በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 11

ለጥምቀት ዝግጁ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

ለጥምቀት ዝግጁ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

“እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?”—ሥራ 8:36

መዝሙር 50 ራሴን ለአምላክ ለመወሰን ያቀረብኩት ጸሎት

ማስተዋወቂያ a

በዓለም ዙሪያ ያሉ ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን እድገት አድርገው እየተጠመቁ ነው (ከአንቀጽ 1-2⁠ን ተመልከት)

1-2. ለመጠመቅ የሚያስፈልገውን ብቃት ካላሟላህ ተስፋ መቁረጥ የሌለብህ ለምንድን ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

 መጠመቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በጣም ጥሩ ግብ አውጥተሃል። አሁን ላይ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነህ? ዝግጁ እንደሆንክ የሚሰማህ ከሆነና ሽማግሌዎችም በዚህ ሐሳብ ከተስማሙ የሚቀጥለው አጋጣሚ አያምልጥህ። ይህን ውሳኔ ካደረግክ በይሖዋ አገልግሎት የሚክስ ሕይወት ይጠብቅሃል።

2 በሌላ በኩል ደግሞ ከመጠመቅህ በፊት ተጨማሪ እድገት ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ተነግሮሃል? አሊያም ስለ ራስህ እንዲህ ይሰማሃል? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ወጣትም ሆንክ አረጋዊ ይህን ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስፈልገውን ብቃት ልታሟላ ትችላለህ።

“የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?”

3. ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ፊልጶስን ምን በማለት ጠይቆታል? ምን ጥያቄስ ይነሳል? (የሐዋርያት ሥራ 8:36, 38)

3 የሐዋርያት ሥራ 8:36, 38ን አንብብ። አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ወንጌላዊውን ፊልጶስን “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” በማለት ጠይቆታል። ይህ ሰው የመጠመቅ ፍላጎት ነበረው፤ ሆኖም ይህን ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ በእርግጥ ዝግጁ ነው?

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ስለ ይሖዋ መማሩን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)

4. ኢትዮጵያዊው ሰው ተጨማሪ እውቀት የማግኘት ፍላጎት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

4 ኢትዮጵያዊው ሰው “ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር።” (ሥራ 8:27) ከዚህ እንደምንረዳው ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠ ሰው መሆን አለበት። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማንበብ ስለ ይሖዋ እንደተማረ ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ይበልጥ የማወቅ ጉጉት አድሮበታል። እንዲያውም ፊልጶስ መንገድ ላይ ሲያገኘው ይህ ሰው ምን እያደረገ ነበር? የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ የያዘ ጥቅልል እያነበበ ነበር። (ሥራ 8:28) ይህ መጽሐፍ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ የያዘ ነው። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የተወሰኑ መሠረታዊ ነገሮችን በማወቁ ብቻ ረክቶ አልተቀመጠም፤ ተጨማሪ እውቀት የማግኘት ፍላጎት ነበረው።

5. ኢትዮጵያዊው ሰው ከተማረ በኋላ ምን እርምጃ ወስዷል?

5 ይህ ሰው የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ከፍተኛ ባለሥልጣን ነው፤ “የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊ” ነበር። (ሥራ 8:27) ስለዚህ ብዙ ኃላፊነቶች ያሉበትና ሥራ የሚበዛበት ሰው መሆን አለበት። ያም ሆኖ ይሖዋን ለማምለክ ጊዜ መድቧል። እውነትን በመማር ብቻ ረክቶ አልተቀመጠም፤ ከዚህ ይልቅ የተማረውን ሥራ ላይ ማዋል ይፈልግ ነበር። በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ለይሖዋ አምልኮ ለማቅረብ ሲል ከኢትዮጵያ ተነስቶ ረጅም ጉዞ ያደረገው ለዚህ ነው። ይህ ጉዞ ሰፊ ጊዜና ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው፤ ሆኖም ኢትዮጵያዊው ሰው ከይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዘ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ነበር።

6-7. ኢትዮጵያዊው ለይሖዋ ያለው ፍቅር እያደገ የሄደው እንዴት ነው?

6 ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የመሲሑን ማንነት ጨምሮ አንዳንድ አስፈላጊ እውነቶችን አስተምሮታል። (ሥራ 8:34, 35) ይህ ባለሥልጣን ኢየሱስ ስላደረገለት ነገር ሲያውቅ ልቡ በጥልቅ ተነክቶ መሆን አለበት። ታዲያ ምን እርምጃ ይወስድ ይሆን? ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠ የተከበረ ሰው ሆኖ መቀጠል ይችል ነበር። እሱ ግን ለይሖዋና ለልጁ ያለው ፍቅር ስለጨመረ ሕይወቱን የሚቀይር ውሳኔ ለማድረግ ተነሳሳ። ተጠምቆ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ የመሆን ፍላጎት አደረበት። ፊልጶስም ሰውየው ዝግጁ እንደሆነ ሲያይ አጠመቀው።

7 አንተም የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ምሳሌ የምትከተል ከሆነ ለመጠመቅ ዝግጁ መሆን ትችላለህ። ልክ እንደ እሱ በልበ ሙሉነት “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” ማለት ትችላለህ። ከዚህ በመቀጠል ኢትዮጵያዊው የወሰዳቸውን የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን፦ ይህ ሰው መማሩን ቀጥሏል፣ የተማረውን ነገር ሥራ ላይ አውሏል እንዲሁም ለአምላክ ያለው ፍቅር እያደገ እንዲሄድ አድርጓል።

መማርህን ቀጥል

8. ዮሐንስ 17:3 ምን እንድታደርግ ያበረታታሃል?

8 ዮሐንስ 17:3ን አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንድትወስን ያደረጉህ ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ናቸው? ብዙዎቻችን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የወሰንነው በዚህ ጥቅስ የተነሳ ነው። ሆኖም ይህ ጥቅስ፣ መማራችንን እንድንቀጥልስ አያበረታታንም? ያበረታታናል። ስለ “እውነተኛው አምላክ” የምንቀስመው ‘እውቀት’ ማቆሚያ የለውም። (መክ. 3:11፤ ዮሐ. 17:3 ግርጌ) ለዘላለም መማራችንን እንቀጥላለን። ይበልጥ በተማርን ቁጥር ወደ ይሖዋ ይበልጥ እየቀረብን እንሄዳለን።—መዝ. 73:28

9. የእውነትን መሠረታዊ እውቀት ካገኘን በኋላ ምን ማድረግ አለብን?

9 ስለ ይሖዋ ስንማር መጀመሪያ ላይ የምንማረው መሠረታዊ እውነቶችን እንደሆነ ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ያለውን እውቀት ‘መሠረታዊ ነገር’ በማለት ጠርቶታል። እንዲህ ሲል ‘መሠረታዊ ትምህርቶችን’ ማቃለሉ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ለልጆች ሰውነት ገንቢ ከሆነ ወተት ጋር ማመሳሰሉ ነው። (ዕብ. 5:12፤ 6:1) ሆኖም ይህ ብቻ በቂ አይደለም፤ ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች መሠረታዊ ከሆኑት ትምህርቶች አልፈው እንዲሄዱና በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን ጥልቀት ያላቸው እውነቶች እንዲማሩም አበረታቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ላሉት ጥልቀት ያላቸው ትምህርቶች ጉጉት አዳብረሃል? እድገት ለማድረግ እንዲሁም ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ መማርህን ለመቀጠል ፈቃደኛ ነህ?

10. አንዳንዶች ማጥናት ፈታኝ የሚሆንባቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

10 ለአብዛኞቻችን ግን ጥናት ቀላል ነገር አይደለም። የአንተስ ሁኔታ እንዴት ነው? ትምህርት ቤት ሳለህ የማንበብና የማጥናት ክህሎትህን በደንብ አዳብረሃል? ማጥናት አስደሳችና ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማሃል? ወይስ ‘መጽሐፍ በማንበብ መማር የምችል ዓይነት ሰው አይደለሁም’ ብለህ ደምድመሃል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ይሖዋ ግን ሊረዳህ ይችላል። እሱ ፍጹምና ከማንም የተሻለ አስተማሪ ነው።

11. ይሖዋ ‘ታላቅ አስተማሪ’ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ ‘ታላቅ አስተማሪ’ እንደሆነ ተናግሯል። (ኢሳ. 30:20, 21) ታጋሽ፣ ደግና የሌሎችን ሁኔታ የሚረዳ አስተማሪ ነው። በተማሪዎቹ ጥሩ ጎን ላይ ትኩረት ያደርጋል። (መዝ. 130:3) ደግሞም ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። ልዩ ስጦታ የሆነውን አንጎላችንን የፈጠረው እሱ እንደሆነ አስታውስ። (መዝ. 139:14) አብሮን የተፈጠረ የመማር ፍላጎት አለን። ፈጣሪያችን ለዘላለም መማራችንን እንድንቀጥልና ከዚህም ደስታ እንድናገኝ ይፈልጋል። ከዚህ አንጻር ከወዲሁ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ‘ጉጉት ማዳበራችን’ ጥበብ ነው። (1 ጴጥ. 2:2) ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦች አውጣ፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት ያወጣኸውን ፕሮግራም በጥብቅ ተከተል። (ኢያሱ 1:8) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ይሖዋ ጥረትህን ስለሚባርክልህ ስለ እሱ ማንበብና መማር ይበልጥ አስደሳች እየሆነልህ ይሄዳል።

12. የግል ጥናት ስናደርግ በኢየሱስ ላይ ማተኮር ያለብን ለምንድን ነው?

12 በኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ላይ አዘውትረህ አሰላስል። በተለይ በእነዚህ ፈታኝ ጊዜያት ይሖዋን ማገልገላችንን ለመቀጠል ቁልፉ የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል ነው። (1 ጴጥ. 2:21) ኢየሱስ ተከታዮቹ ስለሚያጋጥሟቸው ችግሮች በግልጽ ተናግሯል። (ሉቃስ 14:27, 28) ሆኖም እውነተኛ ተከታዮቹ ልክ እንደ እሱ እንደሚሳካላቸው እርግጠኛ ነበር። (ዮሐ. 16:33) ከኢየሱስ ሕይወት ጋር የተያያዙ ዝርዝር ነገሮችን አጥና፤ ደግሞም በዕለት ተዕለት ሕይወትህ የእሱን ምሳሌ ለመከተል ግብ አውጣ።

13. ይሖዋን ስለ ምን ነገር አዘውትረህ ልትጠይቀው ይገባል? ለምንስ?

13 እውቀት ብቻውን በቂ አይደለም። እውቀት መቅሰም የሚያስገኘው ዋነኛ ጥቅም ስለ ይሖዋ ይበልጥ እንድታውቅ እንዲሁም ለእሱ ያለህ ፍቅርና በእሱ ላይ ያለህ እምነት እንዲያድግ ማስቻል ነው። (1 ቆሮ. 8:1-3) መማርህን ስትቀጥል ይሖዋ እምነት እንዲጨምርልህ አዘውትረህ ጠይቀው። (ሉቃስ 17:5) ይሖዋ እንዲህ ላሉ ጸሎቶች መልስ ይሰጣል። ስለ አምላክ በቀሰምከው ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ እውነተኛ እምነት ተጨማሪ እርምጃ እንድትወስድ ያነሳሳሃል።—ያዕ. 2:26

የተማርከውን ሥራ ላይ አውል

ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃው በፊት የተነገራቸውን ነገር በታማኝነት ሥራ ላይ አውለዋል (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. ሐዋርያው ጴጥሮስ የተማርነውን ነገር ሥራ ላይ የማዋልን አስፈላጊነት ያጎላው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 ሐዋርያው ጴጥሮስ የክርስቶስ ተከታዮች የተማሩትን ሥራ ላይ ማዋላቸውን መቀጠላቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተናግሯል። ስለ ኖኅ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጠቅሷል። ይሖዋ የጥፋት ውኃ አምጥቶ በዘመኑ የነበሩትን ክፉ ሰዎች እንደሚያጠፋ ለኖኅ ነግሮት ነበር። የጥፋት ውኃ እንደሚመጣ ማወቅ ብቻ ኖኅንም ሆነ ቤተሰቡን ሊያድናቸው አይችልም። ጴጥሮስ ከጥፋት ውኃው በፊት የነበረውን ወቅት “መርከብ እየተሠራ በነበረበት ጊዜ” በማለት እንደገለጸው ልብ በል። (1 ጴጥ. 3:20) አዎ፣ ኖኅም ሆነ ቤተሰቡ ትልቅ መርከብ በመሥራት ከአምላክ የሰሙትን ነገር ሥራ ላይ አውለዋል። (ዕብ. 11:7) ከዚያም ጴጥሮስ፣ ኖኅ ያደረገውን ነገር ከጥምቀት ጋር በማመሳሰል “ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት እናንተን እያዳናችሁ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥ. 3:21) በሌላ አባባል አሁን ለጥምቀት ዝግጁ ለመሆን እያከናወንክ ያለኸውን ሥራ ኖኅና ቤተሰቡ ለዓመታት መርከቡን ለመገንባት ካከናወኑት ሥራ ጋር ልናመሳስለው እንችላለን ማለት ነው። ለጥምቀት ዝግጁ ለመሆን ምን ነገሮችን ማድረግ ያስፈልግሃል?

15. እውነተኛ ንስሐ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

15 መጀመሪያ ልናደርጋቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል አንዱ ለኃጢአታችን ከልብ ንስሐ መግባት ነው። (ሥራ 2:37, 38) እውነተኛ ንስሐ እውነተኛ ለውጥ ለማድረግ ያስችላል። እንደ ሥነ ምግባር ብልግና፣ ትንባሆ ማጨስ ወይም ጸያፍ ንግግር ያሉ ይሖዋን የሚያሳዝኑ ልማዶችን አስወግደሃል? (1 ቆሮ. 6:9, 10፤ 2 ቆሮ. 7:1፤ ኤፌ. 4:29) አሁንም በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልግህ ከሆነ ለውጥ ለማድረግ መጣጣርህን አታቋርጥ። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠናህን ሰው ስለዚህ ጉዳይ አነጋግረው፤ ወይም የጉባኤህን ሽማግሌዎች እንዲረዱህ አሊያም ምክር እንዲሰጡህ ጠይቃቸው። ከቤተሰቦችህ ጋር የምትኖር ወጣት ከሆንክ እንዳትጠመቅ የሚከለክልህን ማንኛውንም መጥፎ ልማድ ለማስወገድ የወላጆችህን እርዳታ ጠይቅ።

16. ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

16 ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበርህም አስፈላጊ ነው። ይህም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትንና ተሳትፎ ማድረግን ይጨምራል። (ዕብ. 10:24, 25) በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቃቱን ካሟላህ በኋላ ደግሞ አዘውትረህ የምትሰብክበት ፕሮግራም ይኑርህ። በዚህ ሕይወት አድን ሥራ ላይ ይበልጥ በተካፈልክ ቁጥር ሥራው ይበልጥ አስደሳች እየሆነልህ ይሄዳል። (2 ጢሞ. 4:5) ከቤተሰቦችህ ጋር የምትኖር ወጣት ከሆንክ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በስብሰባዎች ላይ ለመካፈል ወይም አገልግሎት ለመውጣት የወላጆቼ አስታዋሽነት ያስፈልገኛል? ወይስ በራሴ ተነሳሽነት በእነዚህ እንቅስቃሴዎች እካፈላለሁ?’ እነዚህን ነገሮች በራስህ ተነሳስተህ ማድረግህ እምነትህን እንዲሁም ለይሖዋ አምላክ ያለህን ፍቅርና አድናቆት ያሳያል። እነዚህ ‘ለአምላክ ያደርክ መሆንህን የሚያሳዩ ተግባሮች’ ማለትም ለይሖዋ የምትሰጣቸው ስጦታዎች ናቸው። (2 ጴጥ. 3:11፤ ዕብ. 13:15) ማንም ጫና ሳያደርግብን በራሳችን ተነሳስተን የምንሰጠው ማንኛውም ዓይነት ስጦታ አምላካችንን ያስደስተዋል። (ከ2 ቆሮንቶስ 9:7 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ያሉ እርምጃዎችን የምንወስደው ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት ስለሚያስደስተን ነው።

ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሂድ

17-18. ለመጠመቅ የሚያስፈልገውን ብቃት እንድታሟላ የሚረዳህ የትኛው ወሳኝ ባሕርይ ነው? ለምንስ? (ምሳሌ 3:3-6)

17 ለጥምቀት የሚያስፈልጉትን ብቃቶች እያሟላህ ስትሄድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙህ የታወቀ ነው። አንዳንዶች በአዲሱ እምነትህ የተነሳ ሊያፌዙብህ፣ አልፎ ተርፎም ሊቃወሙህ ወይም ስደት ሊያደርሱብህ ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:12) አንድን መጥፎ ልማድ ለማስወገድ ጥረት ብታደርግም አልፎ አልፎ ይህ ልማድ ሊያገረሽብህ ይችላል። አሊያም ደግሞ ግብህ ፈጽሞ ሊደረስበት የማይችል እንደሆነ በማሰብ ትዕግሥትህ ሊሟጠጥና ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። ታዲያ ለመጽናት የሚረዳህ ምንድን ነው? በዚህ ረገድ የሚረዳህ ወሳኝ ባሕርይ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ነው።

18 ሊኖሩህ ከሚችሉት ባሕርያት ሁሉ እጅግ የላቀው ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ነው። (ምሳሌ 3:3-6ን አንብብ።) ለአምላክ ያለህ ጥልቅ ፍቅር በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች በተሳካ መንገድ እንድትወጣ ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ስላለው ታማኝ ፍቅር በተደጋጋሚ ይናገራል። ታማኝ ፍቅር ከሚወዱት አካል ጋር እስከ መጨረሻው መጣበቅን የሚጠይቅ ጠንካራ ባሕርይ ነው። (መዝ. 100:5) የተፈጠርከው በአምላክ መልክ ነው። (ዘፍ. 1:26) ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ማንጸባረቅ የምትችለው እንዴት ነው?

በየዕለቱ ለይሖዋ ያለህን አመስጋኝነት መግለጽ ትችላለህ (አንቀጽ 19⁠ን ተመልከት) b

19. ይሖዋ ላደረገልህ ነገሮች ሁሉ ያለህ አመስጋኝነት እንዲጨምር ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? (ገላትያ 2:20)

19 በቅድሚያ አመስጋኝ ልትሆን ይገባል። (1 ተሰ. 5:18) በየዕለቱ ‘ይሖዋ ፍቅር ያሳየኝ እንዴት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ከዚያም ይሖዋ ያደረገልህን ነገር ለይተህ በመጥቀስ በጸሎትህ ላይ እሱን ማመስገንህን አትርሳ። የይሖዋን የፍቅር መግለጫዎች ለአንተ በግለሰብ ደረጃ እንደተደረጉልህ አድርገህ ተመልከታቸው፤ ሐዋርያው ጳውሎስም ይሖዋ እንዲህ እንዳደረገለት ተገንዝቧል። (ገላትያ 2:20ን አንብብ።) ከዚያም ‘እኔስ በምላሹ ለይሖዋ ፍቅሬን ማሳየት እፈልጋለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ፈተናዎችን እንድትቋቋምና ችግሮችን በተሳካ ሁኔታ እንድትወጣ ይረዳሃል። መንፈሳዊ ልማዶችህን ይዘህ በመቀጠል ለአባትህ ያለህን ፍቅር በየዕለቱ እንድታሳይ ይገፋፋሃል።

20. ራስን ለይሖዋ መወሰን ምን ይጨምራል? ይህን ውሳኔ ማድረግህ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

20 በጊዜ ሂደት፣ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር አንድ ልዩ ጸሎት ለማቅረብ ያነሳሳሃል። በዚህ ጸሎት አማካኝነት ራስህን ለአምላክ ትወስናለህ። ራስህን ለይሖዋ ስትወስን ለዘላለም የእሱ ንብረት የመሆን ግሩም ተስፋ እንደሚኖርህ አስታውስ። ለይሖዋ ራስህን ስትወስን በሕይወትህ ውስጥ ምንም ዓይነት ውጣ ውረድ ቢያጋጥምህ እሱን ማገልገልህን ለመቀጠል ቃል ትገባለህ። ይህ ቃል ኪዳን መታደስ አያስፈልገውም። በእርግጥም ራስህን ለይሖዋ መወሰን በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ውሳኔ ነው። ሆኖም ይህን ለማሰብ ሞክር፦ በሕይወትህ ውስጥ ብዙ ውሳኔዎችን ታደርጋለህ፤ አንዳንዶቹ ውሳኔዎች በጣም ጥሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ራስህን ለይሖዋ ከመወሰን የተሻለ ውሳኔ ሊኖር አይችልም። (መዝ. 50:14) ሰይጣን ለአባትህ ለይሖዋ ያለህን ፍቅር በማዳከም ንጹሕ አቋምህን እንድታላላ ለማድረግ ይሞክራል። ይህ እንዲሳካለት ፈጽሞ አትፍቀድ! (ኢዮብ 27:5) ለይሖዋ ያለህ ጥልቅ ፍቅር ራስህን ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ እንድትኖርና ወደ ሰማዩ አባትህ ይበልጥ እንድትቀርብ ይረዳሃል።

21. ጥምቀት የጉዞው መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

21 ራስህን ለይሖዋ ከወሰንክ በኋላ ቀጣዩን ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ የጉባኤህን ሽማግሌዎች አነጋግር። ሆኖም ጥምቀት የጉዞው መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ እንዳልሆነ አትርሳ። ይሖዋን የምታገለግልበት ዘላለማዊ ጉዞ የሚጀምረው በዚህ እርምጃ ነው። እንግዲያው ለአባትህ ያለህን ፍቅር ከወዲሁ አጠናክር። ፍቅርህ ዕለት ዕለት እየጠነከረ እንዲሄድ ለማድረግ የሚረዱህን ግቦች አውጣ። እንዲህ ማድረግህ ለመጠመቅ እንድትነሳሳ ያደርግሃል። የምትጠመቅበት ቀን ምንኛ አስደሳች ይሆናል! ሆኖም ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ነው። ለይሖዋና ለልጁ ያለህ ፍቅር ለዘላለም እያደገ መሄዱን እንዲቀጥል እንመኛለን!

መዝሙር 135 የይሖዋ ፍቅራዊ ግብዣ፦ ‘ልጄ ሆይ፣ ጥበበኛ ሁን’

a አስፈላጊውን እድገት አድርገን ለጥምቀት ብቁ ለመሆን ትክክለኛው ውስጣዊ ግፊት ሊኖረን ይገባል። ተገቢውን እርምጃ መውሰድም ያስፈልገናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ምሳሌ በመጠቀም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለጥምቀት ብቁ ለመሆን ምን እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት እንመለከታለን።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት ወጣት እህት ይሖዋ ላደረጋቸው ነገሮች ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆነች በጸሎት ስትነግረው።