብብ።) በመሆኑም ይሖዋ በሚሰጠው ተግሣጽና መመሪያ ላይ እምነት ይኑራችሁ። የይሖዋን ትእዛዝ መፈጸም ከወላጅ አንጻር በጣም ቢከብዳችሁም እንኳ እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አትበሉ። አዎ፣ ከአምላክ ተግሣጽ ጋር የሚስማማ እንጂ የሚቃረን ነገር አታድርጉ።

በጉባኤ ውስጥ

14. ይሖዋ ‘በታማኙ መጋቢ’ በኩል ከሚሰጠን መመሪያ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ይሖዋ የክርስቲያን ጉባኤን እንደሚንከባከብ፣ እንደሚጠብቅና እንደሚመራ ቃል ገብቷል። እንዲህ የሚያደርገው በተለያዩ መንገዶች ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ልጁን የጉባኤው ራስ አድርጎ የሾመው ሲሆን ልጁ ደግሞ በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብ ‘ታማኝ መጋቢ’ ሾሟል። (ሉቃስ 12:42) በተለያየ መልኩ የሚቀርበው ይህ መንፈሳዊ ምግብ ጠቃሚ መመሪያ ወይም ተግሣጽ ይሰጠናል። ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘በአንድ ንግግር ላይ የተጠቀሰ ሐሳብ ወይም በጽሑፎቻችን ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ ጉዳይ በአስተሳሰቤ ወይም በምግባሬ ላይ ማስተካከያ እንዳደርግ አነሳስቶኝ ያውቃል?’ መልሳችሁ ‘አዎ’ ከሆነ ደስ ሊላችሁ ይገባል! ምክንያቱም ይሖዋ ለእናንተው ጥቅም ሲል እንዲቀርጻችሁ ወይም እንዲገሥጻችሁ እየፈቀዳችሁለት ነው ማለት ነው።—ምሳሌ 2:1-5

15, 16. (ሀ) በጉባኤው ውስጥ ካሉ ‘ስጦታ የሆኑ ሰዎች’ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ሥራቸውን በደስታ እንዲያከናውኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

15 በተጨማሪም ክርስቶስ የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ ሆነው የሚጠብቁ ሽማግሌዎችን በመሾም ለጉባኤው ‘ሰዎችን ስጦታ አድርጎ ሰጥቷል።’ (ኤፌ. 4:8, 11-13) ውድ ስጦታ ከሆኑት ከእነዚህ ሽማግሌዎች ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ እነሱን በእምነታቸው በመምሰልና መልካም ምሳሌያቸውን በመከተል ነው። ሌላው መንገድ ደግሞ የሚሰጡንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመቀበል ነው። (ዕብራውያን 13:7, 17ን አንብብ።) ሽማግሌዎች እንደሚወዱንና መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ እንደሚፈልጉ አትርሱ። ለምሳሌ ያህል፣ ከስብሰባዎች መቅረት እንደጀመርን ወይም ቅንዓታችን እየቀዘቀዘ እንደሆነ ካስተዋሉ ወዲያውኑ እኛን ለመርዳት ጥረት እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። ሐሳባችንን ስንገልጽ የሚያዳምጡን ከመሆኑም ሌላ ፍቅራዊ ማበረታቻና አስፈላጊውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመስጠት በመንፈሳዊ ሊያጠናክሩን ይሞክራሉ። እንዲህ ያለው ማበረታቻ ይሖዋ ለአንተ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ እንደሆነ ይሰማሃል?

16 ወደ እኛ ቀርቦ አስፈላጊውን ምክር መስጠት ለሽማግሌዎች ቀላል እንደማይሆን ማስታወስ አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ዳዊት የፈጸመውን ከባድ ኃጢአት ለመሸፋፈን ጥረት ባደረገበት ወቅት ነቢዩ ናታን እሱን ቀርቦ ማነጋገር ምን ያህል ከብዶት ሊሆን እንደሚችል ማሰብ እንችላለን። (2 ሳሙ. 12:1-14) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ የነበረው ጴጥሮስ ለአይሁዳውያን ወንድሞቹ እንደሚያዳላ የሚያሳይ ድርጊት በፈጸመበት ወቅት ለእሱ እርማት ለመስጠት ድፍረት ጠይቆበት እንደሚሆን ግልጽ ነው። (ገላ. 2:11-14) ታዲያ በጉባኤህ ውስጥ ያሉትን ሽማግሌዎች ሸክም ማቅለል የምትችለው እንዴት ነው? ትሑት፣ በቀላሉ የምትቀረብና አመስጋኝ ሁን። እነሱ የሚሰጡህን እርዳታ አምላክ ለአንተ ያለው ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገህ ተመልከተው። እንዲህ ማድረግህ ራስህን የሚጠቅምህ ከመሆኑም በላይ እነሱም ሥራቸውን በደስታ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል።

17. የጉባኤ ሽማግሌዎች አንዲትን እህት የረዷት እንዴት ነው?

17 አንዲት እህት ባሳለፈችው ሕይወት የተነሳ ለይሖዋ ፍቅር ማዳበር ከብዷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ባሳለፍኩት ሕይወት ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በስሜት በምዝልበት ጊዜ ሽማግሌዎችን ማነጋገር እንዳለብኝ አውቃለሁ። ሽማግሌዎቹ ተቆጥተውኝም ሆነ ነቅፈውኝ አያውቁም፤ ከዚህ ይልቅ እንድበረታታና እንድጠናከር ይረዱኛል። ሥራ በሚበዛባቸው ጊዜም እንኳ ከእያንዳንዱ የጉባኤ ስብሰባ በኋላ ቢያንስ አንድ ሽማግሌ ወደ እኔ ቀርቦ ስላለሁበት ሁኔታ ይጠይቀኛል። ባሳለፍኩት ሕይወት የተነሳ፣ አምላክ ሊወደኝ እንደሚችል ማሰብ ይከብደኝ ነበር። ሆኖም ይሖዋ በተደጋጋሚ ጊዜ በጉባኤውና በሽማግሌዎች አማካኝነት እኔን እንደሚወደኝ አረጋግጦልኛል። እኔም እሱን እስከ መጨረሻው የሙጥኝ ብዬ ለመኖር እጸልያለሁ።”

ተግሣጽ ከሚያስከትለው ሕመም ይበልጥ ሊጎዳን የሚችል ነገር

18, 19. ተግሣጽ ከሚያስከትለው ሕመም ይበልጥ ሊጎዳን የሚችለው ምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

18 ተግሣጽ ሕመም ሊያስከትል ቢችልም ከዚያ የከፋ ሕመም ሊያስከትልብን የሚችለው ተግሣጹን አለመቀበላችን ነው። (ዕብ. 12:11) የቃየንንና የንጉሥ ሴዴቅያስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ቃየን አቤልን ወደ መግደል ሊያመራ የሚችል ጥላቻ በውስጡ እያቆጠቆጠ በነበረበት ወቅት አምላክ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቶት ነበር፦ “ለምን ተናደድክ? ለምንስ አዘንክ? መልካም ወደ ማድረግ ብታዘነብል ኖሮ ሞገስ አታገኝም ነበር? መልካም ወደ ማድረግ ካላዘነበልክ ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባ ነው፤ ሊቆጣጠርህም ይፈልጋል፤ ታዲያ አንተ ትቆጣጠረው ይሆን?” (ዘፍ. 4:6, 7) ቃየን ግን አልሰማም። በመሆኑም ኃጢአት ተቆጣጠረው። በዚህም የተነሳ ቃየን አላስፈላጊ ሕመምና ሥቃይ በራሱ ላይ አመጣ! (ዘፍ. 4:11, 12) ይሖዋ የሰጠው ተግሣጽ የሚያስከትልበት ሕመም ከዚህ ጋር ሲነጻጸር ምንኛ የተሻለ ነበር!

19 ደካማና ክፉ ንጉሥ የነበረው ሴዴቅያስ ይገዛ በነበረበት ጊዜ የኢየሩሳሌም ሁኔታ በጣም አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ነቢዩ ኤርምያስ፣ ሴዴቅያስ መጥፎ አካሄዱን እንዲያስተካክል በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቢሰጠውም ንጉሡ ተግሣጹን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም እሱም ልክ እንደ ቃየን ለውድቀት ተዳርጓል። (ኤር. 52:8-11) በእርግጥም ይሖዋ እንዲህ ካለው አላስፈላጊ ሥቃይ ሊያድነን ይፈልጋል!—ኢሳይያስ 48:17, 18ን አንብብ።

20. የአምላክን ተግሣጽ የማይቀበሉ ሰዎች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል? የሚቀበሉትስ ምን ጥቅም ያገኛሉ?

20 በምንኖርበት ዓለም ውስጥ በርካታ ሰዎች ራስን መገሠጽን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ተግሣጽ ይንቃሉ። ሆኖም እንዲህ ያለውን የሞኝነት አስተሳሰብ የሚያራምዱ ክፉ ሰዎች በቅርቡ አሳዛኝ ውጤት እንደሚጠብቃቸው እናውቃለን። (ምሳሌ 1:24-31) በመሆኑም ‘ተግሣጽን በመስማት ጥበበኞች እንሁን።’ በምሳሌ 4:13 ላይ የሚገኘውን “ተግሣጽን ያዛት፤ አትልቀቃትም። ጠብቃት፤ ሕይወትህ ናትና” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እናድርግ።