በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተግሣጽ—የአምላክ ፍቅር መግለጫ

ተግሣጽ—የአምላክ ፍቅር መግለጫ

“ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻል።”—ዕብ. 12:6

መዝሙሮች፦ 123, 86

1. መጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛውን ጊዜ ተግሣጽን የሚገልጸው በምን መንገድ ነው?

“ተግሣጽ” የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ነገር ምንድን ነው? ምናልባት ወዲያውኑ የምታስበው ስለ ቅጣት ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ተግሣጽ ከዚህ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛውን ጊዜ ተግሣጽን የሚገልጸው አዎንታዊ በሆነ መንገድ ሲሆን ቃሉ ከእውቀት፣ ከጥበብ፣ ከፍቅርና ከሕይወት ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል። (ምሳሌ 1:2-7፤ 4:11-13) ደግሞም የአምላክ ተግሣጽ እሱ ለእኛ ያለው ፍቅር መገለጫ ከመሆኑም ሌላ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ያለውን ፍላጎት ያሳያል። (ዕብ. 12:6) አምላክ የሚሰጠን ተግሣጽ ቅጣትን የሚጨምርበት ጊዜ ቢኖርም ቅጣቱ የሚጎዳ ወይም ጭካኔ የተሞላበት አይደለም። እንዲያውም “ተግሣጽ” የሚለው ቃል ዋነኛ ትርጉም ትምህርት ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው፤ ለምሳሌ አንድ ወላጅ ለሚወደው ልጁ የሚሰጠውን ትምህርት ሊያመለክት ይችላል።

2, 3. ተግሣጽ ማስተማርንና መቅጣትን ሊያካትት የሚችለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

2 እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት፦ ጆኒ የተባለ አንድ ትንሽ ልጅ ቤት ውስጥ ኳስ ይጫወታል። እናቱ “ቤት ውስጥ ኳስ አትጫወት! ዕቃ ትሰብራለህ” ትለዋለች። ጆኒ ግን የእናቱን ትእዛዝ ችላ በማለት መጫወቱን ይቀጥላል፤ ከዚያም ሳያስበው ጠረጴዛ ላይ ያለውን የአበባ ማስቀመጫ ይሰብረዋል። በዚህ ጊዜ እናቱ ተግሣጽ የምትሰጠው እንዴት ነው? ተግሣጹ ማስተማርንና መቅጣትን የሚያካትት ሊሆን ይችላል። ድርጊቱ ስህተት የሆነበትን ምክንያት በማስረዳት ትምህርት ትሰጠዋለች። ይህን የምታደርገው ወላጆቹ ያወጡለት ሕጎች አስፈላጊና ምክንያታዊ መሆናቸውን እንዲገነዘብና እነሱን መታዘዙ ጥበብ እንደሆነ እንዲያስተውል ለመርዳት ነው። ከዚያም የተናገረችውን ነገር እንዳይረሳው ለማድረግ ስትል ተገቢ ነው ብላ ያሰበችውን ቅጣት ትቀጣው ይሆናል። ለምሳሌ ኳሱን ቀምታ ለተወሰነ ጊዜ ያህል እንዳይጫወት ልትከለክለው ትችላለች። ይህም ልጁ አለመታዘዝ የሚያስከትለው መዘዝ እንዳለ እንዲገነዘብ ያደርገዋል።

3 እኛም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ቤተሰብ አባላት ነን። (1 ጢሞ. 3:15) በመሆኑም ይሖዋ የምንመራባቸውን መሥፈርቶች የማውጣት እንዲሁም እነዚህን መሥፈርቶች ስንጥስ ፍቅራዊ ተግሣጽ የመስጠት መብት እንዳለው አምነን እንቀበላለን። በተጨማሪም የፈጸምነው የተሳሳተ ድርጊት የሚያስከትልብን መዘዝ በሰማይ ያለውን አባታችንን መስማት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስገነዝበናል፤ ይህም ቢሆን ይሖዋ እኛን የሚገሥጽበት አንዱ መንገድ ነው። (ገላ. 6:7) አምላክ ከልብ የሚያስብልን ከመሆኑም በላይ ለሐዘን ከሚዳርጉ ነገሮች ሊጠብቀን ይፈልጋል።—1 ጴጥ. 5:6, 7

4. (ሀ) ይሖዋ የሚባርከው እንዴት ያለውን ሥልጠና ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

4 ለልጆቻችን ወይም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ቅዱስ ጽሑፋዊ ተግሣጽ መስጠታችን የክርስቶስ ተከታዮች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ሌሎችን ለማሠልጠን የምንጠቀምበት ዋነኛው መሣሪያችን የአምላክ ቃል ሲሆን ቃሉ “በጽድቅ ለመገሠጽ” ይጠቅመናል። በዚህ መንገድ ልጆቻችን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ኢየሱስ ያዘዘንን ነገሮች ሁሉ እንዲያስተውሉና እንዲጠብቁ መርዳት እንችላለን። (2 ጢሞ. 3:16፤ ማቴ. 28:19, 20) ይሖዋ እንዲህ ያለውን ሥልጠና ይባርካል፤ ምክንያቱም በዚህ መልኩ ሥልጠና ያገኙ ተማሪዎች እነሱም በምላሹ ሌሎችን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት የታጠቁ ይሆናሉ። (ቲቶ 2:11-14ን አንብብ።) ከዚህ በመቀጠል የሚከተሉትን ሦስት አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን፦ (1) አምላክ የሚሰጠን ተግሣጽ እሱ እንደሚወደን የሚያሳየው እንዴት ነው? (2) አምላክ ከዚህ በፊት ተግሣጽ ከሰጣቸው ሰዎች ምን እንማራለን? (3) ተግሣጽ በምንሰጥበት ጊዜ የይሖዋንና የልጁን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

የአምላክ ተግሣጽ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው

5. ይሖዋ የሚሰጠን ተግሣጽ እሱ እንደሚወደን የሚያሳየው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ ስለሚወደን ከእሱ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖርና በሕይወት ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል ሲል እርማት፣ ትምህርትና ሥልጠና ይሰጠናል። (1 ዮሐ. 4:16) እኛን በማዋረድ ወይም ክብራችንን የሚነካ ነገር በማድረግ ዋጋ ቢስ እንደሆንን እንዲሰማን አያደርግም። (ምሳሌ 12:18) ከዚህ ይልቅ በልባችን ውስጥ ባሉት ጥሩ ባሕርያት ተገፋፍተን እንድናገለግለው በማበረታታት እንዲሁም የመምረጥ ነፃነታችንን እንድንጠቀም በመፍቀድ በአክብሮት ይይዘናል። አንተስ የአምላክ ተግሣጽ የእሱ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ ይሰማሃል? አምላክ በቃሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች፣ በክርስቲያን ወላጆች አሊያም በጉባኤ ሽማግሌዎች በኩል ተግሣጽ ሊሰጠን ይችላል። ምናልባትም ሳይታወቀን “የተሳሳተ ጎዳና” በምንከተልበት ጊዜ ሽማግሌዎች በገርነትና በፍቅር እኛን ለማስተካከል ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ ያሉ ሽማግሌዎች ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያንጸባርቃሉ።—ገላ. 6:1

6. የተሰጠን ተግሣጽ መብቶቻችንን የሚያሳጣን በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ተግሣጹ የይሖዋን ፍቅር የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?

6 አንዳንድ ጊዜ ግን ተግሣጽ በቃል ከሚሰጥ ምክር ወይም እርማት ያለፈ ነገርን ሊጨምር ይችላል። አንድ ሰው ከበድ ያለ ኃጢአት ከሠራ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን መብቶች ሊያጣ ይችላል። እንዲህ ያለው ተግሣጽም ቢሆን አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያል። ለምሳሌ አንድ ሰው መብቶቹን ማጣቱ ለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ለማሰላሰልና ለጸሎት ይበልጥ ትኩረት መስጠቱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘብ ሊያደርገው ይችላል። ይህ ደግሞ በመንፈሳዊ እንዲጠናከር ይረዳዋል። (መዝ. 19:7) ከጊዜ በኋላ ግለሰቡ መብቶቹን መልሶ ሊያገኝ ይችላል። ሌላው ቀርቶ ኃጢአተኛው ከጉባኤ እንዲወገድ መደረጉም እንኳ የይሖዋን ፍቅር ያንጸባርቃል፤ ምክንያቱም ይህ እርምጃ መወሰዱ ጉባኤውን ከመጥፎ ተጽዕኖ ይጠብቃል። (1 ቆሮ. 5:6, 7, 11) ደግሞም አምላክ የሚገሥጸው በተገቢው መጠን ስለሆነ የውገዳ ዝግጅት፣ መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ሰው ኃጢአቱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዲገነዘብና ንስሐ ለመግባት እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል።—ሥራ 3:19

የይሖዋ ተግሣጽ ጠቅሞታል

7. ሸብና ማን ነበር? ምን መጥፎ ባሕርይስ አዳብሯል?

7 ተግሣጽ የሚያስገኘውን ጥቅም ለማስተዋል ይሖዋ የገሠጻቸውን ሁለት ሰዎች ምሳሌ እንመልከት፤ አንደኛው በሕዝቅያስ ዘመን የኖረው ሸብና ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በዘመናችን ያለው ወንድም ግሬሃም ነው። ሸብና ‘በቤቱ ላይ [በሕዝቅያስ ቤት ላይ ሳይሆን አይቀርም] የተሾመ መጋቢ’ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። (ኢሳ. 22:15) የሚያሳዝነው ግን ኩሩ በመሆን ለራሱ ክብር መፈለግ ጀመረ። ሌላው ቀርቶ ለራሱ እጅግ ውድ የመቃብር ቦታ ያሠራ ከመሆኑም ሌላ ‘ባማሩ ሠረገሎች’ ይሄድ ነበር!—ኢሳ. 22:16-18

በትሕትና አመለካከታችንን ማስተካከላችን የአምላክን በረከት ያስገኝልናል (ከአንቀጽ 8-10⁠ን ተመልከት)

8. ይሖዋ ሸብናን የገሠጸው እንዴት ነው? ሸብና ከተግሣጹ ጥቅም አግኝቶ ሊሆን ይችላል የምንለውስ ለምንድን ነው?

8 ሸብና ለራሱ ክብር ማግኘት ስለፈለገ አምላክ ‘ከኃላፊነቱ አባርሮ’ በእሱ ምትክ ኤልያቄምን ሾመው። (ኢሳ. 22:19-21) ይህ ለውጥ የተደረገው የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ለማጥቃት እያሰበ በነበረበት ወቅት ላይ ነው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰናክሬም ሕዝቅያስንም ሆነ አይሁዳውያንን ወኔ እንዲከዳቸውና እጅ እንዲሰጡ ለማድረግ ሲል በብዙ ሠራዊት የታጀቡ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ወደ ኢየሩሳሌም ላከ። (2 ነገ. 18:17-25) እነዚህን ባለሥልጣናት እንዲያነጋግር የተላከው ኤልያቄም ነበር፤ ሆኖም ብቻውን አልነበረም። ሌሎች ሁለት ሰዎች አብረውት የነበሩ ሲሆን ከሁለቱ አንዱ ሸብና ነበር፤ ሸብና በዚህ ወቅት በጸሐፊነት እያገለገለ ነበር። ይህ ሁኔታ ሸብና በተወሰደበት እርምጃ ከመከፋትና ቅር ከመሰኘት ይልቅ የተሰጠውን ከቀድሞው ዝቅ ያለ ኃላፊነት በትሕትና እንደተቀበለ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ታዲያ እኛ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? እስቲ ሦስት ነጥቦችን እንመልከት።

9-11. (ሀ) ከሸብና ታሪክ ምን ጠቃሚ ትምህርቶች እናገኛለን? (ለ) ይሖዋ ሸብናን የያዘበት መንገድ የሚያበረታታህ እንዴት ነው?

9 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሸብና የነበረውን ኃላፊነት አጥቷል። በእሱ ላይ የደረሰው ነገር “ኩራት ጥፋትን፣ የትዕቢት መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” የሚለውን ማስጠንቀቂያ እንድናስታውስ ያደርገናል። (ምሳሌ 16:18) እኛም በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ ኃላፊነቶች ይኖሩን ይሆናል፤ ምናልባትም አንዳንዶች በዚህ የተነሳ ከፍ ያለ ቦታ ሊሰጡን ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ትሑቶች በመሆን ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት እናደርጋለን? ላሉን ተሰጥኦዎችም ሆነ ላከናወንናቸው ነገሮች ሁሉ ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ አምነን እንቀበላለን? (1 ቆሮ. 4:7) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ . . . ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው . . . እመክራለሁ።”—ሮም 12:3

10 በሁለተኛ ደረጃ፣ ይሖዋ ለሸብና ጠንከር ያለ ተግሣጽ መስጠቱ ሸብናን ‘ፈጽሞ ሊለወጥ አይችልም’ ብሎ ተስፋ እንዳልቆረጠበት የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 3:11, 12) ይህ በአምላክ ጉባኤ ውስጥ ያላቸውን የአገልግሎት መብት ላጡ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! በሁኔታው ከመበሳጨት ወይም ቅር ከመሰኘት ይልቅ የተሰጣቸውን ተግሣጽ የአምላክ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገው ሊመለከቱትና አሁን ያሉበት ሁኔታ በፈቀደላቸው መጠን ምርጣቸውን በመስጠት አምላክን ማገልገላቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ። አባታችን ራሳችንን በፊቱ ዝቅ እስካደረግን ድረስ ፈጽሞ ተስፋ እንደማይቆርጥብን እናስታውስ። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7ን አንብብ።) ፍቅር የሚንጸባረቅበት ተግሣጽ፣ አምላክ እኛን የሚቀርጽበት አንዱ መንገድ ስለሆነ በእሱ እጅ በቀላሉ ለመቀረጽ ፈቃደኞች እንሁን።

11 በሦስተኛ ደረጃ፣ ይሖዋ ሸብናን የያዘበት መንገድ ተግሣጽ የመስጠት ኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ ለምሳሌ ለወላጆችና ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ትልቅ ትምህርት ይሰጣል። ትምህርቱ ምንድን ነው? ይሖዋ የሚሰጠው ተግሣጽ ለኃጢአት ያለውን ጥላቻ ብቻ ሳይሆን ኃጢአት ለሠራው ግለሰብ ያለውን አሳቢነትም ያሳያል። አንተም ወላጅ ወይም የበላይ ተመልካች ከሆንክ ተግሣጽ መስጠት የሚያስፈልግህ ጊዜ ሊኖር ይችላል፤ ታዲያ በዚህ ጊዜ መጥፎ የሆነውን ነገር እንደምትጠላ በማሳየት ብቻ ሳይሆን የእምነት ባልንጀራህ ባለው መልካም ባሕርይ ላይ በማተኮርም ይሖዋን ለመምሰል ጥረት ታደርጋለህ?—ይሁዳ 22, 23

12-14. (ሀ) አንዳንዶች ለሚሰጣቸው መለኮታዊ ተግሣጽ ምን ምላሽ ይሰጣሉ? (ለ) የአምላክ ቃል አንድ ወንድም አመለካከቱን እንዲያስተካክል የረዳው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?

12 የሚያሳዝነው አንዳንዶች በተሰጣቸው ተግሣጽ ከልክ በላይ በመጎዳት ከአምላክና ከሕዝቡ ይርቃሉ። (ዕብ. 3:12, 13) ይሁንና እንዲህ ያሉ ሰዎች ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት ነው? እስቲ የግሬሃምን ተሞክሮ እንመልከት። ግሬሃም ከጉባኤ ተወግዶ ከቆየ በኋላ የተመለሰ ቢሆንም በአገልግሎት መካፈልና በስብሰባዎች ላይ መገኘት አቆመ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ግን ቀርቦ ሊረዳው ጥረት ያደርግ የነበረን አንድ ሽማግሌ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠናው ጠየቀው።

13 ግሬሃምን የረዳው ሽማግሌ እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ግሬሃም ከኩራት ጋር የተያያዘ ችግር ነበረበት። በውገዳው ውሳኔ ላይ የተካፈሉትን ሽማግሌዎች ይነቅፍ ነበር። በመሆኑም ለተወሰነ ጊዜ ያህል በጥናት ፕሮግራማችን ላይ ስለ ኩራትና ኩራት ስለሚያስከትለው ውጤት በሚናገሩ ጥቅሶች ላይ ተወያየን። ግሬሃም ራሱን በአምላክ ቃል መስተዋት መመልከት የጀመረ ሲሆን መስተዋቱ ውስጥ የሚያየውን የራሱን ምስል አልወደደውም። ውጤቱ በጣም አስገራሚ ነበር! የኩራት ‘ግንድ’ ዓይኑን እንዳሳወረው አምኖ በመቀበልና ሌሎችን የሚነቅፈው እሱ ራሱ ችግር ስላለበት እንደሆነ በመገንዘብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ አደረገ። አዘውትሮ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና የአምላክን ቃል በቁም ነገር ማጥናት ጀመረ፤ እንዲሁም በየዕለቱ የመጸለይ ልማድ አዳበረ። በተጨማሪም የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ያሉበትን መንፈሳዊ ኃላፊነቶች መወጣት ጀመረ። ይህም ሚስቱንና ልጆቹን በእጅጉ አስደስቷቸዋል።”—ሉቃስ 6:41, 42፤ ያዕ. 1:23-25

14 ወንድም እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል፦ “አንድ ቀን ግሬሃም በጣም ልብ የሚነካ ነገር ነገረኝ። እንዲህ አለኝ፦ ‘ለበርካታ ዓመታት በእውነት ቤት ውስጥ ኖሬያለሁ። ሌላው ቀርቶ አቅኚ ሆኜ ያገለገልኩበት ጊዜም ነበር። በሐቀኝነት ይሖዋን እንደምወደው መናገር የቻልኩት ግን ገና አሁን ነው።’ ብዙም ሳይቆይ በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ የድምፅ መሣሪያ የማዞር መብት የተሰጠው ሲሆን ለዚህ መብት ከፍተኛ አድናቆት አለው። የእሱ ተሞክሮ፣ አንድ ሰው የተሰጠውን ተግሣጽ በትሕትና በመቀበል ራሱን በአምላክ ፊት ዝቅ ሲያደርግ ብዙ በረከቶች እንደሚትረፈረፉለት አስተምሮኛል!”

ተግሣጽ በምትሰጡበት ጊዜ የአምላክንና የክርስቶስን ምሳሌ ተከተሉ

15. የምንሰጠው ተግሣጽ የሌሎችን ልብ እንዲነካ ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 ጥሩ አስተማሪ ለመሆን በመጀመሪያ ጥሩ ተማሪ መሆን ያስፈልጋል። (1 ጢሞ. 4:15, 16) በመሆኑም አምላክ ተግሣጽ የመስጠት ኃላፊነት የሰጣቸው ሰዎች እነሱ ራሳቸው ለይሖዋ አመራር በፈቃደኝነት መገዛታቸውን መቀጠል አለባቸው። በዚህ መልኩ በትሕትና መገዛታቸው በሌሎች ዘንድ አክብሮት እንዲያተርፉ የሚያስችላቸው ከመሆኑም ሌላ ለሌሎች ሥልጠና ወይም እርማት በሚሰጡበት ጊዜ የመናገር ነፃነት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። ኢየሱስ በዚህ ረገድ የተወውን ምሳሌ እስቲ እንመልከት።

16. ተገቢውን ተግሣጽ በመስጠትና ውጤታማ በሆነ መንገድ በማስተማር ረገድ ከኢየሱስ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

16 ኢየሱስ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ምንጊዜም አባቱን ይታዘዝ ነበር። (ማቴ. 26:39) በተጨማሪም የነበረው ጥበብም ሆነ የሚያስተምረው ትምህርት ምንጭ አባቱ እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐ. 5:19, 30) ኢየሱስ ትሑትና ታዛዥ መሆኑ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ እሱ እንዲሳቡ አድርጓል፤ እንዲሁም ሩኅሩኅና ደግ አስተማሪ እንዲሆን አስችሎታል። (ማቴዎስ 11:29ን አንብብ።) የሚናገራቸው ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት፣ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደተቀጠቀጠ ሸንበቆ ወይም ሊጠፋ እንደተቃረበ የጧፍ ክር ያሉ ሰዎችን አበረታተዋል። (ማቴ. 12:20) ኢየሱስ ትዕግሥቱን የሚፈትን ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜም እንኳ ደግና አፍቃሪ መሆኑን አሳይቷል። ሐዋርያቱ የራስ ወዳድነት መንፈስና ከፍ ያለ ቦታ የማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር ባደረጉበት ወቅት ለእነሱ እርማት የሰጠበት መንገድ ይህን በግልጽ ያሳያል።—ማር. 9:33-37፤ ሉቃስ 22:24-27

17. ሽማግሌዎች የአምላክ መንጋ እረኞች በመሆን ረገድ እንዲሳካላቸው የሚረዷቸው የትኞቹ መልካም ባሕርያት ናቸው?

17 ቅዱስ ጽሑፋዊ ተግሣጽ የመስጠት ኃላፊነት የተጣለባቸው ሁሉ የክርስቶስን ምሳሌ መከተላቸው ጥበብ ነው። በእርግጥም እንዲህ ማድረጋቸው በአምላክና በልጁ ለመቀረጽ እንደሚፈልጉ ያሳያል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የበላይ ተመልካቾች ሆናችሁ በማገልገል በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ ጠብቁ፤ ሥራችሁን በግዴታ ሳይሆን በአምላክ ፊት በፈቃደኝነት ተወጡ፤ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን ለማገልገል በመጓጓት፣ የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣናችሁን በማሳየት ሳይሆን ለመንጋው ምሳሌ በመሆን ጠብቁ።” (1 ጴጥ. 5:2-4) ለአምላክና የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ለሆነው ለክርስቶስ በደስታ የሚገዙ የበላይ ተመልካቾች ራሳቸውንም ሆነ በአደራ የተሰጣቸውን የአምላክን መንጋ እንደሚጠቅሙ የተረጋገጠ ነው።—ኢሳ. 32:1, 2, 17, 18

18. (ሀ) ይሖዋ ወላጆችን ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል? (ለ) አምላክ ወላጆች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

18 ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ከቤተሰብ ጋር በተያያዘም ይሠራል። የቤተሰብ ራሶች እንዲህ የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል፦ “አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።” (ኤፌ. 6:4) ይህ ጉዳይ ምን ያህል አሳሳቢ ነው? ምሳሌ 19:18 “ገና ተስፋ ሳለ ልጅህን ገሥጽ፤ ለእሱም ሞት ተጠያቂ አትሁን” ይላል። አዎ፣ ለልጃቸው ተገቢውን ተግሣጽ ከመስጠት ወደኋላ የሚሉ ወላጆች በይሖዋ ዘንድ ተጠያቂ ይሆናሉ! (1 ሳሙ. 3:12-14) ሆኖም ወላጆች ይሖዋን በትሕትና የሚለምኑና በቃሉም ሆነ በቅዱስ መንፈሱ ለመመራት ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ እሱ ጥበብና ኃይል እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።—ያዕቆብ 1:5ን አንብብ።

ለዘላለም በሰላም መኖር የሚቻልበትን መንገድ መማር

19, 20. (ሀ) የአምላክን ተግሣጽ መቀበል ምን በረከቶች ያስገኛል? (ለ) በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

19 መለኮታዊ ተግሣጽን መቀበል እንዲሁም ለሌሎች ተግሣጽ በምንሰጥበት ጊዜ የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚያስገኛቸውን በረከቶች ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ለምሳሌ ቤተሰቦችም ሆኑ ጉባኤዎች ሰላም የሰፈነባቸው ይሆናሉ፤ በተጨማሪም እያንዳንዱ ሰው በሌሎች ዘንድ ተወዳጅና ተፈላጊ እንደሆነ የሚሰማው ከመሆኑም ሌላ ያለምንም ስጋት ተረጋግቶ ይኖራል። ይህ ሁኔታ ወደፊት ለምናገኘው በረከት እንደ ቅምሻ ነው ማለት ይቻላል። (መዝ. 72:7) አዎ፣ የይሖዋ ተግሣጽ በእሱ አባታዊ እንክብካቤ ሥር እንዳለ አንድ ቤተሰብ ለዘላለም በሰላምና በአንድነት የምንኖርበትን መንገድ ያስተምረናል ብንል ማጋነን አይሆንም። (ኢሳይያስ 11:9ን አንብብ።) መለኮታዊ ተግሣጽን በዚህ መልኩ የምንመለከተው ከሆነ ለተግሣጽ ትክክለኛውን አመለካከት ማዳበር ቀላል ይሆንልናል፤ በእርግጥም ተግሣጽ አምላክ ለእኛ ያለውን ወደር የለሽ ፍቅር የሚያሳይ ግሩም ማስረጃ ነው።

20 በቀጣዩ ርዕስ ላይ በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ተግሣጽ የሚሰጥባቸውን መንገዶች በተመለከተ ተጨማሪ ነጥቦችን እንመረምራለን። በተጨማሪም ራስን ስለ መገሠጽ እንዲሁም ተግሣጽ ከሚያስከትለው ጊዜያዊ ሕመም የከፋ ውጤት ሊያስከትል ስለሚችል ነገር እንመለከታለን።