በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 11

የይሖዋን ድምፅ ስሙ

የይሖዋን ድምፅ ስሙ

“ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት።”—ማቴ. 17:5

መዝሙር 89 ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ

የትምህርቱ ዓላማ *

1-2. (ሀ) ይሖዋ ለሰው ልጆች ሐሳቡን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

ይሖዋ ሐሳቡን ለእኛ መግለጽ ያስደስተዋል። በጥንት ጊዜ ሐሳቡን ለአገልጋዮቹ ለመግለጽ ነቢያትን፣ መላእክትንና ልጁን ክርስቶስ ኢየሱስን ተጠቅሟል። (አሞጽ 3:7፤ ገላ. 3:19፤ ራእይ 1:1) በዛሬው ጊዜ ደግሞ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቀማል። ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠን የእሱን መንገድና አስተሳሰብ መረዳት እንድንችል ነው።

2 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ይሖዋ በሦስት የተለያዩ አጋጣሚዎች ከሰማይ ተናግሯል። ይሖዋ በእነዚህ አጋጣሚዎች ምን እንደተናገረ፣ የተናገራቸው ነገሮች ምን ትርጉም እንዳላቸውና ከተናገራቸው ነገሮች ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።

“አንተ የምወድህ ልጄ ነህ”

3. በማርቆስ 1:9-11 መሠረት ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ይሖዋ ምን ተናግሯል? ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት የትኞቹን አስፈላጊ እውነታዎች ያረጋግጣሉ?

3 ይሖዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰማይ የተናገረበት ዘገባ የሚገኘው በማርቆስ 1:9-11 ላይ ነው። (ጥቅሱን አንብብ።) ይሖዋ “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” በማለት ተናግሯል። ኢየሱስ አባቱ ለእሱ ያለውን ፍቅርና በእሱ ላይ ያለውን እምነት ሲገልጽ ሲሰማ ልቡ ምን ያህል ተነክቶ ይሆን! ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት ስለ ኢየሱስ ሦስት አስፈላጊ እውነታዎችን ያረጋግጣሉ። አንደኛ፣ ኢየሱስ የይሖዋ ልጅ ነው። ሁለተኛ፣ ይሖዋ ልጁን ይወደዋል። ሦስተኛ፣ ይሖዋ በልጁ ደስ ይሰኛል። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመልከት።

4. ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ከአምላክ ጋር ምን ዓይነት አዲስ ዝምድና መሥርቷል?

4 ‘አንተ ልጄ ነህ።’ ይሖዋ እነዚህን ቃላት በመናገር ከሚወደው ልጁ ከኢየሱስ ጋር አዲስ ዓይነት ዝምድና እንደመሠረተ አሳይቷል። ኢየሱስ ሰማይ ላይ ሳለ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ነበር። በተጠመቀበት ወቅት ግን በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል። በዚህ ወቅት ይሖዋ በመንፈስ የተቀባው ልጁ ኢየሱስ ወደ ሰማይ በመመለስ ንጉሥና ሊቀ ካህናት ሆኖ የማገልገል ተስፋ እንዳለው ጠቁሟል። (ሉቃስ 1:31-33፤ ዕብ. 1:8, 9፤ 2:17) ስለዚህ ኢየሱስ ሲጠመቅ አባቱ ‘አንተ ልጄ ነህ’ ያለበት በቂ ምክንያት ነበረው።—ሉቃስ 3:22

ሌሎች አድናቆታቸውን ሲገልጹልንና ሲያበረታቱን እንደሰታለን (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት) *

5. ይሖዋ ፍቅሩን በመግለጽና ሌሎችን በማበረታታት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

5 “የምወድህ።” ይሖዋ ልጁን እንደሚወደውና ደስ እንደሚሰኝበት በመግለጽ የተወው ግሩም ምሳሌ ሌሎችን የምናበረታታበትን አጋጣሚ መፈለግ እንዳለብን ያስገነዝበናል። (ዮሐ. 5:20) ከፍ አድርገን የምንመለከተው ሰው ለእኛ ያለውን ፍቅር ሲገልጽልንና ላከናወንነው መልካም ነገር ሲያመሰግነን ደስ ይለናል። በተመሳሳይም በጉባኤያችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም የቤተሰባችን አባላት የእኛ ፍቅርና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ለሌሎች አመስጋኝነታችንን መግለጻችን እምነታቸውን ለማጠናከርና ይሖዋን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ለማበረታታት ያስችለናል። በተለይ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን ማበረታታት ይኖርባቸዋል። ልጆቻቸውን ከልብ ማመስገናቸውና ፍቅራቸውን መግለጻቸው ልጆቹ ስኬታማ እንዲሆኑ ይረዳል።

6. በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው?

6 “በአንተ ደስ ይለኛል።” ይህ አገላለጽ ይሖዋ ልጁ የአባቱን ፈቃድ በታማኝነት እንደሚፈጽም ያለውን እምነት ያሳያል። ይሖዋ በልጁ ይተማመንበታል፤ ስለዚህ እኛም ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎች ሁሉ ኢየሱስ በታማኝነት እንደሚያስፈጽም ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። (2 ቆሮ. 1:20) ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ስንመረምር ከእሱ ለመማርና የእሱን ፈለግ ለመከተል ያለን ቁርጠኝነት ይበልጥ ይጠናከራል። ይሖዋ በኢየሱስ ላይ እምነት እንደነበረው ሁሉ አገልጋዮቹም በቡድን ደረጃ ከልጁ መማራቸውን እንደሚቀጥሉ እምነት አለው።—1 ጴጥ. 2:21

“እሱን ስሙት”

7. በማቴዎስ 17:1-5 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ከሰማይ የተናገረው በየትኛው አጋጣሚ ነው? ምን በማለትስ ተናግሯል?

7 ማቴዎስ 17:1-5ን አንብብ። ይሖዋ ለሁለተኛ ጊዜ ከሰማይ የተናገረው ኢየሱስ ‘በተለወጠበት’ ወቅት ነው። ኢየሱስ ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ አንድ ከፍ ያለ ተራራ ሄደ። በዚያም እነዚህ ሐዋርያት አስደናቂ ራእይ ተመለከቱ። የኢየሱስ ፊት በደማቁ አበራ፤ ልብሱም ማንጸባረቅ ጀመረ። ከዚያም ሙሴንና ኤልያስን የሚወክሉ ሁለት ሰዎች ተገልጠው ከኢየሱስ ጋር ከፊቱ ስለሚጠብቀው ሞትና ስለ ትንሣኤው ይነጋገሩ ጀመር። ሦስቱ ሐዋርያት “እንቅልፍ ተጫጭኗቸው” የነበረ ቢሆንም ይህን አስገራሚ ራእይ የተመለከቱት ሙሉ በሙሉ ነቅተው ነው። (ሉቃስ 9:29-32) ከዚያም ብሩህ ደመና ከጋረዳቸው በኋላ ከደመናው ውስጥ አንድ ድምፅ ሰሙ። ይህ ድምፅ የአምላክ ድምፅ ነበር! ይሖዋ፣ ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት እንዳደረገው ሁሉ በዚህ ጊዜም “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ልጁን እንደሚወደውና ደስ እንደሚሰኝበት ገለጸ። በዚህ ጊዜ ግን “እሱን ስሙት” በማለት አክሎ ተናገረ።

8. ራእዩ በኢየሱስና በደቀ መዛሙርቱ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል?

8 ይህ ራእይ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ሲሾም ምን ያህል ክብርና ኃይል እንደሚኖረው ያሳያል። ራእዩ ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀውን መከራና አሰቃቂ ሞት በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ብርታትና ጥንካሬ እንዲያገኝ እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም የደቀ መዛሙርቱን እምነት አጠናክሮላቸዋል። ወደፊት በንጹሕ አቋማቸው ላይ የሚደርሰውን ፈተና ለመቋቋምና ለበርካታ ዓመታት ሊያከናውኑት የሚገባውን ሥራ ለመወጣት የሚያስችል ጥንካሬ ሰጥቷቸዋል። ከ30 ዓመታት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ስለተለወጠበት ራእይ የጠቀሰ ሲሆን ይህም ራእዩን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በሚገባ እንደሚያስታውሰው ያሳያል።—2 ጴጥ. 1:16-18

9. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ጠቃሚ ምክር ሰጥቷቸዋል?

9 “እሱን ስሙት።” ይሖዋ ልጁ የተናገራቸውን ነገሮች እንድንሰማና እንድንታዘዝ ያለውን ፍላጎት ግልጽ አድርጓል። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ምን ነገሮችን ተናግሯል? ኢየሱስ ልንሰማቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮችን ተናግሯል! ለምሳሌ ተከታዮቹ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ እንዳለባቸው ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ አስተምሯቸዋል፤ እንዲሁም ነቅተው እንዲጠብቁ በተደጋጋሚ አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 24:42፤ 28:19, 20) በተጨማሪም ሕይወት ለማግኘት ከፍተኛ ተጋድሎ እንዲያደርጉ የመከራቸው ከመሆኑም ሌላ ተስፋ እንዳይቆርጡ አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 13:24) ከዚህም በላይ ተከታዮቹ እርስ በርስ መዋደድ፣ አንድነታቸውን መጠበቅና ትእዛዛቱን መፈጸም እንደሚያስፈልጋቸው አጽንኦት ሰጥቶ ተናግሯል። (ዮሐ. 15:10, 12, 13) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ምክር ምንኛ ጠቃሚ ነው! ይህ ምክር በዚያን ጊዜ ጠቃሚ እንደነበር ሁሉ ዛሬም ጠቃሚ ነው።

10-11. ኢየሱስን እንደምንሰማ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ “ከእውነት ጎን የቆመ ሁሉ ቃሌን ይሰማል” ብሏል። (ዮሐ. 18:37) የኢየሱስን ድምፅ እንደምንሰማ የምናሳየው “እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ነው። (ቆላ. 3:13፤ ሉቃስ 17:3, 4) በተጨማሪም “አመቺ በሆነ ጊዜም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ” ምሥራቹን በቅንዓት በመስበክ ድምፁን እንደምንሰማ እናሳያለን።—2 ጢሞ. 4:2

11 ኢየሱስ “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 10:27) የክርስቶስ ተከታዮች ቃሉን በማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ በማድረግ ጭምር ኢየሱስን እንደሚሰሙ ያሳያሉ። ‘የኑሮ ጭንቀት’ ትኩረታቸውን እንዲከፋፍለው አይፈቅዱም። (ሉቃስ 21:34) ከዚህ ይልቅ በተፈታታኝ ሁኔታዎች ሥር እንኳ በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጡት የኢየሱስን ትእዛዛት ለመፈጸም ነው። በርካታ ወንድሞቻችን የተቃዋሚዎችን ጥቃት፣ አስከፊ ድህነትንና የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ የተለያዩ ፈተናዎች እየደረሱባቸው ነው። ሆኖም ምንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍላቸው ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ለመጠበቅ ቆርጠዋል። ኢየሱስ ለእነዚህ ወንድሞች የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥቷል፦ “እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው። እኔን የሚወደኝን ሁሉ ደግሞ አባቴ ይወደዋል።”—ዮሐ. 14:21

አገልግሎታችን ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ይረዳናል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት) *

12. ኢየሱስን እንደምንሰማ የምናሳይበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?

12 ኢየሱስን እንደምንሰማ የምናሳይበት ሌላም መንገድ አለ፤ ይህም በመካከላችን ሆነው አመራር እንዲሰጡ ከሾማቸው ጋር በመተባበር ነው። (ዕብ. 13:7, 17) የአምላክ ድርጅት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ ማስተካከያዎችን አድርጓል፤ ከእነዚህ መካከል ለአገልግሎት በምንጠቀምባቸው መሣሪያዎችና ዘዴዎች ላይ፣ በሳምንቱ መካከል በምናደርገው ስብሰባ ይዘት ላይ እንዲሁም የስብሰባ አዳራሾችን በምንገነባበት፣ በምናድስበትና በምንጠግንበት መንገድ ላይ የተደረጉት ለውጦች ይገኙበታል። በዚህ ረገድ ለተሰጠን ፍቅር የሚንጸባረቅበትና በሚገባ የታሰበበት መመሪያ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ድርጅቱ የሚሰጠንን ወቅታዊ አመራር ለመከተል የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርክልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

13. ኢየሱስን መስማት ምን ጥቅም ያስገኛል?

13 ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶች በሙሉ መስማታችን ይጠቅመናል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ትምህርቶቹ እረፍት እንደሚያስገኙ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። “[ለራሳችሁ] እረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና” ብሏቸዋል። (ማቴ. 11:28-30) ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚናገሩትን አራት የወንጌል ዘገባዎች አካትቶ የያዘው የአምላክ ቃል እረፍት ይሰጠናል፣ መንፈሳዊ ኃይላችንን ያድስልናል እንዲሁም ጥበበኛ ያደርገናል። (መዝ. 19:7፤ 23:3) ኢየሱስ “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” ብሏል።—ሉቃስ 11:28

‘ስሜን አከብረዋለሁ’

14-15. (ሀ) በዮሐንስ 12:27, 28 ላይ የሚገኘው ይሖዋ ለሦስተኛ ጊዜ ከሰማይ የተናገረበት አጋጣሚ የትኛው ነው? (ለ) ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት ኢየሱስን አጽናንተውትና አበረታተውት የሚሆነው ለምንድን ነው?

14 ዮሐንስ 12:27, 28ን አንብብ። ይሖዋ ለሦስተኛ ጊዜ ከሰማይ የተናገረበት ዘገባ የሚገኘው በዮሐንስ ወንጌል ላይ ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት የፋሲካ በዓልን ለመጨረሻ ጊዜ ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። በወቅቱ የነበረውን ስሜት ሲገልጽ “ተጨንቄአለሁ” ብሏል። ከዚያም “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” በማለት ጸልዮአል። በምላሹም አባቱ “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” በማለት ከሰማይ ተናገረ።

15 ኢየሱስ እስከ መጨረሻው ለይሖዋ ታማኝ የመሆኑ ጉዳይ በጣም አስጨንቆት ነበር። ኃይለኛ ግርፋት እንደሚጠብቀውና በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚገደል ያውቃል። (ማቴ. 26:38) ከምንም በላይ ኢየሱስ የአባቱን ስም ማስከበር ይፈልግ ነበር። ኢየሱስ ‘አምላክን ሰድቧል’ በሚል ወንጀል ተከስሶ መገደሉ በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ እንዳያመጣ ፈርቶ ነበር። ኢየሱስ ይሖዋ የተናገራቸውን ቃላት ሲሰማ ምንኛ ተበረታቶ ይሆን! ምክንያቱም የይሖዋ ስም መከበሩ እንደማይቀር እርግጠኛ መሆን ይችላል። አባቱ የተናገራቸው ቃላት ኢየሱስን አበረታተውትና ወደፊት የሚጠብቀውን ነገር በድፍረት እንዲጋፈጥ አጠናክረውት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። በወቅቱ ይሖዋ የተናገረውን ነገር የተረዳው ኢየሱስ ብቻ ሊሆን ቢችልም ይሖዋ ሁላችንም ተጠቃሚ እንድንሆን ሲል ይህ ሐሳብ በቃሉ ውስጥ ተመዝግቦ እንዲቆይልን አድርጓል።—ዮሐ. 12:29, 30

ይሖዋ ስሙን ያስከብራል፤ ሕዝቡንም ያድናል (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት) *

16. አንዳንድ ጊዜ፣ በአምላክ ስም ላይ ስለሚደርሰው ነቀፋ እንድንጨነቅ የሚያደርጉን የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው?

16 ልክ እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም በይሖዋ ስም ላይ የሚደርሰው ነቀፋ ሊያሳስበን ይችላል። ምናልባትም እንደ ኢየሱስ ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞብን ይሆናል። አሊያም ተቃዋሚዎች ስለ እኛ በሚያሰራጩት የሐሰት ወሬ ምክንያት ተረብሸን ሊሆን ይችላል። እነዚህ ወሬዎች በይሖዋ ስምና በድርጅቱ ላይ የሚያስከትሉትን ነቀፋ እያሰብን ልንጨነቅ እንችላለን። እንዲህ ባሉ ጊዜያት፣ ይሖዋ የተናገራቸውን ቃላት ማስታወሳችን በእጅጉ ያጽናናናል። ከልክ በላይ መጨነቅ አያስፈልገንም። ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችንንና አእምሯችንን እንደሚጠብቅ’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ፊልጵ. 4:6, 7) ይሖዋ በምንም ዓይነት ስሙን ሳያስከብር አይቀርም። ሰይጣንና ይህ ዓለም በታማኝ አገልጋዮቹ ላይ ያደረሱትን ጉዳት በሙሉ በመንግሥቱ አማካኝነት ይቀለብሰዋል።—መዝ. 94:22, 23፤ ኢሳ. 65:17

የይሖዋን ድምፅ መስማታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

17. ኢሳይያስ 30:21 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ በዛሬው ጊዜ አገልጋዮቹን እያናገረ ያለው እንዴት ነው?

17 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ አገልጋዮቹን እያናገረ ነው። (ኢሳይያስ 30:21ን አንብብ።) እርግጥ ይሖዋ ከሰማይ ሲናገር አንሰማውም። ሆኖም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈልን ሲሆን በቃሉ በኩል መመሪያ ይሰጠናል። በተጨማሪም የይሖዋ መንፈስ ‘ታማኙ መጋቢ’ ለአምላክ አገልጋዮች ምግብ ማቅረቡን እንዲቀጥል ያደርጋል። (ሉቃስ 12:42) በታተሙም ሆነ ኢንተርኔት ላይ በሚገኙ ጽሑፎች፣ ቪዲዮዎችና ኦዲዮዎች አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብልናል!

18. ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት እምነትህን የሚያጠናክሩልህና ደፋር እንድትሆን የሚረዱህ እንዴት ነው?

18 ይሖዋ ልጁ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የተናገራቸውን ቃላት እናስታውስ! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት አምላክ ራሱ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት፣ ይሖዋ ሁሉንም ነገር እንደሚቆጣጠር እንዲሁም ሰይጣንና እሱ የሚገዛው ክፉ ዓለም ያስከተሉትን ማንኛውንም ጉዳት እንደሚቀለብስ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርጉናል። እንግዲያው የይሖዋን ድምፅ በጥሞና ለመስማት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ ካደረግን አሁንም ሆነ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ችግሮች በሙሉ በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክን ፈቃድ ከፈጸማችሁ በኋላ የተስፋው ቃል ሲፈጸም ማየት እንድትችሉ መጽናት ያስፈልጋችኋል” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጠናል።—ዕብ. 10:36

መዝሙር 4 “ይሖዋ እረኛዬ ነው”

^ አን.5 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ በሦስት የተለያዩ አጋጣሚዎች ከሰማይ ተናግሯል። ከእነዚህ አጋጣሚዎች በአንዱ ላይ ልጁን እንዲሰሙት ለክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ነግሯቸዋል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የኢየሱስን ትምህርቶችና ሌሎች ጠቃሚ ሐሳቦች አካቶ በያዘው በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ እንዲሁም በድርጅቱ አማካኝነት ያናግረናል። ይህ ርዕስ ይሖዋንና ኢየሱስን መስማታችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን ያብራራል።

^ አን.52 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ የጉባኤ አገልጋይ የስብሰባ አዳራሹን ሲያጸዳና በጽሑፍ ክፍል ላይ ሲሠራ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ይመለከተዋል። ከዚያም ከልብ ያመሰግነዋል።

^ አን.54 የሥዕሉ መግለጫ፦ በሴራ ሊዮን ያሉ ባልና ሚስት በአካባቢያቸው ላለ ዓሣ አጥማጅ የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት ሲሰጡ።

^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ የስብከቱ ሥራችን በታገደበት አገር ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በመኖሪያ ቤት ውስጥ ስብሰባ እያደረጉ። ትኩረት ላለመሳብ ሲሉ የአዘቦት ልብስ ለብሰዋል።