በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 13

ፍጥረትን በመጠቀም ልጆቻችሁን ስለ ይሖዋ አስተምሩ

ፍጥረትን በመጠቀም ልጆቻችሁን ስለ ይሖዋ አስተምሩ

“እነዚህን ነገሮች የፈጠረ ማን ነው?”—ኢሳ. 40:26

መዝሙር 11 ፍጥረት ይሖዋን ያወድሳል

ማስተዋወቂያ a

1. ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በተያያዘ ምን ፍላጎት አላቸው?

 ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲያውቁትና እንዲወዱት መርዳት እንደምትፈልጉ እናውቃለን። ሆኖም አምላክ በዓይን አይታይም። ታዲያ ልጆቻችሁ ይሖዋ እውን እንዲሆንላቸውና ወደ እሱ እንዲቀርቡ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?—ያዕ. 4:8

2. ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ይሖዋ ባሕርያት ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው?

2 ልጆች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ መርዳት የሚቻልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት ነው። (2 ጢሞ. 3:14-17) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ስለ ይሖዋ መማር የሚችሉበት ሌላም መንገድ እንዳለ ይጠቁማል። በምሳሌ መጽሐፍ ላይ አንድ አባት በፍጥረት ላይ ተንጸባርቀው የሚታዩትን የይሖዋን ባሕርያት ከእይታው እንዳያርቅ ልጁን አሳስቦታል። (ምሳሌ 3:19-21) ወላጆች ፍጥረትን በመጠቀም ልጆቻቸውን ስለ ይሖዋ ባሕርያት ማስተማር የሚችሉባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመለከታለን።

ፍጥረትን በመጠቀም ልጆቻችሁን ማስተማር የምትችሉት እንዴት ነው?

3. ወላጆች ልጆቻቸውን ምን እንዲያስተውሉ ሊረዷቸው ይገባል?

3 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ‘የማይታዩ ባሕርያት ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል’ ይላል። (ሮም 1:20) ወላጆች፣ ከልጆቻችሁ ጋር ከቤት ወጣ ብላችሁ ጊዜ ማሳለፍ እንደሚያስደስታችሁ የታወቀ ነው። ይህን አጋጣሚ ‘በተሠሩት ነገሮች’ እና አስደናቂ በሆኑት የይሖዋ ባሕርያት መካከል ያለውን ግንኙነት ልጆቻችሁ እንዲያስተውሉ ለመርዳት ተጠቀሙበት። ወላጆች በዚህ ረገድ ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንደሚችሉ እንመልከት።

4. ኢየሱስ ፍጥረትን ተጠቅሞ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማረው እንዴት ነው? (ሉቃስ 12:24, 27-30)

4 ኢየሱስ ፍጥረትን ተጠቅሞ ያስተማረው እንዴት እንደሆነ ልብ በሉ። በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱን ቁራዎችንና የሜዳ አበቦችን እንዲመለከቱ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 12:24, 27-30ን አንብብ።) ኢየሱስ ማንኛውንም እንስሳ ወይም ተክል መጥቀስ ይችል ነበር፤ ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ በደንብ የሚያውቁትን ወፍና አበባ እንደ ምሳሌ ለመጠቀም መርጧል። ደቀ መዛሙርቱ ቁራዎች ሲበርሩና አበቦች ሲያብቡ አይተው እንደሚሆን ግልጽ ነው። ኢየሱስ ወደ እነዚህ ነገሮች እየጠቆመ ሲናገር በዓይነ ሕሊናችሁ መሣል ትችላላችሁ? ደግሞስ እነዚህን ምሳሌዎች ከጠቀሰ በኋላ ምን አደረገ? ለደቀ መዛሙርቱ በሰማይ ስላለው አባቱ ልግስናና ደግነት የሚከተለውን ወሳኝ ትምህርት አስተማራቸው፦ ይሖዋ ለቁራዎችና ለሜዳ አበቦች እንደሚያደርገው ሁሉ ታማኝ አገልጋዮቹንም ይመግባቸዋል እንዲሁም ያለብሳቸዋል።

5. ወላጆች ልጃቸውን ስለ ይሖዋ ለማስተማር የትኞቹን የፍጥረት ሥራዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ?

5 ወላጆች፣ ኢየሱስ ያስተማረበትን መንገድ መኮረጅ የምትችሉት እንዴት ነው? እናንተ በግላችሁ በጣም ስለምትወዱት የፍጥረት ሥራ፣ ለምሳሌ ስለምትወዱት እንስሳ ወይም ተክል ለልጃችሁ ልትነግሩት ትችላላችሁ። በዚህ ጊዜ ያ የፍጥረት ሥራ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምረን መግለጻችሁን አትርሱ። ከዚያም ልጃችሁን እሱ ስለሚወደው እንስሳ ወይም ተክል ልትጠይቁት ትችላላችሁ። እሱ የሚወደውን የፍጥረት ሥራ ተጠቅማችሁ ስለ ይሖዋ ባሕርያት መናገራችሁ ልጃችሁ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ ሊያደርገው ይችላል።

6. የክሪስቶፈር እናት ከተወችው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

6 ወላጆች አንድ እንስሳ ወይም ተክል ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምረን ለልጆቻቸው ለማስረዳት ብዙ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋቸዋል? ላያስፈልጋቸው ይችላል። ኢየሱስ ስለ ቁራዎች አመጋገብ ወይም ስለ ሜዳ አበቦች አፈጣጠር ረጅም ማብራሪያ አልሰጠም። እርግጥ ነው፣ ልጃችሁ አልፎ አልፎ ስለ ፍጥረት ጥልቀት ያለው ውይይት ማድረግ ሊያስደስተው ይችላል፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ልጃችሁ ነጥቡን እንዲረዳው ለማድረግ ቀላል ሐሳብ መጥቀስ ወይም ጥያቄ መጠየቅ ብቻ በቂ ይሆናል። ክሪስቶፈር የተባለ ወንድም ስለ ልጅነቱ የሚያስታውሰውን ነገር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እናቴ በዙሪያችን ያሉትን የፍጥረት ሥራዎች እንድናደንቅ የሚያደርጉ ቀለል ያሉ ሐሳቦችን ትናገር ነበር። ለምሳሌ ተራሮች ወዳሉበት አካባቢ ስንሄድ ‘የተራሮቹን ግዝፈትና ውበት ተመልከቱ! ይሖዋ አስደናቂ አምላክ አይደል?’ ትለናለች። ወደ ባሕር ዳርቻዎች ስንሄድ ደግሞ ‘የባሕሩ ሞገድ ምን ያህል ኃይለኛ እንደሆነ አያችሁ? አምላክ እንዴት ኃያል ነው!’ ትላለች።” ክሪስቶፈር “እነዚያ ቀላል ሆኖም የሚያመራምሩ ሐሳቦች በእኛ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረዋል” ብሏል።

7. ልጆቻችሁ በፍጥረት ሥራዎች ላይ እንዲያሰላስሉ ልታሠለጥኗቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

7 ልጆቻችሁ ከፍ እያሉ ሲሄዱ ስለ ፍጥረት ይበልጥ እንዲያስቡና የፍጥረት ሥራዎች ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምሯቸው እንዲያስተውሉ ልታሠለጥኗቸው ትችላላችሁ። ከአምላክ ፍጥረታት መካከል አንዱን በመጥቀስ “ስለ ይሖዋ ምን ያስተምርሃል?” በማለት ልጃችሁን ልትጠይቁት ትችላላችሁ። የሚሰጠውን ሐሳብ ስትሰሙ ትገረሙ ይሆናል።—ማቴ. 21:16

ፍጥረትን ተጠቅማችሁ ልጆቻችሁን ማስተማር የምትችሉት መቼ ነው?

8. እስራኤላውያን ወላጆች “በመንገድ ላይ” ሲሄዱ ምን የማድረግ አጋጣሚ ነበራቸው?

8 እስራኤላውያን ወላጆች ‘በመንገድ ላይ ሲሄዱ’ ልጆቻቸውን ስለ ይሖዋ ትእዛዛት እንዲያስተምሩ ተነግሯቸው ነበር። (ዘዳ. 11:19) መንገዶቹ የእስራኤልን ገጠራማ አካባቢ አቋርጠው የሚያልፉ ነበሩ። በእነዚህ መንገዶች ላይ ሲጓዙ የተለያዩ እንስሳትን፣ ወፎችንና አበቦችን ማየት ይችሉ ነበር። እስራኤላውያን ወላጆች ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ልጆቻቸው በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ እንዲያስቡ መርዳት ይችላሉ። ወላጆች፣ እናንተም ፍጥረትን ተጠቅማችሁ ልጆቻችሁን ማስተማር የምትችሉባቸው ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ይኖሯችሁ ይሆናል። አንዳንድ ወላጆች ይህን ያደረጉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

9. ከፑኒታና ከካትያ ተሞክሮ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላላችሁ?

9 በሕንድ በሚገኝ ትልቅ ከተማ ውስጥ የምትኖር ፑኒታ የተባለች እናት እንዲህ ብላለች፦ “ገጠር ያሉ ቤተሰቦቻችንን ልንጠይቅ የምንሄድበትን ጊዜ ለልጆቻችን ስለ ይሖዋ አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች ማስተማር የምንችልበት አጋጣሚ አድርገን እንቆጥረዋለን። ልጆቼ ከተጨናነቁት መንገዶችና ከከተማው ግርግር ወጣ ሲሉ የፍጥረት ሥራዎችን ይበልጥ ማድነቅ እንደሚችሉ ይሰማኛል።” ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በአብዛኛው ከእናንተ ጋር ውብ በሆነ አካባቢ ያሳለፉትን ጊዜ እንደማይረሱት እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ። በሞልዶቫ የምትኖር ካትያ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ከልጅነት ሕይወቴ ውስጥ ፈጽሞ የማልረሳው ከወላጆቼ ጋር ወደ ገጠራማ አካባቢ ሄደን ያሳለፍናቸውን ጊዜያት ነው። ወላጆቼ ከልጅነቴ አንስቶ የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች ቆም ብዬ እንዳስተውልና በፍጥረት ሥራዎቹ አማካኝነት ስለ እሱ እንድማር ስለረዱኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”

በከተማ ውስጥም እንኳ ልጆቻችሁን ስለ ይሖዋ ማስተማር የምትችሉባቸው የተለያዩ የፍጥረት ሥራዎችን ልታገኙ ትችላላችሁ (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. ወላጆች ከከተማ ወጣ ብለው መጓዝ የሚከብዳቸው ከሆነ ምን ማድረግ ይችላሉ? (“ ለወላጆች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

10 ወደ ገጠራማ አካባቢዎች መሄድ ካልቻላችሁስ? በሕንድ የሚኖረው አሞል እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “በምኖርበት አካባቢ ወላጆች ረጅም ሰዓት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ ወደ ገጠራማ አካባቢ መሄድ ደግሞ ብዙ ወጪ ይጠይቃል። ሆኖም አነስ ወዳሉ የመናፈሻ ቦታዎች ሄዳችሁ ወይም ወደ በረንዳ ወጣ ብላችሁ የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች መመልከትና ስለ ባሕርያቱ ማውራት ትችላላችሁ።” በትኩረት ከተመለከታችሁ ከቤታችሁ ብዙም ሳትርቁ ለልጆቻችሁ ልታሳዩ የምትችሏቸው የተለያዩ የፍጥረት ሥራዎችን ታገኙ ይሆናል። (መዝ. 104:24) ወፎችን፣ ነፍሳትን፣ ተክሎችንና የተለያዩ ፍጥረታትን ልታገኙ ትችላላችሁ። በጀርመን የምትኖረው ካሪና እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ አበቦች ትወዳለች፤ ስለዚህ ልጅ ሳለሁ አብረን በእግራችን ስንሄድ የሚያማምሩ አበቦችን ታሳየኛለች።” ድርጅታችን ያዘጋጃቸውን ስለ ፍጥረት የሚናገሩ በርካታ ቪዲዮዎችና ጽሑፎች በመጠቀምም ልጆቻችሁን ማስተማር ትችላላችሁ። አዎ፣ ሁኔታችሁ ምንም ይሁን ምን ልጆቻችሁ የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች እንዲያስተውሉ መርዳት ትችላላችሁ። እስቲ አሁን፣ ልጆቻችሁ እንዲያስተውሉ ልትረዷቸው የምትሏቸውን አንዳንድ የይሖዋ ባሕርያት እንመልከት።

የይሖዋ ‘የማይታዩ ባሕርያት በግልጽ ይታያሉ’

11. ወላጆች ልጆቻቸው የይሖዋን ፍቅር እንዲያስተውሉ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

11 ልጆቻችሁ የይሖዋን ፍቅር እንዲያስተውሉ ለመርዳት ብዙ እንስሳት ልጆቻቸውን የሚንከባከቡበትን መንገድ እንዲመለከቱ ልታደርጓቸው ትችላላችሁ። (ማቴ. 23:37) ለደስታችን ምክንያት የሚሆኑትን የተለያዩ ዓይነት አስደናቂ ፍጥረታትም አሳዩአቸው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካሪና እንዲህ ብላለች፦ “ከእናቴ ጋር መንገድ ላይ ስንሄድ እናቴ እያንዳንዱ አበባ እንዴት ልዩ እንደሆነና የአበቦቹ ውበት የይሖዋን ፍቅር የሚያንጸባርቀው እንዴት እንደሆነ ቆም ብዬ እንዳስተውል ታበረታታኛለች። አሁን ዓመታት አልፈውም አበቦችን በትኩረት እመለከታለሁ፤ እያንዳንዱ አበባ የተለየ ቅርጽ፣ ንድፍና ቀለም አለው። አበቦችን ሳይ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን አስባለሁ።”

በሰውነታችን ላይ የሚታየውን አስደናቂ ንድፍ ተጠቅማችሁ ልጆቻችሁን ስለ አምላክ ጥበብ ልታስተምሯቸው ትችላላችሁ (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. ወላጆች ልጆቻቸው የአምላክን ጥበብ እንዲያስተውሉ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? (መዝሙር 139:14) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 ልጆቻችሁ የአምላክን ጥበብ እንዲያተውሉ እርዷቸው። የይሖዋ ጥበብ ከእኛ እጅግ የላቀ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። (ሮም 11:33) ለምሳሌ ውኃ ወደ ላይ ወጥቶ ደመና የሚሠራው እንዴት እንደሆነና ያ ደመና ውኃውን ተሸክሞ ከቦታ ቦታ ያለምንም ችግር የሚንቀሳቀሰው እንዴት እንደሆነ ለልጆቻችሁ ልትጠቅሱላቸው ትችላላችሁ። (ኢዮብ 38:36, 37) በሰዎች አካል ላይ ስለሚታየው አስደናቂ ንድፍም መጥቀስ ይቻላል። (መዝሙር 139:14ን አንብብ።) ቭላዲሚር የተባለ አባት ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ልብ በሉ። እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ቀን ልጃችን ከብስክሌቱ ላይ ወድቆ ቆሰለ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ቁስሉ ዳነ። እኔና ባለቤቴ ይሖዋ ሴሎቻችንን ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያድሱ አድርጎ እንደፈጠራቸው ነገርነው። ሰዎች የሠሩት ማንኛውም ነገር እንዲህ ማድረግ እንደማይችል ገለጽንለት። ለምሳሌ አንድ መኪና አደጋ ከደረሰበት በኋላ ራሱን በራሱ መጠገን አይችልም። ይህ አጋጣሚ ልጃችን የይሖዋን ጥበብ እንዲያስተውል ረድቶታል።”

13. ወላጆች ልጆቻቸው የይሖዋን ኃይል እንዲያስተውሉ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 40:26)

13 ይሖዋ ዓይናችንን ወደ ሰማይ አንስተን እንድንመለከትና እሱ ያለው አስደናቂ ኃይል ጽንፈ ዓለም በሥርዓት እንዲንቀሳቀስ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ እንድናስብ ጋብዞናል። (ኢሳይያስ 40:26ን አንብብ።) ልጆቻችሁን ወደ ሰማይ ቀና ብለው እንዲመለከቱና ቆም ብለው እንዲያስቡ ልታበረታቷቸው ትችላላችሁ። ሺንግሺንግ የተባለች በታይዋን የምትኖር እህት ስለ ልጅነት ሕይወቷ ስታስታውስ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን እናቴ ውጭ ድንኳን ተተክሎ ወደሚታደርበት ቦታ ወሰደችኝ። እዚያ ሳለን በከተማ መብራቶች ያልደበዘዘውን የምሽት ሰማይ ቀና ብለን ተመለከትን። ያ ወቅት በእኩዮች ተጽዕኖ ምክንያት የተጨነቅኩበትና ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሌን መቀጠል ስለመቻሌ የተጠራጠርኩበት ጊዜ ነበር። እናቴ ይሖዋ እነዚያን ሁሉ ከዋክብት ለመፍጠር ስለተጠቀመበት ኃይል እንዳስብ አበረታታችኝ፤ በተጨማሪም ይሖዋ ይህን ኃይሉን በመጠቀም ማንኛውንም ፈተና እንድጋፈጥ ሊረዳኝ እንደሚችል አስታወሰችኝ። በዚያ ጉዞ ላይ ፍጥረትን ከተመለከትኩ በኋላ ይሖዋን ይበልጥ ለማወቅ ተነሳሳሁ፤ እሱን ለማገልገል ያለኝ ቁርጠኝነትም ተጠናከረ።”

14. ወላጆች ፍጥረትን ተጠቅመው ይሖዋ ደስተኛ አምላክ እንደሆነ ለልጆቻቸው ማስረዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

14 የፍጥረት ሥራዎች ይሖዋ ደስተኛ አምላክ እንደሆነ ያሳያሉ። ሳይንቲስቶች ወፎችንና ዓሣዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ እንስሳት እንደሚጫወቱ አስተውለዋል። (ኢዮብ 40:20) ልጆቻችሁ እንስሳት ሲጫወቱ አይተው የሳቁበት ጊዜ አለ? ምናልባት አንዲት ትንሽዬ ድመት ኳስ እያባረረች ስትጫወት ወይም ቡችሎች ሲላፉ አይተው ይሆናል። በቀጣዩ ጊዜ ልጆቻችሁ አንድ እንስሳ የሚያደርገውን አስቂኝ ነገር አይተው ሲስቁ የምናገለግለው አምላክ ደስተኛ እንደሆነ ለምን አታስታውሷቸውም?—1 ጢሞ. 1:11

በቤተሰብ ሆናችሁ ተፈጥሮን የምታደንቁበት ጊዜ ይኑራችሁ

ልጆቻችሁ ከእናንተ ጋር ተፈጥሮን በሚመለከቱበት ወቅት ይበልጥ ዘና ሊሉና ስሜታቸውን አውጥተው ለመናገር ሊነሳሱ ይችላሉ (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. ወላጆች ልጆቻቸው የልባቸውን አውጥተው እንዲነግሯቸው ለማድረግ ምን ሊረዳቸው ይችላል? (ምሳሌ 20:5) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸው ስለሚያጋጥሟቸው ችግሮች እንዲነግሯቸው ማድረግ ይከብዳቸዋል። የእናንተም ሁኔታ እንዲህ ከሆነ የልጆቻችሁን ሐሳብ ቀድታችሁ ማውጣት ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። (ምሳሌ 20:5ን አንብብ።) አንዳንድ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ተፈጥሮን በሚመለከቱበት ጊዜ እንዲህ ማድረግ ይበልጥ ቀላል እንደሚሆንላቸው አስተውለዋል። ለምን? አንዱ ምክንያት የልጆችንም ሆነ የወላጆችን ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ስለሚቀንሱ ነው። በታይዋን የሚኖር ማሳሂኮ የተባለ አባት ሌላኛውን ምክንያት ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል፦ “ከልጆቻችን ጋር ከቤታችን ወጣ ብለን ስንዝናና፣ ለምሳሌ ተራሮችን ስንወጣ ወይም ባሕር ዳርቻ ላይ ስንንሸራሸር ልጆቹ በአብዛኛው ዘና ያለ መንፈስ ይኖራቸዋል። በዚህ ጊዜ የውስጣቸውን አውጥተው እንዲነግሩን ማድረግ ቀላል ይሆንልናል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካትያ እንዲህ ብላለች፦ “ከትምህርት በኋላ እናቴ ወደ አንድ የሚያምር መናፈሻ ትወስደኛለች። እዚያ ስሆን ዘና ስለምል ትምህርት ቤት ያጋጠመኝን ወይም ያስጨነቀኝን ነገር ለእሷ መንገር ቀላል ይሆንልኛል።”

16. ቤተሰቦች በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ዘና ማለትና መደሰት የሚችሉት እንዴት ነው?

16 የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ቤተሰቦች ዘና ብለው አስደሳች ጊዜ እንዲያሳልፉም ያስችላሉ፤ ይህም ቤተሰቦች እርስ በርስ ይበልጥ እንዲቀራረቡ ይረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመሳቅ ጊዜ አለው’ እንዲሁም “ለመፈንጨት ጊዜ አለው” ይላል። (መክ. 3:1, 4 ግርጌ) ይሖዋ የሚያስደስቱንን ነገሮች የምናደርግባቸው ውብ የሆኑ ቦታዎችን ፈጥሮልናል። ብዙ ቤተሰቦች ወደ መናፈሻ ቦታዎች፣ ገጠራማ አካባቢዎች፣ ተራሮች ወይም ሐይቆች ሄደው መዝናናት ያስደስታቸዋል። አንዳንድ ልጆች መናፈሻዎች ውስጥ መሯሯጥና መጫወት፣ እንስሳትን መመልከት አሊያም ወንዝ፣ ሐይቅ ወይም ባሕር ውስጥ መዋኘት ደስ ይላቸዋል። በእርግጥም ይሖዋ በፈጠራቸው ነገሮች መዝናናት የምንችልባቸው ብዙ ግሩም አጋጣሚዎች አሉን!

17. ወላጆች ልጆቻቸው በይሖዋ የፍጥረት ሥራ እንዲደሰቱ መርዳት ያለባቸው ለምንድን ነው?

17 በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ወላጆችም ሆኑ ልጆች ከዚህ በፊት አድርገውት በማያውቁት መጠን በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ይደሰታሉ። እንደ አሁኑ እንስሳትን የምንፈራበት ምንም ምክንያት አይኖርም፤ እነሱም እኛን አይፈሩንም። (ኢሳ. 11:6-9) ይሖዋ በሠራቸው ነገሮች ለዘላለም እንደሰታለን። (መዝ. 22:26) ሆኖም ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በፍጥረት ሥራዎች እንዲደሰቱ ለማድረግ ያ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ አያስፈልጋችሁም። ፍጥረትን ተጠቅማችሁ ልጆቻችሁን ስለ ይሖዋ የምታስተምሯቸው ከሆነ ንጉሥ ዳዊት በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ መስማማታቸው አይቀርም፦ “ይሖዋ ሆይ . . . ከአንተ ሥራ ጋር የሚወዳደር አንድም ሥራ የለም።”—መዝ. 86:8

መዝሙር 134 ልጆች ከአምላክ በአደራ የተሰጡ ናቸው

a ብዙ ወንድሞችና እህቶች ከክርስቲያን ወላጆቻቸው ጋር ፍጥረትን በመመልከት ስላሳለፉት ጊዜ ጥሩ ትዝታ አላቸው። ወላጆቻቸው እነዚያን አጋጣሚዎች ተጠቅመው ስለ ይሖዋ ባሕርያት እንዴት እንዳስተማሯቸው ፈጽሞ አይረሱትም። ልጆች ካሏችሁ ተፈጥሮን ተጠቅማችሁ ስለ አምላክ ባሕርያት ልታስተምሯቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ይህ ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።