የጥናት ርዕስ 13
እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ
“እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ።”—1 ጴጥ. 1:22
መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ
ማስተዋወቂያ *
1. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የትኛውን ግልጽ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል? (ሽፋኑን ተመልከት።)
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ግልጽ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል። “እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ብሏቸዋል። አክሎም እንዲህ አለ፦ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐ. 13:34, 35
2. እርስ በርስ መዋደዳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ኢየሱስ ተከታዮቹ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ መሆናቸው የሚታወቀው የእሱን ዓይነት ፍቅር ካሳዩ እንደሆነ ገልጿል። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በዘመናችን ይህ ሐሳብ እውነት መሆኑ ታይቷል። የትኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ ተቋቁመን እርስ በርስ መዋደዳችን በእርግጥም በጣም አስፈላጊ ነው!
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን እርስ በርስ አጥብቀን መዋደድ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ያም ቢሆን ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ማድረግ አለብን። ፍቅር ሰላም ፈጣሪ፣ ከአድልዎ ነፃ እና እንግዳ ተቀባይ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። ይህን ርዕስ ስታጠና ‘ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ፍቅር ማሳየታቸውን ከቀጠሉ ወንድሞችና እህቶች ምን ትምህርት ማግኘት እችላለሁ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።
ሰላም ፈጣሪ ሁኑ
4. በማቴዎስ 5:23, 24 መሠረት ቅር ከተሰኘብን ወንድም ጋር ሰላም መፍጠር ያለብን ለምንድን ነው?
4 ኢየሱስ ቅር ከተሰኘብን ወንድም ጋር ሰላም መፍጠር ምን ያህል አስፈላጊ ማቴዎስ 5:23, 24ን አንብብ።) አምላክን ማስደሰት ከፈለግን ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ከወንድሞቻችን ጋር ሰላም ለመፍጠር የቻልነውን ሁሉ ስናደርግ ይሖዋ ይደሰታል። ቂም የምንይዝ ብሎም ሰላም ፈጣሪ ለመሆን ጥረት ለማድረግ እንኳ ፈቃደኛ የማንሆን ከሆነ ግን አምልኳችንን አይቀበልም።—1 ዮሐ. 4:20
እንደሆነ አስተምሯል። (5. አንድ ወንድም ሰላም መፍጠር ከባድ እንዲሆንበት ያደረገው ምን ነበር?
5 ሰላም መፍጠር አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ለምን? ማርክ * ያጋጠመውን ነገር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንድ ወንድም በእሱ ላይ ትችት በሰነዘረበትና በጉባኤው ውስጥ ላሉ ሰዎች ስለ እሱ መጥፎ ነገር ባወራበት ጊዜ ማርክ ስሜቱ ተጎድቶ ነበር። ታዲያ ማርክ ምን አደረገ? “በጣም ስለተበሳጨሁ በቁጣ ተናገርኩት” ብሏል። በኋላ ግን ማርክ በድርጊቱ ስለተጸጸተ ወንድምን ይቅርታ በመጠየቅ ሰላም ለመፍጠር ሞከረ። ያ ወንድም ግን ፈቃደኛ አልሆነም። መጀመሪያ ላይ ማርክ “እሱ ሰላም መፍጠር ካልፈለገ እኔ ብቻ መጣር ያለብኝ ለምንድን ነው?” በማለት አስቦ ነበር። ይሁንና የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ማርክን ተስፋ እንዳይቆርጥ አበረታታው። ማርክ ምን ያደርግ ይሆን?
6. (ሀ) ማርክ ሰላም ለመፍጠር ጥረት ማድረጉን የቀጠለው እንዴት ነው? (ለ) ማርክ በቆላስይስ 3:13, 14 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተግባራዊ ያደረገው እንዴት ነው?
6 ማርክ አመለካከቱን ሲያጤን ትሕትና እንደሚጎድለውና ራሱን የማመጻደቅ ዝንባሌ እንዳለው አስተዋለ። በመሆኑም አመለካከቱን መቀየር እንዳለበት ተገነዘበ። (ቆላ. 3:8, 9, 12) በትሕትና ወደዚያ ወንድም ሄዶ በድጋሚ ይቅርታ ጠየቀው። በተጨማሪም ማርክ ለወንድም በተደጋጋሚ ደብዳቤ በመጻፍ ባደረገው ነገር በጣም እንደተጸጸተና ወዳጅነታቸውን ማደስ እንደሚፈልግ ገለጸለት። እንዲያውም ወንድም ሊደሰትባቸው ይችላል ብሎ ያሰባቸውን አንዳንድ አነስተኛ ስጦታዎች ይሰጠው ነበር። የሚያሳዝነው ግን ወንድም ቂም እንደያዘ ቀጠለ። ያም ቢሆን ማርክ የኢየሱስን ትእዛዝ በመከተል ወንድሙን መውደዱንና ይቅር ማለቱን ቀጥሏል። (ቆላስይስ 3:13, 14ን አንብብ።) ሌሎች ሰዎች ሰላም ለመፍጠር ለምናደርገው ጥረት ጥሩ ምላሽ ባይሰጡም ክርስቲያናዊ ፍቅር እነሱን ይቅር ማለታችንንና ከእነሱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን መጸለያችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።—ማቴ. 18:21, 22፤ ገላ. 6:9
7. (ሀ) ኢየሱስ ምን እንድናደርግ መክሮናል? (ለ) አንዲት እህት ምን አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሟት ነበር?
7 ኢየሱስ ሌሎች እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ነገር እኛም እንድናደርግላቸው መክሮናል። በተጨማሪም መውደድ ያለብን የሚወዱንን ሰዎች ብቻ እንዳልሆነ ተናግሯል። (ሉቃስ 6:31-33) ብዙ የሚያጋጥም ነገር ባይሆንም፣ በጉባኤህ ውስጥ ያለ አንድ ሰው ከአንተ ጋር ሊቀራረብ ሌላው ቀርቶ ሰላም ሊልህ እንኳ ባይፈልግ ምን ታደርጋለህ? ላራ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “በማላውቀው ምክንያት አንዲት እህት ዘጋችኝ። ጉዳዩ በጣም ስላስጨነቀኝ ስብሰባ የመሄድ ፍላጎቴ እንኳ ጠፋ።” መጀመሪያ ላይ ላራ ‘ምንም ያጠፋሁት ነገር የለም። ደግሞም ይህች እህት ባሕርይዋ አስቸጋሪ እንደሆነ ሌሎች ወንድሞችና እህቶችም ይሰማቸዋል’ በማለት አስባ ነበር።
8. ላራ ሰላም ለመፍጠር ስትል ምን አድርጋለች? ከእሷ ተሞክሮ ምን እንማራለን?
8 ላራ ሰላም ለመፍጠር እርምጃ ወሰደች። ወደ ይሖዋ ከጸለየች በኋላ እህትን አነጋገረቻት። ስለ ጉዳዩ ከተወያዩ በኋላ ተቃቀፉ፤ ከዚያም ሰላም ፈጠሩ። ሁሉም ነገር የተፈታ ይመስል ነበር። ላራ እንዲህ ብላለች፦ “በኋላ ግን ያቺ እህት እንደ በፊቱ መሆኗን ቀጠለች። በጣም አዝኜ ነበር።” መጀመሪያ ላይ ላራ ደስተኛ መሆን የምትችለው ያቺ እህት አመለካከቷን ከቀየረች ብቻ እንደሆነ ተሰምቷት ነበር። ውሎ አድሮ ግን ላራ ከሁሉ የተሻለው እርምጃ እህትን በፍቅር መያዟንና “በነፃ ይቅር” ማለቷን መቀጠል እንደሆነ ተገነዘበች። (ኤፌ. 4:32 እስከ 5:2) ላራ እውነተኛ ፍቅር ‘የበደል መዝገብ እንደሌለው፣ ሁሉን ችሎ እንደሚያልፍ፣ ሁሉን እንደሚያምን፣ ሁሉን ተስፋ እንደሚያደርግና ሁሉን ነገር በጽናት እንደሚቋቋም’ አስታወሰች። (1 ቆሮ. 13:5, 7) ላራ የአእምሮ ሰላሟን መልሳ አገኘች። ከጊዜ በኋላም ከእህት ጋር ያላት ግንኙነት ተሻሻለ። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ሰላም ለመፍጠር የምንሞክር እንዲሁም ምንጊዜም ፍቅር የምናሳያቸው ከሆነ “የፍቅርና የሰላም አምላክ” ከእኛ ጋር እንደሚሆን መተማመን እንችላለን።—2 ቆሮ. 13:11
ከአድልዎ ነፃ ሁኑ
9. በሐዋርያት ሥራ 10:34, 35 መሠረት ከአድልዎ ነፃ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
9 ይሖዋ አያዳላም። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35ን አንብብ።) እኛም ከአድልዎ ነፃ ስንሆን የእሱ ልጆች መሆናችንን እናሳያለን። ከዚህም ሌላ ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንድንወድ የተሰጠንን መመሪያ እንታዘዛለን፤ እንዲሁም በመንፈሳዊ ቤተሰባችን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።—ሮም 12:9, 10፤ ያዕ. 2:8, 9
10-11. አንዲት እህት አሉታዊ አመለካከቷን ያስተካከለችው እንዴት ነው?
10 አንዳንዶች ከአድልዎ ነፃ መሆን ሊከብዳቸው ይችላል። ሩት የተባለች እህት ያጋጠማትን ነገር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለች የሌላ አገር ተወላጅ የሆነች ሴት ከባድ በደል አድርሳባት ነበር። ይህ ሁኔታ በሩት ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? እንዲህ ብላለች፦ “ከዚያ አገር ጋር የተያያዘ ነገር በሙሉ ያስጠላኝ ነበር። ወንድሞችንና እህቶችን ጨምሮ የዚያ አገር ሰዎች ሁሉ አንድ ዓይነት ይመስሉኝ ነበር።” ታዲያ ሩት አሉታዊ አመለካከቷን ማስተካከል የቻለችው እንዴት ነው?
11 ሩት አሉታዊ አመለካከቷን ማስተካከል እንዳለባት ተገንዝባ ነበር። ከዚያ አገር የተገኙ ተሞክሮዎችንና ሪፖርቶችን ከዓመት መጽሐፍ ላይ አነበበች። እንዲህ ብላለች፦ “በዚያ አገር ስለሚኖሩ ሰዎች አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር ጥረት አደረግኩ። ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን በቅንዓት እንደሚያገለግሉ ማስተዋል ጀመርኩ። እነሱም የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን ክፍል እንደሆኑ ግልጽ እየሆነልኝ መጣ።” በጊዜ ሂደት ሩት ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንዳለባት ተረዳች። “ከዚያ አገር የመጡ ወንድሞችንና እህቶችን ሳገኝ ለእነሱ ወዳጃዊ ስሜት ለማሳየት ለየት ያለ ጥረት አደርግ ነበር። በደንብ ሳነጋግራቸው ስለ እነሱ ይበልጥ እያወቅኩ መጣሁ” በማለት ተናግራለች። ውጤቱስ ምን ሆነ? ሩት “ውሎ አድሮ አሉታዊ አመለካከቴ ተወገደ” ብላለች።
12. ሣራ የተባለች እህት ምን ችግር ነበረባት?
12 አንዳንዶች አድልዎ የሚያደርጉት ሳይታወቃቸው ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ሣራ አድልዎ እንደምታደርግ አይሰማትም ነበር፤ ምክንያቱም ለሰዎች በዘራቸው፣ በኑሮ ደረጃቸው ወይም በድርጅቱ ውስጥ ባላቸው ኃላፊነት ላይ ተመሥርታ አታዳላም። ሆኖም “አድልዎ እንደማደርግ ማስተዋል ጀመርኩ” በማለት በሐቀኝነት ተናግራለች። ሣራ ምን ማለቷ ነበር? የሣራና የቤተሰቦቿ የትምህርት ደረጃ ከፍ ያለ ነው፤ ስለዚህ ሣራ ከተማሩ ሰዎች ጋር መሆን ትመርጥ ነበር። እንዲያውም ለአንድ ጓደኛዋ “ከተማሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር መሆን ያስደስተኛል። ካልተማሩ ወንድሞች ጋር ግን አልቀራረብም” በማለት ተናግራ ነበር። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሣራ አመለካከቷን ማስተካከል ነበረባት። ታዲያ አመለካከቷን ያስተካከለችው እንዴት ነው?
13. ሣራ አመለካከቷን ካስተካከለችበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?
13 አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሣራ አመለካከቷን እንድታጤን ረዳት። እንዲህ ብላለች፦ “በታማኝነት ስለማከናውነው አገልግሎት፣ በስብሰባ ላይ ስለምሰጠው ጥሩ ሐሳብ እንዲሁም ስላለኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አድናቆቱን ገለጸልኝ። ከዚያ ግን እውቀታችን እያደገ ሲሄድ እንደ ትሕትና፣ ልክን ማወቅና ምሕረት ያሉ ክርስቲያናዊ ባሕርያትንም ማዳበር እንደሚኖርብን አብራራልኝ።” ሣራ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የሰጣትን ምክር በሥራ ላይ አዋለች። “ዋናው ነገር ደግነትና ፍቅር ማሳየታችን እንደሆነ ተገነዘብኩ” ብላለች። በመሆኑም ለወንድሞችና ለእህቶች ያላትን አመለካከት አስተካከለች። “ወንድሞቻችንን በይሖዋ ዓይን ውድ የሚያደርጓቸውን ባሕርያት ለማስተዋል ጥረት ማድረግ ጀመርኩ” በማለት ተናግራለች። እኛስ በዚህ ረገድ እንዴት ነን? በትምህርት ደረጃችን የተነሳ ከሌሎች እንደምንበልጥ ሊሰማን 1 ጴጥ. 2:17
አይገባም! “ለመላው የወንድማማች ማኅበር” የጠበቀ ፍቅር ካለን ከአድልዎ ነፃ እንሆናለን።—እንግዳ ተቀባይ ሁኑ
14. በዕብራውያን 13:16 መሠረት ይሖዋ እንግዳ ተቀባይ ስንሆን ምን ይሰማዋል?
14 ይሖዋ ለእንግዳ ተቀባይነት ትልቅ ቦታ ይሰጣል። (ዕብራውያን 13:16ን አንብብ።) በተለይ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳትን የአምልኳችን ክፍል አድርጎ ይመለከተዋል። (ያዕ. 1:27፤ 2:14-17) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል አዳብሩ” በማለት ያበረታታናል። (ሮም 12:13) እንግዳ ተቀባይ ስንሆን ለሌሎች ፍቅራችንንና ወዳጅነታችንን እናሳያለን። ይሖዋ ወንድሞቻችንን ቤታችን ስንጋብዝ፣ ሻይ ቡና ስንላቸው ወይም ጊዜና ትኩረት ስንሰጣቸው በጣም ይደሰታል። (1 ጴጥ. 4:8-10) ያም ቢሆን እንግዳ ተቀባይ እንዳንሆን እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ።
15-16. (ሀ) አንዳንዶች እንግዳ ከመቀበል ወደኋላ የሚሉት ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ኤዲት በእንግዳ ተቀባይነት ረገድ አመለካከቷን ማስተካከል የቻለችው እንዴት ነው?
15 ያለንበት ሁኔታ እንግዳ ተቀባይ ከመሆን ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን ይችላል። ኤዲት የተባለችን አንዲት መበለት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የይሖዋ ምሥክር ከመሆኗ በፊት ከሰዎች ጋር መገናኘት ብዙም አያስደስታትም ነበር። ከእሷ ይልቅ ሌሎች ሰዎች እንግዶችን ቢያስተናግዱ የተሻለ እንደሆነ ይሰማት ነበር።
16 የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ ግን ኤዲት አመለካከቷን አስተካከለች። እንግዳ ተቀባይ ለመሆን ጥረት ማድረግ ጀመረች። እንዲህ ብላለች፦ “የስብሰባ አዳራሻችን ሲገነባ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ በፕሮጀክቱ ላይ ለመካፈል የሚመጡ ባልና ሚስት እንዳሉ ነገረኝ፤ ከዚያም ለሁለት ሳምንት ቤቴ እንዳስተናግዳቸው ጠየቀኝ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ የሰራፕታዋን መበለት እንዴት እንደባረካት አስታወስኩ።” (1 ነገ. 17:12-16) ኤዲት እነዚህን ባልና ሚስት ቤቷ ለመቀበል ተስማማች። ታዲያ እንዲህ በማድረጓ ተባርካለች? እንዲህ ብላለች፦ “እኔ ጋር የቆዩት ለሁለት ሳምንት ሳይሆን ለሁለት ወር ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ ጥሩ ወዳጆች ሆንን።” ኤዲት በጉባኤዋ ውስጥም ጥሩ ጓደኞች በማግኘት ተባርካለች። በአሁኑ ወቅት በአቅኚነት እያገለገለች ሲሆን አብረዋት የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች ቤቷ ገብተው አረፍ እንዲሉ የመጋበዝ ልማድ አላት። እንዲህ ብላለች፦ “መስጠት ያስደስተኛል። ደግሞም እውነቱን ለመናገር ከምሰጠው ይልቅ የማገኘው በረከት ይበልጣል።”—ዕብ. 13:1, 2
17. ሉክና ባለቤቱ ምን አስተዋሉ?
17 እርግጥ ነው፣ እንግዶችን የመቀበል ልማድ ይኖረን ይሆናል፤ ይሁንና በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንችል ይሆን? ለምሳሌ ሉክና ባለቤቱ እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። ወላጆቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውን፣ የቅርብ ጓደኞቻቸውን እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቹንና ባለቤቱን ቤታቸው የመጋበዝ ልማድ ነበራቸው። ሆኖም ሉክ “የምንጋብዘው የምንቀርባቸውን ሰዎች ብቻ እንደሆነ አስተዋልን” ብሏል። ታዲያ ሉክና ባለቤቱ እንግዳ ተቀባይ በመሆን ረገድ ማሻሻያ ያደረጉት እንዴት ነው?
18. ሉክና ባለቤቱ እንግዳ ተቀባይ በመሆን ረገድ ማሻሻያ ያደረጉት እንዴት ነው?
18 ሉክና ባለቤቱ “የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን ብድራት ታገኛላችሁ?” በሚለው የኢየሱስ ንግግር ላይ ካሰላሰሉ በኋላ አመለካከታቸውን አስተካከሉ። (ማቴ. 5:45-47) ለሁሉም ሰው ለጋስ የሆነውን የይሖዋን ምሳሌ መከተል እንዳለባቸው ተገነዘቡ። በመሆኑም ከዚህ ቀደም ጋብዘዋቸው የማያውቁ ወንድሞችንና እህቶችን ለመጋበዝ ግብ አወጡ። ሉክ እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ሁላችንም በግብዣው እንደሰታለን። ሁላችንም እንበረታታለን እንዲሁም እንታነጻለን።”
19. የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ቁርጥ ውሳኔህስ ምንድን ነው?
19 እርስ በርሳችን አጥብቀን መዋደዳችን ሰላም ፈጣሪ፣ ከአድልዎ ነፃ እንዲሁም እንግዳ ተቀባይ ለመሆን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ተመልክተናል። ማንኛውንም አሉታዊ ስሜት በማስወገድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን አጥብቀን ከልብ ልንወዳቸው ይገባል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ደስተኞች እንሆናለን፤ እንዲሁም የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እናሳያለን።—ዮሐ. 13:17, 35
መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ