በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንግዳ ተቀባይነት—በጣም አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ!

እንግዳ ተቀባይነት—በጣም አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ!

“ሳታጉረመርሙ አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ።”—1 ጴጥ. 4:9

መዝሙሮች፦ 100, 87

1. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል?

ሐዋርያው ጴጥሮስ “በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢቲኒያ ተበትነው ለሚገኙ፣ ጊዜያዊ ነዋሪዎች” ከ62 እስከ 64 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ደብዳቤ ጽፎላቸው ነበር። (1 ጴጥ. 1:1) የተለያየ ባሕል ያላቸው ክርስቲያኖችን ያቀፉት በትንሿ እስያ የሚገኙት እነዚያ ጉባኤዎች ማበረታቻና መመሪያ ያስፈልጋቸው ነበር። ምክንያቱም ተቃዋሚዎች በእነዚህ ወንድሞች ላይ ስደት ያደርሱባቸው እንዲሁም ይሰድቧቸው ነበር። በተጨማሪም “እንደ እሳት [ያሉ] ከባድ ፈተናዎች” አጋጥመዋቸዋል። የሚኖሩትም በጣም አደገኛ በሆነ ወቅት ላይ ነበር። ጴጥሮስ “የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል” ሲል ጽፏል። ደግሞም ጴጥሮስ ይህን ከተናገረ አሥር ዓመት እንኳ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአይሁድ ሥርዓት ጠፍቷል። ታዲያ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉትን አስጨናቂ ነገሮች እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው የሚችለው ምንድን ነው?—1 ጴጥ. 4:4, 7, 12

2, 3. ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲያሳዩ ያበረታታቸው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

2 ጴጥሮስ ለእነዚያ ክርስቲያኖች ከሰጣቸው ማበረታቻዎች መካከል “አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ” የሚል ሐሳብ ይገኝበታል። (1 ጴጥ. 4:9) “እንግዳ ተቀባይነት” የሚለው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ለእንግዶች ፍቅር ወይም ደግነት ማሳየት” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ሆኖም ጴጥሮስ፣ ክርስቲያን ወንድሞቹንና እህቶቹን ያበረታታቸው ‘አንዳቸው ሌላውን’ በእንግድነት እንዲቀበሉ በሌላ አባባል በደንብ የሚያውቋቸውንና የሚቀርቧቸውን ሰዎች እንዲያስተናግዱ መሆኑን ልብ እንበል። የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየታቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

3 እርስ በርስ ያቀራርባቸዋል። አንተስ በግልህ ይህን አልተመለከትክም? ሌሎች ቤታቸው በእንግድነት ጋብዘውህ ያውቃሉ? በዚያ ወቅት ምን ያህል አስደሳች ጊዜ እንዳሳለፋችሁ ታስታውሳለህ? በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የጉባኤህን አባላት አንተ ስትጋብዛቸው ወዳጅነታችሁ አልተጠናከረም? ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በእንግድነት ስንቀበል እነሱን በቅርበት ለማወቅ የተሻለ አጋጣሚ እናገኛለን። በጴጥሮስ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ሁኔታዎች እየተባባሱ ሲሄዱ ይበልጥ መቀራረብ ያስፈልጋቸው ነበር። በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ከሚኖሩ ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—2 ጢሞ. 3:1

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

4 ‘አንዳችን ለሌላው’ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት የምንችልባቸው አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው? የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዳናሳይ እንቅፋት የሚሆኑብንን ነገሮች እንዴት ማሸነፍ እንችላለን? ሌሎች በሚጋብዙን ጊዜስ ጥሩ እንግዶች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

እንግዳ ተቀባይ መሆን የምንችልባቸው አጋጣሚዎች

5. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ እንግዳ ተቀባዮች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

5 በስብሰባዎቻችን ላይ፦ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ ከመንፈሳዊው ማዕድ አብረውን እንዲካፈሉ እንደተጋበዙ እንግዶች አድርገን እንቀበላቸዋለን። ጋባዦቹ ይሖዋ እና ድርጅቱ ናቸው። (ሮም 15:7) አዲሶች ወደ ስብሰባዎቻችን ሲመጡ እኛም እንደ ጋባዥ ሆነን እነሱን የማስተናገድ መብት እናገኛለን። እንግዲያው እነዚህ ሰዎች አለባበሳቸው ወይም የፀጉር አበጣጠራቸው ምንም ዓይነት ቢሆን ሞቅ ያለ አቀባበል ልናደርግላቸው ይገባል። (ያዕ. 2:1-4) አንድ እንግዳ አጠገቡ ወንድሞች እንደሌሉ ካስተዋልን አብሮን እንዲቀመጥ ልንጋብዘው እንችላለን። ፕሮግራሙን እንዲከታተል ብንረዳው እንዲሁም የሚነበቡትን ጥቅሶች አውጥተን ብናሳየው ደስ እንደሚለው የታወቀ ነው። “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል [ማዳበር]” ከምንችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ይህ ነው።—ሮም 12:13

6. በዋነኝነት ቤታችን ልንጋብዛቸው ከሚገቡ እንግዶች መካከል እነማን ይገኙበታል?

6 ምግብ መጋበዝ፦ በጥንት ዘመን ሰዎች እንግዶችን ቤታቸው ምግብ በመጋበዝ ማስተናገዳቸው የተለመደ ነበር። (ዘፍ. 18:1-8፤ መሳ. 13:15፤ ሉቃስ 24:28-30) እንግዶቹን አብረዋቸው እንዲመገቡ መጋበዛቸው ከእነሱ ጋር ወዳጅነትና ሰላማዊ ግንኙነት መመሥረት እንደሚፈልጉ የሚያሳይ ነበር። ታዲያ እኛስ ቤታችን ልንጋብዝ የሚገባው እነማንን ነው? በዋነኝነት ከምንጋብዛቸው እንግዶች መካከል በጉባኤያችን ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ሊገኙበት እንደሚገባ የታወቀ ነው። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን እርስ በርስ መደጋገፋችን አይቀርም። በመሆኑም ከሁሉም ወንድሞቻችን ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረታችንና ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። በ2011 የበላይ አካሉ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የቤቴል ቤተሰብ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የሚያደርግበት ሰዓት ከምሽቱ 12:45 ወደ 12:15 እንዲቀየር ወሰነ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የቤተሰብ ጥናቱ ቀደም ብሎ ማብቃቱ አብዛኞቹ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሌሎች ቤቴላውያንን ክፍላቸው ጋብዘው ለማስተናገድና እነሱም የሚቀርብላቸውን ግብዣ ለመቀበል አመቺ እንዲሆንላቸው ያደርጋል። ሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎችም ተመሳሳይ የሰዓት ማስተካከያ አድርገዋል። ይህ ዝግጅት የቤቴል ቤተሰቦች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንዲቀራረቡ አጋጣሚ ከፍቷል።

7, 8. የይሖዋን ድርጅት ወክለው ለሚመጡ ወንድሞች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

7 የሕዝብ ተናጋሪዎች፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና አንዳንድ ጊዜም የቅርንጫፍ ቢሮው ተወካዮች ወደ ጉባኤያችን ሲመጡ እነዚህን ወንድሞች የማስተናገድ አጋጣሚ እናገኛለን። (3 ዮሐንስ 5-8ን አንብብ።) ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምግብ ወይም ሻይ ቡና መጋበዝ ነው። አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችል ይሆን?

8 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “እኔና ባለቤቴ ባለፉት ዓመታት በርካታ የሕዝብ ተናጋሪዎችንና ሚስቶቻቸውን ቤታችን የመጋበዝ መብት አግኝተናል። እነዚህን ወንድሞች በጋበዝንባቸው ጊዜያት ሁሉ በጣም የተደሰትን ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ ታንጸናል። እንግዶችን በመጋበዛችን ፈጽሞ ተቆጭተን አናውቅም።”

9, 10. (ሀ) ማረፊያ ማዘጋጀት የሚያስፈልገን ለእነማን ሊሆን ይችላል? (ለ) ትልቅ ቤት የሌላቸው ክርስቲያኖችም እንግዶችን ቤታቸው ማሳረፍ ይችላሉ? ምሳሌ ስጥ።

9 ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ እንግዶች፦ በጥንት ዘመን የነበሩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ እንግዶችን ተቀብለው ቤታቸው ያሳርፉ ነበር። (ኢዮብ 31:32፤ ፊልሞና 22) በዘመናችንም እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን ሲጎበኙ ብዙውን ጊዜ ማረፊያ ያስፈልጋቸዋል። በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ክርስቲያኖች እንዲሁም የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለተወሰነ ጊዜ ማረፊያ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ቤታቸውን ያጡ አንዳንድ ቤተሰቦችም ቤታቸው እንደገና እስኪገነባ ድረስ የሚቆዩበት ቦታ ያስፈልጋቸው ይሆናል። እንዲህ ያሉትን ወንድሞች ማሳረፍ የሚችሉት በጣም ምቹ ቤት ያላቸው ክርስቲያኖች ብቻ እንደሆኑ አድርገን ማሰብ የለብንም፤ እነዚህ ወንድሞች ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጊዜያት እንግዶችን ተቀብለው ሊሆን ይችላል። አንተስ ቤትህ ትልቅ ባይሆንም እንኳ እንግዶችን መቀበል ትችል ይሆን?

10 በደቡብ ኮሪያ የሚኖር አንድ ወንድም በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤት የሚካፈሉ ተማሪዎችን ቤቱ ማሳረፉ ጥሩ ትዝታ ጥሎበት አልፏል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔና ባለቤቴ ገና መጋባታችን ሲሆን ቤታችንም ትንሽ ነበረች፤ በመሆኑም እንግዶችን ለመቀበል መጀመሪያ ላይ አመንትቼ ነበር። ሆኖም ተማሪዎቹን ቤታችን በእንግድነት በመቀበላችን አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ ችለናል። አዲስ ተጋቢዎች እንደመሆናችን መጠን፣ ባለትዳሮች አብረው ይሖዋን ማገልገላቸውና መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ መጣጣራቸው ምን ያህል እንደሚያስደስታቸው መመልከታችን ጠቅሞናል።”

11. ወደ ጉባኤያችን ለተዛወሩ ክርስቲያኖች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

11 ወደ ጉባኤያችን የተዛወሩ ክርስቲያኖች፦ አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦች ወይም ግለሰቦች እናንተ ወደምትኖሩበት አካባቢ ተዛውረው ይመጡ ይሆናል። አንዳንዶቹ የመጡት የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሊሆን ይችላል። ሌሎቹ ደግሞ ጉባኤያችሁን እንዲረዱ የተላኩ አቅኚዎች ይሆናሉ። መጀመሪያ ላይ እነዚህ ወንድሞች አንዳንድ ነገሮች ለምሳሌ አካባቢው፣ ጉባኤው ምናልባትም ቋንቋውና ባሕሉ እንግዳ ሊሆኑባቸው ይችላሉ። ቤታችን ሻይ ቡና ብንጋብዛቸው፣ ምግብ ሠርተን ብንጠራቸው አሊያም ደግሞ አብረናቸው ወጣ ብለን ብንዝናና አዳዲስ ጓደኞችን እንዲያፈሩ እንዲሁም ከአዲሱ ሕይወታቸው ጋር እንዲላመዱ እንረዳቸዋለን።

12. እንግዶችን ለማስተናገድ የግድ ብዙ ነገር ማቅረብ እንደማያስፈልግ የሚያሳየው የትኛው ተሞክሮ ነው?

12 እንግዶችን ለማስተናገድ የግድ ብዙ ነገር ማቅረብ አያስፈልግም። (ሉቃስ 10:41, 42ን አንብብ።) አንድ ወንድም ከባለቤቱ ጋር ሚስዮናውያን ሆነው ማገልገል የጀመሩበትን ጊዜ ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦ “ወጣቶች ከመሆናችንም ሌላ ተሞክሮ አልነበረንም፤ በዚያ ላይ ደግሞ ቤተሰቦቻችን ይናፍቁን ነበር። በተለይ አንድ ምሽት ባለቤቴ የቤተሰብ ናፍቆት በጣም አስቸገራት፤ ምንም ባደርግ ላረጋጋት አልቻልኩም። ከዚያም ከምሽቱ 1:30 አካባቢ በራችን ተንኳኳ። የመጣችው መጽሐፍ ቅዱስን የምታጠና አንዲት ሴት ስትሆን ሦስት ብርቱካኖችን ይዛ ነበር። ሴትየዋ አዲሶቹን ሚስዮናውያን ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ ማለት ፈልጋ ነበር። ወደ ቤት እንድትገባ ከጋበዝናት በኋላ የምትጠጣው ውኃ ሰጠናት። ከዚያም ሻይና ሆት ቸኮሌት አፈላን። በወቅቱ ስዋሂሊ ገና አልቻልንም ነበር፤ እሷ ደግሞ እንግሊዝኛ አትችልም። ሆኖም ያ አጋጣሚ ከአካባቢው ወንድሞች ጋር ለመሠረትነው አስደሳች ወዳጅነት መጀመሪያ ሆኗል።”

እንግዳ ተቀባይ እንዳንሆን እንቅፋት የሚፈጥሩብንን ነገሮች ማሸነፍ

13. እንግዳ ተቀባይ መሆን ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

13 እንግዶችን ከመቀበል ወደኋላ ያልክበት ጊዜ አለ? ከሆነ ከወንድሞችህ ጋር አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍና ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችል አጋጣሚ አምልጦሃል። እንግዳ ተቀባይ መሆን የብቸኝነት ስሜትን ለማሸነፍ ከሚረዱ ግሩም መንገዶች አንዱ ነው። ይሁንና ‘አንድ ሰው እንግዳ ተቀባይ እንዳይሆን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?’ የተለያዩ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል።

14. እንግዶችን ለማስተናገድም ሆነ የሌሎችን ግብዣ ለመቀበል ጊዜውና ጉልበቱ እንደሌለን የሚሰማን ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን?

14 ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅ መሆኑ፦ የይሖዋ አገልጋዮች ሥራ የሚበዛባቸው ከመሆኑም ሌላ በአብዛኛው ተደራራቢ ኃላፊነቶች አሉባቸው። በመሆኑም አንዳንዶች እንግዶችን ለማስተናገድ ጊዜውም ሆነ ጉልበቱ እንደሌላቸው ይሰማቸው ይሆናል። አንተም እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ፕሮግራምህን መለስ ብለህ መቃኘትህ ጠቃሚ ነው። ሌሎችን በእንግድነት ለማስተናገድ አሊያም የሚቀርብልህን ግብዣ ለመቀበል የሚያስችል ጊዜና ጉልበት እንድታገኝ በፕሮግራምህ ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ማድረግ ትችል ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች እንግዳ ተቀባይ እንዲሆኑ ያበረታታል። (ዕብ. 13:2) እንግዶችን ለማስተናገድ ጊዜ መመደብ ምንም ስህተት የለውም፤ እንዲያውም እንዲህ ማድረግ ተገቢ ነው። እርግጥ፣ እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን መቀነስ ሊያስፈልግህ ይችላል።

15. አንዳንዶች እንግዳ ለመቀበል የሚፈሩት ለምንድን ነው?

15 ለራስህ ያለህ አመለካከት፦ እንግዶችን መቀበል ብትፈልግም ይህን ማድረግ ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ተሰምቶህ ያውቃል? አንዳንዶች ዓይናፋር ስለሆኑ እንግዶቻቸውን በደንብ ማጫወት እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ የገንዘብ አቅማቸው ውስን ስለሆነ አንዳንድ የጉባኤያቸው አባላት እንደሚያደርጉት እንግዶቻቸውን ጥሩ አድርገው ማስተናገድ እንደማይችሉ ያስባሉ። ቁም ነገሩ ቤታችን ትልቅና በውድ ዕቃዎች የተሞላ መሆኑ አይደለም፤ ቤታችን ንጹሕና ያልተዝረከረከ ከሆነ እንግዶቻችን በግብዣው መደሰታቸው አይቀርም።

16, 17. እንግዶችን መቀበል ሊያስጨንቀን የማይገባው ለምንድን ነው?

16 እንግዶችን መቀበል የሚያስፈራህ ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በብሪታንያ የሚኖር አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዶችን ማስተናገድ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ያስጨንቃል። ሆኖም በይሖዋ አገልግሎት እንደምናከናውነው እንደ ማንኛውም ነገር ሁሉ፣ እንግዶችን መቀበል የሚፈጥረው ጭንቀትም ከምናገኘው ጥቅምና ደስታ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከእንግዶቼ ጋር ቡና ብቻ እየጠጣን በመጫወት አስደሳች ጊዜ አሳልፈን እናውቃለን።” ለእንግዶች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት መስጠት ምንጊዜም ጥሩ ውጤት እንዳለው አስታውስ። (ፊልጵ. 2:4) አብዛኞቹ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ስላጋጠሟቸው ነገሮች ማውራት ያስደስታቸዋል። ወንድሞቻችን ተሞክሯችንን ለመስማት አጋጣሚ የሚያገኙት አንድ ላይ ሰብሰብ ብለን በምንጫወትበት ጊዜ ብቻ ሊሆን ይችላል። አንድ ሌላ የጉባኤ ሽማግሌ ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ ወንድሞችን ቤቴ መጋበዜ፣ አመለካከታቸውን በተሻለ መንገድ ለመረዳት እንዲሁም ስለ እነሱ ይበልጥ ለማወቅ በተለይም ወደ እውነት እንዴት እንደመጡ ለመስማት አጋጣሚ ይሰጠኛል።” ለእንግዶቻችን ፍቅርና አሳቢነት የምናሳይ ከሆነ ሁላችንም በግብዣው እንደምንደሰት አያጠራጥርም።

17 በተለያዩ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች የተካፈሉ ተማሪዎችን በእንግድነት የተቀበለች አንዲት አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ቤቴ ትንሽ ከመሆኑም ሌላ የምጠቀመው ባገለገሉ የቤት ዕቃዎች ነው፤ በመሆኑም መጀመሪያ ላይ ተሳቅቄ ነበር። ይሁንና ከአስተማሪዎቹ የአንዱ ሚስት እንዳልጨነቅ ረዳችኝ። እሷና ባለቤቷ በጉብኝት ሥራ ላይ ሲካፈሉ በጣም አስደሳች ጊዜ ያሳለፉት፣ በቁሳዊ ብዙ ባይኖራቸውም እንደ እነሱ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ በሚያተኩሩ ወንድሞች ቤት ባረፉበት ወቅት እንደሆነ ነገረችኝ፤ ያስተናገዷቸው ወንድሞች ለይሖዋ አገልግሎት ትልቅ ቦታ በመስጠት አኗኗራቸውን ቀላል አድርገዋል። ይህም ልጆች እያለን እናቴ ትለን የነበረውን ነገር አስታወሰኝ፤ ‘ፍቅር ባለበት አትክልት መብላት ይሻላል’ ትል ነበር።” (ምሳሌ 15:17) በእርግጥም በፍቅር ተነሳስታችሁ እንግዶቻችሁን እስካስተናገዳችሁ ድረስ መጨነቅ አያስፈልጋችሁም።

18, 19. እንግዳ ተቀባዮች መሆናችን ለሌሎች ያለንን አሉታዊ አመለካከት ለማስተካከል የሚረዳን እንዴት ነው?

18 ለሌሎች ያለህ አመለካከት፦ በጉባኤያችሁ ውስጥ ባሕርይው ብዙም የማይጥምህ ሰው አለ? ስለ ግለሰቡ ያለህን አሉታዊ አመለካከት ለማስተካከል ምንም ዓይነት ጥረት ካላደረግክ ይህ ስሜትህ ሥር እየሰደደ ሊሄድ ይችላል። ከግለሰቡ ጋር ያለህ የባሕርይ ልዩነት እንግዳ ተቀባይ እንዳትሆን እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ከዚህ ቀደም ቅር አሰኝቶህ ነገሩን ለመርሳት ተቸግረህ ይሆናል።

19 መጽሐፍ ቅዱስ፣ እንግዳ ተቀባይ መሆን ከሌሎች ጋር እንዲያውም ከጠላቶቻችን ጋር እንኳ ያለንን ግንኙነት ለማሻሻል እንደሚረዳ ይናገራል። (ምሳሌ 25:21, 22ን አንብብ።) ሌሎችን መጋበዛችን በመካከላችን ያለውን ቅሬታ ለማስወገድና ሰላማዊ ግንኙነት ለመመሥረት ይረዳናል። አንድን ሰው በእንግድነት ማስተናገዳችን፣ ይሖዋ ይህን ግለሰብ ወደ እውነት እንዲስበው ያደረጉትን ግሩም ባሕርያት ለማስተዋል አጋጣሚ ይፈጥርልናል። (ዮሐ. 6:44) በፍቅር ተነሳስተን አንድን ሰው መጋበዛችን ግንኙነታችን ሙሉ በሙሉ እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል። ወንድሞችህን ለመጋበዝ የሚያነሳሳህ ፍቅር እንዲሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? ፍቅር ለማዳበር የሚረዳህ አንዱ መንገድ በፊልጵስዩስ 2:3 ላይ የሚገኘውን “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ” የሚለውን ማበረታቻ በተግባር ማዋል ነው። ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን ከእኛ የሚበልጡባቸውን መንገዶች ለምሳሌ እምነታቸውን፣ ጽናታቸውን፣ ድፍረታቸውን ወይም ያሏቸውን ሌሎች ክርስቲያናዊ ባሕርያት ለማስተዋል ጥረት ካደረግን ለእነሱ ያለን ፍቅር ይጠናከራል፤ ከልብ ተነሳስተን እነሱን በእንግድነት መቀበልም ቀላል ይሆንልናል።

ጥሩ እንግዶች ሁኑ

ጋባዦች እንግዶቻቸውን ለማስተናገድ ብዙ ዝግጅት ያደርጋሉ (አንቀጽ 20⁠ን ተመልከት)

20. የቀረበልንን ግብዣ ከተቀበልን ቃላችንን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

20 መዝሙራዊው ዳዊት “ይሖዋ ሆይ፣ በድንኳንህ ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ማን ነው?” ሲል ጠይቆ ነበር። (መዝ. 15:1) ከዚያም አምላክ ከእንግዶቹ የሚጠብቃቸውን ባሕርያት ዘርዝሯል። መዝሙራዊው ከጠቀሳቸው ባሕርያት አንዱ ቃልን መጠበቅ ነው፤ ዳዊት የይሖዋ እንግዳ ስለሚሆን ሰው ሲናገር “ጉዳት ላይ ሊጥለው ቢችልም እንኳ ቃሉን አያጥፍም” ብሏል። (መዝ. 15:4) የቀረበልንን ግብዣ ከተቀበልን ያለበቂ ምክንያት ቃላችንን ማጠፍ የለብንም። የጋበዘን ሰው እኛን ለማስተናገድ ብዙ ዝግጅት አድርጎ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም ግብዣውን ከሰረዝን ልፋቱ ሁሉ መና ይቀራል። (ማቴ. 5:37) አንዳንዶች፣ የተሻለ እንደሆነ ያሰቡት ግብዣ ላይ ለመገኘት ሲሉ ቀደም ሲል የተቀበሉትን ግብዣ ይሰርዛሉ። ይህ ለወንድሞቻችን ፍቅርና አክብሮት እንዳለን ያሳያል? የጋበዘን ሰው የሚያቀርብልን ምንም ይሁን ምን ለግብዣው ልባዊ አድናቆት ማሳየት ይኖርብናል። (ሉቃስ 10:7) ከአቅማችን በላይ የሆነ ሁኔታ አጋጥሞን ግብዣውን ለመሰረዝ ከተገደድን ደግሞ ለጋበዘን ሰው እንደማንመጣ ወዲያውኑ በማሳወቅ ፍቅርና አሳቢነት እናሳይ።

21. የጋበዙንን ሰዎች ባሕል ግምት ውስጥ በማስገባት ጥሩ እንግዶች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

21 በእንግድነት በምንጋበዝበት ጊዜ የአካባቢውን ባሕል ማክበራችንም አስፈላጊ ነው። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ሳይጋበዙ ሰው ቤት መሄድ ምንም ችግር የለውም፤ በሌሎች ባሕሎች ግን አስቀድሞ ፕሮግራም መያዝ ይመረጣል። ጋባዦች ምርጥ የሆነውን ነገር ለእንግዶቻቸው አቅርበው ለቤተሰባቸው ከዚያ የቀረውን የሚያቀርቡባቸው አካባቢዎች አሉ፤ በሌሎች ቦታዎች ግን ለሁሉም ሰው የሚቀርበው ተመሳሳይ ማዕድ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች እንግዶች ወደተጋበዙበት ቦታ ሲሄዱ የሆነ ነገር ይዘው መሄዳቸው የተለመደ ነው፤ ሌሎች ደግሞ እንግዳው እንዲህ ማድረግ እንዳለበት ባይሰማው ደስ ይላቸዋል። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ እንግዶች የሚቀርብላቸውን ግብዣ ወዲያውኑ ከመቀበል ይልቅ ትንሽ መግደርደራቸው ተገቢ እንደሆነ ይታሰባል፤ ግብዣን ወዲያው አለመቀበል አክብሮት አለማሳየት እንደሆነ ተደርጎ የሚቆጠርባቸው ባሕሎችም አሉ። እንግዲያው የጋበዙንን ሰዎች ለማስደሰት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ።

22. ‘አንዳችን ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየታችን’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

22 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ “የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል።” (1 ጴጥ. 4:7) በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ መከራ ከፊታችን ይጠብቀናል። ሁኔታዎች እየከፉ በሄዱ መጠን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለንን ፍቅር ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብናል። ጴጥሮስ “አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ” በማለት ለክርስቲያኖች የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው፤ እንግዳ ተቀባይነት በአሁኑ ጊዜም ሆነ ለዘላለም ደስታ የሚያስገኝና አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ነው!—1 ጴጥ. 4:9