በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥምቀት—ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት

ጥምቀት—ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት

“ጥምቀት . . . እናንተን እያዳናችሁ ነው።”—1 ጴጥ. 3:21

መዝሙሮች፦ 52, 41

1, 2. (ሀ) አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች ልጃቸው መጠመቅ እንደሚፈልግ ሲገልጽ ምን ይሰማቸዋል? (ለ) የጥምቀት እጩዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው እንደሆነ ጥያቄ የሚቀርብላቸው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

ማሪያ * እና ሌሎቹ የጥምቀት እጩዎች ተነስተው ቆሙ፤ የማሪያ ወላጆችም ፕሮግራሙን በትኩረት እየተከታተሉ ነው። ከዚያም ትንሿ ልጃቸው ተናጋሪው ላነሳቸው ሁለት ጥያቄዎች ጎላ ባለ ድምፅ መልስ ሰጠች። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ማሪያ ተጠመቀች።

2 የማሪያ ወላጆች ልጃቸው ራሷን ለይሖዋ ለመወሰንና ለመጠመቅ ውሳኔ በማድረጓ በጣም ተደስተዋል። ያም ቢሆን እናቷ አንዳንድ ያሳሰቧት ነገሮች ነበሩ። ‘ማሪያ ለመጠመቅ ዕድሜዋ አልደረሰ ይሆን? ጥምቀት በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ እርምጃ መሆኑ ገብቷታል? ሳትጠመቅ ትንሽ ብትቆይ ይሻል ይሆን?’ የሚሉት ጥያቄዎች ተፈጥረውባት ነበር። አፍቃሪ የሆኑ በርካታ ወላጆች፣ ልጃቸው መጠመቅ እንደሚፈልግ ሲገልጽ እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች ወደ አእምሯቸው ይመጣሉ። (መክ. 5:5) ደግሞም ይህ የሚያስገርም አይደለም፤ ምክንያቱም ራስን መወሰንና መጠመቅ አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው።— ራስህን ለይሖዋ ወስነሃል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

3, 4. (ሀ) ሐዋርያው ጴጥሮስ ጥምቀት አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው? (ለ) ጴጥሮስ መጠመቅን ኖኅ መርከብ ከመሥራቱ ጋር ያመሳሰለው ለምንድን ነው?

3 ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ጥምቀት ሲጽፍ፣ ኖኅ መርከብ መሥራቱን ከጠቀሰ በኋላ “አሁንም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት እናንተን እያዳናችሁ ነው” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 3:20, 21ን አንብብ።) መርከቡ፣ ኖኅ የአምላክን ፈቃድ የመፈጸም ልባዊ ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነበር። ኖኅ ይሖዋ የሰጠውን ሥራ በታማኝነት አከናውኗል። በእርግጥም ኖኅና ቤተሰቡ እምነታቸውን በተግባር ማሳየታቸው ከጥፋት ውኃው ለመትረፍ አስችሏቸዋል። ይሁንና ጴጥሮስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው ለምንድን ነው?

4 መርከቡ፣ ኖኅ በአምላክ ላይ እምነት እንዳለው የሚጠቁም ማስረጃ ነበር። በተመሳሳይም አንድ ሰው በሕዝብ ፊት መጠመቁ የሚያሳየው ነገር አለ። ጥምቀት፣ ግለሰቡ በክርስቶስ መሥዋዕትና ትንሣኤ ላይ እምነት በማሳደር ራሱን ለይሖዋ መወሰኑን ያሳያል። ኖኅ እንዳደረገው ሁሉ፣ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ደቀ መዛሙርትም አምላክ የሰጣቸውን ሥራ በታዛዥነት ያከናውናሉ። ኖኅ ከጥፋት ውኃው እንደተረፈ ሁሉ ታማኝ የሆኑ የተጠመቁ ክርስቲያኖችም ይህ ክፉ ዓለም በሚጠፋበት ጊዜ በሕይወት ይተርፋሉ። (ማር. 13:10፤ ራእይ 7:9, 10) ራስን መወሰን እንዲሁም መጠመቅ በጣም አስፈላጊ እርምጃ የሆነው ለዚህ ነው። ለመጠመቅ ዛሬ ነገ የሚል ሰው የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ሊያጣ ይችላል።

5. በዚህ ርዕስ ውስጥ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?

5 ጥምቀት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እርምጃ ከመሆኑ አንጻር የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች ማንሳታችን ተገቢ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥምቀት ምን ይላል? አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርበታል? ልጃችንን አሊያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን በምናስጠናበት ጊዜ፣ ጥምቀት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን በአእምሯችን መያዝ ያለብንስ ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥምቀት ምን ይላል?

6, 7. (ሀ) ዮሐንስ ጋ የመጡት ሰዎች ጥምቀት ምን ያሳይ ነበር? (ለ) ዮሐንስ ካከናወናቸው ጥምቀቶች ሁሉ ለየት የሚለው የማን ጥምቀት ነው? ለምንስ?

6 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥምቀት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው መጥምቁ ዮሐንስ ካከናወነው ጥምቀት ጋር ተያይዞ ነው። (ማቴ. 3:1-6) ለመጠመቅ ወደ ዮሐንስ የመጡት ሰዎች ይህን ያደረጉት የሙሴን ሕግ በመተላለፍ ለፈጸሙት ኃጢአት ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት ነበር። ይሁን እንጂ ዮሐንስ ካከናወናቸው ጥምቀቶች ሁሉ የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጥምቀት፣ ከኃጢአት ንስሐ ከመግባት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ልብ ማለት ያስፈልጋል። ዮሐንስ፣ የአምላክ ልጅ የሆነውን ኢየሱስን የማጥመቅ ልዩ መብት አግኝቷል። (ማቴ. 3:13-17) ፍጹም የሆነው ኢየሱስ ኃጢአት ስላልሠራ ንስሐ መግባት አላስፈለገውም። (1 ጴጥ. 2:22) ኢየሱስ የተጠመቀው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ማቅረቡን ለማሳየት ነው።—ዕብ. 10:7

7 በተጨማሪም ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ያከናውን በነበረበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ሰዎችን አጥምቀዋል። (ዮሐ. 3:22፤ 4:1, 2) ዮሐንስ እንዳጠመቃቸው ሰዎች ሁሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያጠመቋቸው ሰዎችም የተጠመቁት፣ የሙሴን ሕግ በመተላለፍ ለፈጸሙት ኃጢአት ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት ነበር። ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ግን ተከታዮቹ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች የሚጠመቁበት ምክንያት ከዚህ የተለየ ሆኗል።

8. (ሀ) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለተከታዮቹ ምን መመሪያ ሰጥቷቸዋል? (ለ) ክርስቲያኖች መጠመቃቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ይኸውም በ33 ዓ.ም. ከ500 ለሚበልጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ምናልባትም ልጆች ተገልጦ ነበር። የሚከተለውን መመሪያ የሰጠው በዚያ ወቅት ሳይሆን አይቀርም፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ቆሮ. 15:6) ኢየሱስ፣ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ስለማድረግ መመሪያ በሰጠበት ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተከታዮቹ በቦታው የነበሩ ይመስላል። ኢየሱስ ይህንን መመሪያ መስጠቱ፣ ጥምቀት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመሆንን ቀንበር ለመሸከም ከሚፈልጉ ሁሉ የሚጠበቅ ብቃት መሆኑን በግልጽ ያሳያል። (ማቴ. 11:29, 30) አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማገልገል የሚፈልግ ማንኛውም ሰው፣ ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ የሚጫወተው ሚና እንዳለ አምኖ መቀበል ይኖርበታል። ግለሰቡ ይህን አምኖ ከተቀበለ መጠመቅ ይችላል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የውኃ ጥምቀት ይህ ብቻ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በግልጽ እንደሚያሳየው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አዳዲስ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ጥምቀት አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። ደግሞም የሚጠመቁበትን ጊዜ ሳያስፈልግ አላዘገዩትም።—ሥራ 2:41፤ 9:18፤ 16:14, 15, 32, 33

ዛሬ ነገ አትበሉ

9, 10. ጥምቀትን በተመለከተ ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እና ከሐዋርያው ጳውሎስ ታሪክ ምን እንማራለን?

9 የሐዋርያት ሥራ 8:35, 36ን አንብብ። የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ምሳሌ እንመልከት፤ ወደ ይሁዲነት የተለወጠው ይህ ሰው ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ወደ አገሩ እየተመለሰ ነበር። ፊልጶስ፣ የይሖዋ መልአክ የሰጠውን መመሪያ በመከተል ወደ ኢትዮጵያዊው ቀርቦ “ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች ነገረው።” ታዲያ ኢትዮጵያዊው ምን ምላሽ ሰጠ? ለተማረው እውነት ልባዊ አድናቆት እንዳደረበት ቀጥሎ ካደረገው ነገር መመልከት ይቻላል። ይህ ግለሰብ፣ ይሖዋ ከክርስቲያኖች የሚጠብቀውን ብቃት ማሟላት ስለፈለገ ወዲያውኑ ተጠመቀ።

10 ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረን አንድ አይሁዳዊ ምሳሌም እንውሰድ። ይህ ሰው የተወለደው፣ ራሱን ለአምላክ በወሰነ ብሔር ውስጥ ነው። ይሁንና በወቅቱ አይሁዳውያን ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን ልዩ ዝምድና አጥተው ነበር። ግለሰቡ ለአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ ወጎች ከፍተኛ ቅንዓት ነበረው፤ ሆኖም ከዚያ የላቀ ነገር እንዳለ ተማረ። ለዚህ ሰው የመሠከረለት ከሞት የተነሳውና ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ ይህ ግለሰብ ምን ምላሽ ሰጠ? ሐናንያ የተባለ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ያደረገለትን እርዳታ በደስታ ተቀበለ። ከዚያ በኋላ ስለተከናወነው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ተነስቶ ተጠመቀ” ይላል። (ሥራ 9:17, 18፤ ገላ. 1:14) ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው አይሁዳዊው ሳኦል እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ሆኖም እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ነገር አለ፤ ጳውሎስ፣ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ስለሚጫወተው ሚና እውነቱን እንደተገነዘበ እርምጃ ወስዷል። ጳውሎስ ወዲያውኑ ተጠምቋል።—የሐዋርያት ሥራ 22:12-16ን አንብብ።

11. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለመጠመቅ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? (ለ) አዲሶች ራሳቸውን ወስነው ሲጠመቁ ምን ይሰማናል?

11 በዛሬው ጊዜ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳሉ። እምነት ያላቸውና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልባዊ አድናቆት ያዳበሩ ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ሰዎች፣ ራሳቸውን ለአምላክ ከመወሰንና ከመጠመቅ ወደኋላ አይሉም። ለጥምቀት እጩዎች ተብሎ የሚዘጋጀው ንግግር በሁሉም ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። የይሖዋ ምሥክሮች አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እውነትን ተቀብሎ እድገት ሲያደርግና ሲጠመቅ በጣም ይደሰታሉ። ክርስቲያን ወላጆችም ቢሆኑ ከሚጠመቁት አዳዲስ ደቀ መዛሙርት መካከል ልጆቻቸውን መመልከታቸው እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ነው። በ2017 የአገልግሎት ዓመት ከ284,000 የሚበልጡ “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት ተጠምቀዋል። (ሥራ 13:48) በእርግጥም እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት፣ ጥምቀት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት መሆኑን ተገንዝበዋል። ይሁን እንጂ ከመጠመቃቸው በፊት የትኞቹን እርምጃዎች ወስደዋል?

12. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመጠመቁ በፊት የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ አለበት?

12 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመጠመቁ በፊት ስለ አምላክ፣ ስለ ዓላማዎቹና የሰው ልጆችን ለማዳን ስላደረገው ዝግጅት ትክክለኛ እውቀት ማግኘት እንዲሁም በተማረው ነገር ላይ እምነት ማሳደር ይገባዋል። (1 ጢሞ. 2:3-6) እንዲህ ያለው እምነት፣ ተማሪው አምላክን ከሚያሳዝኑ ድርጊቶች እንዲርቅና ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲኖር ያነሳሳዋል። (ሥራ 3:19) አንድ ግለሰብ የአምላክን መንግሥት እንዳይወርስ በሚያደርግ በማንኛውም ድርጊት እየተካፈለ ራሱን ለአምላክ ቢወስን ይህ እርምጃ ተቀባይነት እንደማይኖረው ጥርጥር የለውም። (1 ቆሮ. 6:9, 10) ሆኖም ላቅ ያሉትን የይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ማክበር ብቻውን በቂ አይደለም። በጽድቅ ጎዳና ላይ መመላለስ የሚፈልግ ግለሰብ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም ሕይወት አድን በሆነው የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ አቅሙ በፈቀደ መጠን መካፈል ይኖርበታል። ኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሥራ እንደሚያከናውኑ ተናግሯል። (ሥራ 1:8) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እነዚህን እርምጃዎች ከወሰደ በኋላ ራሱን መወሰኑን ለይሖዋ በጸሎት ቢገልጽ ተቀባይነት ይኖረዋል፤ ከዚያም በሕዝብ ፊት መጠመቅ ይችላል።

ጥናቶቻችሁ ለመጠመቅ ግብ እንዲያወጡ እርዷቸው

ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና ጥምቀት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በተገቢው ጊዜ ሁሉ ታስረዳቸዋለህ? (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. መጽሐፍ ቅዱስን ስናስጠና ጥምቀት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት መሆኑን በአእምሯችን መያዝ ያለብን ለምንድን ነው?

13 ልጆቻችንንም ሆኑ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን እድገት እንዲያደርጉ በምንረዳበት ጊዜ፣ ጥምቀት ከእውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሚጠበቅ ብቃት መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። ይህንን በአእምሯችን ከያዝን ራስን መወሰንና ጥምቀት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በተገቢው ጊዜ ሁሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ከመናገር ወደኋላ አንልም። በእርግጥም ልጆቻችንም ሆኑ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ እንፈልጋለን!

14. ማንኛውንም ሰው እንዲጠመቅ ጫና ልናሳድርበት የማይገባው ለምንድን ነው?

14 እርግጥ ነው፣ ማናችንም ብንሆን ልጃችንን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ወይም ሌላ ማንኛውንም ሰው እንዲጠመቅ ጫና ልናሳድርበት አይገባም። ይሖዋም ቢሆን ማንም ተገድዶ እንዲያገለግለው አይፈልግም። (1 ዮሐ. 4:8) ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በምናስጠናበት ጊዜ ከአምላክ ጋር በግለሰብ ደረጃ ዝምድና የመመሥረትን አስፈላጊነት ጎላ አድርገን ልንገልጽላቸው ይገባል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለእውነት ልባዊ አድናቆት ሲያድርበት እንዲሁም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመሆንን ቀንበር ለመሸከም ፍላጎት ሲያዳብር ለመጠመቅ ይነሳሳል።—2 ቆሮ. 5:14, 15

15, 16. (ሀ) አንድ ሰው ለመጠመቅ የተወሰነ ዕድሜ ላይ መድረስ አለበት? አብራራ። (ለ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሌላ ሃይማኖት አባል እያለ ተጠምቆ የነበረ ቢሆንም እንኳ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን መጠመቅ የሚኖርበት ለምንድን ነው?

15 አንድ ሰው በስንት ዓመቱ መጠመቅ እንዳለበት የሚገልጽ መመሪያ የለም። ደግሞም እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እድገት የሚያደርግበት ፍጥነት ይለያያል። ብዙዎች በልጅነታቸው የሚጠመቁ ሲሆን ከዚያ በኋላም ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ይኖራሉ። ሌሎች ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚማሩት በዕድሜ ከገፉ ምናልባትም ከ100 ዓመት በላይ ከሆናቸው በኋላ ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን የመጠመቅን አስፈላጊነት በመገንዘባቸው ተጠምቀዋል!

16 መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ አንዲት በዕድሜ የገፉ ሴት፣ ቀደም ሲል በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ተጠምቀው ስለነበር አሁንም በድጋሚ መጠመቃቸው አስፈላጊ ስለመሆኑ አስጠኚያቸውን ጠየቋት። አስጠኚያቸው ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አሳየቻቸው። ሴትየዋም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥምቀት ምን እንደሚል ስለተገነዘቡ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቁ። በወቅቱ ዕድሜያቸው ወደ 70ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ቢሆንም መጠመቅ እንደማያስፈልጋቸው አልተሰማቸውም። በእርግጥም ጥምቀት ተቀባይነት የሚኖረው ስለ ይሖዋ ፈቃድ ባለን ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ብቻ ነው። በመሆኑም አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በሌላ ሃይማኖት ውስጥ እያሉ ተጠምቀው የነበረ ቢሆንም በድጋሚ መጠመቅ ይኖርባቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 19:3-5ን አንብብ።

17. አንድ ሰው በሚጠመቅበት ዕለት በቁም ነገር ሊያስብበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

17 አንድ ሰው በሚጠመቅበት ዕለት በጣም እንደሚደሰት የታወቀ ነው። ሆኖም በዚያ ዕለት፣ ስላደረገው ውሳኔ በቁም ነገር ማሰቡም ተገቢ ነው። ራስን ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር ተስማምቶ መኖር ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። ኢየሱስ የእሱ ደቀ መዝሙር መሆንን፣ ቀንበር ከመሸከም ጋር ያመሳሰለው ለዚህ ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው [ሊኖሩ]” እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—2 ቆሮ. 5:15፤ ማቴ. 16:24

18. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

18 በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰችው የማሪያ እናት እነዚያ ጥያቄዎች የተፈጠሩባት፣ ጥምቀት በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ስለተገነዘበች ነው። ወላጆች ከሆናችሁ እናንተም የሚከተሉት ጥያቄዎች ወደ አእምሯችሁ ይመጡ ይሆናል፦ ‘ልጄ ለመጠመቅ ዝግጁ ነው? ራሱን ለይሖዋ ለመወሰን የሚያስችል በቂ እውቀት አለው? ልጄ ከመጠመቁ በፊት በትምህርቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስና ጥሩ ሥራ ቢይዝ ይሻል ይሆን? ከተጠመቀ በኋላ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምስ?’ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እነዚህን ጥያቄዎች እንመረምራለን፤ በተጨማሪም ክርስቲያን ወላጆች ስለ ጥምቀት ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

^ አን.1 ስሟ ተቀይሯል።