የሕይወት ታሪክ
“እነሆኝ! እኛን ላኩን!”
የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ምናልባትም ወደ ሌላ አገር በመሄድ አገልግሎትህን ማስፋት ትፈልጋለህ? ከሆነ የወንድም ጃክንና የእህት ማሪሊንን ተሞክሮ ማንበብህ ሊረዳህ ይችላል።
ጃክና ማሪሊን ከ1988 አንስቶ አብረው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ነው። ከአዲስ አካባቢ ጋር ቶሎ በመላመድ ችሎታቸው የሚታወቁት እነዚህ ባልና ሚስት በጓዴሎፕ እና በፍሬንች ጊያና ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ተመድበው አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት በሁለቱም አገሮች ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት የሚከታተለው የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ ነው። እስቲ ለጃክና ለማሪሊን አንዳንድ ጥያቄዎችን እናቅርብላቸው።
ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ያነሳሳችሁ ምንድን ነው?
ማሪሊን፦ ያደግኩት በጓዴሎፕ ነው። በልጅነቴ ብዙ ጊዜ ከእናቴ ጋር ቀኑን ሙሉ እናገለግል ነበር፤ እናቴ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር ነበረች። ሰዎችን እወዳለሁ፤ በመሆኑም በ1985 ትምህርት እንደጨረስኩ አቅኚ ሆንኩ።
ጃክ፦ በወጣትነቴ አገልግሎት ከሚወዱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጋር ብዙ ጊዜ አሳልፍ ነበር። ትምህርት ቤት ሲዘጋ ረዳት አቅኚ ሆኜ አገለግላለሁ። አንዳንድ ጊዜ፣ ቅዳሜና እሁድ አቅኚዎቹ ወደሚያገለግሉበት ክልል በአውቶቡስ ሄደን ቀኑን ሙሉ አብረናቸው እናገለግል ነበር፤ ከዚያም ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሄደን ዘና እንላለን። በጣም ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል!
በ1988 ከማሪሊን ጋር ከተጋባን በኋላ ‘ብዙ ኃላፊነት የለብንም፤ ታዲያ ለምን አገልግሎታችንን አናሰፋም?’ ብዬ አሰብኩ። በመሆኑም እኔም እንደ ማሪሊን አቅኚ ሆንኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ በአቅኚዎች ትምህርት ቤት ተካፈልኩ፤ ከዚያም ልዩ አቅኚዎች ሆነን ተመደብን። ጓዴሎፕ ውስጥ በተለያዩ አስደሳች ምድቦች ካገለገልን በኋላ ወደ ፍሬንች ጊያና እንድንሄድ ተጋበዝን።
እስካሁን በተለያዩ የአገልግሎት ምድቦች አገልግላችኋል። አዳዲስ ምድቦችን ለመልመድ የረዳችሁ ምንድን ነው?
ማሪሊን፦ በፍሬንች ጊያና ቤቴል የሚያገለግሉት ወንድሞች በጣም የምንወደው ጥቅስ ኢሳይያስ 6:8 እንደሆነ ያውቁ ነበር። ስለዚህ ስልክ ሲደውሉልን በቀልድ መልክ “የምትወዱት ጥቅስ ትዝ ይላችኋል?” ይሉን ነበር። እንዲህ ሲሉን ምድባችን ሊቀየር እንደሆነ ስለሚገባን “እነሆኝ! እኛን ላኩን!” እንላቸዋለን።
አዲሱን ምድባችንን ከቀድሞዎቹ ምድቦቻችን ጋር ከማወዳደር
እንቆጠባለን፤ ምክንያቱም ማወዳደር እጃችን ላይ ያለውን ነገር እንዳናደንቅ ሊያደርገን ይችላል። በአዲሱ ክልል ካሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ለመተዋወቅም ቅድሚያውን እንወስዳለን።ጃክ፦ ቀደም ሲል አንዳንድ ወዳጆቻችን ከእነሱ እንዳንርቅ ስለሚፈልጉ በቅን ልቦና ተነሳስተው ወደ ሌላ ቦታ እንዳንሄድ ሊያሳምኑን ይሞክሩ ነበር። ሆኖም ከጓዴሎፕ ስንወጣ አንድ ወንድም ኢየሱስ በማቴዎስ 13:38 ላይ የተናገረውን “እርሻው ዓለም ነው” የሚለውን ሐሳብ አስታወሰን። ስለዚህ ምድባችን ሲቀየር፣ የትም ቦታ ብንሆን የምናገለግለው በዚያው እርሻ ወይም መስክ ላይ እንደሆነ ለማስታወስ እንሞክራለን። ደግሞም ዋናው ነገር ክልሉና ሰዎቹ ናቸው።
ወደ አዲሱ ምድባችን ስንደርስ በዚያ ቦታም ሰዎች ደስተኛ ሆነው እንደሚኖሩ እናስተውላለን። ስለዚህ እንደ አገሬው ሰዎች ለመኖር እንሞክራለን። ምግቡ ከለመድነው ሊለይ ቢችልም ለጤናችን እየተጠነቀቅን ሰዎቹ የሚበሉትን እንበላለን፣ የሚጠጡትንም እንጠጣለን። በተጨማሪም ስለ ሁሉም ምድቦቻችን ስንናገር አዎንታዊ ለመሆን ጥረት እናደርጋለን።
ማሪሊን፦ ደግሞም ከአካባቢው ወንድሞች ብዙ ነገር ተምረናል። ለመጀመሪያ ጊዜ ፍሬንች ጊያና ስንሄድ ያጋጠመን ነገር ትዝ ይለኛል። ኃይለኛ ዝናብ እየጣለ ስለነበር ዝናቡ እስኪያባራ ድረስ አገልግሎት መውጣት የማንችል መስሎን ነበር። ከዚያ ግን አንዲት እህት “እንውጣ?” አለችኝ። እኔም በአግራሞት “እንዴት ነው የምንወጣው?” አልኳት። እሷም “ጃንጥላሽን ያዢና በብስክሌት እንሄዳለን” አለችኝ። በዚህ መልኩ፣ ጃንጥላ ይዞ ብስክሌት መንዳት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ተማርኩ። ይህን ባልማር ኖሮ በክረምት ጨርሶ አገልግሎት መውጣት አልችልም ነበር።
ወደ 15 ጊዜ ያህል መኖሪያ ቀያይራችኋል። ቤት ስለመቀየር የምትሰጡት ምክር ይኖራል?
ማሪሊን፦ መኖሪያ መቀየር ቀላል አይደለም። ሆኖም ቤታችሁ ከአገልግሎት ስትመለሱ በደንብ ልታርፉ የምትችሉበት ቦታ ሊሆን ይገባል።
ጃክ፦ ቤት ስንቀይር አብዛኛውን ጊዜ ቤቱን ቀለም እቀባዋለሁ። አንዳንድ ጊዜ፣ በቅርንጫፍ ቢሮው ያሉ ወንድሞች ብዙ ጊዜ ላንቆይ እንደምንችል ከተሰማቸው “ጃክ፣ የአሁኑን ቤት መቀባት አያስፈልግህም” እያሉ ይቀልዱብኛል።
ማሪሊን ዕቃ ስትሸክፍ በጣም ጎበዝ ነች! ሁሉንም ነገር ካርቶን ውስጥ ታስገባና በካርቶኖቹ ላይ “መጸዳጃ ቤት፣”
“መኝታ ቤት፣” “ኩሽና” እያለች ትጽፋለች። ስለዚህ ወደ አዲሱ ቤታችን ስንገባ ካርቶኖቹን በየክፍላቸው ማስቀመጥ እንችላለን። እንዲሁም በካርቶኖቹ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ዝርዝር ስለምታዘጋጅ የምንፈልገውን ነገር በቀላሉ ማግኘት እንችላለን።ማሪሊን፦ በደንብ የተደራጀን ለመሆን ስለምንሞክር ወዲያውኑ አገልግሎታችንን መጀመር እንችላለን።
‘አገልግሎታችሁን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም’ ምን ዓይነት ፕሮግራም አውጥታችኋል?—2 ጢሞ. 4:5
ማሪሊን፦ ሰኞ የእረፍትና የጉባኤ ዝግጅት ቀን ነው። ከማክሰኞ አንስቶ ደግሞ አገልግሎት እንወጣለን።
ጃክ፦ የሰዓት ግብ ቢኖረንም ትኩረት የምናደርገው በእሱ ላይ አይደለም። ሕይወታችን በአገልግሎታችን ዙሪያ ያጠነጠነ ነው። ከቤት ከምንወጣበት ሰዓት አንስቶ እስከምንመለስበት ጊዜ ድረስ የምናገኛቸውን ሰዎች በሙሉ ለማነጋገር ጥረት እናደርጋለን።
ማሪሊን፦ ለምሳሌ ለመዝናናት ወጣ ስንል ትራክቶች እይዛለሁ። አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ባንነግራቸውም እንኳ መጥተው ጽሑፍ ይጠይቁናል። በመሆኑም ለአለባበሳችንና ለምግባራችን ትኩረት እንሰጣለን። ሰዎች እነዚህን ነገሮች ማስተዋላቸው አይቀርም።
ጃክ፦ ለጎረቤቶቻችን መልካም በማድረግም ምሥክርነት ለመስጠት እንሞክራለን። ለምሳሌ ሰፈር ውስጥ የወዳደቁ ወረቀቶችን አነሳለሁ፣ ቆሻሻውን ወስጄ እደፋለሁ እንዲሁም የወዳደቁ ቅጠሎችን እጠርጋለሁ። ጎረቤቶቻችን ይህን ያስተውላሉ፤ በመሆኑም አንዳንዴ “መጽሐፍ ቅዱስ ልትሰጠኝ ትችላለህ?” ብለው ይጠይቁኛል።
ርቀው ወደሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ሄዳችሁ ሰብካችኋል። ካደረጋችኋቸው ጉዞዎች መካከል በጣም የምታስታውሱት የትኛውን ነው?
ጃክ፦ በጊያና ወደ አንዳንድ ክልሎች መሄድ በጣም አስቸጋሪ ነው። በተደጋጋሚ ጊዜያት በአስቸጋሪ መንገድ ላይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደ 600 ኪሎ ሜትር ያህል መጓዝ አስፈልጎናል። በአማዞን ደን ውስጥ ወደሚገኘው ወደ ሴንት ኤሊ ያደረግነውን ጉዞ አንረሳውም። ወደዚያ ለመድረስ በመኪናና በጀልባ ለረጅም ሰዓት ተጉዘናል። በዚያ የሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች የወርቅ ማዕድን አውጪዎች ናቸው። አንዳንዶቹ ጽሑፍ ስንሰጣቸው በጣም ተደስተው ወርቅ የያዙ ትናንሽ ድንጋዮችን በመዋጮነት ሰጥተውናል። ምሽት ላይ ከድርጅቱ ቪዲዮዎች አንዱን አሳየናቸው። ቪዲዮውን ለማየት ብዙ ሰዎች መጥተዋል።
ማሪሊን፦ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ጃክ በካሞፒ የመታሰቢያውን በዓል ንግግር እንዲሰጥ ተጠይቆ ነበር። እዚያ ለመድረስ በኦያፖክ ወንዝ ላይ በሞተር ጀልባ ለአራት ሰዓት ያህል ተጉዘናል። በጣም አስደናቂ ጉዞ ነበር።
ጃክ፦ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ውኃው ከድንጋይ ጋር እየተላተመ በፍጥነት ስለሚወርድ አደገኛ ነበር። እንዲህ ያሉትን ቦታዎች ማየት የሚገርም ስሜት ይፈጥራል። የጀልባው ነጂ ከፍተኛ ችሎታ ሊኖረው ይገባል። ሆኖም ጉዞው አስደሳች ነበር። በአካባቢው የሚኖሩት 6 የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ቢሆኑም አንዳንድ የአሜሪካ ሕንዶችን ጨምሮ 50 የሚያህሉ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተዋል።
ማሪሊን፦ ለይሖዋ ምርጣቸውን መስጠት የሚፈልጉ ወጣቶች እንዲህ ያለውን አስገራሚ ተሞክሮ ማግኘት ይችላሉ። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን በይሖዋ መታመን ይጠበቅብናል፤ በእሱ ላይ ያለን እምነትም ይጠናከራል። የይሖዋን እጅ የምናይበት ብዙ አጋጣሚ እናገኛለን።
ብዙ ቋንቋዎችን ተምራችኋል። የቋንቋ ተሰጥኦ አላችሁ?
ጃክ፦ በፍጹም። እነዚህን ቋንቋዎች የተማርኩት መማር ስለነበረብኝ ነው። በስራናንቶንጎ * ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል እንኳ ከማቅረቤ በፊት የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መምራት ነበረብኝ። አመራሬ እንዴት እንደነበር አንዱን ወንድም ስጠይቀው “አንዳንድ ያልገቡን ነገሮች ነበሩ፤ ግን በጣም ጥሩ ነበር” አለኝ። በተለይ ልጆች በጣም ረድተውኛል። የተሳሳተ ነገር ስናገር አዋቂዎቹ ዝም ቢሉም ልጆቹ ግን ይነግሩኝ ነበር። እነሱ ብዙ ነገር አስተምረውኛል።
ማሪሊን፦ በአንዱ ምድባችን ውስጥ በፈረንሳይኛ፣ በፖርቱጋልኛና በስራናንቶንጎ ጥናቶችን እመራ ነበር። አንዲት እህት በመጀመሪያ በሚከብደኝ ቋንቋ ማለትም በፖርቱጋልኛ እንዳስጠና ከዚያም ወደሚቀሉኝ ቋንቋዎች እንድሄድ መከረችኝ። ብዙም ሳይቆይ ይህ ምክር ጥበብ የሚንጸባረቅበት መሆኑን አስተውያለሁ።
አንድ ቀን፣ መጀመሪያ በስራናንቶንጎ ከዚያም በፖርቱጋልኛ ጥናት ነበረኝ። ሁለተኛውን ጥናት ማስጠናት ስጀምር አብራኝ የነበረችው እህት “ማሪሊን፣ ምን ሆነሻል?” አለችኝ። ብራዚሊያዊቷን ሴት በፖርቱጋልኛ ሳይሆን በስራናንቶንጎ ቋንቋ እያነጋገርኳት እንደነበር ያወቅኩት ያኔ ነው።
ባገለገላችሁባቸው ቦታዎች ያሉ ወንድሞች በጣም ይወዷችኋል። ከወንድሞች ጋር መቀራረብ የቻላችሁት እንዴት ነው?
ጃክ፦ ምሳሌ 11:25 “ለጋስ ሰው ይበለጽጋል” ይላል። ራሳችንን ሳንቆጥብ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን። ከስብሰባ አዳራሽ ጥገና ጋር በተያያዘ አንዳንዶች “እሱን ለምን ለአስፋፊዎቹ አትተወውም?” ይሉኛል። እኔ ግን “እኔም አስፋፊ ነኝ። የሚሠራ ሥራ ካለ እኔም መሳተፍ አለብኝ” እላቸዋለሁ። እርግጥ እንደ ማንኛውም ሰው ብቻችንን መሆን የምንፈልግበት ጊዜ አለ፤ ሆኖም ይህ ፍላጎት ለሌሎች መልካም ከማድረግ እንዲያግደን ላለመፍቀድ እንሞክራለን።
ማሪሊን፦ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ለመስጠት ጥረት እናደርጋለን። ይህም ወንድሞች ልጆቻቸውን የሚይዝላቸው ወይም ከትምህርት ቤት የሚያመጣላቸው ሰው ሲፈልጉ ማወቅ እንድንችል ይረዳናል። ከዚያም ፕሮግራማችንን አስተካክለን ልንረዳቸው እንችላለን። ወንድሞቻችን እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ስንረዳቸው ከእነሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና ይኖረናል።
የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ በማገልገላችሁ ምን በረከት አግኝታችኋል?
ጃክ፦ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለሕይወታችን ጣዕም ጨምሮለታል። የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች የምናደንቅበት ብዙ አጋጣሚ አግኝተናል። እርግጥ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውናል፤ ሆኖም የትም እንሁን የት የይሖዋ ሕዝቦች ድጋፍ እንደማይለየን ስለምናውቅ የአእምሮ ሰላም አለን።
ወጣት ሳለሁ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነቴን በመጠበቄ የተነሳ በፍሬንች ጊያና ታስሬ ነበር። አንድ ቀን ሚስዮናዊ ሆኜ እንደምመለስና በዚያ እስረኞችን መጽሐፍ ቅዱስ የማስተማር መብት እንደማገኝ ጨርሶ አስቤ አላውቅም ነበር። በእርግጥም ይሖዋ አትረፍርፎ ባርኮናል!
ማሪሊን፦ ሌሎችን መርዳት መቻሌ በጣም ያስደስተኛል። በይሖዋ አገልግሎት በመካፈላችን እጅግ ደስተኞች ነን። ይሖዋን ማገልገላችን ትዳራችንንም አጠናክሮልናል። አንዳንድ ጊዜ ጃክ ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን ባልና ሚስት ቤታችን እንድንጋብዝ ይጠይቀኛል። አብዛኛውን ጊዜ “እኔም እሱን ሳስብ ነበር እኮ!” እለዋለሁ። እንዲህ ዓይነት ነገር ብዙ ጊዜ ያጋጥመናል።
ጃክ፦ በቅርቡ ፕሮስቴት ካንሰር እንዳለብኝ ታወቀ። ማሪሊን ይህን መስማት ባያስደስታትም እንዲህ ብያት አውቃለሁ፦ “ውዴ፣ ነገ ብሞት የምሞተው ‘ዕድሜ ጠግቤ’ አይደለም። ያም ቢሆን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ሕይወት ስለመራሁ የምሞተው በሕይወቴ ረክቼ ነው።”—ዘፍ. 25:8
ማሪሊን፦ ይሖዋ ያላሰብናቸውን በሮች በመክፈት ጨርሶ ያልጠበቅናቸውን ነገሮች እንድናደርግ አስችሎናል። በእርግጥም ሕይወታችን በመልካም ነገሮች የተሞላ ነበር። በአምላክ ሙሉ በሙሉ ስለምንታመን ድርጅቱ ወደሚልከን ወደ ማንኛውም ቦታ ለመሄድ ዝግጁ ነን!
^ አን.32 ስራናንቶንጎ የእንግሊዝኛ፣ የደች፣ የፖርቱጋልኛና የአፍሪካ ቋንቋዎች ድብልቅ ሲሆን ቋንቋውን የፈጠሩት ባሪያዎች ናቸው።