በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 10

መጠመቅ ያለብህ ለምንድን ነው?

መጠመቅ ያለብህ ለምንድን ነው?

“እያንዳንዳችሁ . . . ተጠመቁ።”—ሥራ 2:38

መዝሙር 34 በንጹሕ አቋም መመላለስ

ማስተዋወቂያ a

1-2. ሰዎች በሚጠመቁበት ወቅት በአብዛኛው ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል? የትኞቹን ነገሮች መመርመርህ ተገቢ ነው?

 ሊጠመቁ የተዘጋጁ የጥምቀት ዕጩዎችን አይተህ ታውቃለህ? ከመጠመቃቸው በፊት ለሚቀርቡላቸው ሁለት ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ከድምፃቸው ቁርጠኝነታቸውን መረዳት ትችላለህ። ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ፊታቸው በደስታ ፈክቷል። የጥምቀት ዕጩዎቹ ከውኃው ሲወጡ ተሰብሳቢዎቹ ሞቅ አድርገው ያጨበጭባሉ፤ የተጠማቂዎቹም ደስታ ፊታቸው ላይ ይነበባል። በየሳምንቱ በአማካይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ወስነው ይህን እርምጃ በመውሰድ የተጠመቁ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ይሆናሉ።

2 የአንተስ ሁኔታ እንዴት ነው? ለመጠመቅ እያሰብክ ከሆነ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ለየት ያለ አቋም ያለህ ሰው ነህ ማለት ነው፤ ምክንያቱም ‘ይሖዋን እየፈለግክ’ ነው። (መዝ. 14:1, 2) ወጣትም ሆንክ አረጋዊ ይህ ርዕስ አንተን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው። ሆኖም የተጠመቅን ክርስቲያኖችም ብንሆን ይሖዋን ለዘላለም ለማገልገል ያለንን ቁርጠኝነት ማጠናከር እንፈልጋለን። እንግዲያው ይሖዋን ለማገለገል ከሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች ውስጥ ሦስቱን መመርመራችን ተገቢ ነው።

ለእውነትና ለጽድቅ ያለህ ፍቅር

ሰይጣን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የይሖዋን መልካም ስም ሲያጎድፍ ቆይቷል፤ አሁንም ቢሆን እንዲህ ማድረጉን ቀጥሏል (ከአንቀጽ 3-4⁠ን ተመልከት)

3. የይሖዋ አገልጋዮች እውነትንና ጽድቅን የሚወዱት ለምንድን ነው? (መዝሙር 119:128, 163)

3 ይሖዋ ሕዝቦቹን ‘እውነትን እንዲወዱ’ አዟቸዋል። (ዘካ. 8:19) ኢየሱስ ተከታዮቹን ጽድቅን እንዲከተሉ አበረታቷቸዋል። (ማቴ. 5:6) ይህ ሲባል በአምላክ ዓይን ትክክል፣ መልካምና ንጹሕ የሆነውን ነገር ለማድረግ ጠንካራ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል ማለት ነው። እውነትንና ጽድቅን ትወዳለህ? እንደምትወድ እርግጠኞች ነን። ለውሸት እንዲሁም መጥፎና ክፉ ለሆኑ ነገሮች ጥላቻ አለህ። (መዝሙር 119:128, 163ን አንብብ።) ውሸት የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው የሰይጣን መለያ ነው። (ዮሐ. 8:44፤ 12:31) አንዱ የሰይጣን ዓላማ የይሖዋ አምላክን ቅዱስ ስም ማጉደፍ ነው። ሰይጣን በኤደን ዓመፅ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ስለ አምላካችን ውሸት ሲያናፍስ ቆይቷል። ይሖዋን ከሰው ልጆች መልካም ነገርን የሚነፍግ፣ ራስ ወዳድና ውሸታም ገዢ እንደሆነ አድርጎ ገልጾታል። (ዘፍ. 3:1, 4, 5) ሰይጣን ስለ ይሖዋ የሚያናፍሳቸው ውሸቶች የሰዎችን አእምሮና ልብ መመረዛቸውን ቀጥለዋል። ሰዎች ‘እውነትን ለመውደድ’ የማይመርጡ ከሆነ ሰይጣን ከጽድቅ ወደራቁና በክፋት ወደተሞሉ የተለያዩ ዓይነት ድርጊቶች ሊመራቸው ይችላል።—ሮም 1:25-31

4. ይሖዋ “የእውነት አምላክ” መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው፤ ደግሞም እሱን ለሚወዱት ሰዎች እውነትን በሰፊው ያስተምራቸዋል። (መዝ. 31:5) እንዲህ በማድረግ ከሰይጣን ውሸቶች ነፃ እንዲወጡ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም ይሖዋ አገልጋዮቹን ሐቀኛና ጻድቅ እንዲሆኑ ያስተምራቸዋል። ይህም ለራሳቸው ይበልጥ አክብሮት እንዲኖራቸውና ውስጣዊ ሰላም እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 13:5, 6) አንተ መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና የዚህን እውነተኝነት አልተመለከትክም? የይሖዋ መንገዶች ለሰው ዘር በአጠቃላይም ሆነ ለአንተ በግለሰብ ደረጃ ከሁሉ የተሻሉ እንደሆኑ ተምረሃል። (መዝ. 77:13) ስለዚህ የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች እንደምትደግፍ ማሳየት ትፈልጋለህ። (ማቴ. 6:33) ለእውነት ጥብቅና የመቆምና በአምላካችን በይሖዋ ላይ የተሰነዘረውን ክስ ውድቅ የማድረግ ፍላጎት አለህ። ታዲያ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

5. ለእውነትና ለጽድቅ እንደቆምክ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

5 የምትመርጠው ሕይወት በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲህ እንደምትል የሚያሳይ ሊሆን ይችላል፦ “የሰይጣንን ውሸት እቃወማለሁ፤ ለእውነት ጥብቅና እቆማለሁ። የይሖዋን ሉዓላዊ ገዢነት እቀበላለሁ፤ እንዲሁም እሱ ትክክል ነው የሚለውን ነገር ማድረግ እፈልጋለሁ።” እንዲህ ያለ አቋም እንደያዝክ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ወደ ይሖዋ በመጸለይና ራስህን ለእሱ በመወሰን ከዚያም በጥምቀት አማካኝነት ይህን ውሳኔህን በሕዝብ ፊት ይፋ በማድረግ ነው። ለእውነትና ለጽድቅ ያለህ ፍቅር እንድትጠመቅ የሚያነሳሳህ አንዱ ጠንካራ ምክንያት ነው።

ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለህ ፍቅር

6. በመዝሙር 45:4 መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንወደው የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

6 ኢየሱስ ክርስቶስን የምትወደው ለምንድን ነው? ኢየሱስን እንድንወደው የሚያደርጉን አንዳንድ ምክንያቶች በመዝሙር 45:4 ላይ ተጠቅሰዋል። (ጥቅሱን አንብብ።) ኢየሱስ ለእውነት፣ ለትሕትናና ለጽድቅ ጥብቅና ይቆማል። እውነትንና ጽድቅን የምትወድ ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስንም እንደምትወደው ግልጽ ነው። ኢየሱስ እውነትና ጽድቅ ለሆነው ነገር እንዴት በድፍረት ጥብቅና እንደቆመ ለማሰብ ሞክር። (ዮሐ. 18:37) ሆኖም ኢየሱስ ለትሕትና የሚቆመው እንዴት ነው?

7. ከኢየሱስ ትሕትና ጋር በተያያዘ አንተን ይበልጥ የሚማርክህ ምንድን ነው?

7 ኢየሱስ በሕይወቱ የተወው ምሳሌ ለትሕትና እንደሚቆም ያሳያል። ለምሳሌ ያህል፣ ለራሱ ክብር የሰጠበት አንድም ጊዜ የለም፤ በሁሉም ነገር አባቱ እንዲከበር አድርጓል። (ማር. 10:17, 18፤ ዮሐ. 5:19) የአምላክ ልጅ ስላሳየው ትሕትና ስታስብ ምን ይሰማሃል? እሱን ለመውደድና ምሳሌውን ለመከተል አትነሳሳም? እንደምትነሳሳ ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ትሑት የሆነው ለምንድን ነው? ትሑት የሆነውን አባቱን ስለሚወደውና የእሱን ምሳሌ ስለሚከተል ነው። (መዝ. 18:35፤ ዕብ. 1:3) ኢየሱስ የይሖዋን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ የሚያንጸባርቅ መሆኑ እሱን ይበልጥ እንድትወደው አያደርግህም?

8. ኢየሱስ ንጉሣችን በመሆኑ ደስተኞች የሆንነው ለምንድን ነው?

8 ኢየሱስ ከማንም የተሻለ ገዢ ስለሆነ ንጉሣችን በመሆኑ ደስተኞች ነን። ኢየሱስን ያሠለጠነውና ገዢ እንዲሆን የሾመው ይሖዋ ነው። (ኢሳ. 50:4, 5) ኢየሱስ ስላሳየው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅርም ለማሰብ ሞክር። (ዮሐ. 13:1) በእርግጥም ንጉሣችን ኢየሱስ ሊወደድ ይገባዋል። ወዳጆቼ ብሎ የሚጠራቸው እሱን ከልባቸው የሚወዱ ሰዎች ትእዛዛቱን በመጠበቅ ፍቅራቸውን እንደሚያሳዩ ተናግሯል። (ዮሐ. 14:15፤ 15:14, 15) የይሖዋ ልጅ ወዳጅ መሆን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

9. የክርስቲያኖች ጥምቀት ከክርስቶስ ጥምቀት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸው አንዱ ትእዛዝ እንዲጠመቁ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በዚህ ረገድ ምሳሌ ትቶላቸዋል። እርግጥ የኢየሱስ ጥምቀት ከተከታዮቹ ጥምቀት የሚለይባቸው አንዳንድ መንገዶች አሉ። (“ በኢየሱስ ጥምቀትና በተከታዮቹ ጥምቀት መካከል ምን ልዩነት አለ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ሆኖም የሚመሳሰልባቸው መንገዶችም አሉ። ኢየሱስ ሲጠመቅ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን አቅርቧል። (ዕብ. 10:7) የክርስቶስ ተከታዮች የሚጠመቁት ሕይወታቸውን ለይሖዋ አምላክ መወሰናቸውን ይፋ ለማድረግ ነው። ከተጠመቁ በኋላ ልክ እንደ ኢየሱስ ሕይወታቸው የራሳቸውን ሳይሆን የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ላይ ያተኮረ ይሆናል። በዚህ መንገድ የጌታቸውን አርዓያ ይከተላሉ።

10. ለኢየሱስ ያለህ ፍቅር ለመጠመቅ ሊያነሳሳህ የሚገባው ለምንድን ነው?

10 ኢየሱስ የይሖዋ አንድያ ልጅ እንደሆነና አምላክ እኛን እንዲገዛ የሾመው ንጉሥ እንደሆነ ትቀበላለህ። ኢየሱስ ትሑትና የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ እንደሆነ ታውቃለህ። የተራቡትን እንደመገበ፣ ተስፋ የቆረጡትን እንዳጽናና፣ አልፎ ተርፎም የታመሙትን እንደፈወሰ ተምረሃል። (ማቴ. 14:14-21) በዛሬው ጊዜ ጉባኤውን እንዴት እየመራ እንዳለ ተመልክተሃል። (ማቴ. 23:10) ደግሞም የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ወደፊት ከአሁኑ እጅግ የላቁ ነገሮችን እንደሚያከናውን ታምናለህ። ታዲያ ኢየሱስን እንደምትወደው ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ምሳሌውን በመከተል ነው። (ዮሐ. 14:21) ራስህን መወሰንህና መጠመቅህ ይህን ማድረግ ከምትችልባቸው የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች መካከል አንዱ ነው ሊባል ይችላል።

ለይሖዋ አምላክ ያለህ ፍቅር

11. ለመጠመቅ ሊያነሳሳህ የሚገባው ከሁሉ የላቀው ምክንያት ምንድን ነው? ለምንስ?

11 ለመጠመቅ ሊያነሳሳህ የሚገባው ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? ኢየሱስ ከአምላክ ትእዛዛት መካከል ከሁሉ የላቀው የቱ እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።” (ማር. 12:30) እነዚህ ቃላት ለአምላክ ያለህን ፍቅር ጥሩ አድርገው እንደሚገልጹት ይሰማሃል?

እስካሁን ያገኘሃቸውም ሆነ ወደፊት የምታገኛቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ምንጭ ይሖዋ ነው (ከአንቀጽ 12-13⁠ን ተመልከት)

12. ይሖዋን የምትወደው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 ይሖዋን እንድትወደው የሚያደርጉህ በጣም ብዙ ምክንያቶች አሉህ። ለምሳሌ እሱ “የሕይወት ምንጭ” እንደሆነ እንዲሁም “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” የሚገኘው ከእሱ እንደሆነ ተምረሃል። (መዝ. 36:9፤ ያዕ. 1:17) በሕይወትህ ደስተኛ እንድትሆን የሚያደርጉህ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ለጋስና አፍቃሪ የሆነው አምላክ ነው።

13. ቤዛው በጣም አስደናቂ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

13 ቤዛው ይሖዋ የሰጠን እጅግ አስደናቂ ስጦታ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በይሖዋና በልጁ መካከል ያለውን የጠበቀ ዝምድና ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ “አብ ይወደኛል” እንዲሁም ‘እኔ አብን እወደዋለሁ’ በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 10:17፤ 14:31) በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓመታት አብረው ስለኖሩ በመካከላቸው ያለው ዝምድና በጣም ጠንካራ ነው። (ምሳሌ 8:22, 23, 30) ከዚህ አንጻር አምላክ ልጁ ተሠቃይቶ እንዲሞት ሲፈቅድ ምን ያህል አዝኖ ሊሆን እንደሚችል አስበው። ይሖዋ አንተን ጨምሮ ለመላው የሰው ዘር ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ አንተም ሆንክ ሌሎች ሰዎች ለዘላለም መኖር እንድትችሉ ሲል የሚወደው ልጁ መሥዋዕት እንዲሆን ፈቅዷል። (ዮሐ. 3:16፤ ገላ. 2:20) አምላክን ለመውደድ የሚያነሳሳ ከዚህ የበለጠ ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል?

14. በሕይወትህ ውስጥ ልታወጣ የምትችለው ከሁሉ የተሻለ ግብ ምንድን ነው?

14 ስለ ይሖዋ ይበልጥ እያወቅክ ስትሄድ ለእሱ ያለህ ፍቅርም ይበልጥ እየጨመረ እንደሄደ ግልጽ ነው። አሁንም ሆነ ለዘላለም ወደ እሱ ይበልጥ መቅረብ እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። ደግሞም ትችላለህ። ይሖዋ ልቡን ደስ እንድታሰኘው በደግነት ግብዣ አቅርቦልሃል። (ምሳሌ 23:15, 16) ይህን ማድረግ የምትችለው በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊት ጭምር ነው። ይሖዋን ከልብህ እንደምትወደው በሚያሳይ መንገድ ሕይወትህን መምራት ትችላለህ። (1 ዮሐ. 5:3) በሕይወትህ ውስጥ ልታወጣ የምትችለው ከሁሉ የተሻለ ግብ ይህ ነው።

15. ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

15 ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? በቅድሚያ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ራስህን ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ ትወስናለህ። (መዝ. 40:8) ከዚያም በሰዎች ፊት በመጠመቅ በግልህ ያደረግከውን ውሳኔ ይፋ ታደርጋለህ። በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሰው ይህ በሕይወትህ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት አስደሳች እርምጃ ይሆናል። ለራስህ ሳይሆን ለይሖዋ የምትኖረውን አዲስ ሕይወት ትጀምራለህ። (ሮም 14:8፤ 1 ጴጥ. 4:1, 2) ይህ በጣም ከባድ እርምጃ ሊመስል ይችላል፤ ደግሞም ነው። ሆኖም ከሁሉ የተሻለ ሕይወት መምራት የምትችልበትን አጋጣሚ ይከፍትልሃል። እንዴት?

16. መዝሙር 41:12 እንደሚጠቁመው ይሖዋ ሕይወታቸውን ለእሱ አገልግሎት ለሚወስኑ ሰዎች ወሮታቸውን የሚከፍላቸው እንዴት ነው?

16 በጽንፈ ዓለም ውስጥ የይሖዋን ያህል ለጋስ የሆነ አካል የለም። ምንም ያህል ብትሰጠው ብዙ እጥፍ አድርጎ ይመልስልሃል። (ማር. 10:29, 30) ጥቂት ጊዜ በቀረው በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥም እንኳ እጅግ አስደሳች፣ የሚክስና አርኪ የሆነ ሕይወት ይሰጥሃል። በዚህ ብቻ አያበቃም። ስትጠመቅ የጀመርከው ጉዞ ለዘላለም ሊቀጥል ይችላል። አፍቃሪ የሆነውን አባትህን ለዘላለም ማገልገል የምትችልበት አጋጣሚ ተከፍቶልሃል። በአንተና በአባትህ መካከል ያለው ፍቅር ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል፤ ደግሞም ልክ እንደ እሱ መጨረሻ ለሌለው ጊዜ ትኖራለህ።—መዝሙር 41:12ን አንብብ።

17. ለይሖዋ ልትሰጠው የምትችለው እሱ የሌለው ነገር ምንድን ነው?

17 ራስህን ወስነህ ስትጠመቅ ለአባትህ እጅግ ውድ የሆነ ነገር የመስጠት መብት ታገኛለህ። እስከዛሬ ያገኘሃቸው መልካምና አስደሳች ነገሮች ሁሉ ምንጭ እሱ ነው። አንተም በምላሹ የሰማይና የምድር ባለቤት ለሆነው አምላክ፣ የሌለውን ነገር ልትሰጠው ትችላለህ፤ ይህም በፈቃደኝነት ተነሳስተህ የምታቀርበው የታማኝነት አገልግሎት ነው። (ኢዮብ 1:8፤ 41:11፤ ምሳሌ 27:11) ሕይወትህን ልትጠቀም የምትችልበት ከዚህ የተሻለ መንገድ ይኖራል? በእርግጥም ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ለመጠመቅ ሊያነሳሳህ የሚገባ ዋነኛ ምክንያት ነው።

ምን ትጠብቃለህ?

18. የትኞቹን ጥያቄዎች ልትጠይቅ ትችላለህ?

18 ታዲያ ለመጠመቅ ዝግጁ ነህ? ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት የምትችለው አንተ ብቻ ነህ። ሆኖም ‘ምን እየጠበቅኩ ነው?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 8:36) በዚህ ርዕስ ውስጥ የተመለከትናቸውን ሦስት ምክንያቶች አስታውስ። አንደኛ፣ እውነትንና ጽድቅን ትወዳለህ። ‘ሁሉም ሰዎች እውነት የሚናገሩበትንና ጽድቅን የሚያደርጉበትን ጊዜ ለማየት እናፍቃለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ትወደዋለህ። ‘የአምላክን ልጅ ንግሥና እቀበላለሁ? ምሳሌውን መከተልስ እፈልጋለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ሦስተኛውና ዋነኛው ደግሞ ይሖዋን ትወደዋለህ። ‘ይሖዋን እንደ አምላኬ በማገልገል ልቡን ደስ ማሰኘት እፈልጋለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ለእነዚህ ጥያቄዎች ‘አዎ’ የሚል መልስ ከሰጠህ የማትጠመቅበት ምን ምክንያት አለ? ምን እየጠበቅክ ነው?—ሥራ 16:33

19. ለመጠመቅ ልታመነታ የማይገባው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ዮሐንስ 4:34)

19 ለመጠመቅ እያመነታህ ከሆነ ኢየሱስ የተጠቀመበትን ምሳሌ ልብ በል። (ዮሐንስ 4:34ን አንብብ።) ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ ማድረግን ከምግብ ጋር አመሳስሎታል። ለምን? ምግብ መብላታችን ይጠቅመናል። ኢየሱስ፣ ይሖዋ እንድናደርግ የሚያዘን ማንኛውም ነገር ለእኛ ጥቅም እንደሆነ ያውቃል። ይሖዋ ጉዳት ሊያስከትልብን የሚችል ምንም ነገር እንድናደርግ አይፈልግም። ይሖዋ ለአንተ ያለው ፈቃድ መጠመቅን ይጨምራል? አዎ። (ሥራ 2:38) እንግዲያው ይሖዋ እንድትጠመቅ የሰጠህን ትእዛዝ መጠበቅህ አንተኑ እንደሚጠቅምህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። አንድን ምርጥ የሆነ ምግብ ለመብላት የማታመነታ ከሆነ ለመጠመቅ የምታመነታበት ምን ምክንያት ይኖራል?

20. በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

20 ምን እየጠበቅክ ነው? ብዙዎች “ገና ዝግጁ አይደለሁም” ብለው ይመልሱ ይሆናል። እርግጥ ራስህን ለይሖዋ ለመወሰንና ለመጠመቅ የምታደርገው ውሳኔ በሕይወትህ ውስጥ ከምታደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ስለዚህ ዝግጁ ለመሆን ጊዜ ወስዶ በጥንቃቄ ማሰብና ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ሆኖም ይህን እርምጃ ለመውሰድ ልባዊ ፍላጎት ካለህ ራስህን ለማዘጋጀት ምን ማድረግ ትችላለህ? በቀጣዩ ርዕስ ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ እንመለከታለን።

መዝሙር 28 የይሖዋ ወዳጅ መሆን

a ጥምቀት ከእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሚጠበቅ ወሳኝ እርምጃ ነው። አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ይህን እርምጃ እንዲወስድ የሚያነሳሳው ምንድን ነው? በአጭር አነጋገር ፍቅር ነው። ሆኖም ለምን እና ለማን ያለው ፍቅር? በዚህ ርዕስ ውስጥ የዚህን ጥያቄ መልስ እንዲሁም ከተጠመቅን በኋላ ምን ዓይነት ሕይወት ሊኖረን እንደሚችል እንመለከታለን።