በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የይሖዋ ምሥክሮች ሐዋርያው ጳውሎስን ራሰ በራ እንደሆነ አድርገው የሚሥሉት ለምንድን ነው?

እውነቱን ለመናገር በዛሬው ጊዜ ማንም ሰው ስለ ጳውሎስ መልክ በእርግጠኝነት መናገር አይችልም። በጽሑፎቻችን ላይ የሚቀርቡት ሥዕሎች፣ ጳውሎስን ለመግለጽ የገቡ ሥዕላዊ መግለጫዎች ናቸው እንጂ በተረጋገጡ አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረቱ አይደሉም።

ይሁንና የጳውሎስ መልክ ምን ሊመስል እንደሚችል የሚጠቁሙ አንዳንድ መረጃዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የመጋቢት 1, 1902 እትም እንዲህ ይላል፦ “የጳውሎስን መልክ በተመለከተ፦ . . . በ150 ዓ.ም. ገደማ በተዘጋጀ ‘አክትስ ኦቭ ፖል ኤንድ ቴክላ’ የተሰኘ . . . ጽሑፍ ላይ ስለ ጳውሎስ የሚገልጽ ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና ምናልባትም ከሁሉ የተሻለ ሐሳብ ይገኛል። በዚህ ጽሑፍ ላይ ጳውሎስ ‘ቁመቱ አጭር፣ ራሰ በራ፣ እግረ ወረሃ እና ፈርጣማ ሰውነት ያለው፣ ቅንድቦቹ የገጠሙ፣ አፍንጫው ረጅም’ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል።”

ዚ ኦክስፎርድ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ክርስቺያን ቸርች (የ1997 እትም) “‘ዚ አክትስ ኦቭ ፖል ኤንድ ቴክላ’ ከያዛቸው ሐሳቦች አንዳንዶቹ ከታሪክ አንጻር ጨርሶ እውነት አይደሉም ማለት አይቻልም’ ይላል። ዚ አክትስ ኦቭ ፖል ኤንድ ቴክላ የተሰኘው ጥንታዊ ጽሑፍ፣ ከተዘጋጀ በኋላ በነበሩት ጥቂት መቶ ዓመታት ትልቅ ቦታ ይሰጠው ነበር፤ በአሁኑ ጊዜ 80 የሚያህሉ የዚህ መጽሐፍ ጥንታዊ የግሪክኛ ቅጂዎች መኖራቸውና ወደ ሌሎች ቋንቋዎችም መተርጎሙ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። በመሆኑም በጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡት ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ አንዳንድ ጥንታዊ ጽሑፎች የሐዋርያው ጳውሎስ መልክ ምን ይመስል እንደነበር ከሚሰጡት ሐሳብ ጋር ይስማማሉ።

ሆኖም ከጳውሎስ ጋር በተያያዘ፣ ከመልኩ የበለጠ ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮች እንዳሉ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ አገልግሎቱን እያከናወነ በነበረበት ጊዜም ሥጋዊ አስተሳሰብ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች “በመካከላችን በአካል ሲገኝ . . . ደካማ ከመሆኑም በላይ ንግግሩ የተናቀ ነው” በማለት ተችተውት ነበር። (2 ቆሮ. 10:10) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ክርስቲያን የሆነው ኢየሱስ ራሱ በተአምራዊ መንገድ ስለተገለጠለት መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። በተጨማሪም ጳውሎስ “በአሕዛብ . . . ፊት [የኢየሱስን ስም] እንዲሸከም [ለክርስቶስ] የተመረጠ ዕቃ” በመሆን ያከናወነውን ሥራ ማሰብ እንችላለን። (ሥራ 9:3-5, 15፤ 22:6-8) ከዚህም ሌላ ጳውሎስ በይሖዋ መንፈስ መሪነት ከጻፋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ምን ያህል ጥቅም እንደምናገኝ አንርሳ።

ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ስላከናወናቸው ነገሮች በትምክህት አልተናገረም፤ ስለ መልክና ቁመናውም ቢሆን የገለጸው ነገር የለም። (ሥራ 26:4, 5፤ ፊልጵ. 3:4-6) እንዲያውም “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስና ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:9) ከጊዜ በኋላም “ከቅዱሳን ሁሉ ለማንስ ለእኔ ይህ ጸጋ ተሰጠኝ፤ ይህም ሊደረስበት ስለማይችለው የክርስቶስ ብልጽግና የሚገልጸውን ምሥራች ለአሕዛብ እንዳውጅ [ነው]” በማለት ጽፏል። (ኤፌ. 3:8) ይህ ምሥራች ከጳውሎስ መልክ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጥርጥር የለውም።