የጥናት ርዕስ 14
“ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ”
“እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐ. 13:35
መዝሙር 106 ፍቅርን ማዳበር
ማስተዋወቂያ a
1. በስብሰባችን ላይ የሚገኙ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በአብዛኛው የሚያስደንቃቸው ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለተገኙ አንድ ባልና ሚስት ለማሰብ ሞክሩ። የተደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበልና በስብሰባው ላይ በተገኙት ሰዎች መካከል ያለው ፍቅር በጣም አስደንቋቸዋል። ከስብሰባው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ሚስትየው ለባሏ “የይሖዋ ምሥክሮች ለየት ያሉ ሰዎች ናቸው፤ በጣም ደስ ይላሉ” አለችው።
2. አንዳንዶች የተሰናከሉት ለምንድን ነው?
2 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ባሉት ሰዎች መካከል ያለው ፍቅር በእርግጥም አስደናቂ ነው። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች ፍጹማን አይደሉም። (1 ዮሐ. 1:8) በመሆኑም በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች ይበልጥ ባወቅናቸው ቁጥር አንዳንድ ድክመቶቻቸውን የምናይበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። (ሮም 3:23) የሚያሳዝነው አንዳንዶች የሌሎች አለፍጽምና እንዲያሰናክላቸው ፈቅደዋል።
3. የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ተለይተው የሚታወቁት በምንድን ነው? (ዮሐንስ 13:34, 35)
3 ይህ ርዕስ የተመሠረተበትን የጭብጥ ጥቅስ በድጋሚ ተመልከቱ። (ዮሐንስ 13:34, 35ን አንብብ።) የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች መለያ ምልክት ምንድን ነው? ፍቅር እንጂ ፍጽምና አይደለም። በተጨማሪም ኢየሱስ ‘ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ታውቃላችሁ’ እንዳላለ ልብ በሉ። ከዚህ ይልቅ “ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ነው ያለው። ኢየሱስ ተከታዮቹ ብቻ ሳይሆኑ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያሉ ሰዎችም እውነተኛ ተከታዮቹን እርስ በርሳቸው ባላቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ለይተው እንደሚያውቋቸው መናገሩ ነበር።
4. አንዳንዶች ስለ እውነተኛዎቹ ክርስቲያኖች ምን ማወቅ ሊፈልጉ ይችላሉ?
4 የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ የሚል ጥያቄ ሊፈጠርባቸው ይችላል፦ ‘ፍቅር የኢየሱስን እውነተኛ ተከታዮች ለይቶ የሚያሳውቃቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ ሐዋርያቱን እንደሚወዳቸው ያሳየው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚቻለውስ እንዴት ነው?’ የይሖዋ ምሥክሮች የሆንንም በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላችን ተገቢ ነው። እንዲህ ማድረጋችን በተለይ ሌሎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ በተሟላ መንገድ ፍቅር ማሳየት እንድንችል ይረዳናል።—ኤፌ. 5:2
ፍቅር የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች መለያ የሆነው ለምንድን ነው?
5. በዮሐንስ 15:12, 13 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ አብራራ።
5 ኢየሱስ ተከታዮቹ እርስ በርስ ባላቸው ለየት ያለ ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:12, 13ን አንብብ።) ኢየሱስ “እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ብሎ እንዳዘዛቸው ልብ በሉ። ይህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ቀጥሎ እንዳብራራው ይህ ዓይነቱ ፍቅር ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ነው፤ አንድ ክርስቲያን አስፈላጊ ከሆነ ለእምነት ባልንጀራው ሲል ሕይወቱን አሳልፎ እንዲሰጥ ጭምር ሊገፋፋው የሚችል የፍቅር ዓይነት ነው። b
6. የአምላክ ቃል ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚጠቁመው እንዴት ነው?
6 የአምላክ ቃል ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ ባሕርይ እንደሆነ ይጠቁማል። ብዙ ሰዎች በጣም ከሚወዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ “አምላክ ፍቅር ነው።” (1 ዮሐ. 4:8) “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” (ማቴ. 22:39) “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።” (1 ጴጥ. 4:8) “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።” (1 ቆሮ. 13:8) እነዚህን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ጥቅሶች ይህን ግሩም ባሕርይ ማዳበርና ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ።
7. ሰይጣን ሰዎችን በእውነተኛ ፍቅር አንድ ማድረግ የማይችለው ለምንድን ነው?
7 ብዙዎች እንዲህ ብለው ይጠይቃሉ፦ ‘እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው? ሁሉም ሃይማኖቶች እውነትን እንደያዙ ይናገራሉ፤ ግን ስለ አምላክ የሚያስተምሩት ትምህርት የተለያየ ነው።’ ሰይጣን ብዙ የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶችን በማቋቋም ሰዎችን ግራ ማጋባት ችሏል። ሆኖም እርስ በርሱ የሚዋደድ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ሊያቋቁም አይችልም። ይህን ማድረግ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። ይህ መሆኑ አያስገርምም፤ ምክንያቱም እውነተኛ ፍቅር የሚመነጨው ከይሖዋ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ማሳየት የሚችሉት የይሖዋን መንፈስና በረከት ያገኙ ሰዎች ብቻ ናቸው። (1 ዮሐ. 4:7) ታዲያ ኢየሱስ የእሱ እውነተኛ ተከታዮች እርስ በርሳቸው በሚያሳዩት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ መናገሩ ተገቢ አይደለም?
8-9. ብዙ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን ፍቅር ሲያዩ ምን ተሰምቷቸዋል?
8 ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ብዙዎች የእሱን እውነተኛ ተከታዮች በመካከላቸው ባለው እውነተኛ ፍቅር ለይተው ማወቅ ችለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየን የተባለ ወንድም በትልቅ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘበትን ወቅት በደንብ ያስታውሳል። ስብሰባው የተደረገው ቤቱ አቅራቢያ በሚገኝ ስፖርታዊ ውድድር የሚካሄድበት ስታዲየም ውስጥ ነበር። ከተወሰኑ ወራት በፊት ኢየን አንድ ውድድር ለመመልከት ወደዚያ ስታዲየም ሄዶ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በወቅቱ የነበረው ሁኔታ አሁን ካየሁት ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ በጣም ሰፊ ነው። በቦታው የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ትሑቶችና ሥርዓታማ አለባበስ ያላቸው ሲሆኑ ልጆቻቸውም መልካም ምግባር ነበራቸው።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ከሁሉ በላይ ደግሞ እነዚህ ሰዎች አጥብቄ የምፈልገው ነገር ይኸውም ውስጣዊ ሰላምና እርካታ እንዳላቸው በግልጽ ይታይ ነበር። በዚያን ዕለት ከቀረቡት ንግግሮች አንዱም ትዝ አይለኝም፤ ሆኖም ምግባራቸው በጥልቅ ነክቶኛል።” c እንዲህ ያለ ምግባር ልናሳይ የቻልነው አንዳችን ለሌላው እውነተኛ ፍቅር ስላለን እንደሆነ ግልጽ ነው። ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ስለምንወዳቸው ደግነትና አክብሮት እናሳያቸዋለን።
9 ጆን የተባለ ወንድምም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲጀምር ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶታል፤ እንዲህ ብሏል፦ “በመካከላቸው የሚታየው ወዳጃዊ ስሜት . . . በጣም አስገረመኝ፤ በቅዱሳን መካከል የተገኘሁ ያህል ተሰማኝ። የሚያሳዩትን ልባዊ ፍቅር ስመለከት እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ።” d በተደጋጋሚ የምንሰማቸው እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎች የይሖዋ ሕዝቦች እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ያረጋግጣሉ።
10. ክርስቲያናዊ ፍቅር እንዳለን የምናሳየው በተለይ በየትኛው አጋጣሚ ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
10 መግቢያው ላይ እንደተገለጸው የእምነት ባልንጀሮቻችን ፍጹማን አይደሉም። የሚያበሳጨንን ነገር የሚናገሩበት ወይም የሚያደርጉበት ጊዜ ይኖራል። e (ያዕ. 3:2) ክርስቲያናዊ ፍቅር እንዳለን የሚያሳየው በተለይ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች የምንሰጠው ምላሽ ነው። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ከተወልን ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?—ዮሐ. 13:15
ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?
11. ያዕቆብና ዮሐንስ የትኞቹን መጥፎ ባሕርያት አሳይተዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 ኢየሱስ ሐዋርያቱን ፍጹም እንዲሆኑ አልጠበቀባቸውም። ከዚህ ይልቅ መጥፎ ጎናቸውን አስተካክለው የይሖዋን ሞገስ እንዲያገኙ በፍቅር ረድቷቸዋል። በአንድ ወቅት ከሐዋርያቱ መካከል ሁለቱ ማለትም ያዕቆብና ዮሐንስ ኢየሱስ በመንግሥቱ ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው በእናታቸው በኩል አስጠይቀውት ነበር። (ማቴ. 20:20, 21) ይህም ያዕቆብና ዮሐንስ ኩራትና የሥልጣን ጥም እንደነበራቸው የሚያሳይ ነው።—ምሳሌ 16:18
12. መጥፎ ባሕርይ ያሳዩት ያዕቆብና ዮሐንስ ብቻ ነበሩ? አብራራ።
12 በዚያ ወቅት መጥፎ ባሕርይ ያሳዩት ያዕቆብና ዮሐንስ ብቻ አልነበሩም። ሌሎቹ ሐዋርያት ምላሽ የሰጡበትን መንገድ ልብ በሉ፦ “የቀሩት አሥሩ ይህን ሲሰሙ በሁለቱ ወንድማማቾች ላይ ተቆጡ።” (ማቴ. 20:24) በያዕቆብ፣ በዮሐንስና በሌሎቹ ሐዋርያት መካከል የከረረ ጠብ ተነስቶ ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን። ሌሎቹ ሐዋርያት እንዲህ ብለው ሊሆን ይችላል፦ ‘እናንተ በመንግሥቱ ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣችሁ የምትጠይቁት ማን ስለሆናችሁ ነው? ከኢየሱስ ጋር በትጋት የሠራችሁት እናንተ ብቻ አይደላችሁም። እኛም ልክ እንደ እናንተ ልዩ ቦታ የማግኘት መብት አለን!’ የተፈጠረው ነገር ምንም ይሁን ምን ሐዋርያቱ ይህ ጉዳይ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በመካከላቸው ያለውን የወንድማማች ፍቅር እንዲያደፈርስ ፈቅደዋል።
13. ኢየሱስ ሐዋርያቱ ስህተት በሠሩበት ጊዜ ጉዳዩን የያዘው እንዴት ነው? (ማቴዎስ 20:25-28)
13 ኢየሱስ ሁኔታውን የያዘው እንዴት ነው? በሐዋርያቱ ላይ አልተበሳጨባቸውም። እነሱን ትቶ ይበልጥ ትሑት የሆኑና አንዳቸው ለሌላው ሁሌም ፍቅር የሚያሳዩ የተሻሉ ሐዋርያትን እንደሚፈልግ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ሐዋርያቱ ልባቸው ቅን እንደሆነ ስለሚያውቅ በትዕግሥት እርማት ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 20:25-28ን አንብብ።) ሐዋርያቱ “ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?” በሚል ሲከራከሩ ይህ መጀመሪያቸውም ሆነ መጨረሻቸው አልነበረም፤ ኢየሱስ ግን እነሱን በፍቅር መያዙን ቀጥሏል።—ማር. 9:34፤ ሉቃስ 22:24
14. የኢየሱስ ሐዋርያት ያደጉት በምን ዓይነት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው?
14 ኢየሱስ ሐዋርያቱ ያደጉበትን ማኅበረሰብ ግምት ውስጥ እንዳስገባ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዮሐ. 2:24, 25) ሐዋርያቱ ያደጉት ለክብርና ለሥልጣን ትልቅ ቦታ የሚሰጡ የሃይማኖት መሪዎች ባሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። (ማቴ. 23:6፤ በሚያዝያ 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 16-18 ላይ ከሚገኘው “ምኩራቦች—ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የሰበኩባቸው ቦታዎች” ከሚለው ርዕስ ጋር አወዳድር።) የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ራሳቸውን የሚያመጻድቁም ነበሩ። f (ሉቃስ 18:9-12) ኢየሱስ ሐዋርያቱ እንዲህ ባለ ባሕል ውስጥ ማደጋቸው ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ያላቸውን አመለካከት እንደሚቀርጸው ተገንዝቧል። (ምሳሌ 19:11) ከደቀ መዛሙርቱ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነበር፤ ደግሞም ስህተት ሲሠሩ ጉዳዩን አጋኖ አልተመለከተውም። ልባቸው ቅን እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ ኩራትንና የሥልጣን ጥመኝነትን አስወግደው በምትኩ ፍቅርን እንዲያዳብሩ በትዕግሥት ረድቷቸዋል።
የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
15. ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር በተያያዘ ከተፈጠረው ነገር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
15 ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር በተያያዘ ከተፈጠረው ነገር ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ያዕቆብና ዮሐንስ በመንግሥቱ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው ስህተት ነበር። ሆኖም ሌሎቹ ሐዋርያትም ቢሆኑ ይህ ሁኔታ አንድነታቸውን እንዲያናጋው በመፍቀድ ስህተት ሠርተዋል። ኢየሱስ ግን ለ12ቱም ሐዋርያት ደግነትና ፍቅር አሳይቷቸዋል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ዋናው ነገር ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ብቻ ሳይሆን እኛ ለስህተታቸው ወይም ለድክመታቸው ምላሽ የምንሰጥበት መንገድ ነው። ታዲያ ምን ሊረዳን ይችላል? አንድ የእምነት ባልንጀራችን ሲያበሳጨን ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ያደረገው ነገር ይህን ያህል ቅር ያሰኘኝ ለምንድን ነው? እንዲህ የተሰማኝ መሆኑ ማስተካከል ያለብኝ መጥፎ ባሕርይ እንዳለ የሚጠቁም ይሆን? ያበሳጨኝ ሰው እንደዚያ ያደረገው ከባድ ሁኔታ ውስጥ ስለነበረ ነው? መበሳጨቴ ተገቢ እንደሆነ ቢሰማኝ እንኳ ጉዳዩን ችላ ብዬ በማለፍ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት እችላለሁ?’ ሌሎችን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመያዝ ይበልጥ ጥረት ባደረግን ቁጥር የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች መሆናችንን እናረጋግጣለን።
16. ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ሌላ ምን ትምህርት እናገኛለን?
16 ኢየሱስ የተወልን ምሳሌ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመረዳት ጥረት ማድረግ እንዳለብንም ያስተምረናል። (ምሳሌ 20:5) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ የሰዎችን ልብ ማንበብ ይችላል። እኛ ግን አንችልም። ሆኖም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስህተት ሊሠሩ እንደሚችሉ በመጠበቅ እነሱን በትዕግሥት ለመያዝ ጥረት ማድረግ እንችላለን። (ኤፌ. 4:1, 2፤ 1 ጴጥ. 3:8) እነሱን በደንብ ለማወቅ መሞከራችን እንዲህ ማድረግ ይበልጥ ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
17. አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች የእምነት ባልንጀራውን ይበልጥ ለማወቅ ጥረት ማድረጉ ምን ጥቅም አስገኝቶለታል?
17 በምሥራቅ አፍሪካ የሚያገለግል አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች አንድ ወንድም ደግነት የጎደለው እንደሆነ ተሰምቶት እንደነበር ያስታውሳል። ታዲያ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ምን አደረገ? “ወንድምን ከመራቅ ይልቅ እሱን ይበልጥ ለማወቅ ወሰንኩ” በማለት ተናግሯል። እንዲህ ማድረጉ ወንድም ያደገበት መንገድ በባሕርይው ላይ ተጽዕኖ እንዳደረገበት እንዲያስተውል ረዳው። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል፦ “ወንድም አስተዳደጉ ያሳደረበትን ተጽዕኖ ለማስተካከል ያደረገውን ትግልና ምን ያህል እንደተለወጠ ሳውቅ በጣም አደነቅኩት። በኋላም ጥሩ ወዳጆች ሆንን።” በእርግጥም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመረዳት ጥረት ስናደርግ በአብዛኛው ለእነሱ ፍቅር ማሳየት ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል።
18. የእምነት ባልንጀራችን ባደረገው ነገር ቅር ከተሰኘን ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች ልንጠይቅ እንችላለን? (ምሳሌ 26:20)
18 አንዳንድ ጊዜ ቅር ያሰኘንን ግለሰብ ማነጋገር እንዳለብን ሊሰማን ይችላል። በቅድሚያ ግን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ስለ ጉዳዩ በቂ መረጃ አለኝ?’ (ምሳሌ 18:13) ‘ግለሰቡ ያን ነገር ያደረገው ሆን ብሎ ባይሆንስ?’ (መክ. 7:20) ‘እኔስ ተመሳሳይ ስህተት የሠራሁበት ጊዜ የለም?’ (መክ. 7:21, 22) ‘ግለሰቡን ማነጋገሬ ለመፍታት እየሞከርኩ ካለሁት ችግር የከፋ ሌላ ችግር ያስከትል ይሆን?’ (ምሳሌ 26:20ን አንብብ።) እንዲህ ባሉ ጥያቄዎች ላይ ቆም ብለን ካሰብን በኋላ ለወንድማችን ባለን ፍቅር ተነሳስተን በደሉን ችላ ብለን ለማለፍ ልንወስን እንችላለን።
19. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
19 የይሖዋ ምሥክሮች በቡድን ደረጃ የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ እያሳዩ ነው። እኛም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍጹማን ባይሆኑም ለእነሱ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ስናሳይ በግለሰብ ደረጃ እውነተኛ የኢየሱስ ተከታዮች እንደሆንን እናሳያለን። ይህም ሌሎች እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተው እንዲያውቁና የፍቅር አምላክ የሆነውን ይሖዋን ከእኛ ጋር አብረው እንዲያመልኩ ለማድረግ ሊረዳ ይችላል። እንግዲያው የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነውን ፍቅር ማሳየታችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”
a ብዙ ሰዎች በመካከላችን በሚያዩት እውነተኛ ፍቅር የተነሳ ወደ እውነት ይሳባሉ። ሆኖም ፍጹማን አይደለንም፤ ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ለእምነት ባልንጀራችን ፍቅር ማሳየት ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። ፍቅር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነና ሌሎች የተሳሳተ ነገር በሚያደርጉበት ጊዜ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
c በኅዳር 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 13-14 ላይ የሚገኘውን “በመጨረሻ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ችያለሁ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d በግንቦት 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 18-19 ላይ የሚገኘውን “የተሳካ ሕይወት ያለኝ ይመስል ነበር” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
e ይህ ርዕስ እየተናገረ ያለው በ1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 ላይ እንደተጠቀሱት ስላሉ በሽማግሌዎች መያዝ ያለባቸው ከባድ ኃጢአቶች አይደለም።
f ከረጅም ጊዜ በኋላ አንድ ረቢ እንዲህ እንዳለ ይነገራል፦ “በዓለም ላይ የአብርሃምን ያህል ጻድቅ የሆኑ ሰዎች ሠላሳ ቢሆኑ ነው። ሠላሳ ሰዎች ካሉ ከሠላሳዎቹ ሁለቱ እኔና ልጄ ነን፤ አሥር ሰዎች ካሉ ከአሥሩ ሁለቱ እኔና ልጄ ነን፤ አምስት ሰዎች ካሉ ከአምስቱ ሁለቱ እኔና ልጄ ነን፤ ሁለት ሰዎች ካሉ እነዚያ ሁለት ሰዎች እኔና ልጄ ነን፤ አንድ ሰው ብቻ ከሆነ ደግሞ ያ ሰው እኔ ነኝ።”